ንስሓ የተስፋ በር ናት፤ ተስፋ አትቁረጡ! ውድ ወጣቶች፣ በንስሐ ሕይወት ውስጥ እየታገላችሁ ላላችሁ፣ ከአንዳንድ ኃጢአቶች ለመራቅ ደጋግማችሁ ሞክራችሁ ነገር ግን እንደገና ለድክመታችሁ ለምትሸነፉ፣ አንድ ነገር ልንገራችሁ። ተስፋ አትቁረጡ! አንዳንድ ጊዜ ሰው ከኃጢአቱ ለመመለስ ይወስናል፤ ይጸልያል፣ ይጾማል፣ ንስሓ ይገባል። ሆኖም የቀድሞ ልማዶቹ እንደገና ይፈትኑታል። በዚህ ጊዜ አንዳንዶች «እኔ አልችልም፤ እኔ አልለወጥም» ብለው ተስፋ ይቆርጣሉ። ነገር ግን መውደቅህ የመጨረሻ ፍጻሜህ አይደለም። ከወደቅህበት ተነስተህ ወደ እግዚአብሔር መመለስህ ነው ዋናው። መጽሐፍ ቅዱስ የተመለሱ ሰዎችን ታሪክ ያሳየናል። የጠፋው ልጅ ከአባቱ ቤት ርቆ ሄዶ ሕይወቱን አባከነ። በመጨረሻ ግን ራሱን አውቆ ወደ አባቱ ተመለሰ። አባቱም በፍቅር ተቀበለው። ይህ ታሪክ እግዚአብሔር ወደ እርሱ የሚመለሱትን በምሕረት እንደሚቀበል ያስተምረናል። (ሉቃስ 15፥11-24) ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደ። ነገር ግን በስህተቱ አልቀረም፤ አለቀሰ፣ ተመለሰ፣ በኋላም በእምነት አገለገለ። (ሉቃስ 22፥54-62፤ ዮሐንስ 21፥15-19) ጳውሎስ ቀድሞ የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ ነበር። ነገር ግን በክርስቶስ ጸጋ ሕይወቱ ተለወጠ፤ ከዚያም የወንጌል አገልጋይ ሆነ። (ሐዋርያት ሥራ 9፥1-22) እነዚህ ታሪኮች ኃጢአትን ቀላል እንድናደርግ አይደለም፤ ከኃጢአት የሚመልሰን የእግዚአብሔር ምሕረት እንዳለ እንድናምን ነው። ስለዚህ በንስሓ ሕይወት ውስጥ ለምትታገሉ ሰዎች፦ በድክመታችሁ ምክንያት ከጸሎት አትራቁ። በድጋሚ ከወደቃችሁ በእውነተኛ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። የሚያስወድቃችሁን ሁኔታና ልማድ ለዩ፤ ከእነሱም ለመራቅ ተግተው ሥሩ። ከአባታዊ መንፈሳዊ መሪያችሁ ጋር በቅንነት ተነጋገሩ፤ የንስሐንም መንገድ በትዕግሥት ተከተሉ። ትንሽ እድገትን አትናቁ፤ በየቀኑ የሚደረግ ትጋት በጊዜ ሂደት ፍሬ ያፈራል። የእግዚአብሔር ምሕረት ከድክመታችን ይበልጣል። ይህ ግን በኃጢአት እንድንቀጥል ፈቃድ አይደለም፤ ከኃጢአት ተነስተን ወደ እርሱ እንድንመለስ የሚሰጠን ተስፋ ነው። እንጸልይ፦ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፣ በንስሓ መንገድ እየታገሉ ያሉትን ልጆችህን በምሕረትህ ተመልከት። ከድክመታቸው በላይ የሆነ ጸጋህን ስጣቸው። ከኃጢአት የሚመልስ ንጹሕ ልብ፣ የሚያጸና እምነት፣ የሚያስችል ትዕግሥትና የማይቋረጥ የንስሐ ፍላጎት ስጣቸው። በተስፋ መቁረጥ እንዳይሸነፉ፣ ከአንተም እንዳይርቁ እርዳቸው። በንስሐ አባቶቻቸው አማካይነት ትክክለኛውን መንገድ እንዲያውቁ ምራቸው። የተሰበረውን ልብ አጽናና፤ የደከመውን አበርታ፤ የራቀውን መልስ። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም። አሜን! ወጣት ሆይ፣ ዛሬ ብትወድቅም በዚያው አትቅር። ተነስ፣ ንስሐ ግባ፣ ተጋደል፤ ወደ እግዚአብሔርም ተመለስ። የንስሓ በር ክፍት ነው። የተፃፈ በስነልቦና ባለሞያ ቢኒ ግርማቸው በስነልቦና ዙሪያ የተለያዩ ትምህርቶች እና የእኔን አዲሱን መፅሐፍ ለማግኘት(መቼ ገበያ ላይ እንደ ሚወጣ ) እዚህ የቴሌግራም ቻናል መቀላቀል ይቻላል https://t.me/+-2fM7F5XBnZjYWM0 @Orthodox_sibket @Orthodox_sibket @Orthodox_sibket
Open in TelegramViews growthHide views growth
Views growth
Hours after publication
Show as table
| Hours after publication | Views |
|---|---|
| 0 h | 0 |
| 1 h | 156 |
| 3 h | 203 |
- After 1 hour156
- Total to date203








