
ኖላዊ ኄር ዘ-ኦርቶዶክስ
ዘየአምን ለአማኑኤል በስሙ ፣ ኅቱም በማኅተመ ደሙ ፣ ውኩል በጸሎተ ማርያም እሙ ፣ ወለቅዱሳን ተላዌ ሃይማኖቶሙ ። አቤቱ አንተን ለመስማት ያዘነበለ ልብ ስጠን! #ለሃሳብ ለአስተያየት - @Nolawiher1
Average views per post by day
By publication day
Show as table
| Date | Avg views per post |
|---|---|
| Nov 1, 2026 | 44,200 |
| Nov 6, 2026 | 3,310 |
Latest posts
የድኅነት ፈትል /6/ በማቴዎስ 24 ማጠቃለያ ላይ ጌታችን ስለ ታማኙ አገልጋይና ሰነፎች ደናግል (በምዕራፍ 25 የሚቀጥለው) የሚያስተምረን ትምህርት ከትዕግሥት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ሙሽራው (ክርስቶስ) ቢዘገይም፣ ታማኙ አገልጋይ ግን በትዕግሥት ይጠብቀዋል። እዚህ ላይ ትዕግሥት ሰነፍ አያደርግም፤ ይልቁንም ዘይት (መልካም ሥራንና ሃይማኖትን) ይዞ በንቃት እንድንጠባበቅ ያደርገናል። ትዕግሥት ለብቻዋ አትቆምም፤ ከጸሎት፣ ከጾም እና ከበጎ ምግባር ጋር የተሳሰረች የ ድኅነት ፈትል አካል ናት። እግዚአብሔር የመምጣቱን ዘመኑንና ሰዓቱን የሰወረበት ዋና ምክኒያት፣ እኛ ዘወትር በትዕግሥትና በንቃት እንድንኖርና የጽናት አክሊል እንድንቀዳጅ ነው። በማቴዎስ 24 የተጻፈው ትንቢት የዓለምን መፍረስ ብቻ የሚያሳይ ሳይሆን፣ አማኞች በጽናት አልፈው የሚድኑበትን መንገድ የሚያበራ ብርሃንም ጭምር ው ። የድኅነት ፈትል የሆነችው ትዕግሥትም ፣ አማኙን ከምድር መከራ አውጥታ ከሰማያዊው ክብር ጋር የምታገናኝ ድልድይ ናት። ስለዚህ፣ በዚህ ምዕራፍ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲፈጸሙ ስናይ የምንደነግጥ ሳይሆን፣ በትዕግሥት የምንጸናበትና የድኅነታችንን ቀን የምንናፍቅበት ሊሆን ይገባል። በማቴዎስ 24፡13 ላይ ያለውን ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል❞ የሚለውን የጌታ ቃል፣ የቤተክርስቲያን አባቶች በጥልቀት ተርጉመውታል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህ ታላቅ አባት የጌታን ቃል ሲተረጉም እንዲህ ይላል፦ "ጌታችን 'እስከ መጨረሻ የሚጸና' ሲል፣ መከራው ለአንድ አፍታ መጥቶ የሚያልፍ ሳይሆን፣ እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ የሚቀጥል መሆኑን ለማሳየት ነው። የብዙዎች ፍቅር በሚቀዘቅዝበት በዚያ ጨለማ ሰዓት ውስጥ፣ አማኝ እንደ መብራት በትዕግሥት ማብራት አለበት። መዳን የሚገኘው በትግሉ መጀመሪያ ላይ ሳይሆን፣ በትግሉ ማጠቃለያ ላይ በጽናት ለተገኘው ነው" ደጰይላል። ቅዱስ ቆጵሪያኖስ ስለ ትዕግሥት በጻፈው ድርሳኑ ላይ፦ "የእኛ እምነትና ተስፋ ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርገው ትዕግሥት ነው። ክርስቲያን መሆን በራሱ በትዕግሥት ጎዳና ላይ መጓዝ ማለት ነው። ያነበብነውን ቃልና የተቀበልነውን ምስጢር አጽንቶ የሚያቆየው ትዕግሥት ነው በማለት ያስተምራል። አረጋዊ መንፈሳዊ በጽናት መከራን ስለመቀበል ሲናገር፦ መከራን በትዕግሥት መሸከም ሰማዕትነት ነው። ሰማዕትነት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምታስገባ የድኅነት በር ናት ይላል። በማቴዎስ 24 የተጠቀሰውን መከራ በትዕግሥት በማለፍ፣ "የድኅነት ፈትል" የሆነችውን ሃይማኖታቸውን አጥብቀው የያዙት ሕያው ምስክሮቻችን ሰማዕታት ናቸው። ለምሳሌ የሰባስጥያ ሰማዕታትን ብንወስድ በብርድ ሐይቅ ውስጥ እንዲቀዘቅዙ በተፈረደባቸው ጊዜ፣ አንደኛው መከራውን መታገሥ አቅቶት ከመካከላቸው ወጥቶ ወደ ሞቀው ቤት ሲሮጥ፣ "የድኅነት ፈትል" የሆነችውን ትዕግሥትን አጣ ። የቀሩት 39ኙ ግን በብርዱ ማዕበል ውስጥ ሆነው በትዕግሥት ጸለዩ። በመጨረሻም እስከ መጨረሻው የጸናው ጠባቂ ወታደር የእነርሱን ክብር አይቶ በመቀላቀሉ፣ አርባውም አክሊልን ተቀዳጁ። የመንፈስ ቅዱስ በገና ተብሎ በቤተክርስቲያናችን የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ በትዕግሥት እጥረት ምክንያት የሚመጣውን የፍቅር መቀዝቀዝ በዕንባ ያስተምራል፦ “ትዕግሥት የሌለው ሰው እንደ ተናወጠ ቤት ነው፤ በትንሽ ነፋስ ይወድቃል። በትዕግሥት የምትጸና ነፍስ ግን የጸናች አለት ናት። መከራ ሲበዛብህ ትዕግሥትን እንደ ልብስ ልበሳት፤ እርሷ ከክፉው ፍላጻ ትጠብቅሃለች” ይላል። #ዲያቆን_እስጢፋኖስ_ደጀኔ ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ........
Open in Telegramየድኅነት ፈትል /5/ ስለዚህ ትዕግሥት ከእምነት ተነጥላ ልትታይ አትችልም። ከተስፋ ተነጥላ ልትቆም አትችልም ። ከፍቅር ተነጥላ ልትጠነክር አትችልም። ከንስሐ ተነጥላ ውድቀትን ልታሸንፍ አትችልም። ከጸሎት ተነጥላ የሰውን ድካም ልትቋቋም አትችልም። ከጽናት ተነጥላም ❝እስከ መጨረሻ❞ የሚለውን የጌታ ቃል መፈጸም አይቻልም። አንድ ፈትል ቀጭን ሊሆን ይችላል፤ ብዙ ፈትሎች ግን ተጠራርተው ጠንካራ ገመድ ይሆናሉ። የክርስቲያንም ሕይወት እንዲሁ ነው። እ ምነት ብቻውን፣ ተስፋ ብቻውን፣ ፍቅር ብቻውን፣ ጸሎት ብቻውን ወይም ትዕግሥት ብቻዋን ሳይሆን እነዚህ ሁሉ ተያይዘው የክርስቲያናዊ ሕይወትን ይጠነክራሉ። መከራ ትዕግሥትን ያሳያል፤ ትዕግሥት እምነትን ያጠናክራል፤ እምነት ተስፋን ይወልዳል፤ ተስፋ ፍቅርን ያሳድጋል፤ ፍቅር ንስሐንና በጎ ሥራን ያነሳሳል፤ ንስሐ ወደ ጸሎት ይመልሳል፤ ጸሎት ኃይልን ይሰጣል፤ ኃይል ጽናትን ያበረታታል፤ ጽናትም እስከ መጨረሻ ያደርሳል። ይህ ነው የድኅነት ፈትል ምሥጢር። ስለዚህ ትዕግሥት ማለት ችግር እስኪያልፍ ድረስ ብቻ መጠበቅ አይደለም። ትዕግሥት ማለት ችግሩ ባይወገድም እምነትን መጠበቅ፣ መልሱ ባይታይም ተስፋን መጠበቅ፣ ሰው ቢበድልም ፍቅርን መጠበቅ፣ ብንወድቅም በንስሐ መነሳት፣ ብንደክምም በጸሎት መቆየት፣ መንገዱ ቢረዝምም እስከ መጨረሻ መጽናት ነው ። እናም የጌታችን ቃል ወደ እኛ እንደገና ይመለሳል፦ ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።❞ የድኅነት ፈትሉ እንዳይበጠስ፣ እምነታችን እንዳይፈታ፣ ተስፋችን እንዳይጠፋ፣ ፍቅራችን እንዳይቀዘቅዝ፣ ንስሐችን እንዳይቋረጥና ጸሎታችን እንዳይደርቅ፤ በመከራ መካከል በትዕግሥት፣ በእምነትና በጽናት እስከ መጨረሻ መጓዝ ይገባናል። ምክንያቱም የጀመርነው ጉዞ የሚያምረው ስለጀመርነው ብቻ ሳይሆን፣ እስከ መጨረሻ ስለጸናንበት ነው ። እናም የድኅነት ፈትል የሚጠነክረው በትዕግሥት ነው። በማቴዎስ 24፡13 ላይ የሚገኘው "እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል" የሚለው የጌታችን ቃል፣ የክርስቲያን ሕይወት መለያው "ትዕግሥት" (ጽናት) መሆኑን ያሳያል። በማቴዎስ 24 ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘመን መጨረሻ የተናገራቸው ምልክቶች በሙሉ (ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ የፍቅር መቀዝቀዝ) አማኙን የሚያስጨንቁና እምነቱን የሚፈትኑ ናቸው። በዚህ ታላቅ መናወጥ ውስጥ ግን፣ እግዚአብሔር ለአማንያን የሰጣቸው የሕይወት ሰንሰለት ወይም ❝የድኅነት ፈትል❞ ትዕግሥት ነው ። በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ፣ ትዕግሥት ማለት ዝም ብሎ መከራን መቀበል ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ውስጥ ሳይናወጡ፣ የእግዚአብሔርን ማዳን በጽናት መጠበቅ ማለት ነው። ጌታችን ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና❞ ሲል፣ መከራው እስከሚያበቃ ወይም የሰው ልጅ ዕድሜ እስኪፈጸም ድረስ እምነትን ሳያጎድሉ፣ በሃይማኖት ቀጥ ብሎ መቆምን ያመለክታል። ይህች ጽናት ደግሞ አማኙን በቀጥታ ወደ ዘላለም ድኅነት የምታደርስ ፈትል ናት። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 12 ላይ ጌታችን፦ ❝ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች❞ ይላል። ይህ ለአማኝ ትልቁ ፈተና ነው። በዓለም ላይ ክፋት ሲበዛ፣ ሰላም ሲጠፋና ፍቅር ሲጠፋ የሰው ልጅ በቀላሉ ተስፋ ይቆርጣል፤ በክፋት ፋንታ ክፋትን ለመመለስ ይገፋፋል። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ የድኅነት ፈትል የሆነችው ትዕግሥት የምታስፈልገው ። የቅዱሳን አባቶች ትርጓሜ እንደሚያስተምረን፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሁሉ ፍቅራቸው ቢቀዘቅዝም፣ ክርስቲያን ግን በትዕግሥት እሳቱን ጠብቆ መቆየት አለበት። ክፋትን በትዕግሥት ማሸነፍ፣ የክርስቶስ መስቀል ምስጢር ነው ። መከራውን በትዕግሥት ያለፈው ሰው፣ ፍቅሩን ሳይለውጥ እስከ መጨረሻው ይጸናል። #ዲያቆን_እስጢፋኖስ_ደጀኔ ጥቅምት 5 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል .......
Open in Telegramየድኅነት ፈትል /4/ 4. ትዕግሥትና ፍቅር ጌታችን ከማቴዎስ 24፥13 በፊት በ24፥12፦ ❝ክፉነትም ስለሚበዛ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል❞ ብሎ ተናግሯል። ይህ በጣም ጥልቅ ትስስር አለው። ክፋት ሲበዛ ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል፤ ፍቅር ሲቀዘቅዝ ሰው ለሌሎች መራራ ይሆናል፤ መራራነትም ወደ ቂምና በቀል ሊመራ ይችላል። ትዕግሥት ግን በዚህ ሰንሰለት ላይ መከላከያ ትሆናለች። ሰው ቢበድለንም ቂም እንዳንይዝ፣ ቢጎዳንም ፍቅርን እንዳንጥል፣ ቢያስቸግረንም በበቀል እንዳንመለስ ትዕግሥት ትረዳናለች። ስለዚህ ትዕግሥት ፍቅርን ከመቀዝቀዝ የምትጠብቅ ፈትል ናት። እውነተኛ በፍቅርም በትዕግሥት ይታወቃል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ፦ ❝ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትንም ያደርጋል ❞ ብሎ መስክሯል (1ኛ ቆሮንቶስ 13፥4)። 5. ትዕግሥትና ንስሐ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ ሁልጊዜ ያለመውደቅ ጉዞ መጓዝ አይችልም ። ደካማ ነን፤ እንሳሳታለን፤ እንወድቃለን ። አደገኛው ነገር መውደቃችን ብቻ ሳይሆን ከወደቅን በኋላ መነሳትን መተው ነው። እዚህ ላይ ትዕግሥት ከንስሐ ጋር ትገናኛለች። ሰው ኃጢአት ከሠራ በኋላ፦ ❝እኔ ከእንግዲህ አልሻሻልም❞ ብሎ ተስፋ ከቆረጠ በመንፈሳዊ ጉዞው ይቆማል። ትዕግሥት ግን፦ ❝ወድቄያለሁ፤ ነገር ግን እነሳለሁ፤ ንስሐ እገባለሁ፤ እንደገናም እጓዛለሁ❞ እንዲል ትረዳዋለች። ስለዚህ ትዕግሥት ከኃጢአት ጋር መታገሥ አይደለችም፤ ከኃጢአት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል አለመሰልቸት ናት። 6. ትዕግሥትና ጸሎት ትዕግሥት ያለ ጸሎት በሰው ኃይል ብቻ ለመጽናት መሞከር ይሆናል። የሰው ኃይል ግን ውስን ነው። ሰው ይደክማል፤ ይሰለቻል፤ ተስፋም ሊቆርጥ ይችላል። ስለዚህ ጸሎት የትዕግሥት መጠጊያ ነው። በጸሎት ውስጥ ሰው የልቡን ሸክም ለእግዚአብሔር ይሰጣል። የማይችለውን ይነግረዋል፤ የማያውቀውን ይጠይቃል፤ የሚያስፈራውን ያስረክባል። በዚህም ምክንያት ጸሎት ችግሩን ሁልጊዜ ወዲያውኑ ባያስወግድም፣ ችግሩን ለመሸከም የሚያስፈልገውን ጸጋ ይሰጣል። አንዳንድ ጊዜ ጌታ የምንጠይቀውን ነገር ከመስጠት ይልቅ እርሱን ለመሸከም ኃይል ይሰጠናል። ይህም የትዕግሥት ምሥጢር ነው። 7. ትዕግሥትና ጽናት ትዕግሥትና ጽናት ተቀራራቢ ቃላት ቢሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ አንዱ ሌላውን ያጠናክራል። ትዕግሥት በጊዜ ሂደት የሚቆይ ችሎታ ከሆነች፣ ጽናት ደግሞ በአቋም መቆም ነው ማለት እንችላለን ። ይህን ለመረዳት የየትላት ውድቀታችን የዛሬው ጽናታችን ምሥክር ነው ። ችግር ሲመጣ ትዕግሥት፦ ❝ቆይ❞ ትላለች፤ ጽናት ደግሞ፦ ❝አትመለስ❞ ይላል። ፈተና ሲጨምር ትዕግሥት፦ ❝ተሸከም❞ ትላለች፤ ጽናት ደግሞ፦ ❝እምነትህን አትጣ❞ ይላል። መንገዱ ሲረዝም ትዕግሥት፦ ❝ቀጥል❞ ትላለች፤ ጽናት ደግሞ፦ ❝እስከ መጨረሻ❞ ይላል። ስለዚህ ማቴዎስ 24፥13 ላይ ያለው “እስከ መጨረሻ የሚጸና” የሚለው ሐሳብ የትዕግሥትን የመጨረሻ ግብ ያሳያል። ትዕግሥት ለጊዜው ሳይሆን እስከ መጨረሻ እንድንጸና የሚያደርገን የሕይወት ዓምድ ነው ። እግዚአብሔር የክርስቲያኖችን ድኅነት በትዕግሥት የገመደው ለዚህ ነው ። ስለዚህ ዘገኖቼ ትዕግሥት እምነትን ከድኅነት ጋር የምታገናኝ ፈትል ናት ። ይህ የድኅነት ፈትል እነዚህን ሳባት ፈትሎች ገምዶ የሚያጠነክር ዓምድ ነውና ትዕግሥትን የኑሮ ውበታችን ፣ የጉዞ ስንቃችን ፣ የምንደምቅበት ጌጣችን ልናደርጋት ይገባል ። እምነት የመንገዱ መነሻ ናት። ተስፋ ወደፊት የምንመለከትበት ዓይን ናት። ፍቅር በመንገዱ ላይ ከእግዚአብሔርና ከባልንጀሮቻችን ጋር የሚያገናኘን ነው። ንስሐ ከወደቅን በኋላ የምንመለስበት መንገድ ናት። ጸሎት በመንገዱ የምንተነፍስበት መንፈሳዊ ኃይል ነው። ትዕግሥት ግን እነዚህን ሁሉ እስከ መጨረሻ የምታስቀጥል ፈትል ናት። ጽናት ደግሞ በዚያ ፈትል ላይ ተጠምደን እንዳንለይ የሚያደርገን ኃይል ነው። በዲያቆን እስጢፋኖስ ደጀኔ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ..........
Open in TelegramConnections
Similar channels
Orthodox picture ✝@orthodox_photoReligion14K
ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል - Tewahedo Media Center - TMC@tewahedomediacenterReligion13.9K
Mujib Amino Z islam@mujibbinislamReligion13.8K
EQUIP Media/Mamusha Fenta@mamusha_fentaReligion14.4K
ወርቃማ ንግግሮች@golden_speechReligion13.8K
የኡስታዝ ሱልጣን ኸድር የትምህርት መድረክ (official)@sultan_54Religion13.3K
ISLAM IS UNIVERSITY@islamisuniverstiy_public_groupReligion13.2K
𝙞𝙗𝙧𝙖𝙝𝙞𝙢 𝙝𝙚𝙮𝙧𝙚𝙙𝙞𝙣 𝙘𝙝𝙖𝙣𝙣𝙚𝙡@ibrahim_furiiReligion15.1K