Account
ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ

ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ

✨Philosophy For Higher Consciousness✨

Username
@zephilosophy
Category
Edutainment
Country
EthiopiaEthiopia
Subscribers32,965
Avg views per post, 7d3,710−33.4% vs prev 7d
ERR11.25%last 7 days

Average views per post by day

By publication day

Show as table
DateAvg views per post
Nov 2, 20269,100
Nov 6, 202610,600
Nov 12, 20268,670
Nov 18, 20265,920
Nov 19, 20265,220
Nov 22, 20263,710

Most viewed this month

  1. 01

    የኃይል ፈቃድ (Will to Power) ​«ሕያው ፍጥረት ከሁሉም በላይ ኃይሉን መልቀቅ ይሻል፤ ሕይወት ራሷ የኃይል ፈቃድ ናት።» — ኒቼ ​አንዲት ሕፃን መራመድ ስትለማመድ ትወድቃለች፣ ትነሳለች፣ እንደገናም ትሞክራለች። በሕይወት ለመቆየት መራመድ አያስፈልጋትም፤ መዳህ ወይም መቀመጥ ትችላለች። ታዲያ ቀደሞውኑ ማድረግ በምትችለው ነገር ሳትረካ እንዲህ እንድትተጋ የሚያደርጋት ምንድን ነው? የነርቭ ሳይንቲስት ሂደቱን ማብራራት ይችላል። የፊዚዮሎጂ ባለሙያ ጡንቻዎችን፣ ሚዛንን እና እየዳበረ የሚሄደውን የእንቅስቃሴ ቅንጅት መግለጽ ይችላል። የስነ-ልቦና ባለሙያ ደግሞ ስለ መማር፣ መኮረጅ (imitation) እና ማጠናከሪያ ማስረዳት ይችላል። እነዚህ ሁሉ ማብራሪያዎች ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ፍልስፍና ሁልጊዜም ማብራሪያው ምክንያታዊ መስሎ መታየት ከጀመረ በኋላ እንኳን ጥያቄዎችን መጠየቅ የመቀጠል አስገራሚ ባህሪ አለው። ባለበት ለመቆየት አሻፈረን የሚለው ይሄ በውስጣችን ያለው እንቅስቃሴ ምንድን ነው? ለምንስ ነው አብዛኛውን ጊዜ ራሳችንን ከመጠበቅ (preserve ከማድረግ) ባለፈ፣ ትናንት ከነበርነው የበለጠ አቅም ያላቸው ለመሆን የምንፈልገው? ግልጹ መልስ ህልውናን ማስቀጠል (survival) ነው። ሕያው ፍጥረታት ህልውናቸውን ማስቀጠል አለባቸው። ምግብ፣ መጠለያ፣ መራባት እና ከአደጋ መከለል ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛው የባህሪ ዓይነት በሕይወት ከመቆየት ግፊት አንጻር ልንረዳው ይችላል። ሌላው መልስ ደግሞ ደስታ (pleasure) ነው። ምናልባት ጥሩ ስሜት ያለውን እንፈልጋለን፤ የሚያመንን ደግሞ እንሸሻለን። በሁለቱም ማብራሪያዎች ውስጥ እውነት አለ። ግን የሰው ልጅ ሕይወት እነዚህን ማብራሪያዎች ተሻግረው የሚፈሱ ምሳሌዎችን እንዳሳየን ነው። ቀድሞውኑ በቂ ገንዘብ ያለው ሰው የበለጠ ይፈልጋል። አንድ ሰዓሊ ሀብታም ሊያደርገው የማይችል ነገር ለመፍጠር አስር ዓመታት ያሳልፋል። አንድ የሂሳብ ሊቅ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተግባራዊ ጥቅም የሌለውን ችግር ለመፍታት ሌሊቶችን ቁጭ ብሎ ያድራል። አንድ ደራሲ ሰዓታትን ወስዶ የጻፈውን ገጽ ገና እንደፈለገ ስላልሆነለት ይቀደዋል። የሆነ ሰው በጫፉ ላይ የሚጠብቀው ምንም ዓይነት ሀብት የሌለበትን ተራራ ይወጣል። ሌላው መናገር መቻል ስለፈለገ ብቻ ከባድ ቋንቋ ይማራል። አንድ ሰው የማይመግበውን፣ የማያስከፍለውን ወይም ሕይወቱን የማያድንለትን ሀሳብ ለመረዳት ዓመታትን ያሳልፋል። እና ደግሞ ሆን ብለው ፈታኝ ነገሮችን የሚመርጡ ሰዎችም አሉ። ምቾትን የሚተው መነኩሴ፤ ከአስደሳች ቅዠት ይልቅ የሚረብሽ እውነትን የሚመርጥ ፈላስፋ፤ ሰውነቱን ከቀደመው ወሰን በላይ የሚገፋ ስፖርተኛ፤ ቀላል ስታይሎችን የማይቀበል አርቲስት፤ መላመድን መሸከም አቅቶት የተለመደ ሕይወቱን ትቶ የሚሄድ ሰው። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ምን እየፈለጉ ነው? ምናልባት ኒቼ በምኞታችን ግብ ላይ ብቻ ከመጠን በላይ እንዳተኮርንና ከጀርባው ስላለው ኃይል ግን በቂ ትኩረት እንዳልሰጠን ይነግረን ይሆናል። እኛ አንድ ሰው ምን እንደሚፈልግ እንጠይቃለን። ኒቼ ግን በዚያ ሰው ውስጥ የሚያልፈውና የሚያንቀሳቅሰው ነገር ምን እንደሆነ ይጠይቃል። ከዚያም ከታዋቂ ጽንሰ-ሃሳቦቹ አንዱ ይመጣል: «የኃይል ፈቃድ (Will to power)»። አብዛኛውን ጊዜ ፍላጎትን ወይም ፈቃድን እንደ ንቁ አእምሯዊ ውሳኔ እናስበዋለን። እወስናለሁ። እመርጣለሁ። እፈልጋለሁ። እሰራለሁ። እንላለን ኒቼ ግን ጭንቅላታችን ውስጥ ተቀምጦ ለሁሉም ነገር ትእዛዝ የሚሰጠውን ይህን ትንሽ ገዢ በጥርጣሬ ነው የሚያየው። በኒቼ የስነ-ልቦና እይታ፣ የሰው ልጅ እንደሚታየው አንድ ወጥ (unified) አይደለም። በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚንቀሳቀሱ ስሜታዊ ግፊቶች፣ ልምዶች፣ ምኞቶች፣ ፍርሃቶች፣ ተፈጥሯዊ ድራይቮች እና የተወረሱ እሴቶች አሉ። “እኔነት/the self” የምንለው ነገር መንግስቱን እንደሚገዛ ንጉሥ ሳይሆን፣ እርስ በርስ በሚፎካከሩ ኃይሎች መካከል ያለ ጊዜያዊ ስምምነት ወይም arrangement ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ “ማድረግ ስለፈለግኩ ነው ያደረግኩት” እንላለን፤ ነገር ግን እውነተኛ ትርጉሙ በውስጣችን ያለው አንድ ነገር በውስጣችን ካሉት ሌሎቹ ነገሮች ላይ የበላይነት አገኘ ማለት ነው ምቾትን እንፈልጋለን፤ ግን ስኬትንም እንፈልጋለን። እውነትን እንፈልጋለን፤ ግን ከቅዠቶቻችን የምናገኘውን መጽናኛም እንፈልጋለን። መደነቅ እንፈልጋለን፤ ግን አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ ለብቻችን መተው እንፈልጋለን። የሰው ልጅ በነዚህ መሰል ተቃርኖዎች የተሞላ ነው። ስለዚህ በኒቼ ዘንድ “ፈቃድ” ወይም “ፍላጎት” እንደ ተራ ንቁ ምኞት ብቻ መወሰድ የለበትም፣ ምክንያቱም ሃሳቡ ከንቁ ምኞት ይልቅ ወደ ጥረት፣ ወደ ውስጣዊ ግፊት እና ወደ ኃይሎች እንቅስቃሴ የቀረበ ነው። ኃይል" የሚለውን ቃልም ስንረዳ በቀላሉ የበላይነትን (domination) ብቻ መምሰል የለበትም፦ ​ኃይል ማለት የመንቀሳቀስ፣ የመቋቋም፣ የመለወጥ እና ለአንድ ነገር ቅርጽ የመስጠት አቅም ነው። ራስን ማሸነፍ (self-overcoming) ማለት ማልዶ መንቃት፣ ጂም መሄድ፣ ገንዘብ መስራት እና የበለጠ ውጤታማ መሆን ብቻ አይደለም። የኒቼ ጥያቄ በጣም የበለጠ ረባሽ ነው። ልታሻሽለው የምትሞክረው ሰው የተገነባው በፍጹም መርጠሃቸው ከማታውቃቸው እሴቶች ቢሆንስ? ብርቱ መሻትህ የተወረሰ ቢሆንስ? ስለ ስኬት ያለህ ሀሳብ ከአንተ ይልቅ የማህበረሰብህ ቢሆንስ? ልዩ የመሆን ፍላጎትህ በራሱ ሌላ የታዛዥነት ዓይነት ብቻ ቢሆንስ? ኒቼ ዛሬም ረባሽ የሆነው እሴቶች ከሰማይ እንዳልወረዱ ስለሚያሳይ ነው። ከየት መጡ? ምን ዓይነት ሰው እንደፈለጋቸው? ምን ዓይነት ሕይወትን እንዳገለገሉ? በእነሱ በኩል ምን ዓይነት ኃይሎች እንደተገለጹ ይጠይቃል። ዋጋ ያለው ምንድን ነው? ምን ክቡር፣ ምን ኃጢአት፣ ምን ጠንካራ፣ ምን ደካማ እንደሚባል ይጠይቃል? እናም ወደ ራሳችን ይመልሰናል፦ የምትፈልጉትን እንድትፈልጉት ያስተማራችሁ ማነው? ማንም ባያያችሁ ከብርቱ መሻታችሁ ምን ይቀራል? ማንም ባያመሰግናችሁ ከሞራላችሁ ምን ይተርፋል? ግን እዚህ ላይ ኒቼን መቃወም አለብን ብዬ አስባለሁ። የሰው ልጅ ወደ አንድ ዋና ግፊት/ድራይቭ አይቀነስም። ደህንነትንና ነፃነትን፣ እውነትንና ምቾትን፣ እውቅናንና ብቸኝነትን እንፈልጋለን፤ ራሳችንን መጠበቅ እንፈልጋለን፣ አንዳንዴም ከራሳችን ማለፍ። ስለዚህ የኃይል ፈቃድ እንደተረጋገጠ ሳይንሳዊ ሕግ ወይም እያንዳንዱን እንቆቅልሽ የሚከፍት ምትሃታዊ ቁልፍ ሳይሆን ጥያቄ፣ መነፅር እና መቀስቀሻ ቢሆን ይሻላል። ሲጠቀሙበት አንድ ነገር ይታያል፤ ዞር ሲያደርጉት ሌላ ነገር ይመለሳል። አንዲት ሕፃን በክፍሉ መሃል ትቆማለች። ትወድቃለች። ትነሳለች። እንደገና ትሞክራለች። ምናልባት መራመድ እየተማረች ነው። ምናልባት የኃይል ፈቃዷን እየገለፀች ነው። ምናልባትም ሕያው ነች። እነዚህ ሦስቱ መጀመሪያ እንደሚታዩት የተራራቁ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ምክንያቱም ከታላላቅ ቃላት በታች ትንሽ የሚያስደንቅ እውነት አለ፦ እኛ አላለቅንም። ሁሌም የሆነ ነገር እየሆንን ነው። ከባዱ ጥያቄ ኃይል አለን ወይ የሚለው አይደለም። ኃይላችን እኛን ምን እያደረገን ነው የሚለው ነው። እናም ወድቆ እንደገና ለተነሳ ሰው ሁሉ የሚጠብቀው ጥያቄ ይህ ነው፦ ባለበት ቦታ ላይ ለመቆየት አሻፈረኝ የሚለው በውስጣችን ያለው ይህ ነገር ምንድን ነው? ፀሀፊ- ዮናታን አቢስ @zephilosophy

    Text
    Views10.6K
    Forwards—
    Reactions74
    Comments—
  2. 02

    ኩርት ቮነጉት የጦርነትን አሰቃቂነት እና የሰው ልጅ ዕብደትን በህይወቱ ተሞክሮ ልክ እንዳልሆነ አይቶ የሚያሳይ ደራሲ ነው፡፡ ኩርት ቮነጉት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ድሬስደን ከተማ የቦምብ ድብደባ ውስጥ ተይዞ ከሞት የተረፈ ሰው ነው። ይህ ገጠመኙ ጦርነት የጀግንነት ማሳያ ሳይሆን ንጹሐንን የሚጨፈጭፍ፣ ሰብአዊነትን የሚያጠፋ እና ትርጉም የለሽ አረመናዊ ድርጊት መሆኑን ይናገራል፡፡ ኩርት ቮነጉት በሞራል እና በፖለቲካ መካከል ስላለው  ግጭት "ማዘር ናይት" ብሎ በሰየመው ድረሰቱ  በጦርነት ጊዜ መንግሥታት ሕዝቦችን ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ "ጥሩ" እና "ክፉ" ብለው ይከፋፍሏቸዋል ይለናል። ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ "ለሀገር ብዬ ነው" "ተላላኪ ነበርኩ" ወይም "የትዕዛዝ ግዴታ ነው" ተብሎ የሚሰራው ክፉ ነገር የሰውን ህሊና እና እውነተኛ ማንነት ለዘላለም እንደሚበክለው ለማሳየት ይሞክራል። ኩርት ቮነጉት "እኛ የምንመስለው የምንመስልበትን ነገር ነን" ይለናል፡፡ ይህም ማለት በውስጣችን ጥሩ ሐሳብ አለን ብንልም በውጭ ላይ የምንፈጽመው ተግባር ጥላቻን መስበክ፣ መከራን ማባባስ ይሆናል፡፡ ይህም በሂደት የእኛ እውነተኛ ማንነት ይሆናል ስለዚህ ድርጊታችን ከሐሳባችን ጋር ሊጣጣም ይገባል እያለ አበክሮ ይሞግተናል። ኩርት ቮነጉት በጦርነትና በግጭት ጊዜ "እኛ ፍጹም ጻድቃን ነን፣ እነሱ ደግሞ ፍጹም ክፉዎች ናቸው" የሚለው አመለካከት የሐሰት ትርክት መሆኑን እና ሁለቱም ወገን የሰውን ልጅ ሕይወት እንደሚያጠፉ ያሳያል። እንደ "ማዘር ናይት" ታሪክ ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ እና በቡድን ስም ተነስተው ጥላቻን የሚሰብኩ ሕዝብን እርስ በእርስ የሚያጣሉ አካላት አሉ። ኋላ ላይ "ለዓላማ ብዬ ነው" ወይም "በትዕዛዝ ስር ስለነበርኩ ነው" "ተላላኪ ነበርኩ"  የሚሉ ማስተባበያዎች ቢቀርቡም በምድር ላይ የጠፋው ንጹህ ሕይወት እና የተበላሸው ማህበራዊ ትስስር ግን ሊመለስ አይችልም። ስለዚህ ማይክ በያዝን ወቅትም ሆነ አደበታችንን በከፈተን ጊዜ ሁሉ "ምን እየፈጠርን እና ምን እያስተላለፍን ነው?"ብሎ መጠየቅ የጊዜው ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ባሳለፈቻቸው ግጭቶችና ጦርነቶች ያየነው እውነት ቮነጉት ከድሬስደን ውድቀት ጋር ካስተማረው ትምህርት ጋር አንድ ነው። በጦርነት ውስጥ አሸናፊ የሚባል ወገን የለም፡፡ ሁለቱም ወገን የሚያጡት ወጣቶቻቸውን፣ ሰብአዊነታቸውን እና ሀገራዊ ሀብታቸውን ነው። ስለሆነም ዛሬም ቆም ብለን ብናስብ፡፡ ለሕይወት እና ለአብሮነት መስጠት ያለብን ዋጋ ብንሰጥ በየቀኑ የሚሞተውን ህይወት መታደግ እንችላለን፡፡ ቮነጉት በድረስቱ እንዳለው  ሰው በምድር ላይ የሚቆየው እጅግ ለአጭር ጊዜ ነው። ይህችን አጭር ዕድሜ በጎጥ፣ በዘር እና በጥላቻ ከማጥፋት ይልቅ እርስ በእርስ በመተሳሰብ፤ ተፈጥሮን በመውደደ ና በመዋደድ የተሰጠንን የሕይወት ስጦታ በምስጋና ማሳለፍ እንዳለብን ይነግረናል፡፡ ቮነጉት በ"ካትስ ክሬድል" ስራው ላይ  እንዲህ እያለ ይቃትታል "እግዚአብሔርም ብቸኛ ሆኖ ተሰማው። እግዚአብሔር ጭቃ ፈጠረ። ስለዚህ ለአንዳንድ ጭቃዎች እንዲህ አላቸው፦ "ተነስታችሁ ተቀመጡ!" እግዚአብሔርም "የፈጠርኳቸውን ሁሉ ተመልከቱ፤ ኮረብታዎቹን፣ ባሕሩን፣ ሰማዩን፣ ከዋክብቱን" አለ። እኔም ተነሥቼ እንድዞር እና እንድመለከት ከተደረጉት ጭቃዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። ዕድለኛ ነኝ፡፡ ዕድለኛ ጭቃ! እኔ ጭቃው ተነሥቼ ተቀመጥኩ፡፡ እግዚአብሔርም ምንኛ ድንቅ ሥራ እንደሠራ ተመለከትኩ። በጣም አሪፍ ሥራ ነው እግዚአብሔር! ከአንተ በቀር ማንም ይህንን ሊያደርገው አይችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሆይ! እኔማ ከቶውንም አልችለውም ነበር። ከአንተ አንጻር ስታይ እኔ ከቶውንም ዋጋ የሌለኝ ሆኖ ይሰማኛል። እኔ ትንሽ መሆኔን ረሳሁ ብዬ የምፅናናበት ብቸኛ መንገድ ተነሥተው እንዲቀመጡ እና ዓለምን እንዲመለከቱ ዕድል ያልገጠማቸውን ያን ሁሉ ጭቃ ሳስብ ብቻ ነው። እኔ ብዙ አገኘሁ፡፡ አብዛኛው ጭቃ ግን ይህ እድል አልሆነለትም። ለዚህ ታላቅ ክብርም አመሰግናለሁ! አሁን ጭቃው እንደገና  ይተኛል። ጭቃው ሊኖሩት የሚችሉ ምን ያህል አስደናቂ ትዝታዎች ናቸው! የገጠሙኝ ሌሎች አስደናቂ ተነስተው የተቀመጡ ጭቃዎች (ሰዎች) ምንኛ ድንቅ ነበሩ! ያየሁትን ሁሉ ወደድኩት!" ይለናል፡፡ በየቀኑ የሰውን ልጅ የሞት ዜና መስማት ያማል ፡፡ በጋራ ለመዳን በጋራ መቆም አለብን፡፡ለየብቻው እና በየተራ የሚያለቅስ ህዝብ አይሻገርም!! ፀሀፊ - ዮናስ ዘውዴ @zephilosophy

    Text
    Views10.2K
    Forwards—
    Reactions67
    Comments—
  3. 03

    የምክንያታዊ ነፍስ ተፈጥሮ Marcus Aurelius 📖Meditation ሂፖክራተስ ብዙ በሽተኞችን አከመ፤ በኋላ ግን ራሱ ታሞ ሞተ። ኮከብ ቆጣሪዎች የብዙ ሰዎችን ሞት ተነበዩ፤ በመጨረሻ ግን የራሳቸውም ሰዓት ደረሰ። ብዙ ከተሞችን ያጠፉና በጦርነት በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን የገደሉት እነ ታላቁ እስክንድር፣ ፖምፔ እና ቄሳርም ከዚህ አለም ተሰናበቱ። አለም በእሳት ትጠፋለች እያለ ሲሰብክ የነበረው ሄራክሊተስ ሰውነቱ ውሃ ቋጥሮ በጠና ታሞ ሞተ። ዴሞክሪተስን ተራ ተባዮች ገደሉት፤ ሶቅራጥስን ደግሞ ሰው የተባሉ ተባዮች ገደሉት። ይህ ምን ማለት ነው? መርከብ ላይ ተሳፍረሃል፣ ጉዞህን ጨርሰህ የምትወርድበት ሰዓት ይደርሳል። በየቀኑ የሕይወታችን ክፍል እየተሸረሸረና የቀረው ጊዜ እያጠረ መምጣቱ ብቻ ሊያሳስበን አይገባም፡፡ ይህንንም ማሰብ አለብን፦ ዕድሜያችን ቢረዝም እንኳ፤ ዓለምን ለመረዳትና መለኮታዊ እንዲሁም ሰብአዊ እውቀቶችን ለመመርመር የሚያስችል የአእምሮ ብቃት እንደቀድሞው አብሮን እንደሚዘልቅ እርግጠኛ መሆንስ እንችላለን? ምክንያቱም አእምሯችን መጃጀት ከጀመረ መተንፈስ፣ መብላት፣ ማሰብና ስሜታዊ መሆን አናቆም ይሆናል። ነገር ግን እምቅ አቅማችንን መጠቀም፣ ግዴታችንን መለየት፣ የምንሰማውንና የምናየውን መተንተን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጤናማ አእምሮ የሚጠይቁ ናቸውና ይጠፋሉ። ስለዚህ መፍጠን አለብን፡፡ ወደ ሞት በየቀኑ እየቀረብን ከመሄዳችንም ባሻገር ነገሮችን የመረዳትና የአለምን ሁኔታ የመገንዘብ አቅማችን ሕይወታችን ከማለፉ በፊት ሊጠፋም ይችላል። በግዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ በራስ ወዳድነት ሳይሆን ለጋራ ጥቅም፣ ያለ ጥንቃቄ ሳይሆን በምክንያት፣ በፍርሃት ሳይሆን በልበ ሙሉነት ሥራ። ሃሳብህን አትቀባባ፡፡ አላስፈላጊ ቃላትን አትናገር፤ ብዙ ነገሮች ውስጥ አትግባ። በውስጥህ ያለው መንፈስ የወንድን፣ የብስለትን፣ የመሪን ስብዕና ይላበስ፡፡ ቦታውን እንደያዘና የመጠራትን ጥሪ በትዕግስት እንደሚጠብቅ፣ መሐላ ወይም ምስክር እንደማያስፈልገው ወታደር ሁን። በራስህ ደስተኛ ሁን፤ የሌሎችን እርዳታ ወይም ከሌሎች የሚገኝ ሰላምን አትጠበቅ᎓᎓ በራስህ ቀጥ በል እንጂ በሌሎች ድጋፍ አትቁም፡፡ የጠራና የተስተካከለ ሰው አእምሮ ውስጥ ቆሻሻ የለም፡፡ ሕይወቱ በሞት ሲቋረጥ፣ ተውኔቱ ሳያልቅ እንደሚያቋርጥ ተዋናይ አይሰማውም᎓᎓ ባርነት ወይም ትዕቢት አይታይበትም᎓᎓ ማጎብደድ ወይም ንቀት የለበትም። ሰበብ መደርደር ወይም መሸሽ የለበትም፡፡ አስተሳሰብህን የመቆጣጠር ችሎታህን አክብረው:: አእምሮህ ለተፈጥሮህና ለምክንያታዊ ፍጥረታት የማይስማማ የተሳሳተ አመለካከት እንዳይኖረው የሚጠብቅህ እርሱ ብቻ ነው። ማስተዋልን፣ ለሰዎች ፍቅርን እና ለመለኮታዊ ፈቃድ መገዛትን የሚያስችልህም ይህ ችሎታ ነው፡፡ ፈጽሞ አስታውስም፦ እያንዳንዳችን የምንኖረው አሁን በዚህች ቅጽበት ብቻ ነው:: የቀረው ጊዜ ወይ አልፏል፣ ወይም ገና ስላልመጣ አይታወቅም፡፡ የምንኖርበት ጊዜ አጭር ነው፤ የምንኖርባትም ምድር ጠባብ ናት:: ትልቁ ዝናም ቢሆን አጭር ነው፡፡ ስለራሳቸውም ሆነ ቀድሞ ስለሞቱት ምንም በማያውቁ ሰዎች በአንደበታቸው ሲላላኩት የሚጠፋ ነው፡ ትናንት የዘር ጠብታ ፤ ነገ አመድ ነህ። ይህችን አጭር ጊዜ ተፈጥሮ በሚጠይቀው መንገድ አሳልፈው:: የወለደችውን ምድር እያመሰገነ፣ ያሳደገውን ዛፍ እያከበረ፤ በለስ ሲበስል እንደሚወድቅ፣ ያለ ጩኸትና ቅሬታ ሕይወትን ተሰናበታት፡፡ ማዕበል በላዩ ላይ እንደሚገለባበጥበት ጽኑ ዓለት ሁን፡፡ እርሱ ሳይናወጥ ይቆማል፤ የባሕሩም ቁጣ በዙሪያው ፀጥ ይላል፡፡ “ይህ ነገር በኔ ላይ የደረሰው እድለቢስ ስለሆንኩ ነው” ትላለህ? እንዲህስ አይደለም፡፡ ይልቁንስ “ይህ ቢደርስብኝም እንኳ፣ በአሁኑ ሳልሰበር፣ ስለሚመጣውም ሳልጨነቅና ሳልፈራ፣ ያለ ሐዘን በጽናት ስለምወጣው የታደልሁ ነኝ” ልትል ይገባሃል።" ይቀጥላል.. @zephilosophy

    Text
    Views8.67K
    Forwards—
    Reactions102
    Comments—
  4. 04

    No text

    Photo
    Views8K
    Forwards—
    Reactions13
    Comments—

Latest posts

#1343Text

ሦስተኛው መንገድ? የሃይማኖት ሊቃውንትና ፈላስፎች የሰጡት ጥልቅ መልስ The Third Way Out? Goodness as God’s Essential Nature እንደ Thomas Aquinas፣ C.S. Lewis፣ Alvin Plantinga፣ Robert Merrihew Adams እና William Lane Craig ያሉ ታላላቅ ፈላስፎች የEuthyphro Dilemma ሐሰተኛ ምርጫ ነው፣ ምክንያቱም ሦስተኛውንና እውነተኛውን አማራጭ ደብቆታል ይላሉ። ጥሩነት የእግዚአብሔር የራሱ ባሕሪ ነው። Modified Divine Command Theory ጥሩነት ከእግዚአብሔር ውጭ ያለ ሕግም አይደለም። እግዚአብሔር በድንገት የፈጠረው የዘፈቀደ ትእዛዝም አይደለም። የእግዚአብሔር ራሱ ዘላለማዊና የማይለወጥ ባሕሪ የጥሩነት መለኪያ ነው። ይህንን በቀላል ምሳሌ አስበው። እሳት ዛሬ ሞቃታማ ልሁን ብሎ በዘፈቀደ አይወስንም። እንዲሁም ከእርሱ በላይ ያለን የሙቀት ሕግ አይታዘዝም። ሙቀት ማለት ራሱ የእሳት ማንነት ነው። በተመሳሳይ መልኩ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ርኅራኄና እውነት ከእግዚአብሔር ማንነት የሚፈልቁ ባሕርያት ናቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር ጭካኔን ማዘዝ አይችልም። ቢያዝ ኖሮ የራሱን ባሕሪ መቃረን ይሆንበት ነበር። Thomas Aquinas እና Natural Law ታላቁ የሥነ መለኮት ሊቅ Thomas Aquinas በ13ኛው ክፍለ ዘመን የእግዚአብሔር ፈቃድና የእግዚአብሔር ጥበብ የተለያዩ አይደሉም ሲል አስተምሯል። የሰው ልጅም በአእምሮውና በሕሊናው ተጠቅሞ ያንን የእግዚአብሔርን ጥበብ በተፈጥሮ ውስጥ ማንበብ ይችላል። Natural Law ማለትም አንድ ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ሳያነብ እንኳን መግደልና መስረቅ ስህተት መሆኑን በሕሊናው ያውቀዋል። Can Goodness Stand Alone? Secular & Philosophical Alternatives ያለ እግዚአብሔር ጥሩነት አለ? የዓለማዊ ፍልስፍና መልሶች ሃይማኖታዊ ባልሆኑ ፈላስፎች ዘንድ ደግሞ ጥሩነት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ሊለይ ይገባል፣ ወይም ደግሞ የሰው ልጅ ሥነ ምግባር ሌላ መሠረት አለው የሚሉ ሦስት ዋና ዋና አመለካከቶች አሉ። ንጹሕ አመክንዮ፣ Immanuel Kant ጀርመናዊው ፈላስፋ Immanuel Kant ሥነ ምግባር በሽልማት ፍለጋ ወይም በቅጣት ፍርሃት ላይ መመሥረት የለበትም ይላል። ጥሩነት የሚመነጨው ከሰው ልጅ ንጹሕ አእምሮና ግዴታ ነው። Categorical Imperative ማንኛውንም ሰው እንደ መሣሪያ ሳይሆን እንደ ዓላማ አክብር። እና ለመላው ዓለም ሕግ እንዲሆን የምትፈልገውን ተግባር ብቻ ፈጽም። Moral Realism እና Open Question Argument፣ G.E. Moore ብዙ ዘመናዊ ፈላስፎች ልክ 2 + 2 = 4 ከሰውም ከእግዚአብሔርም ውሳኔ ውጭ እውነት እንደሆነ ሁሉ፣ ንጹሕን ሕፃን ማሰቃየት መጥፎ መሆኑም የራሱ ተጨባጭ እውነት ነው ይላሉ። ፈላስፋው G.E. Moore ደግሞ ጥሩ ማለት እግዚአብሔር ያዘዘው ማለት ነው ብትል እንኳን፣ ሁልጊዜ እሺ፣ እግዚአብሔር ይህንን አዘዘ። ነገር ግን ያዘዘው ነገር በእርግጥ ጥሩ ነው? ብለን መጠየቅ መቻላችን፣ ጥሩ የሚለው ቃል ከትእዛዝ የተለየ ትርጉም እንዳለው ያሳያል ይላል። Evolutionary Ethics እና Error Theory፣ J.L. Mackie በተቃራኒው እንደ J.L. Mackie ያሉ ተጠራጣሪዎችና የEvolution ተመራማሪዎች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የማይታይ የሥነ ምግባር ሕግ የለም ይላሉ። ጥሩ እና መጥፎ የሚባሉት ስሜቶች የጥንት ሰዎች በቡድን ተባብረው ከአደጋ እንዲተርፉ በተፈጥሮ የዳበሩ የርኅራኄና የኅብረት ስሜቶች ናቸው። Altruism ሁለቱም ወገኖች በዚህ ጥልቅ ክርክር ውስጥ ከባድ የመልስ ምቶች ይገጥሟቸዋል። የእግዚአብሔር ባሕሪ ነው የሚለው መልስ ጥያቄውን ወደ ኋላ አያሸሽውም? Dr. Louise Antony እና Wes Morriston ተቺ ፈላስፎች፣ ለምሳሌ Dr. Walter Sinnott-Armstrong፣ Dr. Louise Antony እና Wes Morriston፣ እንዲህ ብለው ይሞግታሉ። እሺ፣ ጥሩነት የእግዚአብሔር ባሕሪ ነው እንበል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ባሕሪ ለምን አፍቃሪና ፍትሐዊ ሆነ? ለምን ጨካኝ አልሆነም? በአጋጣሚ ባሕሪው እንዲያ ስለሆነ ካልክ፣ እንደገና የዘፈቀደ ይሆናል። Arbitrary አፍቃሪነት በራሱ ስለሚበልጥ ካልክ ደግሞ፣ እንደገና የእግዚአብሔርን ባሕሪ ከእርሱ ውጭ ባለ የጥሩነት መለኪያ እየለካህ ወደ ሁለተኛው ቀንድ ተመለስክ ማለት ነው። ያለ የበላይ መሠረት፣ ተጨባጭ ግዴታ ከየት ይመጣል? Objective Morality በሌላ በኩል የሃይማኖት ፈላስፎች ዓለማዊ አመለካከትን እንዲህ ይፈታተኑታል። ሰው በድንገተኛ Evolution የመጣ እንስሳ ብቻ ከሆነ፣ የአንድ ሰው ደግነትና የሌላው ሰው ጭካኔ ልክ አንዱ ቡና ሌላው ሻይ እንደሚወደው ዓይነት የግል ምርጫ ብቻ እንጂ፣ ለምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ክፉ ወይም ግዴታ ይሆናል? ታላቁ ጸሐፊ Fyodor Dostoevsky እንዳስጠነቀቀው፣ ከሁሉ በላይ የሆነ የሥነ ምግባር መሠረት ከጠፋ፣ ትክክል የሚሆነው የጉልበተኛው ፍላጎት ብቻ ሊሆን ይችላል።                __ Euthyphro የራሱን አባት ለመወንጀል የቸኮለው ጽድቅን አውቃለሁ በሚል ዕውር እርግጠኝነት ነበር። Socrates ግን የትክክለኛ ጥበብ መጀመሪያ በጥልቀት ማሰብና መጠየቅ እንደሆነ አሳየው። ጥሩነትን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ የፍቅር ባሕሪ ውስጥ ብታገኘውም ሆነ በሰው ልጅ ንጹሕ ሕሊናና አመክንዮ ውስጥ ብታየው፣ እውነተኛ ጥሩነት ከፍርሃት ወይም ከሽልማት ፍለጋ የሚመጣ የባሪያ ታዛዥነት አይደለም። ከሁሉም የላቀው ሥነ ምግባር፣ አንድ ነገር ስለታዘዘ ብቻ ሳይሆን፣ ፍቅር፣ እውነትና ፍትሕ ራሳቸው ሕይወትን የሚያከብሩ ውብ እሴቶች ስለሆኑ በነጻ ልብ መልካምን መምረጥ ነው። ©️የአፅናፈ ሰማይ ዜማ @zephilosophy

Open in Telegram
Views3,660−48%vs avg
Forwards—
Reactions38
Comments—
#1342Text

"አንድ ነገር ጥሩ የሚሆነው እግዚአብሔር ስላዘዘው ነው? ወይስ ጥሩ ስለሆነ ነው እግዚአብሔር ያዘዘው?" ከክርስቶስ ልደት በፊት በ399 ዓመት ገደማ፣ በጥንቷ Athens ፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ ሁለት ሰዎች ተገናኙ። አንደኛው ወጣቶችን አበላሽተሃል፣ የከተማዋንም አማልክት አታከብርም ተብሎ የሞት ፍርድ እየጠበቀው የነበረው ታላቁ ፈላስፋ Socrates ነው። ሁለተኛው ደግሞ የራሱን አባት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ለመክሰስ የመጣው፣ በሃይማኖታዊ ዕውቀቱ እጅግ የሚኮራው Euthyphro የተባለ ሊቅ ነበር። Euthyphro ጽድቅና ጥሩነት ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አውቃለሁ፣ ጥሩ ማለት አማልክት የሚወዱት ነገር ነው ሲል በድፍረት ተናገረ። በዚያች ቅጽበት Socrates ለ2,400 ዓመታት ዓለምን ያናወጠ አንድ ጥያቄ ጠየቀው። ይህንንም ተማሪው Plato በመጽሐፉ መዘገበው። አንድ ነገር ጥሩ የሚሆነው አማልክት ስለወደዱት ነው? ወይስ ጥሩ ስለሆነ ነው አማልክት የወደዱት? ይህንን ወደ ዘመናዊው የሃይማኖት ፍልስፍና ስንመልሰው እንዲህ ይሆናል። አንድ ነገር ጥሩ የሚሆነው እግዚአብሔር ስላዘዘው ነው? ወይስ ጥሩ ስለሆነ ነው እግዚአብሔር ያዘዘው? የትኛውንም መልስ ብትመርጥ፣ አእምሮን በከባድ ወጥመድ ውስጥ የሚከት ይህ ጥያቄ Euthyphro Dilemma ይባላል። የጥሩነት ምንጭ፣ Euthyphro Dilemma, አንድ ነገር ጥሩ የሚሆነው እግዚአብሔር ስላዘዘው ነው ወይስ ጥሩ ስለሆነ ነው እግዚአብሔር ያዘዘው? ይህንን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ፍልስፍና ውስጥ እጅግ ዝነኛ የሆነውን መንታ መንገድ እንመልከተው። The Two Horns of the Dilemma: Caught Between Two Traps የጥያቄው ሁለት ቀንዶች፣ ወደ ግራም ወደ ቀኝም የሚያስጨንቀው ወጥመድ Socrates ያቀረበው ጥያቄ ልክ እንደ ሁለት ሹል ቀንዶች ነው። አንዱን ብትይዝ ሌላኛው ይወጋሃል። የመጀመሪያው ቀንድ፣ ጥሩ የሆነው እግዚአብሔር ስላዘዘው ብቻ ነው። Divine Command Theory ይህ አመለካከት የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ያከብራል። በመካከለኛው ዘመን የኖረው የሃይማኖት ሊቅ William of Ockham እንኳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሁሉም በላይ እንደሆነ አምኖ ነበር። ነገር ግን አስፈሪ ችግር ያስከትላል። Arbitrariness Problem መስረቅ፣ መዋሸት ወይም ንጹሐን ሕፃናትን ማሰቃየት ክፉ የሆነው እግዚአብሔር ስለከለከለው ብቻ ከሆነ፣ ታዲያ እግዚአብሔር ነገ ንጹሐን ሕፃናትን አሰቃዩ ብሎ ቢያዝ ኖሮ፣ ሕፃናትን ማሰቃየት በቅጽበት ጥሩና ጽድቅ ይሆን ነበር ማለት ነው? ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ቸርና ጻድቅ ነው ማለት ትርጉሙን ያጣል። Tautology ምክንያቱም እግዚአብሔር የራሱን ትእዛዝ ይፈጽማል ከማለት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። ሁለተኛው ቀንድ፣ ጥሩ ስለሆነ ነው እግዚአብሔር ያዘዘው። Independence Problem አይ፣ ፍቅር፣ ፍትሕና እውነት በራሳቸው ጥሩ ስለሆኑ ነው እግዚአብሔር ያዘዛቸው። ጭካኔም በራሱ ክፉ ስለሆነ ነው የከለከለው ብለህ ብትመልስ፣ ከመጀመሪያው ወጥመድ ትተርፋለህ። ነገር ግን በሌላ ከባድ ችግር ውስጥ ትወድቃለህ። ይህ መልስ ከእግዚአብሔር በላይ እና ከእግዚአብሔር ውጭ የሆነ የጥሩነት ሕግ አለ ማለት ነው። እግዚአብሔር ራሱ ያንን ከእርሱ በላይ ያለውን የሥነ ምግባር መመሪያ አንብቦ ለእኛ የሚያስተላልፍ መምህር እንጂ የጥሩነት ምንጭ አይሆንም። ይህ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍጹም ፈጣሪነትና ሉዓላዊነት ይቀንሳል። የሃይማኖት ሊቃውንትና ፈላስፎች ከሁለቱ የተሻለ ሶስተኛ መንገድ አለ ይላሉ ይቀጥላል... @zephilosophy

Open in Telegram
Views3,760−46%vs avg
Forwards—
Reactions46
Comments—
#1341Text

የፖለቲከኞች እግዚአብሔር ማን ነው? ኒኮሎ ማኪያቬሊ እንደሚለው “መሪዎች ሕዝብን ለመቆጣጠር ሃይማኖትን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ሊጠቀሙበት ይገባል ምንም እንኳ እነሱ ራሳቸው ባያምኑበትም" ሲል  ስፒኖዛ የተባለውም ፈላስፋ ደግሞ በበኩሉ  “መንግሥታት ስለ አምላክ የሚያስተምሩት ሕዝቡ በፍርሃት እንዲታዘዝላቸው ሲሉ ነው፡፡  ይህ ደግሞ ከእውነተኛ ሃይማኖት ይልቅ ለሥልጣን ጥበቃ ነው" ይላል፡፡ ካርል ማርክስ በበኩሉ ሲያብራራ ደግሞ እንዲህ ያላል “ፖለቲከኞች አምላክን የሚጠቅሱት ሕዝብን ለመጨቆን ነው “ በራሱ ቃል ደግሞ “ኦፒየም ” ነው ይላል። በአጭር አነጋገር ፈላስፋዎች እንደሚመለከቱት የፖለቲከኛው አምላክ ከእውነተኛ እምነት ይልቅ ለሥልጣን፣ ለሥርዓትና ለፖለቲካ ጥቅም የሚቀረጽ ጽንሰ ሐሳብ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች አሳቢዎች ስለ ፖለቲከኛው አምላክ የሚሉትም አላቸው፡፡ ቶማስ ሆብስ  “ሉዓላዊ ኃይል ራሱ ሟች አምላክ” ነው (ሌዊያታን) ፖለቲከኞች ይህን አምላክ በመጥቀስ ፍፁም ታዛዥነት ያስገኛሉ ሲል። ጆርጅ ኦርዌል “ፖለቲከኛው ራሱን እንደ አምላክ አድርጎ ያቀርባል” ይላል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ አሳቢዎች የሚያሳዩት ፖለቲከኛው “አምላክ” ሲል ከሃይማኖታዊ እምነት ይልቅ ሥልጣንን፣ ፍርሃትን፣ ታዛዥነትንና ሕዝብን ለመጨቆን የሚጠቀሙበት ጽንሰ ሀሳብ መሆኑን ነው። ሦስቱም ሃይማኖቶች (አይሁድ፣ ክርስቲያን እና  እስልምና) አብርሃማዊ ሃይማኖቶች በመባል ይታወቃሉ። ሦስቱም አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ያምናሉ። ይህ አምላክ ዓለምን ፈጠረ፤ ነቢያትን ልኳል፤ መላእክት አሉ፤ ከሞት በኋላ ትንሣኤ እና ፍርድ አለ፤ ሰው በጎ ሥራ ሊሠራ፣ ክፉን ሊርቅ ይገባል፤ ጸሎት፣ ጾም፣ እና ምጽዋት አስፈላጊ ናቸው ወዘተ ይላሉ፡፡ነገር ግን ስለዚህ አንድ አምላክ ማንነት፣ ባህሪ እና ከሰው ጋር ስላለው ግንኙነት የተለያየ አመለካከት እና አስተምህሮ  አላቸው። የአይሁድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን የገባ (ዘፍጥረት 15) እስራኤልን ከግብጽ ያወጣ፣ ቅዱስና ፍትሐዊ፣ አንድ እና ሥጋ ያልለበሰ አምላክ ነው። ኢየሱስን እንደ መሲሕ አይቀበሉም። የክርስቲያኖች እግዚአብሔር (ሥላሴ) አንድ አምላክ በሦስት አካል (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ)። ኢየሱስ ተውልዷል፣ ተሠቃይቷል፤ሞቷል፣ተነስቷልል፤አርጉል፤ይመለሳል ይላሉ ። የእስልምና  (አላህ) አንድ ነው። አላህ ማንም የማያስፈልገው ፍጹም ነው። አልወለደም፣ አልተወለደም። ሥጋ አልለበሰም። ምንም የሚመስለውም የለም ይላሉ፡፡ የፈላስፋዎች እግዚአብሔር (የሎጂክ እና የምክንያት አምላክ ነው)  ፍጹም ኃይል እና ዕውቀት ያለው ነው፣ ስሜት የሌለው ነው፣ ከዓለም ጋር የማይገናኝ  ነው፡፡ረቂቅ (Abstract) ነው ፡፡ በቦታና በጊዜ ውስጥ የማይገኝ ነው፡፡  ቁሳዊ ያልሆነ ነው፡፡ የማይለወጥ (Immutable) ነው፡፡  ምንም አይነት ለውጥ (ዕውቀት፣ ኃይል፣ ስሜት) የለውም፡፡ ራሱ ሳይንቀሳቀስ ሌላውን ሁሉ የሚያንቀሳቅስ (Unmoved Mover  አርስቶትል እንዳለው ነው፡፡ ከዓለም ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው (Impersonal)ነው፡፡ አይጸለይበትም፣ አያመልኩትም፣ መልስ አይሰጥም። ከፍቅር እና  ከቁጣ ነጻ ነው፡፡ ይህ አምላክ በሰው ሎጂክና ምክንያት የተገኘ ነው። የፈላስፎች አምላክ እንደ በረዶ ንጹሕ፣ ደግሞም  እንደ በረዶ ቀዝቃዛ ነው። ፓስካል እንደሚለው “የአርስቶትል አምላክ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ሳይሆን፣ የፈላስፋዎችና አምላክ ነው፡፡ ይህ አምላክ ሕይወት አይሰጥም የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ብቻ ነው ሕይወት የሚሰጠው ይላል። የፖለቲከኞች እግዚአብሔር ሃይማኖታዊ አይደለም መሣሪያ ነው። ለምርጫ ድምጽ፣ ጦርነትን ለማጽደቅ፣ ለራስ ጥቅም ይጠቅማል። የእነርሱ እግዚአብሔር ጸጥ ያለ፣ የማይገሥጽ፣ የማይመራ። እንደ መስታወት የሆነ ማንኛውም ሰው ራሱን የሚያይበት ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሦስቱም ሃይማኖታዊ እምነቶች ስለ እግዚአብሔር ማንነት ቢለያዩም፣ቢያንስ እግዚአብሔር እንዳለ እና እርሱ ቅዱስ፣ ፍትሐዊ፣ እውነተኛ እንደሆነ ይስማማሉ።የፖለቲከኞች እግዚአብሔር ግን ብዙ ጊዜ ከእነዚህ ባህሪያት ጋር አይጣጣምም። የፖለቲከኞች እግዚአብሔር ማን ነው? የፖለቲከኞች እግዚአብሔር ማለት በፖለቲከኞች አእምሮ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ምስል ነው። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከሃይማኖት ትምህርት ይልቅ ከሥልጣን ጥማት፣ ከፖለቲካ ስልት እና ከራስ ጥቅም ጋር የተያያዘ ነው። የዚህ "አምላክ" ባህሪያት ደግሞ የመጀመሪያው ተጠቃሚ (Utilitarian) እግዚአብሔር እንደ አንድ መሣሪያ ይታያል። ለምሳሌ ለምርጫ ድምጽ ለማግኘት በመድረክ ላይ ስሙ ይጠራል። ፖለቲከኞች መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርኣን የሚያነሡት ሕዝቡን ለማስደንገጥ እንጂ በእውነት ለመከተል አይደለም። ይህ እግዚአብሔር እንደ ኤሌክትሪክ ማብሪያ እና ማጥፊያ ነው፡፡ በሚፈለጉበት  ጊዜ ይበራል ሥራውን ሲጨርስ ይጠፋል። ሁለተኛው በሰው ምስል የተሠራ (Anthropomorphic) “እግዚአብሔር በእኔ በኩል ነው” የሚል ነው፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ባላጋራዬ ላይ ፍርድ ያመጣል የሚል ነው፡፡  በዚህ ምርጫ እግዚአብሔር ፈቃዱን አሳይቷል ይላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ንግግሮች የፖለቲከኞች እግዚአብሔር በራሳቸው ምስል እንደተሠራ ያሳያሉ። ይህ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከእነሱ ጋር ነው፡፡ይህ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር አይደለም ምክኒያቱም በፖለቲከኞች ምስል የተሠራ  ነው።  ይህ በፖለቲከኞች ምስል የተሠራው  እግዚአብሔር እንደ ጦር ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ማንኛውም ወገን ራሱን ለማስመለክ ይጠቀምበታል። ሶስተኛው ጸጥ ያለ (Silent) ይህ እግዚአብሔር በጣም የሚያስደንቀው ነገር ቢኖር ፈጽሞ መልስ አለመስጠቱ ነው። ሙሴን ያነጋገረው እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ፖለቲከኞች ሲናገሩ ይህ እግዚአብሔር ጸጥ ይላል። ውሸት ሲናገሩ ጸጥ ይላል። ድሆችን ሲዘርፉ ጸጥ ይላል። ይህ እግዚአብሔር ጸጥታው የሚሰበረው በምርጫ ዘመን በተሰነዘሩ የሃይማኖት መሪ ቃላት ብቻ ነው። ይህ እግዚአብሔር እንደ ግድግዳ ላይ እንደተሰቀለ ሥዕል ነው ፡፡ ታላቅ ቢመስልም መናገር ግ ን አይችልም። አራተኛው ጦርነትን ቅዱስ የሚያደርግ (Sanctifier of War) በታሪክ ውስጥ ብዙ ጦርነቶች ተካሄደዋል እንዳንዶቹም የተካሄዱት “በእግዚአብሔር ስም” ነው። ፖለቲከኞ ጦርነት ከመግባቱ በፊት ጸሎት ይደረጋል። የፖለቲከኞች እግዚአብሔር ሁለቱም ወገኖች እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር እንዳለ ያምናሉ። ይህ እግዚአብሔር ለየፖለቲከኞች እንደ ጋሻ ነው ፡፡ አንዱ ወገን ጠላትን ለመግደል ሲጠቀምበት ሌላኛው ደግሞ ራሱን ለመከላከል ይጠቀምበታል። አምስተኛው ፈጣን ዘንግ (Plank) ፖለቲከኞች እንደሚፈልጉት ሁሉ ይህ እግዚአብሔር በፍጥነት አመለካከቱን ይለውጣል። ትናንት በንግግሩ ላይ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንዲህና እንዲያ እናደርጋለን፤ ድህነትን እናስወግዳለን” ያለው ፖለቲከኛ ዛሬ ከሥልጣን ጋር ሲገናኝ ስለ እግዚአብሔርም ሆነ ስለ ደሀው ምንም አያስታውስም። ልክ  አሸዋ ላይ እንደተሳለ መስመር ነው እግር ሲረግጠው ይጠፋል። እነዚህንና መስል ነገሮችን ሳስብ የማስታውሰው ነገር ቢኖር ትልቁ የሩስያ ጸሐፊ አሌክሳንደር ሶልዚኒትሲን ያለውን ነው  “ዓለምን ከክፋት የሚያድነው የፖለቲከኞች እግዚአብሔር አይደለም በሰው ልብ ውስጥ የሚኖረው እግዚአብሔር እንጂ ” ፀሀፊ-ዮናስ ዘውዴ @zephilosophy

Open in Telegram
Views5,220−25%vs avg
Forwards—
Reactions62
Comments—
#1340Text

"ኢ-ፍትኃዊነት ፈጣሪን የመስደብ ያህል ታላቅ ኃጢአት ነው:: ምክንያቱም የተፈጥሮ ሕግ ምክንያታዊ ለሆኑ ፍጥረታት ይህንን ሥርዓት ሠርቷልና። ይኸውም እንደየባሕርያቸው እርስ በርስ ሊረዳዱ እንጂ ሊጎዳዱ አይደለም። ስለዚህም የተፈጥሮን ፈቃድ የሚተላለፍ ሰው አምላኩን ይሳደባል።" "ነገሮች እንዲሆኑ ወይም እንዳይሆኑ ከመጸለይ ይልቅ፣ ምንም ነገር ቢሆን እንዳትፈራ፣ እንዳትመኝ ወይም እንዳታዝን ለምን አትጸልይም? አምላክ ሰዎችን መርዳት የሚችል ከሆነ በዚህ መንገድ ሊረዳን አይችልምን? ምናልባት “እነዚህን ነገሮች አምላክ በእኔ ስልጣን - ስር አድርጓቸዋል” ትልም ይሆናል᎓᎓ ታዲያ በቁጥጥርህ ስር ያልሆነውን ነገር ለመለወጥ እንደ ባሪያ ወይም እንደ ለማኝ ከምትማጸን፣ በስልጣንህ ስር ያለውን በነጻነት መፈጸም አይሻልህምን?" “ይህ ነገር ሁሌም ይገርመኛል፦ ራሳችንን ከሌሎች ሰዎች ይልቅ አብልጠን እንደምንወድ የታወቀ ነው። ሆኖም ስለ ራሳችን ከምናስበው ይልቅ ሌሎች ስለ እኛ ስለሚያስቡት እንጨነቃለን። መልአከ ወይም ጠቢብ ሰው ተገልጦን በልብህ የምታስበውን አትደብቅ፤ ወዲያውኑ ጩኸሀ ተናገረው ቢለን፣ አንዲት ቀን እንኳ አንዘልቅም ነበር። ለራሳችን ካለን እወነታኝነት ይልቅ የሌሎች አስተያየት ያንን ያህል ይገዛናል።” “ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነቃ ለራስህ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ዛሬ የማገኛቸው ሰዎች ጣልቃ ገቦች፣ ምስጋና ቢሶች፣ ትዕቢተኞች፣ አታላዮች፣ ምቀኞችና ርሀራሄ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ የሆኑት መልካሙን ከክፉው መለያት ስለማይችሉ ነው። እኔ ግን የመልካምን ነገር ውበትና የክፉንም ነገር አስቀያሚነት አይቻለሁ፤ ስለዚህ አንዳቸውም ሊጎዱኝ አይችሉም።” "እውነተኛ እድለኛነት ማለት፣ ውሸትን፣ ግብዝነትን፣  ትዕቢትን ሳያውቁና ሳይቀምሱ ከዚህ ዓለም መሰናበት ነበር፡፡ ነገር ግን “ቀጣዩ ምርጥ ዕድል” እነዚህን ክፉ ነገሮች ከተጠየፍክ በኋላ መሞት ነው:: ወይስ ከክፋት ጋር ለመተኛት ወስነሃል? ልምድህ እንኳ እንደ ቸነፈር በሽታ እንድትሸሸው  አላስተማረህምን? ምክንያቱም የአእምሮ ክፋት ከተበከለ አየር ከሚመጣ በሽታ ይልቅ እጅግ የከፋ ቸነፈር ነውና። የሥጋ በሽታ ሕይወትህን ብቻ ያጠፋል፤ ይህኛው ግን ሰውነትህንና ሰብአዊነትህን ይገድላል።" Marcus Aurelius 📖Meditation @zephilosophy

Open in Telegram
Views5,920−15%vs avg
Forwards—
Reactions40
Comments—
#1339Text

የምክንያታዊ ነፍስ ተፈጥሮ Marcus Aurelius 📖Meditation ሂፖክራተስ ብዙ በሽተኞችን አከመ፤ በኋላ ግን ራሱ ታሞ ሞተ። ኮከብ ቆጣሪዎች የብዙ ሰዎችን ሞት ተነበዩ፤ በመጨረሻ ግን የራሳቸውም ሰዓት ደረሰ። ብዙ ከተሞችን ያጠፉና በጦርነት በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን የገደሉት እነ ታላቁ እስክንድር፣ ፖምፔ እና ቄሳርም ከዚህ አለም ተሰናበቱ። አለም በእሳት ትጠፋለች እያለ ሲሰብክ የነበረው ሄራክሊተስ ሰውነቱ ውሃ ቋጥሮ በጠና ታሞ ሞተ። ዴሞክሪተስን ተራ ተባዮች ገደሉት፤ ሶቅራጥስን ደግሞ ሰው የተባሉ ተባዮች ገደሉት። ይህ ምን ማለት ነው? መርከብ ላይ ተሳፍረሃል፣ ጉዞህን ጨርሰህ የምትወርድበት ሰዓት ይደርሳል። በየቀኑ የሕይወታችን ክፍል እየተሸረሸረና የቀረው ጊዜ እያጠረ መምጣቱ ብቻ ሊያሳስበን አይገባም፡፡ ይህንንም ማሰብ አለብን፦ ዕድሜያችን ቢረዝም እንኳ፤ ዓለምን ለመረዳትና መለኮታዊ እንዲሁም ሰብአዊ እውቀቶችን ለመመርመር የሚያስችል የአእምሮ ብቃት እንደቀድሞው አብሮን እንደሚዘልቅ እርግጠኛ መሆንስ እንችላለን? ምክንያቱም አእምሯችን መጃጀት ከጀመረ መተንፈስ፣ መብላት፣ ማሰብና ስሜታዊ መሆን አናቆም ይሆናል። ነገር ግን እምቅ አቅማችንን መጠቀም፣ ግዴታችንን መለየት፣ የምንሰማውንና የምናየውን መተንተን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጤናማ አእምሮ የሚጠይቁ ናቸውና ይጠፋሉ። ስለዚህ መፍጠን አለብን፡፡ ወደ ሞት በየቀኑ እየቀረብን ከመሄዳችንም ባሻገር ነገሮችን የመረዳትና የአለምን ሁኔታ የመገንዘብ አቅማችን ሕይወታችን ከማለፉ በፊት ሊጠፋም ይችላል። በግዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ በራስ ወዳድነት ሳይሆን ለጋራ ጥቅም፣ ያለ ጥንቃቄ ሳይሆን በምክንያት፣ በፍርሃት ሳይሆን በልበ ሙሉነት ሥራ። ሃሳብህን አትቀባባ፡፡ አላስፈላጊ ቃላትን አትናገር፤ ብዙ ነገሮች ውስጥ አትግባ። በውስጥህ ያለው መንፈስ የወንድን፣ የብስለትን፣ የመሪን ስብዕና ይላበስ፡፡ ቦታውን እንደያዘና የመጠራትን ጥሪ በትዕግስት እንደሚጠብቅ፣ መሐላ ወይም ምስክር እንደማያስፈልገው ወታደር ሁን። በራስህ ደስተኛ ሁን፤ የሌሎችን እርዳታ ወይም ከሌሎች የሚገኝ ሰላምን አትጠበቅ᎓᎓ በራስህ ቀጥ በል እንጂ በሌሎች ድጋፍ አትቁም፡፡ የጠራና የተስተካከለ ሰው አእምሮ ውስጥ ቆሻሻ የለም፡፡ ሕይወቱ በሞት ሲቋረጥ፣ ተውኔቱ ሳያልቅ እንደሚያቋርጥ ተዋናይ አይሰማውም᎓᎓ ባርነት ወይም ትዕቢት አይታይበትም᎓᎓ ማጎብደድ ወይም ንቀት የለበትም። ሰበብ መደርደር ወይም መሸሽ የለበትም፡፡ አስተሳሰብህን የመቆጣጠር ችሎታህን አክብረው:: አእምሮህ ለተፈጥሮህና ለምክንያታዊ ፍጥረታት የማይስማማ የተሳሳተ አመለካከት እንዳይኖረው የሚጠብቅህ እርሱ ብቻ ነው። ማስተዋልን፣ ለሰዎች ፍቅርን እና ለመለኮታዊ ፈቃድ መገዛትን የሚያስችልህም ይህ ችሎታ ነው፡፡ ፈጽሞ አስታውስም፦ እያንዳንዳችን የምንኖረው አሁን በዚህች ቅጽበት ብቻ ነው:: የቀረው ጊዜ ወይ አልፏል፣ ወይም ገና ስላልመጣ አይታወቅም፡፡ የምንኖርበት ጊዜ አጭር ነው፤ የምንኖርባትም ምድር ጠባብ ናት:: ትልቁ ዝናም ቢሆን አጭር ነው፡፡ ስለራሳቸውም ሆነ ቀድሞ ስለሞቱት ምንም በማያውቁ ሰዎች በአንደበታቸው ሲላላኩት የሚጠፋ ነው፡ ትናንት የዘር ጠብታ ፤ ነገ አመድ ነህ። ይህችን አጭር ጊዜ ተፈጥሮ በሚጠይቀው መንገድ አሳልፈው:: የወለደችውን ምድር እያመሰገነ፣ ያሳደገውን ዛፍ እያከበረ፤ በለስ ሲበስል እንደሚወድቅ፣ ያለ ጩኸትና ቅሬታ ሕይወትን ተሰናበታት፡፡ ማዕበል በላዩ ላይ እንደሚገለባበጥበት ጽኑ ዓለት ሁን፡፡ እርሱ ሳይናወጥ ይቆማል፤ የባሕሩም ቁጣ በዙሪያው ፀጥ ይላል፡፡ “ይህ ነገር በኔ ላይ የደረሰው እድለቢስ ስለሆንኩ ነው” ትላለህ? እንዲህስ አይደለም፡፡ ይልቁንስ “ይህ ቢደርስብኝም እንኳ፣ በአሁኑ ሳልሰበር፣ ስለሚመጣውም ሳልጨነቅና ሳልፈራ፣ ያለ ሐዘን በጽናት ስለምወጣው የታደልሁ ነኝ” ልትል ይገባሃል።" ይቀጥላል.. @zephilosophy

Open in Telegram
Views8,670+24%vs avg
Forwards—
Reactions102
Comments—
#1338Text

የኃይል ፈቃድ (Will to Power) ​«ሕያው ፍጥረት ከሁሉም በላይ ኃይሉን መልቀቅ ይሻል፤ ሕይወት ራሷ የኃይል ፈቃድ ናት።» — ኒቼ ​አንዲት ሕፃን መራመድ ስትለማመድ ትወድቃለች፣ ትነሳለች፣ እንደገናም ትሞክራለች። በሕይወት ለመቆየት መራመድ አያስፈልጋትም፤ መዳህ ወይም መቀመጥ ትችላለች። ታዲያ ቀደሞውኑ ማድረግ በምትችለው ነገር ሳትረካ እንዲህ እንድትተጋ የሚያደርጋት ምንድን ነው? የነርቭ ሳይንቲስት ሂደቱን ማብራራት ይችላል። የፊዚዮሎጂ ባለሙያ ጡንቻዎችን፣ ሚዛንን እና እየዳበረ የሚሄደውን የእንቅስቃሴ ቅንጅት መግለጽ ይችላል። የስነ-ልቦና ባለሙያ ደግሞ ስለ መማር፣ መኮረጅ (imitation) እና ማጠናከሪያ ማስረዳት ይችላል። እነዚህ ሁሉ ማብራሪያዎች ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ፍልስፍና ሁልጊዜም ማብራሪያው ምክንያታዊ መስሎ መታየት ከጀመረ በኋላ እንኳን ጥያቄዎችን መጠየቅ የመቀጠል አስገራሚ ባህሪ አለው። ባለበት ለመቆየት አሻፈረን የሚለው ይሄ በውስጣችን ያለው እንቅስቃሴ ምንድን ነው? ለምንስ ነው አብዛኛውን ጊዜ ራሳችንን ከመጠበቅ (preserve ከማድረግ) ባለፈ፣ ትናንት ከነበርነው የበለጠ አቅም ያላቸው ለመሆን የምንፈልገው? ግልጹ መልስ ህልውናን ማስቀጠል (survival) ነው። ሕያው ፍጥረታት ህልውናቸውን ማስቀጠል አለባቸው። ምግብ፣ መጠለያ፣ መራባት እና ከአደጋ መከለል ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛው የባህሪ ዓይነት በሕይወት ከመቆየት ግፊት አንጻር ልንረዳው ይችላል። ሌላው መልስ ደግሞ ደስታ (pleasure) ነው። ምናልባት ጥሩ ስሜት ያለውን እንፈልጋለን፤ የሚያመንን ደግሞ እንሸሻለን። በሁለቱም ማብራሪያዎች ውስጥ እውነት አለ። ግን የሰው ልጅ ሕይወት እነዚህን ማብራሪያዎች ተሻግረው የሚፈሱ ምሳሌዎችን እንዳሳየን ነው። ቀድሞውኑ በቂ ገንዘብ ያለው ሰው የበለጠ ይፈልጋል። አንድ ሰዓሊ ሀብታም ሊያደርገው የማይችል ነገር ለመፍጠር አስር ዓመታት ያሳልፋል። አንድ የሂሳብ ሊቅ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተግባራዊ ጥቅም የሌለውን ችግር ለመፍታት ሌሊቶችን ቁጭ ብሎ ያድራል። አንድ ደራሲ ሰዓታትን ወስዶ የጻፈውን ገጽ ገና እንደፈለገ ስላልሆነለት ይቀደዋል። የሆነ ሰው በጫፉ ላይ የሚጠብቀው ምንም ዓይነት ሀብት የሌለበትን ተራራ ይወጣል። ሌላው መናገር መቻል ስለፈለገ ብቻ ከባድ ቋንቋ ይማራል። አንድ ሰው የማይመግበውን፣ የማያስከፍለውን ወይም ሕይወቱን የማያድንለትን ሀሳብ ለመረዳት ዓመታትን ያሳልፋል። እና ደግሞ ሆን ብለው ፈታኝ ነገሮችን የሚመርጡ ሰዎችም አሉ። ምቾትን የሚተው መነኩሴ፤ ከአስደሳች ቅዠት ይልቅ የሚረብሽ እውነትን የሚመርጥ ፈላስፋ፤ ሰውነቱን ከቀደመው ወሰን በላይ የሚገፋ ስፖርተኛ፤ ቀላል ስታይሎችን የማይቀበል አርቲስት፤ መላመድን መሸከም አቅቶት የተለመደ ሕይወቱን ትቶ የሚሄድ ሰው። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ምን እየፈለጉ ነው? ምናልባት ኒቼ በምኞታችን ግብ ላይ ብቻ ከመጠን በላይ እንዳተኮርንና ከጀርባው ስላለው ኃይል ግን በቂ ትኩረት እንዳልሰጠን ይነግረን ይሆናል። እኛ አንድ ሰው ምን እንደሚፈልግ እንጠይቃለን። ኒቼ ግን በዚያ ሰው ውስጥ የሚያልፈውና የሚያንቀሳቅሰው ነገር ምን እንደሆነ ይጠይቃል። ከዚያም ከታዋቂ ጽንሰ-ሃሳቦቹ አንዱ ይመጣል: «የኃይል ፈቃድ (Will to power)»። አብዛኛውን ጊዜ ፍላጎትን ወይም ፈቃድን እንደ ንቁ አእምሯዊ ውሳኔ እናስበዋለን። እወስናለሁ። እመርጣለሁ። እፈልጋለሁ። እሰራለሁ። እንላለን ኒቼ ግን ጭንቅላታችን ውስጥ ተቀምጦ ለሁሉም ነገር ትእዛዝ የሚሰጠውን ይህን ትንሽ ገዢ በጥርጣሬ ነው የሚያየው። በኒቼ የስነ-ልቦና እይታ፣ የሰው ልጅ እንደሚታየው አንድ ወጥ (unified) አይደለም። በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚንቀሳቀሱ ስሜታዊ ግፊቶች፣ ልምዶች፣ ምኞቶች፣ ፍርሃቶች፣ ተፈጥሯዊ ድራይቮች እና የተወረሱ እሴቶች አሉ። “እኔነት/the self” የምንለው ነገር መንግስቱን እንደሚገዛ ንጉሥ ሳይሆን፣ እርስ በርስ በሚፎካከሩ ኃይሎች መካከል ያለ ጊዜያዊ ስምምነት ወይም arrangement ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ “ማድረግ ስለፈለግኩ ነው ያደረግኩት” እንላለን፤ ነገር ግን እውነተኛ ትርጉሙ በውስጣችን ያለው አንድ ነገር በውስጣችን ካሉት ሌሎቹ ነገሮች ላይ የበላይነት አገኘ ማለት ነው ምቾትን እንፈልጋለን፤ ግን ስኬትንም እንፈልጋለን። እውነትን እንፈልጋለን፤ ግን ከቅዠቶቻችን የምናገኘውን መጽናኛም እንፈልጋለን። መደነቅ እንፈልጋለን፤ ግን አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ ለብቻችን መተው እንፈልጋለን። የሰው ልጅ በነዚህ መሰል ተቃርኖዎች የተሞላ ነው። ስለዚህ በኒቼ ዘንድ “ፈቃድ” ወይም “ፍላጎት” እንደ ተራ ንቁ ምኞት ብቻ መወሰድ የለበትም፣ ምክንያቱም ሃሳቡ ከንቁ ምኞት ይልቅ ወደ ጥረት፣ ወደ ውስጣዊ ግፊት እና ወደ ኃይሎች እንቅስቃሴ የቀረበ ነው። ኃይል" የሚለውን ቃልም ስንረዳ በቀላሉ የበላይነትን (domination) ብቻ መምሰል የለበትም፦ ​ኃይል ማለት የመንቀሳቀስ፣ የመቋቋም፣ የመለወጥ እና ለአንድ ነገር ቅርጽ የመስጠት አቅም ነው። ራስን ማሸነፍ (self-overcoming) ማለት ማልዶ መንቃት፣ ጂም መሄድ፣ ገንዘብ መስራት እና የበለጠ ውጤታማ መሆን ብቻ አይደለም። የኒቼ ጥያቄ በጣም የበለጠ ረባሽ ነው። ልታሻሽለው የምትሞክረው ሰው የተገነባው በፍጹም መርጠሃቸው ከማታውቃቸው እሴቶች ቢሆንስ? ብርቱ መሻትህ የተወረሰ ቢሆንስ? ስለ ስኬት ያለህ ሀሳብ ከአንተ ይልቅ የማህበረሰብህ ቢሆንስ? ልዩ የመሆን ፍላጎትህ በራሱ ሌላ የታዛዥነት ዓይነት ብቻ ቢሆንስ? ኒቼ ዛሬም ረባሽ የሆነው እሴቶች ከሰማይ እንዳልወረዱ ስለሚያሳይ ነው። ከየት መጡ? ምን ዓይነት ሰው እንደፈለጋቸው? ምን ዓይነት ሕይወትን እንዳገለገሉ? በእነሱ በኩል ምን ዓይነት ኃይሎች እንደተገለጹ ይጠይቃል። ዋጋ ያለው ምንድን ነው? ምን ክቡር፣ ምን ኃጢአት፣ ምን ጠንካራ፣ ምን ደካማ እንደሚባል ይጠይቃል? እናም ወደ ራሳችን ይመልሰናል፦ የምትፈልጉትን እንድትፈልጉት ያስተማራችሁ ማነው? ማንም ባያያችሁ ከብርቱ መሻታችሁ ምን ይቀራል? ማንም ባያመሰግናችሁ ከሞራላችሁ ምን ይተርፋል? ግን እዚህ ላይ ኒቼን መቃወም አለብን ብዬ አስባለሁ። የሰው ልጅ ወደ አንድ ዋና ግፊት/ድራይቭ አይቀነስም። ደህንነትንና ነፃነትን፣ እውነትንና ምቾትን፣ እውቅናንና ብቸኝነትን እንፈልጋለን፤ ራሳችንን መጠበቅ እንፈልጋለን፣ አንዳንዴም ከራሳችን ማለፍ። ስለዚህ የኃይል ፈቃድ እንደተረጋገጠ ሳይንሳዊ ሕግ ወይም እያንዳንዱን እንቆቅልሽ የሚከፍት ምትሃታዊ ቁልፍ ሳይሆን ጥያቄ፣ መነፅር እና መቀስቀሻ ቢሆን ይሻላል። ሲጠቀሙበት አንድ ነገር ይታያል፤ ዞር ሲያደርጉት ሌላ ነገር ይመለሳል። አንዲት ሕፃን በክፍሉ መሃል ትቆማለች። ትወድቃለች። ትነሳለች። እንደገና ትሞክራለች። ምናልባት መራመድ እየተማረች ነው። ምናልባት የኃይል ፈቃዷን እየገለፀች ነው። ምናልባትም ሕያው ነች። እነዚህ ሦስቱ መጀመሪያ እንደሚታዩት የተራራቁ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ምክንያቱም ከታላላቅ ቃላት በታች ትንሽ የሚያስደንቅ እውነት አለ፦ እኛ አላለቅንም። ሁሌም የሆነ ነገር እየሆንን ነው። ከባዱ ጥያቄ ኃይል አለን ወይ የሚለው አይደለም። ኃይላችን እኛን ምን እያደረገን ነው የሚለው ነው። እናም ወድቆ እንደገና ለተነሳ ሰው ሁሉ የሚጠብቀው ጥያቄ ይህ ነው፦ ባለበት ቦታ ላይ ለመቆየት አሻፈረኝ የሚለው በውስጣችን ያለው ይህ ነገር ምንድን ነው? ፀሀፊ- ዮናታን አቢስ @zephilosophy

Open in Telegram
Views10,600+51%vs avg
Forwards—
Reactions74
Comments—
#1337Text

ኩርት ቮነጉት የጦርነትን አሰቃቂነት እና የሰው ልጅ ዕብደትን በህይወቱ ተሞክሮ ልክ እንዳልሆነ አይቶ የሚያሳይ ደራሲ ነው፡፡ ኩርት ቮነጉት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ድሬስደን ከተማ የቦምብ ድብደባ ውስጥ ተይዞ ከሞት የተረፈ ሰው ነው። ይህ ገጠመኙ ጦርነት የጀግንነት ማሳያ ሳይሆን ንጹሐንን የሚጨፈጭፍ፣ ሰብአዊነትን የሚያጠፋ እና ትርጉም የለሽ አረመናዊ ድርጊት መሆኑን ይናገራል፡፡ ኩርት ቮነጉት በሞራል እና በፖለቲካ መካከል ስላለው  ግጭት "ማዘር ናይት" ብሎ በሰየመው ድረሰቱ  በጦርነት ጊዜ መንግሥታት ሕዝቦችን ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ "ጥሩ" እና "ክፉ" ብለው ይከፋፍሏቸዋል ይለናል። ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ "ለሀገር ብዬ ነው" "ተላላኪ ነበርኩ" ወይም "የትዕዛዝ ግዴታ ነው" ተብሎ የሚሰራው ክፉ ነገር የሰውን ህሊና እና እውነተኛ ማንነት ለዘላለም እንደሚበክለው ለማሳየት ይሞክራል። ኩርት ቮነጉት "እኛ የምንመስለው የምንመስልበትን ነገር ነን" ይለናል፡፡ ይህም ማለት በውስጣችን ጥሩ ሐሳብ አለን ብንልም በውጭ ላይ የምንፈጽመው ተግባር ጥላቻን መስበክ፣ መከራን ማባባስ ይሆናል፡፡ ይህም በሂደት የእኛ እውነተኛ ማንነት ይሆናል ስለዚህ ድርጊታችን ከሐሳባችን ጋር ሊጣጣም ይገባል እያለ አበክሮ ይሞግተናል። ኩርት ቮነጉት በጦርነትና በግጭት ጊዜ "እኛ ፍጹም ጻድቃን ነን፣ እነሱ ደግሞ ፍጹም ክፉዎች ናቸው" የሚለው አመለካከት የሐሰት ትርክት መሆኑን እና ሁለቱም ወገን የሰውን ልጅ ሕይወት እንደሚያጠፉ ያሳያል። እንደ "ማዘር ናይት" ታሪክ ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ እና በቡድን ስም ተነስተው ጥላቻን የሚሰብኩ ሕዝብን እርስ በእርስ የሚያጣሉ አካላት አሉ። ኋላ ላይ "ለዓላማ ብዬ ነው" ወይም "በትዕዛዝ ስር ስለነበርኩ ነው" "ተላላኪ ነበርኩ"  የሚሉ ማስተባበያዎች ቢቀርቡም በምድር ላይ የጠፋው ንጹህ ሕይወት እና የተበላሸው ማህበራዊ ትስስር ግን ሊመለስ አይችልም። ስለዚህ ማይክ በያዝን ወቅትም ሆነ አደበታችንን በከፈተን ጊዜ ሁሉ "ምን እየፈጠርን እና ምን እያስተላለፍን ነው?"ብሎ መጠየቅ የጊዜው ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ባሳለፈቻቸው ግጭቶችና ጦርነቶች ያየነው እውነት ቮነጉት ከድሬስደን ውድቀት ጋር ካስተማረው ትምህርት ጋር አንድ ነው። በጦርነት ውስጥ አሸናፊ የሚባል ወገን የለም፡፡ ሁለቱም ወገን የሚያጡት ወጣቶቻቸውን፣ ሰብአዊነታቸውን እና ሀገራዊ ሀብታቸውን ነው። ስለሆነም ዛሬም ቆም ብለን ብናስብ፡፡ ለሕይወት እና ለአብሮነት መስጠት ያለብን ዋጋ ብንሰጥ በየቀኑ የሚሞተውን ህይወት መታደግ እንችላለን፡፡ ቮነጉት በድረስቱ እንዳለው  ሰው በምድር ላይ የሚቆየው እጅግ ለአጭር ጊዜ ነው። ይህችን አጭር ዕድሜ በጎጥ፣ በዘር እና በጥላቻ ከማጥፋት ይልቅ እርስ በእርስ በመተሳሰብ፤ ተፈጥሮን በመውደደ ና በመዋደድ የተሰጠንን የሕይወት ስጦታ በምስጋና ማሳለፍ እንዳለብን ይነግረናል፡፡ ቮነጉት በ"ካትስ ክሬድል" ስራው ላይ  እንዲህ እያለ ይቃትታል "እግዚአብሔርም ብቸኛ ሆኖ ተሰማው። እግዚአብሔር ጭቃ ፈጠረ። ስለዚህ ለአንዳንድ ጭቃዎች እንዲህ አላቸው፦ "ተነስታችሁ ተቀመጡ!" እግዚአብሔርም "የፈጠርኳቸውን ሁሉ ተመልከቱ፤ ኮረብታዎቹን፣ ባሕሩን፣ ሰማዩን፣ ከዋክብቱን" አለ። እኔም ተነሥቼ እንድዞር እና እንድመለከት ከተደረጉት ጭቃዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። ዕድለኛ ነኝ፡፡ ዕድለኛ ጭቃ! እኔ ጭቃው ተነሥቼ ተቀመጥኩ፡፡ እግዚአብሔርም ምንኛ ድንቅ ሥራ እንደሠራ ተመለከትኩ። በጣም አሪፍ ሥራ ነው እግዚአብሔር! ከአንተ በቀር ማንም ይህንን ሊያደርገው አይችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሆይ! እኔማ ከቶውንም አልችለውም ነበር። ከአንተ አንጻር ስታይ እኔ ከቶውንም ዋጋ የሌለኝ ሆኖ ይሰማኛል። እኔ ትንሽ መሆኔን ረሳሁ ብዬ የምፅናናበት ብቸኛ መንገድ ተነሥተው እንዲቀመጡ እና ዓለምን እንዲመለከቱ ዕድል ያልገጠማቸውን ያን ሁሉ ጭቃ ሳስብ ብቻ ነው። እኔ ብዙ አገኘሁ፡፡ አብዛኛው ጭቃ ግን ይህ እድል አልሆነለትም። ለዚህ ታላቅ ክብርም አመሰግናለሁ! አሁን ጭቃው እንደገና  ይተኛል። ጭቃው ሊኖሩት የሚችሉ ምን ያህል አስደናቂ ትዝታዎች ናቸው! የገጠሙኝ ሌሎች አስደናቂ ተነስተው የተቀመጡ ጭቃዎች (ሰዎች) ምንኛ ድንቅ ነበሩ! ያየሁትን ሁሉ ወደድኩት!" ይለናል፡፡ በየቀኑ የሰውን ልጅ የሞት ዜና መስማት ያማል ፡፡ በጋራ ለመዳን በጋራ መቆም አለብን፡፡ለየብቻው እና በየተራ የሚያለቅስ ህዝብ አይሻገርም!! ፀሀፊ - ዮናስ ዘውዴ @zephilosophy

Open in Telegram
Views10,200+46%vs avg
Forwards—
Reactions67
Comments—
#1335Text

ካድሬነት የሚገርም ነገር ነው። (በዋናነት ስለካድሬዎች አይደለም) ካድሬነት ሦስት ነገር ይፈልጋል። ፐብሊኩን መዋሸት፣ ራስን መዋሸት ወይም ለልክነት ግድ ማጣት። የመጀመሪያው የመንግስት አገልጋይ ካድሬ፣ ፐብሊኩን መዋሸት የሥራው አካል አድርጎ የሚቀበል ነው። በግል ቢያወሩት ያው "ለመኖር ብዬ" የሚል አይነት ነው። ፐርፎርመር ናቸው። የሚሉትን ባያምኑም፣ ያላመኑበትን ለማሳመን የሚጥሩ ተቀጣሪ ደላሎች ናቸው። "ሸቀል ሸቀል አድርጊ ልምጣ" የሚሉ አይነት ናቸው። የሚሰሩትን ያውቃሉ። ሁለተኞቹ፣ ህሊናቸውን ለመከላከል ወይ የመንግስታቸውን አቋም ስለሚያምኑበት ራሳቸውን እየዋሹ የሚዘልቁ ናቸው። በየትኛውም አውድ ውስጥ ልክ ነን ብለው የሚከራከሩ ናቸው። የሚሰሩትን አያውቁምና... የሚባልላቸው አይነት ናቸው። ትኩረቴ ግን ሶስተኞቹ ናቸው። ሦስተኞቹ ልክ ሆኑ ልክ አልሆኑ አያሳስበቸውም። ካድሬነትን የሚቀርቡት መካኒካል ከሆነ የሥራ አንግል ነው። "ለምን እንዲህ አይነት ነገር ታደርጋላችሁ? ወይ ትላላችሁ?" የሚል የሞራል ጥያቄ አይጥማቸውም። ስለሰው ባህሪ ብዙ የሚገልጡት አላቸው። የፍራንዝ ካፍካ The trial ላይ K የተባለውን ገፀ ባህሪ በቁጥጥር ስር ውለሃል ብለው ቤቱ የመጡት ሰዎች እኚህ አይነቶቹ ናቸው። ለK እንዲህ ይሉታል፣ "እኛ ይታሰር ስለተባልክበት ኬዝ ምን አናውቅም። ... ግን እርግጠኞች ነን። የምናገለግላቸው ባለስልጣናት እንዲህ አይነት እስር ከማዘዛቸው በፊት ለምን እስሩ እንደሚገባህ በቂ መረጃ እንዳላቸው። ያ ጥርጥር የሌለው ጉዳይ ነው።" "I am just doing what I am told" የሚሉ አይነት ናቸው። የEichman አይነት ሰዎች ናቸው። ብዙ ጥፋት እያጠፉ እኔ የታዘዝኩትን ከመስራት ውጪ ምንም አላደረኩም የሚሉ ናቸው። በሚልግራም ኤክስፐርመንት ውስጥ ያሉ፣ ሰዎችን በኤሌክትሪክ ሾክ እያደረጉ ምንም የማይመስላቸው ሰዎች ናቸው። ፓርቲው ያውቃል የሚሉ። እኔ ጉዳይ አስፈፃሚ ብቻ ነኝ ብለው የሚያምኑ። በሰራችሁት ስራ ጥፋት ተከሰተ ሲሏቸው የሚገረሙ፣ ህሊናቸውን outsource ያደረጉ ሰዎች ናቸው። አይጠይቁም። መጠየቅም(ጠብቆ) አይወዱም። ከነሱ የተሻለ በፀጋዬ ተውኔት ውስጥ የዳምባል ገራፊ የተሻለ ኮንቪክሽን አለው። "እኔ በተረት ጅራፍ የተገረፍኩ ነኝ..." ብሎ የራሱን ፖለቲካል ፖዚሽን ይረዳል። እነዚህ ግን የጭካኔ መካኒክስ ሀገር ላይ ሲወድቅ ኦፕሬተሮች ናቸው። ድርጊታቸውን ብሎን እንደመፍታት፣ ግድያን ዝገት እንደማፅዳት ነው የሚያዩት። በደርግ ሰዓት ወጣቶች ተገድለው በአንድ ጉድጋድ ሲቀበሩ፣ እጃቸው ላይ ያለ ሰዓት ፈትተው ከጉድጓፍ አስጨምረዋቸዋል። ኢህአፓ ውስጥ ሆነው ግደሉ የተባሉትን ገድለዋል። ድርጅቱ አይሳሳትም ብለው ብዙ ስህተት ቅም ሳይላቸው ፈፅመዋል። ዛሬ ድረስ ልክ ነበርን ብለው ይከራከራሉ። ዛሬ ወጣቶችን የሚያፍሱ፣ ተጠርጥረዋል የተባሉትን የሚገድሉ፣ በክልላቸው ወጣቶች ከተረሸኑ በኋላ "ሰላምና ደህነትን ለማስጠበቅ ከምንሰራቸው ስራዎች መካከል..." ብለው የሚናገሩ፣ ማታ ቤት ሲገቡ ያለምንም መደናቀፍ ከቤተሰባቸው የሚቀላቀሉ፣ ልጆቻቸውን የሚያቅፉ "ኖርማል" ሰዎች ናቸው። የሚሰሩት ስለሚሰራው ነገር(ስለሚያመጣው ውጤት ግድ የላቸውም)። ዋናው ነገር ሥራው መሰራቱ ነው። እኚህ ሰዎች ካድሬዎች ብቻ አይደሉም። ጥበቃ ሆነው የትልልቅ መስራያ ቤቶች በር ላይ አሉ። ፖሊስ ሆነው ጓዳናዎች ላይ ይገኛሉ። የቢሮ ኃላፊ፣ ዲን፣ ዳይሬክተር ሆነው ይመጣሉ። ማታ ሰው አስገድለው ጠዋት ቤተክርስትያን ይስማሉ። ጠዋት ልጃቸውን ትምህርት ቤት አድርሰው ከሰዓት የሌላ ሰው ልጅ አጥንት ይሰብራሉ። Hana Arent Eichmannን አይታ Banality of violence የሚል ሃሳቧን ያመጣችው ይሄን ባህሪ ታዝባ ነው። Eichmann ብዙ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ከሆነ በኋላ ፍርድ ላይ ሲቀርብ፣ "እኔ ሥራዬን ከመስራት ውጪ ምንም ያደርኩት ነገር የለም" ነው ያለው። እኚህ ሰዎች ካድሬዎች ብቻ ባይሆኑም፣ ካድሬነት ይሄንን ባህሪ አብዝቶ የሚሸልም የስራ መስክ ነው። ትሁት ሁሉ ሊመስሉ ይችላሉ። "እኔ እኮ ባግዝሽ ደስ ይለኛል፣ አሰራሩ ሆኖብኝ ነው" በሚል የቢሮክራሲ ተገን ሚስጥራዊ የጭካኔ ደስታ የሚያፈልቁ ለስላሳ አንባገነኖች ናቸው። ደንቡ ጣኦታቸው፣ አዋጁ አምላካቸው ነው። ሥርዓቱ ይወዳቸዋል። የተባሉትን ከመፈፀም ውጭ ጥያቄ አያበዙም። ለአሰራሩ ታማኝ ናቸው። "ደንቡ እና አሰራሩ" ሲሉ፣ ከአሰራሩ ተከራከር እኔን አትጨቅጭቀኝ ማለታቸው ይመስላል። ቀላል የምትመስል ጥፋት ከራሳቸው የምታባርር detachment መፍጠሪያ ቃል ናት። አስፈሪነታቸው እዚህ ላይ ነው። መንግስታዊ በደል ለዚህ ሁሉ ጊዜ እንዴት ቀጠለ ብለው ሲጠይቁ የሚያገኟቸው መልሶች ናቸው። They are the footsoldiers of state violence. The ontology of dictatorship ምንድነው ስንል የምናገኛቸው ፍቺዎች ናቸው። ሰዎች ድንገት ጎዳና ላይ ተገደሉ የሚል ዜና ስሰማ፣ ታፍሰው ተሰወሩ ሲባል፣ በአቃቂ ሁኔታ ተደብድቡ ዜና ሲሆን ከዜናው አሰቃቂነት ጋር ፈፃሚዎቹን/አስፈፃሚዎቹን አስባለሁ። ዜናው በወጣ ጠዋት የሚያዘወትሩበት ቤት ቁርሳቸውን እየበሉ፣ ቡና እየጠጡ ከሰው እየተጨዋውቱ ይሆናል። "እንዴት ተኝተው ያድራሉ?" የሚል ጥያቄ አይመጣልኝ። The chilling side of it is they might have a better sleep pattern than most of us. "We are creatures of consequences" የሚል አባባል አለ። እዚህ ጥግ ላይ ያ የለም። They do and they don't care about the consequence. Anything that happens has got nothing to do with them but the system in place. ከሆነ ጊዜ በፊት የሆኑ ፖሊሶች የያዟቸውን ሰዎች በዱላ ሲደበድቡ፣ ያለርህራሄ ሲረግጡ የሚያሳይ ቪድዮ ሶሻል ሚዲያ ላይ ወጣ። አንድ ወዳጄ አንዴ እንዲህ አለ፣ "እኔን የሚገርመኝ ከነዚህ ጋር አንድ እድር ያለው፣ አንድ ማህበር የሚሳተፈው ነው። ሕዝቡ ማግለል አለበት"። ታሪክና የእለት ኑሯችንን ላየ፣ ሕዝቡ መሃል እንዲህ አይነት መገለል ይደርስባቸዋል ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት ይመስለኛል። እርግጥ ነው እኚህ ሰዎች ጎረቤቶቻሽን ናቸው። የእድራችን አባል፣ የእቁባችን ተሳታፊ ናቸው። ግን በጭካኔ የምንደነግጠውን ያህል፣ የጨካኞችን ቦታ አንገመግምም። እኔን ጥያቄ የሚሆንብኝ ጥፋቱ የማይታየውን ሰው ምን ያደርጉታል የሚለው ነው እና በጥፋት የሚደነግጥ ግን ጥፋተኞችን የሚያቅፍ ሕዝብስ እራሱን ከጥፋት እንዴት ያድናል የሚሉት ናቸው። ፀሀፊ-አገኘሁ አሰግድ @zephilosophy

Open in Telegram
Views11,800+68%vs avg
Forwards—
Reactions93
Comments—
#1334Photo

ታሪክ የምስክር ወረቀት ሳይሆን የደም መጽሐፍ ነው፡፡ ዛሬ  መሬት ሲጨንቃት፣ ሰማይ ሲያለቅስ እና የደም ወንዝ ሲፈስ ማህበረሰባችን  ለምን ዝምታን ይመርጣል? ዝምታ ገለልተኝነት ሳይሆን የግድያ ቀጥተኛ ተባባሪነት እና የሞራል ውድቀት ማሳያ ነው። የቀድሞ አባቶቻችን በግፍ ጊዜ “በቃ!” ይሉ  ነበር፡፡ ዛሬ ግን የታሪክን ክብር ረስተን የደም አበቦችን በዝምታ እያረገፍን እንገኛለን። ነገ ልጆቻችን “አባቶቻችን ለምን ዝም አላችሁ?” ብለው እንዳይጠይቁን ይህንን አሳፋሪ የጥፋት አሻራ ዛሬውኑ እንቃወመው። የሰው ልጅ በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረ የተቀደሰ መቅደስ ነው፡፡ የአቤል ደም ወደ ሰማይ እንደሚጮኸው ሁሉ ንጹህ ህይወት ሲጠፋ ዝም ማለት የሰውን ሰብአዊነት መካድ ነው፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ በደል ነው። ታላቁ ፈላስፋ ኤድመንድ በርክ እንዳለው “ለክፉዎች ድል አድራጊነት ብቸኛው ቅድመ ሁኔታ ጥሩ ሰዎች ዝም ማለት ብቻ ነው”፡፡ ዛሬ ዝምታችን የሞራል ቆዳችንን እያረገፈው፣ ሰብአዊነታችንን በህይወት እንዳለ እየቀበረው ይገኛል። ፖለቲካዊ ፍርሃት ሰፍኖ፣ የፍትህ ሚዛን ተዛብቶ፣ ዜጎች እንደ ቅጠል ሲረግፉ ዝም ማለት የባሪያ አስተሳሰብ እና የገዳዮች አጋር መሆን ነው። የንጹሃን ደም እንደ ጎርፍ መሬቱን አርሶታል፡፡ ሬሳዎች ያለ መቃብር ተበትነዋል፤ እናቶች በለቅሶ ድምፅ ሰማይን እየሰነጠቁ ነው። ዝምታችን አጥንታችንን የሚበላ የነበልባል እሳት ሆኗል። ዛሬ ዐይኖቻችንን ገልጠን፣ ጡንቻዎቻችንን አበርትተን፣ እንደ አንድ ሕዝብ በአንድ ድምፅ መጮህ ያስፈልጋል፡፡ የሰው ሕይወት ዋጋ አለው! በግፍ መገደል ይብቃ! ዛሬ ዝምታችንን ሰብረን ለፍትህ እንቁም!! በቃ አትግደሉን እንበል !! በየተራና ለብቻው የሚያለቅስ ህዝብ አይድንም!! ዮናስ ዘውዴ @zephilosophy

Open in Telegram
Views11,800+68%vs avg
Forwards—
Reactions129
Comments—

All posts

Connections