Account

Posts of ኖላዊ ኄር ዘ-ኦርቶዶክስ

newest first

#2169Text

የድኅነት ፈትል /6/ በማቴዎስ 24 ማጠቃለያ ላይ ጌታችን ስለ ታማኙ አገልጋይና ሰነፎች ደናግል (በምዕራፍ 25 የሚቀጥለው) የሚያስተምረን ትምህርት ከትዕግሥት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ሙሽራው (ክርስቶስ) ቢዘገይም፣ ታማኙ አገልጋይ ግን በትዕግሥት ይጠብቀዋል። እዚህ ላይ ትዕግሥት ሰነፍ አያደርግም፤ ይልቁንም ዘይት (መልካም ሥራንና ሃይማኖትን) ይዞ በንቃት እንድንጠባበቅ ያደርገናል። ትዕግሥት ለብቻዋ አትቆምም፤ ከጸሎት፣ ከጾም እና ከበጎ ምግባር ጋር የተሳሰረች የ ድኅነት ፈትል አካል ናት። እግዚአብሔር የመምጣቱን ዘመኑንና ሰዓቱን የሰወረበት ዋና ምክኒያት፣ እኛ ዘወትር በትዕግሥትና በንቃት እንድንኖርና የጽናት አክሊል እንድንቀዳጅ ነው። በማቴዎስ 24 የተጻፈው ትንቢት የዓለምን መፍረስ ብቻ የሚያሳይ ሳይሆን፣ አማኞች በጽናት አልፈው የሚድኑበትን መንገድ የሚያበራ ብርሃንም ጭምር ው ። የድኅነት ፈትል የሆነችው ትዕግሥትም ፣ አማኙን ከምድር መከራ አውጥታ ከሰማያዊው ክብር ጋር የምታገናኝ ድልድይ ናት። ስለዚህ፣ በዚህ ምዕራፍ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲፈጸሙ ስናይ የምንደነግጥ ሳይሆን፣ በትዕግሥት የምንጸናበትና የድኅነታችንን ቀን የምንናፍቅበት ሊሆን ይገባል። በማቴዎስ 24፡13 ላይ ያለውን ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል❞ የሚለውን የጌታ ቃል፣ የቤተክርስቲያን አባቶች በጥልቀት ተርጉመውታል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህ ታላቅ አባት የጌታን ቃል ሲተረጉም እንዲህ ይላል፦ "ጌታችን 'እስከ መጨረሻ የሚጸና' ሲል፣ መከራው ለአንድ አፍታ መጥቶ የሚያልፍ ሳይሆን፣ እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ የሚቀጥል መሆኑን ለማሳየት ነው። የብዙዎች ፍቅር በሚቀዘቅዝበት በዚያ ጨለማ ሰዓት ውስጥ፣ አማኝ እንደ መብራት በትዕግሥት ማብራት አለበት። መዳን የሚገኘው በትግሉ መጀመሪያ ላይ ሳይሆን፣ በትግሉ ማጠቃለያ ላይ በጽናት ለተገኘው ነው" ደጰይላል። ቅዱስ ቆጵሪያኖስ ስለ ትዕግሥት በጻፈው ድርሳኑ ላይ፦ "የእኛ እምነትና ተስፋ ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርገው ትዕግሥት ነው። ክርስቲያን መሆን በራሱ በትዕግሥት ጎዳና ላይ መጓዝ ማለት ነው። ያነበብነውን ቃልና የተቀበልነውን ምስጢር አጽንቶ የሚያቆየው ትዕግሥት ነው በማለት ያስተምራል። አረጋዊ መንፈሳዊ በጽናት መከራን ስለመቀበል ሲናገር፦ መከራን በትዕግሥት መሸከም ሰማዕትነት ነው። ሰማዕትነት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምታስገባ የድኅነት በር ናት ይላል። በማቴዎስ 24 የተጠቀሰውን መከራ በትዕግሥት በማለፍ፣ "የድኅነት ፈትል" የሆነችውን ሃይማኖታቸውን አጥብቀው የያዙት ሕያው ምስክሮቻችን ሰማዕታት ናቸው። ለምሳሌ የሰባስጥያ ሰማዕታትን ብንወስድ በብርድ ሐይቅ ውስጥ እንዲቀዘቅዙ በተፈረደባቸው ጊዜ፣ አንደኛው መከራውን መታገሥ አቅቶት ከመካከላቸው ወጥቶ ወደ ሞቀው ቤት ሲሮጥ፣ "የድኅነት ፈትል" የሆነችውን ትዕግሥትን አጣ ። የቀሩት 39ኙ ግን በብርዱ ማዕበል ውስጥ ሆነው በትዕግሥት ጸለዩ። በመጨረሻም እስከ መጨረሻው የጸናው ጠባቂ ወታደር የእነርሱን ክብር አይቶ በመቀላቀሉ፣ አርባውም አክሊልን ተቀዳጁ። የመንፈስ ቅዱስ በገና ተብሎ በቤተክርስቲያናችን የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ በትዕግሥት እጥረት ምክንያት የሚመጣውን የፍቅር መቀዝቀዝ በዕንባ ያስተምራል፦ “ትዕግሥት የሌለው ሰው እንደ ተናወጠ ቤት ነው፤ በትንሽ ነፋስ ይወድቃል። በትዕግሥት የምትጸና ነፍስ ግን የጸናች አለት ናት። መከራ ሲበዛብህ ትዕግሥትን እንደ ልብስ ልበሳት፤ እርሷ ከክፉው ፍላጻ ትጠብቅሃለች” ይላል። #ዲያቆን_እስጢፋኖስ_ደጀኔ ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ........

Open in Telegram
Views6,480−73%vs avg
Forwards—
Reactions42
Comments—
#2167Text

የድኅነት ፈትል /5/ ስለዚህ ትዕግሥት ከእምነት ተነጥላ ልትታይ አትችልም። ከተስፋ ተነጥላ ልትቆም አትችልም ። ከፍቅር ተነጥላ ልትጠነክር አትችልም። ከንስሐ ተነጥላ ውድቀትን ልታሸንፍ አትችልም። ከጸሎት ተነጥላ የሰውን ድካም ልትቋቋም አትችልም። ከጽናት ተነጥላም ❝እስከ መጨረሻ❞  የሚለውን የጌታ ቃል መፈጸም አይቻልም። አንድ ፈትል ቀጭን ሊሆን ይችላል፤ ብዙ ፈትሎች ግን ተጠራርተው ጠንካራ ገመድ ይሆናሉ። የክርስቲያንም ሕይወት እንዲሁ ነው። እ ምነት ብቻውን፣ ተስፋ ብቻውን፣ ፍቅር ብቻውን፣ ጸሎት ብቻውን ወይም ትዕግሥት ብቻዋን ሳይሆን እነዚህ ሁሉ ተያይዘው የክርስቲያናዊ ሕይወትን ይጠነክራሉ። መከራ ትዕግሥትን ያሳያል፤ ትዕግሥት እምነትን ያጠናክራል፤ እምነት ተስፋን ይወልዳል፤ ተስፋ ፍቅርን ያሳድጋል፤ ፍቅር ንስሐንና በጎ ሥራን ያነሳሳል፤ ንስሐ ወደ ጸሎት ይመልሳል፤ ጸሎት ኃይልን ይሰጣል፤ ኃይል ጽናትን ያበረታታል፤ ጽናትም እስከ መጨረሻ ያደርሳል። ይህ ነው የድኅነት ፈትል ምሥጢር። ስለዚህ ትዕግሥት ማለት ችግር እስኪያልፍ ድረስ ብቻ መጠበቅ አይደለም። ትዕግሥት ማለት ችግሩ ባይወገድም እምነትን መጠበቅ፣ መልሱ ባይታይም ተስፋን መጠበቅ፣ ሰው ቢበድልም ፍቅርን መጠበቅ፣ ብንወድቅም በንስሐ መነሳት፣ ብንደክምም በጸሎት መቆየት፣ መንገዱ ቢረዝምም እስከ መጨረሻ መጽናት ነው ። እናም የጌታችን ቃል ወደ እኛ እንደገና ይመለሳል፦  ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።❞   የድኅነት ፈትሉ እንዳይበጠስ፣ እምነታችን እንዳይፈታ፣ ተስፋችን እንዳይጠፋ፣ ፍቅራችን እንዳይቀዘቅዝ፣ ንስሐችን እንዳይቋረጥና ጸሎታችን እንዳይደርቅ፤ በመከራ መካከል በትዕግሥት፣ በእምነትና በጽናት እስከ መጨረሻ መጓዝ ይገባናል። ምክንያቱም የጀመርነው ጉዞ የሚያምረው ስለጀመርነው ብቻ ሳይሆን፣ እስከ መጨረሻ ስለጸናንበት ነው ። እናም የድኅነት ፈትል የሚጠነክረው በትዕግሥት ነው። በማቴዎስ 24፡13 ላይ የሚገኘው "እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል" የሚለው የጌታችን ቃል፣ የክርስቲያን ሕይወት መለያው "ትዕግሥት" (ጽናት) መሆኑን ያሳያል። በማቴዎስ 24 ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘመን መጨረሻ የተናገራቸው ምልክቶች በሙሉ (ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ የፍቅር መቀዝቀዝ) አማኙን የሚያስጨንቁና እምነቱን የሚፈትኑ ናቸው። በዚህ ታላቅ መናወጥ ውስጥ ግን፣ እግዚአብሔር ለአማንያን የሰጣቸው የሕይወት ሰንሰለት ወይም  ❝የድኅነት ፈትል❞   ትዕግሥት ነው ። በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ፣ ትዕግሥት ማለት ዝም ብሎ መከራን መቀበል ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ውስጥ ሳይናወጡ፣ የእግዚአብሔርን ማዳን በጽናት መጠበቅ ማለት ነው። ጌታችን  ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና❞  ሲል፣ መከራው እስከሚያበቃ ወይም የሰው ልጅ ዕድሜ እስኪፈጸም ድረስ እምነትን ሳያጎድሉ፣ በሃይማኖት ቀጥ ብሎ መቆምን ያመለክታል። ይህች ጽናት ደግሞ አማኙን በቀጥታ ወደ ዘላለም ድኅነት የምታደርስ ፈትል ናት። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 12 ላይ ጌታችን፦ ❝ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች❞ ይላል። ይህ ለአማኝ ትልቁ ፈተና ነው። በዓለም ላይ ክፋት ሲበዛ፣ ሰላም ሲጠፋና ፍቅር ሲጠፋ የሰው ልጅ በቀላሉ ተስፋ ይቆርጣል፤ በክፋት ፋንታ ክፋትን ለመመለስ ይገፋፋል። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ የድኅነት ፈትል የሆነችው ትዕግሥት የምታስፈልገው ። የቅዱሳን አባቶች ትርጓሜ እንደሚያስተምረን፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሁሉ ፍቅራቸው ቢቀዘቅዝም፣ ክርስቲያን ግን በትዕግሥት እሳቱን ጠብቆ መቆየት አለበት። ክፋትን በትዕግሥት ማሸነፍ፣ የክርስቶስ መስቀል ምስጢር ነው ። መከራውን በትዕግሥት ያለፈው ሰው፣ ፍቅሩን ሳይለውጥ እስከ መጨረሻው ይጸናል። #ዲያቆን_እስጢፋኖስ_ደጀኔ ጥቅምት 5 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል .......

Open in Telegram
Views6,620−72%vs avg
Forwards—
Reactions50
Comments—
#2165Text

የድኅነት ፈትል /4/ 4. ትዕግሥትና ፍቅር ጌታችን ከማቴዎስ 24፥13 በፊት በ24፥12፦ ❝ክፉነትም ስለሚበዛ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል❞ ብሎ ተናግሯል። ይህ በጣም ጥልቅ ትስስር አለው። ክፋት ሲበዛ ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል፤ ፍቅር ሲቀዘቅዝ ሰው ለሌሎች መራራ ይሆናል፤ መራራነትም ወደ ቂምና በቀል ሊመራ ይችላል። ትዕግሥት ግን በዚህ ሰንሰለት ላይ መከላከያ ትሆናለች። ሰው ቢበድለንም ቂም እንዳንይዝ፣ ቢጎዳንም ፍቅርን እንዳንጥል፣ ቢያስቸግረንም በበቀል እንዳንመለስ ትዕግሥት ትረዳናለች። ስለዚህ ትዕግሥት ፍቅርን ከመቀዝቀዝ የምትጠብቅ ፈትል ናት። እውነተኛ በፍቅርም በትዕግሥት ይታወቃል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ፦ ❝ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትንም ያደርጋል ❞ ብሎ መስክሯል (1ኛ ቆሮንቶስ 13፥4)። 5. ትዕግሥትና ንስሐ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ ሁልጊዜ ያለመውደቅ ጉዞ መጓዝ አይችልም ። ደካማ ነን፤ እንሳሳታለን፤ እንወድቃለን ። አደገኛው ነገር መውደቃችን ብቻ ሳይሆን ከወደቅን በኋላ መነሳትን መተው ነው። እዚህ ላይ ትዕግሥት ከንስሐ ጋር ትገናኛለች። ሰው ኃጢአት ከሠራ በኋላ፦ ❝እኔ ከእንግዲህ አልሻሻልም❞ ብሎ ተስፋ ከቆረጠ በመንፈሳዊ ጉዞው ይቆማል። ትዕግሥት ግን፦ ❝ወድቄያለሁ፤ ነገር ግን እነሳለሁ፤ ንስሐ እገባለሁ፤ እንደገናም እጓዛለሁ❞ እንዲል ትረዳዋለች። ስለዚህ ትዕግሥት ከኃጢአት ጋር መታገሥ አይደለችም፤ ከኃጢአት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል አለመሰልቸት ናት። 6. ትዕግሥትና ጸሎት ትዕግሥት ያለ ጸሎት በሰው ኃይል ብቻ ለመጽናት መሞከር ይሆናል። የሰው ኃይል ግን ውስን ነው። ሰው ይደክማል፤ ይሰለቻል፤ ተስፋም ሊቆርጥ ይችላል። ስለዚህ ጸሎት የትዕግሥት መጠጊያ ነው። በጸሎት ውስጥ ሰው የልቡን ሸክም ለእግዚአብሔር ይሰጣል። የማይችለውን ይነግረዋል፤ የማያውቀውን ይጠይቃል፤ የሚያስፈራውን ያስረክባል። በዚህም ምክንያት ጸሎት ችግሩን ሁልጊዜ ወዲያውኑ ባያስወግድም፣ ችግሩን ለመሸከም የሚያስፈልገውን ጸጋ ይሰጣል። አንዳንድ ጊዜ ጌታ የምንጠይቀውን ነገር ከመስጠት ይልቅ እርሱን ለመሸከም ኃይል ይሰጠናል። ይህም የትዕግሥት ምሥጢር ነው። 7. ትዕግሥትና ጽናት ትዕግሥትና ጽናት ተቀራራቢ ቃላት ቢሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ አንዱ ሌላውን ያጠናክራል። ትዕግሥት በጊዜ ሂደት የሚቆይ ችሎታ ከሆነች፣ ጽናት ደግሞ በአቋም መቆም ነው ማለት እንችላለን ። ይህን ለመረዳት የየትላት ውድቀታችን የዛሬው ጽናታችን ምሥክር ነው ። ችግር ሲመጣ ትዕግሥት፦ ❝ቆይ❞ ትላለች፤ ጽናት ደግሞ፦ ❝አትመለስ❞ ይላል። ፈተና ሲጨምር ትዕግሥት፦ ❝ተሸከም❞ ትላለች፤ ጽናት ደግሞ፦ ❝እምነትህን አትጣ❞ ይላል። መንገዱ ሲረዝም ትዕግሥት፦ ❝ቀጥል❞ ትላለች፤ ጽናት ደግሞ፦ ❝እስከ መጨረሻ❞ ይላል። ስለዚህ ማቴዎስ 24፥13 ላይ ያለው “እስከ መጨረሻ የሚጸና” የሚለው ሐሳብ የትዕግሥትን የመጨረሻ ግብ ያሳያል። ትዕግሥት ለጊዜው ሳይሆን እስከ መጨረሻ እንድንጸና የሚያደርገን የሕይወት ዓምድ ነው ። እግዚአብሔር የክርስቲያኖችን ድኅነት በትዕግሥት የገመደው ለዚህ ነው ። ስለዚህ ዘገኖቼ ትዕግሥት እምነትን ከድኅነት ጋር የምታገናኝ ፈትል ናት ። ይህ የድኅነት ፈትል እነዚህን ሳባት ፈትሎች ገምዶ የሚያጠነክር ዓምድ ነውና ትዕግሥትን የኑሮ ውበታችን ፣ የጉዞ ስንቃችን ፣ የምንደምቅበት ጌጣችን ልናደርጋት ይገባል ። እምነት የመንገዱ መነሻ ናት። ተስፋ ወደፊት የምንመለከትበት ዓይን ናት። ፍቅር በመንገዱ ላይ ከእግዚአብሔርና ከባልንጀሮቻችን ጋር የሚያገናኘን ነው። ንስሐ ከወደቅን በኋላ የምንመለስበት መንገድ ናት። ጸሎት በመንገዱ የምንተነፍስበት መንፈሳዊ ኃይል ነው። ትዕግሥት ግን እነዚህን ሁሉ እስከ መጨረሻ የምታስቀጥል ፈትል ናት። ጽናት ደግሞ በዚያ ፈትል ላይ ተጠምደን እንዳንለይ የሚያደርገን ኃይል ነው። በዲያቆን እስጢፋኖስ ደጀኔ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ..........

Open in Telegram
Views7,900−67%vs avg
Forwards—
Reactions61
Comments—
#2163Text

የድኅነት ፈትል /3/ 1. ትዕግሥትና መከራ ትዕግሥት በምቾት ጊዜ ብቻ አትፈተንም፤ እውነተኛ ባሕርይዋ የሚገለጠው በመከራ ጊዜ ነው። መከራ የሰውን ውስጥ የሚመረምር መስታወት ነው። በሰላም ጊዜ ያለን እምነት በመከራ ጊዜ ይፈተናል፤ በአፋችን የምንናገረው ተስፋ በመከራ ጊዜ በሕይወታችን ይመዘናል። መከራ ሲመጣ ሰው ሁለት መንገዶች ፊት ሊቆም ይችላል። አንደኛው በመከራው ተሸንፎ ከእግዚአብሔር መራቅ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ በመከራው መካከል ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ መቅረብ ነው። ትዕግሥት የሚመርጠው ሁለተኛውን መንገድ ነው። ስለዚህ መከራ የትዕግሥት ጠላት ብቻ አይደለም፤ ትዕግሥት የምትገለጥበት መድረክም ነው ። ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፣ እምነትም በፈተና ይፈተናል። ስለዚህ በመከራ ጊዜ መታገሥ ማለት መከራውን መውደድ ሳይሆን፣ በመከራው መካከል ከክርስቶስ ጋር መቆየት ነው። 2. ትዕግሥትና እምነት ትዕግሥት ከእምነት የተለየች አይደለችም። ሰው የሚታገሠው በመጨረሻ ነገሩ እንደሚሻል በሚያምንበት ጊዜ ነው። ክርስቲያን ደግሞ ትዕግሥቱን የሚመሠርተው በሰው ኃይል ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት ነው። እምነት የሚለው፦ ❝እግዚአብሔር አለ፣ ይሰማኛል፣ ያውቀኛል፣ ይጠብቀኛል❞ ብሎ መታመን ነው። ትዕግሥት ደግሞ፦ ❝እምንም እንኳን መልሱ ዛሬ ባይታየኝም እግዚአብሔርን አልተውም❞ ብሎ መጠበቅ ነው። ስለዚህ እምነት የትዕግሥት ሥር ነው ። ሥር ከሌለው ዛፍ ፍሬ እንደማይገኝ፣ እምነት ከሌለ እውነተኛ ትዕግሥትም አትጸናም ። 3. ትዕግሥትና ተስፋ ትዕግሥት ያለ ተስፋ እጅግ ከባድ ነው ። ሰው ለምን እንደሚታገሥ ማወቅ አለበት። ክርስቲያን የሚታገሠው ችግሩን ስለሚወደው አይደለም፤ ከችግሩ በላይ ያለውን ተስፋ ስለሚያይ ነው ። ተስፋ ማለት ችግሩ እንደማይኖር ማሰብ አይደለም። ችግሩ ቢኖርም እግዚአብሔር ከችግሩ የሚበልጥ መሆኑን ማመን ነው። ስለዚህ ተስፋ ትዕግሥትን የምትመግብ መንፈሳዊ ምግብ ናት። ተስፋ ሲኖር ሰው፦ ❝ዛሬ ባይሆንም ነገ አለ፤ እኔ ባላየውም እግዚአብሔር ያያል፤ መንገዱን ባላውቅም መሪዬን አውቃለሁ❞ ብሎ ይቀጥላል። በዲያቆን እስጢፋኖስ ደጀኔ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ....

Open in Telegram
Views7,880−67%vs avg
Forwards—
Reactions71
Comments—
#2161Text

የድኅነት ፈትል/2/ ስለዚህ “የድኅነት ፈትል” ብለን ትዕግሥትን ስንጠራ፣ ትዕግሥት ሰውን በራሷ የምታድን ኃይል ናት ማለት አይደለም። ድኅነት ምንጩና መሠረቱ በክርስቶስ ነው። እርሱ ለድኅነታችን መንገዱን ከፍቶልናል፤ እኛም በእምነትና በጸጋው ውስጥ እየኖርን በዚህ መንገድ እንጓዛለን። ትዕግሥት ደግሞ በዚህ መንገድ ላይ እንዳንሰናከል፣ እንዳንመለስና እንዳንተው የሚያግዘን ፈትል ነው። ይህ ፈትል በተለይ የሚፈተነው መከራ ሲመጣ ነው ። በደስታ ጊዜ ሁሉም ሰው ሊያመሰግን ይችላል፤ በብርታት ጊዜ መጽናት ቀላል ሊሆን ይችላል። የትዕግሥት እውነተኛ ዋጋ ግን በሕይወት ነገሮች እንደፈለግነው ባልሆኑ ጊዜ ይገለጣል። ጸሎት መልስ እንዳላገኘ ሲመስል፣ መከራ ሲረዝም፣ ችግር ሲደጋገም፣ ሰው ሲበድለን፣ እኛም ስንደክም ትዕግሥት ይነሳልና ይጠይቀናል፦ “እስከ መጨረሻ ትጸናለህን?” ይህ ጥያቄ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የቀረበ ጥያቄ ነው። ዛሬ ማመን ብቻ አይበቃም፤ እስከ መጨረሻ መጽናት ያስፈልጋል። ዛሬ መጸለይ ብቻ አይበቃም፤ በጸሎት ላይ መጽናት ያስፈልጋል። ዛሬ ፍቅር ማሳየት ብቻ አይበቃም፤ ፍቅራችን በተፈተነ ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል። ዛሬ በንስሐ መጀመር ብቻ አይበቃም፤ ከኃጢአት ጋር ያለውን ትግል እስከ መጨረሻ መቀጠል ያስፈልጋል ። በዚህ ምክንያት ትዕግሥት በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ትንሽ ቦታ የሚይዝ ባሕርይ ሳይሆን፣ መንፈሳዊ ጉዞን እስከ ግቡ የሚያስቀጥል ኃይል ነው። እምነት ይጀምራል፤ ተስፋ ያበረታታል፤ ፍቅር ያስተሳስራል፤ ጸሎት ያጠናክራል፤ ንስሐ ያድሳል፤ ትዕግሥት ግን እስከ መጨረሻ ያስቀጥላል። ስለዚህ የድኅነት መንገድ በብዙ መንፈሳዊ ጸጋዎችና በበጎ ሥራዎች የተሸለመ ቢሆንም፣ በፈተና ጊዜ እነዚህን ሁሉ እስከ መጨረሻ የሚያገናኝ አንድ ጠንካራ ፈትል ያስፈልገዋል። ይህም ትዕግሥት ነው ። እንግዲህ የዚህ ጽሑፍ ዋና ጥያቄ ይህ ይሆናል፦ ትዕግሥት እንዴት የድኅነት ፈትል ይሆናል? እንዴትስ እምነታችንን በመከራ መካከል ጠብቆ እስከ መጨረሻ ያደርሰናል? የዚህን ጥያቄ መልስ ስንፈልግ ትዕግሥትን ከመከራ፣ ከእምነት፣ ከተስፋ፣ ከፍቅር፣ ከንስሐ፣ ከጸሎትና ከጽናት ጋር በማያያዝ እንመለከታለን። ምክንያቱም ጌታችን በግልጽ እንደተናገረው፦ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” ይህ ቃል የድኅነት መንገዳችንን እንዳንተው፣ በፈተና እንዳንሰናከል፣ በመከራ እንዳንደክምና በጨለማ ጊዜ ተስፋችንን እንዳንጥል የሚጠራን የጌታ የፍቅር ጥሪ ነው። እስከ መጨረሻ የሚያስቀጥለን ፈትል፣ በፈተና ውስጥ የሚያጠነክረን ጽናት፣ እና ከክርስቶስ ጋር እስከ ድኅነት የሚያደርሰን ትዕግሥት ነው ። #ዲያቆን_እስጢፋኖስ_ደጀኔ መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም ይቀጥላል ........

Open in Telegram
Views8,310−65%vs avg
Forwards—
Reactions48
Comments—
#2159Text

❝የድኅነት ፈትል❞ /1/ ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። (የማቴዎስ ወንጌል 24:13 )❞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት፣ የወንጌላውያን አለቃ ቅዱስ ማቴዎስ የጻፈው ወንጌል ምዕራፍ 24 ልዩ ስፍራ አለው ። ይህ ክፍል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማቱንና ሞቱን ከመቀበሉ አስቀድሞ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ታላቅ የትንቢትና የትምህርት ክፍል ነው ። በቤተክርስቲያን ሥርዓት ይህ የጌታ ንግግር ❝የደብረ ዘይት ትምህርት❞ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት (ደብረ ዘይት) በስፋት ይዘከራል፣ ይተረጎማል። ምዕራፉ የሚጀምረው ደቀ መዛሙርቱ በዕደ ጥበቡና በድንጋዮቹ ታላቅነት ይደነቁበት የነበረውን የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ለጌታ በማሳየት ነው ። ጌታችን ግን የዓለም ክብርና ውበት አላፊ መሆኑን ሲያስረዳቸው፦ ❝ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም❞ አላቸው ። ይህ ንግግር በደቀ መዛሙርቱ ልብ ውስጥ ታላቅ ድንጋጤንና ጉጉትን ፈጠረ ። በመቀጠል በደብረ ዘይት ተራራ ለብቻቸው በተቀመጡ ጊዜ፣ የነገረ ፍጻሜን (Eschatology) ምስጢር የሚከፍቱ ሦስት ታላላቅ ጥያቄዎችን ሰነዘሩ፦ - ❝ይህ መቼ ይሆናል?❞ (ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋትና ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ) - ❝የመምጣትህ ምልክት ምንድር ነው?❞ (ስለ ዳግም ምጽአቱ) - ❝የዓለምስ መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነው?❞ (ስለ ዘመን ፍጻሜ) የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት (እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያሉ) ይህንን ምዕራፍ ሲተረጉሙ ❝ድርብ ፍጻሜ❞ (Dual Fulfillment) እያሉ ያስተምራሉ። ጌታችን በምላሹ ውስጥ ሁለት የተለያዩ የታሪክ ክስተቶችን አጣምሮ ሰጥቷል ይህም ታሪካዊው ክስተትበነቢያት የተነገረለትና ጌታም አስቀድሞ የተነበየው የኢየሩሳሌም መፈራረስ ነው። ይህ ትንቢት በ70 ዓ.ም በሮማውያን ጦር አዛዥ በቲቶ አማካኝነት ፍጹም ፍጻሜ አግኝቷል። ሁለተኛው ክስተት ደግሞ ምስጢራዊው ክስተት የምንለው ሲሆን ። ይህም የዓለም ማለፍና የጌታችን የክብር ዳግም ምጽአት ነው። ጌታችን እነዚህን ሁለት ክስተቶች አሳስሮ ያስተማረበት ምክንያት፣ የኢየሩሳሌም መጥፋት ለዓለም ማለፊያ ማሳየያ ስለሆነ ነው ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሐሰተኞች ክርስቶሶች መነሳት፣ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈርና የምድር መንቀጥቀጥ ፣ የክርስቲያኖች የምጥ ጣር መጀመሪያ ምልክት ተብለው ተገልጠዋል። ቤተክርስቲያናችን እነዚህን ምልክቶች ስታስተምር ምዕመናን በፍርሃት እንዲዋጡ ሳይሆን፣ መጻተኛ በሆነችው በዚህች ምድር ላይ ሲኖሩ ዘወትር በንቃትና በጸሎት እንዲተጉ ነው ። በተለይም ጌታችን ❝ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም❞ ማለቱ፣ የዕለቱን ቀነ-ቀጠሮ በትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ የሚደክሙ የሐሰት መምህራንን መንገድ የሚዘጋ ነው ። ምስጢሩ የተሸሸገው ክርስቲያኖች ዘወትር ተዘጋጅተው እንዲኖሩ ለማድረግ ነው። ይህ ረጅም ትንቢታዊ ንግግር መደምደሚያ በምዕራፉ መጨረሻ ላይ በሚገኙት በታማኙና በክፉው አገልጋይ ምሳሌዎች ይጠቃለላል። ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትም ዋና ዓላማ የዓለም መጨረሻ የሚሆንበትን ዓመተ ምሕረት መቁጠር ሳይሆን፣ ጌታ በድንገት በሚመጣበት ጊዜ ንቁ ፣ ታማኝና ታጋሽ ሆኖ መገኘት ነው። የምዕራፉን ዋና አሳብ ከተረዳን ለዚህ ትምህርት መግቢያ ያደረግነውን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24:13 ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ቃል እንመልከት ፦ ቃሉ ❝እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ❞ ይላል ። ቅዱስ ፓይስዮስ ❝በአመስጋኝነት ታገሡ ፣ እናም በቅርቡ በእግዚአብሔር ምሕረት ታገኛላችሁ። እግዚአብሔር የሰዎችን መዳን ከትዕግስት ጋር አስሮታል። እስከ መጨረሻ የሚጸና ይድናል ይላል ወንጌል። ሰዎች ትዕግሥትን እንዲለማመዱ እግዚአብሔር መከራንና ልዩ ልዩ ፈተናዎችን የሚፈቅደው ለዚህ ነው ።❞ ይላል ። የሰው ልጅ ከዚህ ዓለም ወደ ማያልፈው ሕይወት የሚያደርገው ጉዞ ቀላልና ያለ ፈተና የሆነ መንገድ አይደለም ። ከተወለድንበት ቀን ጀምሮ እስከ የምድራዊ ሕይወታችን መጨረሻ ድረስ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች፣ በደስታና በሐዘን፣ በድልና በሽንፈት፣ በብርሃንና በጨለማ፣ በቀላልና በከባድ መንገዶች እንጓዛለን ። ክርስቲያናዊ ሕይወትም ከዚህ የሕይወት ጉዞ ውጭ አይደለም ። ይልቁንም ሰው በዚህ ዓለም ላይ እየኖረ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያደርገው መንፈሳዊ ጉዞ ነው ። ይህ ጉዞ ግን ሁልጊዜ በአበባ የተሸፈነ አይደለም ። አንዳንዴ የመከራ ጎዳና ይሆናል፤ አንዳንዴ የፈተና ሸለቆ ውስጥ እንደምንጓዝ ይሰማናል። የሚያስተናግደን ችግር እንደማይጨርስ ሊመስለን ይችላል። የጸሎታችን መልስ ሊዘገይ ይችላል። የተስፋ ብርሃን ሊርቀን ይችላል። በሰዎች ልብ ያለው ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል፤ እኛም እስከመጨረሻው የምንጓዝበትን ኃይል እንዳጣን ልንሰማ እንችላለን ። በዚህ ሁሉ መካከል ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ የተናገረው አንድ አጭር ቃል አለ፤ ነገር ግን በውስጡ የያዘው ትርጉም እጅግ ጥልቅ ነው፦ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” (ማቴዎስ 24፥13) ይህ ቃል የተነገረው በቀላል የሕይወት ሁኔታ ውስጥ አይደለም። ጌታችን ስለ ዘመኑ መጨረሻ፣ ስለሚመጣው መከራ፣ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት፣ ስለ ክፋት መብዛትና ስለ ብዙዎች ፍቅር መቀዝቀዝ ካስጠነቀቀ በኋላ ይህን ቃል ተናገረ። በዚህ አውድ ውስጥ የ“መጽናት” ቃል ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። መከራ ሲመጣ መሸሽ ሳይሆን፣ ፈተና ሲበዛ እምነትን አለመተው፤ ክፋት ሲበዛ በጎነትን አለመተው፤ ፍቅር ሲቀዘቅዝ ፍቅርን መጠበቅ፤ ችግር ሲረዝም ተስፋን አለመጣል ማለት ነው ። በዚህ ቃል ውስጥ የምናገኘው ትዕግሥት ደካማው የሰው ባሕርይ ብቻ አይደለም። ትዕግሥት በፈተና መካከል እምነትን የሚያስቀጥል፣ በውድቀት መካከል ንስሐን የሚያስቀጥል፣ በመከራ መካከል ተስፋን የሚያስቀጥል፣ በሰዎች መካከል ፍቅርን የሚጠብቅ መንፈሳዊ ጽናት ነው። ስለዚህ ትዕግሥት በክርስቲያናዊ ጉዞ ላይ ያለ ተጨማሪ ጌጥ ሳይሆን፣ ጉዞውን እስከ መጨረሻ የሚያስቀጥል ኃይል ነው ። እዚህ ላይ “ፈትል” የሚለው ምሳሌ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። አንድ ፈትል በራሱ ቀጭንና ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ብዙ ፈትሎች ተጠራርተው ሲጠነክሩ ጠንካራ ገመድ ይሆናሉ። እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሕይወት በአንድ ባሕርይ ብቻ የሚገነባ አይደለም። እምነት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ጸሎት፣ ንስሐ፣ ትሕትና፣ ታዛዥነትና ትዕግሥት እርስ በርስ ተጠራርተው የሚጠነክሩ የአንድ መንፈሳዊ ሕይወት ፈትሎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ትዕግሥት ግን በልዩ ሁኔታ የሚያገናኝ ፈትል ነው። ምክንያቱም ሰው በእምነት መጀመር ይችላል፤ በፍቅር ሊሞላ ይችላል፤ በተስፋም ሊነሳሳ ይችላል። ነገር ግን ፈተና ሲመጣ እነዚህን ሁሉ እስከ መጨረሻ እንዲያስቀጥል የሚያደርገው ጽናት ካልነበረው በመንገዱ ሊደክም ይችላል። ትዕግሥት ግን በድካም ጊዜ “ቀጥል” የሚል፣ በውድቀት ጊዜ “ተነሳ” የሚል፣ በጨለማ ጊዜ “ተስፋ አትቁረጥ” የሚል የውስጥ ጥሪ ነው። በዲያቆን እስጢፋኖስ ደጀኔ መስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም. ይቀጥላል ....

Open in Telegram
Views8,190−66%vs avg
Forwards—
Reactions72
Comments—
#2153Text

#ይህችን_ዓመት! አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ (መዝሙረ ዳዊት 51:10) የዘመናት ጌታና ፈጣሪ፣ የሕይወትና የሞት ባለቤት፣ ዘመናትን በእጅህ የያዝህ ቸርና መሐሪ አምላክ ሆይ፤ አንተ በምታውቀው እኔ ግን በማላውቀው ስንቱን አለፍኩት በአንተ ፤ ስንቱን ተሻገርኩት በአንተ ! አቤቱ ከዘመን ወደ ዘመን በምሕረትህ የምታሳልፈኝ አንተ ነህ። ትናንትን አሳልፈህ ዛሬን የሰጠኸኝ፣ ዛሬንም አሳልፈህ ነገን የምትሰጠኝ አንተ ነህ። ቸርነትህን እንደ ወንዝ ያፈሰሦክልኝ ፣ በኃጢአት የተጎዳውን ነፍሴን ያለመለምክለሰኝ ፣ በነውር የደከመ አካሌን ያጸናህልኝ የዘመን ስንቄና በረከቴ አንተ ነህ ለስም አጠራርህ ምስጋና ይገባል። ጌታዬ ሆይ ይህችን ዓመትም በባዶ እንዳልቀር ክንድህን ዘርጋልኝ ። የተደገፉህን ስታጸና ፣ ከአሳብህ የራቁትን በምሕረትህ ስጎበኝ ዓይኖቼ አይተውካል ። አቤቱ መድኃኒቴ ሆይ ይህችን ዓመት እንደ በደሌ አትፍረድብኝ ፤ እንደ ኃጢአቴም አትመልስልኝ ። በብዙ ምሕረትህ እየኝ ። በርኅራኄህ ተመልከተኝ ። በቸርነትህ ይቅር በለኝ ። አቤቱ የዚህን አዲስ ዘመን መጀመሪያ የንስሐ መጀመሪያ አድርግልኝ ። ክፉ ልማዴን እድንተው፣ ከክፉ መንገድ እንድመለስ፣ በንስሐም ወደ አንተ እንድንቀርብ ኃይልህን ከጸባዖት አፍስሥልኝ ። አቤቱ ይህችን ዓመት፣ በአፌ ብቻ “ጌታዬ ጌታዬ” እንዳልልህ፤ በሕይወቴም ፈቃድህን እድፈጽም እርዳኝ። አንተን ማመኔ በቃል ብቻ እንዳይቀር፤ በሥራ፣ በኑሮ፣ በአሳብና በልብ የሚታይ እውነተኛ እምነት አድርግልኝ ። ጌታዬ ሆይ ይህችን ዓመት ከርኩሰት፣ ከስስት፣ ከትዕቢት፣ ከቂም፣ ከጥላቻ፣ ከሐሰት፣ ከስድብ፣ ከሐሜት፣ ከበቀል የኃጢአት ሥራ ሰውረኝ ። ይህችን ዓመት የተሰበረውን ልቤን ፈውስ፤ የጠፋውን እምነቴን መልስ፤ የደከመውን ተስፋዬን አጽና፤ ከክፉ አሳብ አንጻኝ፤ ልቤንም በቅዱስ መንፈስህ ቀድሰህ አድሰው ። በሚያኖረኝ ቸርነትህ ለዘለዓለሙ አሜን!! የደስታ ዘመን ይሁንላችሁ!! #በዲያቆን_እስጢፋኖስ_ደጀኔ መስከረም 2 ቀን 2019 የምሕረት ዓመት.

Open in Telegram
Views12,400−48%vs avg
Forwards—
Reactions109
Comments—