ለቸኮለ! ቅዳሜ፤ ኅዳር 19፣ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የ45 ቀናት ሪፖርቱን ዛሬ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አቀረበ። ዐቢይ፤ ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር የክትትል ግምገማ ውይይት ማድረጋቸውን ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። በውይይቱ፤ አስተዳደሪ ያሳያቸው ርምጃዎች፣ ተግዳሮቶች እና የጋራ የቅድሚያ ጉዳዮች እንደተገመገሙ ዐቢይ ገልጸዋል። የባለአደራ አስተዳደሩ ሥራ አስፈጻሚዎች፤ ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸውን ዋዜማ ከምንጮች መስማቷን ጠቅሳ ትናንት መዘገቧ ይታወሳል። 2፤ አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ሲቪሎችን መርጦ ያስታጥቃል በማለት ተቸ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት በቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን ሲቪሎችን ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ መሳሪያ ማስታጠቁን ሐሙስ'ለት መናገራቸውን የጠቀሠው ቡድኑ፤ ይህ አካሄድ በክልሉ ማኅበረሰቦች መካከል ውጥረቶችና ልዩነቶች እንዲባባሱ ያደርጋል በማለት ወቅሷል። ቡድኑ፤ ግለሰቦች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በራሳቸው መሳሪያ መታጠቃቸው፣ ለጸረ-ሽምቅ ዓላማ መንግሥት-መር ከሆነ የማስታጠቅ ድርጊት ተለይቶ መታየት እንዳለበት አሳስቧል። የታጠቁ ሲቪሎች በመንግሥት የጸረ-ሽምቅ ዘመቻ ውስጥ የሚሳተፉበት ሁኔታ እንዳለ የጠቆመው ቡድኑ፤ ይህ ሁኔታ እነዚህን አካላት ለአደጋ አጋልጧቸዋል ብሏል። 3፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ ዋና ሳጅን አለኹበል እሱነህ በድንገተኛ ጥቃት ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ተገደሉ። ዋና ሳጅን አለኹበል የተገደሉት "ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች" መኾኑን የወረዳው አሥተዳደር የገለጠ ሲኾን፤ የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ግድያውን የፈጸመው "ጽንፈኛው ቡድን" ነው ብሏል። በዋና ሳጅኑ ላይ ጥቃት የተፈጸመው፤ ከዱርቤቴ ከተማ መውጫ አካባቢ በትራፊክ ቁጥጥርና ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ ሳሉ ነው ተብሏል። የወረዳው አስተዳደር፤ ሟቹ በዞንና በወረዳ መዋቅሮች ለ21 ዓመታት በፖሊስ ሙያ ማገልገላቸውን ጠቅሷል። 4፤ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፤ በሶማሊያ በተሠማራው የኅብረቱ ተልዕኮ ዙሪያ ከቀረበለት ባለ ሦስት ምዕራፍ የተቀናጀ የጸጥታ ሽግግር እቅድ ውስጥ እስከ ቀጣዩ ዓመት ታኅሳስ የሚዘልቁትን ሁለቱን ምዕራፎች አጸደቀ። በገንዘብ እጥረትና ባልተቀናጀ አኳኋን የተልዕኮውን ወታደሮች ከአገሪቱ ማስወጣት የጸጥታ ክፍተት ሊፈጥርና አልሸባብ መልሶ ከተሞችን እንዲቆጣጠር እድል ሊሠጠው እንደሚችል ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ ያስጠነቀቀው ምክር ቤቱ፤ የኅብረቱ ኮሚሽን በአገሪቱ ጸጥታ ላይ ጥልቅ ግምገማ አድርጎ እስከ መስከረም 2020 ሪፖርት እንዲያደርግ ምክር ቤቱ ጠይቋል። ዓለማቀፍ አጋሮች ለተልዕኮው የገንዘብና ሎጅስቲክ ድጋፍ ማድረግ እንዲቀጥሉም ምክር ቤቱ ጥሪ አድርጓል። 5፤ የአውሮፓ ፓርላማ፤ የኤርትራ መንግሥት ስዊድናዊ ዜግነት ያለውን ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ ለበርካታ አስርት ዓመታት እስር ላይ የሚገኙ ሁሉንም "የኅሊና እስረኞች" እንዲፈታ ጠየቀ። የዳዊት ሕይወትና ደኅንነት በጥልቅ እንደሚያሳስበው የገለጠው ፓርላማው፤ ጋዜጠኛው በአስቸኳይ ተፈትቶ ወደ ስዊድን እንዲመለስና እስከዚያው በሕይወት ስለመኖሩና ስለታሠረበት ቦታ መንግሥት ማረጋገጫ እንዲያቀርብ፣ ከጠበቃ ጋር እንዲገናኝ እንዲፈቅድና ግርፋት ደርሶበታል በሚሉ ሪፖርቶች ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። ፓርላማው፤ የአውሮፓ ኅብረት ካውንስል በሰብዓዊ መብት ጥሠት ተጠያቂ በሆኑ የኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የተመረጡ ማዕቀቦችን ለመጣል እንዲያጤን ጠይቋል። እንዲሁም፤ 1፤ የአዲስ የሥነ-ጽሑፍ ፌስቲቫል 2026 በመጪው ሳምንት ይካሄዳል። ዓለማቀፍ የሥነጽሑፍ ባለሞያዎች የሚሳተፉበትና "ድንበር የለሽ ገጾች፤ የሚያስተሳስሩን ታሪኮች" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚህ የሦስት ቀናት ፌስቲቫል ላይ፣ ሀሳብ አመንጪ ውይይቶች፣ የሥነ-ጽሑፍ ዳሠሣዎች፣ የግጥም ምሽቶች፣ የሥልጠና ዐውደ ጥናቶችና ሌሎችም ዝግጅቶች ይቀርባሉ። ፌስቲቫሉ ከመጪው ሐሙስ ኅዳር 24 እስከ ቅዳሜ ኅዳር 26 ቀን ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ይካሄዳል። 2፤ የሠዓሊ ጋሻሁን ካሣሁን "የቆዳ ስፋት" የተሠኘ የግል የሥዕል ዐውድ ርዕይ በመጪው ማክሰኞ ኅዳር 22 ቀን ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በገብረክርስቶስ ዘመናዊ የሥነጥበብ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።[ዋዜማ]
Open in TelegramPosts of Wazema Media / Radio
ለቸኮለ! ዓርብ፤ ኅዳር 18፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አመራሮች ነገ ቅዳሜ የአንድ ወር አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለማቅረብ አዲስ አበባ እንደተጠሩ ዋዜማ ሠምታለች። ዐቢይ፤ ጌታቸው ረዳ፣ አብርሃም በላይ እና ሬድዋን ሁሴን ባለአደራ አስተዳደሩን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ መመደባቸውን፣ ሬድዋን የተቆጣጣሪ ቡድኑ ሰብሳቢ መሆናቸውንና ቡድኑ በየሳምንቱ የአስተዳደሩን አፈጻጸም እንደሚገመግም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ነግረውናል። በሌላ በኩል፤ የባለአደራ አስተዳደሩ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፤ በጦርነቱ የወደሙ የክልሉን የመንግሥት ሠራተኞች ሠነዶች መልሶ ለማደራጀት፣ የትምህርት ማስረጃዎችን ለማረጋገጥና በክልሉ የፌደራል ሲቪል ሠርቪስ ማሻሻያ አቅጫጣዎችን ለማስፈጸም እስከ ኅዳር 30 እንደ አዲስ የሠነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡለት ጠይቋል። 2፤ በትግራይ ክልል ሠሜን ምዕራብ ዞን ገጠራማ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በሕወሃት፣ የፋኖ ታጣቂዎችና የኤርትራ ሠራዊት በሌላ በኩል የሚካሄዱ ውጊያዎች መቀጠላቸውን የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለዋዜማ ገለጡ። አህስኣ፣ ዝባን ጉላ እና ዓዲ ፍታው በተባሉ ገጠራማ አካባቢዎች፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል። የትግራይ ሠላም ኃይል፤ ሠምበል እና ገማህሎ የተባሉ የድንበር አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች ሥር መግባታቸውን ገልጧል፡፡ 3፤ የትግራይ ሰላም ኃይል ትጥቅ የመፍቻ ጊዜ ማራዘምንና የጦር መሳሪያዎች ርክክብን የሚመለከቱ መመሪያዎችን ማስተላለፉን ዋዜማ ተመልክታለች፡፡ ቡድኑ፤ ከኅዳር 22 እስከ ኅዳር 24 ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የሚገቡ የሠላም ኃይሉን አባላት ከፋፍሎ ዘርዝሯል። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸውና ሥማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የባለአደራ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር፤ የቡድኑ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ከፈቱ በኋላ ሥልጠና ወስደው እንደየፍላጎታቸው ወደ ክልሉ ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት እንደሚቀላቀሉ ነግረውናል፡፡ ወደ ቀድሞ ሥራቸው የሚመለሱ ታጣቂዎችና አመራሮች እንደሚኖሩም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡ በተያያዘ፤ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የሠላምና ጸጥታ ቢሮ የሚሊሻዎች ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ለጊዜው እንዲቋረጥ አዝዟል። ቢሮው፤ የሚሊሻ አባላትን የጦር መሣሪያ የማስመለስ እንቅስቃሴ እንዲቆም የሚያዝ ደብዳቤ ለሁሉም ዞኖች የሚሊሻ ጽሕፈት ቤቶች ልኳል። የትግራይ የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት በአዋጅና በደንብ የተቋቋመ ራሱን የቻለ ተቋም መሆኑን ያስታወሰው ደብዳቤው፤ ቀደም ሲል በጦርነትና ጦርነቱን ተከትለው በመጡ ለውጦች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የታዩ ክፍተቶች በተቋሙ ደንብና አሠራር መሠረት ብቻ እንዲታረሙ አዟል። ከሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ደንብና አሠራር ውጭ በተለያዩ የጸጥታ ኃይል አባላት የሚሊሻዎች ትጥቅ እየተፈታና እየተወሠደ መሆኑን መረጃ እንደደረሠው ቢሮው የገለጠ ሲሆን፤ ከኅዳር 17 ጀምሮ ያላግባብ የተወሠዱ ትጥቆች ተጣርተው ለባለቤቶቻቸው እንዲመለሱም አሳስቧል። 4፤ ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተቀሠቀሠው ግጭት አለመርገቡን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናገሩ። በየእለቱ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ፣ የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንደሚገደብ እንዲሁም ግድያ እና እገታ መበራከቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በታጣቂዎች መካከል በሚፈጠር ግጭት የተኩስ ልውውጦች መኖራቸውንም ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ ረቡዕ'ለት የቋራ ወረዳ ሁለት መምህራን በታጣቂዎች መገደላቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር፤ ገዛኸኝ ታከለ እና አይጠገብ መለሠ የተባሉ ሁለት መምህራን በአደጋ ሕይወ ማለፉን ቢገልጽም፤ የሞታቸውን መንስኤ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ 5፤ በሞያሌው ግጭት ከሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን ሞያሌ እና ሁደት ወረዳዎች ብቻ ከ207 ሺሕ ሕዝብ በላይ እንደተፈናቀለ ዋዜማ ተመድ እና አጋር ድርጅቶች ሰሞኑን በክልሉ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጣቸውን ዋዜማ ገና ይፋ ካልሆነው የዳሰሳ ጥናት ላይ ተመልክታለች። ከ18 ሺሕ 600 በላይ የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሠደዳቸውን ጥናቱ ያሳያል። በግጭቱ 6 ሺሕ 800 ገደማ የመኖሪያ ቤቶች በ25 ቀበሌዎች ውስጥ እንደወደሙ፣ ከ18 ሺሕ 700 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ እንደሆኑ፣ በሞያሌ ወረዳ ደሞ ሰባት ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሠባቸው ሠነዱ ያሳያል። 37 ትምህርት ቤቶች በሁለቱም ወረዳዎች ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆኑ የሚጠቅሠው ጥናቱ፤ በሞያሌ ወረዳ ብቻ 10 ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ ሆነዋል ይላል። 164 መምህራን ደሞ ከሁለቱም ወረዳዎች ከቀያቸውና ከሚያስተምሩባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለዋል ተብሏል። 6፤ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በትግራይ የፌደራል እና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ከአገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ውይይት አካሄደ። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ የውይይቱ ዓላማ ከባለድርሻ አካላት ምርጫውን ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ሀሳቦችን መሰብሰብ መሆኑን መግለጣቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ሜላትወርቅ፤ በክልሉ በሚካሄደው ምርጫ መወዳደር የሚፈልጉ ፓርቲዎች ለምርጫው እንዲዘጋጁ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ድምጽ ሠጪዎችን ለማስተማር እንዲሠራ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ በመድረኩ ላይ አሳስበዋል ተብሏል። ምርጫ ቦርድ፤ የክልሉ ባለአደራ ለምርጫው በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ ከቦርዱ ጋር ግንኙነት የሚያደርገውን አካል ለይቶ እንዲያሳውቀው ሰሞኑን በደብዳቤ መጠየቁ ይታወሳል። እንዲሁም፤ 1፤ የሠዓሊ አብርሃም ወ/ገብርኤል "የሕይወት መጠበቂያ" የሥዕል ዐውድ ርዕይ የመጨረሻ መርሃግብር ነገ ቅዳሜ በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ይካሄዳል። ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ሠዓሊውን በአካል ማግኘት፣ ሥዕሎቹን መጎብኘት እና የሥዕል ሥራዎቹን መግዛት እንደሚቻል ተገልጿል። 2፣ ታዋቂው የባሕል ሙዚቃ ቡድን ኢትዮ ከለር ከጃፓን ከመጣው ኩራጌ ባንድ ጋር በመተባበር ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ሊያቀርብ ነው። ይኸ ዝግጅት ነገ ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በፈንድቃ የባሕል ማዕከል ይካሄዳል። 3፤ የ"መጠበቅ" መጽሐፍ ደራሲ ፋንታ ገ/ማርያም ነገ ቅዳሜ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከመጽሐፏ አንባቢዎች ጋር የምትገናኝበት የመጽሐፍ ፊርማ መርሃ-ግብር ለገሐር በሚገኘው ጃፋር መጽሐፍት መደብር ይካሄዳል።[ዋዜማ]
Open in TelegramViews growthHide views growth
Views growth
Hours after publication
Show as table
| Hours after publication | Views |
|---|---|
| 0 h | 0 |
| 21 h | 6,650 |
| 28 h | 7,890 |
- After 24 hours6,650
- Total to date7,890
ለቸኮለ፤ ሐሙስ፤ ኅዳር 17፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችን ማስታጠቅ ካላቆመ ኤርትራ ኃላፊነቱን ትወስዳለች በማለት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሠጡት ማብራሪያ አስጠነቀቁ፡፡ ኢትዮጵያ ኤርትራን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት የገለጡት ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ጉዳይ በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት እንደምትሻ ተናግረዋል። ዐቢይ፤ ከሁለት ዓመታት በላይ በተካሄደው የትግራዩ ጦርነት ወቅት የውጭ አገራት የድሮን ባለሞያዎች ትግራይ ውስጥ እንደነበሩም ገልጸዋል። የተወሠኑት የድሮን ባለሙያዎች እንደተያዙም ዐቢይ ጠቅሠዋል። ዐቢይ፤ ተይዘዋል ያላቸውን የድሮን ባለሙያዎች ዜግነት አልጠቀሱም። 2፤ የጸጥታ ተቋማት በፖለቲካ ጉዳይ ከተከፋፈሉ የአገር ሥጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ "የመደመር መሪ ስትራቴጂ ከ2025 እስከ 2050" የተሠኘው የ25 ዓመት የመንግሥት ስትራቴጂ አስጠነቀቀ። ፌዴራል መንግሥቱ ከነሐሴ 2018 ዓ፤ም ጀምሮ ለሚንስትሮች፣ ለምክር ቤት አባላትና ለጋዜጠኞች ሥልጠና እየሠጠበት የሚገኘውና ዋዜማ የተመለተችው የስትራቴጂ ሠነድ፤ ደኅንነት ያለ ሕጋዊነትና የሕዝብ ተቀባይነት በዘላቂነት እንደማይቆም ይጠቅሳል፡፡ እስከ 2030 ዓ፤ም ድረስ ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን የሚያምኑ ዜጎች 60 በመቶ ለማድረስ ስለመታቀዱ አስፍሯል። የውስጥ ግጭቶችን በወታደራዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ መግባባትና በተቋማዊ እርቅ መፍታት እንደሚገባ በሠነዱ ላይ የተጠቀሠ ሲሆን፤ በግጭት የተጎዱ፣ ገጠራማ፣ አርብቶ አደርና ጠረፋማ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ካላገኙ የግጭት አዙሪት እንደማይቆም ያስጠነቅቃል። Detail report - cutt.ly/9yD2on2J 3፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች የያዙትን የ1 ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ መልሶ ለማዋቀር የሚያስችል ይሁንታቸውን ለማግኘት እስከ ታኅሣሥ 2 ቀነ ገደብ አስቀመጠ። ዩሮቦንዱን መልሶ ለማዋቀር የሚያስችል የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ ከቦንዱ 300 ሚሊዮን ዶላር የያዙ ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች ይሁንታ ያስፈልጋል። ባንድ ኮሚቴ የተወከሉ የዩሮቦንዱን 45 በመቶ የያዙ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የቦንድ መልሶ ማዋቀሪያ ሀሳብ ቀደም ሲል መቀበላቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሀሳብ፤ የ1 ቢሊዮን ዶላሩን ዩሮቦንድ እኤአ በሐምሌ 2028 በሚከፈል የ880 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ የሚተካ ሲሆን፤ የቀድሞውን የ6 ነጥብ 62 ዓመታዊ ወልድም ወደ 6 ነጥብ 15 በመቶ ዝቅ የሚያደርግ ነው። 4፤ መንግሥት በርካታ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ጸጥታ ኃይሎችን ዛሬ በሞያሌ ማሠማራቱን ዋዜማ በአካባቢው ከሚገኙ ምንጮቿ ሠምታለች። ጸጥታ ኃይሎቹ፤ የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አስተዳደሮች በቅርቡ የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊነት ይከታተላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ነግረውናል። ይህንኑ ተከትሎ፤ ሞያሌ ላይ ላንድ ወር ቆመው የነበሩ የኬንያ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዛሬ ወደ ኬንያ መንቀሳቀሳቸውን ደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል። ከግጭቱ በፊት ሸቀጦችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩ ከ300 በላይ የኬንያ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሞያሌን አቋርጠው ወደ ኬንያ የገቡት፣ በኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች እጀባ መኾኑን ዘገባው ጠቅሷል። የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ወደ ኬንያ የተንቀሳቀሱት፤ የኬንያ መንግሥት ባለስልጣናት እና የኬንያ የጭነት አሽከርካሪዎች ማኅበር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ነው ተብሏል። መንግሥት ግጭቱን ለማስቆም ጸጥታ ኃይሎቹን በሞያሌ ስለማሠማራቱ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው ነገር የለም። 5፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከቻይናው ቲ ደብሊው ሆልዲንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ውስጥ የመማሪያ መጽሐፍት ማተሚያ ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ተፈራረመ። ፋብሪካው፤ የትምህርት መጽሃፍትን የማተም፣ የመለበድ፣ የመጠረዝና የማሠራጨት ሥራ እንደሚሠራ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፤ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የኅትመት ኢንዱስትሪ ለማጠናከርና የትምህርት ቁሳቁሶችን ጥራት ለማሻሻል፣ ከውጭ ለሚገቡ የመማሪያ መጽሃፍት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እንዲሁም በመማሪያ መጽሃፍት ፍላጎት እና በአገር ውስጥ የማተም አቅም ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለማጥበብ እንደሚረዳ ገልጧል። በስምምነቱ መሠረት፤ የቻይናው ኩባንያ በማተሚያ ቤቱ የ51 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ደሞ የ49 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ተገልጧል። የፋብሪካው የመጀመሪያው ዙር ምዕራፍ 30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል። 6፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ሁለት ሠራተኞች ትላንት ረፋድ ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። በጥቃቱ፤ ፍላቂት ላይ እየተገነባ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት በበላይነት ሲመራ የነበረው አሸናፊ ዑመር እና የፕሮጀክቱ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አሥተዳደር ኃላፊ ዘሪሁን መሐመድ ሕይወታቸው ማለፉን ምንጮች ነግረውናል። ሠራተኞቹ ከሰርኮ ወደ ዳንዴ በር ንብረትነቱ የኮንስትራክሽን ኤጀንሲው በሆነ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው የገለጡት ምንጮች፤ በአካባቢው የሠፈሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በስፍራው ሲደርሱ ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን አስረድተዋል። እንዲሁም፤ 1፤ "ፋውንደርስ ላውንጅ" የተሠኘውና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሠማሩ መሪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት መሠናዶ ዓርብ፣ ኅዳር 18 ቀን በቬንቸር ሀብ ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ይካሄዳል። በዚህኛው ዙር መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ንግዶች በሀገር ውስጥ ያላቸውን አቅም አጠናክረው ወደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ዓለማቀፍ ገበያዎች መግባት በሚችሉባቸው ስልቶች ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል። 2፤ በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ "የዓርብ የጃዝ ምሽት" የሙዚቃ ዝግጅት ነገ ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል። 3፤ የኢትዮጵያ ክላሲክና የጃዝ ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት የቀጥታ ሙዚቃ ዝግጅት ነገ ዓርብ፤ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ ብራስ አካባቢ በሚገኘው ግራንድ ኩዳ ይቀርባል። 4፤ የጭረት ባንድ አባላት በሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል ነገ ዓርብ፤ ከምሽቱ 2 ተኩል ጀምሮ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። [ዋዜማ]
Open in Telegramየ25 አመቱ የብልፅግና መሪ ዕቅድ ምን ይዟል? በዚህ ሠነድ ውስጥ የሀገር ደኅንነት፣ የውስጥ ግጭቶች አፈታት፣ የቀጠናዊ ጦርነት ሥጋቶች፣ የጸጥታና የመከላከያ ተቋማት ገለልተኝነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና ሌሎች መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተካትተዋል፡፡ ሠነዱ የጸጥታ ኃይሎች አካሄድ፣ የጦርነት መንስኤዎችና የሰላማዊ ሽግግር መርሆችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያዎችንም አስፍሯል። ያንብቡት cutt.ly/9yD2on2J
Open in Telegramለቸኮለ፤ ማክሰኞ፤ ኅዳር 15፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ ሁሉም የሱዳን ተፋላሚ ወገኖችና የፖለቲካ ኃይሎች አዲስ አበባ ውስጥ ሁሉን ዓቀፍ ለሆነ ንግግር እንዲቀመጡ ጋበዙ። የንግግሩ ዓላማ፤ ጦርነትን ማቆምና ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችል ሁሉን ዓቀፍ ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚሆን ዐቢይ ዛሬ በጽሁፍ ባቀረቡት ጥሪ ገልጸዋል። ይህ ጥሪ የተለየ የፖለቲካ ዓላማ ወይም ጥቅም ለማሳካት ሳይኾን፤ በአገሪቱ ሰላም እንዲሠፍን ከልብ ከማሰብ የመነጨና ብሄራዊ የአንድነት መንግሥት ለማቋቋም መሠረት የሚጥል እንዲኾን ኢትዮጵያ ካላት ፍላጎት የመነጨ መሆኑን አጽንዖት ሠጥተዋል። ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላም የራሷ ጸጥታና መረጋጋት አካል አድርጋ እንደምታየው ዐቢይ ገልጸዋል። 2፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል በአላማጣ ከተማ ላይ የተኮሷቸው ከባድ መሳሪያዎች የጦር ወንጀልነት ምርመራ ሊደረግባቸው ይገባል አለ። ከመስከረም 16 እስከ 18 በተፈጸሙ አራት የመድፍ ጥቃቶች በከተማዋ 14 ሰዎች እንደተገደሉ ድርጅቱ ጠቅሷል። ድርጅቱ፤ የሕወሓት ኃይሎችም ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው ቦታዎች ወታደራዊ ጦር ሠፈር በማቋቋም ሲቪሎችን ለጥቃት አጋልጠዋል፤ ከከተማዋ ኾነው ከባድ መሳሪያዎችን ተኩሠዋል በማለት ከሷል። መከላከያ ሠራዊትና የትግራይ የሰላም ኃይል በጥቃቶቹ ዙሪያ መረጃ እንዲሠጡ በጥቅምት ወር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ የጠቀሰው ድርጅቱ፤ ሕወሃት ግን ውንጀላውን በማስተባበል ምላሽ ሠጥቷል ብሏል። 3፤ በትግራይ ክልል በደቡብ ትግራይ ዞን በዞን፣ ወረዳዎችና ከተሞች በቅርቡ የተሠጡ ሹመቶች በሙሉ ውድቅ መደረጋቸውን ዋዜማ ሠምታለች። ባለአደራ አስተዳደሩ ሹመቶቹን ያስቀረው፤ ከዞኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች ዛሬ ከአስተዳደሩ አመራሮች ጋር መቀለ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ ነው። ተወካዮቹ፤ የተሿሚዎቹ አመራረጥ ለውጥ ፈላጊዎችን ያገለለ እና "የትውልድ ቦታን" መሠረት ያደረገ ዝንባሌ የታይበት ነው የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል። የባለአደራ አስተዳደሩም፤ ሹመትና ምደባው ከእውቅናው ውጪ እንደተከናወነ እንዳመነና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ቅሬታ እንዳይፈጠር የምደባ ሂደቱ የሚመራበት አዲስ መመሪያ ከነገ ጀምሮ ወደ ዞኖችና ወረዳዎች እንደሚልክ ተረድተናል። 4፤ ብሔራዊ ባንክ፤ አካል ጉዳተኛ የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞች ሀብታቸውን ለማስተዳደር ሞግዚት፣ ተወካይ ወይም ረዳት እንዲያቀርቡ የሚገደዱበትን አሠራር አዲስ ባወጣው ረቂቅ መመሪያ ከለከለ፡፡ ረቂቅ መመሪያው፤ አካል ጉዳተኞች የፋይናንስ አገልግሎቶችን በእኩልነትና ያለ አድልዎ እንዲያገኙ የሚያስችሉ አስገዳጅ ደረጃዎችን ያካተተ ነው። አካል ጉዳተኞች ተደራሽ ባልሆነ የመገናኛ መስመር ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ብቻ "ትብብር የማያደርግ"፣ "ፍቃደኛ ያልኾነ" ወይም "ግዴታውን ያልተወጣ" ተብለው በፋይናንስ ተቋማት እንዳይፈረጁ ረቂቅ መመሪያው ያግዳል። ረቂቅ መመሪያው፤ የአካል ጉዳት ለብድር ብቁ ያለመኾን ወይም የመድኅን ሽፋን ወይም የፋይናንስ አቅም ማረጋገጫ ተደርጎ እንዳይወሠድና በንግድ ሥራ በሚተዳደሩ የአካል ጉዳተኞች ላይ በአካል ጉዳታቸው ምክንያት ተጨማሪ የብቁነት ገደቦች እንዳይጣሉ ይከለክላል፡ ተቋማት፤ ለእያንዳንዱ የመመሪያው ጥሠት 50 ሺሕ ብር ሊቀጡ ይችላሉ ተብሏል። 5፤ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን አስታወቀ። ቦርዱ የክልሉን ባለአደራ አስተዳደር በመወከል በምርጫ ዙሪያ ግንኙነት የሚያደርገውን አካል አስተዳደሩ እንዲያሳውቀው በደብዳቤ ጠይቋል። ለምርጫ ዝግጅት ወደ ክልሉ ቦርዱ የሚልካቸውን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ቦርዱ ለሚያቀርባቸው የተሽከርካሪ፣ የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ጥያቄዎች ባለአደራ አስተዳደሩ ትብብር እንዲያደርግም ቦርዱ ጥያቄ አቅርቧል። ባለአደራ አስተዳደሩ፤ በስድስት ወራት ውስጥ የክልልና ፌዴራል ምርጫዎች እንዲደረጉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ሥልጣን ተሠጥቶታል። 6፤ ብሄራዊ ባንክ ዛሬ ባካሄደው የ140 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የተጫራች ባንኮች ፍላጎት የ20 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አስመዘገበ። ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው ተመሳሳይ መጠን ያለው ጨረታ የተጫራቾች ፍላጎት የ16 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ነበር ያሳየው። ባንኩ በዛሬው ጨረታ አንድን ዶላር በ160 ብር ከ73 ሳንቲም የሸጠ ሲሆን፤ ከቀደመው ጨረታ የብር ዋጋ ከዶላር አንጻር በመጠኑ አሽቆልቁሏል። ለዛሬው ጨረታ የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ 161 ብር 41 ሳንቲም እንዲሁም ዝቅተኛው ዋጋ 155 ብር መሆኑን ባንኩ ጠቅሷል። በጨረታው ከተሳተፉት 32 ባንኮች 28ቱ የውጭ ምንዛሬ አግኝተዋል ተብሏል። እንዲሁም፤ 1፤ "በቀለበቴ" የተሠኘውና በተሻለ ወርቁ ተጽፎ የተዘጋጀ አዲስ ተውኔት በቅርቡ ዕይታ ሊቀርብ ነው። ተውኔቱ የኮሜዲ ዘውግ ያለው ሲኾን፤ በአንጋፋው የአገር ፍቅር ቴዓትር ቤት ለተመልካቾች እንደሚቀርብ ተገለጧል። በተውኔቱ ላይ ከተሳተፉት ተዋንያን መካከል፤ ቅድስት ገ/ሥላሴ፣ ተስፉ ብርሃኔ፣ ለምለም በየነ፣ ሲሳይ አማረ እና ሰላማዊት ካሣዬ ይገኙበታል። 2፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባሕል ማዕከል የተዘጋጀውና ተዋናይ ዓለማየሁ ታደሠ በክብር እንግዳነት የተጋበዘበት ሳምንታዊ ዝግጅት ነገ ረቡዕ ኅዳር 16 ቀን ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው የባሕል ማዕከል ይካሄዳል። መግቢያው በነጻ ነው። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ኅዳር 14፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በሞያሌ ግጭት የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ደርሰዋል ከተባለ ወዲህ በሁለቱ ክልሎች ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ ማታ ማታ መቀጠሉን ሠምተናል። ግጭቱ ያስከተለውን ጉዳት ለማወቅ ተመድና አጋር ድርጅቶች ባካሄዱት የዳሰሳ ጥናት ግጭቱ ከኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ371 ሺሕ ሕዝብ በላይ ከሰባት ወረዳዎች ማፈናቀሉን ዋዜማ ይፋ ካልሆነ የዳሠሳ ጥናቱ ረቂቅ ላይ ተመልክታለች። ከሶማሌ ክልል ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ የሚያሳየውን የዳሰሳ ጥናት ለጊዜው ባናገኝም፣ ግብረ ሰናዩ እስላሚክ ሪሊፍ 329 ሺሕ ነዋሪዎች ከዳዋ ዞን ብቻ ተፈናቅለዋል ሲል ባለፈው ሳምንት መግለጡ ይታወሳል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በደቡብ ኦሮሚያ ብቻ 130 ሰዎች እንደሞቱና 60 ሰዎች እንደቆሠሉ በሪፖርቱ ላይ ተገልጧል። ከ70 ሺሕ በላይ ሕጻናት በደቡባዊ ኦሮሚያ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ ጥናቱ ያመለክታል። 2፤ በትግራይ ክልል ታሕታይ አዲያቦ ወረዳ "ገማህሎ" በተባለ ቦታ አቅራቢያ የሕወሃትና የኤርትራ ኃይሎችን የጦር መሣሪያ ክምችትን ዒላማ አድርጓል የተባለ የድሮን ጥቃት ዛሬ እንደተፈጸመ ዋዜማ ሠምታለች። በጥቃቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳልደረሠ የገለጹት ምንጮች፤ ላለፉት ሁለት ቀናት በአካባቢው ውጊያ እንዳልነበር ጭምር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም፤ የሕወሃት፣ የኤርትራ፣ የፋኖ እና የአፋር ኃይሎች እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የጦር መሳሪያዎች እንቅስቃሴ በስፋት እንደሚታይ ምንጮች ነግረውናል፡፡ 3፤ በመቀለ ከተማ ከጥቅምት 27 ቀን ጀምሮ የተጣለው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የሰዓት እገዳ ከዛሬ ጀምሮ መሻሻሉን የትግራይ ሠላም ኃይል አስታወቀ፡፡ በማሻሻያው መሠረት፤ የአሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ግፕደብ ከምሽቱ 2 ሰዓት ወደ ምሽቱ 4 ሰዓት ተራዝሟል ተብሏል። ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ የተከለከለው የባጃጅና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ገደብ ግን ላልተወሠነ ጊዜ ባለበት እንደሚቀጥል ተገልጿል። ሆቴሎችንና ሬስቶራንቶች ጨምሮ አገልግሎት ሠጪ ተቋማት ለ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሠጡ እንደተፈቀደ ተነግሯል፡፡ ማሻሻያው የተደረገው፤ በከተማዋ የጸጥታ መሻሻል በመታየቱ እንደሆነ ተገልጿል። 4፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ወረዳ ኮሻሌ ቀበሌ፣ የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት ሲጓዙ በታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉ የጸጥታ አባላትን በሚያጥላላና ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጸም በሚገፋፋ ሁኔታ በማኅበራዊ ድረገጽ የጥላቻ ንግግር አሠራጭተዋል የተባሉ አራት ተከሳሾች ላይ ፍርድ ቤት በእያንዳንዳቸው ላይ የሦስት ዓመት የእስር ቅጣት ወሠነ። ሦስቱ ተከሳሾች ድርጊቱን መፈጸማቸውን እንዳመኑና አንዱ ግን ድርጊቱን ክዶ መከራከሩን የወረዳው አስተዳደር ገልጧል። ፍርድ ቤቱ፤ በአራቱም ተከሳሾች ላይ የሦስት ዓመት ቀላል የእሥር ቅጣት ጥሏል ተብሏል። ከሁለት ወራት በፊት ለጸጥታ ሥራ ሲንቀሳቀሱ ዘጠኝ የፖሊስና ሚሊሺያ አባላት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት እንደተገደሉ ይታወሳል። 5፤ የናይጄሪያው ዩናይትድ ባንክ ኦፍ አፍሪካ፤ የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ በጣለው ገደብ ሳቢያ በኢትዮጵያ በዘርፉ የመሠማራት እቅዱ እንደተሠናከለበት አስታወቀ። ባንኩ እቅዱ የተሠናከለበት፤ ማዕከላዊ ባንኩ የአገሪቱ ባንኮች በሌሎች አገራት ቅጥያ ባንኮችን ሲያቋቁሙ የሚያፈሱት ገንዘብ ከአክሲዮን ባለድርሻዎች ገንዘብ ከ10 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ሕግ በማውጣቱ እንደኾነ የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ባንኩ፤ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከሚሠማሩ የውጭ ባንኮች ቀዳሚው ለመሆን አቅዶ እንደነበር ሃላፊዎቹ መናገራቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። በዚሁ ገደብ ሳቢያ፣ ባንኩ ወደ አንጎላ የባንክ ዘርፍ ለመግባት ይዞት የነበረው እቅድ መስተጓጎሉንም ሃላፊዎቹ ገልጸዋል ተብሏል። ማዕከላዊ ባንኩ ገደቡን የጣለው፤ የአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ኢንቨስትመንት ቢገጥማቸው ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እንደሆነ ተገልጧል። 6፤ የግብጽ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ የኤርትራ፣ ሶማሊያና የሱዳን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር ጠየቁ። ሚንስትሮቹ ይህን የጠየቁት፤ ሰሞኑን በግብጽ አስተናጋጅነት ከተካሄደው የአስዋን ፎረም ስብሰባ በተጓዳኝ ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። ሚስትሮቹ፤ በጸጥታና በውሃ ደኅንነት ዘርፎች ላይ አገራት ይወስዷቸዋል ያሏቸውን የተናጠል ዕርምጃዎችም ተቃውመዋል። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዑስማን ሳለሕ፤ የቀይ ባሕር ደኅንነትና አስተዳደር የአዋሳኝ አገራት ብቻ ኃላፊነት መሆኑን በመጥቀስ፣ ቀይ ባሕር ከውጭ ወታደራዊ ፉክክር ሊጠበቅ ይገባዋል በማለት ተናግረዋል። 7፤ ዛሬ ጧት በካርቱም በሚገኘው የተመድ ቢሮ ላይ ጉዳት ያደረሰው የድሮን ጥቃት ከኢትዮጵያ የተነሳ ነው በማለት ሱዳን ከሠሠች። በወቅቱ የድርጅቱ ሠራተኞች ሕንጻው ውስጥ እንደነበሩ ተመድ ባወጣው መግለጫ ገልጧል። ቢሮው ወታደራዊ ዓላማዎች በሌሉበት አካባቢ እንደሚገኝ የገለጠው ተመድ፤ ድርጅቱ ደኅነት ላይ አደጋ መደቀኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል። ተመድ፤ ድሮኑ ከየት እንደተነሳ ያልገለጠ ሲሆን፤ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ያደርግ እንደሆነም ያለው ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን አዲስ ውንጀላ ዙሪያ የሠጠው ምላሽ የለም። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የሚነሱ ድሮኖች ሱዳን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጸማል የሚለውን የሱዳን መንግሥት ክስ ከሳምንታት በፊት ማስተባበሉ አይዘነጋም። እንዲሁም፤ 1፤ ኢትዮጵያዊያን ተዋንያን የተሳተፉበት "ሃጋር ኤሬትዝ" የተሠኘው ፊልም በሃይፋ ፊልም ፌስቲቫል ሽልማት አገኘ። በጸሐፊና ዳይሬክተር ሽሙኤል ቤሩ የተዘጋጀው ፊልሙ፣ በ1970ዎቹ በጎንደር ማርያም መንደር ይኖሩ የነበሩ ቤተ-እስራኤላዊያን ቤተሰቦች ወደ እስራኤል ያደረጉትን የስደት ጉዞ የሚያሳይ ነው። ጫንያለው ወልደጊዮርጊስ፣ ደመወዝ ጎሽሜ፣ መሠረት ሕይወት እና አዜብ ወርቁን ጨምሮ ሌሎች አርቲስቶች በፊልሙ ላይ በትወና የተሳተፉ ሲሆን፤ በመጪው ታኅሣሥ ወር በኢትዮጵያ ለዕይታ እንደሚቀርብ ተገልጿል። 2፤ የሠዓሊ አሌክሳንደር ፍስሐዬ "የሰው እና የቁስ ባሕል" የተሠኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ወሎ ሠፈር በሚገኘው አውሮራ አዲስ ጋለሪ ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል። ሥራዎቹ በዕለት ተዕለት የሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚገኙ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችንና ባሕላዊ ቅርሶችን መነሻ በማድረግ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዙ የሄዱ የጋራ ትውስታዎችን፣ ባሕሎችን እና ተለዋዋጭ ማኅበራዊ ትስስሮችን ይዳስሳሉ። ዐውደ ርዕዩ እስከ ታኅሣሥ 16 ቀን ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ኅዳር 12፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ በኦሮሚያ ክልል በቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ለተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነት ወስዷል መባሉን አስተባበለ። ቡድኑ፤ በወረዳው ከመንግሥት ጋር በሚሠሩ የትርፍ ጊዜ ታጣቂ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ እርምጃ ወስጃለሁ በማለት ሰኞ'ለት ያወጣው መግለጫ በተዛባ መንገድ እንደተተረጎመበት ገልጧል። ርምጃ የወሠደው፤ "የታጠቁ ሲቪሎች" በነበሩበት የወታደራዊ ሥምሪት ካምፕ ላይ እንደነበር የጠቀሠው ቡድኑ፤ በወቅቱ ያወጣው መግለጫ ባልታጣቁ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል እንደማይል ገልጧል። ቡድኑ፤ ታጣቂዎቻችን ከአካባቢው ከወጡ በኋላም በሲቪሎች ላይ ጥቃቶች ቀጥለዋል ብሏል። 2፤ የአሜሪካ የሕግ መወሠኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ጂም ሪች፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዘግናኝ አዝማሚያ ይዘዋልበማለት አወገዙ። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን በተፈጸሙ ጥቃቶች ክርስቲያኖች የሚበዙባቸው ሰዎች ተገድለዋል ያሉት ሪች፤ በኢትዮጵያ የሚታየው አለመረጋጋትና ጥቃት በኢትያዊያን ሲቪሎች፣ በቀጠናው እና በአሜሪካ ጥቅሞች ላይ ከፍተኛ መዘዝ አለው በማለት ማስጠንቀቃቸውን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ የቆዩ ቅሬታዎችን ሊፈታ በሚችል መንገድ የውስጥ ጉዳይዋን መያዝ እንዳለባትም ሪች መክረዋል ተብሏል። አንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ላይ ይፈጸማል የተባለው ጥቃት ተግባራዊ ምላሽ እንደሚፈልግ እና በጥቃቶቹ ላይ ገለልተኛ ምርመራ ሊደረግ እና ተጠያቂነት ሊሠፍን እንደሚገባ አጽንዖት ሠጥተው መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። 3፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ከ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት ከዛሬ ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት መስጠት ጀመረች። የዓለም የጤና ድርጅት ለክትባት ዘመቻው ድጋፍ የሚሠጡ 28 ባለሙያዎች ማሠማራቱን ገልጧል። የክትባት መርሃ ግብሩ፤ በኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የዓለም ጤና ድርጅት የአሁኑ የክትባት ዘመቻ ኢትዮጵያን ከፖሊዮ ነጻ ወደኾነ ደረጃ አንድ ርምጃ ያቀርባታል ብሏል። የክትባት መርሃ ግብሩ እስከ ታኅሳስ አጋማሽ በሁለት ዙሪያ ይካሄዳል። ፖሊዮ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባቸው እና የመቋቋም ክፍተት ባለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች አሁንም ስጋት እንደደቀነ መኾኑን የጠቀሠው ድርጅቱ፤ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ቫይረሱ መገኘቱን ገልጧል። 4፤ ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ኾና በከፍተኛ ድምጽ ተመረጠች። የድርጅቱ አባል አገራት ጉባኤ ሦስት አዲስ አባላትን ለምክር ቤቱ የመረጠው፣ የምክር ቤቱ መቀመጫ ብዛት በቅርቡ ከ36 ወደ 40 ከፍ እንዲል በመተዳደሪያ ሕጉ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ ነው። የአፍሪካ አገራት ባለፈው ወር ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ ለምክር ቤቱ እጩ አባል እንድትኾን ባለፈው ወር እንደመረጧት ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ጋር ለድርጅቱ ምክር ቤት አባልነት የተመረጡት፣ ኦማን እና ኢንዶኔዥያ ናቸው። ኢትዮጵያ 133 የአባል አገራትን ድምጽ ስታገኝ፣ ኦማን 125 እንዲሁም ኢንዶኔዥያ 110 ድምጽ አግኝተዋል። ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት መስራች ናት። 5፤ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንንን የዓለማቀፉ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማስፋት ንቅናቄ መሪ ቡድን አባል አድርገው ሾሙ። ደመቀ ሹመቱ የተሠጣቸው፤ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የያዳም ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ኾነው በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ከግምት በማስገባት እንደሆነ ተገልጧል። የንቅናቄው መሪ ቡድን በዓለማቀፍ ዙሪያ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ድጋፍ የሚሠጥ ነው። ደመቀ በዚህ ሃላፊነታቸው፣ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ያገለግላሉ። እንዲሁም፤ 1፤ የፕሮፌሰር ባዬ ይማም አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቃ። በኢትዮጵያ የሥነ-ልሳን ምርምር እና የአማርኛ ሰዋስው ጥናት ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ባበረከቱት በፕሮፌሰር ባዬ ይማም የተጻፈው «ቋንቋ እና ማኅበረሰብ» የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀርቧል።በዘርፉ ባላቸው እውቀትና ቀደም ሲል ባሳተሟቸው የጥናት መጽሐፍት በስፋት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ባዬ ይማም ያዘጋጁት ይህ አዲስ መጽሐፍ፣ በቋንቋ እና በማኅበረሰብ መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስር የሚዳስስ መሆኑ ተገልጿል። 2፤ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል መርሃ-ግብር የመዝጊያ እና የሽልማት ሥነሥርዓት እሁድ ኅዳር 13 ቀን 2019 ዓ፤ም ይካሄዳል። ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው የህፃናትና ወጣቶች የሲኒማ ኮምፕሌክስ በሲኒማ 3 አዳራሽ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ የመዝጊያ መርሃ-ግብር ላይ የተለያዩ ሁነቶች የሚከናወኑ ሲሆን፤ በዋናነት በፌስቲቫሉ አሸናፊ ለሆኑ ፊልሞችና ባለሙያዎች የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ዓርብ፤ ኅዳር 11፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ከሞያሌ ተፈናቅለው ኬንያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ50 ሺሕ ወደ 60 ሺሕ ማሻቀቡን የኬንያ የዜና አውታሮች ዘገቡ። ቁጥሩ በጊዜያዊ መጠለያዎችና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች ድምር መሆንን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። በሌላ በኩል፤ በግጭቱ ሳቢያ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር 700 ሺሕ ገደማ እንደሚደርስ እስላሚክ ሪሊፍ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ባወጣው መረጃ ገልጧል። 329 ሺሕ ነዋሪዎች ከሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን ብቻ እንደተፈናቀሉ የጠቀሠው ድርጅቱ፤ 359 ሺሕ 798 ያህሉ ደሞ ከደቡባዊ ኦሮሚያ መፈናቀላቸውን ገልጧል። ሞያሌ ላይ የተቀሠቀሠው ግጭት ከከተማዋ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ተጽዕኖውን እንዳሳረፈ ድርጅቱ ገልጧቷል። የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አስተዳደሮች ግጭቱ በየክልላቸው ምን ያህል ነዋሪዎች እንዳፈናቀለ ይፋ አድርገው አያውቁም። 2፤ የአሜሪካ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባል ጂም ባይርድ፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን ያስችላሉ ያሏቸውን ሁለት ረቂቅ ሕጎች አቀረቡ። ረቂቅ ሕጎቹ፤ አሜሪካ ለሁለቱ አገራት የምግብና የግብርና ምርቶችንና መሳሪያዎችን እንዲሁም ክኅሎቶችን በማቅረብ አገራቱ ሰላም እንዲያወርዱ ለማበረታታት ያለሙ ናቸው። ረቂቅ ሕጎቹ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከቻይና ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያላሉ የማበረታታት ዓላማ ጭምር እንዳላቸው ተገልጿል። ወርቅ፣ መዳብ፣ ብር፣ ፖታሽ እና የተፈጥሮ ጋዝ በማውጣትና የወደብ መሠረተ ልማቶችን ጥቅም ላይ በማዋል አሜሪካ ለሁለቱ አገራት ድጋፍ እንድትሠጥም ረቂቅ ሕጎቹ ይጠይቃሉ። 3፤ ከመቀለ እና ዓዲግራት ከተሞች ውጪ በአብዛኛዎቹ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ አለመጀመሩን ዋዜማ ሠምታለች። ባለአደራ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችን የአንድ ዓመት ውዝፍ ደመወዝ ከጥቅምት 30 ጀምሮ እንደሚከፍል ገልጾ ነበር። በመቀለ እና ዓዲግራት ግን የ1 ወር ደመወዝ ብቻ እንደተከፈለ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ሠራተኞች ነግረውናል፡፡ ክፍያውን ለማስጀመር ያስችላል የተባለ መመሪያ ግን ለእያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም እንዲደርስ መደረጉን እንደሚያውቁ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ፤ በመቀለ የሚገኙ ከ300 በላይ የድምጺ ወያነ ጋዜጠኞችና ድጋፍ ሠጪ ሠራተኞች ከመስከረም 2019 ጀምሮ ደመወዛቸው በወቅቱ ባለመከፈሉ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ለዋዜማ በጽሁፍ በላኩት መልዕክት ገልጸዋል። ሠራተኞቹ፤ የቤተሰባቸውን የምግብ፣ የቤት ኪራይና የሕክምና ወጪዎች ለመሸፈን ባለመቻላቸው አስከፊ አደጋ ላይ ወድቀናል ብለዋል። ተቋሙ ጥበቃም ሆነ ሥራ አስኪያጅ ባለመመደቡ ለዘረፋ እንደተጋለጠ ሠራተኞቹ ገልጸዋል። 4፤ የትግራይ ሠላምና ለውጥ ምክር ቤት የሚዴያ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩትና የተቃዋሚው ትንሳኤ 70 እንደርታ ፓርቲ ሊቀመንበር የኾኑት ከበደ አሠፋ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ ከበደ ትላንት እኩለ ቀን በፌደራል ፖሊስ አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው መወሠዳቸውን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሠምታለች፡፡ ችሎቱ፤ ከበደ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ዙሪያ መርማሪ ፖሊስ መረጃዎችን አሰባስቦ እንዲያቀርብ ለኅዳር 14 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል። በሌላ የፍርድ ቤት ዜና፤ የቀድሞው የሠላም ሚንስትር ዴኤታ ታዬ ደንደኣ ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሠቶችን በተመለከተ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ለፌዴራል ፖሊስ ተለዋጭ ትዕዛዝ ሠጥቷል፡፡ ችሎቱ፤ በታዬ ደንደአ ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሠቶች ላይ ፌዴራል ፖሊስ ምላሹን በጽሁፍ ባለመቅረቡ ትዕዛዙን ተፈጻሚ ያላደረገበትን ምክንያት እንዲያስረዳ አዟል፡፡ ችሎቱ ጉዳዩን ለማየት ለማክሠኞ፤ ኅዳር 15 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ታዬ በእስር ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሠት እንደተፈጸመባቸው የሚገልጽ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ 5፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2027 APEX ባለ አምስት ኮከብ ዓለማቀፍ አየር መንገዶች አንዱ ኾኖ ተመረጠ። አየር መንገዱ በአፍሪካ የAPEX ምርጥ አየር መንገድ (Best Overall Airline in Africa) የተባለውን እውቅና ማግኘቱንም ማምሻውን አስታውቋል። እነዚህ የእውቅና ሽልማቶች በዓለማቀፍ የበረራ መረቡ ላይ ለመንገደኞች ምቹ፣ አስተማማኝ እና አስደሳች የጉዞ ተሞክሮዎችን ለማቅረብ ያለውን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቁ መኾናቸውን አየር መንገዱ ጠቅሷል። 6፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ተለይቻለሁ ባለው የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንበረ ሠላማ ሥር የሚገኘው የአክሱም አገረ ስብከት ማኅበረ ቅዱስ ያሬድ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትግራይ፤ በትግራይ የሚገኙ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት የጥቃት ዒላማ ሊኾኑ እንደሚችሉ ፍንጭ የሚሠጥ መግለጫ በባለአደራ አስተዳደሩ የኮምኒኬሽን ኃላፊ ዳሙራ የሕያ በኩል ተሠጥቷል በማለት ወቀሠ። ዳሞራ፤ የሕወሓት ኃይሎች በቤተክርስቲያናትና ገዳማት ውስጥ መሽገዋል በማለት የሠጡትን መግለጫ ጉዳዩ የተመለከተው የባለአደራ አስተዳደሩ ተቋም ማብራሪያ እንዲሠጥበትና እርማት እንዲያደርግ አገረ ስብከቱ ጠይቋል። የሃይማኖት ተቋማትንና የኃይማኖት መሪዎችን ዒላማ ሊያስደርጉ የሚችሉ ኃላፊነት የጎደላቸው መግለጫዎች የሠጡ አካላት በሕግ እንዲጠየቁና ከኃላፊነት እንዲነሱም አገረ ስብከቱ ጥሪ አቅርቧል። 7፤ የባሕረ ሠላጤው የትብብር ካውንስል፤ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ላይ ከፍቷል ያለውን በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄድ ዘመቻ አወገዘ። ካውንስሉ፤ ኡምሬቶች ቀጠናዊና ዓለማቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲሠፍን ቁልፍ ሚና የምትጫወት አገር ናት ብሏል። ካውንስሉ የሶማሊያን መንግሥት ድርጊት ያወገዘው፣ ኤምሬቶች ከሶማሊያ ግዛቶች ጋር በወደብና ጸጥታ ዙሪያ የተናጥል ስምምነቶች ላይ በመድረስ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጥሳለች በማለት የኤምሬቶችን አምባሳደር ባባረረና አቡዳቢ የሚገኙ አምባሳደሩን በጠራ ማግስት ነው። ኤምሬቶችም፤ የሶማሊያ ውሳኔ ውጥረትን የሚያባብስ እና ትብብርን የሚያዳክም ነው በማለት የአምባሳደሯን መባረር አውግዛለች። እንዲሁም፤ 1፤ ዋልያ መጽሐፍት “ሥነጥበብ እና ሳይንስ” በሚል ርዕስ የሐሳብ መድረክ አዘጋጅቷል። ቅዳሜ ኅዳር 12 ቀን በሚካሄደው በዚህ መድረክ ላይ፣ ዶ/ር ገረመው ፈይሳ በተጋባዥ እንግድነት ተገኝተው ሙያዊ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ። መርሐ ግብሩ አራት ኪሎ በሚገኘው የዋልያ መጽሐፍት አዳራሽ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል። 2፤ ቅዳሜ ኅዳር 12 ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው የ"ነገረ መጽሐፍት" ውይይት ላይ ሀብቴ ጀቤሳ (ዶ/ር) በእንግድነት ተጋብዘዋል። ለውይይት የተመረጠው "ቀንጨራነት እና ድኽነት በኢትዮጵያ" የተሠኘ መጽሐፍ ነው። ውይይቱ የሚካሄደው፣ ቀበና አካባቢ በሚገኘው የማኅበራዊ ጥናት መድረክ አዳራሽ ነው። 3፤ 21ኛው የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የፊልም ፌስቲቫል "50 ፊልሞች በ50 ብር' በሚል ርዕስ ከኅዳር 6 እስከ 13 ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው የሕፃናትና ወጣቶች የሲኒማ ኮምፕሌክስ ቀጥሏል። በፌስቲቫሉ ላይ ነገ ቅዳሜ ኅዳር 12 ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ሐሙስ፤ ኅዳር 10፤ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሞያሌውን ግጭት ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በደረሱ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ተደራዳሪዎች ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት ተኩስ እንደከፈቱ ዋዜማ ሠምታለች፡፡ የክልሎች አመራሮች በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ከሞያሌ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ "መዶሚጎ" በተባለ ቦታ በመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ ማክሰኞ'ለት መምከራቸውንና ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን ምንጮች ነግረውናል። ተደራዳሪዎቹ ላይ ተኩስ የተከፈተው፤ ከካምፑ በወታደሮች ታጅበው ከወጡ በኋላ ነበር ተብሏል። በጥቃቱ በሦስት ወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱን ምንጮች ገልጸውልናል፡፡ የተኩስ አቁም ውይይቱ በመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮችና ከሁለቱ ክልሎች በተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች አስተባባሪነት መካሄዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የሚውለበለብ ባንዲራ ጉዳይ ግን በይደር እንደተተወ ተረድተናል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ምሽት ድረስ የሠዎችና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በከተማዋ እንደሌለና በርካታ የንግድ ቤቶችም እንደተዘጉ መኾኑን ሠምተናል፡፡ በተያያዘ፤ በኬንያ ፓርላማ የሰሜናዊቷ ማንዴራ ግዛት ተወካይ የኾኑት አብዱል ሐሮ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የሞያሌውን ግጭት ላንድ ወር ገደማ ሳያስቆም ቀርቷል በማለት ተችተዋል። ኾኖም ፌዴራል መንግሥቱ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አመራሮች ግጭቱን እንዲያቆሙ አስማምቷል መባሉ አስደሳች ዜና መሆኑን አብዱል ገልጸዋል። አብዱል፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለልተኛ አካል ሆኖ ከተማዋን ከሁለት የሚከፍለውን መንገድ ቢቆጣጠር እንደሚሻል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተያየት ሠጥተዋል። 2፤ በባድመ ከተማ በተፈጸመ የአየር ጥቃት የ5 ሠዎች ሕይወት ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። ከትላንት እኩለ ቀን ጀምሮ በከተማዋና ዙሪያዋ ተከታታይ የአየር ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱት የኤርትራ እና የሕወሓት ኃይሎች ባንድ በኩል እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በከባባድ መሣሪያዎች የታገዙ የተኩስ ልውውጦች እስካሁንም መቀጠላቸውንና የጦር መሳሪያ ክምችቱም ተጠናክሮ መቀጠሉን እንደተመለከቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። 3፤ ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን፤ በትግራይ ክልል ከ7 ሺሕ 200 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀዋል አለ። ኮሚሽኑ፤ በትግራይ ክልል ብቻ ከ47 ሺሕ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ መርሃ ግብሩ ለማለፍ መመዝገባቸውን ገልጧል፡፡ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና መልሶ የማዋሃድ መርሃ ግብሩ ከፍተኛ የገንዘብና የሎጂስቲክስ ሀብት እንደሚጠይቅ የጠቀሠው ኮሚሽኑ፤ ለጋሽ አገራትና ዓለማቀፍ አጋሮች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡ 4፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሸባማይልስ በተሠኘው የደንበኞች የዲጂታል ፕሮግራሙ ላይ ሰሞኑን የተፈጸመ የሳይበር መረጃ ጥሠት ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። አየር መንገዱ በሳይበር ጥቃቱ ላይ ምርመራ መጀመሩን ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሠው እንደነገሩት ሮይተርስ ዘግቧል። አየር መንገዱ በፕሮግራሙ ላይ "መጠነኛ" ጥቃት እንደተፈጸመና የተወሠኑ የደንበኞች መረጃዎች ሳይጋለጡ እንዳልቀሩ ጠቅሶ፤ የደንበኞች የፋይናንስ መረጃዎች ስለመጋለጣቸው የሚያሳይ መረጃ ግን እንደሌለ ትናንት ለደንበኞቹ በኢሜል መልዕክት ልኮ ነበር። 5፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ በሮበርት ማካርቲ እና በአሜሪካው ቶሌዶ ሙዚየም ትብብር ከኢትዮጵያ የተወሠዱ አምስት ጥንታዊ ቅርሶችን ተረከበ። የቅርስ ርክክቡ በዚሁ የረጅም ጊዜ የቅርስ ማስመለስ ማዕቀፍ የተከናወነ የመጀመሪያው ርክክብ ነው። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ተጨማሪ ቅርሶች ከማካርቲ ስብስብ ለቶሌዶ ሙዚየም የተሠጡ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚተላለፉ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጧል። አምስቱ ቅርሶች፤ በሥዕሎችና በጌጣጌጥ ያሸበረቁ ሁለት የ15ኛው ክፍለ ዘመን የብራና ጽሑፎችና ከ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በነበረው ጊዜ የተሠሩና ጽሑፍ የተቀረጸባቸው ሦስት የብረት መስቀሎች ናቸው ተብሏል። 6፤ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ቻግኒ ከተማ፣ ሕገወጥ የነዳጅ ዝወውር ወንጀል ሲፈጽም የነበረን ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል የጸጥታ ኃይሎች ዛሬ ረፋዱ ላይ በከፈቱት ተኩስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። ሟቹ ከድርጊቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውና መንገድ ላይ ሲጓዝ የነበረ ግለሠብ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። ተሽከርካሪው በሰዓቱ ከተፈቀደለት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንከር በተጨማሪ፣ ሌላ ታንከር በተሽከርካሪው ላይ አስገጥሞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል። 7፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ያስገባቸውን 500 ኢትዮጵያዊያን ለመመለስ እንደተቸገረ ተሠማ። ስደተኞቹን መመለስ ያልተቻለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተባባሪ ባለመኾኑ እንደኾነ የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። ስደተኞቹን ወደ አገራቸው መመለስ የሚቻለው፤ የአገራቸው መንግሥት ዜግነታቸውን ማረጋገጥ ሲችልና የጉዞ ሠነዶችን ሲያዘጋጅ ብቻ ነው በማለት የኢምግሬሽን ባለስልጣናት መናገራቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። 8፤ ሶማሊያ፤ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች አምባሳዶር በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወጡ አዘዘች። ሶማሊያ፤ አቡዳቢ የሚገኙ አምባሳደሯንም ጠርታለች። ይህን ርምጃ የወሠደችው የግዛት አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ መሆኑን ሶማሊያ ገልጣለች። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ኢምሬቶች ያለ ፌዴራል መንግሥቱ ይሁንታ ከግዛቶች ጋር የወደብ ስምምነት ውስጥ በመግባት በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች በማለት ከትናንት ወዲያ ክስ አቅርበው ነበር። የሶማሌላንድ መንግሥት በበኩሉ፤ ሶማሌላንድ ከየትኛውም አገር ጋር በምታደርገው የውጭ ግኑኝነት ላይ ሶማሊያ አንዳችም ሕጋዊ ሥልጣን የላትም ሲል ዛሬ ምላሽ ሠጥቷል። እንዲሁም፤ 1፤ በዶ/ር ደቻሳ አበበ የተዘጋጀው "አዲስ አበባ (1879-1967)፤ የከተማነትና የከተሜነት ታሪክ" የተሠኘው አዲስ መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀርቧል። መጽሐፉ የመዲናዋን የ88 ዓመታት የከተሜነት ታሪክ የሚዳስስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ አሳታሚነት ለኅትመት በቅቷል። 2፤ "የባስሊቆስ ዐንባ" እና "ጻማ" መጽሐፍት ደራሲ ትዕግሥት ታፈረ ቅዳሜ ኅዳር 12 ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከመጽሐፏ አንባቢዎች ጋር የምትገናኝበት የመጽሐፍ ፊርማ መርሃ-ግብር ለገሐር በሚገኘው ጃፋር መጽሐፍት መደብር ይካሄዳል። [ዋዜማ]
Open in Telegramዩክሬይን የሩሲያ ፊልም በኣዲስ አበባ እንዳይታይ ጠየቀች በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው 21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌሲቲቫል ላይ እንዲቀርብ የተመረጠ የሩሲያ ፊልም ለህዝብ እንዳይታይ ከዩክሬይን መንግስት ለፌስቲቫሉ አዘጋጆችና ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መቅረቡን ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ተረድታለች። ዝርዝሩን ያንብቡት -- cutt.ly/aySq56zF
Open in Telegramለቸኮለ፤ ረቡዕ፤ ኅዳር 9፣ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኤርትራ ሠራዊት ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ባድመ ተመልሶ መግባቱን ዋዜማ ሠምታለች። በትግራይ በድጋሚ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ፤ የኤርትራ ጦር ከባድመ ወደኋላ አፈግፍጎ እንደነበር ይታወሳል። የኤርትራ ጦር በርካታ ሠራዊትና የጦር መሳሪያ "ገማህሎ" እና "ሠምበል" ወደተባሉ አካባቢዎች ማስገባቱን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የሕወሓት እና የአፋር ውስን ኃይሎችም ከኤርትራ ሠራዊት ጋር እንደሚንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ በርካታ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ከተሞች እየሸሹ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል፤ ገማህሎ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎች፤ በአካባቢው የሠራዊትና የጦር መሳሪያዎች እንቅስቃሴ በስፋት ተመልክተናል ብለዋል። የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ስላለው ሁኔታ የሚነገረው ነገር የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ኾኖም በድንበር አካባቢ በሁለቱ አገራት መካከል ቀጥተኛ ግጭት ስለመካሄድ አለመካሄዱ የማነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በቀጥታ ምላሽ እንዳልሠጡ ዘገባው ጠቅሷል። ይሁን እንጂ በድንበር አካባቢ በሁለቱ ጦር ሠራዊቶች መካከል አልፎ አልፎ ውጊያ ሲካሄድ እንደቆየ ለትግራይ የሰላም ኃይል ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደነገሩት ሮይተርስ በዘገባው አካቷል። 2፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ ወረዳ ልዩ ስሙ “አምስት ጥምዝ” በተባለ ቦታ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ትናንት በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ረዳት ኢንስፔክሮችን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት የክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ አባላት መገደላቸውን ዋዜማ ከክልሉ ፖሊስ ምንጮች ሠምታለች። ጥቃቱ የተፈጸመው፤ በቤሮ እና በሱሪ ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከሚቀሠቀሠው የብሔረሰቦች ግጭት ጋር በተያያዘ ለጸጥታ ሥራ በተሸከርካሪ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የአድማ ብተና የአንድ ሻምበል አባላት ላይ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል፡፡ የአድማ ብተና የፖሊስ አባላቱ አስከሬን ወደየትውልድ አካባቢያቸው ተወስዶ፣ በዛሬው ዕለት ቀብራቸው ተፈጽማል ተብሏል። 3፤ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት ሕወሃት፤ መንግሥት በአፋር ክልል አዋሽ አርባ ከ600 በላይ የትግራይ ተወላጆችን በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ አስሮ ይገኛል በማለት ከሠሠ። ቡድኑ፤ አንዳንዶቹ ታሳሪዎች ወዳልታወቁ ሥፍራዎች እንደተወሠዱ እንደሚያውቅ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጧል። ዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዎች እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጣልቃ ገብተው ይህንኑ እስር ያስቆሙ ሲል ቡድኑ ጠይቋል። መንግሥት የሁሉንም ታሳሪዎች ማንነትና በትክክል የታሠሩበትን ቦታ እንዲያሳውቅ፣ ታሳሪዎች በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙ እንዲፈቅድ እንዲሁም ቡድኑ "በዘፈቀደ በማንነታቸው ተለይተው" ታስረዋል ያላቸው እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ቡድኑ ጥሪ አድርጓል። መንግሥት የትግራይ ተወላጆችን አዋሻ አርባ ውስጥ ስለማሠሩ ከዚህ ቀደም ያለው ነገር የለም። 4፤ አሜሪካ፤ ትግራይ በኢኮኖሚ እንድታብብ እና በዲሞክራሲ እንድትራመድ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጠች። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፤ ትናንት ከሌሎች አገራት አምባሳደሮች ጋር በትግራይ ባደረጉት ጉብኝት ከባለአደራ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሠፋ አብርሃ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከበታች የአስተዳደሩ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ ለትግራይ የኢኮኖሚ እድገት መረጋጋት፣ አካታችነት፣ እና ጠንካራ ተቋማት ቁልፍ እና እድል ፈጣሪ መሳሪያ እንደሆኑ ገልጸዋል። አሜሪካ በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ማኅበረሰቦች የነፍስ አድን እርዳታ እንዲዳረስ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላትና ከባለአደራ አስተዳደሩ፣ ከፌደራል መንግሥቱና ከዓለማቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ትግራይን ለመደገፍ እና ባጠቃላይ በግጭት የተጎዳው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ወደፊት እንዲራመድ ለማስቻል ዝግጁ መሆኗን ማሲንጋ አረጋግጠዋል። 5፤ የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው የወልቃይትና ኹመራ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን በሦስት ወራት ውስጥ የመመለስ ሥራ እንደሚጀመር የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ባለአደራ አስተዳደሩ ለአካባቢው በአስተባባሪነት የሾማቸው ዳንኤል ነጋሽ ይህን የተናገሩት፤ የተመድና የአምባሳደሮች ልኡካን ትናንት የመቀለ 70 ካሬ የተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያን በጎበኘበት ወቅት መሆኑን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ዓለማቀፍ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች የሚሠጡት ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሠ በመሄዱ የተፈናቃዮች ችግር መባባሱን አስተባባሪው መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። አስተባባሪው፤ ዓለማቀፍ አጋር ድርጅቶችም በኹመራ ቢሮ በመክፈት ተፈናቃዮችን በመመለስ ረገድ አጋር ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል ተብሏል። 6፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር፤ የብር ግሽበት ፍጥነት መቀነሱና በባንኮች የዶላር መግዣና መሸጫ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት መጥበቡ በአገሪቱ ውስጥ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ መኖሩን አያሳይም አለ። ማኅበሩ፤ ዋና ትኩረቱ በመደበኛው እና በትይዩው የውጭ ምንዛሬ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት መስፋቱ መሆኑን ዛሬ ባወጣው አዲስ ሪፖርት ጠቅሷል። በሁለቱ የምንዛሬ ገበያዎች መካከል ልዩነቱ የሠፋው፣ የትይዩ ገበያው የምንዛሬ ተመን ከመደበኛው የምንዛሬ ተመን አንጻር ከነሃሴ ወዲህ በፍጥነት በመጨመሩ መሆኑን ማኅበሩ ገልጧል። በሌላ በኩል፤ በባንኮች መካከል ያለው የዶላር መግዣ ዋጋ ከ5 ብር ከ30 ሳንቲም ወደ 2 ብር ከ11 ሳንቱም እንዲሁም የመሸጫ ዋጋ ከ5 ብር 41 ሳንቲም ወደ 2 ብር ከ15 ሳንቲም መጥበቡንና ሆኖም ይህ በባንኮች መካከል ጠንካራ ውድድር መኖሩን ወይም ሁሉም ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የማግኘት እድላቸው ተቀራራቢ መሆኑን አያመለክትም- ብሏል ማኅበሩ። 7፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሰሜን ጃናሞራ ወረዳ ሠላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት፤ ከዛሬ ረቡዕ ኅዳር 9 ጀምሮ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ኃይል አባላት ውጪ የትኛውም ሰው የጦር መሳሪያ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ክልከላ ጣለ። ነፍጥ አንስተው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ታጣቂዎች የክልሉ መንግሥት በሠጠው ምሕረት መሠረት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ መፍቀዱን ተከትሎ፤ የወረዳው መቀመጫ መካነ ብርሃን ከተማን ጨምሮ በየቀበሌው ከፍተኛ የሕገ ወጥ መሳሪያ እንቅስቃሴ እንደሚስተዋል ጽሕፈት ቤቱ ገልጧል። 8፤ ስምረት ፓርቲ፤ ዘጠኝ የአመራር አባላቱን እንዳገደ አስታወቀ፡፡ ዘጠኙ የአመራር አባላት የታገዱት፤ የትግራይን መሠረታዊ አጀንዳዎች ለድርድር በማቅረብ በግል ጥቅም ላይ ተጠምደዋል ተብለው መሆኑን ፓርቲው ገልጧል። ሌሎች ሁለት የፓርቲው ምክር ቤት አባላት ደሞ የስንብት ጥያቄ አቅርበው ጥያቄያቸው በሙሉ ድምፅ ተቀባይነት በማግኘቱ እንደተሠናበቱ ፓርቲው አስታውቋል። ፓርቲው፤ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጠራና በመላው ትግራይ ጽሕፈት ቤቶች በመክፈት የሰው ኃይል እንደሚመድብም አስታውቋል። እንዲሁም፤ 1፤ የሠዓሊ ሐሮን ሱለይማን "ውብ አዲስ 3" የተሠኘ የግል የሥዕል ዓውድ ርዕይ ከነገ ኅዳር 10 እስከ 27 ፒያሣ በሚገኘው ጣይቱ የባሕልና የትምህርት ማዕከል ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።[ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ! ማክሰኞ፣ ኅዳር 8፣ 2019 ዓ፤ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር በሚዋሠንበት ኢሮብ ወረዳ አይጋና ወረኣትለ አካባቢዎች የሕወሃት ኃይሎችና የኤርትራ ጦር በጋራ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ላለፉት ሁለት ቀናት መዋጋታቸውን ዋዜማ ሠምታለች፡፡ኾኖም ዛሬ ውጊያው እንደረገበና ውጥረት ግን እንደሠፈነ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል። በሌላ በኩል፤ ቅዳሜ ኅዳር 5 ቀን በወረዳው "ወረኣትለ" ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ጉዳት የደረሠበትን የውጪ የእርዳታ ድርጅቶች የገነቡት የሕዝብ ትምህርት ቤት፤ የሕወሃት እና የኤርትራ ኃይሎች በማረፊያነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ሠምተናል፡፡ ከወረዳው አገረ-ለኮማ እና ሠበያ ተነስቶ እስከ ዓዲግራት የሚወስደው የትራንስፖርት መስመር ከተዘጋ ከአንድ ሳምንት በላይ ማስቆጠሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተያያዘ፤ በክልሉ ሰሜን ምዕራባዊ ዞን ከዛሬ ጀምሮ ባጃጅ እና ሞተር ሳይክሎች ከምሽት 12 ሰዓት በኋላ እንዲሁም ነዋሪዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ የሠአት እላፊ ገደብ ተጥሏል፡፡ በዞኑ በማንኛውም ቦታ እና ሰዓት ከአራት በላይ ሰዎች ባንድ ላይ እንዳይሠበሠቡ እገዳ ተጥሏል። 2፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ ባለፈው ወር በቀድሞው ምስራቅ አርሲ ዞን ሸርካ ወረዳ ለተገደሉት 48 ሰዎች ሃላፊነት ወሠደ። የጦር መሳሪያ የታጠቀ አንድ ነዋሪ አንዲት የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ መንገድ ላይ መግደሉን ተከትሎ፣ ተዋጊዎቹ ርምጃ መውሠዳቸውንና በዚሁ ወቅት "የትርፍ ጊዜ ተዋጊ" ያላቸው ነዋሪዎች መገደላቸውን ቡድኑ ገልጧል። የቡድኑ ተዋጊዎች በወሠዱት ርምጃ የተገደሉት መንግሥት ትዕዛዝ ሲሠጣቸው የታጠቁትን መሳሪያ ይዘው የሚዘምቱ ታጣቂ ነዋሪዎች እንጂ ሙሉ በሙሉ ሲቪሎች አይደሉም ሲል ቡድኑ ባወጣው መግለጫ ገልጧል። በወቅቱ ስንት የታጣቁ ሰዎች እንደተገደሉ ግን ቡድኑ ያልገለጠ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች መሳሪያ የታጠቁት የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ መሆኑን ግን ጠቅሷል። ኢሰመኮ፤ 28 የጸጥታ እና የአካባቢ ሚሊሻ አባላትን ጨምሮ 48 ሰዎች የተገደሉት፣ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች እና ከመንግሥት ጸጥታ መዋቅር ጋር ግንኙነት ባላቸው የታጠቁ ግለሰቦች መሆኑን መግለጡ ይታወሳል። 3፤ ተመድ፤ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን ወታደራዊ ውጥረት ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጠ። የድርጅቱ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት ድርጅቱን በጥልቀት እንዳሳሰበውና ውጥረቱ እንዳይባባስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። የድርጅቱ ልዩ ልዕኮቹ ውጥረቱን ለማርገብ ከሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ ብለዋል። የድርጅቱ የሱዳን መልእክተኛ ፔካ ሃቪስቶ በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር በቅርቡ ወደ አቡዳቢ አቅንተው ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተመካሪው ነበር። 4፤ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ገበያ ከመግባታቸው በፊት በተቆጣጣሪ አካል ክትትል ሥር ለመሞከር የሚያስችል መመሪያ ይፋ አደረገ፡፡ ዋዜማ የተመለከተችው አዲሱ መመሪያ፤ የፋይናንስ ተቋማትና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ያላቸው አካላት ምርቶቻቸውን በተወሠነ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲሞክሩ ይፈቅዳል። ባንኩ ለሙከራው ከሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ከሚከለክሉና ከደንበኞች ከለላ፣ የግል መረጃ ደኅንነት እና የሳይበር ደኅንነት ሕጎች ውጪ የተወሠኑ የቁጥጥር ሕጎችን እንደሚያላላ ገልጧል። መመሪያው፤ አገልግሎቱ ወይም ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል ያልነበረ ወይም ነባሩን አሠራር በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል መሆን እንዳለበት አመልካቾች ማረጋገጫ መስጠት እንዳለባቸው ደንጓል፡፡ አመልካቾች መክፈል ያለባቸውን ተመላሽ የማይደረግ የአገልግሎት ክፍያም መመሪያው ወስኗል። 5፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ገንዘብ ሚንስቴር የፌዴራል ጠበቆች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ ያወጣውን መመሪያ ሻረ። የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የኾኑ የግብይት ፈጻሚዎች ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ሆኖም ስምንት ጠበቆች፤ መመሪያው የደረጃ "ለ" ግብር ከፋይ ጠበቆችን ጨምሮ የሙያ አገልግሎት ሠጪዎች ዓመታዊ ገቢያቸው ከ2 ሚሊዮን ብር በታች ቢሆንም ተጨማሪ እሴት ታክስ መክፈል አለባቸው ማለቱ አዋጁን ይጥሳል በማለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር። ችሎቱ፤ የሂሳብ መዝገብ መያዝን እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ መስፈርት መቁጠር ግብር ከአዋጁ ዓላማ ጋር ይጋጫል በማለት ወስኗል። 6፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዲስ ስታንዳርድ የበይነ መረብ ሜዲያ ላይ ያቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ አደረገ። የአዲስ ስታንዳርድ አሳታሚ ባለሥልጣኑ የአዲስ ስታንዳርድን ምዝገባ ከመሠረዙ በፊት የጽሑፍም ሆነ የቃል ማስጠንቀቂያ እንዳልሠጠና ለቀረበበት ክስ ምላሽ እንዳይሠጥ ዕድል እንደነፈገ አቤቱታ አቅርቦ ነበር። ባለሥልጣኑ በበኩሉ፤ በአስተዳደር ስነ-ሥርዓት ሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ የማይካተት ነጻ ዴሞክራሲያዊ ተቋም እንደሆነ በመግለጽ መቃወሚያ አቅርቦ የነበረ ሲኾን፤ ችሎቱ ግን ባለሥልጣኑ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ኾኖ የተቋቋመ ነው ብሏል። ፍርድ ቤቱ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ክርክሩ እንዲቀጥል ለኅዳር 30 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል። 7፤ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን አሥተዳደር ጓንጓ ወረዳ "በጽንፈኛ ኃይሎች" ታግተው የነበሩ ሦስት ንጹሃን በጸጥታ አካላት ጥረትና በማኅበረሰቡ ርብርብ መለቀቃቸው ተሠማ። እገታው ልዩ ቦታው "ራንች" ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሲጓዙ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደተፈጸመ የቡለን ወረዳ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ባሠራጨው መረጃ ገልጧል። ነዋሪዎቹ የታገቱት፤ ባለፈው እሁድ ኅዳር 6 ከቻግኒ ከተማ ወደ አጎራባቹ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ እንደነበር የቡለን ተገልጧል። እንዲሁም፤ 1፤ የሠዓሊ ኢሳቅ ተወልደ አዳዲስ የሥዕል ሥራዎች የሚቀረቡበት "ፍለጋ" የተሠኘ የግል የሥዕል ዐውደ ርዕይ ነገ ኅዳር 9 ቀን ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በፈንድቃ የባሕል ማዕከል ለተመልካቾች ክፍት ይሆናል። ይኸ ዐውድ ርዕይ፤ እስከ ታህሣሥ 5 ቀን በዕይታ ላይ ይቆያል። 2፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባሕል ማዕከል የተዘጋጀውና ደራሲ ቡርሃን አዲስ የክብር እንግዳ በመሆን የተጋበዘበት ሳምንታዊ ዝግጅት ነገ ረቡዕ ኅዳር 9 ቀን ከ11 ሰዓት ከ30 ጀምሮ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው የባሕል ማዕከል ይካሄዳል። መግቢያው በነፃ ነው። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ! ሰኞ፤ ኅዳር 7፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የገንዘብ ሚንስቴር ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ጭነው የተገኙ የጭነት ተሸከርካሪዎችን መንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ረቂቅ መመሪያ አወጣ። መመሪያው፤ ሕገወጥ የጭነት ዕቃዎች ከጠቅላላው ጭነት በክብደት ወይም በዋጋ ቢያንስ 50 በመቶ ከሸፈኑ ወይም የተሽከርካሪው ባለንብረት በተደጋጋሚ ጥፋቶች ውስጥ ከተገኘ የዕቃው ክብደት ዋጋ ግምት ውስጥ ሳይገባ ተሽከርካሪው በቀጥታ እንደሚወረስም በመመሪያው ላይ ሠፍሯል፡፡ ባለቤቱ በድርጊቱ ላይ ተሳትፎ እንደሌለውና አሳማኝ የማቅለያ ምክንያት ካቀረበ፤ የተሽከርካሪውን ወቅታዊ የገበያ ዋጋ 50 በመቶ የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል መመሪያው አማራጭ አስቀምጧል። 2፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ከተማ አቅራቢያ ኮኪት ድል በር በተባለ አካባቢ በመንግሥትና በፋኖ ኃይሎች መካከል ዛሬ ከንጋት ጀምሮ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት እንደነበር ዋዜማ ሠምታለች፡፡ውጊያውን ተከትሎ፤ በመተማ ከተማ የንግድ ቤቶች ተዘግተው መዋላቸውንና የተሸከርካሪ እንቅስቃሴም መስተጓጎሉን ነዋሪዎች ነግረውናል። በመተማ ወረዳ አዲስ አለም ቀበሌ በተመሳሳይ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪዎች፤ በውጊያው ወቅት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎች እና በውጊያው ተሳታፊ የሆኑ አካላት እንደተገደሉ ገልጸዋል። በአካባቢው ባለው ግጭትና ውጥረት ሳቢያ ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር መጨመሩንም ተረድተናል። 3፤ የትግራይ ክልል የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፤ በክልሉ ተቋርጦ የነበረው የነዳጅ አቅርቦት በድጋሚ በመጀመሩ በሥራ ላይ የቆየው የነዳጅ መመሪያና አሠራር እንዲቆም መወሠኑን ገለጠ። ቢሮው፤ ከኅዳር 8 ጀምሮ ነዳጅ በተለይ ወደ መቀለ ከተማ መግባት እንደሚጀምር ገልጧል። በመቀለ የሚገኙ ሁሉም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚንስቴር ባወጣው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ መሠረት ብቻ ከነዳጅ ማደያዎች ግዥ እንዲፈጽሙ ቢሮው አሳስቧል። የነዳጅ አቅርቦቱ ወደ ሌሎች ከተሞች መግባት በሚጀምርበት ጊዜም ይሄው አሠራር ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል። 4፤ ከ300 በላይ የሚሆኑ የስምረት ፓርቲ የዞን፣ የወረዳ እና የከተሞች አመራሮችና አባላት ራሳቸውን ከፓርቲው ማገለላቸውን አስታወቁ። አመራሮቹና አባላቱ ከፓርቲው ራሳቸውን ያገለሉት፤ በፓርቲው የአመራር ክፍተት በመሠላቸታቸው፣ በትውልድ ቦታ እና ግለሰባዊ ሠንሰለቶች ላይ የተመሠረቱ ብልሹ አሠራሮች በመንሠራፋታቸው እና በሕገ-ደንቡ መሠረት ፓርቲውን በአግባቡ የሚመራ አካል ባለመኖሩ እንደኾነ ጠቅሠዋል፡፡ ግለሰቦቹ፤ ኬሪያ ኢብራሂምንና የመቀለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረን ጨምሮ ከቀናት በፊት ራሳቸውን ከፓርቲው ያገለሉ 11 ከፍተኛ አመራሮች የሚያሳልፏቸውን መመሪያዎች ብቻ ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል። የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ በበኩሉ፤ ግለሰቦቹ ፓርቲውን ለማፍረስ ከሌሎች አካላት ተልዕኮ ተቀብለዋል በማለት ከሷል፡፡ 5፤ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እንደተሾሙ ተሠማ። አደም የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት፤ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ጀነራል ይልማ መርዳሳ ምትክ ነው። ጀነራል ይልማ የኩባንያውን የዳይሬክተሮች ቦርድ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከመንፈቅ ያህል ከመሩ በኋላ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውንና በምትካቸው አደም ፋራህ እንደተሾሙ መስማቱን ጠቅሶ የዘገበው ፎርቹን ነው። ጀነራል ይልማ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት፣ ግርማ ዋቄን በመተካት እንደነበር አይዘነጋም። አደም ይህን ኃላፊነት የተረከቡት፣ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተመደበለት ግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በተጀመረ ማግስት ነው። አየር መንገዱ አዲስ የቦርድ ሰብሳቢ እንደተሾመለት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በይፋ ያለው ነገር የለም። 6፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ሽረ ከተማ መደበኛ በረራ እንደገና ኅዳር 8 ቀን እንደሚጀምር ማምሻውን አስታወቀ። አየር መንገዱ ወደ ሽረ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ በጊዜያዊነት ያቋረጠው፣ የሕወሃት ኃይሎች በመስከረም አጋማሽ ገደማ የመቀለ፣ አክሱም እና ሽረ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በኃይል መያዛቸውን ተከትሎ ነበር። 7፤ አሜሪካ፣ በሶማሊያ ለተሠማራው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ያቋረጠችውን የገንዘብ ድጋፍ እንደምትቀጥል ገለጠች። አሜሪካ፤ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ እና የተመድ ተልዕኮ ላንድ ዓመት ቆይታቸው እንዲራዘም እንደምትፈልግ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል አስታውቃለች። አሜሪካ ለተመድ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ ሠጪ ተልዕኮ የገንዘብ ድጋፍ እንደምታቋርጥ ከጥቂት ወራት በፊት መግለጧ ይታወሳል። አሜሪካ ለተመድ ተልዕኮ የምትሰጠውን ድጋፍ ለማቋርጥ የወሠነችው፣ የሶማሊያ መንግሥት አልሸባብን በመዋጋት ረገድ አዎንታዊ እመርታ ሊያስመዘግብ እንዳልቻለ እና የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ ማጣቱን በመጥቀስ ነበር። እንዲሁም፤ 1፤ ፕሪስቴጅ አዲስ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው መሠናዶ ድምጻዊ ኃይሉ አመርጋ እና ተዋናይት የትናየት ታምራትን በእንግድነት ጋብዟል። ዝግጅቱ ማክሰኞ ኀዳር 7 ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው ሳችም ማዕከል ይካሄዳል። መግቢያው በነፃ ሲሆን፤ ዝግጅቱን ለመሳተፍ አስቀድሞ መመዝገብ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል። 2፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ዙሪያ ትኩረት ያደረገው "ኢትዮፒክስ፤ ሪቮልት ኦቭ ዘ ሶል" የተሠኘው ዘጋቢ ፊልም ረቡዕ ኅዳር 9 ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በፈንድቃ የባሕል ማዕከሉ ለዕይታ ይቀርባል። በዕለቱ ከዘጋቢ ፊልም ዕይታ ባሻገር፤ በደስታ የጃዝ ባንድ አባላት የጃዝ ሙዚቃዎች ለታዳሚዎች እንደሚቀርቡ ተገልጿል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ! ቅዳሜ፣ ኅዳር 5፤ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ የቀድሞውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ፣ የቀድሞውን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን ጨምሮ ዛሬ 32 ግለሰቦችን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አድርገው ሾሙ። ባለፈው መስከረም ከሚንስትርነት የተነሱት የቀድሞው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትር ካሳሁን ጎፌ፣ የቀድሞው የትራንስፖርትና ሎጄስቲክስ ሚንስትር ዓለሙ ስሜ እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ኤርጎጌ ተስፋዬም በተመሳሳይ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው ተሹመዋል። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር አባይ እና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ዮናስ አዳዬ እና አምባዬ ኦጋቶም ከተሾሙት መካከል ይገኙበታል። 2፤ በኬንያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የኢትዮጵያ መንደር ሴቶችንና ሕጻናትን ጨምሮ ስድስት ሰላማዊ ሰዎች ዛሬ ጧት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት እንደተገደሉ ተሠማ። መልካምሪ በተባለ ቦታ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ፣ በአጎራባች የኬንያዋ ማንዴራ ግዛት ውጥረት መስፈኑን ደይሊ ኔሽን ዘግቧል። ኾኖም ጥቃቱ ሞያሌ ላይ ከሚካሄደው ግጭት ጋር የተያያዘ ነው ብለው እንደማያምኑ የግዛቲቲ የጸጥታ ባለሥልጣናት መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ጥቃቱን በመፈጸም የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ወደ ኬንያዋ ማንዴራ ግዛት ገብተው ከተደበቁ፤ በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ እንደሚመሠረትባቸው የጸጥታ ባለሥልጣናቱ አረጋግጠዋል ተብሏል። በአካባቢው በሶማሊ ጋሪ እና ደጎዲያ ጎሳዎች መካከል ለዓመታት ግጭት ሲካሄድ እንደቆየ የዜና ምንጩ አስታውሷል። 3፤ የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ከፍታ ቦታ ላይ መገኘት ጋር በተያያዘ ለናይጀሪያዊያን ጤናን የተመለከተ የጉዞ ማሳሰቢያ አወጣ። ሚንስቴሩ፤ በአውሮፓዊያኑ 2026 በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ያለፉ 16 ናይጄሪያዊያን የከተማዋ የአየር ሁኔታ ባስከተለባቸው የጤና እክል ሕይወታቸው አልፏል ብሏል። በተለይ የልብ፣ የደም ቧንቧ እና የመተንፈሻ አካላት የጤና እክል ያለባቸው መንገደኞች ከተማዋ ከ7 ሺሕ ጫማ በላይ በኾነ ከፍታ ላይ መገኘቷ የሚፈጥረውን የኦክስጅን እጥረት ከግምት በማስገባት እንዲጠነቀቁ ሚንስቴሩ አሳስቧል። 4፤ የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ በኩል ወደ አገሪቱ ግዛት ገብቷል ያለውን ድሮን ትናንት መትቶ መጣሉን አስታወቀ። የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት፤ ድሮኑን መትቶ የጣለው ብሉ ናይል ግዛት ውስጥ ዳንደሮ በተባለ ቦታ ላይ መኾኑን ገልጧል። ሱዳን፤ ከኢትዮጵያ በተለይም ከባሕርዳር አውሮፕላን ማረፊያ ይነሳሉ ባለቻቸው ድሮኖች ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙባት መሆኑን በመግለጽ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረቧ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፤ ውንጀላውን አስተባብሎ ይልቁንም ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እጇ አለበት በማለት ይከሳል። 5፤ የእስራኤል መንግሥት አገሪቱ ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ የቆዩ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገራቸው በፍቃዳቸው እንዲመለሱ የ3 ሺሕ 500 ዶላር የገንዘብ ሥጦታ አቀረበ። ይህ አሠራር ቀደም ሲል በኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን እና ሱዳናዊያን ስደተኞች ላይ እንዲተገበር ቀርቦ ነበር። አሁን ግን ፕሮግራሙ ሁሉንም የአፍሪካ አገራት ዜጎች እንዲመለከት ሆኖ መቅረቡን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። በፕሮግራሙ ለመታቀፍ ያመለከቱ አመልካቾች፤ ከአገሪቱ እስኪወጡ ድረስ በኢምግሬሽን ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ የሁለት ሳምንት ከለላ ያገኛሉ ተብሏል። እንዲሁም፤ 1፤የገጣሚ አስታወሰኝ ረጋሣ “ልብ በቃኝ አይልም” የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲስ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ በቀጣይ ሳምንት ለንባብ ይበቃል። ገጣሚው ከአምስት ዓመታት በፊት “ወደ ነገ ሒያጅ ነኝና” የተሠኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን አድርሷል። 2፤ “50 ፊልሞች በ50 ብር’ በሚል ርዕስ 21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ከኅዳር 6 እስከ 13 ቦሌ ፍላሚንጐ በሚገኘው የህፃናትና ወጣቶች የሲኒማ ኮምፕሌክስ ይካሄዳል። ለሳምንት በሚቆየው በዚህ ፊልም ፌስቲቫል በሞባይል ስልኮች ብቻ የተሰሩ አጫጭር ፊልሞች ይቀርባሉ ፣ “50 ፊልሞች በ50 ብር’ እንቅስቃሴ (አንድ ሰው በ50 ብር በሚቆርጠው አንድ ትኬት ብቻ 50 የሀገር ውስጥና የውጪ ፊልሞችን ይመለከታል) እንዲሁም የፊልም ገበያ ኤክስፖና ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ዓርብ፣ ኅዳር 4፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ዓዲ ቦኽራይ እና ዓዲ አስመሩ በተባሉ አከባቢዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ ሠራዊቶች መካከል ዛሬ ውጊያ መካሄዱን ዋዜማ ሠምታለች፡፡ በአካባቢው በደኅንነት ሥጋት ምክንያት የሚፈናቀሉ ሠዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱንም ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ በሌላ በኩል፤ ትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራባዊ ዞን ሽራሮ፣ ሠየምቲ እና አድያቦ በተባሉ አካባቢዎች በመንግሥትና በሕወሃት ኃይሎች መካከል ላለፉት ሁለት ቀናት ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ነግረውናል። የኤርትራና የሕወሃት ኃይሎች በጋራ ሲንቀሳቀሱባት ነበር የተባለችው ሽራሮ ከተማ ከአንድ ሳምንት በፊት በመንግሥትና በትግራይ ሠላም ኃይሎች ሥር እንደምትገኝም ነዋሪዎች ገልጸዋል። በአድያቦ ወረዳ ልዩ ስሙ "ዓዲ ካሕሱ" በሚባል አካባቢም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በመንግሥትና በሕወሃት ኃይሎች መካከል ውጊያ መቀጠሉንና የከባድ መሳሪያዎች ድምጽና የጦር ጄቶች እንቅስቃሴ እንደሚስተዋል ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡ በበሽሬ ከተማም ከዛሬ ጀምሮ ከምሽቱ 1 ሰዓት በኋላ ተሸከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች እንዳይንቀሳቀሱ የሰዓት ገደብ ተጥሏል። 2፤ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ በጓሳ፣ ወለላ ባሕር እና ሾለክት በተባሉ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከሠኞ ጀምሮ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ እየተካሄደ መኾኑን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ከሠሰባሠበችው መረጃ አረጋግጣለች፡፡ በውጊያው ከክምር ድንጋይ ከተማ እስከ ንፋስ መውጫ ከተማ ያለው መንገድ ለተሽከርካሪዎች ዝግ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል። ኾኖም ውጊያ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች የመንግሥትም ኾነ የፋኖ ኃይሎች ለረጅም ጊዜ ይዘዋቸው እንደማይቆዩና ሁኔታው ቶሎ ቶሎ እንደሚቀያየር ነዋሪዎች ገልጸዋል። 3፤ ፖሊዮ ቫይረስ በኦሮሚያ ክልል ማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን በአምቦ አካባቢ፣ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በደራሼና ጎፋ ዞኖች ተከሠተ። ቫይረሱ ቀደም ሲል በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ፣ በኑዌር ዞን እና ኢታንግ ልዩ ወረዳ መከሠቱንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጧል። ቫይረሱ በተከሠተባቸውና ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ አምስት ክልሎች ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የሚያካትት የክትባት ዘመቻ ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ እንደሚካሄድ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። በዘመቻው በ120 የአዲስ አበባ ወረዳዎች 884 ሺሕ 323፣ በ81 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወረዳዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ በ276 የኦሮሚያ ወረዳዎች 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን፣ በ91 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወረዳዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ በ61 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወረዳዎች 661 ሺሕ 539 በድምሩ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ለመከተብ ታቅዷል ተብሏል። 4፤ ከ100 ሺሕ በላይ ቤቶችን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በቱሉ ዲምቱ 33 ብሎኮችን እና በአዲስ ከተማ ቅጠል ተራ ዘጠኝ የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ዛሬ በጎበኙበት ወቅት ተናገሩ። በአገር ዓቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ መያዙን የጠቀሱት ዐቢይ፤ ዕቅዱን ለማሳካት በሦስት ዋና ዋና ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። በመዲናዋ ብቻ ከ100 ሺሕ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ግንባታው ሲጠናቀቅ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ዐቢይ ተናግረዋል። በቀጣዮቹ ጊዜያት በመርካቶ አካባቢ "ከሠው ልጅ የመኖሪያ ደረጃ በታች" ሲሉ በገለጧቸው አካባቢዎች መኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ እቅድ መኖሩንም ዐቢይ ጠቁመዋል፡፡ ዐቢይ፤ ገንዘብ ሲገኝ በመርካቶ ግራና በቀኝ የሚገኙ በርካታ ቤቶችን በማፍረስና በማሻሻል የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 5፤ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት፤ ለውጭ ገበያ ካቀረበችው ቡና 1 ነጥብ 16 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጠ። ገቢው የተገኘው፤ ወደ ውጭ ከተላከው 167 ነጥብ 8 ሺሕ ቶን ቡና መኾኑን ባለሥልጣኑ ጠቅሷል። የሩብ ዓመቱ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ24 ነጥብ 6 ሺሕ ቶን እንዲሁም በገቢ የ157 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው ተብሏል። ሦስቱ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻዎች፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጀርመን እና ቻይና መሆናቸውን ባለሥልጣኑ በቅርቡ መግለጡ ይታወሳል። 6፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት ከቀረበ የኃይል ሽያጭና ከተጓዳኝ አገልግሎቶች 31 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል አለ። በሩብ ዓመቱ ከኃይል ሽያጭና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ 27 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ተቋሙ ገልጧል። የሩብ ዓመቱ ገቢ፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ4 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ተብሏል። ከአገር ውስጥ ከተገኘው ገቢ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች 26 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ ሲይዙ፤ የውጭ አገራት 21 ነጥብ 02 በመቶ ድርሻ መያዛቸው ተጠቅሷል። 7፤ በሱዳን ድንበር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ "አርሚ 13" እና "አርሚ 70" የተሠኙ የሕወኃት አባላት ናቸው የተባሉ 27 ታጣቂዎች እጅ መስጠታቸውን መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ። ታጣቂዎቹ ከሱዳ ግዛት በመውጣት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መመለሳቸውን የገለጠው ሠራዊቱ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩሙሩክ ላይ እጃቸውን መስጠታቸውን ገልጿል። ታጣቂዎቹ መነሻቸው አሶሳን የመቆጣጠር ግዳጅ ተሠጥቷቸው እንደነበር የጠቀሠው ሠራዊቱ፤ ከተልዕኮው መጠናቀቅ በኋላ በዶላር ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ተነግሯቸው ነበር በማለት አክሏል። 8፤ የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሠን አስመላሽ ኮሚቴ፣ ሰሞኑን በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በራያ ስድስቱ ወረዳዎች የተቋቋመውን የትግራይ ባለአደራ አሥተዳደር አስመልክቶ የተሠራጨው መረጃ ከኮሚቴው አቋምና ከአውድ ውጭ የተተረጎመ ነው አለ። ኮሚቴው በራያ ወረዳዎች የተቋቋመው የትግራይ ባለአደራ አሥተዳደር በሕጋዊ ምርጫ ያልተመረጠ፣ የአካባቢውን ሕዝብ ነጻና እኩል ተሳትፎ ያላረጋገጠ፣ ራሱን የትግራይ ሠላም ኃይል ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ኃይል ተጽዕኖ ሥር የወደቀና ሕዝባዊ ቅቡልነት የሌለው ነው በማለት ኮኗል። ኮሚቴው፤ ለጥያቄያችን ሕጋዊ ምላሽ ስላልተሠጠ ብቻ ራያ ላይ የተዋቀረውን ባለአደራ አስተዳደር እንደተቀበልን ተደርጎ መወሠድ የለበትም ብሏል። 9፤ የኬንያዋ መርሳቢት ግዛት ገዥ መሃመድ ዓሊ፤ በኢትዮጵያ ሞያሌ በሚካሄደው ግጭት ሳቢያ 10 ሺሕ ኬንያዊያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል አሉ። ገዥው፤ ከሞያሌ በተተኮሱ ተባራሪ ጥይቶች ኬንያ ውስጥ 22 ሰዎች እንደቆሠሉና የሌሎች ሁለት ኬንያዊያን ሕይወት እንዳለፈ ዛሬ በሠጡት መግለጫ ተናግረዋል። ግዛቲቱ የገጠማት ቀውስ ከአቅሟ በላይ ነው ያሉት ገዥው፣ የኬንያ መንግሥት፣፣ ተመድ እና ለጋሾች ለስደተኞች የሚሠጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተማጽነዋል። ገዥው፤ ስደተኞቹን ከድንበር ግጭቱ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ጊዜያዊ መጠለያዎችን በመገንባት ማዛወር ያስፈልጋል ብለዋል። ዓለማቀፉ ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (ኤም ኤስ ኤፍ) በበኩሉ፤ ስደተኞች በተጠለሉባቸው አካባቢዎች የተቅማጥ በሽታ መከሠቱን ገልጧል።[ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ሐሙስ፣ ኅዳር 3፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እድገት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት 20 ነጥብ 5 ሆኖ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ያወጣው አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት አመለከተ። አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት እድገት ባንጻሩ በቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት በ2 ነጥብ 96 እንዲሁም በ2028 በ2 ነጥብ 93 እንደሚቀንስ ሪፖርቱ ጠቅሷል። በሌላ በኩል፤ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚቻለው በገበያ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ሲገደብ መሆኑን ያወሳው ሪፖርቱ፤ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበቱ ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ 14 ነጥብ 9 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተንብዩዋል። ሪፖርቱ፤ የትጥቅ ግጭቶችን ማቆምና በፖለቲካዊ ንግግር መፍታት፣ የብርን የመግዛት አቅም በማዳከም ላይ ብቻ የተመሠረተውን አካሄድ ማቆም አስፈላጊ መኾኑን በምክረ ሀሳብ ደረጃ አቅርቧል። 2፤ በቀድሞ አጠራሩ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአዲሱ አደረጃጀት ማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ሱሉልታ ወረዳ፣ ከጎርፎ ከተማ ወጣ ባለ ሥፍራ የአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ዛሬ ሐሙስ ማለዳ 12 ሰዓት ተኩል ገደማ ከተሽከርካሪ ላይ ከ50 በላይ ሰዎችን አግተው መውሠዳቸውን ዋዜማ ሠምታለች። ሰዎቹ የታገቱት፣ መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ ወደ ማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ደራ ወረዳ ጉንዶ መስቀል ከተማ በተለምዶ ''ኤፍ ኤስ አር ቅጥቅጥ'' ተብሎ በሚጠራ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ እንደነበር ምንጮች ነግረውናል። ከእገታው ለማምለጥ የሞከሩ ሁለት ሰዎች ታጣቂዎቹ በተኮሱት ጥይት ተመትተው በአካባቢው ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም መወሠዳቸውን ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል። 3፤ የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር በሕገ-ወጥ የማዕድን ቁፋሮና ዝውውር በተሠማሩ ግለሰቦች ላይ የጸጥታና አስተዳደር አካላት ርምጃ እንዲወስዱ አዘዘ፡፡አስተዳደሩ፤ ሕገ-ወጥ የወርቅና ሌሎች ማዕድናት ቁፋሮ፣ አደገኛ ኬሚካሎችን የመጠቀም ልማድ እና ማዕድናትን ከክልሉ ውጭ በሕገ-ወጥ መንገድ የማዘዋወር ድርጊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጧል። መመሪያውን በማስፈጸም ሂደት ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ወይም ከሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር የሚተባበሩ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል። 4፤ ባለፉት ሳምንታት በመንግሥትና በሕወሃት ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲያካሄድበት በቆየው የተምቤን ዓብይ ዓዲ ከተማ ከሠኞ ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ እንደተጣለ ዋዜማ ሠምታለች፡፡ በሰዓት እላፊ ገደቡ መሠረት፤ ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ እንዲሁም እግረኞች ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ እንደተጣለ የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል። ኾኖም የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር፤ በከተማዋ የሰዓት እላፊ ገደብ እንደተጣለ በይፋ አልገለጠም። አካባቢው በአሁኑ ወቅት በመንግሥት እና በትግራይ ሠላም ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ነዋሪዎች ገልጸዋል። 5፤ ከሳምንታት በፊት እጃቸውን ለመንግሥት የሠጡት የትግራይ ኃይሎች የደቡብ ግንባር አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር ወይም በቅጽል ስማቸው መዲድ፤ የሕወሓት የፖለቲካና ወታደራዊ አመራር "በተሳሳተ ስሌት" እና ሙሉ መግባባት ባልተደረሠበት ሁኔታ ጦርነቱን ወደ ኤርትራ ለማሻገር ወስኖ ነበር በማለት ተናገሩ። ጀነራሉ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሰሞኑን በተላለፈ ዘጋቢ ፊልም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርበው በሠጡት ቃል፤ የትግራይ ኃይል የመከላከያ ሠራዊትን የጸረ-ማጥቃት ርምጃ ሊቋቋም የሚችል አቅም እንዳልነበረው ገልጸዋል። ጀነራሉ፤ በዕዝና ቁጥጥር መበታተን ሳቢያ በግንባር ለነበሩ አዛዦች "አፈግፍጉ" የሚል ግልጽ ወታደራዊ እንዳል በወቅቱ እንዳልተሠጠም ብለዋል። 6፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሕልፈት በኋላ የዐይን ብሌን መለገስ በሸሪዓ ሕግ የተፈቀድ ተግባር መሆኑን ገለጠ። ምክር ቤቱ ከሕልፈት በኋላ የዐይንን ብሌን በመለገስ ረገድ ዙሪያ ጥያቄ በጤና ሚንስቴር እና በኢትዮጵያ ደም ባንክ አገልግሎት በኩል ጥያቄ እንደቀረበለትና ቁርዓን እና የሸሪዓ መርሆችን መሠረት በማድረግ የዓይን ብሌን መለገስ ከኃይማኖቱ ጋር አይጻረርም የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጧል፡፡ የዐይን ብሌን ልገሳ የሚፈቀደው፤ የለጋሹ ሕልፈት በትክክል ከተረጋገጠ፣ ለጋሹ በሕይወት እያለ በግልጽ ከተናዘዘ እና ከሞት በኋላ የሟች ወራሾችና ቤተሰቦች ለልገሳው ፍቃደኛ ሲሆኑ ብቻ መሆኑን ምክር ቤቱ አብራርቷል፡፡ 7፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የኃይማኖት ነጻነትን በማበረታታት፣ በእምነቶች መካከል መስተጋብሮችን በማጠናከር እና አማኞች በሰላም ማምለክ በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር ዛሬ መወያየታቸውን ገለጡ። አምባሳደሩ፤ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን በውይይቱ ወቅት መግለጣቸውን የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል። በቅርቡ በአርሲ በርካታ የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች መገደላቸው እንዲሁም ከቀዬአቸውና ከንብረታቸው መፈናቀላቸው አሜሪካን እንዳሳዘነ አምባሳደሩ መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ፓትርያርኩ በበኩላቸው፤ ችግሩን ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ዘላቂ መፍትሔ ግን ሊገኝ አልተቻለም በማለት ለአምባሳደሩ ነግረዋቸዋል ተብሏል። እንዲሁም፤ 1፤ በአንድ የመጽሐፍ ጥራዝ ዘጠና ታሪኮችን ያካተተው የደራሲ ሕይወት እምሻው "ቀብር እና ማስካራ" የተሠኘ አዲስ መጽሐፍ ቅዳሜ ኅዳር 5 ቀን ለንባብ ይበቃል። ይህ የደራሲዋ ሰባተኛ መጽሐፍ ሲሆን፣ የመጽሐፉ የሽያጭ መጀመሪያና የፊርማ ሥነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ ለገሐር በሚገኘው ጃፋር መጽሐፍት መደብር ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ይከናወናል። 2፤ አርታዊ ጋለሪ “ከቶኪዮ እስከ አዲስ አበባ፤ በቀለም ያሸበረቀች ከተማ” የተሠኘ የጃፓናዊው አርቲስት ዮሺሃሩ ኡሩሺዛኮ የግል ሥዕል ዐውደ ርዕይ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ። የዐውደ ርዕዩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ሕዳር 5 ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ ብራስ አካባቢ በሚገኘው አርታዊ ጋለሪ የሚከናወን ሲሆን፣ እስከ ሕዳር 12 ቀን ድረስ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ረቡዕ፣ ኅዳር 2፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የቡድን 7 አገራት፤ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል እያሽቆለቆለ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ዛሬ ባወጡት መግለጫ ገለጡ። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ድንበር ተሻጋሪ ውጥረት ቀጠናዊ መልክ ሊይዝ እንደሚችል ያስጠነቀቁት የቡድኑ አባል አገራት፤ ሁኔታው ከተባባሰ በቀጠናዊ መረጋጋት፣ በሰብዓዊ ቀውስ፣ በጸጥታ እና የቀይ ባሕር መስመርን ጨምሮ በዓለማቀፍ ንግድ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዱፈልጉና ሲቪሎችን ከጥቃት እንዲጠብቁ አገራቱ ጠይቀዋል። አገራቱ፤ የአገራትን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ማክበር እንደሚያስፈልግም አጽንዖት ሠጥተዋል። 2፤ ሦስት የአሜሪካ የሕግ መወሠኛ ምክር ቤት አባላት፤ በኢትዮጵያ "የርስበርስ ጦርነት" እንዳይከሠት አሜሪካ በቂ ዲፕሎማሲያዊ ሚና እየተጫወተች አይደለም በማለት ለውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ በጻፉት ደብዳቤ ወቀሱ። አሰብ ወደብን በወታደራዊ ኃይል የመያዝ ጉዳይ መነሳት የለበትም ያለት ሴናተሮቹ፤ አሜሪካ በማናቸውም የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድርድር ውስጥ የወደብ መያዝን የዲፕሎማሲ መሳሪያ እንዳታደርገው ጠይቀዋል። ሴናተሮቹ፤ ኢትዮጵያ አሰብ ወደብን በኃይል ለመያዝ ብትሞክር፣ አሜሪካ ድርጊቱን እንደማትደግፍ ከወዲሁ ግልጽ ማድረግ አለባት ብለዋል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ጦር መሳሪያ እንዳትሸጥም ሴናተሮቹ ጠይቀዋል። 3፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የበለጸጉ አገራት የካርበን ልቀታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ቱርክ እያስተናገደችው ባለችው የዘንድሮው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ጠየቁ። ዐቢይ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ብዙ ወጪ ባወጣን ቁጥር በትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ላይ የምናፈሠው ሙዓለ ንዋይ ይቀንሳል በማለት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ከውጭ እንዳይገቡ ማገዷን የጠቀሱት ዐቢይ፤ የቀጣዩ ጉባኤ አስተናጋጅ የሆነችው ኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችን የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው ጉዳት ለመከላከል በቶሎ ርምጃ ለመውሠድ ቅድሚያ እንደምትሠጥ ተናግረዋል። 4፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አማካሪ ጌታቸው ረዳ፤ የኤርትራ እና ሱዳን መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ አማጺ ቡድኖችን የማስታጠቅና የማስተባበር ሥራ ይሠራሉ በማለት ከሰሱ። ጌታቸው ይህን ያሉት፣ ከተመድ ዋና ጸሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉዋንግ ኮንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። ጌታቸው፤ የኤርትራ መንግሥት በቀጠናው ያደርገዋል ባሉት አፍራሽ ሚና ዙሪያ ለልዩ መልዕክተኛው ሠፊ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል። በቀጠናው የባሠ ውጥረት እንዳይከሠት የሚያስችል ንግግር ለማድረግ ኤርትራ እና ሱዳን በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አማጺ ቡድኖችን ከማስታጠቅና ከመደገፍ መቆጠብ አለባቸው የሚለውን የኢትዮጵያ አቋም ለልዩ መልዕክተኛው እንዳስረዱም ጌታቸው ጠቅሠዋል። 5፤ ዓለማቀፍ የአዳዲስ መድሃኒቶችና የሕክምና መሳሪያዎች አምራች ኩባንያዎች አዳዲስ መድሃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን ተደራሽ ለማድረግ በእቅዳቸው ከሚይዟቸው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ አንድ ሪፖርት አመለከተ። አክሰስ ቱ ሜዲሲን ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት፤ ኩባንያዎች አዳዲስ መድሃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከያዟቸውና በሪፖርቱ ከተካተቱት 245 እቅዶች ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፑብሊክ እያንዳንዳቸው የተካተቱት በ10ሩ እቅዶች ብቻ መሆኑን ጠቅሷል። የሦስቱ አገራት በበቂ ሁኔታ አለመካተት፤ መድሃኒት አምራቾች የሕዝብ ብዛትንና የበሽታዎችን ሥርጭት ዋነኛ መስፈርት እንደማያደርጉ የሚጠቁም ተደርጎ ተወስዷል። 6፤ የፌደራል መንግሥቱ የሚንስትር ደዔታነት ሹመት የሠጣቸው የስምረት ፓርቲ አመራሮች የሆኑት ኬርያ ኢብራሂም፣ አዲሱ የመቀለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረና ሌሎች ዘጠኝ አመራሮችና አባላት ራሳቸውን ከፓርቲው አገለሉ። አባላቱ፤ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ጥቂት አባላት የፓርቲውን ሕገ-ደንብ በመጣስ ፓርቲው የመፍረስ አደጋ እንዲደቀንበት አድርገዋል በማለት ከሠዋል። የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በበኩሉ፤ ከፓርቲው ራሳቸውን ያገለሉ አመራሮች የሕዝብ ተቃውሞ ሲበዛባቸው ትኩረት ለማስቀየር የፈለጉና ፓርቲውን ከውስጥ ለማፍረስ በሚስጢር ሲሠሩ የቆዩ ናቸው በማለት ከሷል። በሌላ በኩል፤ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን ሰብሳቢ የሆኑት ገብረሕይወት ገብረስላሴ የፓርቲውን "ሕገ-ደንብ ጥሠዋል" በሚል ከሳምንታት በፊት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገበት አካሄድ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ነበር ሲል ውሳኔውን ውድቅ አድርጓል። 7፤ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ50 ሺሕ ብር በላይ የሆኑ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች 15 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ የሚደነግገው አዲስ ደንብ ሥራ ላይ ዋለ። ዓመታዊ ገቢያቸው ከተጠቀሠው መጠን የማያልፍ የይዘት ፈጣሪዎች ደሞ ቀድሞ የከፈሉት ግብር ለወደፊት ከሚከፍሉት ጋር እንዲካካስላቸው ወይም ተመላሽ እንዲደረግላቸው ደንቡ ደንግጓል። በአዋጁ መሠረት፤ በዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ ባለቤት የሆኑ ግብር ከፋዮች ገቢያቸውን አሳውቀው እያንዳንዱ ሩብ ዓመት በተጠናቀቀ በ30 ቀናት ውስጥ ግብሩን መክፈል ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ ነዋሪ የኾነ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪ የባንክ ሂሳቡ የተከፈተው ከአገር ውጪ መኾኑ ወይም ክፍያው ከአገር ውጪ መፈጸሙ ብቻ ግብር ከመክፈል እንደማያድነው በደንቡ ላይ ሠፍሯል፡፡ እንዲሁም፤ 1፤ "ጉሽን" የተሠኘው አዲስ ተውኔት በሳምንት ሁለት ቀናት መታየት ሊጀምር ነው። በሳምንት አንድ ቀን ዘወትር ረቡዕ ሲቀረብ የቆየው ተውኔቱ፤ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ዘወትር እሁድ በ12 ሰዓት በዓለም ሲኒማ መታየት እንደሚጀምር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል። 2፤ "በር የሌለው ቤት" የተሠኘውና በቡርሃን አል-አሚን ተደርሶ የተዘጋጀ አዲስ ተውኔት ዘወትር ሐሙስ ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በዕይታ ላይ ይገኛል። 3፤ "የመጨረሻው መጀመሪያ" መጽሐፍ ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከመጽሐፉ አንባቢዎቹ ጋር የሚገናኝበት የመጽሐፍ ፊርማ መርሃ-ግብር ለገሐር በሚገኘው ጃፋር መጽሐፍት መደብር ይካሄዳል።[ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ፤ ማክሰኞ፣ ኅዳር 1፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በባድመ ከተማ የኤርትራ ጦር ጭምር የተሳተፈበት ውጊያ በመንግሥት እና በሕወሃት ኃይሎች መካከል መካሄዱን ዋዜማ ሠምታለች፡፡ በትግራይ በድጋሚ ጦርነት ከተቀሠቀሠ ወዲህ ከቀናት በፊት ባድመ ላይ ውጊያ እስኪቀሰቀስ ድረስ የኤርትራ ሠራዊት ከባድመ አካባቢ ወጥቶ እንደነበር ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ካለፈው አንድ ሳምንት ወዲህ ባድመ በሕወሃትም ሆነ በኤርትራ ጦር ሥር እንዳልኾነች ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከትላንት ጀምሮ የኤርትራ ሠራዊት ሠምበል፣ ገማህሎ እና ዓዲ ጸጸር በተባሉ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ሠምተናል። በሌላ በኩል፤ የኤርትራ አዋሳኝ በኾኑት ራማ እና ገማህሎ በተባሉ አካባቢዎች የመንግሥት ሠራዊት ከሕወሃትን፣ የፋኖ ታጣቂዎችንና የአፋር አማጺዎችን ካቀፈው ኃይል ጋር ውጊያ ማካሄዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ የሕወሃት፣ የፋኖ፣ የአፋር እና የኤርትራ ኃይሎች በአካባቢው በጋራ ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ የገለጹት ነዋሪዎች፤ በተለይ ትላንት ሠኞ ከባድ የተባለ ውጊያ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ 2፤ ፌደራል መንግሥቱ ለትግራይ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ የሚውል ገንዘብ ከ1 ሳምንት በፊት ወደ መቀለ መላኩን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካሪ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። ጌታቸው፤ ባለአደራ አስተዳደሩ የሠራተኞችን ውዝፍ ደመወዝ ከነገ ጀምሮ እንደሚከፍል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ 140 ሺሕ ገደማ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉ የጠቀሱት ጌታቸው፤ ኾኖም ምን ያህሉ ወደ ሥራ እንደተመለሱ ወይም ምን ያህሉ ከሕወሃት ጋር ጫካ እንደገቡ ማጣራት እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ፤ በአካል ተገኝቶ ሪፖርት ላደረገ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ መክፈል እንደሚጀምር ገልጧል። 3፤ የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ምዕራብ ትግራይ ተብሎ ለሚጠራው ትግራይ እና አማራ ክልሎች ለሚወዛገቡበት አካባቢ አስተባባሪ ሾመ፡፡ የባለአደራ አስተዳደሩ ሥራ አስፈጻሚ ካውንሥል ሰብሳቢ አሠፋ አብርሃ በጻፉት ደብዳቤ፤ ዳንኤል ነጋሽ ለአወዛጋቢው ዞን ዋና አስተባባሪ ሆነው እንደተሾሙ አስታውቀዋል። ሆኖም፤ ዋና አስተዳዳሪ በሚል ማዕረግ ፋንታ ዋና አስተባባሪውም በሚለው ማዕረግ የተሿሚው ዋና ዋና ኃላፊነቶች ምን እንደሆኑ ደብዳቤው አላብራራም፡፡ ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ ባለአደራ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ 4፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ የሚልኩት ገንዘብ ከቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትና ከለጋሾች ገንዘብ በመብለጥ የአገሪቱ ትልቁ የውጭ ገንዘብ ምንጭ መሆኑን የአፍሪካ ልማት ባንክ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ገለጠ። ሆኖም ወደ አገሪቱ የሚላከው ገንዘብ ባብዛኛው ቤት፣ ጤና እና ትምህርት በመሳሰሉ ፍጆታዎች ላይ እንጂ በኢንቨስትመንት ላይ እንደማይውል ሪፖርቱ ጠቅሷል። ሪፖርቱ፤ የአስተማማኝ ፖለቲካዊ ሁኔታ አለመኖር፣ የፖሊሲዎች መቀያየርና በንብረት ባለቤትነት መብት ላይ ርግጠኛነት ማጣት የገንዘብ ላኪዎችን አመኔታ እንደሚሸረሽር ሪፖርቱ አውስቷል። ሪፖርቱ፤ የገንዘብ ፍሠቱን ለመጨመር የውጭ ምንዛሬን አስተማማኝነት መጠበቅ፣ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወጪዎችን መቀነስና የገንዘብ ቁጠባ ሥርዓቶችን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብሏል። 5፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ፣ ''የዴንጊ ትኩሳት'' ቫይረስ ወረርሽኝ በክልሉ ተከስቷል አለ። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው በተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ናሙና ላይ ምርመራ አድርጎ፤ አምስቱም በቫይረሱ መያዛቸውን እንዳረጋገጠ ቢሮው ገልጧል። ቢሮው፤ በክልሉ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ አስፈላጊ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲሠሩ አሳስቧል። የደንጊ ትኩሳት በወባ ትንኝ የሚተላለፍ፣ ፍቱን መድሃኒት የሌለው፣ ከባድ ራስ ምታትን፣ ማቅለሽለሽን፣ የድድ መድማትንና ማስታወክን የሚያስከትልና ገዳይ ሊሆን የሚችል በሽታ ነው። 6፤ በስካንድናቪያን ባለሀብቶች የተያዘውና በጋምቤላ ክልል በወርቅ ልማት የተሠማራው አኮቦ ሚኒራልስ የወርቅ አውጪ ኩባንያ፤ በጥቅምት ወር 12 ኪሎ ግራም ወርቅ ማምረቱን አስታወቀ። ኩባንያው በነሃሴ ወር 16 ኪሎ ግራም ወርቅ ማምረቱን ገልጦ ነበር። ኩባንያው ከሁለት ዓመት በፊት ወርቅ ማምርት ከጀመረ ወዲህ በጠቅላላው ያመረተው ወርቅ 181 ኪሎ ግራም መድረሱን አዲስ ባወጣው መረጃ ጠቅሷል። የካናዳው አላይድ ወርቅ አውጪ ኩባንያ በበኩሉ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ኩርሙክ ከሚገኘው ጣቢያው ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የማጣራት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል። 7፤ ብሄራዊ ባንክ ዛሬ ባካሄደው የ140 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የተጫራቾች ፍላጎት ከ16 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አስመዘገበ። በጨረታው አንድ የአሜሪካ ዶላር የተሸጠው ከሁለት ሳምንት በፊት ከተካሄደው ጨረታ ጋር ተመሳሳይ በኾነ 159 ብር ከ70 ሳንቲም በሆነ አማካይ ዋጋ ነው። በዛሬው ጨረታ ከተሳተፉት 31 ባንኮች መካከል 26ቱ የውጭ ምንዛሬ አግኝተዋል። ተጫራች ባንኮች በጨረታው ላንድ ዶላር ያቀረቡት ከፍተኛ ዋጋ 160 ብር ከ99 ሳንቲም ሲኾን፣ ዝቅተኛው ዋጋ 159 ብር ከ18 ሳንቲም ነበር። እንዲሁም፣ 1፤ የሠዓሊ አብርሃም ወልደገብርኤል የሥዕል ሥራዎች የቀረቡበት "የሕይወት መጠበቅ" የተሠኘ የሥዕል ዐውደ-ርዕይ ለዕይታ በቅቷል። ይህ ዐውደ ርዕይ፣ እስከ ህዳር 21 ቀን ድረስ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፤ ጎብኝዎች ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ መጎብኘት እንደሚችሉ ተገልጿል። 2፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባሕል ማዕከል የተዘጋጀውና የፊልም አዘጋጁ ሰውመሆን ይስማው የክብር እንግዳ በመሆን የተጋበዘበት ሳምንታዊ ዝግጅት ነገ ረቡዕ ኅዳር 2 ቀን ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው የባሕል ማዕከል ይካሄዳል። መግቢያው በነፃ ነው። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ! ሰኞ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ የባለአደራ አስተዳደር የውክልናና ሹመት አሠጣጥ ሂደት ጋር በተያያዘ፤ በትግራይ የሠላም ኃይል አመራሮች መካከል ክፍፍል መፈጠሩን ዋዜማ ሠምታለች። የክፍፍሉ ዋነኛ መንስኤ፤ ሹመት አሠጣጡ የትውልድ አካባቢንና የግለሠቦችን ሠንሰለት ማዕከል ያደረገና ለትግሉ አስተዋጽኦ ያላደረጉ ግለሰቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው የሚል መኾኑን ምንጮች ነግረውናል፡፡ በሌላ በኩል፤ በአሁኑ በቡድኑ ዋና አዛዥ ሜ/ጀነራል ገብረእግዚያብሔር በየነ መሪነት በመቀለ እና አዲግራት ከተሞች አዲስ የታጣቂ ቡድን አደረጃጀት እየተመሠረተ ነው የሚል ቅሬታ መኖሩንም ተረድተናል። ክፍፍሉን ተከትሎ፤ መመሪያ አንቀበልም ያሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት አሉ ተብሏል። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው አንድ የቡድኑ ወታደራዊ አመራር በበኩላቸው፤ "የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት የሚያሠሙት ሀሰተኛ ውንጀላ ነው" የሚል ምላሽ ሠጥተዋል፡፡ 2፤ በሞያሌ በቀጠለው ግጭት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሠዎች መገደላቸውን ዋዜማ ሠምታለች። በከተማዋ ጫሙቅ፣ መላብ ፣ 01 እና 02 በተባሉ አካባቢዎች ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ነዋሪዎች ነግረውናል። ከዓርብ፣ ጥቅምት 27 ቀን ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት የተኩስ ድምጽ እንደሚሠማ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ይህ ዘገባ አስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የፌደራል መንግሥት ኃይሎች ግጭቱን ለማርገብ ወደ አካባቢው አለመግባታቸውን ተረድተናል። በተያያዘ፤ በሞያሌው ግጭት ወደ ኬንያ የተሠደዱ ስደተኞች የምግብ፣ የውሃ እና የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸው ተገልጧል። የተመድ የፍልሠት ድርጅት፤ ከስደተኞቹ 80 በመቶዎቹ ዋና ችግራቸው የምግብ እጥረት መሆኑን በዳሰሳ ጥናት እንዳረጋገጠ ገልጧል። ከ10 ስደተኞች ዘጠኙ የመንደራቸው ሁሉም ነዋሪዎች እንደተሠደዱ ገልጸዋል ተብሏል። 3፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፤ "ከአቅም በላይ" ተብለው በተጠቀሱ ምክንያቶች የታክስ ዕዳ ጫና ላለባቸው ግብር ከፋዮች ግልጽ፣ ፍትሃዊ እና ወጥ የምኅረት አሠጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ አዘጋጀ፡፡ ዋዜማ የተመለከተችው ረቂቅ መመሪያ፤ ከአቅም በላይ በኾኑ ምክንያቶች ሕጋዊ የታክስ ግዴታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው የዕዳ ምኅረት ጥያቄ ባቀረቡ አካላት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይገልጻል። ጎርፍ፣ መሬት መንሸራተት ወይም እሳት ቃጠሎ ሲከሠት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የድጋፍ ደብዳቤዎች፤ የንግድ ድርጅት ኪሳራ ወይም አቅም ማነስ ሲያጋጥም በኦዲተር የተረጋገጠ የኦዲት ሪፖርትና የፋይናንስ ኪሳራ መግለጫ እንዲሁም ከባድ ሕመም ወይም የአካል ጉዳት ሲያጋጥም፤ ከሕክምና ተቋም ማረጋገጫ ማቅረብ ግዴታ መኾኑ በመመሪያው ላይ ሠፍሯል፡፡ ይሁን እንጂ፤ መመሪያው ሕገ-ወጥ የታክስ ስወራ በፈጸሙ አካላት ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም ተብሏል። 4፤ በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ዛሬ ሰኞ ማለዳ ላይ በፈጸሙት ጥቃት የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ቤጊ አዱኛን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንደገደሏቸው ዋዜማ ሠምታለች። ግድያው የተፈጸመው፤ በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች ወደ ወረዳዋ መቀመጫ ፊታል ቀድመው በመግባት ቦታ ቦታ ከያዙ በኋላ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። ጥቃቱን ተከትሎ፤ ታጣቂዎቹ በከተማዋ የሚገኙ በርካታ የንግድ መደብሮችን፣ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆችን፣ እንዲሁም የግለሰቦችን መኖሪያ ቤቶች መዝረፋቸውን ምንጮች ገልጸዋል። 5፤ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በክልሉ በተፈጠረው ዳግም ጦርነት ምክንያት ለጊዜው በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የነበሩ ተማሪዎቹን መቀበል ጀመረ። ዩኒቨርሲቲው፤ በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ቀድሞ የትምህርት ተቋማቸው ለመመለስ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ የምዝገባ ቀኑን ማራዘሙን ጠቁሟል። ነገና ከነገ ወዲያም በተያዘው የትምህርት ዘመን በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመድበው የቆዩ ተማሪዎች ወደ ግቢው እንደሚገቡ ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ባሠራጨው መረጃ ገልጧል። ዩኒቨርስቲው፤ ስንት ተማሪዎቹ በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመድበው እንደቆዩ አልጠቀሠም። 6፤ ግብጽ እና ሱዳን፤ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ በምትወስዳቸው የተናጥል ርምጃዎች ይደርሱብናል ያሏቸውን "ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ጉዳቶች" የሚያጠናና የካሳ ጥያቄ የሚያቀርብ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ። ኮሚቴው የሚያጠናው "ጉዳት" ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊና አካባቢያዊ ጉዳቶችን ጭምር እንደሚያካትት የአገራቱ ባለሥልጣናት መግለጣቸውን የግብጽ ጋዜጦች ዘግበዋል። በኮሚቴ ጥናት ላይ በመመስረት፣ ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገራት ካሳ እንድትከፍል ጥያቄ እንደሚቀርብ ባለሥልጣናኑ ተናግረዋል ተብሏል። ኢትዮጵያ፣ በግብጽ ጫና እና ሴራ ለዓመታት የተስተጓጎሉባትን የውሃ ፕሮጀክቶችና በዚህም ሳቢያ የደረሠባትን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ የሚገመግምና የካሳ ጥያቄ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ "የዓባይ የካሳ ብሄራዊ ኮሚቴ" በቅርቡ ማቋቋሟ ይታወሳል። እንዲሁም፤ 1፤ በተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ1999 ዓ፤ም የተከፈተውና ዘንድሮ 20ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የተፈሪ መኮንን ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የሥነጥበብ ትምህርት ክፍል የሥዕል ዐውደ ርዕይ አዘጋጅቷል። በዐውደ ርዕይው ላይ ተመራቂ ተማሪዎች ያዘጋጇቸው የሥዕል ሥራዎች ይቀርባሉ። ዐውድ ርዕይው ማክሰኞ፣ ኅዳር 1 ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በኮሌጁ የሥዕል ማሳያ ይከፈታል። 2፤ "ጃዝ ቲዩስዴይ" የተሠኘ የጃዝ (ብሉዝ እና ፈንክ) ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት ዝግጅት በየሳምንቱ ማክሰኞ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው ባዝራ ኮፊ (BazraCoffee) ይካሄዳል። የዝግጅቱ መግቢያ ዋጋ 200 የኢትዮጵያ ብር ነው። [ዋዜማ]
Open in Telegramዛሬ ቅዳሜ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቡልዲግሉ ወረዳ ታጣቂዎች ሐሙስ'ለት በፈጸሙት ጥቃት 52 ሰዎች እንደተገደሉ ተሠማ። ዳለቲ በተባለች ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉት መካከል፤ 21ዱ ሲቪሎች፣ 18ቱ የክልሉ የፖሊስ አባላት እና 13ቱ የአካባቢው የሚሊሻ አባላት መኾናቸውን ዋዜማ ሰምታች። ወረዳዋ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የምትዋሠን ስትኾን፤ ጥቃቱን የፈጸሙት የአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። 2፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እግድ የጣለበት የቀድሞው የኤፈርት ባለአደራ ቦርድ የአዳዲስ የቦርድ አባላትን ሹመት "ሕገወጥ" ሲል ውድቅ አደረገ፡፡ የሕወሓት የሥራ አስፈጻሚ አባል አብርሃም ተከስተ ይመሩት የነበረው ቦርድ፤ አዲሱ ሹመት ተቋማዊ አሠራርን የጣሠ፣ ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው እና የተቋሙን ሀብትና ንብረት በሕገ-ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር ያለመ ነው በማለት ተቃውሞውን ገልጧል፡፡ ለኩባንያው ጊዜያዊ ቦርድ የመሠየም ሕጋዊ ሥልጣን የድርጅቱ ምክር ቤቱ ነው ያለው የቀድሞው ቦርድ፤ የተቋሙ ሠራተኞች፣ የፍትሕ አካላት እና የክልሉ ሕዝብ ውሳኔውን ውድቅ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። 3፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፤ በሞያሌው ግጭት ሳቢያ ወደ ኬንያ ለተሠደዱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አስቸኳይ ድጋፍ የሚውል 3 ሚሊዮን ዶላር መደበ። ተመድ፤ የገንዘብ ድጋፉ ለነፍስ አድን የሚውል የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያና የጤና ድጋፍ ለሚያደርጉ የረድኤት ድርጅቶች እንደሚሠጥ ገልጧል። ተመድ፤ እስካሁን ወደ ኬንያዋ መርሳቢት ግዛት የተሠደዱት ኢትዮጵያዊያን ብዛት 50 ሺሕ ይሆናሉ ብሏል። ድርጅቱ የእርዳታ አሠጣጡን የሚያስተባብር ቡድን ወደ ሞያሌ ማሠማራቱን አስታውቋል። 4፤ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ለውጭ ገበያ ከላከችው ቡና 878 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች። በተጠቀሠው ጊዜ ውስጥ ከቡና 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ የእቅዱ 85 በመቶ እንደተሳካ የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ገልጧል። ይህ ገቢ የተገኘው፤ 144 ሺሕ 433 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ እንደሆነ የገለጠው ባለሥልጣኑ፤ ለውጭ ገበያ መላክ የተቻለው ግን 131 ሺሕ ቶን ገደማ እንደነበር ጠቅሷል። ውጤቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በቡና መጠን የ17 ሺሕ 527 ቶን እንዲኹም በገቢ የ115 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ተገልጧል። በቡና መዳረሻ፤ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጀርመን እና ቻይና በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል ተብሏል። እንዲሁም፤ 1፤ በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የተዘጋጀው የመጽሐፍት ባዛር ተከፍቷል። በዚህ ባዛር ላይ፤ አዳዲስና የአካዳሚክ የጥናት መጽሐፍት ስብስቦች ለሽያጭ መቅረባቸውን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል። ባዛሩ በቤተ መጽሐፍቱ ዋናው መግቢያ ላይ እስከ ሕዳር 7 ቀን እየተካሄደ ይቆያል። 2፤ በገጣሚ ረድዔት ተረፈ የተዘጋጀውና ግጥም ሙዚቃና ጨዋታ የሚቀርቡበት "መገናኛ" ጥበባዊ ዝግጅት ነገ፤ ጥቅምት 29 ቀን በሞሶብ የሙዚቃ ማዕከል ከ11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ይካሄዳል። መግቢያ ዋጋ 600 የኢትዮጵያ ብር ነው። [ዋዜማ]
Open in Telegramለቸኮለ! ዓርብ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ያወጣው የመንግስት ሠራተኞችን ምዘና የሚመለከተው አዲሱ ረቂቅ መመሪያ፤ ማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ የቴክኒክ፣ የባሕሪ እና የተግባር ምዘና እንዲወስድ የሚያስገድድ መሆኑን ዋዜማ ሠምታለች። መመሪያው፤ ሠራተኞች በሥራ መደባቸው ለመቀጠል እንዲሁም ዕድገትና ዝውውር ለማግኘት በሦስቱም የምዘና መስኮች 70 በመቶና ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው መደንገጉን ምንጮች ጠቁመዋል። 70 በመቶ ማስመዝገብ ያልቻሉ ሠራተኞች፤ ከሥልጠና በኋላ ዳግም ምዘና የሚያደርጉበት አሠራር እንደሚኖር ምንጮች ገልጸዋል። በምዘናው በቂ ውጤት ማምጣት ያልቻሉ ሠራተኞች፤ ጥቅማቸው ተጠብቆላቸው በገዛ ፍቃዳቸው ከሥራ መልቀቅ የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቷል ተብሏል። 2፤ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ታጣቂዎች በድጋሚ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ላይ ጥቃት ፈጸሙ። ታጣቂዎች ትናንት ጥቃቱን የፈጸሙት፣ በሮቤ ወረዳ እንዳቶ ቀበሌ መኾኑን የቤተክርስቲያኗ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል። በጥቃቱ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችና ክርስቲያኖች እንደተገደሉ ከወረዳው ቤተ ክሕነት መረዳቱን ጣቢያው ጠቅሷል። የአርሲና የሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ ራቅ ባሉ በተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር በሚያጋጥምባቸው በርካታ ቀበሌዎች የመንግሥት አካላት ጥበቃና ከለላ እንዲሠጡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ዘገባው አመልክቷል። 3፤ በማእከላዊ ትግራይ ዞን ዓዴት፣ ዛና እና ብዘት በተባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ዛሬ በመንግሥትና በሕወሃት ኃይሎች መካከል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መካሄዱን ዋዜማ ሠምታለች፡፡ በተለይ "ብዘት" በተባለው አካባቢ በውጊያው በበርካታ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት እንደደረሠ የአካባቢዎው ነዋሪዎች ገልጸውልናል። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የትግራይ ሠላም ኃይል የሚድያ ዘርፍ ኃላፊ መንግሥተዓብ ተስፋይ በበኩላቸው፤ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚካሄዱ መጠነኛ የተኩስ ልውውጦች በስተቀር "ውጊያ ቆሟል" ብለዋል፡፡ በተያያዘ፤ መከላከያ ሠራዊት፤ ከሕወሓት ማረኳቸው ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች አዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ዛሬ አሳይቷል። ለእይታ ከቀረቡት መካከል፤ ከባድ መሳሪያዎች እንዲሁም አነስተኛ ድሮኖችና ወታደራዊ አጥቂ ድሮኖች ይገኙበታል። መሳሪያዎች ለእይታ የቀረቡት፤ መልካ ቃሊቲ በመባል በሚታወቀው የመከላከያ ሎጀስቲክ መመሪያ ውስጥ ነው። 4፤ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የመረከብና በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ትግበራ በመቐለ ከተማ የመለስ ካምፓስ ማዕከል ጀመረ። ኮሚሽኑ፤ አዲስ በተመረጡ አምስት ጊዜያዊ ማዕከላት የቅድመ-መልሶ ማቋቋም መስፈርቶችን ያሟሉ ከ5 ሺሕ 500 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች የምዝገባ ሂደት መጀመራቸውን ገልጧል። በጉዳዩ ዙሪያ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የትግራይ ሠላም ኃይል የሚድያ ዘርፍ ኃላፊ መንግሥተዓብ ተስፋይ፤ ከመቀለ በተጨማሪ በአክሱም፣ ሽሬ፣ አድዋ፣ ማይጨው እና ውቅሮ አዳዲስ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ነግረውናል። ኾኖም በሂደቱ ላይ ታጣቂዎቹ ከቀድሞው በተለየ ዩኒፎርሞችን ባለመልበሳቸው የቀድሞ ተዋጊ መኾን አለመኾናቸውን ለመለየት ትንሽ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደፈጠረ ኃላፊው ተናግረዋል። 5፤ በመቀለ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ በተሸከርካሪዎች ላይ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ጧቱ 12 ሰዓት የሚዘልቅ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ፡፡ ሕወሃት ከተማዋን ለቅቆ ሲወጣ ከማረሚያ ቤት የወጡ ሰባት ሺሕ የሚጠጉ ታራሚዎችና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በሚፈጽሟቸው የሥርቆትና ሕገ-ወጥ ተግባራት በነዋሪዎች ደኅንነት ላይ ሥጋቶች እንደተደቀኑ የሰዓት እላፊውን የጣለው መከላከያ ሠራዊት ገልጧል፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ በቤታቸውም ሆነ በሥራ ቦታቸው ያስቀመጡ ነዋሪዎች በሦስት ቀናት ውስጥ ያለምንም ቅድመ ምርመራ ለፖሊስ እንዲያስረክቡም ታዘዋል። የጸጥታ አካላት ሕጋዊ የፍተሻ ደብዳቤ በመያዝ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት የመኖሪያ ቤቶች ፍተሻ እንደሚያካሂዱም ተገልጧል። ኾኖም፤ የቤት ለቤት ፍተሻውና ፍቃድ ያላቸውም ኾነ የሌላቸው የጦር መሳሪያዎችን የመሰብሰብ ሥራ ከቀናት በፊት እንደተጀመረ ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት ተረድታለች። 6፤ በጋምቤላ ክልል የጋምቤላ ወረዳ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ በወረዳው ዘላቂ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ሲል አዲስ የሰዓት እላፊ) አወጀ። ከዛሬ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ኅብረተሰቡ ከመኖሪያ ቤቱ ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይችል አስተዳደሩ ገልጧል። ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው የጸጥታ አካላት ውጭ የጦር መሣሪያ በማናቸውም ሰዓት ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ ክልክል መሆኑንም አስተዳደሩ አስታውቋል። የሰዓት ገደብና የጸጥታ ቁጥጥር ሥርዓቱ፤ በወረዳዋ የጸጥታ ማስከበር ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና አካባቢውን በፍጥነት ወደ መደበኛ ሰላም ለመመለስ ታስቦ ነው ተብሏል። 7፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የትምህርት ዘመኑ ሳይጠናቀቅ የቀጣይ ዓመት ቅድመ ምዝገባ በሚያካሂዱ ትምህርት ቤቶች ላይ እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ እገዳ የሚጥል ረቂቅ መመሪያ አዘጋጀ። ዋዜማ የተመለከተችው የአዲስ ረቂቅ መመሪያ፣ መመሪያውን የሚጥሱ ትምህርት ቤቶች መጀመሪያ ምክርና ከዚያም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሠጣቸውና ጥፋታቸውን ማረም ካልቻሉ ግን ለአንድ ዓመት የእውቅና ፈቃዳቸው እንደሚታገድ ደንግጓል። በተማሪዎች ቅበላም ኾነ በትምህርት አሠጣጥ ሂደት በጾታ፣ ኃይማኖት፣ ብሔር፣ ማኅበራዊ መሠረትና የፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ወይም አድልዎ ማድረግንም መመሪያው ይከለክላል። እንዲሁም፤ 1፤ ድምጻዊት አበባ ደሣለኝ ከአሥራ ሦስት ዓመታት በኋላ "መርቂኝ" የተሠኘ አራተኛ የሙዚቃ አልበሟን ኅዳር 4 ለአድማጮች እንደምታቀርብ አስታውቃለች። 2፤ የድምጻዊ እሱባለው ይታየው (የሺ) አዲስ የሙዚቃ አልበም ሕዳር 11 ለአድማጮች እንደሚቀርብ ተሠምቷል። ከሙሉ አልበሙ አስቀድሞ የሙዚቃ ቪዲዮ የተሠራለትና አልበሙ ውስጥ የተካተተው "ለየቱ ጊዜ ነው?" የተሠኘው ሙዚቃ ይለቀቃል። 3፤ ድምፃዊት ሄለን በርሄ "የበረታ" የተሠኘ ሦስተኛውን የሙዚቃ አልበሟን ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን ለአድማጮች ይፋ አድርጋለች። [ዋዜማ]
Open in Telegram