ካፍካ እንዲህ ይላል፦«You are free, and that is why you are lost» አዎን የሰው ልጅ የሚጠፋው ነፃነት ስለሌለው ሳይሆን ነፃነቱን በሌሎች ባርነት ውስጥ ስለሚጥለው ነው። እንደ ወፍ ክንፍ ተሰጥቶት በሰዎች ጣት ላይ እድሜ ዘመኑን ተቀምጦ የሚኖር ሰው አለ። ሊበር እየቻለ ግን ሰማይን ማየት ይፈራል። ሞትን አይቶ ቢመለስ ግን ክንፍ እንዳለው ያስታውሳል።
ሞተን ስንመለስ የሕይወትን ጣዕም በደንብ እናውቃለን። ከጣፋጭ እስከሚያቃጥል የሚበላውን ምግብ በጠቅላላ እናጣጥማለን፤ እያንዳንዱ ጉርሻ በለሆሳስ የታጀበ ማኘክ ነው። ምክንያቱም አንድ ቀን አጠገባችን በተቀመጠው ሳህን ላይ ያለውን ምግብ መልሰን እንደማናገኘው እናውቃለን። ሻወር ስንወስድ በገላችን ላይ የሚፈሰውን እያንዳንዱን ውሃ እናስተውላለን፤ የውሃው ነጠብጣብ በቆዳችን ላይ ሲገባ ይሰማናል። ያንን ቅጽበት እንደ ተራ ነገር አናልፈውም። ምክንያቱም አንድ ቀን ከውሃ ጋር እስከወዲያኛው እንደማንገናኝ ጠንቅቀን ተረድተናል፤ ንፋሱ ፊታችንን ሲነካው፣ ፀሐይዋ በቆዳችን ሰርጉዳ ስትገባና፣ በሲኒ ያለውን ቡና ስንጎነጭ በሙሉዓት ተሰጥተን ማጣጣም እንጀምራለን። ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ስንነጋገር ቃላታቸው ብቻ ሳይሆን የድምፃቸውን ቃና ጭምር እናስተውላለን።
ሕይወት በታላላቅ ክስተቶች የተከበበች አይደለችም፤ ይልቅስ ሕይወት በዚች ትንሽዬ የውሃ ጠብታ ውስጥ ተቀምጣለች። በምግብ መዓዛ ውስጥ፣ በምንወዳቸው ሰዎች ጠረን ውስጥ፣ በመስኮት በምታጮልቀው ፀዐይ ውስጥ ደግሞም በሌሊት ፀጥታ ውስጥ ህይወት ደግማ ደጋግማ ትንቀሳቀሳለች።
ሞትን ያላየነው እኛ ግን እነዚህን ሁሉ በረከቶች ችላ ብለን በሌላ ትኩረት ተወስደናል። ስለነገ እናስባለን፣ ለሰዎች እንኖራለን፣ ለገንዘብ እንለፋለን፣ ለስም እንጨነቃለን በዚህ ምክንያት ዛሬያችንን ተነጥቀን እንቀራለን። ዛሬ ማለት አሁን ነው አሁንም በውሃ ጠብታ መካከል የምትፈስ ህይወት ነች።
ዶስቶይቭስኪ በ«The Brothers Karamazov» ውስጥ እንዲህ ይላል፦«The mystery of human existence lies not in just staying alive, but in finding something to live for» ይህ ንግግሩ በቂ ትምህርት ታቅፏል። የምንኖርለት ነገር ሁልጊዜ በታላቅ እቅዶች የተከበበ ውጣ ውረድ አይደለም። አንዳንድ ቀን ለመጻፍ፣ አንዳንድ ቀን ለመውደድ፣ አንዳንድ ቀን ለመሳቅ፣ አንዳንድ ቀን በጸጥታ ለመቀመጥ፣ በሌላ ግዜ ደግሞ ለራሳችን በመኖር ውስጥ ማለፍ ትልቅ ትርፍ ነው። በርግጥ ይህ ራስ ወዳድነት አይደለም። ይህ ለራስህ ያለ ክብር ነው። ማንም ለእራሱ ሳይኖር ለሌሎች የሚሰጠው ፍቅር በመጨረሻ ባዶ ኪሳራ ነው የሚያስታቅፈው። የራሱ እሳት የጠፋበት ለሌላ ሰው ብርሃም መሆን አይቻለውም!።
ኒቼ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦«He who has a why to live can bear almost any how» መንገዱን የተገነዘበ ሰው መሬት ላይ የተዘረጋውን እሾህ ተመልክቶ ወደኋላ አይቀርም፤ ይልቅስ መድረሻውን እያሰበ ይራመዳል። አዎን ሞት የሚያስተምረንም ይህን ብቻ ነው። የሚያልቅ ነገር ላይ የሚኖር እስከሚያልቅ ያጣጥማታል። እያንዳንዷን ደቂቃ በከንቱ ሳያሳልፍ በለሆሳስ ይገፋታል።
ዛሬ ለመጨረሻ ግዜ ምግብ የሚባለውን ነገር የምንበላ ቢሆን የቀረበላችሁን ምግብ እንዴት ነበር የምታጣጥሙት?፤ በፍጥነት አትውጡትም ይልቅስ ቀስ ብላችሁ ትቀምሱታላችሁ፤ ጣዕሙን በምላሳችሁ ላይ መረቁን እያመነጨ በጉሮሯችሁ በኩል ያልፋል።
ዛሬ ለአንዴና ለመጨረሸ ግዜ ነው ውሃ የሚኖረው ከነገ በኋላ ይጠፋል ቢባል ሻወር እንዴት ነበር የምትወስዱት?፤ የውሃው አንኳር ነጠብጣብ በገላችሁ ላይ ሲፈስ ምን ያህል ይሰማችሁ ነበር?። ዛሬ የመጨረሻው ፀሐይ የምትወጣበት ቀን ነው ብትባሉ ሰማዩን በችኮላ እንዴት እንደምታዩት አሰብኩት።
ዛሬ የምትወዱትን ሰው ድምፅ ለመጨረሻ ግዜ ነው የምትሰሙት ብትባሉ እያንዳንዷን ቃላት እንደ ዝናብ ነጠብጣብ በእናንተ ላይ እንዲወርድ በፈቀዳችሁ ነበር። አዎን ያኔ ነው የምንገነዘበው፤ ሕይወት የምንጠብቃት አንድ ሽልማት አይደለችም። ሕይወት እዚህ ነች ዛሬን ብሎም አሁናችንን ኖሮ ማለፍ። ስለዚህ ሞትን ማወቅ ማለት ሞትን መፈለግ አይደለም። ሞት እንደሚመጣ ማወቅ ሕይወት እንዳለን በመጨረሻ ማስታወስ መቻል ነው።
ያንን ከተረዳን በኋላ ለማንም ምንም ለማሳየት አንጋጋጥም። ይልቅ ዛሬን እንኖራለን፣ ምግባችንን እናጣጥማለን፣ ውሃው በገላችን ላይ ሲፈስ ይሰማናል፣ ፀሐይዋን በከፍተኛ ፍላጎት እንሞቃታለን፣ ንፋሱን በፊታችን ላይ እንዲርመሰመስ እንፈቅዳለን፣ የምንወደውን እንወዳለን የማይወደንንን እንለቃለን። እና ለመጀመሪያ ጊዜ ለራሳችን ብቻ የሚበቃ ሕይወት እንኖራለን። ምክንያቱም አንድ ቀን ይህ ሁሉ ነገር ለዘላለም ይጠፋል። እኛ ግን አሁን ላይ አለን። እዚሁ እንደተቀመጥን፤ ብቻችንን ሆነን ከእነዚህ ተፈጥሮዎች ጋር የሕይወት ምስጢርን በምንወደው በረከት ውስጥ እያጣጣምን። ጸጥ..We are all going to die. And I drink to that because we are still alive. Here’s to life🥂
@Armemo_offical