ቀን 294 ድምጹን ለመለየት ወደ እርሱ መጠጋት የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል - ዮሐንስ 9፤ ዮሐንስ 10፡1-21 ''በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። '' ዮሐንስ 10:3 “በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤” ዮሐ. 10፡3 በእያንዳንዷ እርምጃችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ የምንችለው አካሄዳችንን ከእርሱ ጋር ያደረግን እንደሆን ብቻ ነው። ኢየሱስ ይህንን ሃሳብ በእረኛና በበጎች ምሳሌነት ሲያብራራው እንዲህ አለ፦ “በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎች እረኛ ነው፤ በር ጠባቂውም በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምጹን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምጹን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ድምጹን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም። . . . በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ እኔ አውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል።” ዮሐ. 10፥2-5፣27። ልክ እንደ እነዚህ በጎች እኛም ከእረኛችን ጋር ያለን ቀረቤታ የጠበቀ ሲሆን ድምጹን የበለጠ እየለየን እንሄዳለን። ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ አንድ ወንድም የሰጠው ሀሳብ አይረሳኝም። እንዲህ ነበር ያለው፦ “ሁለት ልጆች አሉኝ። በለጥ የሚለው ወንድ ሲሆን ሴቷ ደግሞ የእርሱ ተከታይ ገና አፏን በደንብ ያልፈታች ነበረች። ቀኑን ሙሉ ከቤት ርቄ በስራ ተጠምጄ ማታ ስገባ ትንሿ ልጄ ልታነጋግረኝ ፈልጋ ትቀርበኛለች። ሆኖም ግን የምትለውን ለማስተዋል ስለምቸገር ከመግባባት ይልቅ መደናቆር ይሆንብናል። ይሄን ጊዜ ተለቅ የሚለው ልጄ ‘አባዬ የምትልህ እኮ እንደዚህ ነው’ ይለኛል። የሚገርመው ደግሞ በእርግጥም የምትለኝ እንደዛ መሆኑ ነበር። ከዚያም ለምንድን ነው እኔ ሳይገባኝ እርሱ የገባው ብዬ ሳስብ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ በሁለቱ መካከል ያለው ቅርርብ ልዩነት ማምጣቱን ነበር። እርሱ አብሯት ስለሚውል ለእኔ ትርጉም ያልሰጠኝ መንተባተብ ለእርሱ ግን የተሟላ ንግግር ሆነለት።” እኛም ከእግዚአብሔር ጋር በተቀራረብን ጊዜ ለሌላው ምንም ትርጉም የሌለውን የጌታን መልእክትና ቋንቋ በቀላሉ እንረዳለን። ፈቃዱን እንማርበታለን። እንዴት ያለ ድንቅ መረዳት ነው! “የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል” የሚለው መግለጫ ይህ መልካም እረኛችን ከእያንዳንዳችን ጋር የጠበቀ ሕብረት ማድረግ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። እርሱ በስማችን ያውቀናል። የእኛ ነገር ለእርሱ ታላቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ በጎቹን ፊት ፊታቸው በመሄድ በፍቅር የሚመራቸው እንጂ በኋላ በዱላ የሚነዳቸው እንዳልሆነ ልብ ይሏል! ታዲያ በዘለዓለማዊ ፍቅሩ ወደ እርሱ ሲስበን እኛም ወደ እርሱ ተጠግተን፣ ድምጹን በመስማት በእያንዳንዱ እርምጃችን እርሱን መከተል ምኞታችን ሊሆን ይገባል። አባት ሆይ፣ ለእኛ ባለህ ታላቅ ፍቅር በግል የምታውቀን ወደ ራስህም ልታስጠጋን የምትፈልግ መልካም እረኛችን መሆንህን በመረዳት፣ እኛም ሁል ጊዜ ድምጽህን በመስማት ዱካህንም በመከተል ከአንተ ፈቃድ ጋር የተስማማ ህይወት መኖር እንድንችል በጸጋህ እርዳን። አሜን!
Open in TelegramViews growthHide views growth
Views growth
Hours after publication
Show as table
| Hours after publication | Views |
|---|---|
| 0 h | 0 |
| 6 h | 104 |
| 15 h | 192 |
- After 6 hours104
- Total to date192