Account

Posts of AHADU RADIO FM 94.3

newest first

#26077Text

“የኤርትራ መንግሥት ጊዜያዊ ነው፤ በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ ልማትና ዕድገት የሚባል ነገር የለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በጋራ ለመልማት ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም፤ የኤርትራ መንግሥት ግን ለልማትና ለዕድገት ፍላጎትም ሆነ ግንዛቤ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል። “የኤርትራ መንግሥት በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ ልማትና ዕድገት የሚባል ጽንሰ ሐሳብ የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ምክንያት መንገድ እንሥራ ወይም በጋራ እንልማ ሲባል እንደ አለማወቅና ቂልነት አድርጎ እንደሚመለከተው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በጋራ ከተሠራ ትልቅ የዕድገት አቅም መኖሩን በማመን ከኤርትራ ጋር አብሮ ለመልማት ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። ለአብነትም በኤርትራ ያለውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በኢትዮጵያ ወጪ በመዘርጋት በሀገር ውስጥ ተመን ኃይል ለማቅረብ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር አስታውሰዋል። በተጨማሪም ሁለቱን ሀገራት የሚያስተሳስሩ መንገዶችንና ወደቦችን በጋራ ለመገንባት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም በኤርትራ መንግሥት በኩል ፈቃደኝነት አለመገኘቱን አስረድተዋል። ሁለቱ ሀገራት በትብብር ቢሠሩ ኖሮ አስመራን ከኢትዮጵያ ልምድ በመውሰድ በኮሪደር ልማት ማሳደግ ይቻል እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ አለመሆኑ የኤርትራ መንግሥት ትልቅ ድክመት መሆኑን ገልጸዋል። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ለጋራ ልማት ሐሳቧን ፣ ገንዘቧንና ጉልበቷን በሙሉ ለማዋጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠው የኤርትራ መንግሥት ምንም ዓይነት ገንዘብም ሆነ ሐሳብ ሳይጠበቅበት ተባባሪ ብቻ በመሆን በሰላምና በጋራ ዕድገት ጎዳና እንዲጓዝ ጥሪ አቅርበዋል። በወልደሐዋርያት ዘነበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views281−36%vs avg
Forwards—
Reactions3
Comments—
#26074Photo

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለወጣቶች ዕድል የሚፈጥር የ 10 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በስሩ የሚገኙ ስምንት የልማት ድርጅቶች ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ወጣት ስራ ፈጣሪዎች መፍትሔ እንዲያመነጩ ዕድል የሚያመቻች እና 10 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት "ካማ" የተሰኘ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት ያህል የሚቆይ ሲሆን ካማ በመባል የሚጠራው ይህ ፕሮጀክት ሀገር በቀል መፍትሔዎችንና ስታርት አፕዎችን በማገዝና ወደ ገበያ የማሻገር ሂደትን ለማፍጠን ያለመ እንደሆነ ተቋሙ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚያደርገው ከኤ.ኤል.ኤክስ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር ሲሆን መርሐ ግብሩም በአራት ዙሮች የሚተገበር መሆኑን ተገልጿል። "ካማ" ሀገር በቀል መፍትሔዎችንና ስታርትአፕዎችን በማገዝና ወደ ገበያ የማሸጋገር ሂደትን ከማፍጠን በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ ዲጂታል እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያበለጽጉ እንዲሁም በተግባር እንዲውሉ ዕድል በመፍጠር ለ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ግቦች መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተጠቁሟል። የ"ካማ" የመጀመሪያ ዙር ማመልከቻ ከህዳር 17 እስከ ታህሳስ 29 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን መስፈርቱን የሚያሟሉ ኢንተርፕርነሮች ፣ ስታርትአፕዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም የልማት ድርጅቶች ያቀረቧቸውን የፈጠራ ፍላጎቶች ማመልከት እንደሚችሉ ተገልጿል። በተመስገን ተጋፋው #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views379−14%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
#26073Photo

ትግራይን ጨምሮ የተሟላ ሰላም ሲኖር የህዝብ ቆጠራ እንደሚደረግ ተገለጸ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ትግራይን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የተሟላ ሰላም ሲሰፍን እና ነገሮች መልክ ሲይዙ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። የምክር ቤት አባላት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለሀገሪቱ የልማት ዕቅዶች ፣ ለፍትሐዊ የበጀት ድልድል እንዲሁም ለምርጫ ክልሎች አከላለል ወሳኝ መሠረት መሆኑን አንስተው ቆጠራው እንዲካሄድ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 13 እና 14 ዓመታት የአካባቢ ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱን የገለጹት አባላቱ ምርጫው የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ በመንግስት አቅጣጫ ውስጥ እንዲካተት ፣ ለሕዝብ ግልጽ እንዲደረግና አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲከናወን ጥያቄ አቅርበዋል። ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕዝብ ቆጠራው ትግራይን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች የተሟላ ሰላም ሲኖር መካሄድ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው "ነገሮች መልክ ሲይዙ ይደረጋል" ብለዋል። የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ የአካባቢ ምርጫ በዋናው ምርጫ መካከል የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው የዘንድሮው የመንግስት ዕቅድ ቀደም ሲል ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ላይ የማሟያ ምርጫ ማካሄድ መሆኑን አስረድተዋል። አያይዘውም የማሟያ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ምናልባት ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ አካባቢ ምርጫ እንደሚገባ ገልጸዋል። በፋሲል አረጋይ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views491+11%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
#26072Text

35 ሺሕ የህጻናት መዋያ ተቋማት በፌዴራልና በክልል መንግስታት መገንባታቸው ተገለጸ 👉 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ከመነሻው መሰረታዊ እውቀት እንዲያገኙ መደረጉ ተነስቷል ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያና ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ፍኖተ ካርታውና የትምህርት ስርዓቱ መቀየሩን ተከትሎ በዘርፉ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አስታውቀዋል። በመንግስት የትምህርት ፖሊሲና ስርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ ህጻናትን ከመጀመሪያው በመሰረታዊ እውቀት ለማብቃት ያለመ ነው ብለዋል። በዚህም መሰረት በፌዴራልና በክልል መንግስታት 35 ሺሕ የህጻናት መዋያ ተቋማት መገንባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ከመነሻው ጀምሮ መሰረታዊ እውቀትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ መሰረታዊ ስራ ከ20 ዓመታት በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨባጭና ዘላቂ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የሞዴል ቦርዲንግ ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር 50 ሞዴል አዳሪ ትምህርት ቤት መገንባቱ ጠቁመዋል። የፈተና ስርዓትን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለማዘመን በተያዘው አቅጣጫም ከጥቂት ዓመታት በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና 90 በመቶ በዲጂታል እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል የመምህራንን የማስተማር አቅም ለማሳደግ የስልጠና ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፍኖተ ካርታና የስርዓት ለውጡ በትምህርት ዘርፉ አዎንታዊ ለውጥ ማስገኘቱን ለምክር ቤቱ አስገንዝበዋል። በወልደሐዋርያት ዘነበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views432−2%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26070Text

በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራትና በአንድ ቋንቋ መቆም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)   አሳሰቡ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻልና እድገት መኖሩን ገልጸው፣ የቀሩ ጉዳዮችን በጋራና በትብብር ለመፍታት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት በሚሰማው አካል ልክ በጉዳዩ ላይ «አንድ ቋንቋ» መናገር እንደሚገባ ያነሱ ሲሆን፣ ጥፋትና ጥቃት ሲከሰት የፖለቲካ አጀንዳ ከማድረግ ይልቅ በጋራ ማውገዝና መታገል እንደሚገባ አመልክተዋል። በንግግራቸውም በቅርቡ በአርሲ አካባቢ ሕዝብን ለማዳን ሲሉ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የፖሊስና የሚሊሻ አባላት መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ቤተሰብና ልጆች ላሏቸው እነዚህ አካላት ተገቢው እውቅናና ክብር ካልተሰጣቸው ወደፊት ሕይወቱን የሚሰጥ አካል እንደማይገኝ አስጠንቅቀዋል። በአርሲ የአመራር ለውጥ መደረጉን፣ ሕዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸውን፣ ራስን ከጥቃት የመጠበቅ አሰራር መዘርጋቱን  እንዲሁም ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ጥረት መደረጉን ገልጸው፣ የጸጥታ ኃይሎችም ዋጋ መክፈላቸውን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በአማራ ክልል በጎጃም አካባቢም የአካባቢ ሚሊሻና ፖሊስ ሕዝብን ለመጠበቅ ሲሉ ሕይወታቸውን እያጡ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝብን የሚጠብቀው ራሱ ሕዝብና የጸጥታ ኃይሉ እንጂ ከሌላ ቦታ መጥቶ የሚሞት እንደማይኖር ተናግረዋል። ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርበትና በመንደር በተበታተነ ሀገር ውስጥ በእያንዳንዱ ቀበሌና ቤት መቆም እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘላቂ መፍትሔው ሕዝቡና የጸጥታ ተቋማት ተናበውና መረጃ ተለዋውጠው ጥቃት የሚፈጽሙ አካላትን በጋራ መከላከል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህንንም በ«አውቶኢሚዩን ዲዚዝ» (በሰውነት ውስጥ ሆኖ የሚያጠቃ በሽታ) በመምሰል ገልጸውታል። አክለውም በብሔር የተሞከረው ሙከራ እንዳልተሳካ ሁሉ በእምነትም ሊሳካ እንደማይችል ጠቅሰው፣ የጸጥታ ኃይሎች ጥፋተኛን ሲገድሉ «ጥፋተኛ ነው፣ አሸባሪ ነው፣ ሕዝብን ይጎዳል» በሚል በአንድ ድምጽ መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል። የትኛውም ሀገር መንግሥት የጸጥታ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ብቻውን ሊቆጣጠር እንደማይችል በምሳሌ ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻም በትብብርና በቅንጅት በመስራት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተስፋቸውን ገልጸዋል። በሊዲያ አበበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views409−7%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#26067Photo

ሚኒስትሮች ወደ ሁርሶ ስልጠና የገቡት ሰው ለመሆን፣ ሀገርን ለመውደድና ሰንደቅ ዓላማን ለማክበር እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ሹመትና ሥልጣን የሰውን ጠባይ ሊቀይር እንደሚችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስልጠናው አገልጋይነትን ለማስረጽ፣ ቀላል የሚመስሉ ስራዎችን ጨምሮ መሠረታዊ ሕይወትን ለመለማመድ እንዲሁም በአካልና በስትራቴጂ ለመዘጋጀት የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል። የሁርሶ ስልጠና ዋና ዓላማ ዜጎችን ማዋጋት ሳይሆን ዜጎች «ሰው» እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ወላጆችም ልጆቻቸው የተበላሸ ትውልድ እንዳይሆኑ በወታደራዊና በሥነ-ምግባር አሰልጥነው እንዲያሳድጓቸው መክረዋል። አክለውም አንዳንድ ባለሥልጣናት በስልጠናው ካገኙት ልምድና በሀገር ፍቅር ስሜት ባህሪያቸውን ማስተካከላቸውን ገልጸው፣ ጉዳዮችን ከሌሎች ሀገራት የግዳጅ ወታደራዊ ሰልጠናዎች ጋር ማቀራረብ ብዙም ፋይዳ እንደሌለው አመልክተዋል። በሊዲያ አበበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views395−10%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26066Photo

"ዐድዋን እንደግመዋለን" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ኢትዮጵያ የሱ 35 የጦር ጄቶችን የታጠቀችው ሉዓላዊነቷንና የቀጣናውን ደህንነት ለማስጠበቅ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "አድዋን እንደግመዋለን ሲሉ ገለፀው፣ ማንም ሲሉ የጠሩትን ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መጥቶ በክብር መመለስ እንደማይችል" ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነትና የቀጣናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ዘመናዊ የሱ-35 የጦር ጄቶችን መታጠቋንም አስታውቀዋል። እነዚህን ዘመናዊ የአየር ኃይል ቴክኖሎጂዎች የታጠቀችው በዋናነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነቷንና እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እንዲሁም ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ማንኛውንም የውጭ ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል ፣ የሀገሪቱን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ እና ለአፍሪካ ቀንድ የጋራ ሰላምና ደህንነት አስተዋጽኦ ለማበርከት መሆኑን ገልጸዋል። ዘመናዊ የጦር ጄቶችን ከመታጠቅ ባሻገር ይህን አቅም በዘላቂነት ለመጠቀምና ውጤታማ ለማድረግ ኢትዮጵያ በቀጣይ ትኩረት ሰጥታ ልትሰራባቸው የሚገቡ ቁልፍ ተግባራት መኖራቸውንም ጠቁመዋል። በደረጀ መንግስቱ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views368−17%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26064Photo

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀረቡ የሕገ መንግስት ማሻሻያ የሚፈልጉ ምክረ ሐሳቦች በሕግ ባለሙያዎች ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ተገለጸ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት ተጠቃለው በምክረ ሐሳብ መልክ ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል የሕገ መንግስት ማሻሻያ የሚፈልጉትን አስመልክቶ ላለፉት ወራት በሕግ ባለሙያዎች ጥልቅ ምክክር እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የሕግ ባለሙያዎቹ እያደረጉት ያለው ይህ የምክክር ሂደት በሚቀጥሉት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን ውጤቱም ለምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔው ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ከባዱን የውይይት ሂደት መርተው ካጠናቀቁ በኋላ በመጽሐፍ መልክ ያቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች በፖሊሲ ፣ በአስተዳደር እንዲሁም በሕገ መንግስት ማሻሻያ የሚመለሱ ጉዳዮችን የያዙ መሆናቸውን አብራርተዋል። አጠቃላይ የምክክር ሂደቱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲናገሩ ከሁሉም አቅጣጫ መነጋገር መቻሉ እንደ ትልቅ እርምጃ የሚቆጠር መሆኑን ጠቅሰዋል። ለአራት ዓመታት የዘለቀ እልህ አስጨራሽ ውይይት መካሄዱን እና በዚህም 4 ሺህ ተሳታፊዎች ለ46 ቀናት መምከራቸውን አስታውሰዋል። በትዕግሥትና በውይይት ችግሮችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ጠቃሚ እንጂ ጎጂ ሆኖ እንዳልተገኘ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። በፋሲል አረጋይ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views344−22%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26063Text

የፕሪቶሪያ ስምምነት ታሪካዊና የተከበረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ አሸንፎ ሰላምን መፈራረም ቀላል ባይሆንም «ሰላም ይሻላል» በሚል ሀሳብ ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል። ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ገዘፍ ያለ እና መረር ያለ እውነታን መቀበል የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወገኑን ኃይል ባለመፍታት እና አቅፎ በመሥራት ይቅርታ መቀበል ቢከብድም በክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም መግባታቸውን ተናግረዋል። የንግግርና የሰላማዊ አካሄድ ለኢትዮጵያም ለቀጣናውም ጠቃሚ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም የሚፈታተኑ ኃይሎችን ሁኔታ ከ«አውቶ ኢሚዩን ዲዚዝ» ጋር በማነጻጸር ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰውነት በሽታ መከላከል ሥርዓት ጤናማ ህዋስን እንደሚያጠቃ ሁሉ፣ አንዳንድ ኃይሎችም የራሳቸውን ሕዝብና ሀገር በማጥቃት ላይ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል። በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ያሉ አንዳንድ የታጠቁ ኃይሎችና ግጭቶችን የሚያባብሱ አካላት ልማትና ሰላምን እየጎዱ መሆኑን ገልጸው፣ የትግራይ ሕዝብ በተለይም የትግራይ ወጣቶች የአንድ ቡድን ዕድሜ ማራዘሚያ ላለመሆን መንቃታቸውንና ወደ ሰላማዊ መንገድ ማዘንበላቸውን አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ የብሔርን ወይም የሃይማኖትን ስም በመጠቀም የሚደረጉ ቀስቃሽ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንደማይሆኑ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የ20 ዓመት ራዕይ ይዞ የሚሠራ መሆኑን እና በቀላሉ የማይናወጥ መሆኑን ተናግረዋል። በመጨረሻም፣ ዜጎች የሌሎች መሣሪያ ከመሆን ይልቅ በሰላማዊ መንገድ በመግባት፣ በሕግና በሥርዓት ውስጥ ሆነው ለሀገርና ለራሳቸው ሰላም እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። በሊዲያ አበበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views335−24%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26061Photo

የመከላከያ ተቋም ግንባታ፣ የቀጠናውን ወንድሞች ለመደገፍ የሚያስችል ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በሁሉም ዘርፎች ሚዛናዊና ጠንካራ አቅም እየገነባ መሆኑንና ራሱን በራሱ መቻልና ቴክኖሎጂን ማዘመን ዋና ትኩረት መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያን ስትራቴጂ በአራት ዋና ዋና ነጥቦች ለይተው ሲያብራሩ፤ የጂኦ-ፖለቲክስ አዝማሚያዎችንና የሀገር ውስጥ ሁኔታዎችን ቀድሞ የማወቅና የመለየት አቅም መፍጠር፤ ግጭቶችን አስቀድሞ ማስቀረት፤ከዚያ አልፎ የሚመጣን ጥቃት በአጸፋዊ እርምጃ ጭምር መመከትና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ፤ከድል በኋላ በመዘናጋት ሳይሆን ድልንና ሰላምን አጠናክሮ ማስቀጠል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ግንባታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ችግር ሲገጥማቸው የቀጠናውን ሀገራትና ወንድሞችን ለመደገፍ የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ የታጠቅነው የሱ-35 አውሮፕላንም የማንንም የማጥቃት ፍላጎት ሳይሆን ኢትዮጵያንና ቀጠናውን ከሚታዩ ስጋቶች ለመከላከል ያለመ መሆኑን እና ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም ሀገር ወራ አታውቅም ፤ ዛሬ አይደለም በታሪኳ። ወደፊትም ያ ፍላጎት የላትም። ሌሎች ማወቅ ያለባቸው ግን ትንሽም ይሁን ትልቅ ማንም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መጥቶ ኢትዮጵያን ወሮ በክብር መመለስ አይችልም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። በሊዲያ አበበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views420−5%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26059Photo

መከላከያ ሰራዊት ባለፈው ዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ወደ ውጭ መላኩ ተገለጸ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ባለፈው ዓመት ብቻ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ወደ ውጭ ሀገር መላኩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። ሰራዊቱ ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች መካከል ጥይት ፣ ድሮኖች እንዲሁም የአውሮፕላን ጥገና አገልግሎቶች ከፍተኛውን የገቢ ድርሻ ማስገኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም መከላከያ ሰራዊቱ ራሱን በመቻል ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሁኑ ወቅት ሰራዊቱ የራሱን አልባሳት ፣ ምግብ እና ተተኳሾችን በራሱ አቅም ማምረት መጀመሩን አብራርተዋል። በመጨረሻም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የተወሰኑ የመከላከያ ፋብሪካዎችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። በፋሲል አረጋይ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views4420%vs avg
Forwards—
Reactions3
Comments—
#26058Photo

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ የሚነሱ ትችቶችን ተቃወሙ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች "ዜጎችን ለማፈናቀል የሚሰሩ ናቸው" በሚል የሚቀርቡ ትችቶችን "መሰረተ ቢስ እና ጋሬጣ" ሲሉ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ዜጎችን ለማፈናቀል ነው የሚለውን መከራከሪያ በማንሳት "ይህንን ምክንያት ብንቀበል እንኳን በጎንደር ፣ ባህርዳር ፣ ሀዋሳ ፣ ጅማ፣ አርባምንጭ እንዲሁም ጅግጅጋ እየሰራናቸው ያሉ የኮሪደር ልማቶች ማንን ለማፈናቀል ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል። በሀገር ልማት ላይ እንቅፋት የሚሆኑ ክሶች እንደማይጠቅሙ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚበጀው ከተቻለ ተባብሮ መስራት ካልሆነም መንግስት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። አክለውም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን "ማራከስ ተገቢ አለመሆኑን" አሳስበዋል። በኢትዮጵያ ከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዘንድ ጭምር ትልቅ ምኞት እና ፍላጎት እየፈጠረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አመልክተዋል። #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views513+16%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
Views growthHide views growth

Views growth

Hours after publication

Show as table
Hours after publicationViews
0 h140
3 h513
  1. Total to date513
#26057Text

ነዳጅን ጨምሮ ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሠራር ወደ ዲጂታል እንደሚቀይር ተገለጸ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ሕገወጥና መደበኛ ያልሆነ ገበያን ለመከላከል እንዲሁም የሰውን ንክኪ በመቀነስ የቁጥጥር ሥርዓትን ለማጠናከር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሠራሩን ወደ ዲጂታል እንደሚቀይር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያና ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ ነዳጅን ጨምሮ ተፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን በተቀናጀና በተሳሰረ መንገድ የሚሰርቁ አካላት የሚፈጥሩትን ሕገወጥና መደበኛ ያልሆነ ገበያ ፈተና ለመከላከል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል እንደሚቀይር አስታውቀዋል። አብዛኛው አሠራር መቀየሩንና የቀሩትንም በዚህ ዓመት በተሟላ መንገድ ለመቀየርና የሰው ንክኪን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። በፋይናንስ ዘርፉ የሰውን ንክኪ መቀነስ ጉልህ ውጤት ማምጣቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በንግድ ዘርፉም ይህንኑ አካሄድ መከተል ሕገወጥትን ለመቀነስና የስርቆት ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመለየት እንዲሁም ለመከታተል እንደሚያግዝ አብራርተዋል። ሕግ ማስከበርና ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን መቆጣጠር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከስድስት ወር በፊት ወደ ነጠላ አኃዝ ወርዶ የነበረው የዋጋ ግሽበት ተመልሶ 11.7 በመቶ መድረሱን በመጥቀስ፤ የግጭትና አጠቃላይ የመስተጓጎል ሁኔታዎች እየቀነሱ ሲሄዱ ግሽበቱን በዚህ ዓመት መልሶ ለማውረድ ከፍተኛ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። በወልደሐዋርያት ዘነበ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views240−46%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26054Photo

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣይ አምስት ዓመታት በአፍሪካ ያለውን ደረጃ እንደሚያሻሽል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፎች ማገገም መጀመሩንና በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በአፍሪካ ያለውን የኢኮኖሚ ደረጃ እንደሚያሻሽል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከነበረችበት አረንቋ ወጥታ በትክክለኛው የዕድገት ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምራለች። በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቀና ማለትና ማገገም መጀመሩን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጀምበር ይፈታሉ ማለት እንዳልሆነ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት፣ ድካምና ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተዋል። በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በትብብር መሥራት ከተቻለ፣ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ሦስተኛ የሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ከአምስት ዓመት በኋላ ደረጃውን እንደሚያሻሽል ምንም ጥርጥር እንደሌለ አረጋግጠዋል። #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views237−46%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26053Text

የግብርናው ዘርፍ ከ7 በመቶ በላይ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው የ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከ7 በመቶ በላይ ዕድገት ያስመዘግባል። ዘርፉ ይህንን የዕድገት ምጣኔ እንዲያስመዘግብ ያስቻለው "መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በወሰዳቸው መጠነ ሰፊ የማሻሻያ እርምጃዎች ነው" ብለዋል። ይህ ዕድገት እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ሲያብራሩ፣ በመላ ሀገሪቱ የተስፋፋው የኩታ ገጠም እርሻ አሠራር ፣ የመስኖ ልማት መስፋፋት እንዲሁም የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽነት ማደግ ቁልፍ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል። በተለይም እንደ ትራክተር እና ኮምባይነር ያሉ ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል። በተጨማሪም በዝናብ እጥረት ይታወቁ የነበሩ ቆላማ አካባቢዎችን በመስኖ በማልማት ከፍተኛ የስንዴ ምርት ማምረት መቻሉና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ውጤታማነት ለዘርፉ ፈጣን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል። የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችንና የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችም የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የውኃ አቅርቦትን በማሻሻል የግብርናውን ምርታማነት ዘላቂ እንዲሆን ማገዛቸውን ተናግረዋል። መንግሥት የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ የማቅረብና የሀገር ውስጥ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ የማረጋገጥ ግቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በደረጀ መንግስቱ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views207−53%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
#26051Text

የሰው ኃይል እጥረት፣ የሞራል ብልሽትና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) በመንግሥት በቀጥታ የሚከታተሏቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሰራተኛ ማግኘትና የሥራ ሥነ-ምግባር ማስጠበቅ ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ፕሮጀክቶች በቀን ከ500 እስከ 700 ብር እየተከፈለ እስረኞች እንኳን የሚሠሩበት ሁኔታ ያለ ቢሆንም፣ ሾፌር፣ የቀለም ቀቢ፣ የጽዳት ሰራተኛ እና የወለል አንጣፊ የመሳሰሉ በቀላሉ የሚገኙ የሚባሉ ባለሙያዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ስራ እያለ ሰራተኛ ጠፍቶ እንደሚቸገሩ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን እውነታ ሳያጤኑ ከሀገር መሰደድን መመኘት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን አስገንዝበዋል። ከሥራ እጥነት ባሻገር ሌብነትና የማኅበረሰብ የሞራል ብልሽት ትልቅ ችግር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። ለፕሮጀክቶች የሚመጡ ቁሳቁሶችና የኤሌክትሪክ መስመሮች ተቆራርጠው መሸጥን የመሳሰሉት ችግሮች፣ በማኅበረሰብ ደረጃ ካልተፈቱ የታሰበውን ብልጽግና ማምጣት እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል። በኢ-መደበኛ ገበያ ውስጥ የሚፈጠረውን ሕገ-ወጥነትና የሰው ንክኪ ለመቀነስ በማለምም የንግድ ሚኒስቴር በዚህ ዓመት አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል እንደሚቀይር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ሕግ ማስከበርና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን መቆጣጠር ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። ከስድስት ወራት በፊት ወደ ነጠላ አኃዝ ወርዶ የነበረው የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት፣ አሁን ተመልሶ ወደ 11.7 በመቶ መድረሱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን አዝማሚያ በመቀልበስ የዋጋ ግሽበቱንና አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን እንደገና ለማውረድ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል። #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views308−30%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26049Photo

መንግስት በ6 ወራት ውስጥ ለገቢ ንግድ 6.5 ቢሊየን ዶላር ወጪ ማውጣቱን አስታወቀ 👉 ለነዳጅ የወጣው ወጪ 70 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለገቢ ንግድ 6.5 ቢሊየን ዶላር ወጪ መደረጉንና ከዚህ ውስጥ ለነዳጅ ግዥ የወጣው ወጪ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ70 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 1ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ነው። በማብራሪያቸውም የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ያቀረቡ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 3.1 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የወጪ ንግድ መከናወኑን ገልጸዋል። ይህ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በሶስት ወራት ውስጥ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.28 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ34 በመቶ ጭማሪ እንዳለው አስረድተዋል። የፋይናንስ እና የብድር አቅርቦትን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት ውስጥ ከቀረበው አጠቃላይ 426 ቢሊየን ብር ብድር ውስጥ 98 በመቶ የሚሆነው ለግል ዘርፉ መቅረቡን ገልጸዋል። መንግስት የወሰደው ብድር 2 በመቶ ብቻ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሪፖርታቸው አመላክተዋል። በፋሲል አረጋይ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views282−36%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26048Text

የኢትዮጵያ የፋይናንስና የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ እድገት ተመዝግቧል፡፡  ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ  እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በባንኮች ውስጥ ያለው ተቀማጭ ሀብት 5.3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። በተለይም የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢትዮ ቴሌኮም (ቴሌብር) እና በሳፋሪኮም (ኤም-ፔሳ) አማካኝነት ወደ 70 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል። በተጨማሪም በሁሉም ባንኮች ባሉ የሞባይል ዋሌት እና ዲጂታል ሥርዓቶች 164 ሚሊዮን አካውንቶች ተከፍተው በአጠቃላይ በዲጂታል ሥርዓቱ የሚንቀሳቀሰው ሀብት 11 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል። ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ለኢኮኖሚው የተለቀቀው ብድር 426 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት (የመጀመሪያ ሩብ ዓመት) ጋር ሲነጻጸር የ62 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከለውጡ በፊት ከአጠቃላይ ብድር ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ለመንግሥት ይውል እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዚህ ሩብ ዓመት ከተለቀቀው 426 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 98 በመቶው ለግሉ ዘርፍ መሰጠቱንና መንግሥት የወሰደው ድርሻ ከ2 በመቶ በታች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ ግኝት ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ፦ ·  የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት)፦ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ እድገት ያለው ሲሆን፣ ከሪፎርሙ በፊት ኢትዮጵያ በዓመት ታገኝ የነበረውን የኤክስፖርት ገቢ በአንድ ሩብ ዓመት ብቻ ማሳካት ተችሏል። · የአገልግሎት ዘርፍ፦ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት አንጻር የ27 በመቶ እድገት አሳይቷል። ·  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.28 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ34 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። በተጨማሪም በሐዋላ እና በሌሎች መንገዶች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ ከፍ ማለቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የገቢ ንግድ (ኢምፖርት) መጠን 6.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክተዋል። #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views333−24%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#26046Photo

“ከ15 በላይ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ተገንብተው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው በዚህ ወቅት ቀደም ሲል በመንግስት በኩል ብቻ ተገንብተው የነበሩ ፓርኮች ቁጥራቸው ውስን ከመሆኑም ባለፈ አብዛኞቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሳይገቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። “ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በመንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር ተገንብተው የነበሩት ፓርኮች ባለሀብቶችን በበቂ ሁኔታ ያልሳቡና በአብዛኛው በመንግስት ወጪ ብቻ የተገነቡ ነበር” ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የግሉ ዘርፍ በዘርፉ እንዲሳተፍ በተፈጠረው ዕድል በመንግስትና በግል ባለሀብቶች የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ቁጥር ከ15 በላይ መድረሱን ተናግረዋል። መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥራትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል። በተለይም ወደ ስራ ያልገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በመደረጉ የባለሀብቶች ቁጥር ከነበረበት 36 ወደ 300 በላይ ማደጉን ተናግረዋል። በግል ባለሀብቶች የተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በዝቅተኛ ወጪና በተሻለ ቅልጥፍና እየተገነቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል። በደረጀ መንግስቱ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views350−21%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
#26045Text

የአካባቢ ምርጫ እንዲደረግ እና የሕዝብ ቆጠራ በመንግስት አቅጣጫ እንዲካተት የሚጠይቅን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎች ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ቀረቡ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) በ7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተገኙ የምክር ቤቱ አባላት ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአካባቢ ምርጫን ፣ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን እንዲሁም የውጭ ገጽታ ግንባታና ዲፕሎማሲን የተመለከቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የብሔረሰብ ዞን ፣ የዞን ፣ የወረዳ ፣ የከተማ ፣ የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ በሕግ በተወሰነው ጊዜ መካሄድ እንዳለበት ተጠቅሷል። ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 13 እስከ 14 ዓመታት የአካባቢ ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱን ያነሱት አባላቱ ምርጫው የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ በመንግስት አቅጣጫ እንዲካተት ፣ ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆንና አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ አሳስበዋል። በተጨማሪም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለሀገሪቱ የልማት ዕቅዶች ፣ ለበጀት ድልድል እና ለምርጫ ክልሎች አከላለል ወሳኝ መሠረት መሆኑን አባላቱ አጽንኦት ሰጥተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በየ10 ዓመቱ የሚከናወነውን ቆጠራ መነሻ በማድረግ የበጀት ቀመር እንደሚያዘጋጅ የጠቆሙት አባላቱ የሕዝብ ቁጥር በውል ባልታወቀበት የሚደረግ ድልድልና ዕቅድ ግምታዊነትን በመፍጠር ፍትሐዊነትን እንደሚያጓድልና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን እንደሚያቀጭጭ ገልጸዋል። በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ ገበያ ማሻሻያውን ተከትሎ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ፣ የመድኃኒት እና የትራንስፖርት ዋጋ መናሩን በመግለጽ የህዝቡን የመግዛት አቅም ለመደገፍ እና ገበያውን ለማረጋጋት መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲብራሩ ጠይቀዋል። በማሻሻያው ሰበብ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ፣ ምርት የሚደብቁ እና ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር መንግስት የያዘው የህግ ማስከበር አሰራር ላይ ጥያቄ ቀርቧል። ከዚህ ባለፈም የታክስ አስተዳደር ማሻሻያ አዋጅን ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር ፣ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ አሰራርን በማስፋፋት እና በታክስ አሰባሰብ ላይ ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ መንግስት የያዘው ተጨባጭ የአፈጻጸም እቅድ እንዲብራራ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ቀርቧል። በደረጀ መንግስቱ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views418−5%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
#26043Text

በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት ባሉ ታዳጊና ወጣት ሴቶች ላይ አዲስ በኤችአይቪ የመያዝ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ጥናት አመላከተ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ኤድስ ሄልዝኬር ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ. በ2025 ባካሄደው ሀገራዊ ጥናት በኢትዮጵያ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር 660 ሺህ ገደማ መሆኑን ገልጿል። በ5ኛውን የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባኤ ላይ የኤች አይቪ ስርጭት እንደ ሀገር ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ በጥናት አስደግፈው የተናገሩት የኤድስ ሄልዝኬር ፋውንዴሽን ተቋም የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ቶለሳ ኦላና ናቸው ፡፡ ስራ አስኪያጁ፡ እንደ ሀገር በበሽታው ከተጠቁ በኋላ ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ ሰዎች 80 በመቶ ያህሉ ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 20 በመቶ የሚሆኑት ገና ያልተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በየዓመቱ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቶለሳ፣ በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ታዳጊና ወጣት ሴቶች ላይ አዲስ በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት መካከል በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው ከሚገመቱት ውስጥ ተመርምረው የተለዩትና ሕክምና ላይ የሚገኙት 40 በመቶ አካባቢ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በተለይም በታዳጊና ወጣት ሴቶች እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ዘንድ አዲስ የመያዝ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት ከሆኑት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መስፋፋት፣ በወጣቶች ዘንድ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤና የምርመራ ባህል ዝቅተኛ መሆን ይጠቀሳል ፡፡ በተጨማሪም ለኤችአይቪ መከላከል የሚሰጠው ትኩረትና የድጋፍ መዋቅር መቀዛቀዝ፣ የአልኮልና አደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነት መጨመር እና ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነትና መሰል ችግሮች መሆናቸው ጠቁመዋል ። ይህንን የበሽታ ስርጭት ለመከላከል ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ የህብረተሰብ የጤና ጉባኤ ያሉ ጉባኤዎችን ማዘጋጀት መቻሏ ትልቅ እድል እንዳለውም ተናግረዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ በ2025 ባወጡት ሪፖርት በሀገሪቱ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 595 ሺህ 447 ገደማ መሆኑን ያሳያል። በዚህ ሪፖርት መሰረት በዓመት የሚከሰት አዲስ የመያዝ መጠን 7 ሺህ 545 ሲሆን፣ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በዓመት 9 ሺህ 560 አካባቢ መሆኑን የተቋማቱ መረጃዎች ያመላክታሉ። በደረጀ መንግስቱ #አሐዱ_ሬዲዮ_94.3 #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ

Open in Telegram
Views573+30%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—