ለቸኮለ! ቅዳሜ፤ ኅዳር 19፣ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የ45 ቀናት ሪፖርቱን ዛሬ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አቀረበ። ዐቢይ፤ ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር የክትትል ግምገማ ውይይት ማድረጋቸውን ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። በውይይቱ፤ አስተዳደሪ ያሳያቸው ርምጃዎች፣ ተግዳሮቶች እና የጋራ የቅድሚያ ጉዳዮች እንደተገመገሙ ዐቢይ ገልጸዋል። የባለአደራ አስተዳደሩ ሥራ አስፈጻሚዎች፤ ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸውን ዋዜማ ከምንጮች መስማቷን ጠቅሳ ትናንት መዘገቧ ይታወሳል። 2፤ አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ሲቪሎችን መርጦ ያስታጥቃል በማለት ተቸ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት በቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን ሲቪሎችን ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ መሳሪያ ማስታጠቁን ሐሙስ'ለት መናገራቸውን የጠቀሠው ቡድኑ፤ ይህ አካሄድ በክልሉ ማኅበረሰቦች መካከል ውጥረቶችና ልዩነቶች እንዲባባሱ ያደርጋል በማለት ወቅሷል። ቡድኑ፤ ግለሰቦች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በራሳቸው መሳሪያ መታጠቃቸው፣ ለጸረ-ሽምቅ ዓላማ መንግሥት-መር ከሆነ የማስታጠቅ ድርጊት ተለይቶ መታየት እንዳለበት አሳስቧል። የታጠቁ ሲቪሎች በመንግሥት የጸረ-ሽምቅ ዘመቻ ውስጥ የሚሳተፉበት ሁኔታ እንዳለ የጠቆመው ቡድኑ፤ ይህ ሁኔታ እነዚህን አካላት ለአደጋ አጋልጧቸዋል ብሏል። 3፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ ዋና ሳጅን አለኹበል እሱነህ በድንገተኛ ጥቃት ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ተገደሉ። ዋና ሳጅን አለኹበል የተገደሉት "ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች" መኾኑን የወረዳው አሥተዳደር የገለጠ ሲኾን፤ የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ግድያውን የፈጸመው "ጽንፈኛው ቡድን" ነው ብሏል። በዋና ሳጅኑ ላይ ጥቃት የተፈጸመው፤ ከዱርቤቴ ከተማ መውጫ አካባቢ በትራፊክ ቁጥጥርና ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ ሳሉ ነው ተብሏል። የወረዳው አስተዳደር፤ ሟቹ በዞንና በወረዳ መዋቅሮች ለ21 ዓመታት በፖሊስ ሙያ ማገልገላቸውን ጠቅሷል። 4፤ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፤ በሶማሊያ በተሠማራው የኅብረቱ ተልዕኮ ዙሪያ ከቀረበለት ባለ ሦስት ምዕራፍ የተቀናጀ የጸጥታ ሽግግር እቅድ ውስጥ እስከ ቀጣዩ ዓመት ታኅሳስ የሚዘልቁትን ሁለቱን ምዕራፎች አጸደቀ። በገንዘብ እጥረትና ባልተቀናጀ አኳኋን የተልዕኮውን ወታደሮች ከአገሪቱ ማስወጣት የጸጥታ ክፍተት ሊፈጥርና አልሸባብ መልሶ ከተሞችን እንዲቆጣጠር እድል ሊሠጠው እንደሚችል ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ ያስጠነቀቀው ምክር ቤቱ፤ የኅብረቱ ኮሚሽን በአገሪቱ ጸጥታ ላይ ጥልቅ ግምገማ አድርጎ እስከ መስከረም 2020 ሪፖርት እንዲያደርግ ምክር ቤቱ ጠይቋል። ዓለማቀፍ አጋሮች ለተልዕኮው የገንዘብና ሎጅስቲክ ድጋፍ ማድረግ እንዲቀጥሉም ምክር ቤቱ ጥሪ አድርጓል። 5፤ የአውሮፓ ፓርላማ፤ የኤርትራ መንግሥት ስዊድናዊ ዜግነት ያለውን ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ ለበርካታ አስርት ዓመታት እስር ላይ የሚገኙ ሁሉንም "የኅሊና እስረኞች" እንዲፈታ ጠየቀ። የዳዊት ሕይወትና ደኅንነት በጥልቅ እንደሚያሳስበው የገለጠው ፓርላማው፤ ጋዜጠኛው በአስቸኳይ ተፈትቶ ወደ ስዊድን እንዲመለስና እስከዚያው በሕይወት ስለመኖሩና ስለታሠረበት ቦታ መንግሥት ማረጋገጫ እንዲያቀርብ፣ ከጠበቃ ጋር እንዲገናኝ እንዲፈቅድና ግርፋት ደርሶበታል በሚሉ ሪፖርቶች ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። ፓርላማው፤ የአውሮፓ ኅብረት ካውንስል በሰብዓዊ መብት ጥሠት ተጠያቂ በሆኑ የኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የተመረጡ ማዕቀቦችን ለመጣል እንዲያጤን ጠይቋል። እንዲሁም፤ 1፤ የአዲስ የሥነ-ጽሑፍ ፌስቲቫል 2026 በመጪው ሳምንት ይካሄዳል። ዓለማቀፍ የሥነጽሑፍ ባለሞያዎች የሚሳተፉበትና "ድንበር የለሽ ገጾች፤ የሚያስተሳስሩን ታሪኮች" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚህ የሦስት ቀናት ፌስቲቫል ላይ፣ ሀሳብ አመንጪ ውይይቶች፣ የሥነ-ጽሑፍ ዳሠሣዎች፣ የግጥም ምሽቶች፣ የሥልጠና ዐውደ ጥናቶችና ሌሎችም ዝግጅቶች ይቀርባሉ። ፌስቲቫሉ ከመጪው ሐሙስ ኅዳር 24 እስከ ቅዳሜ ኅዳር 26 ቀን ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ይካሄዳል። 2፤ የሠዓሊ ጋሻሁን ካሣሁን "የቆዳ ስፋት" የተሠኘ የግል የሥዕል ዐውድ ርዕይ በመጪው ማክሰኞ ኅዳር 22 ቀን ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በገብረክርስቶስ ዘመናዊ የሥነጥበብ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።[ዋዜማ]
Open in Telegram
Wazema Media / Radio
Wazema is Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Average views per post by day
By publication day
Show as table
| Date | Avg views per post |
|---|---|
| Nov 6, 2026 | 23,700 |
| Nov 7, 2026 | 24,200 |
| Nov 9, 2026 | 21,200 |
| Nov 10, 2026 | 20,900 |
| Nov 11, 2026 | 17,000 |
| Nov 12, 2026 | 19,400 |
| Nov 13, 2026 | 20,500 |
| Nov 14, 2026 | 21,500 |
| Nov 16, 2026 | 16,700 |
| Nov 17, 2026 | 16,000 |
| Nov 18, 2026 | 16,000 |
| Nov 19, 2026 | 15,100 |
| Nov 20, 2026 | 16,400 |
| Nov 21, 2026 | 16,200 |
| Nov 23, 2026 | 14,400 |
| Nov 24, 2026 | 12,700 |
| Nov 26, 2026 | 9,025 |
| Nov 27, 2026 | 7,890 |
| Nov 28, 2026 | 3,680 |
Most viewed this month
- 01Views24.2KForwards—Reactions70Comments—
- 02Views23.7KForwards—Reactions113Comments—
- 03Views21.5KForwards—Reactions74Comments—
- 04Views21.2KForwards—Reactions83Comments—
Latest posts
ለቸኮለ! ዓርብ፤ ኅዳር 18፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አመራሮች ነገ ቅዳሜ የአንድ ወር አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለማቅረብ አዲስ አበባ እንደተጠሩ ዋዜማ ሠምታለች። ዐቢይ፤ ጌታቸው ረዳ፣ አብርሃም በላይ እና ሬድዋን ሁሴን ባለአደራ አስተዳደሩን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ መመደባቸውን፣ ሬድዋን የተቆጣጣሪ ቡድኑ ሰብሳቢ መሆናቸውንና ቡድኑ በየሳምንቱ የአስተዳደሩን አፈጻጸም እንደሚገመግም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ነግረውናል። በሌላ በኩል፤ የባለአደራ አስተዳደሩ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፤ በጦርነቱ የወደሙ የክልሉን የመንግሥት ሠራተኞች ሠነዶች መልሶ ለማደራጀት፣ የትምህርት ማስረጃዎችን ለማረጋገጥና በክልሉ የፌደራል ሲቪል ሠርቪስ ማሻሻያ አቅጫጣዎችን ለማስፈጸም እስከ ኅዳር 30 እንደ አዲስ የሠነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡለት ጠይቋል። 2፤ በትግራይ ክልል ሠሜን ምዕራብ ዞን ገጠራማ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በሕወሃት፣ የፋኖ ታጣቂዎችና የኤርትራ ሠራዊት በሌላ በኩል የሚካሄዱ ውጊያዎች መቀጠላቸውን የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለዋዜማ ገለጡ። አህስኣ፣ ዝባን ጉላ እና ዓዲ ፍታው በተባሉ ገጠራማ አካባቢዎች፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል። የትግራይ ሠላም ኃይል፤ ሠምበል እና ገማህሎ የተባሉ የድንበር አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች ሥር መግባታቸውን ገልጧል፡፡ 3፤ የትግራይ ሰላም ኃይል ትጥቅ የመፍቻ ጊዜ ማራዘምንና የጦር መሳሪያዎች ርክክብን የሚመለከቱ መመሪያዎችን ማስተላለፉን ዋዜማ ተመልክታለች፡፡ ቡድኑ፤ ከኅዳር 22 እስከ ኅዳር 24 ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የሚገቡ የሠላም ኃይሉን አባላት ከፋፍሎ ዘርዝሯል። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸውና ሥማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የባለአደራ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር፤ የቡድኑ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ከፈቱ በኋላ ሥልጠና ወስደው እንደየፍላጎታቸው ወደ ክልሉ ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት እንደሚቀላቀሉ ነግረውናል፡፡ ወደ ቀድሞ ሥራቸው የሚመለሱ ታጣቂዎችና አመራሮች እንደሚኖሩም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡ በተያያዘ፤ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የሠላምና ጸጥታ ቢሮ የሚሊሻዎች ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ለጊዜው እንዲቋረጥ አዝዟል። ቢሮው፤ የሚሊሻ አባላትን የጦር መሣሪያ የማስመለስ እንቅስቃሴ እንዲቆም የሚያዝ ደብዳቤ ለሁሉም ዞኖች የሚሊሻ ጽሕፈት ቤቶች ልኳል። የትግራይ የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት በአዋጅና በደንብ የተቋቋመ ራሱን የቻለ ተቋም መሆኑን ያስታወሰው ደብዳቤው፤ ቀደም ሲል በጦርነትና ጦርነቱን ተከትለው በመጡ ለውጦች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የታዩ ክፍተቶች በተቋሙ ደንብና አሠራር መሠረት ብቻ እንዲታረሙ አዟል። ከሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ደንብና አሠራር ውጭ በተለያዩ የጸጥታ ኃይል አባላት የሚሊሻዎች ትጥቅ እየተፈታና እየተወሠደ መሆኑን መረጃ እንደደረሠው ቢሮው የገለጠ ሲሆን፤ ከኅዳር 17 ጀምሮ ያላግባብ የተወሠዱ ትጥቆች ተጣርተው ለባለቤቶቻቸው እንዲመለሱም አሳስቧል። 4፤ ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተቀሠቀሠው ግጭት አለመርገቡን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናገሩ። በየእለቱ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ፣ የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንደሚገደብ እንዲሁም ግድያ እና እገታ መበራከቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በታጣቂዎች መካከል በሚፈጠር ግጭት የተኩስ ልውውጦች መኖራቸውንም ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ ረቡዕ'ለት የቋራ ወረዳ ሁለት መምህራን በታጣቂዎች መገደላቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር፤ ገዛኸኝ ታከለ እና አይጠገብ መለሠ የተባሉ ሁለት መምህራን በአደጋ ሕይወ ማለፉን ቢገልጽም፤ የሞታቸውን መንስኤ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ 5፤ በሞያሌው ግጭት ከሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን ሞያሌ እና ሁደት ወረዳዎች ብቻ ከ207 ሺሕ ሕዝብ በላይ እንደተፈናቀለ ዋዜማ ተመድ እና አጋር ድርጅቶች ሰሞኑን በክልሉ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጣቸውን ዋዜማ ገና ይፋ ካልሆነው የዳሰሳ ጥናት ላይ ተመልክታለች። ከ18 ሺሕ 600 በላይ የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሠደዳቸውን ጥናቱ ያሳያል። በግጭቱ 6 ሺሕ 800 ገደማ የመኖሪያ ቤቶች በ25 ቀበሌዎች ውስጥ እንደወደሙ፣ ከ18 ሺሕ 700 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ እንደሆኑ፣ በሞያሌ ወረዳ ደሞ ሰባት ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሠባቸው ሠነዱ ያሳያል። 37 ትምህርት ቤቶች በሁለቱም ወረዳዎች ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆኑ የሚጠቅሠው ጥናቱ፤ በሞያሌ ወረዳ ብቻ 10 ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ ሆነዋል ይላል። 164 መምህራን ደሞ ከሁለቱም ወረዳዎች ከቀያቸውና ከሚያስተምሩባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለዋል ተብሏል። 6፤ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በትግራይ የፌደራል እና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ከአገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ውይይት አካሄደ። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ የውይይቱ ዓላማ ከባለድርሻ አካላት ምርጫውን ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ሀሳቦችን መሰብሰብ መሆኑን መግለጣቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ሜላትወርቅ፤ በክልሉ በሚካሄደው ምርጫ መወዳደር የሚፈልጉ ፓርቲዎች ለምርጫው እንዲዘጋጁ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ድምጽ ሠጪዎችን ለማስተማር እንዲሠራ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ በመድረኩ ላይ አሳስበዋል ተብሏል። ምርጫ ቦርድ፤ የክልሉ ባለአደራ ለምርጫው በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ ከቦርዱ ጋር ግንኙነት የሚያደርገውን አካል ለይቶ እንዲያሳውቀው ሰሞኑን በደብዳቤ መጠየቁ ይታወሳል። እንዲሁም፤ 1፤ የሠዓሊ አብርሃም ወ/ገብርኤል "የሕይወት መጠበቂያ" የሥዕል ዐውድ ርዕይ የመጨረሻ መርሃግብር ነገ ቅዳሜ በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ይካሄዳል። ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ሠዓሊውን በአካል ማግኘት፣ ሥዕሎቹን መጎብኘት እና የሥዕል ሥራዎቹን መግዛት እንደሚቻል ተገልጿል። 2፣ ታዋቂው የባሕል ሙዚቃ ቡድን ኢትዮ ከለር ከጃፓን ከመጣው ኩራጌ ባንድ ጋር በመተባበር ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ሊያቀርብ ነው። ይኸ ዝግጅት ነገ ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በፈንድቃ የባሕል ማዕከል ይካሄዳል። 3፤ የ"መጠበቅ" መጽሐፍ ደራሲ ፋንታ ገ/ማርያም ነገ ቅዳሜ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከመጽሐፏ አንባቢዎች ጋር የምትገናኝበት የመጽሐፍ ፊርማ መርሃ-ግብር ለገሐር በሚገኘው ጃፋር መጽሐፍት መደብር ይካሄዳል።[ዋዜማ]
Open in TelegramViews growthHide views growth
Views growth
Hours after publication
Show as table
| Hours after publication | Views |
|---|---|
| 0 h | 0 |
| 21 h | 6,650 |
| 28 h | 7,890 |
- After 24 hours6,650
- Total to date7,890
ለቸኮለ፤ ሐሙስ፤ ኅዳር 17፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችን ማስታጠቅ ካላቆመ ኤርትራ ኃላፊነቱን ትወስዳለች በማለት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሠጡት ማብራሪያ አስጠነቀቁ፡፡ ኢትዮጵያ ኤርትራን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት የገለጡት ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ጉዳይ በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት እንደምትሻ ተናግረዋል። ዐቢይ፤ ከሁለት ዓመታት በላይ በተካሄደው የትግራዩ ጦርነት ወቅት የውጭ አገራት የድሮን ባለሞያዎች ትግራይ ውስጥ እንደነበሩም ገልጸዋል። የተወሠኑት የድሮን ባለሙያዎች እንደተያዙም ዐቢይ ጠቅሠዋል። ዐቢይ፤ ተይዘዋል ያላቸውን የድሮን ባለሙያዎች ዜግነት አልጠቀሱም። 2፤ የጸጥታ ተቋማት በፖለቲካ ጉዳይ ከተከፋፈሉ የአገር ሥጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ "የመደመር መሪ ስትራቴጂ ከ2025 እስከ 2050" የተሠኘው የ25 ዓመት የመንግሥት ስትራቴጂ አስጠነቀቀ። ፌዴራል መንግሥቱ ከነሐሴ 2018 ዓ፤ም ጀምሮ ለሚንስትሮች፣ ለምክር ቤት አባላትና ለጋዜጠኞች ሥልጠና እየሠጠበት የሚገኘውና ዋዜማ የተመለተችው የስትራቴጂ ሠነድ፤ ደኅንነት ያለ ሕጋዊነትና የሕዝብ ተቀባይነት በዘላቂነት እንደማይቆም ይጠቅሳል፡፡ እስከ 2030 ዓ፤ም ድረስ ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን የሚያምኑ ዜጎች 60 በመቶ ለማድረስ ስለመታቀዱ አስፍሯል። የውስጥ ግጭቶችን በወታደራዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ መግባባትና በተቋማዊ እርቅ መፍታት እንደሚገባ በሠነዱ ላይ የተጠቀሠ ሲሆን፤ በግጭት የተጎዱ፣ ገጠራማ፣ አርብቶ አደርና ጠረፋማ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ካላገኙ የግጭት አዙሪት እንደማይቆም ያስጠነቅቃል። Detail report - cutt.ly/9yD2on2J 3፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች የያዙትን የ1 ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ መልሶ ለማዋቀር የሚያስችል ይሁንታቸውን ለማግኘት እስከ ታኅሣሥ 2 ቀነ ገደብ አስቀመጠ። ዩሮቦንዱን መልሶ ለማዋቀር የሚያስችል የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ ከቦንዱ 300 ሚሊዮን ዶላር የያዙ ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች ይሁንታ ያስፈልጋል። ባንድ ኮሚቴ የተወከሉ የዩሮቦንዱን 45 በመቶ የያዙ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የቦንድ መልሶ ማዋቀሪያ ሀሳብ ቀደም ሲል መቀበላቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሀሳብ፤ የ1 ቢሊዮን ዶላሩን ዩሮቦንድ እኤአ በሐምሌ 2028 በሚከፈል የ880 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ የሚተካ ሲሆን፤ የቀድሞውን የ6 ነጥብ 62 ዓመታዊ ወልድም ወደ 6 ነጥብ 15 በመቶ ዝቅ የሚያደርግ ነው። 4፤ መንግሥት በርካታ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ጸጥታ ኃይሎችን ዛሬ በሞያሌ ማሠማራቱን ዋዜማ በአካባቢው ከሚገኙ ምንጮቿ ሠምታለች። ጸጥታ ኃይሎቹ፤ የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አስተዳደሮች በቅርቡ የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊነት ይከታተላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ነግረውናል። ይህንኑ ተከትሎ፤ ሞያሌ ላይ ላንድ ወር ቆመው የነበሩ የኬንያ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዛሬ ወደ ኬንያ መንቀሳቀሳቸውን ደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል። ከግጭቱ በፊት ሸቀጦችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩ ከ300 በላይ የኬንያ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሞያሌን አቋርጠው ወደ ኬንያ የገቡት፣ በኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች እጀባ መኾኑን ዘገባው ጠቅሷል። የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ወደ ኬንያ የተንቀሳቀሱት፤ የኬንያ መንግሥት ባለስልጣናት እና የኬንያ የጭነት አሽከርካሪዎች ማኅበር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ነው ተብሏል። መንግሥት ግጭቱን ለማስቆም ጸጥታ ኃይሎቹን በሞያሌ ስለማሠማራቱ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው ነገር የለም። 5፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከቻይናው ቲ ደብሊው ሆልዲንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ውስጥ የመማሪያ መጽሐፍት ማተሚያ ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ተፈራረመ። ፋብሪካው፤ የትምህርት መጽሃፍትን የማተም፣ የመለበድ፣ የመጠረዝና የማሠራጨት ሥራ እንደሚሠራ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፤ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የኅትመት ኢንዱስትሪ ለማጠናከርና የትምህርት ቁሳቁሶችን ጥራት ለማሻሻል፣ ከውጭ ለሚገቡ የመማሪያ መጽሃፍት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እንዲሁም በመማሪያ መጽሃፍት ፍላጎት እና በአገር ውስጥ የማተም አቅም ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለማጥበብ እንደሚረዳ ገልጧል። በስምምነቱ መሠረት፤ የቻይናው ኩባንያ በማተሚያ ቤቱ የ51 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ደሞ የ49 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ተገልጧል። የፋብሪካው የመጀመሪያው ዙር ምዕራፍ 30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል። 6፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ሁለት ሠራተኞች ትላንት ረፋድ ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። በጥቃቱ፤ ፍላቂት ላይ እየተገነባ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት በበላይነት ሲመራ የነበረው አሸናፊ ዑመር እና የፕሮጀክቱ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አሥተዳደር ኃላፊ ዘሪሁን መሐመድ ሕይወታቸው ማለፉን ምንጮች ነግረውናል። ሠራተኞቹ ከሰርኮ ወደ ዳንዴ በር ንብረትነቱ የኮንስትራክሽን ኤጀንሲው በሆነ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው የገለጡት ምንጮች፤ በአካባቢው የሠፈሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በስፍራው ሲደርሱ ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን አስረድተዋል። እንዲሁም፤ 1፤ "ፋውንደርስ ላውንጅ" የተሠኘውና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሠማሩ መሪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት መሠናዶ ዓርብ፣ ኅዳር 18 ቀን በቬንቸር ሀብ ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ይካሄዳል። በዚህኛው ዙር መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ንግዶች በሀገር ውስጥ ያላቸውን አቅም አጠናክረው ወደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ዓለማቀፍ ገበያዎች መግባት በሚችሉባቸው ስልቶች ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል። 2፤ በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ "የዓርብ የጃዝ ምሽት" የሙዚቃ ዝግጅት ነገ ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል። 3፤ የኢትዮጵያ ክላሲክና የጃዝ ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት የቀጥታ ሙዚቃ ዝግጅት ነገ ዓርብ፤ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ ብራስ አካባቢ በሚገኘው ግራንድ ኩዳ ይቀርባል። 4፤ የጭረት ባንድ አባላት በሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል ነገ ዓርብ፤ ከምሽቱ 2 ተኩል ጀምሮ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። [ዋዜማ]
Open in Telegramየ25 አመቱ የብልፅግና መሪ ዕቅድ ምን ይዟል? በዚህ ሠነድ ውስጥ የሀገር ደኅንነት፣ የውስጥ ግጭቶች አፈታት፣ የቀጠናዊ ጦርነት ሥጋቶች፣ የጸጥታና የመከላከያ ተቋማት ገለልተኝነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና ሌሎች መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተካትተዋል፡፡ ሠነዱ የጸጥታ ኃይሎች አካሄድ፣ የጦርነት መንስኤዎችና የሰላማዊ ሽግግር መርሆችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያዎችንም አስፍሯል። ያንብቡት cutt.ly/9yD2on2J
Open in Telegramለቸኮለ፤ ማክሰኞ፤ ኅዳር 15፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ ሁሉም የሱዳን ተፋላሚ ወገኖችና የፖለቲካ ኃይሎች አዲስ አበባ ውስጥ ሁሉን ዓቀፍ ለሆነ ንግግር እንዲቀመጡ ጋበዙ። የንግግሩ ዓላማ፤ ጦርነትን ማቆምና ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችል ሁሉን ዓቀፍ ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚሆን ዐቢይ ዛሬ በጽሁፍ ባቀረቡት ጥሪ ገልጸዋል። ይህ ጥሪ የተለየ የፖለቲካ ዓላማ ወይም ጥቅም ለማሳካት ሳይኾን፤ በአገሪቱ ሰላም እንዲሠፍን ከልብ ከማሰብ የመነጨና ብሄራዊ የአንድነት መንግሥት ለማቋቋም መሠረት የሚጥል እንዲኾን ኢትዮጵያ ካላት ፍላጎት የመነጨ መሆኑን አጽንዖት ሠጥተዋል። ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላም የራሷ ጸጥታና መረጋጋት አካል አድርጋ እንደምታየው ዐቢይ ገልጸዋል። 2፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል በአላማጣ ከተማ ላይ የተኮሷቸው ከባድ መሳሪያዎች የጦር ወንጀልነት ምርመራ ሊደረግባቸው ይገባል አለ። ከመስከረም 16 እስከ 18 በተፈጸሙ አራት የመድፍ ጥቃቶች በከተማዋ 14 ሰዎች እንደተገደሉ ድርጅቱ ጠቅሷል። ድርጅቱ፤ የሕወሓት ኃይሎችም ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው ቦታዎች ወታደራዊ ጦር ሠፈር በማቋቋም ሲቪሎችን ለጥቃት አጋልጠዋል፤ ከከተማዋ ኾነው ከባድ መሳሪያዎችን ተኩሠዋል በማለት ከሷል። መከላከያ ሠራዊትና የትግራይ የሰላም ኃይል በጥቃቶቹ ዙሪያ መረጃ እንዲሠጡ በጥቅምት ወር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ የጠቀሰው ድርጅቱ፤ ሕወሃት ግን ውንጀላውን በማስተባበል ምላሽ ሠጥቷል ብሏል። 3፤ በትግራይ ክልል በደቡብ ትግራይ ዞን በዞን፣ ወረዳዎችና ከተሞች በቅርቡ የተሠጡ ሹመቶች በሙሉ ውድቅ መደረጋቸውን ዋዜማ ሠምታለች። ባለአደራ አስተዳደሩ ሹመቶቹን ያስቀረው፤ ከዞኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች ዛሬ ከአስተዳደሩ አመራሮች ጋር መቀለ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ ነው። ተወካዮቹ፤ የተሿሚዎቹ አመራረጥ ለውጥ ፈላጊዎችን ያገለለ እና "የትውልድ ቦታን" መሠረት ያደረገ ዝንባሌ የታይበት ነው የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል። የባለአደራ አስተዳደሩም፤ ሹመትና ምደባው ከእውቅናው ውጪ እንደተከናወነ እንዳመነና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ቅሬታ እንዳይፈጠር የምደባ ሂደቱ የሚመራበት አዲስ መመሪያ ከነገ ጀምሮ ወደ ዞኖችና ወረዳዎች እንደሚልክ ተረድተናል። 4፤ ብሔራዊ ባንክ፤ አካል ጉዳተኛ የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞች ሀብታቸውን ለማስተዳደር ሞግዚት፣ ተወካይ ወይም ረዳት እንዲያቀርቡ የሚገደዱበትን አሠራር አዲስ ባወጣው ረቂቅ መመሪያ ከለከለ፡፡ ረቂቅ መመሪያው፤ አካል ጉዳተኞች የፋይናንስ አገልግሎቶችን በእኩልነትና ያለ አድልዎ እንዲያገኙ የሚያስችሉ አስገዳጅ ደረጃዎችን ያካተተ ነው። አካል ጉዳተኞች ተደራሽ ባልሆነ የመገናኛ መስመር ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ብቻ "ትብብር የማያደርግ"፣ "ፍቃደኛ ያልኾነ" ወይም "ግዴታውን ያልተወጣ" ተብለው በፋይናንስ ተቋማት እንዳይፈረጁ ረቂቅ መመሪያው ያግዳል። ረቂቅ መመሪያው፤ የአካል ጉዳት ለብድር ብቁ ያለመኾን ወይም የመድኅን ሽፋን ወይም የፋይናንስ አቅም ማረጋገጫ ተደርጎ እንዳይወሠድና በንግድ ሥራ በሚተዳደሩ የአካል ጉዳተኞች ላይ በአካል ጉዳታቸው ምክንያት ተጨማሪ የብቁነት ገደቦች እንዳይጣሉ ይከለክላል፡ ተቋማት፤ ለእያንዳንዱ የመመሪያው ጥሠት 50 ሺሕ ብር ሊቀጡ ይችላሉ ተብሏል። 5፤ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን አስታወቀ። ቦርዱ የክልሉን ባለአደራ አስተዳደር በመወከል በምርጫ ዙሪያ ግንኙነት የሚያደርገውን አካል አስተዳደሩ እንዲያሳውቀው በደብዳቤ ጠይቋል። ለምርጫ ዝግጅት ወደ ክልሉ ቦርዱ የሚልካቸውን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ቦርዱ ለሚያቀርባቸው የተሽከርካሪ፣ የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ጥያቄዎች ባለአደራ አስተዳደሩ ትብብር እንዲያደርግም ቦርዱ ጥያቄ አቅርቧል። ባለአደራ አስተዳደሩ፤ በስድስት ወራት ውስጥ የክልልና ፌዴራል ምርጫዎች እንዲደረጉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ሥልጣን ተሠጥቶታል። 6፤ ብሄራዊ ባንክ ዛሬ ባካሄደው የ140 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የተጫራች ባንኮች ፍላጎት የ20 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አስመዘገበ። ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው ተመሳሳይ መጠን ያለው ጨረታ የተጫራቾች ፍላጎት የ16 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ነበር ያሳየው። ባንኩ በዛሬው ጨረታ አንድን ዶላር በ160 ብር ከ73 ሳንቲም የሸጠ ሲሆን፤ ከቀደመው ጨረታ የብር ዋጋ ከዶላር አንጻር በመጠኑ አሽቆልቁሏል። ለዛሬው ጨረታ የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ 161 ብር 41 ሳንቲም እንዲሁም ዝቅተኛው ዋጋ 155 ብር መሆኑን ባንኩ ጠቅሷል። በጨረታው ከተሳተፉት 32 ባንኮች 28ቱ የውጭ ምንዛሬ አግኝተዋል ተብሏል። እንዲሁም፤ 1፤ "በቀለበቴ" የተሠኘውና በተሻለ ወርቁ ተጽፎ የተዘጋጀ አዲስ ተውኔት በቅርቡ ዕይታ ሊቀርብ ነው። ተውኔቱ የኮሜዲ ዘውግ ያለው ሲኾን፤ በአንጋፋው የአገር ፍቅር ቴዓትር ቤት ለተመልካቾች እንደሚቀርብ ተገለጧል። በተውኔቱ ላይ ከተሳተፉት ተዋንያን መካከል፤ ቅድስት ገ/ሥላሴ፣ ተስፉ ብርሃኔ፣ ለምለም በየነ፣ ሲሳይ አማረ እና ሰላማዊት ካሣዬ ይገኙበታል። 2፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባሕል ማዕከል የተዘጋጀውና ተዋናይ ዓለማየሁ ታደሠ በክብር እንግዳነት የተጋበዘበት ሳምንታዊ ዝግጅት ነገ ረቡዕ ኅዳር 16 ቀን ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው የባሕል ማዕከል ይካሄዳል። መግቢያው በነጻ ነው። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ኅዳር 14፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በሞያሌ ግጭት የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ደርሰዋል ከተባለ ወዲህ በሁለቱ ክልሎች ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ ማታ ማታ መቀጠሉን ሠምተናል። ግጭቱ ያስከተለውን ጉዳት ለማወቅ ተመድና አጋር ድርጅቶች ባካሄዱት የዳሰሳ ጥናት ግጭቱ ከኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ371 ሺሕ ሕዝብ በላይ ከሰባት ወረዳዎች ማፈናቀሉን ዋዜማ ይፋ ካልሆነ የዳሠሳ ጥናቱ ረቂቅ ላይ ተመልክታለች። ከሶማሌ ክልል ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ የሚያሳየውን የዳሰሳ ጥናት ለጊዜው ባናገኝም፣ ግብረ ሰናዩ እስላሚክ ሪሊፍ 329 ሺሕ ነዋሪዎች ከዳዋ ዞን ብቻ ተፈናቅለዋል ሲል ባለፈው ሳምንት መግለጡ ይታወሳል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በደቡብ ኦሮሚያ ብቻ 130 ሰዎች እንደሞቱና 60 ሰዎች እንደቆሠሉ በሪፖርቱ ላይ ተገልጧል። ከ70 ሺሕ በላይ ሕጻናት በደቡባዊ ኦሮሚያ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ ጥናቱ ያመለክታል። 2፤ በትግራይ ክልል ታሕታይ አዲያቦ ወረዳ "ገማህሎ" በተባለ ቦታ አቅራቢያ የሕወሃትና የኤርትራ ኃይሎችን የጦር መሣሪያ ክምችትን ዒላማ አድርጓል የተባለ የድሮን ጥቃት ዛሬ እንደተፈጸመ ዋዜማ ሠምታለች። በጥቃቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳልደረሠ የገለጹት ምንጮች፤ ላለፉት ሁለት ቀናት በአካባቢው ውጊያ እንዳልነበር ጭምር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም፤ የሕወሃት፣ የኤርትራ፣ የፋኖ እና የአፋር ኃይሎች እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የጦር መሳሪያዎች እንቅስቃሴ በስፋት እንደሚታይ ምንጮች ነግረውናል፡፡ 3፤ በመቀለ ከተማ ከጥቅምት 27 ቀን ጀምሮ የተጣለው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የሰዓት እገዳ ከዛሬ ጀምሮ መሻሻሉን የትግራይ ሠላም ኃይል አስታወቀ፡፡ በማሻሻያው መሠረት፤ የአሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ግፕደብ ከምሽቱ 2 ሰዓት ወደ ምሽቱ 4 ሰዓት ተራዝሟል ተብሏል። ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ የተከለከለው የባጃጅና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ገደብ ግን ላልተወሠነ ጊዜ ባለበት እንደሚቀጥል ተገልጿል። ሆቴሎችንና ሬስቶራንቶች ጨምሮ አገልግሎት ሠጪ ተቋማት ለ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሠጡ እንደተፈቀደ ተነግሯል፡፡ ማሻሻያው የተደረገው፤ በከተማዋ የጸጥታ መሻሻል በመታየቱ እንደሆነ ተገልጿል። 4፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ወረዳ ኮሻሌ ቀበሌ፣ የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት ሲጓዙ በታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉ የጸጥታ አባላትን በሚያጥላላና ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጸም በሚገፋፋ ሁኔታ በማኅበራዊ ድረገጽ የጥላቻ ንግግር አሠራጭተዋል የተባሉ አራት ተከሳሾች ላይ ፍርድ ቤት በእያንዳንዳቸው ላይ የሦስት ዓመት የእስር ቅጣት ወሠነ። ሦስቱ ተከሳሾች ድርጊቱን መፈጸማቸውን እንዳመኑና አንዱ ግን ድርጊቱን ክዶ መከራከሩን የወረዳው አስተዳደር ገልጧል። ፍርድ ቤቱ፤ በአራቱም ተከሳሾች ላይ የሦስት ዓመት ቀላል የእሥር ቅጣት ጥሏል ተብሏል። ከሁለት ወራት በፊት ለጸጥታ ሥራ ሲንቀሳቀሱ ዘጠኝ የፖሊስና ሚሊሺያ አባላት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት እንደተገደሉ ይታወሳል። 5፤ የናይጄሪያው ዩናይትድ ባንክ ኦፍ አፍሪካ፤ የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ በጣለው ገደብ ሳቢያ በኢትዮጵያ በዘርፉ የመሠማራት እቅዱ እንደተሠናከለበት አስታወቀ። ባንኩ እቅዱ የተሠናከለበት፤ ማዕከላዊ ባንኩ የአገሪቱ ባንኮች በሌሎች አገራት ቅጥያ ባንኮችን ሲያቋቁሙ የሚያፈሱት ገንዘብ ከአክሲዮን ባለድርሻዎች ገንዘብ ከ10 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ሕግ በማውጣቱ እንደኾነ የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ባንኩ፤ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከሚሠማሩ የውጭ ባንኮች ቀዳሚው ለመሆን አቅዶ እንደነበር ሃላፊዎቹ መናገራቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። በዚሁ ገደብ ሳቢያ፣ ባንኩ ወደ አንጎላ የባንክ ዘርፍ ለመግባት ይዞት የነበረው እቅድ መስተጓጎሉንም ሃላፊዎቹ ገልጸዋል ተብሏል። ማዕከላዊ ባንኩ ገደቡን የጣለው፤ የአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ኢንቨስትመንት ቢገጥማቸው ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እንደሆነ ተገልጧል። 6፤ የግብጽ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ የኤርትራ፣ ሶማሊያና የሱዳን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር ጠየቁ። ሚንስትሮቹ ይህን የጠየቁት፤ ሰሞኑን በግብጽ አስተናጋጅነት ከተካሄደው የአስዋን ፎረም ስብሰባ በተጓዳኝ ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። ሚስትሮቹ፤ በጸጥታና በውሃ ደኅንነት ዘርፎች ላይ አገራት ይወስዷቸዋል ያሏቸውን የተናጠል ዕርምጃዎችም ተቃውመዋል። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዑስማን ሳለሕ፤ የቀይ ባሕር ደኅንነትና አስተዳደር የአዋሳኝ አገራት ብቻ ኃላፊነት መሆኑን በመጥቀስ፣ ቀይ ባሕር ከውጭ ወታደራዊ ፉክክር ሊጠበቅ ይገባዋል በማለት ተናግረዋል። 7፤ ዛሬ ጧት በካርቱም በሚገኘው የተመድ ቢሮ ላይ ጉዳት ያደረሰው የድሮን ጥቃት ከኢትዮጵያ የተነሳ ነው በማለት ሱዳን ከሠሠች። በወቅቱ የድርጅቱ ሠራተኞች ሕንጻው ውስጥ እንደነበሩ ተመድ ባወጣው መግለጫ ገልጧል። ቢሮው ወታደራዊ ዓላማዎች በሌሉበት አካባቢ እንደሚገኝ የገለጠው ተመድ፤ ድርጅቱ ደኅነት ላይ አደጋ መደቀኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል። ተመድ፤ ድሮኑ ከየት እንደተነሳ ያልገለጠ ሲሆን፤ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ያደርግ እንደሆነም ያለው ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን አዲስ ውንጀላ ዙሪያ የሠጠው ምላሽ የለም። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የሚነሱ ድሮኖች ሱዳን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጸማል የሚለውን የሱዳን መንግሥት ክስ ከሳምንታት በፊት ማስተባበሉ አይዘነጋም። እንዲሁም፤ 1፤ ኢትዮጵያዊያን ተዋንያን የተሳተፉበት "ሃጋር ኤሬትዝ" የተሠኘው ፊልም በሃይፋ ፊልም ፌስቲቫል ሽልማት አገኘ። በጸሐፊና ዳይሬክተር ሽሙኤል ቤሩ የተዘጋጀው ፊልሙ፣ በ1970ዎቹ በጎንደር ማርያም መንደር ይኖሩ የነበሩ ቤተ-እስራኤላዊያን ቤተሰቦች ወደ እስራኤል ያደረጉትን የስደት ጉዞ የሚያሳይ ነው። ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ፣ ደመወዝ ጎሽሜ፣ መሠረት ሕይወት እና አዜብ ወርቁን ጨምሮ ሌሎች አርቲስቶች በፊልሙ ላይ በትወና የተሳተፉ ሲሆን፤ በመጪው ታኅሣሥ ወር በኢትዮጵያ ለዕይታ እንደሚቀርብ ተገልጿል። 2፤ የሠዓሊ አሌክሳንደር ፍስሐዬ "የሰው እና የቁስ ባሕል" የተሠኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ወሎ ሠፈር በሚገኘው አውሮራ አዲስ ጋለሪ ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል። ሥራዎቹ በዕለት ተዕለት የሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚገኙ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችንና ባሕላዊ ቅርሶችን መነሻ በማድረግ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዙ የሄዱ የጋራ ትውስታዎችን፣ ባሕሎችን እና ተለዋዋጭ ማኅበራዊ ትስስሮችን ይዳስሳሉ። ዐውደ ርዕዩ እስከ ታኅሣሥ 16 ቀን ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ኅዳር 12፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ በኦሮሚያ ክልል በቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ለተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነት ወስዷል መባሉን አስተባበለ። ቡድኑ፤ በወረዳው ከመንግሥት ጋር በሚሠሩ የትርፍ ጊዜ ታጣቂ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ እርምጃ ወስጃለሁ በማለት ሰኞ'ለት ያወጣው መግለጫ በተዛባ መንገድ እንደተተረጎመበት ገልጧል። ርምጃ የወሠደው፤ "የታጠቁ ሲቪሎች" በነበሩበት የወታደራዊ ሥምሪት ካምፕ ላይ እንደነበር የጠቀሠው ቡድኑ፤ በወቅቱ ያወጣው መግለጫ ባልታጣቁ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል እንደማይል ገልጧል። ቡድኑ፤ ታጣቂዎቻችን ከአካባቢው ከወጡ በኋላም በሲቪሎች ላይ ጥቃቶች ቀጥለዋል ብሏል። 2፤ የአሜሪካ የሕግ መወሠኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ጂም ሪች፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዘግናኝ አዝማሚያ ይዘዋልበማለት አወገዙ። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን በተፈጸሙ ጥቃቶች ክርስቲያኖች የሚበዙባቸው ሰዎች ተገድለዋል ያሉት ሪች፤ በኢትዮጵያ የሚታየው አለመረጋጋትና ጥቃት በኢትያዊያን ሲቪሎች፣ በቀጠናው እና በአሜሪካ ጥቅሞች ላይ ከፍተኛ መዘዝ አለው በማለት ማስጠንቀቃቸውን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ የቆዩ ቅሬታዎችን ሊፈታ በሚችል መንገድ የውስጥ ጉዳይዋን መያዝ እንዳለባትም ሪች መክረዋል ተብሏል። አንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ላይ ይፈጸማል የተባለው ጥቃት ተግባራዊ ምላሽ እንደሚፈልግ እና በጥቃቶቹ ላይ ገለልተኛ ምርመራ ሊደረግ እና ተጠያቂነት ሊሠፍን እንደሚገባ አጽንዖት ሠጥተው መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። 3፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ከ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት ከዛሬ ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት መስጠት ጀመረች። የዓለም የጤና ድርጅት ለክትባት ዘመቻው ድጋፍ የሚሠጡ 28 ባለሙያዎች ማሠማራቱን ገልጧል። የክትባት መርሃ ግብሩ፤ በኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የዓለም ጤና ድርጅት የአሁኑ የክትባት ዘመቻ ኢትዮጵያን ከፖሊዮ ነጻ ወደኾነ ደረጃ አንድ ርምጃ ያቀርባታል ብሏል። የክትባት መርሃ ግብሩ እስከ ታኅሳስ አጋማሽ በሁለት ዙሪያ ይካሄዳል። ፖሊዮ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባቸው እና የመቋቋም ክፍተት ባለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች አሁንም ስጋት እንደደቀነ መኾኑን የጠቀሠው ድርጅቱ፤ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ቫይረሱ መገኘቱን ገልጧል። 4፤ ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ኾና በከፍተኛ ድምጽ ተመረጠች። የድርጅቱ አባል አገራት ጉባኤ ሦስት አዲስ አባላትን ለምክር ቤቱ የመረጠው፣ የምክር ቤቱ መቀመጫ ብዛት በቅርቡ ከ36 ወደ 40 ከፍ እንዲል በመተዳደሪያ ሕጉ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ ነው። የአፍሪካ አገራት ባለፈው ወር ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ ለምክር ቤቱ እጩ አባል እንድትኾን ባለፈው ወር እንደመረጧት ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ጋር ለድርጅቱ ምክር ቤት አባልነት የተመረጡት፣ ኦማን እና ኢንዶኔዥያ ናቸው። ኢትዮጵያ 133 የአባል አገራትን ድምጽ ስታገኝ፣ ኦማን 125 እንዲሁም ኢንዶኔዥያ 110 ድምጽ አግኝተዋል። ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት መስራች ናት። 5፤ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንንን የዓለማቀፉ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማስፋት ንቅናቄ መሪ ቡድን አባል አድርገው ሾሙ። ደመቀ ሹመቱ የተሠጣቸው፤ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የያዳም ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ኾነው በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ከግምት በማስገባት እንደሆነ ተገልጧል። የንቅናቄው መሪ ቡድን በዓለማቀፍ ዙሪያ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ድጋፍ የሚሠጥ ነው። ደመቀ በዚህ ሃላፊነታቸው፣ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ያገለግላሉ። እንዲሁም፤ 1፤ የፕሮፌሰር ባዬ ይማም አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቃ። በኢትዮጵያ የሥነ-ልሳን ምርምር እና የአማርኛ ሰዋስው ጥናት ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ባበረከቱት በፕሮፌሰር ባዬ ይማም የተጻፈው «ቋንቋ እና ማኅበረሰብ» የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀርቧል።በዘርፉ ባላቸው እውቀትና ቀደም ሲል ባሳተሟቸው የጥናት መጽሐፍት በስፋት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ባዬ ይማም ያዘጋጁት ይህ አዲስ መጽሐፍ፣ በቋንቋ እና በማኅበረሰብ መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስር የሚዳስስ መሆኑ ተገልጿል። 2፤ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል መርሃ-ግብር የመዝጊያ እና የሽልማት ሥነሥርዓት እሁድ ኅዳር 13 ቀን 2019 ዓ፤ም ይካሄዳል። ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው የህፃናትና ወጣቶች የሲኒማ ኮምፕሌክስ በሲኒማ 3 አዳራሽ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ የመዝጊያ መርሃ-ግብር ላይ የተለያዩ ሁነቶች የሚከናወኑ ሲሆን፤ በዋናነት በፌስቲቫሉ አሸናፊ ለሆኑ ፊልሞችና ባለሙያዎች የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ዓርብ፤ ኅዳር 11፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ከሞያሌ ተፈናቅለው ኬንያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ50 ሺሕ ወደ 60 ሺሕ ማሻቀቡን የኬንያ የዜና አውታሮች ዘገቡ። ቁጥሩ በጊዜያዊ መጠለያዎችና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች ድምር መሆንን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። በሌላ በኩል፤ በግጭቱ ሳቢያ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር 700 ሺሕ ገደማ እንደሚደርስ እስላሚክ ሪሊፍ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ባወጣው መረጃ ገልጧል። 329 ሺሕ ነዋሪዎች ከሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን ብቻ እንደተፈናቀሉ የጠቀሠው ድርጅቱ፤ 359 ሺሕ 798 ያህሉ ደሞ ከደቡባዊ ኦሮሚያ መፈናቀላቸውን ገልጧል። ሞያሌ ላይ የተቀሠቀሠው ግጭት ከከተማዋ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ተጽዕኖውን እንዳሳረፈ ድርጅቱ ገልጧቷል። የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አስተዳደሮች ግጭቱ በየክልላቸው ምን ያህል ነዋሪዎች እንዳፈናቀለ ይፋ አድርገው አያውቁም። 2፤ የአሜሪካ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባል ጂም ባይርድ፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን ያስችላሉ ያሏቸውን ሁለት ረቂቅ ሕጎች አቀረቡ። ረቂቅ ሕጎቹ፤ አሜሪካ ለሁለቱ አገራት የምግብና የግብርና ምርቶችንና መሳሪያዎችን እንዲሁም ክኅሎቶችን በማቅረብ አገራቱ ሰላም እንዲያወርዱ ለማበረታታት ያለሙ ናቸው። ረቂቅ ሕጎቹ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከቻይና ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያላሉ የማበረታታት ዓላማ ጭምር እንዳላቸው ተገልጿል። ወርቅ፣ መዳብ፣ ብር፣ ፖታሽ እና የተፈጥሮ ጋዝ በማውጣትና የወደብ መሠረተ ልማቶችን ጥቅም ላይ በማዋል አሜሪካ ለሁለቱ አገራት ድጋፍ እንድትሠጥም ረቂቅ ሕጎቹ ይጠይቃሉ። 3፤ ከመቀለ እና ዓዲግራት ከተሞች ውጪ በአብዛኛዎቹ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ አለመጀመሩን ዋዜማ ሠምታለች። ባለአደራ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችን የአንድ ዓመት ውዝፍ ደመወዝ ከጥቅምት 30 ጀምሮ እንደሚከፍል ገልጾ ነበር። በመቀለ እና ዓዲግራት ግን የ1 ወር ደመወዝ ብቻ እንደተከፈለ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ሠራተኞች ነግረውናል፡፡ ክፍያውን ለማስጀመር ያስችላል የተባለ መመሪያ ግን ለእያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም እንዲደርስ መደረጉን እንደሚያውቁ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ፤ በመቀለ የሚገኙ ከ300 በላይ የድምጺ ወያነ ጋዜጠኞችና ድጋፍ ሠጪ ሠራተኞች ከመስከረም 2019 ጀምሮ ደመወዛቸው በወቅቱ ባለመከፈሉ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ለዋዜማ በጽሁፍ በላኩት መልዕክት ገልጸዋል። ሠራተኞቹ፤ የቤተሰባቸውን የምግብ፣ የቤት ኪራይና የሕክምና ወጪዎች ለመሸፈን ባለመቻላቸው አስከፊ አደጋ ላይ ወድቀናል ብለዋል። ተቋሙ ጥበቃም ሆነ ሥራ አስኪያጅ ባለመመደቡ ለዘረፋ እንደተጋለጠ ሠራተኞቹ ገልጸዋል። 4፤ የትግራይ ሠላምና ለውጥ ምክር ቤት የሚዴያ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩትና የተቃዋሚው ትንሳኤ 70 እንደርታ ፓርቲ ሊቀመንበር የኾኑት ከበደ አሠፋ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ ከበደ ትላንት እኩለ ቀን በፌደራል ፖሊስ አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው መወሠዳቸውን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሠምታለች፡፡ ችሎቱ፤ ከበደ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ዙሪያ መርማሪ ፖሊስ መረጃዎችን አሰባስቦ እንዲያቀርብ ለኅዳር 14 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል። በሌላ የፍርድ ቤት ዜና፤ የቀድሞው የሠላም ሚንስትር ዴኤታ ታዬ ደንደኣ ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሠቶችን በተመለከተ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ለፌዴራል ፖሊስ ተለዋጭ ትዕዛዝ ሠጥቷል፡፡ ችሎቱ፤ በታዬ ደንደአ ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሠቶች ላይ ፌዴራል ፖሊስ ምላሹን በጽሁፍ ባለመቅረቡ ትዕዛዙን ተፈጻሚ ያላደረገበትን ምክንያት እንዲያስረዳ አዟል፡፡ ችሎቱ ጉዳዩን ለማየት ለማክሠኞ፤ ኅዳር 15 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ታዬ በእስር ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሠት እንደተፈጸመባቸው የሚገልጽ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ 5፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2027 APEX ባለ አምስት ኮከብ ዓለማቀፍ አየር መንገዶች አንዱ ኾኖ ተመረጠ። አየር መንገዱ በአፍሪካ የAPEX ምርጥ አየር መንገድ (Best Overall Airline in Africa) የተባለውን እውቅና ማግኘቱንም ማምሻውን አስታውቋል። እነዚህ የእውቅና ሽልማቶች በዓለማቀፍ የበረራ መረቡ ላይ ለመንገደኞች ምቹ፣ አስተማማኝ እና አስደሳች የጉዞ ተሞክሮዎችን ለማቅረብ ያለውን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቁ መኾናቸውን አየር መንገዱ ጠቅሷል። 6፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ተለይቻለሁ ባለው የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንበረ ሠላማ ሥር የሚገኘው የአክሱም አገረ ስብከት ማኅበረ ቅዱስ ያሬድ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትግራይ፤ በትግራይ የሚገኙ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት የጥቃት ዒላማ ሊኾኑ እንደሚችሉ ፍንጭ የሚሠጥ መግለጫ በባለአደራ አስተዳደሩ የኮምኒኬሽን ኃላፊ ዳሙራ የሕያ በኩል ተሠጥቷል በማለት ወቀሠ። ዳሞራ፤ የሕወሓት ኃይሎች በቤተክርስቲያናትና ገዳማት ውስጥ መሽገዋል በማለት የሠጡትን መግለጫ ጉዳዩ የተመለከተው የባለአደራ አስተዳደሩ ተቋም ማብራሪያ እንዲሠጥበትና እርማት እንዲያደርግ አገረ ስብከቱ ጠይቋል። የሃይማኖት ተቋማትንና የኃይማኖት መሪዎችን ዒላማ ሊያስደርጉ የሚችሉ ኃላፊነት የጎደላቸው መግለጫዎች የሠጡ አካላት በሕግ እንዲጠየቁና ከኃላፊነት እንዲነሱም አገረ ስብከቱ ጥሪ አቅርቧል። 7፤ የባሕረ ሠላጤው የትብብር ካውንስል፤ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ላይ ከፍቷል ያለውን በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄድ ዘመቻ አወገዘ። ካውንስሉ፤ ኡምሬቶች ቀጠናዊና ዓለማቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲሠፍን ቁልፍ ሚና የምትጫወት አገር ናት ብሏል። ካውንስሉ የሶማሊያን መንግሥት ድርጊት ያወገዘው፣ ኤምሬቶች ከሶማሊያ ግዛቶች ጋር በወደብና ጸጥታ ዙሪያ የተናጥል ስምምነቶች ላይ በመድረስ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጥሳለች በማለት የኤምሬቶችን አምባሳደር ባባረረና አቡዳቢ የሚገኙ አምባሳደሩን በጠራ ማግስት ነው። ኤምሬቶችም፤ የሶማሊያ ውሳኔ ውጥረትን የሚያባብስ እና ትብብርን የሚያዳክም ነው በማለት የአምባሳደሯን መባረር አውግዛለች። እንዲሁም፤ 1፤ ዋልያ መጽሐፍት “ሥነጥበብ እና ሳይንስ” በሚል ርዕስ የሐሳብ መድረክ አዘጋጅቷል። ቅዳሜ ኅዳር 12 ቀን በሚካሄደው በዚህ መድረክ ላይ፣ ዶ/ር ገረመው ፈይሳ በተጋባዥ እንግድነት ተገኝተው ሙያዊ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ። መርሐ ግብሩ አራት ኪሎ በሚገኘው የዋልያ መጽሐፍት አዳራሽ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል። 2፤ ቅዳሜ ኅዳር 12 ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው የ"ነገረ መጽሐፍት" ውይይት ላይ ሀብቴ ጀቤሳ (ዶ/ር) በእንግድነት ተጋብዘዋል። ለውይይት የተመረጠው "ቀንጨራነት እና ድኽነት በኢትዮጵያ" የተሠኘ መጽሐፍ ነው። ውይይቱ የሚካሄደው፣ ቀበና አካባቢ በሚገኘው የማኅበራዊ ጥናት መድረክ አዳራሽ ነው። 3፤ 21ኛው የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የፊልም ፌስቲቫል "50 ፊልሞች በ50 ብር' በሚል ርዕስ ከኅዳር 6 እስከ 13 ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው የሕፃናትና ወጣቶች የሲኒማ ኮምፕሌክስ ቀጥሏል። በፌስቲቫሉ ላይ ነገ ቅዳሜ ኅዳር 12 ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ሐሙስ፤ ኅዳር 10፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሞያሌውን ግጭት ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በደረሱ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ተደራዳሪዎች ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት ተኩስ እንደከፈቱ ዋዜማ ሠምታለች፡፡ የክልሎች አመራሮች በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ከሞያሌ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ "መዶሚጎ" በተባለ ቦታ በመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ ማክሰኞ'ለት መምከራቸውንና ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን ምንጮች ነግረውናል። ተደራዳሪዎቹ ላይ ተኩስ የተከፈተው፤ ከካምፑ በወታደሮች ታጅበው ከወጡ በኋላ ነበር ተብሏል። በጥቃቱ በሦስት ወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱን ምንጮች ገልጸውልናል፡፡ የተኩስ አቁም ውይይቱ በመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮችና ከሁለቱ ክልሎች በተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች አስተባባሪነት መካሄዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የሚውለበለብ ባንዲራ ጉዳይ ግን በይደር እንደተተወ ተረድተናል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ምሽት ድረስ የሠዎችና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በከተማዋ እንደሌለና በርካታ የንግድ ቤቶችም እንደተዘጉ መኾኑን ሠምተናል፡፡ በተያያዘ፤ በኬንያ ፓርላማ የሰሜናዊቷ ማንዴራ ግዛት ተወካይ የኾኑት አብዱል ሐሮ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የሞያሌውን ግጭት ላንድ ወር ገደማ ሳያስቆም ቀርቷል በማለት ተችተዋል። ኾኖም ፌዴራል መንግሥቱ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አመራሮች ግጭቱን እንዲያቆሙ አስማምቷል መባሉ አስደሳች ዜና መሆኑን አብዱል ገልጸዋል። አብዱል፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለልተኛ አካል ሆኖ ከተማዋን ከሁለት የሚከፍለውን መንገድ ቢቆጣጠር እንደሚሻል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተያየት ሠጥተዋል። 2፤ በባድመ ከተማ በተፈጸመ የአየር ጥቃት የ5 ሠዎች ሕይወት ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። ከትላንት እኩለ ቀን ጀምሮ በከተማዋና ዙሪያዋ ተከታታይ የአየር ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱት የኤርትራ እና የሕወሓት ኃይሎች ባንድ በኩል እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በከባባድ መሣሪያዎች የታገዙ የተኩስ ልውውጦች እስካሁንም መቀጠላቸውንና የጦር መሳሪያ ክምችቱም ተጠናክሮ መቀጠሉን እንደተመለከቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። 3፤ ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን፤ በትግራይ ክልል ከ7 ሺሕ 200 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀዋል አለ። ኮሚሽኑ፤ በትግራይ ክልል ብቻ ከ47 ሺሕ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ መርሃ ግብሩ ለማለፍ መመዝገባቸውን ገልጧል፡፡ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና መልሶ የማዋሃድ መርሃ ግብሩ ከፍተኛ የገንዘብና የሎጂስቲክስ ሀብት እንደሚጠይቅ የጠቀሠው ኮሚሽኑ፤ ለጋሽ አገራትና ዓለማቀፍ አጋሮች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡ 4፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሸባማይልስ በተሠኘው የደንበኞች የዲጂታል ፕሮግራሙ ላይ ሰሞኑን የተፈጸመ የሳይበር መረጃ ጥሠት ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። አየር መንገዱ በሳይበር ጥቃቱ ላይ ምርመራ መጀመሩን ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሠው እንደነገሩት ሮይተርስ ዘግቧል። አየር መንገዱ በፕሮግራሙ ላይ "መጠነኛ" ጥቃት እንደተፈጸመና የተወሠኑ የደንበኞች መረጃዎች ሳይጋለጡ እንዳልቀሩ ጠቅሶ፤ የደንበኞች የፋይናንስ መረጃዎች ስለመጋለጣቸው የሚያሳይ መረጃ ግን እንደሌለ ትናንት ለደንበኞቹ በኢሜል መልዕክት ልኮ ነበር። 5፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ በሮበርት ማካርቲ እና በአሜሪካው ቶሌዶ ሙዚየም ትብብር ከኢትዮጵያ የተወሠዱ አምስት ጥንታዊ ቅርሶችን ተረከበ። የቅርስ ርክክቡ በዚሁ የረጅም ጊዜ የቅርስ ማስመለስ ማዕቀፍ የተከናወነ የመጀመሪያው ርክክብ ነው። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ተጨማሪ ቅርሶች ከማካርቲ ስብስብ ለቶሌዶ ሙዚየም የተሠጡ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚተላለፉ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጧል። አምስቱ ቅርሶች፤ በሥዕሎችና በጌጣጌጥ ያሸበረቁ ሁለት የ15ኛው ክፍለ ዘመን የብራና ጽሑፎችና ከ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በነበረው ጊዜ የተሠሩና ጽሑፍ የተቀረጸባቸው ሦስት የብረት መስቀሎች ናቸው ተብሏል። 6፤ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ቻግኒ ከተማ፣ ሕገወጥ የነዳጅ ዝወውር ወንጀል ሲፈጽም የነበረን ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል የጸጥታ ኃይሎች ዛሬ ረፋዱ ላይ በከፈቱት ተኩስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። ሟቹ ከድርጊቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውና መንገድ ላይ ሲጓዝ የነበረ ግለሠብ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። ተሽከርካሪው በሰዓቱ ከተፈቀደለት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከር በተጨማሪ፣ ሌላ ታንከር በተሽከርካሪው ላይ አስገጥሞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል። 7፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ያስገባቸውን 500 ኢትዮጵያዊያን ለመመለስ እንደተቸገረ ተሠማ። ስደተኞቹን መመለስ ያልተቻለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተባባሪ ባለመኾኑ እንደኾነ የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። ስደተኞቹን ወደ አገራቸው መመለስ የሚቻለው፤ የአገራቸው መንግሥት ዜግነታቸውን ማረጋገጥ ሲችልና የጉዞ ሠነዶችን ሲያዘጋጅ ብቻ ነው በማለት የኢምግሬሽን ባለስልጣናት መናገራቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። 8፤ ሶማሊያ፤ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች አምባሳዶር በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወጡ አዘዘች። ሶማሊያ፤ አቡዳቢ የሚገኙ አምባሳደሯንም ጠርታለች። ይህን ርምጃ የወሠደችው የግዛት አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ መሆኑን ሶማሊያ ገልጣለች። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ኢምሬቶች ያለ ፌዴራል መንግሥቱ ይሁንታ ከግዛቶች ጋር የወደብ ስምምነት ውስጥ በመግባት በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች በማለት ከትናንት ወዲያ ክስ አቅርበው ነበር። የሶማሌላንድ መንግሥት በበኩሉ፤ ሶማሌላንድ ከየትኛውም አገር ጋር በምታደርገው የውጭ ግኑኝነት ላይ ሶማሊያ አንዳችም ሕጋዊ ሥልጣን የላትም ሲል ዛሬ ምላሽ ሠጥቷል። እንዲሁም፤ 1፤ በዶ/ር ደቻሳ አበበ የተዘጋጀው "አዲስ አበባ (1879-1967)፤ የከተማነትና የከተሜነት ታሪክ" የተሠኘው አዲስ መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀርቧል። መጽሐፉ የመዲናዋን የ88 ዓመታት የከተሜነት ታሪክ የሚዳስስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ አሳታሚነት ለኅትመት በቅቷል። 2፤ "የባስሊቆስ ዐንባ" እና "ጻማ" መጽሐፍት ደራሲ ትዕግሥት ታፈረ ቅዳሜ ኅዳር 12 ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከመጽሐፏ አንባቢዎች ጋር የምትገናኝበት የመጽሐፍ ፊርማ መርሃ-ግብር ለገሐር በሚገኘው ጃፋር መጽሐፍት መደብር ይካሄዳል። [ዋዜማ]
Open in Telegramዩክሬይን የሩሲያ ፊልም በኣዲስ አበባ እንዳይታይ ጠየቀች በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው 21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌሲቲቫል ላይ እንዲቀርብ የተመረጠ የሩሲያ ፊልም ለህዝብ እንዳይታይ ከዩክሬይን መንግስት ለፌስቲቫሉ አዘጋጆችና ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መቅረቡን ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ተረድታለች። ዝርዝሩን ያንብቡት -- cutt.ly/aySq56zF
Open in TelegramConnections
Similar channels
4-3-3 World News@ethionews433News and media50.4K
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ@sputnik_ethiopiaNews and media50.7K
BBC News Afaan Oromoo@bbcafaanoromooNews and media51.5K
ሪፖርተር (Ethiopian Reporter)@ethiopianreporteramharicNews and media47.8K
Zehabesha@zehabeshanewsNews and media53.5K
ሰሌዳ | Seleda@seledadotioNews and media53.6K
ኢትዮ መረጃ - NEWS@ethio_mereja_newsNews and media44.9K
አንኳር ዜና | Ankuar News Network@ankuarnewsNews and media55.2K