Posts of Ahmed — أحمـــد
From No Where “ይሄማ ግልፅ የሰይጣን አምልኮን ያሳያል …“ እያሉ ሰይጣንን መተዳደሪያ ያደረጉ ሰዎችን ሰይጣን እያየ ምን እንደሚሰማው ባውቅ ደስ ይለኛል🥲 (እኔም ልጀምረው እንዴ🙄)
Open in Telegramአሜሪካዊው ፈላስፋ እና ዐቃቤ እምነት 'አልቪን ፕላንቲንጋ' "Does God Have A Nature?" በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ካነሳቸው ግሩም ነጥቦች መካከል :)) ፈላስፋው በአንድ ጎን እንዲህ ያለ ሙግትን ያደረጃል፦ 1. Person ለመሆን interior consciousness (ውስጣዊ ንቃተ-ህሊና) ሊኖርህ ይገባል! 2. Properties ደግሞ በራሳቸው ገለልተኛ ንቃተ-ህሊና የላቸውም! ካላቸው አምላክ ከባህሪያቱ ጋር ተቆጥሮ ስለ ብዙ ማንነት ብሎም ስለ ብዙ አማልክት ማውራት ልንጀምር ነው! 3. ADS ደግሞ አምላክ ከባሕርያቱ ጋር ፍፁም አንድ ወይም Identical ነው ይላል! 4. ስለዚህ በ ADS Explain የሚደረግ አምላክ Consciousness የሌለው Property እንጂ አካል Person አይደለም! So እንደ Simple Conclusion ንቃተ-ህሊና የሌለው አምላክ ደግሞ ግዑዝ ወይም Abstract Object ነው እንጂ ሕያው አምላክ ሊሆን አይችልም! ሲል እንደ ተጨማሪ እና ጠንካራ ሙግት አምላክን እንደ ሁሉን አዋቂ (Omniscient) አምላክን እንደ ሁሉን ቻይ (Omnipotent) እያስረዳን ከሆነና መልሰን አምላክ ከነዚሁ ባህሪያቱ ጋር identical ነው የምንል ከሆነ የአምላክ ሁሉን አዋቂነት በራሱ የአምላክ ሁሉን ቻይነት ነው ማለታችን ነው የሚል ነጥብ ያነሳል፣ ስለዚህ ባህሪያቱ የየራሳቸው ልዩ ማብራሪያ እንዳላቸው (ሁሉን አዋቂነትን እንደ ሁሉንም እውነት የማወቅ ባሕርይ፣ ሁሉን ቻይነትን ሁሉንም ነገር እንደ ማድረግ የመቻል ባሕሪይ) ከተረዳን ዘንዳ በ Identity of Indiscernibles አምክንዮአዊ መሠረት የ ADS አራማጆች ሁለት የተለያየ ማብራሪያ ያላቸው ባሕሪያትን አንድ በማድረግ የ Category Mistake ውስጥ እየወደቁ ነው የሚል ጠንካራ ሀሳብ ያቀርባል! … ባረከላሁ ፊክ አቡኪ!
Open in TelegramForwarded from ÀƁÙBEĶEŔ ابوبكر(izharull haq)
ፍፁም መለኮታዊ ቀላልነት በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኃሩኃ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው:: አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ይላል:- لَوۡ كَانَ فِيهِمَآ ءَالِهَةٌ إِلَّا ٱللَّهُ لَفَسَدَتَاۚ فَسُبۡحَٰنَ ٱللَّهِ رَبِّ ٱلۡعَرۡشِ عَمَّا يَصِفُونَ በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፡፡ የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ፡፡ — አል አንቢያ (21:22) በአረቢኛው البساطة الإلهية المطلقة ወይም በተለምዶ Absolute Divine Simplicity የምንለው በአማርኛ ፍፁም መለኮታዊ ቀላልነት ማለት የአምላክ ማንነት በምንም ዓይነት መልኩ የተገጣጠመ፣ የተደባለቀ ወይም ወደ ትናንሽ ክፍሎች የሚከፋፈል አይደለም የሚል ነው:: ሀሳቡ ከላይ ስንመለከት ጥሩ እና ትክክለኛ ቢመስልም ውስጡ ስንመለከተው ትልቅ ችግር ያመጣል:: ሀሳቡን የዋህደተል ውጁድ አቀንቃኝ የሆነው ኢብኑ ሲና በአመክንዮአዊ ጥገኝነት ሙግቱ ውስጥ ያሰፈረው ሲሆን ሄዶ ሄዶ የአላህ ባህሪያትን እና ስሞችን ወደ ማሯቀት ገብቷል:: የዚህ ሀሳብ ዋና አቀንቃኞች ሙዕተዚላ ብለን የምንጠራቸው አንጃዎች ናቸው:: የሙዕተዚላዎች ሙግት 2 ሲሆን እንዲህ የሚል ነው:: (1) አላህ ባህሪያት አለው ካልን እና ባህሪያቱ ብዙ ከሆኑ አላህ ብዙ ነው ማለት ነው የሚል ነው:: ( ተአዱድ አል አሊሃ) (2) አላህ ጥንታዊ ነው ባህሬያቱም ጥንታዊ ናቸው ስለዚህ ቡዙ ጥንታዊ አሉ ማለት ነው:: (ተአዱድ አል ኡሉሂያ) ዛሬ ቁጥር አንድን የምንመለከት ይሆናል:: ሙዕተዚላዎች የአላህ ባህሪያት (ሲፋት) የራሱ የማንነቱ (የዛቱ) ዐይን ናቸው ወይም "ዛቱ በባህሪያቱ ቦታ ይተካል" ማለታቸው በቡዙ መንገድ ውድቅ ነው:: ሀ) ቋንቋዊ እና አመክንዮአዊ ውድቀት በቋንቋም ሆነ በአእምሮ ህግ "ባህሪ" (ሲፋህ) እና "ባለቤቱ" (መውሱፍ) አንድ ሊሆኑ አይችሉም። አንድ ሰው ሀይለኛ ተብሎ ሊጠራ ይችላል እንጂ እርሱ ራሱ ሀይል ሊሆን አይችልም:: አዋቂ እንጂ እውቀት ሊሆን አይችልም:: ተናዳጅ እንጂ ንዴት ሊሆን አይችልም:: ያለዚያ ወደ አደገኛ ድምዳሜ ይወስደናል እሱም የአላህ እዝነት ማለት ቁጣው ነው የሚል ነው:: እንዴት መሰላቹ:: አላህ ባህሪውን ነው ካልን አላህ ቁጣ ነው አላህ እዝነት ነው ስለዚህ እዝነቱ ቁጣ ነው ማለት ይሆናል:: ለ) ባህሪያትን ወደ መካድ የሚያደርስ መንገድ ነው ሙዕተዚላዎች "ባህሪያቱ ከዛቱ ጋር አንድ ናቸው" ሲሉ ዓላማቸው ባህሪያቱን ማረጋገጥ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ባህሪያት የሚባሉ እውነተኛ ነገሮች መኖራቸውን መካድ (ተዕጢል) ነው። "አላህ ያለ ዕውቀት አዋቂ ነው፣ ያለ ኃይል ቻይ ነው" ማለት በተጨባጭ ምንም ባህሪ የሌለውን ባዶ( ማዕዱም) ነገር እንደ መግለጽ ነው። ባህሪ የሌለው ነገር ደግሞ በአእምሮ ምናብ ውስጥ እንጂ በተጨባጭ ውጫዊ ዓለም ሊኖር አይችልም። ሐ) ለቁርኣን እና ለሐዲስ ግልጽ ቃላት ተቃራኒ መሆን ቁርኣን አላህ እውነተኛ ባህሪያት እንዳሉት በግልጽ አስቀምጧል፦ «በዕውቀቱ አወረደው» _ (አን-ኒሳእ 4: 166) ዕውቀትን እንደ ባህሪ ጠቅሷል። «እርሱ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው» _ (አዝ-ዛሪያት 51: 58) ነቢዩም (ﷺ) በዱዓቸው፦ "በዕውቀትህ መልካሙን እጠይቅሃለሁ በኃይልህም ችሎታን እለምንሃለሁ" ብለዋል። {አል ቡኻሪይ 1166} "ባህሪው ራሱ ዛቱ ነው" ከተባለ እነዚህን ግልጽ መረጃዎች ማጣመም (ተእዊል) ወይም መካድ ግድ ይላል። እና እንዴት አብራራዋለሁ ? አሰሪዮች ፈላስፎቹ ሆን ብለው ሁለት የተለያዩ ነገሮችን እንደቀላቀሉ ይገልጻሉ። በርካታ ዘላለማውያን መኖራቸው ችግር የሚሆነው እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ አምላኮች (ዘዋት ሙስተቂላህ) ናቸው ከተባለ ብቻ ነው። ነገር ግን «ባህሪ» (ሲፋህ) ራሱን ችሎ የሚቆም አካል አይደለም የሚኖረው ከተገለጸው አካል (አል-መውሱፍ) ጋር ብቻ ነው። አንድ ዘላለማዊ አምላክ ዘላለማዊ ዕውቀትና ኃይል አለው ማለት ብዙ አምላኮች አሉ አያሰኝም አንድ ሰው ዕውቀትና እይታ አለው ሲባል ብዙ ሰዎች እንደማይባለው ሁሉ ማለት ነው። በተጨማሪም ምንም ዓይነት እውነተኛ ባህሪ የሌለው (ባዶ ማንነት) በሰው ምናብ ውስጥ ብቻ እንጂ በተጨባጭ ዓለም ውስጥ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም። በውጫዊው ተጨባጭ ዓለም ያለ ማንኛውም ሕያው አካል ከሌሎች የሚለይበት እውነተኛ መገለጫዎች ሊኖሩት ግድ ነው። ስለዚህ ያለው አንድ ዘላለማዊ አምላክ ብቻ ሲሆን እርሱም ሙሉ በሆኑ ዘላለማዊ ባህሪያቱ የተገለጸ ነው። ይህም በሙሥሊም ሙሁራኖች ዘንድ "ኻሪጂ" እና "ዚህኒ" ተብሎ ይቀመጣል:: ሀሳቡ ቀላል መሰለኝ በጥሞና እና በእርጋታ ጊዜ ወስዳቹ አንብቡት:: ወንድም አቡበከር https://t.me/buki145
Open in Telegramእንደምን ቆያችሁ? አዎን ጠፍቻለሁ … ቢሆንም በኔ ዙሪያ ያላችሁን ማንኛውንም አይነት አስተያየት፣ ትችት እና ወቀሳ በዚህ አቅርቡልኝ፦ @Ahmedresbot
Open in Telegram“One apple fell and the whole world knew gravity however, millions of bodies fell and no one knew humanity!“
Open in TelegramForwarded from عبدالفتاح🖋️ Abdulfetah
በነቢይነታቸው አሥረኛ ዓመት፣ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባለቤታቸውን እናታችን ኸዲጃን እና አጎታቸውን አቡ ጣሊብን በሞት ካጡ በኋላ፣ በቁረይሾች በኩል የሚደርስባቸው መከራና እንግልት በእጅጉ በረታ። በዚህም ምክንያት የመካ ሰዎች ጥሪያቸውን ባለመቀበላቸው፣ የእስልምናን መልእክት ለማድረስና ድጋፍ ለማግኘት ከአጎታቸው ልጅ ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ ጋር በመሆን ወደ ጣኢፍ ለመሄድ ተነሱ። ወደ ጣኢፍም በሄዱ ጊዜ የሰቂፍ ጎሳ መሪዎች ወደሆኑት ወደ ሦስቱ ወንድማማቾች — ዐብድ ያሊል፣ መስዑድ እና ሐቢብ — ዘንድ በመሄድ የእስልምናን ጥሪ አቀረቡላቸው፤ ከቁረይሾች ጥቃትም እንዲጠብቋቸው ጠየቋቸው። ነገር ግን መሪዎቹ በጥሪው ላይ አፌዙ፤ በጣም ባልተገባና ነቀፌታ በተሞላው መንገድ ጥሪያቸውን ውድቅ አደረጉት። መሪዎቹ ጥሪውን ውድቅ ከማድረጋቸውም በላይ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በአስቸኳይ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ። ከከተማዋ ሲወጡም የከተማዋን እብዶች፣ ባሪያዎችና ሕፃናት በሁለት መስመር አሰልፈው ድንጋይ እንዲወረውሩባቸው አደረጉ። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ ከተማዋን ለቀው እስኪወጡ ድረስ በድንጋይ ተደበደቡ፤ እግራቸው በደም ተለወሰ፤ ዘይድም ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ለመከላከል ሲሞክር ራሱ ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰበት። ከከተማዋ ትንሽ ራቅ ብሎ በሚገኘው የቁረይሽ ከበርቴዎች በነበሩት በኡትባ እና ሸይባ የአትክልት ስፍራ በደረሱና ባረፉ ጊዜም፣ ውዱ ነቢይ ወደ አላህ እንዲህ ሲሉ ጥሪያቸውን አሰሙ፦ "اللَّهُمَّ إِلَيْكَ أَشْكُو ضَعْفَ قُوَّتِي، وَقِلَّةَ حِيلَتِي، وَهَوَانِي عَلَى النَّاسِ، أَنْتَ رَبُّ الْمُسْتَضْعَفِينَ وَأَنْتَ رَبِّي، إِلَى مَنْ تَكِلُنِي؟ إِلَى بَعِيدٍ يَتَجَهَّمُنِي؟ أَمْ إِلَى عَدُوٍّ مَلَّكْتَهُ أَمْرِي؟ إِنْ لَمْ يَكُنْ بِكَ غَضَبٌ عَلَيَّ فَلَا أُبَالِي، وَلَكِنَّ عَافِيَتَكَ هِيَ أَوْسَعُ لِي، أَعُوذُ بِنُورِ وَجْهِكَ الَّذِي أَشْرَقَتْ لَهُ الظُّلُمَاتُ، وَصَلَحَ عَلَيْهِ أَمْرُ الدُّنْيَا وَالْآخِرَةِ، مِنْ أَنْ تُنْزِلَ بِي غَضَبَكَ، أَوْ يَحِلَّ عَلَيَّ سَخَطُكَ، لَكَ الْعُتْبَى حَتَّى تَرْضَى، وَلَا حَوْلَ وَلَا قُوَّةَ إِلَّا بِكَ». አላህ ሆይ የጉልበቴን ደካማነት የመላዬን (የብልሃቴን)ማነስ በሰዎች ዘንድ ማነሴን (መናቄን) አቤቱታዬን ወደ አንተ አቀርባለው ።አንተ የደካሞች ጌታ ነህ ፤ አንተም ጌታዬ ነህ ። ለማን አሳልፈህ ትሰጠኛለህ? በጭካኔ ለሚያስተናግደኝ ሩቅ ሰው ወይስ ጉዳዬን ለሰጠኸው ጠላት? አንተ ካልተቆጣህብኝ ሌላው ግድ አይሰጠኝም ፤ ሆኖም የአንተ ጥበቃና እዝነት ለእኔ የበለጠ ሰፊና በቂ ነው ። ቁጣህ በኔ ላይ እንዳይወርድ መዓትህም በኔ ላይ እንዳይሆን ጨለማን በሚያበራውና የዚህን ዓለምም ሆነ የመጨረሻውን ዓለም ጉዳዮች በሚያስተካክለው በፊትህ ብርሃን እጠበቃለው ። አንተ እስክትረካ ድረስ ይቅርታህን እሻለው ፤ ከአንተ ውጪ ምንም ዓይነት ሃይልም ብርታትም የለም ። ይህን ሁኔታቸውን በአትክልት ስፍራው የሚያገለግል አንድ ባሪያ ባየ ጊዜ፣ በሁኔታቸው አዝኖ ወደ እነሱ ተጠግቶ የወይን ፍሬ ሰጣቸው። ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) ፍሬውን ከመብላታቸው በፊት "ቢስሚላህ" ባሉ ጊዜ፣ ይህ ባሪያ በንግግራቸው በመደነቅ «የዚህ አካባቢ ሰዎች ይህን ቃል አይጠቀሙም» አለ። ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) የየት ሀገር ሰው እንደሆነና ሃይማኖቱ ምን እንደሆነ ጠየቁት። እርሱም የነይነዋ (የነቢዩላህ ዩኑስ ሀገር) ሰው እንደሆነና ሃይማኖቱም መሲሐዊ (ክርስቲያን) እንደሆነ ነገራቸው። ዓዳስ (ባሪያው) ስለ ነቢዩላህ ዩኑስ በምን እንደሚያውቁ በጠየቃቸው ጊዜ «እርሱ ወንድሜ ነው፤ ነቢይም ነበር፤ እኔም ነቢይ ነኝ» አሉት። ይህን በሰማ ጊዜ ባሪያው ግንባራቸውን፣ እጃቸውን እና እግራቸውን በመሳም እስልምናን ተቀበለ። ይህንን ያየው አሳዳሪውም «ወየውልህ! የዚህን ሰው እጅ፣ እግርና ግንባር ትስማለህ?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ፣ ባሪያውም «ከዚህ የተሻለ ነገር ምን አለ? ነቢይ እንጂ ሌላ የማያውቀውን ነገር ነገረኝ» በማለት መለሰለት። ከዚህም በኋላ ጉዟቸውን በመቀጠል ላይ ሳሉ፣ 'ቀርኑል መናዚል' የሚባል ስፍራ ላይ በደረሱ ጊዜ አላህ መላእክትን ላከላቸው። የመላእክት አለቃ ጅብሪልም ሰላምታ ካቀረበ በኋላ እንዲህ አላቸው፦ «አላህ የሕዝቦችህን ምላሽ ሰምቷል። የተራሮችን መልአክም እነሱ ላይ የፈለግከውን እንድታዝባቸው ልኮልሃል።» የተራሮች መልአክም ሰላምታ ካቀረበ በኋላ «ጌታህ በእርግጥም ወደ አንተ ትእዛዝህን እንድፈጽም ልኮኛል። ከፈለግክ እነዚህን ሁለቱን ተራሮች በጣኢፍ ሕዝቦች ላይ አጣብቄ ላጥፋቸው።» አለ። መልአኩ ይህን ቢላቸውም፣ ለዓለማት እዝነት ሆነው የተላኩት የኛ ነቢይ መልስ ግን በጣም አስገራሚ ነበር። «በእርግጥ ከእነዚህ ሕዝቦች ውስጥ ወደፊት አላህን በብቸኝነት፣ ማንንም ሳያጋሩ የሚያመልኩ ትውልዶች ይፈጠራሉ ብዬ እከጅላለሁ።» በማለት እነዚህን ሕዝቦች ከመጥፋት ታደጓቸው።
Open in Telegramምሁራኑ ይህንን ጥያቄ ከ ተፈጥሮ ሥርዓት ጋር አያይዘው ሰፋ ያለ መረዳታቸውን አስቀምጠዋል። አምላክ አለምን የሰራት ዘፈቀዳዊ ሳይሆን ቋሚ በሆኑ ህግጋት (Laws Of Nature) እንድትመራ አድርጎ ነው። እነኚህ እንደ ስበት፣ ሙቀት፣ እንቅስቃሴ ያሉ መሰል ህግጋት ካልተለወጡና ቋሚ ከሆኑ ብቻም ነው ዓለም ሥርዓት አላት ልንል የምንችለው። ዛሬ የምበላውን መብል ያሞቀ እሳት ነገ ያቀዘቅዘዋል ብለን የማንጠብቀው፣ ድንጋይ ከላይ ሲለቀቅ ወደ ታች እንደሚወድቅ እርግጠኛ መሆን የምንችለው የተፈጥሮ ሕግ ቋሚ እና የማይለዋወጥ ስለሆነ ነው። በሃይማኖት ፍልስፍና (Philosophy Of Religion) ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው አሜሪካዊ ፈላስፋ 'ብሩስ ራይከንባክ' እነዚህ ሕጎች በጎ ነገርን ለማምጣት አስፈላጊ የሆኑትን ያህል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥቃይን የማምጣት ውጤት ይኖራቸዋል ሲለን እንግሊዛዊው ደራሲ 'ሲ. ኤስ. ሉዊስ' እ.ኤ.አ በ 1910 ባበረከተው "The Problem Of Pain" የተሰኘ መጽሐፉ ላይ የሰው ልጆች እርስ በርስ ለመግባባትና ነፃ ምርጫቸውን ለመለማመድ ገለልተኛና የማይለወጥ መድረክ ያስፈልጋቸዋል። ይህ መድረክ ደግሞ ቋሚው የተፈጥሮ ሕግ ነው። ሕጎቹ እንደፈለጉ የሚቀያየሩ ቢሆኑና አምላክ ጣልቃ ቢገባ ማኅበራዊ ሕይወትና ሥነ ምግባር ሊኖር አይችልም ነበር ሲል አበክሮ ይሟገታል። ከነዚህ ትርጓሜዎች በመነሳት ተፈጥሯዊ እኩይ (Natural Evil) በ ኢስላማዊው ሥነ-መለኮት ውስጥ ሁለት ተያያዥ ገጽታዎችን ይይዛል። የመጀመሪያው የሥነ ፍጥረቱ ሥርዓት አካል መሆኑን ቁርዓን እንዲህ ሲል ያስረዳል “እኛ ሁሉንም ነገር በልክ (በልክም) ፈጠርነው።“ — 54:49 ይህንን አንቀጽ በ 20ኛው ክ/ዘመን ከነበሩ ታላላቅ ሊቃውንት መካከል ቱኒዝያዊው 'ሙሐመድ አጥ ጣሂር ኢብን ዓሹር' እንዲህ ሲሉ ፈትተውታል፦ “ሸይእ (ነገር) ማለት፦ በባህሪያትና በአካላት (በቁስ) መካከል ያለ ነባራዊ ነገር ማለት ነው። ይኸውም፦ ሁሉንም ነባራዊ ነገሮች፣ አካላቶቻቸውንና ባህሪያቶቻቸውን በልክ ፈጠርናቸው ማለት ነው።“[⁴] ሲሉ በዚሁ በልክ የተሰራ ፍጥረተ አለም ላይ የሚታየው ተፈጥሯዊ እኩይ (Natural Evil) በውስጡ መካተቱን እንድንረዳ በር ከፍተውልናል፣ ሁለተኛው ደግሞ "ወርቅ በእሳት ይፈተናል" እንዲሉ አበው የሰው ልጅ በ ህመም የ ጤናን በ ማጣት የ ማግኘትን ፀጋ እንዲያስተውል በ መከራ ትዕግስትን በ ረሀብ ርኅራኄን የሚማርበት "የ ነፍስ ስሪት ፍትሐ መለኮትን (Soul Making Theodicy)" ያስይዘናል። የነገረ እኩይ ጥያቄዎችን በምክንያታዊነት ብቻ ለመፍታት የሚሞክሩ ምሁራን፣ በመጨረሻ የሚጋጩት ከሰው ልጅ አእምሮ በላይ ካለው ጥበብ ጋር ይሆናል። እዚህ ጋር ነው መለኮታዊ ጥበብን የመመርመር ገደብ ወይም "Skeptical Theism" የሚባለው እሳቤ የሚመጣው። ይህ እሳቤ አምላክ ክፋትን እንዲኖር የፈቀደበት በቂ ምክንያት ቢኖረውም፣ እኛ የሰው ልጆች ያንን ምክንያት የመረዳት አቅሙ የለንም የሚል ነው። በነቢዩ ሙሳ እና በኸድር ታሪክ ውስጥ ሙሳ በጉዞው ላይ ኸድር ምስኪኖች የሚጠቀሙባትን ጀልባ ሲበሳ፣ አንድን ወጣት ሲገድል እና በማይቀበሏቸው ሰዎች መንደር ውስጥ የወደቀ ግንብ ሲያቀና ይመለከታል። ለሙሳ እነዚህ ድርጊቶች "እኩይ" (Evil) መስለው ቢታዩትም፣ ኸድር በመጨረሻ ጀልባዋ የተበሳችው ጀልባዎችን ከቀማኛ ንጉሥ ለመታደግ፣ ወጣቱ የተገደለው ለወላጆቹ የተሻለ ልጅ ለመተካት፣ ግንቡ የታደሰው ደግሞ ከሥሩ ያለውን የየቲሞች ሀብት ለመጠበቅ እንደነበር ሲያስረዳው እንመለከታለን። በዚህ ታሪክ ውስጥ "Relative Evil" (አንጻራዊ እኩይ) የምንለው ነገር፣ በመለኮታዊው እቅድ ውስጥ ለበለጠ በጎ ነገር (Greater Good) መንገድ የሚጠርግ መሆኑን እንረዳለን። ከመሆኑም ጋር፣ አንድ አማኝ በምድር ላይ ለሚገጥመው መከራና ክፋት ሊኖረው የሚገባው ምላሽ አምላክ ሁሉን አዋቂ መሆኑን በማመን፣ ከቁጥጥራችን ውጭ ለሆኑ ነገሮች አምላክን ተጠያቂ ከማድረግ መታቀብ ነው። መከራ ለአማኙ ስብዕና መገንቢያና ወደ ፈጣሪው መቃረቢያ ድልድይም ነውና፣ በሁኔታዎች ሁሉ አመስጋኝ ባሪያ ሆኖ በመቆየት በዚህች ዓለም ላይ ከሚገጥመው አንጻራዊ ክፋት ይልቅ፣ ከፈተናው በኋላ ያለውን ዘላለማዊ ህይወት ተስፋ በማድረግ ጉዞውን ሊቀጥል ይገባዋል እላለሁ። "ነገረ እኩይ አምላክ የለም ለማለት የሚያበቃ ጽንሰ ሀሳብ ነው!" የሚለውን መረዳት ወደ ጎን በማድረግ፣ ይልቁንም አምላክ ከእኛ እውቀት በላይ መሆኑን የምንረዳበት ምስጢር አድርገን መውሰዱ ወደ እኛ በተወረወረው ጠጠር ቤታችንን እንደ መገንባት ያለ ብልህነት ነው የሚል ግንዛቤ አለኝ። ደኅና ቆዩኝ። __ ማጣቀሻዎች፦ [1] Leibniz, Theodicy, Part I, Section 21 [2] ሀዲስ አለማየሁ፣ የልምዣት (1980)፣ ገጽ 108 [3] Alvin Plantinga, The Nature Of Necessity (1974), pp. 167 [4] Muhammed At Tahir Ibn Ashur, Tafsir At Tahrir Wa At Tanwir (2021), Volume 11, pp. 171 ... Written By: Akhi Ahmed Respond https://t.me/ahmedrespond
Open in Telegramየ ነገረ እኩይ (Problem Of Evil) ፍልስፍናዊና ሥነ-መለኮታዊ ትንታኔ — ክፍል ሁለት … ባለፈው ክፍላችን የ እኩይ ምንነቱን በማስረዳት የጀመርነውን ጉዞ አጠናቅቀን በሌላኛው ሀተታ የ እኩይ ለምንነቱ'ን ለሚያነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሚሆኑ ትንተናዎች የ እኩይ መኖር በፍትሐ መለኮት (Theodicy) ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ምን ይመስላል? የሚለውን የምንቃኝ ይሆናል። የ 18ኛው ክ/ዘመን ጀርመናዊው ፈላስፋ 'ጎትፍሪድ ዊልሄልም ላይብኒዝ' እ.ኤ.አ በ 1710 ዓ.ል ባበረከተው "Théodicée" የተሰኘ ታዋቂ መጽሐፉ ላይ እኩይ'ን ዲበ አካላዊ (Metaphysical)፣ ምግባራዊ (Moral) እና ተፈጥሯዊ (Physical/Natural) ሲል በ ሦስት መሠረታዊ መደቦች ከፍሎ ይመለከተዋል።[¹] ዲበ አካል (Metaphysics) የነገሮችን ምንነት፣ ህልውና እና መሠረታዊ ባሕርይ የሚያጠና የፍልስፍና ዘርፍ ሲሆን ከዚህ እይታ በመነሳት የ አንድ ነገር ህልውና በጎ (Good) ወይም እኩይ (Evil) ሊባል የሚችልበት እሴት ካለው የህልውና ሙላት እና ፍጽምና የሚመነጭ ነው ሲል ያስረዳል። ከ ዲበ አካላዊ እኩይ (Metaphysical Evil) መረዳቱ ጋር ተያይዞ ፈላስፋው 'ላይብኒዝ' ይህንን የ እኩይ መደብ አምላክ ፍጹም ሲሆን ፍጥረተ ዓለሙ አምላክ ስላልሆነ ፍጽምና ሊኖረው አይችልም። ፍጡር በ ባሕሪው ውስን መሆኑ ደግሞ ለስህተት በር ይከፍታል በሚል ያብራራዋል። ለምሳሌ፦ አንድ ሰው ስለ ነገ የሚያውቀው ነገር ውስን በመሆኑ ዛሬ ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔ ሊወስን ይችላል። ይህም የውሳኔ ስህተት የመጣው ከክፋቱ ሳይሆን ከእውቀቱ ግድብነት የተነሳ እንደሆነ ይነግረናል። 'ላይብኒዝ' ይህንን መጽሐፍ እንዲያበረክት ተጽዕኖ ካሳደሩ እና ምክንያት ከሆኑት ሰዎች መካከል የ 17ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ ላይ የነበረው ፈረንሳዊ ፈላስፋ 'ፒየር ባይል' ተጠቃሽ ነው፤ ይህ ደራሲ እ.ኤ.አ በ 1697 ዓ.ል ባወጣው "Dictionnaire Historique et Critique" የተሰኘ መጽሐፉ ላይ ዲበ አካላዊውን (Metaphysical) መደብ በመተው እኩይ'ን በ ሁለት መሠረታዊ መደቦች ከፍሎ ይመለከተዋል። እነርሱም፦ ምግባራዊ እኩይ (Moral Evil) እና ተፈጥሯዊ እኩይ (Physical/Natural Evil) ብለን የጠቀስናቸው ናቸው። እነዚህን ምሁራዊ የ እኩይ መደቦች መረዳታችን፣ ከ ምግባራዊ እኩይ (Moral Evil) እና ተፈጥሯዊ እኩይ (Physical/Natural Evil) አንፃር ለሚነሱ ወደ አምላክ የተቀሰሩ ክሶች ምላሽ የሚሰጡ ትንታኔዎች ያሸጋግረናል። ፩. የ ምግባራዊ እኩይ (Moral Evil) ሀተታ፦ ጊዜው እ.ኢ.አ 1928 ዓ.ል ነው። የኢትዮጵያ ሰማይ በጣሊያን የ ብረት አሞራዎች ታውኳል፤ ምድሪቱም በቦምብ ናዳ እየተናወጠች ነው። በዚሁ የታሪክ ክፍል አንዲት ኢትዮጵያዊት እንስት አባት እና እናቷ፣ እህት እና ወንድሟ በጠላት ሀይል መገደላቸውን መስማቷ ሳያንስ በዚሁ የሀዘን ስብራት ውስጥ ሳለች ጥላ ትሆንኛለች ብላ የምታስባት የማርያም ቤተክርስቲያን በቦምብ ነበልባል ስትጋይ ትመለከታለች! የሰማዩ ጌታ የራሱን ቤት እንኳ አለመታደጉ ለሚስኪኗ ሴት የመከራ ልክ ሆኖ ታያት። ከዚህም የተነሳ ለፈጣሪዋ እንዲህ ስትል ተጠየቋን አቅርባለች፦ “አንተ ከላይ ሆነህ ስታላግጥ፣ በሰው እናትህ ነደደች፤ ሀዘንን ቅመሰው!” ሲባል በታሪክ ይነገራል። እንዲሁ "ፍቅር እስከ መቃብር" በተሰኘ ስራው የምናውቀው ጸሐፊ እና ፖለቲከኛ 'ሀዲስ ዓለማየሁ' በ 1980 ባበረከተው "የልምዣት" የተሰኘ ስራው ላይ እንዲህ ይለናል፦ "እኛምኮ እግዜርን የምንወቅስበት ዋና ምክንያቱ፣ አርጎ ከፈጠረን ሀብታምና ድሀ ደካማና ብርቱ፣ ግፍ ሲሰራ እያየ ባለመፍረዱ ነው ዝም በማለቱ። ችሎት ተቀምጦ እየመረመረ ፍርድ ቢሰጥማ፣ ሀብታም ደሀ ሳይል ወይ ብርቱ ደካማ፣ ይመሰገን ነበር እንኳንስ ሊታማ።"[²] አምላክ መላእክት እርሱን እንዲገዙና ትእዛዙን ብቻ እንዲፈጽሙ አድርጎ ሲፈጥራቸው፣ የሰው ልጆችን ግን በጎን'ም ሆነ እኩይ'ን የመምረጥ፣ አንዱን ትቶ አንዱን የመከተል ሉዓላዊ አቅም በመስጠት ኃላፊነትን ተሸካሚ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። ለዚህም ነው አላህ በቁርዓን ላይ፦ “ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፡፡“ — (67:2) ሲል የሚናገረው! በዚህ አውድ ውስጥ የምርጫ ነፃነት ያላቸው ፍጡራን የመምረጥ አቅማቸውን በመጠቀም በፈጸሙት ተግባር አማካኝነት ወደዚህች ምድር የሚያመጡት ስቃይና በደል "ምግባራዊ እኩይ (Moral Evil)" ተብሎ ይጠራል። ከ ምግባራዊ እኩይ (Moral Evil) ጋር ተያይዞ “አምላክ ነፃ የሆኑ ፍጡራንን ካስገኘ በኋላ ስለ ምን በጎ የሆነውን ተግባር ብቻ እንዲሰሩ አላደረገም?“ ብሎም መጠየቅ በራሱ ቅራኔን ይፈጥራል። ክፋት ለመኖር የሚችልበት ዕድል (Possibility Of Evil) በሌለበት ዓለም ውስጥ እንደ ትዕግሥት፣ ይቅር ባይነት እና ሐቀኝነት ያሉ መሰል እሴቶች ትርጉም አይኖራቸውም! ምክንያቱም ለመዋሸት በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ እውነትን መናገር "ሐቀኛ"፣ ለመበቀል በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ አለመበቀል "ይቅር ባይ" አያሰኘንምና! ከ ሞት በኋላ ያለ ህይወት እንደመኖሩ በዚህች አለም ላይ መልካም ማድረግ የሚችሉ ፍጡራንን ከፈጠረ በኋላ እኩይ'ን በነፃነት ማከናወን እንዳይችሉ ያደረገ አምላክ በምርጫቸው ባላደረጉት መልካምነት ሥነ ምግባራዊ እሴት ሰጥቶ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ሊያውጅ አይችልም! — አሜሪካዊው ፈላስፋ እና ዐቃቤ እምነት 'አልቪን ፕላንቲንጋ' በሰፊው ካስተዋወቃቸው እይታዎች መካከል ይህ "የምርጫ ነፃነት ሙግት (Free Will Defense)" የተሰኘው መከራከሪያ ሲሆን እ.ኤ.አ በ 1974 ባበረከተው "The Nature Of Necessity" የተሰኘ መጽሐፉ ላይ እንዲህ ያለ ቁም ነገር ያስጨብጠናል፦ “በጎ ነገር ማድረግ የሚችሉ ፍጥረታትን ለመፍጠር፣ ምግባራዊ እኩይ'ን የመፈፀም ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት መፍጠር አለበት። እነዚህ ፍጥረታት እኩይ'ን እንዲያደርጉ ነጻነት ሰጥቷቸው፣ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ያንን እንዳያደርጉ ሊከለክላቸው አይችልም።“[³] ፪. የ ተፈጥሯዊ እኩይ (Natural Evil) ሀተታ፦ በተፈጥሮ ሂደቶች ምክንያት ሕይወት ባላቸው ፍጡራን ላይ የሚደርስ ስቃይና መከራ "ተፈጥሯዊ እኩይ (Natural Evil)" ተብሎ ይጠራል። የሰው ልጅ የራሱን የምርጫ ነፃነት ተጠቅሞ ለሚያመጣው ጥፋትና ግፍ ፈጣሪን ተጠያቂ ማድረግ አዳጋች ቢሆንም፤ ከዚህ ድምዳሜ ጎን ለጎን ግን ሌላ አሳሳቢ ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፦ ይኸው የሰው ልጅ በማይሳተፍባቸው፣ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ እና በሽታዎች ምክንያት የሚከሰቱ ስቃዮችስ እንዴት እንረዳቸዋለን?
Open in Telegramየ ነገረ እኩይ (Problem Of Evil) ፍልስፍናዊና ሥነ-መለኮታዊ ትንታኔ — ክፍል አንድ … “ያ የጎጃም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ቁርስ አርጎ ጨረሰው ጣልያንን በአንድ ሌት” (ገጣሚው ያልታወቀ) የተባለላቸው የጎጃሙ 'ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት' (የቀድሞው ራስ አዳል ተሰማ) በጽኑ በታመሙ ጊዜ፣ በወቅቱ የነበረው ማኅበረሰብ “ንጉሥ በቀላሉ እንዲህ አይታመምም፤ ካልመረዙት በቀር— በጭንቅ አይያዝም።” የሚል ጽኑ ጥርጣሬ የነበረው በመሆኑ ይኸው ጥርጣሬ እስከ ቤተ መንግሥቱ ድረስ ይገባና፣ የንጉሡ የበኩር ልጅ 'በለው አዳል' “አባቱን መርዟል” በሚል ተጠርጥረው ወደ ወህኒ ይወርዳሉ። 'አያ በለው አዳል' በወህኒ ውስጥ ከባድ ሥቃይና መከራ ሲቀበሉ፣ በደረሰባቸው ግፍ እና የብቸኝነት ስሜት እጅጉን ተማረሩ። በዚህ የፍትሕ መጓደልና የግራ መጋባት ሁኔታ ውስጥ፣ የሰው ልጅን ዘላለማዊ የሕልውና ጥያቄ የሚያነሳ ይህን ዝነኛ ቅኔም ተቀኙ፦ “አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፤ የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል።” ይህ የ በለው አዳል እሮሮ፣ የሰው ልጅ የመኖር ትርጉምን እና መለኮታዊ ፍትሕን ለመፈለግ ያለውን ጥልቅ እና ዘላቂ ጥያቄ ያንጸባርቃል። በምድር ላይ የሚታየው መከራና ግፍ “የተገፉትን የማይሰማ አምላክ አለ?” የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል። ይህ በሀገራችን ታሪክ የተመለከትነውን መሰል እሮሮ በምዕራባውያኑም ዘንድ በ 341 ዓ.ዓ አካባቢ ተወልዶ በ 270 ዓ.ዓ ገደማ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የ "ኢጲቆሮሳዊነት" የፍልስፍና ትምህርት መስራች 'ኢጲቆሮስ ሳሞስ' ልክ እንደ አያ በለው ሁሉ ምንም እንኳ የአምላክን ህልውና የካደ ሰው ባይሆንም በ ኢጲቆሮሳዊው ፍልስፍና በአፈ ቃል ደረጃ ካስተላለፋቸው ትምህርቶቹ ውስጥ "Epicurean Paradox" በመባል የሚታወቀውን ውሩይ አያዎ የነገረ መለኮት ምሁርና የሮማው 'ንጉስ ቆስጠንጢኖስ' አማካሪ የነበረው 'ላክታንቲየስ' "De Ira Dei" በተሰኘ መጽሐፉ ላይ "አምላክ ፍጹም ሰላማዊ ስለሆነ አይቆጣም፣ በሰው ልጅ ጉዳይም ላይ ጣልቃ አይገባም" የሚለውን የኢጲቆሮሳውያን አቋም ለመሞገት ሲል በዚህ መልክ አስፍሮት ነበር፦ "ክፋትን ማጥፋት እየፈለገ ነገር ግን ካልቻለ እርሱ (አምላክ) ደካማ ነው፣ ማጥፋት እየቻለ ነገር ግን ማድረግን ካልሻ ክፉ ነው፣ ማጥፋት የማይችልና የማይሻ ከሆነ ስለ ምን አምላክ እንለዋለን?፣ የሚችልና የሚሻ ከሆነ የክፋት መኖር ስለ ምንድን ነው?" ይህ ጥያቄ በሥነ-መለኮትና ፍልስፍና እይታ "ነገረ እኩይ" (Problem of Evil) ተብሎ የሚጠራው እሳቤ ነው፤ “ፈጣሪ ቸር፣ ሁሉን አዋቂ እና ሁሉን ቻይ ከሆነ፣ ክፋትና መከራ በንጹሐን ላይ ስለ ምን ይኖራሉ?” የሚል ጥልቅና እስካሁን ከመነሳት ያልነጠፈ ጥያቄ! ፨ ለመሆኑ እኩይ (Evil) ምንድን ነው? "እኩይ" የሚለው ቃል "አከየ" (ከፋ፣ መጥፎ ሆነ) ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን "ክፉ፣ መጥፎ" እና መሰል ትርጉሞች አለት። እኩይ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ የተሰነዘሩ አያሌ መላምቶች ቢኖሩም በስፋት ከሚታዩ ማብራሪያዎች መካከል "ዓለም በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች (የብርሃን አምላክ እና የጨለማ አምላክ) መካከል ያለች የጦርነት ሜዳ ነችና ክፋት የመጣው ክፉ ከሆነው የጨለማ አምላክ ነው።" የሚለው በጥንታዊቷ ፋርስ ተነስቷል ተብሎ በሚታመነው 'ዞራስተር' ኋላም ከክ/ልደት በኋላ በ 3ተኛው ክ/ዘመን በተነሳው 'ማኒ' ሲቀነቀን የነበረው ክልኤታዊ (Dualistic) አስተሳሰብ አንዱ ነው። ሆኖም አምላክን ራሱን የቻለ ተቀናቃኝ ያለው ከሆነ "ሁሉን ቻይ" (Omnipotent) አይደለም! አልፎም አንዱ ከአንዱ ጋር የሚሸናነፍበት አጋጣሚ አለመኖሩ ዓለምን ትርጉም የለሽ የሁከት ቦታ ያደርጋታል በሚሉ ትችቶች ምንም እንኳ በስፋት ተንሰራፍቶ የነበረ እይታ ቢሆንም እንዲህ በቀላሉ ውድቅ ይሆናል። በሌላ በኩል ለዘጠኝ አመታት በዚሁ ክልኤታዊ አስተሳሰብ ተፅዕኖ ስር የነበረው ክርስቲያን ፈላስፋ 'ቅዱስ አውግስጢኖስ' ራሱን ከዚህ አስተሳሰብ በማላቀቅ ክፋት በራሱ ህልውና እንደሌለውና ጨለማ የብርሃን እጦት፣ በሽታ የጤና እጦት እንደሆነው ሁሉ፤ ክፋትም የበጎ ነገር እጦት/መጓደል ነው በሚል መረዳት "Privatio Boni" የተሰኘውን እይታ ስልታዊ በሆነ መንገድ ቀርጾ ሊያስቀምጥ ችሏል! ቢሆንም ግን እንደ 'ካርል ዩንግ' እና 'ዴቪድ ሬይ ግሪፊን' ያሉ ምሁራን አንድ ሰው ሲሰቃይ የሚሰማው ስሜት ተጨባጭ ተሞክሮ ከመሆኑ ጋር "እጦት" የሚለው ገለፃ ለክፋት የምንምነትን ባህሪ ይሰጣልና በዓለም ላይ ያለውን አውዳሚ ኃይልና የክፋትን ግዙፍነት በትክክል አይገልፅም በሚል ይህም ጽንሰ ሀሳብ እንዲሁ ይተቻል! እነኚህን ምሁራዊ ክፍተቶች ለመሙላት ክፋትን እንደ እጦት (Privation) ሳይሆን እንደ በጎ ነገሮች መዛባት (Misplacement Theory) አድርጎ መረዳት የግድ ይላል። በዚህ እይታ መሠረት፣ ክፋት ራሱን የቻለ ህልውና ያለው ፍጥረት ባይሆንም፣ አምላክ የፈጠራቸው በጎ አቅሞች መዋል ከሚገባቸው መልካም ዓላማ ፈቀቅ ሲሉ የሚፈጠር አጥፊ ሁኔታ ነው። ይህ ንድፈ-ሐሳብ ክፋትን እንደ ምንምነት ከሚያየው የ አውግስጢኖስ እይታ የሚለየው፣ መዛባቱ የሚፈጥረውን ንቁ ጥፋት "Active Destruction" በማመኑ ነው። ለምሳሌ፦ እሳት በተገቢ ቦታ ሲውል ይጠቅማል፤ ከስርዓቱ ሲወጣ ግን ጥፋት ያመጣል። ስለዚህ ክፋት በራሱ የቆመ ህልውና ሳይሆን፣ የበጎ ነገሮች መዛባት መሆኑን እንረዳለን። ይሁን እንጂ፣ ክፋት መዛባት መሆኑን ማወቃችን ብቻውን ለበለው አዳል እና መሰል የቆሰሉ ነፍሶች በቂ ምላሽ አይሆንም። ይልቁንም "አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል" የሚለው እሮሮ ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ፣ ይህንን ስቃይና መከራ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ እንዲሰለጥን የመፍቀዱ ምስጢር ምንድን ነው? የሚል ሌላ ጥልቅ ጥያቄን ይወልዳል! የዚህንና መሰል ጥያቄዎች ምላሽ በተከታዩ የጽሑፋችን ክፍል በዝርዝር የምንዳስሰው ይሆናል። ደኅና ቆዩኝ። ... Written By: Akhi Ahmed Respond https://t.me/ahmedrespond
Open in Telegramነገ ረቡዕ፣ ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ (Ethiopian Local Time) ከኡሥታዝ ቃለ-አሚን ፀጋዬ ጋር በቲክታክ የቀጥታ ስርጭት (Live) እንገናኛለን። ቆይታችንንም በኡሥታዝ ሳላህ ዘይን ከተዘጋጀው «ሰማዕቱ ብራና» የተሰኘ ስራ ጋር በማድረግ በመጽሐፉ ዙሪያ ሰፊ ግምገማ የምናካሂድ ይሆናል። ሁላችሁም ተጋብዛችኋል። እንዳትቀሩ!
Open in Telegram“እያንዳንዱ ሰው የሚኖረው ከሁለት ዓለማት ጋር በሚያካሂደው መስተጋብር ነው። አንደኛው ዓለም ውጫዊ ዓለም ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓለም ደግሞ በውስጡ ያለው ዓለም ነው። በውስጣችን ያለው ዓለም እኛ በህይወት እስካለን ድረስ ብቻ የሚኖር ሲሆን፣ ውጫዊው ዓለም ግን እኛ በህይወት ብንኖርም ባንኖርም የሚኖር ዓለም ነው። የአንድ ሰው ውስጣዊ ዓለም የሚባለው ግለሰቡ ያለውን አመለካከት፣ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ስሜት ወዘተ … ያጠቃልላል። ስለሆነም አንድ ሰው ውጫዊውን ዓለም የሚመለከትበትም ሆነ መጠቀም የሚችልበት አቅም በውስጣዊ ዓለሙ ባለው ብቃት ይወሰናል። ይህም ማለት አንድ ሰው የሚያውቀው፣ የሚረዳውና ሊሠራ የሚችለው የተማረው ነገር ውጤት ነው እንደማለት ነው። ዛሬ በዓለማችን ያሉ ዜጎች የአኗኗር ልዩነት የመጣው በአብዛኛው ለመማር ባገኙት ወይም ባጡት ዕድል ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ በገሀድ የሚታወቅ ሐቅ ነው።“ — የተወሰደ
Open in Telegramየቆየች ጽሑፌ ብትሆንም ተጋበዙልኝ :) አላህ ‘ﷻ’ በቁርዓን ላይ እንዲህ ይለናል፦ “የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን ዐሥራ ሁለት ወር ነው፡፡ ከእነሱ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው፡፡ በእነርሱ ውስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ።“ — Quran ስለዚህም አይደል አላህ ለፍጥረታቱ በወሰነው ትክክለኛ የጊዜ ቀመር ለመገልገል ስንል አሥራ ሁለት ወራትን ያለምንም ተጨማሪ እና ተቀናሽ ወራት “Leap Month” የያዘውን የጨረቃ የቀን መቁጠሪያ “Lunar Calendar” ለመቁጠሪያነት የምንጠቀመው — ይህ የቀን መቁጠሪያ ከያዛቸው አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ አሁን ያለንበት የረመዳን ወር አንዱ ሲሆን ረሡል ‘ﷺ’ ከመካ ወደ መዲና ጉዞ ባደረጉ በሁለተኛው ዓመት እንደ ኤሮፓውያንን አቆጣጠር በ 624 CE ለመላው ሙሥሊም ማህበረሰብ ረመዳንን እንዲፆም ታዘዘ፦ “እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነገገ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡” — Quran ረመዳን “رمضان” የሚለው ቃል ረመደ “رمض” ማለትም “አቃጠለ” ከሚለው ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን “አቃጣይ” “የሚያቃጥል” ማለት ነው። የጨረቃ የቀን መቁጠሪያ “Lunar Calendar” ከፀሃዩ የቀን መቁጠሪያ “Solar Calendar” በ 11 ቀን አካባቢ ያነሰ ሲሆን የረመዳን ወር በአራቱም ወቅቶች ማለትም፦ ፀደይ፣ በጋ፣ በልግ እና ክረምት ውስጥ በየ ሠላሣ ሦሥት አመቱ ያልፋል፡፡ ለምሳሌ፦ በሀገራችን የዘመን መቁጠሪያ ከመስከረም እስከ ህዳር “ፀደይ” ...ከታህሳስ እስከ የካቲት “በጋ” ...ከመጋቢት እስከ ግንቦት “በልግ” ...ከሰኔ እስከ ነሀሴ “ክረምት” …ተብሎ ወራትን በየወቅቱ ላይ ተመድበው የሚገኙበት ድልድል ሲኖር! ይህ የድልድል ስርዓት “Intercalation” በኢሥላማዊ የዘመን መቁጠሪያ ውስጥ ግን የለም፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ወራትን በየ ወቅቱ መመደብ “Intercalation’’ አምላካችን አላህ በቁርዓን ውስጥ ስለከለከለ ነው፦ “የአንዱን ወር ክብር ወደ ሌላው ማዘግየት በክህደት ላይ (ክህደትን) መጨመር ብቻ ነው፡፡ በእርሱ እነዚያ የካዱት ሰዎች ይሳሳቱበታል፡፡ በአንድ ዓመት የተፈቀደ ያደርጉታል፡፡ በሌላው ዓመትም ያወግዙታል፡፡ (ይህ) አላህ ያከበራቸውን ወሮች ቁጥር ሊያስተካክሉ፣ አላህም እርም ያደረገውን የተፈቀደ ሊያደርጉ ነው፡፡” — Quran ከዚህም ጋር ተያይዞ የመካከለኛው ክፍለ ዘመን የታሪክ አጥኚ እና የዓረቢኛ ቋንቋ ሊቅ ‘ሙሐመድ ኢብን ሙከረም ኢብን መንዙር’ “ሊሳን ዓል ዓረቢ” በተሰኘ ታላቅ መፅሐፋቸው ላይ የስርው ፍቺውን “Etymological Definition” ጉዳይ አስቀጥለው ይህን ንግግር ይጠቅሳሉ፦ “ኢብን ዱረይድ እንደተናገረው፦ ከጥንታዊ ቋንቋዎች የወራት ስሞችን በሚያስተላልፉበት ጊዜ ወራቶቹ ከተከሰቱበት ወቅት በኋላ በዚያ ይሰይሟቸው ነበር። ረመዳን ከፍ ያለ ሙቀት ባጋጠመበት ጊዜ ተከሰተ ስለዚህም ከዚያ በኋላ በዚያ ሰየሙት።“[¹] ረመዳን የወሩ ስያሜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሰየመበት ምክንያት የ ድልድል "Intercalation" ስርዓት በሌለው የዓረቦች ዘመን መቁጠሪያ ውስጥ ያረፈበት ወቅት ሞቃታማው/በጋ ስለነበር ነው። ቃሉን ከፈታንበት ስርው ፍቺ “Etymological Definition” በዘለለ “አቃጣይ” ወይም “የሚያቃጥል” የሚለው ትርጉም በረመዳን ላይ ፅንሰ ሀሳባዊ ፍቺ እንዳለው ያውቁ ኖሯል? __ ማጣቀሻዎች፦ [1] Lisan Al 'Arabi By Ibn Manzur Volume 7 Page 161-2 ... Written By: Akhi Ahmed Respond https://t.me/ahmedrespond
Open in Telegramእስኪ ዛሬ ትንሽ ነገር ልጋብዛቹህ🤗 'ነብዩ ሙሃመድ ሰ.አ.ወ ስሙ የገዘፈ የሰው ልጅ እሳቤ ማዕዘን ነው። ምንድን ነው የሚሉት? የሰው ልጅ የሁሉም ነገር ሚዛን ነው አይደል? በቃ ያ ሰው ሙሃመድ ሰ.አ.ወ ነው። የትኛውም የልዕልና ከፍታ የሰው ልጅን ህይወት አይዳስስም። አንዱ ስለ ሰላምና ፍቅር ይሰብክሃል ነገር ግን የሰው ልጅ ጦርነትን ይፈጥራል ያኔ ምን ታደርጋለህ? […ስለሰለም እየሰበክ ትኖራለህ?] ቡድሃ ኑሮ የለውም አንተ ግን አለህ!! እስኪ እሱን መሰረት አድርገህ ኑር። ግማሽ መንገድ ላይ ትቀራለህ። በህይወትህ ልክ ልክክ የማይሉ ታላላቅ ነፍሶች አሉ ግን በሚልየን መካከል እንዳለ አንድ ግለሰብ ለመኖር እንጂ እንደ ህዝብ አዳጋች ነው። የትኛውም በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ የሚከሰት ታላቅ ሰው አንዱን የህይወት መስክ መዝዞ ነው የምታገኘው። ወይ ፍቅር ሰብኮህ ያልፋል ወይ ጦር ያማዝዝሃል። ከላኦ ዙ እስከ ማህቪራ ፥ ከቡድሃ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ነብያቶች. . . ዳህማፓዳ ላይ ይሁን ሌላ ቦታ አንድ ታሪክ አለ። ቡድሃ ላይ ሰውየው ተፋበት። ቡድሃ በፍፁም ትዕግስት ውስጥ ነበር። ምንም አላለም ጭጭ። ዳግመኛ መጥቶ ይቅርታ ጠየቀ "ትናንት የነበረው ማንነታችን ዛሬ የለም ተፊውም የተተፋበትም ዛሬ የሉም" "And whoever is patient and forgives – indeed, that is of the matters [worthy] of resolve.” (42:43) ይህ ግን ሁሌም አይሰራም። ቡድሃን መሆን አለብህ ነገር ግን ህይወት አንድ ቅርፅ ብቻ አይደለም ያላት። በዚህ ህይወት ውስጥ ተተፍቶብህ መታገስ የሚችለውን ቡድሃን ብትፈጥር ስህተቱ የገባው የሚነቃው ተፊ ያስፈልግሃል። ዳግመኛ ቢተፋብህስ? ፍቅር ሁሌም አይሰራም!! ሁሌ ግራህን እያስደበደብክ መኖር ትችላለህ? ከላይ ከጠቀስነው በላይ በመልዕክተኛው ሰ.አ.ወ ላይ ተከስቷል። የመካ ህይወታቸው አብዛኛው የመቻል ፥ የፍቅር ፥ የይቅር ባይነት ነበር። ከዘመድ እስከባዳ የገፋው የከዳው . . . ህዝብን ለመምራት ለመጣ ነብይ ፍቅር ብቻ እንዲሰብክ ከጠበቅክ ስለፍትህ እንዳታወራ። በሚደርስብህ ሁሉ መቻል አለብህ። እሳቸውጋ ግን የነበረው ሰፊ እዝነት ነው። በራሳቸው ጉዳይ ከውልደት እስከ ህልፈት ይቅርታ አድርገዋል። የጌታቸው ሃቅ እስካልተነካ ትዕዛዙ እስካልተጣሰ ፊታቸው ጨፍገግ እንኳ አይልም። ህያው ብርሃን ደብዘዝ ሊል አይችልምኮ . . . [ሁለት ብርሃን ነበሩ አባትና ልጅ - ማን ይረሳል ከነ ስሟስ ፋጢመቱ ዛህራ ረ.ኣ. እንዴት ያለ መግዘፍ ነው?!] . . . . እሳቸው ይህንን የህይወት መስክ ስላልኖሩት ምሳሌዬ ሊሆኑ አይችሉም ልትል አትችልም። ወንድ ከሆንክ ህይወታቸውን አጥና። ከፍርድ አትነሳ ሰው ብቻ ሁነህ አንብበው። Stephen Prothero በ -God Is Not One መፅሃፉ መግቢያ ላይ ፦ . . . religion is not merely a private affair. It matters socially, economically, politically, and militarily. ይህ በሳቸው ህይወት ውስጥ የሚታይ እንጂ በሌላ ስፍራ የምታገኘው አይደለም። አብዮት ካስነሱ ታላላቅ ርዕዮቶች በላይ የዘካ እና የሰደቃ ህግና ባህል ሚልየኖችን መግቧል [ፖለቲካህን ለደቂቃ ገለል ካደረግከው ሁሉም በልቶ ያድራል] እዝነት ያለበት ፖለቲካዊ ርዕዮት የለም። ማሪዮ ፑዞ በGodfather ማብቂያ ላይ "Politics and Crime are the same" የሚለው ወድዶ አይደለም ምክንያቱም መድረስህ እንጂ ለመድረስ የጨፈለቅከው አያሳስብህም "the end justifies the means" ይላልና ኒኮሎ! የስብሃት ትኩሳት ላይ ስለ ቤልጅየም መንግስት [ስልጡን ህዝቦችህ] ግፍ ያሰፈረውን ገረፍ ገረፍ አድርግ። የገነባኸው አለም የHIV መድሃኒት ከመስራት ፥ ኢቦላን እና ካንሰርን ከማጥፋት የመረጠው ለግብረሶዶም በጀቱን መመደብ ነው። ቤተ ክርስትያን እና መስጂዶችን ማጥፋት ቫይረስ ማምረት . . . ስለየትኛው ግብረገብ ነው ምናወራው? አይደለም ህይወትህን ለመዳሰስ በልተህ ማደርህ እንኳ እርግጥ ባልሆነበት ስንኩል ርዕዮት የገነባቸው መንግስታት ባሉበት አለም ነው ምትኖረው። ታውቃለህ ነብዩ ሰ.አ.ወ ሲያልፉ ገንዘባቸው ሳንቲም ሳትቀር ለምስኪን እንደዋለ? ይህ ታላቁ ነብይ ነው!! በሚልየን ስላጎሩ የሃይማኖት አባቶች አናወራም። የምናወራው ስለከፍታው ነው። ያ "ለአለማት እዝነት" ስለተደረገው ንፁህ ነፍስ!! በዚህ ዘመን የትኛውን የሃይማኖት ታላላቅ አባቶች ነው ቀረብ ብለህ ማናገር የምትችለው? ጋርዶቻቸውን ማለፍስ ትችላለህ? ሙሃመድ ሰ.አ.ወ ጠባቂ ያሌለው ንጉስ ነበር። ርሃብ ካለ እኩል የሚርበው መጠማት ካለ እኩል የሚጠማው እንጂ ምዕመኑ ተቸግሮ እያየ አስተምሮ በቅንጡ መኪናው ወደቤቱ የሚያመራ አልነበረም። እስኪ ሚድያህ ላይ ያሉ ቤሳቤስቲን ያሌላቸው የሃይማኖት ታዋቂ አባቶች አምጣልኝ! ይኸውልህ ጓዴ Egoህንም ወደህ ፍትህንም ፈልገህ አይሆንም። በድል አድራጊነት የትውልድ ቀዬውን መካን ሲቆጣጠር የተዋጉት "ምን ታደርገናለህ? ፍርድህስ ምንድን ነው?" ሲሉ . . . "ይቅር ብያችኋለሁ ባላችሁበት ኑሩ" ነበር ያለው!! ተሸንፈህ ይቅርታ ልታደርግ ትችላለህ አማራጭ የለህምና። አሸንፈህ ግን ይቅርታን ማድረግ ግን ሌላ ጉዳይ ነው። የትኛውም የህይወት መምህር ቁንፅል ህይወትህን ብቻ ነው ሊመራህ የሚችለው። ይህንን ሃቅ በራስህ ድረስበትና ታዘብ! አሁን ላለው ውጥንቅጥ መፍትሄ ትፈልጋለህ? ቤተሰብህ ተናግቷል? ወላጆችህ አኩርፈውሃል? ከገባህበት ማጥ መውጣት ተስኖሃል? በቃ ግራ ገብቶሃል? ለማንም አትናገር ተደብቀህ ህይወታቸውን አጥና ምክራቸውን ተግብረው ያኔ ወንበርህ ላይ ሁነህ ያላሰብከው ፈገግታ ፊትህ ላይ ታገኛለህ!! Writing ✍️ 𝐇𝐞𝐫𝐚𝐧 𝐀𝐥𝐞𝐦𝐚𝐲𝐞𝐡𝐮🦋
Open in Telegramሀልዎተ ኢሥላም (ቅድመ ሙሐመድ 'ﷺ' ) ... የክርስቲያን አቃቢያን መታወቂያ ላይ የ አደጋ ጊዜ መውጫ ተብለው ከሰፈሩ ጥያቄዎች አንዱ ይህ "ቅድመ ሙሐመድ 'ﷺ' ባሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች የእስልምና መኖር ሊረጋገጥ ይችላልን?" የተሰኘው ጥያቄ ነው ...ጥያቄውም እንደ ጥያቄ በአድማጩ ማህበረሰብ ላይ በተንሰራፋበት አውድ ተገቢውን መልስ ከማቅረብ አኳያ በኛ በኩል ካሉ አካላት ግልጽ እና አመርቂ እይታ ባለመመልከቴ ይህቺን መጣጥፍ አሰፍር ዘንድ ወደድሁ። የፍጥረተ አለሙ አስገኚ እኛ የሰው ልጆችን ሲፈጥር እሱን ለመገዛት የተመራን በመሆን ውስጥ ቃል የተገባልንን ገነት እንድናገኝ በሚል አላማ እንደሆነ በተከበረ ቃሉ አበክሮ ይነግረናል። (51፥56፣2፥21) ወደዚህች ምድር ሲያመጣንም እሱን ለመታዘዝም ሆነ ለማመፅ ከሚያበቃን የምርጫ ነፃነት “Free Will” ጋር ሲሆን ለፍጡራኑ ካለው ውዴታ በተነሳ ለገዛ ምርጫችን ሳይተወን በመልካም የሚያዙ በመጥፎ የሚያስጠነቅቁ ነብያትና መልዕክተኞችን ሲልክ ቆይቶ የነዚሁ ማገባደጃ እና ማብቂያ በማድረግ ነብዩ ሙሐመድን 'ﷺ' ከተከበረው ቃሉ ጋር ለአለም ልኳቸዋል። ይህ ነብያት የተላኩበት ለብቸኛው አምላክ እጅ የመስጠት (የመታዘዝ፣የመገዛት) መንገድ በዓረቢኛ የቃል አጠቃቀም ውስጥ ኢሥላም "اسلام" ተብሎ ሲጠራ የዚህ መንገድ አስኳል እና ምሰሶ የሆነው የአንድ እና ብቸኛ አምላክ አስተምህሮ "Monotheism" የነብያቱ መሠረታዊ አጀንዳ መሆኑን ጠቋሚ የሆኑ ዘርፈ ብዙ መረጃዎች ቢኖሩም በነዚህ መረጃዎች ላይ እንደ አንድ አርዕስት ለመመለስ በማሰብ በዛሬው ነጥብ ላይ አንዳንድ አስፈላጊ ግምገማዎችን እንቃኝ … ዘርፈ ብዙ መሣሪያዎችን በመጠቀም ስለ አላፊ ክስተቶች የሚያትት የጥናት ዘርፍ "ታሪክ" ተብሎ ሲጠራ በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን ደግሞ "ታሪካውያን" በሚል የማዕረግ ስም እንጠራቸዋለን። ሴኩላር ዘርፉ ቀላል የማይባሉ ክስተቶችን እውነታነት እንዳረጋገጠልን ሁሉ ታሪካውያኑ በተለያየ ጊዜ ውስጥ ከማስረጃ ውስንነት አንፃር በአንዳንድ ክስተቶች ውስጥ ዝምታን መምረጣቸው የክስተቱን ህልውና ሙሉ ለሙሉ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ (አለመከሰቱን፣አለመኖሩን) እንደማያመላክት ያስገነዘቡን ዘርፈ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶች ለቁጥር አታካች ናቸው ለምሳሌ፦ በአያሌ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ውስጥ ሰፍረው የምናገኛቸው ኬጥያውያን "Hittites" 'ሁጎ ዊንክለር' በተሰኘ ጀርመናዊ አርኪዮሎጂስት የመሪነት ውጥን በ 20 ክ/ዘመን ህልውናቸውን ስነ ቅርስ እስኪያረጋግጠው ድረስ ከታሪካውያኑ ዘንድ የነበረው ግምገማ ከአፈ ታሪክ የዘለለ አልነበረም ይለናል 'Dr. Ira M. Price' :- “The Hittites are often mentioned in the Old Testament. Otherwise they were a forgotten people until the second half of the nineteenth century. The lack of extra-biblical testimony to their existence led some scholars about a half-century ago to deny their historicity.” [¹] … በሌላ አቅጣጫ አብዝሀኛው ማህበረሰብ ኢ-ርቱዕ "Secondary" ለምንለው እንደ ታሪክ መጻሕፍት ያሉ የምንጭ አይነቶች ተጋላጭ ከመሆኑ ጋር "history is written by the winners" እንዲል 'Napoleon Bonaparte' የታሪክ ምሁራን እና ጸሐፍት ምንጮች እንኳ አሸናፊ እንደሆነው አካል ፍላጎት ሲቀረፁ እና ሲረቁ የሚስተዋልበት አጋጣሚ እጅጉን ሰፊ ነው። 'Edward H. Carr' "What Is History?" በተሰኘ መጽሐፉ ላይ “Study the historian before you begin to study the facts.” [²] ሲል ያሳሰበን በዚሁ ስሌት እና ቀመር አይደለምን? ለዚህ ነጥብ ማሳያ በመሆን ከሚቀርቡ ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ማስረጃዎች መካከል ቤ/ክርስቲያን አንዷ ነች! ከጥንታዊቷ ቤ/ክርስቲያን ተቃራኒ አቅጣጫ ቆመዋል ተብለው በመታመን ምንፍቅና "Heretics" በሚል የአመለካከት መደብ ውስጥ የተካተቱ አካላት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል! "የነገረ አበው አባት" በመባል የሚታወቀው 'ቅዱስ አውሳብዮስ ዘ ቂሳሪያ' ስራ የሆነው "Church History" የተሰኘ መጽሐፍ (VIII) መቅድም ላይ እንዲህ ከማለቱ ጋር፦ “But we shall introduce into this history ...only those events which may be useful first to ourselves and afterwards to posterity.” ይበልጡኑ ከ2 ተኛው እስከ 5ተኛው ክ/ዘመን ባለው የክርስትና ታሪካዊ ዳራ ውስጥ አያሌ በክርስትና ጎራ ስር ምድብነት የነበራቸው አንጃዎች እንደነበሩና ጠንከር ባለ ግብግብ ውስጥ በመግባት አንዱ አንዱን ሲያዳክም እና ሲጥል በዘለቀበት ፍልሚያ ውስጥ የአሸናፊነቱን ቦታ የያዘችው አካል "Proto Orthodox" በተቃራኒ የአመለካከት አቅጣጫ ላይ ቆመዋል ብላ ያመነችባቸውን አካላት ሄተሮዶክስ "Heterodox" በሚል ቅፅል በመቀፀል ቀላል የማይባል ጥፋትን ከማድረስ አልፎ ለዚህ ጥቃት ተጋላጭ የሆኑትን አካላት ታሪክ እንደመሰላት አድርጋ ከፃፈችው ከራሷ ከድል አድራጊዋ ቤ/ክርስቲያን የመረጃ ምንጮች እንድናገኝ እንዳደረገች 'Bart D. Ehrman' የተሰኘ አሜሪካዊ የአዲስ ኪዳን ምሁር "The Lost Christianities" በተሰኘ መጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ በሰፊው ያትትልናል ... [³] … በማህበራዊ ፖለቲካዊ አውድ የሚወሰነው ታሪክ ዝምታ "Historical Silence" ቅድመ ሙሐመድ 'ﷺ' የእስልምናን ህልውና ውድቅ የሚያደርግ ማሳያ አድርጎ ማቅረቡ "argumuntum ad ignoratium" በተሰኘ ህፀፅ ውስጥ መመደቡን በማስያዝ እስልምና በታሪክ ምንድን ነው? ቢሉ የታሪክ እና ታሪካውያኑስ ምንድን ናቸው? በማለት መጠይቃችንን እያሰፈርን ስነ ቅርፃዊ ግምገማው የብዙሃኑን የህልውና ጥያቄ በቅጡ እንኳ ካለመመለሱ አልፎ ምድራችን በምትገኝበት አውድ የዚህ አለም እግዜሮች ስለ ሁኔታው ዝምታን መምረጣቸው …የትርክት ሀሰትነት አለመረጋገጥ እውነት እንደማያደርገው የትርክት እውነታነት አለመረጋገጥ ሀሰት አያደርገውምና በጊዜ ውስጥ ስለነበረው ጊዜ አሳላፊ ከሆነው ጌታ ቃል (ቁርዓን) ግንዛቤ ስር አርዕስቶቻችንን በማስጠለል የዛሬዋን መጣጥፍ እናገባድዳለን። “ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፡፡ ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)።” — Surah Ash Shuara 42:13 __ ማጣቀሻዎች፦ [1] Ira M. Price, The Monuments and the Old Testament (1909), pp. 75–6 [2] Edward H. Carr, What is History? (1961), p. 26 [3] Bart D. Ehrman, The Lost Christianities (2003), Ch. 1 ... Written By: Akhi Ahmed Respond https://t.me/ahmedrespond
Open in Telegram