Posts of Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ኤርትራን እስከመቼ እንታገሳለን? በፓርላማው የቀረበውን ጥያቄ በዚህ ይከታተሉት፡-https://youtu.be/zGODyxjJX5Q?si=iYfCo9ruwu_8Sxwz
Open in Telegramሱዳን የኢትዮጵያን የሰላም ውይይት ጥሪ ውድቅ ባደረገች በሰዓታት ልዩነት ጌታቸው ረዳ ምላሽ ሰጡ ሐሙስ ፣ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) በጄኔራል አብዱልፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በአዲስ አበባ የሱዳን የሰላም ውይይት ለማስተናገድ ያቀረቡትን ጥሪ እንደማይቀበል በይፋ ካስታወቁ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ አማካሪያቸው ጌታቸው ረዳ ምላሽ ሰጡ፡፡ ጌታቸው በማሃብራዊ መገናኛ ዘዴዎቻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዳመላከቱት፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም ያቀረበችው የውይይት ጥሪ የቀጣናውን ተዋንያን ለማቀራረብና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እና የገልተኝነት ጥርጣሬን ለማጥፋት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሱዳን ሰላም ዙሪያ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ውይይት እንዲካሄድ ያቀረቡት ጥሪ የሱዳንን የፖለቲካ ኃይሎች የመጠቅለል ወይም የተሻለ መድረክ የመምረጥ ዓላማ የሌለው ሲሉ ጽፈዋል። ጌታቸው ጥሪው በሁለቱም የቀይ ባሕር ዳርቻዎች የሚገኙ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ሀገራትና ቀጣናዊ ተቋማት ይህንን እርምጃ ተቀብለው በሱዳን ያለውን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማስቆም በጋራ እንዲሠሩ ያለመ ነው ብለዋል። አክለውም በሱዳን ቀውስ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከተሳተፉ የቀጣናው ተዋንያን ይልቅ በይበልጥ የምትጎዳው፣ በተቃራኒው ደግሞ ከሀገሪቱ ሰላም የበለጠ ተጠቃሚ የምትሆነው ኢትዮጵያ መሆኗንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ይህንን እርምጃ በመውሰድ ለሂደቱም ሆነ ለውጤቱ ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን እያሳየች መሆኑን የገለጹት ጌታቸው፣ ይህም ስለ ገለልተኝነቷ የሚነሱ ጥርጣሬዎችን ለማጥፋትና ለውይይቱ ውጤት “ሙሉ እምነትና ዕውቅና”ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያረጋግጥ አብራርተዋል። ይሁን እንጂ ካርቱም የአዲስ አበባውን መድረክ የማትቀበልበት ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ ገለልተኝነቷን አጥታለች እና የሱዳንን ሉዓላዊነት አላከበረችም በሚል ነው። የሰላም ውይይት የሚያስተናግድ ሀገር ፍጹም ገለልተኛ መሆን እንዳለበት የጠቀሰው የሱዳን መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ለፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል፣ በተለይም በብሉ ናይል በኩል ወታደራዊ ድጋፍና የስልጠና ካምፕ ትሰጣለች በሚል በመወንጀል ለአደራዳሪነት ብቁ አይደለችም ብሏል። ከዚህም ባለፈ ከኢትዮጵያ ግዛት የሚነሱ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (ድሮኖች) በሱዳን መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ተፈቅዶላቸዋል ሲል የወነጀለ ሲሆን፣ ይህም የሱዳንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ በመሆኑ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቋል። በመሆኑም የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያን ከማንኛውም የሱዳን የሰላም ውይይት አመቻችነት እንዲያገሏትና የውይይቱ ቦታና አጀንዳ በሱዳናውያን ስምምነት ብቻ እንዲወሰን ካርቱም አሳስባለች። ጌታቸው ግን ይህን ውገዘት ቃል በቃል ባይጠቅሱትም፣ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃንን ጨምሮ በቀጣናው ለሱዳን ሰላም በቅንነት የሚያስቡ ሁሉ ይህንን ተነሳሽነት በበጎ ፈቃድ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል። የሱዳን ሕዝብም በዓለም ላይ ያለው ሰላም ሁሉ እንደሚገባው በመልእክታቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramበሙስና እና በተለያዩ ጉዳዮች “በህግ ጥላ ስር” ያሉ የመንግስት አመራሮች ላይ ክስ ለመመሥረት የመረጃ እና ማስረጃ የማጠናቀር ስራ እየሰራ መሆኑን ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ ረቡዕ ፣ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) በሙስና እና በተለያዩ ጉዳዮች “በህግ ጥላ ስር” ያሉ የመንግስት አመራሮች ላይ ክስ ለመመሥረት የመረጃ እና ማስረጃ ማጠናቀር ስራ እየተሰራ መሆኑን የፌደራል ሥነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡በህግ ማስከበር ውስጥ ማንኛውም አካል አሳማኝ መረጃ እስከተገኘበት ድረስ ከህግ ውጭ መሆን አይችልም ተብሏል። በመስከረም ወር መጨረሻው ሳምንት ላይ አዲስ መንግስት ሲመሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር በርካታ አመራሮች ከስልጣናቸው ከተነሱባቸው ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ሙስና እና ሀብት ማካበት መሆኑን፣ ለአንድ ዓመት ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበረ ገልጸው ነበር። በመሆኑም ጉዳዩን በተመለከተ አዲስ ማለዳ የፌደራል ሥነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽንን በክትትሉ ሂደት ውስጥ መሳተፉን እንዲሁም ጉዳዩን በዝርዝር ጠይቃለች፡፡ ጥያቄው የቀረበለት ኮሚሽኑ፣ በግልጽ አዲሱ ካቢኔ ሲዋቀር ከስልጣን የተነሱ አመራርን ባያነሳም በተጠርጣሪነት የተያዙ አመራርን በተመለከተ የህግ ማስከበር እና የሀብት ማጣራት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተጠቁሟል። በፌደራል ሥነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና ወንጀሎች ቅበላ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ “በህግ ጥላ ስር” ሆነው የሚካሄዱ ምርመራዎች እንዲሁም ክሶችን ለመመሥረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፤ ከዚህ ቀደም በትላልቅ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንደ ጉምሩክ፣ ገቢዎች፣ በተወሰነ ደረጃ ከማዕድን፣ ከማዳበሪያ እና ከነዳጅ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተጠረጠሩ አካላት በህግ ጥላ ስር ሆነው የምርመራ እና የክስ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በዛሬው ዕለት 23ኛውን ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ከህዳር 1 እስከ 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ “ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ” በሚሉ መሪ ቃላት እየተከበረ መሆኑንም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። እሰካሁን በህግ ጥላ ስር ካሉት መካከል ለአብነት ገቢዎች እና ጉምሩክ “የፖለቲካ ተሿሚዎች” ናቸው የሚሉት መስፍን “መረጃ እና ማስረጃ ካለ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም የህግ ማስከበሩ ስራ ያለ ርህራሄ የሚካሄድ ይመስለኛል” ብለዋል። መስፍን ምክንያቱን ሲያነሱም የህዝብ ጉዳይ ስለሆነ ነው ብለዋል። “ምክንያቱም የህዝብ ጉዳይ ስለሆነ፣ ምክንያቱም ተቋምን ስለሚያናጋ እና የመረጃና ማስረጃውም በግድ በተገቢው ምርመራ እና የህግ ክስ እና ክርክር ሥርዓት ተደግፎ መሄድ ስላለበት” ነው ያሉ ሲሆን፣ “አመራሮች ይጠየቃሉ፤ ምንም የሚያከራክር ነገር የለም” በማለት መረጃ እና ማስረጃ እስከተደኘ ድረስ “የሚቀር አካል የለም” ብለዋል። ለአብነትም የስራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጉዳይ አንስተዋል። የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ባለሙያዎች እና አመራሮች ከዚህ ቀደም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሥርዓትን በማጭበርበር፣ በጉቦና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የኤጀንሲዎችን እገዳ እንዲነሳ ማድረገን ጨምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ከእነ“ግብረ አበሮቻቸው” በቁጥጥር ስር መዋላቸው ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል። ዳይሬክተሩ አክለውም በህግ ጥላ ስር ያሉት ተጠርጣሪዎች መረጃ እንዳያጠፉ እና ከሀገር እንዳይወጡ ጥንቃቄ የሚደረግ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት እስኪወስን ድረስ እንደ ወንጀለኛ እንደማይቆጠሩ እና ነጻ ሆኖ የመታየት መብት እንዳላቸው ተናግረዋል። መስፍን የህግ ማስከበር ስራው “መረጃ እና ማስረጃ” እስከተገኘ ድረስ “ይህኛው እና ያኛው አመራር” ሳይባል ያለ አድልዎ እንደሚካሄድ፣ የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ ማስረጃ የተገኘባቸው አካላት በህግ እንደሚጠየቁ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን የተነሱት ባለስልጣናት በሙስና እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ጭምር በመካበት ነው ቢሉም እነማን እንደሆኑ ስም አልጠቀሱም ነበር፡፡ በመሆኑም አብዘኞቹ በሚባል ደረጃ ሌላ ሹመት ተሰጥቷቸዋል። ይህንንም ለመስፍን ቢነሳላቸውም ጠቅላዩም ስም እንዳላነሱ አስታውሰዋል። ከመስፍን ገለፃ መረዳት እንደሚቻለው ከሆነ፤ ማናቸውም ከስልጣን ቢነሳ ወይም ሌላ ሹመት ቢሰጣቸውም፣ በሙስና ከተጠሩጠሩ ወይም በምርመራ የተረጋገጠ መረጃ እና ማስረጃ የሚገኝ ከሆነ ከጠያቂነት ማምለጥ እንደማይችሉ ነው። በሌላ በኩል ያልተገባ ሀብት ከማካበት አኳያ በሙስናም ይሁን መስና ወለድ ትስስር ማፍራት ላይ ችግሩ አሁንም እንዳለ አንስተው ከ2017 በፊት ያልተገባ ሀብትን ለማስመለስ በህግ ማዕቀፍ የተሟላ አሰራር ባይኖርም፣ ከ2017 በኋላ በወጣው የሀብት ማስመለስ አዋጅ መሰረት ምዝገባ እየተካሄደ ነው ብለዋል። በዘንድሮው ዓመትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር፣ አፈ ጉባኤዎች፣ ሦስቱን የህግ አስፈጻሚ አካላት ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሀብታቸውን ማስመዝገባቸው ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በሀገር ደረጃ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሀብት አስመዝጋቢዎች ሀብታቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት ላይ የማጣራት ስራ እንደተካሄደ አንስተዋል። አክለውም ቀደም ሲል አመራሮች ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ይካሄድ የነበረው የሀብት ማጣራት ስራ አሁን በስራ ላይ እያሉ በአዋጁ መሰረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። በዚህም የሀብት የማጣራት ስራ ውጤቶች በሁለት ተከፍለው ይታያሉ የሚሉት መስፍን ጥቃቅን ስህተቶች በደብዳቤ ማስጠንቀቂያ የሚስተካከሉበት አሰራር ያለ ሲሆን፣ ምንጩ ያልታወቀ አጠራጣሪ ሀብት ሲገኝ ደግሞ ቀጥታ ለፖሊስ ተልኮ በአቃቤ ህግ እና በፍርድ ቤት አማካኝነት የህግ ማስከበር እና ሀብት የማስመለስ እርምጃ ይወሰዳል። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramበኢትዮጵያ በብዛት ሙስና ይፈጽምባቸዋል የተባሉ መንግስታዊ ተቋማት ይፋ ተደረጉ፤ ኢሚግሬሽንና ጉምሩክም እዚህ ዝርዝር ውስጥ ይገኙበታል ረቡዕ ፣ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) በኢትዮጵያ ወሳኝ ኩነት፣ ኢሚግሬሽን፣ የማዕድን ዘርፍ፣ ሪል ስቴት እና ኮንስትራክሽን፣ ማዕድን ፈቃድ እና መሬት አሰጣጥ ዘርፍ፣ የፍተሻ ኬላዎች፣ ጉምሩክ እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያ እና ፍርድቤት ሙስና በብዛት የሚፈፅማባቸው ተቋማት መሆናቸው ተገለጸ በኢትዮጵያ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ ተቋማት ያሉት፤ ወሳኝ ኩነት፣ ኢሚግሬሽን፣ የማዕድን ዘርፍ፣ ሪል ስቴት እና ኮንስትራክሽን፣ ማዕድን ፈቃድ እና መሬት አሰጣጥ ዘርፍ፣ የፍተሻ ኬላዎች፣ ጉምሩክ፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ፍርድ ቤቶች አካባቢ እንዲሁም ሌሎችም ቦታዎች ሙስና በብዛት የሚፈጽማባቸው ተቋማት መሆናቸውን የፌደራል ሥነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ መረጃን ማጥፋት፣ መዝገብ መሰወር፣ ምስክርን ማስፈራራት፣ ያለበቂ ዋስትና ከእስር መልቀቅ እና ሌሎችንም ጨምሮ እንደሚከሰት ተገልጿል። ይህ የተነገረው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የጸረ ሙስና ስምምነት አባል ሀገር እንደመሆኗ 23ኛውን ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ከህዳር 1 እስከ 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ “ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ” በሚሉ መሪ ቃላት እየተከበረ መሆኑን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው። የሙስና ትስስር ውስጥ ያሉ እና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስባቸው ዋና ዋና ዘርፎችና ተቋማትን እነዚህ ናቸው ያለው የፌደራል የሥነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሙስና ከሌሎች ወንጀሎች ጋር በጥብቅ ተሳስሮ ጉዳት እንደሚያደርሱም አስታውቋል። ከዚህ ውጥም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ንግድን በተመለከተ ከቀበሌ ጀምሮ የወሳኝ ኩነት፣ የኢሚግሬሽን፣ የድንበር አካባቢ ህግ አስከባሪዎች፣ የትራፊክ ፖሊስ፣ የፖሊስ ጣቢያ፣ የህግና የፍርድ ቤት መዋቅሮች ድረስ የዘለቀ መሆኑን ገልጿል። ከቀበሌ አንስቶ በወሳኝ ኩነትና በኢሚግሬሽን መዋቅሮች ባሉ አንዳንድ ሙሰኞች አማካይነት እድሜያቸው ላልሞላ ታዳጊዎች ሀሰተኛ የልደት ምስክር ወረቀት፣ መታወቂያና ፓስፖርት በጉቦ ማዘጋጀት፤ በድንበር አካባቢ ባሉ አንዳንድ የህግ አስከባሪዎችና የትራፊክ ፖሊሶች በሚወሰድ ጉቦ ምክንያት ደላሎች ህገወጥ ተጓዦችን በነፃነት ማሻገር፤ እንዲሁም አዘዋዋሪዎች ሲያዙ በፖሊስ ጣቢያ፣ በህግና በፍርድ ቤት መዋቅሮች በሚፈጸም ሙስና መዝገብ ማጥፋት፣ ምስክር ማስፈራራትና ያለ በቂ ዋስትና ማስፈታት ዋናኛው ነው ብሏል። ይህም ዜጎች በበረሃና በባህር ለሞት፣ ለፆታዊ ጥቃት፣ ለግዳጅ ስራና ለሰውነት ክፍሎች ንግድ ይዳረጋሉ፤ ድንበሮች ለአሸባሪዎችና ለጦር መሳሪያ ዝውውር ክፍት እንዲሆኑ እንደሚያደርግ አመልክቷል፡፡ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርም አንዱ የሙስና ምንጭ ነው የተባለ ሲሆን የጉምሩክ፣ የታክስ፣ የባንክ ሴክተር፣ የሪል ስቴት እና የኮንስትራክሽን ተቋማትም በከፍተኛ ሁኔታ ይፈጸምባቸዋል ሲል ገልጿል። በዚህም ምክንያት የንግድ ሰነድ ማጭበርበር ላይ አስመጪዎች የእቃ ዋጋ አጋንነው በመመዝገብ፣ ላኪዎች ደግሞ ዋጋውን አሳንሰው በማሳየት ከጉምሩክና ታክስ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር የውጭ ምንዛሪን በውጭ ባንኮች እንደሚያስቀሩ ተጠቅሷል። እንዲሁም የጥቁር ገበያና የባንክ ተጋላጭነት በተመለከተ ገንዘብ አስተላላፊዎች በባንክ ሴክተር ውስጥ ባሉ አንዳንድ “ሙሰኛ” ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር የውጭ ምንዛሪ ድልድልን ማዛባትና ህገወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስለው ያቀርባሉ ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ የመጣው የሪል እስቴት ዘርፍ እና በኮንስትራክሽን ዘርፍ በወንጀል የተገኘ ገንዘብን በከተሞች መሬትንና ህንፃዎችን በተጋነነ ዋጋ በመግዛት ወደ ህጋዊ ኢኮኖሚ መቀላቀል ይገኙበታ ተብሏል። ይህም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከሀገር እንዲወጣ በማድረግ ለመድኃኒትና ለነዳጅ የሚውል ምንዛሪ ማሳጣት እንዲሁም የኑሮ ውድነትንና የቤት ዋጋ ንረትን እያባባሰ ነው ብሏል። በህገወጥ የማዕድናትና የተፈጥሮ ሀብት ዝውውር ላይ የፈቃድና የመሬት አሰጣጥ መዋቅሮችም ለሙስና ተገላጭ ናቸው። የማዕድን ማውጫን ያለበቂ ጥናት ለሽፋን ድርጅቶች ፍቃድ መስጠት፣ የመሬት ወረራና የአካባቢ ብክለትን አይተው እንዳላዩ ማለፍ በበርካታ ቦታ የሚከወን ተግባር ነው ተብሏል። እንዲሁም የማዕድን ኮንትሮባንድ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች ወደ ብሔራዊ ባንክ ከመግባት ይልቅ በፍተሻ ጣቢያዎች በሚፈጸም ሙስና ወደ ጎረቤት ሀገራት የማሸሽ ስራ ይሰራል ተብሏል። የጉምሩክ፣ የድንበር ጥበቃ፣ የትራፊክ አባላት፣ የፍትህ መዋቅሮች እና በሞጆ ደረቅ ወደብ፣ ቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ መተማ፣ ጅግጅጋና ጋላፊ ያሉ የኮሪደርና የፍተሻ ጣቢያዎች ለኮንትሮባንድ እና ሙስና ተጋላጭ ናቸው ተብሏል። በዚህም ከታክስ ስወራ እሰከ ሀብት ማሸሽ ይሰራበታል የተባለ ሲሆን የመንግስት የልማት በጀት በማዳከም ህጋዊ ነጋዴዎችና የሀገር ውስጥ አምራቾች ከገበያ ውጪ በማድረግ የህዝብን ሰላምና ብሔራዊ ደኀንነትን ያውካል ተብሏል። በተጨማሪም የታጠቁ ወንጀለኞች እንዲበራከቱ በማድረግ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሸሽ እና የልማት በጀትም ወደ ፀጥታ ማስከበር እንዲዛወር ያደርጋል ሲል አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም አገልግሎት ፈላጊው ማለትም ጉዳይን በሙስና ለማስፈጽም የሚፈልጉት መብታቸው በህገውጥ መንገድ በገንዘባቸው እየገዙት እንደሆነ መረዳት አለባቸው ሲል ተቋሙ አስታውቋል። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramበትግራይ ክልል ነዳጅ በመቀሌ ከተማ ለሚንቀሳቀሱ ታክሲዎች መቅረብ መጀመሩን የክልሉ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ ረቡዕ ፣ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ለሚንቀሳቀሱ ታክሲዎች ከትናንት ጀምሮ ነዳጅ መቅረብ መጀመሩን በክልሉ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ዉስጥ የንግድ ሥርዓት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጎዑሽ ወልደገሪማ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል ለመንግስት መስሪያ ቤቶችና ለግል ተቋማት በኮታ ሲሰጥ የነበረዉ ነዳጅ አሁን ላይ ለከተማ ታኪሲዎች እንዲያገኙ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ነዳጅ የገባው በመቀሌ ከተማ ብቻ እንደሆነም አንስተዋል የትግራይ ባለ አደራ መንግስት መቋቋሙን ተከትሎ በክልሉ ያለዉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዉ እንዲነቃቃ እና መሰረታዊ ፍጆታዎች እንዲገቡ በተደረገዉ ጥረት ነዳጅ በክልሉ ባሉ ትላልቅ ከተሞች እንዲገባ መፈቀዱን አስታውሰዋል። በመሆኑም አሁን ላይ በመቀሌ በሥራ ላይ ካሉ 15 የነዳጅ ማደያዎች በዘጠኙ ነዳጅ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ነዳጅ በመቀሌ ብቻ መግባቱን የገለጹት ሀላፊው በቀጣይ ወደ ሌሎች ከተሞች እንደሚዳረስና ነዳጅ አሁንም ድረስ በጅቡቲ በኩል እየገባ መሆኑንና ከተሞቹ ነዳጅ በጠየቁበት ቅደም ተከተል ተደራሽ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡ “በትግራይ ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ናፍጣና ስድስት ቦቴ ነዳጅ” ወደ መቀሌ መግባቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ዋጋዉ የፌደራል መንግስት ባወጣዉ የዋጋ ታሪፍ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡ ሌላዉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የመቀሌ ነዋሪ እንደገለጹት ትናንት በከተማዉ ያለዉ የመኪና እንቅስቃሴ የተሻለ መሆኑን ገለጸዉ በከተማዉ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ቢበዙም በነዳጅ የሚሰሩ ታክሲዎችም በስፋት መመልከታችዉነ ገለጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የታኪሲ የዋጋ ታሪፍን በሚመለከት የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ይፋ ያደረገዉና በዛሬው ዕለት በመቀሌ ከተማ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለ ታሪፍ ይፋ ተደርጓል። በመሆኑም ዝቀተኛዉ እስከ 2.5 ኪ.ሜ፡ 15 ብር (14.70 ብር) እንዲሁም ከፍተኛዉ ከ20.1 – 22.5 ኪ.ሜ፡ 65 ብር (66.15 ብር) መሆኑን አዲስ ማለዳ መመለከት ችላለች፡፡ በክልሉ ፍትህዊ በሆነ መንገድ ነዳጅን ለማዳረስ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘረጋቱን የጠቆሙት ጎዑሽ የነዳጅ ሸያጭ በዲጂታል የክፍያ መንገድ ብቻ እንዲፈጸም መደረጉን አንስተዋል። በዚህም መሰረት ነዳጅ ከተፈቀደ መያዣ በስተቀር በጀሪካንና በሌላ ዕቃ እንዳይቀዳ መመሪያ መውረዱንና ማደያዎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የልኬት ምርመራ እንደተደረገ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ ተስፋፋቶ የነበረዉን የነዳጅ ጥቁር ገበያ ሸያጭ ለመቆጣጠር ምን እየተሰራ ነዉ ስትል አዲስ ማለዳ ላቀረበችዉ ጥያቄ ነዳጅ አቀርቦት ሲሻሻል የጥቁር ገበያ ንግዱም እየከሰመ እንደሚሄድ አንሰተዉ በመንግስት ደረጃም የቁጥጥር ሥራ መጀምሩን ተናግረዋል፡፡ ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramብሔራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን ሙሉ በሙሉ እንዲገዙ የሚፈቅድ ረቂቅ መመሪያ፣ ነባር ባንኮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተናገሩ ረቡዕ ፣ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ነባር ባንኮችን ድርሻ ሙሉ በሙሉ (መቶ በመቶ) እንዲገዙ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ባለፈው ሳምንት ማውጣቱን አስታውቋል። ይህ ረቂቅ መመሪያ በሥራ ላይ ባለው የባንክ ሥራ አዋጅ ላይ የተቀመጠውንና የውጭ ባለሀብቶች በአጠቃላይ እስከ 49 በመቶ ድርሻ ብቻ እንዲይዙ የሚገድበውን ጣሪያ በልዩ ሁኔታ የሚያልፍ ነው። በረቂቅ መመሪያው መሠረት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ባንክን ሙሉ በሙሉ ለመግዛት የሚፈልግ አንድ የውጭ ባንክ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሀብት ያለው፣ የ10 ዓመት የባንክ ሥራ ልምድ ያካበተ እና ከሀገሩ ውጪ ቢያንስ በሦስት ሀገራት የሚሠራ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል። ረቂቅ መመሪያው ሲፀድቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ባንኮችና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ምን ጥቅም ያስገኛል ስትል አዲስ ማለዳ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግራለች። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ መሐመድ ጋዳፊ፣ ረቂቁ ተግባራዊ ሲደረግ በተለይ ኪሳራ ውስጥ ላሉ ባንኮችና ለባለአክሲዮኖቻቸው በውህደት አልያም በሽያጭ ገንዘባቸውን የሚያገኙበት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። እንዲሁም የገንዘብ ፍሰትን እንደሚያጠናክርና የውጭ ባንኮች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ማበረታቻ እንደሚሆን ተናግረዋል። ሆኖም መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን ጥቅሙ ትልቅ ቢሆንም፣ ሊያመጣ የሚችለውን ተፅዕኖ አሁን ላይ በግልጽ ማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑንና በሂደት የሚታይ እንደሆነ አክለዋል። ሌላው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ነገሠ በበኩላቸው፣ ባለፈው ሳምንት የወጣው ረቂቅ መመሪያ ባለፈው ዓመት ከወጣው በተሻሻለና ለየት ባለ መንገድ የውጭ ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን መቶ በመቶ በልዩ ኢንቨስትመንት እንዲገዙ የሚፈቅድ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ችግር ውስጥ ያሉ ባንኮች አቅም ላላቸው የውጭ ባንኮች ተሸጠው ገንዘባቸውን የሚመልሱበትን መንገድ ይፈጥራል ብለዋል። ረቂቅ መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ችግር ውስጥ ያሉ ባንኮች ሸጠው መውጣት ቢፈልጉ ዕድሉን ከማመቻቸቱም ባለፈ የውጭ ባንኮች ግዢውን የሚፈጽሙት በዶላር በመሆኑ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም ለሕዝቡ ተጨማሪ አማራጮችንና የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ ቴክኖሎጂዎችን በማቀላጠፍ፣ እንዲሁም ከባንኮቹ ጋር ትስስር ያላቸው ባለሀብቶችና ድርጅቶች ተበድረው እንዲሠሩ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። በሌላ በኩል አቅም ያላቸው የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በውድድር፣ በቴክኖሎጂና በካፒታል የተሻሉ ስለሚሆኑ ለሀገር ውስጥ ባንኮች ጠንካራ የገበያ ተቀናቃኝ ይሆናሉ ብለዋል። ስለሆነም የሀገር ውስጥ ባንክ አመራሮች “የውጭ ባንኮች ስለገቡ ብቻ እንጎዳለን” በሚል ዕይታ ሳይታጠሩ፣ አስቀድመው ራሳቸውን የሚያዘጋጁባቸውን አማራጭ መንገዶች ካልተጠቀሙ ሊጎዱ እንደሚችሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramበጎጃም እና በጎንደር ሕዝብ ላይ በጅምላ የስም ማጥፋትና የጥላቻ ንግግር ወንጀል ተፈጽሟል በሚል በአቶ ኢዩ ጩፋ ላይ ለፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ጥቆማ ቀረበ ረቡዕ ፣ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) በአማራ ክልል በሚገኘው የጎጃምና የጎንደር አካባቢ ሕዝብ ላይ በኃይማኖት ስብከት ሽፋን በጅምላ የስም ማጥፋትና የጥላቻ ንግግር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በአቶ ኢዩ ጩፋ ላይ ለኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ይፋዊ የወንጀል ጥቆማ መቅረቡ ታወቀ። የወንጀል ጥቆማውን ትናንት ህዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያቀረቡት ጠበቃ እና የህግ አማካሪ ሰለሞን ገዛኸኝ ናቸው። አዲስ ማለዳ በተመለከተችው ደብዳቤ ላይ ጠበቃው እንደገለጹት፣ በኢፌዴሪ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 11 መሠረት ማንኛውም ሰው ወንጀል መፈጸሙን ሲያውቅ ለፖሊስ የማሳወቅ መብትና ግዴታ ስላለው፣ እንዲሁም ራሳቸው በአካባቢው በሚኖሩ ተወላጅ ዘመድ አዝማዶቻቸው አማካይነት ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው በመሆኑ ይህንን ጥቆማ አቅርበዋል። በጥቆማ ደብዳቤው ላይ እንደተመለከተው፣ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) አካባቢ በሚኖረው ሕዝብ ላይ አንድ ግለሰብ በኃይማኖት ስብከት ሰበብ “ጠንቋይ” በማለት ስም በማጥፋቱ እና በማዋረዱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበት በሕዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና በኋላም በሽምግልና መታለፉን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ግለሰቦች ከዚህ ድርጊት መማር ሲገባቸው፣ በተመሳሳይ መልኩ የሌላ አካባቢን ሕዝብ በመጥቀስ የመሳደብና የማንቋሸሽ ተግባር መፈጸማቸውን ቀጥለዋል ብለዋል - ጠበቃው። ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ በዝርዝር ባቀረቡት የወንጀል ጥቆማ ላይ ተጠሪው አቶ ኢዩ ጩፋ ሁለት ከባድ የወንጀል ድርጊቶችን መፈጸማቸውን አመልክተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ተጠሪው በህዳር ወር 2019 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ በኃይማኖት ስብከት ሰበብ የምዕራብ ጎጃም፣ የምሥራቅ ጎጃም፣ የሰሜን ጎጃምና የአዊ አካባቢ ሕዝብን በጅምላ በመጠቅለል “መተተኞች ናቸው” በማለት መናገራቸውን ጠቅሰዋል። ይህ ንግግራቸውም በቪዲዮ ተቀርጾ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም በስፋት ተሰራጭቷል። የጎጃም አካባቢ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን ሀብት በማፍራት የሀገሪቱ የሀብት ምንጭ ሆኖ የቆየ፣ አርሶ፣ አምርቶና አስተምሮ በላቡና በልፋቱ ሀብት፣ ዕውቀት፣ ዝና፣ ልዕልና፣ ቸርነትና ደግነት ያተረፈ ሕዝብ መሆኑ በጥቆማው ተገልጿል። ተጠሪው ይህንን ሁሉ የሕዝቡን የሥራ ትጋት፣ ባህል፣ ሀገር ወዳድነትና ጥበብ በመካድ ሕዝቡ ሀብትና ዕውቀት ያገኘው በአስማት፣ በጥንቆላና በመተት እንደሆነ አድርገው ማቅረባቸው የሕዝቡን መላ እሴት እጅግ ዝቅ ያደረገ መሆኑን ጠበቃው አስረድተዋል። ድርጊቱም በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጪ በመላው ሀገሪቱ የሚኖሩ የጎጃም ተወላጅ አርሶ አደሮችን፣ ነጋዴዎችን፣ ምሁራንን፣ የኃይማኖት ሰዎችንና ተማሪዎችን በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጥርጣሬ ዓይን እንዲታዩ፣ እንዳይታመኑ የሚያደርግና በገንዘብ የማይተመን ከፍተኛ የሥነ-ልቦናና የማኅበራዊ ሕይወት ጉዳት ያስከተለ አደገኛ ድርጊት መሆኑ በማመልከቻው ተመላክቷል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተጠሪው አቶ ኢዩ ጩፋ በሌላ የኃይማኖት ስብከት መድረክ ላይ የጎንደርን እና የጎጃምን ሕዝብ ዒላማ በማድረግ “የጎጃም የሌ፣ የጎንደር የሌ፤ እዚህ ቤት የገባ ሁሉ ይቀጠቀጣል፣ ይረገጣል፤ የትም ይሥራ እናፈርሰዋለን” በማለት በአደባባይ የጥላቻ፣ የውግዘትና የማስፈራሪያ ንግግር ማድረጋቸውን ጥቆማ አቅራቢው ገልጸዋል። እነዚህ ሁለት ንግግሮች በኢትዮጵያ ሕግ ሦስት ዋና ዋና የወንጀል ድንጋጌዎችን የሚጥሱ መሆናቸውን ጠበቃ ሰለሞን በማመልከቻቸው ዘርዝረዋል። አንደኛው በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 613 (ስም ማጥፋትና ማዋረድ) እንዲሁም አንቀጽ 486 (ሕዝብን ማነሳሳትና የሐሰት ወሬ ማሰራጨት) ሲሆን፣ በሕዝብ መካከል መጠራጠርን፣ ጥላቻን ወይም ግጭትን የሚፈጥር የሐሰት ወሬ ማሰራጨት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑ ተጠቅሷል። ሁለተኛው የጥላቻ ንግግርንና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4፣ 5 እና 7(1) ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በአደባባይ ስብሰባዎች፣ በብሮድካስት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምፅ ወይም በቪዲዮ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት በሕግ የተከለከለ መሆኑንና እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተገልጿል። ሦስተኛው ደግሞ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 13 እና 14 ሲሆን፣ ንግግሩ በኢንተርኔትና በማኅበራዊ ሚዲያዎች (ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዩቱዩብ ወዘተ) አማካኝነት በመሰራጨቱ በኮምፒውተር ሥርዓት የሚፈጸም ስም ማጥፋትና ሕዝብን የሚያነሳሳ ሐሳብ ማሰራጨት ወንጀል መሆኑን ያመለክታል። በመጨረሻም ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ተጠሪው እነዚህን ሁለት ንግግሮች ሲያደርጉ የሚያሳዩ የቪዲዮ ማስረጃዎችን ከጥቆማው ጋር አያይዘው ማቅረባቸውን በመግለጽ፣ የኢፌዴሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ተገቢውን ምርመራ አጣርቶ ተጠሪውን ለፍትሕ እንዲያቀርብና መሰል ወንጀሎች ወደፊት እንዳይደገሙ የፍትሕ አካላት ሕጋዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን አዲስ ማለዳ ከደብዳቤው ለመረዳት ችላለች። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramየእነ ዮሐንስ ቧያለው ጉዳይ ለታኅሣሥ 6 ሲቀጠር በርካታ ተከሳሾች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ወደ ሌላ ቦታ መዛወራቸውን ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ ማክሰኞ፣ ህዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእነ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝር ለማቅረብ ለታኅሣሥ 6 ቀን መቀጠሩን እና ከተከሳሾቹ መካከል ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ከዚህ ቀደም “ቅጣት” ከሚባለው ቦታ የወጡትን መልሰው “ታንከር” ተብሎ ወደሚጠራ ቦታ መወሰዳቸውን ጠበቃቸው ሰለሞን ገዝኸኝ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ። ጠበቃው እንደገለጹት በመዝገቡ ቀደም ብለው ተከስሰው ከነበሩ 16 ተከሳሾች ውስጥ 12ቱ ክስ ተቋርጦ የወጡ ሲሆን፣ አራቱ ተከሳሾች ደግሞ “የቅድመ ሁኔታውን አንፈርምም” በማለት ሳይወጡ ቀርተዋል። ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከ“ቅጣት” ቦታ ወጥተው የነበሩት ዮሐንስ ቧያለው አሁን አብረው ባይመለሱም፣ ቅዳሜ ማታ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሌሎች ተከሳሾች ወደ “ታንከር” ተመልሰው እንዲገቡ መደረጉን ጠበቃው አመልክተዋል። በመሆኑም ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ፣ እስክንድር ሽፈራው፣ ሲሳይ አውግቸው (ዶ/ር)፣ ወንድወሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር) እና መንበረ አለሙ መመለሳቸውንና እሳቸውም ገብተው ለመጠየቅ እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል። የዛሬው ቀጠሮም አንዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደነበር አንስተዋል። በተጨማሪም የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝር ለማቅረብ ችሎቱ ለታኅሣሥ 6 ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝር ያላቀረቡት ተከላከሉ የተባሉበት የብይን ግልባጭ እና የተገለበጠ የምስክሮች ቃል ባለመሰጠቱ መሆኑን ጠቁመዋል። ሪጅስትራር ገልብጦ ስላልጨረሰ ማስረጃውን ማዘጋጀት እንዳልቻሉና በቀጣይ ለማቅረብ እንዲቻል ብይኑና የምስክሮች ቃል እንዲሰጣቸው እንዲሁም ይግባኝ ለማለት የመዝገብ ግልባጭ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን አስረድተዋል። እንዲሁም ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ የተቋረጠው ክስን አስመልክቶ አላግባብ ታስረን ስለቆየን ችሎቱ ጉዳዩን ማየት መቀጠል የለበትም የሚል አቤቱታ ቀርቦ ብይን እየተጠበቀ መሆኑን እና የተወሰኑት ለሕዝብ አይጠቅሙም፣ የተወሰኑት ይጠቅማሉ በማለት የተሰጠውን ፍርድ ቤት ማየት እንደነበረበት ገልጸዋል። በመሆኑም እስራታቸው ሕገ ወጥ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ ሊለቃቸው እንደሚገባ መናገራቸውንና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመጣስ የተፈጸመ የእስር ቦታ ዝውውር እንደተደረገ አንስተው እሳቸው ሊገቡ ሲሉ እንደተከለከሉ አንስተዋል። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegramበራያ አላማጣ ከ1,600 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ሪፖርት በማድረጋቸው የጥቅምት ወር ደመወዝ መከፈሉን የራያ አላማጣ ባለ አደራ አስተዳዴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ ማክሰኞ፣ ህዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ) በራያ አላማጣ ከ1,600 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ሪፖርት በማድረጋቸው የጥቅምት ወር ደመወዝ መከፈሉን የራያ ባለአደራ መንግስት አስተዳደር አስተባባሪ ሞላ ህሉፍ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ። ሞላ ከክልሉ ባለ አደራ አስተዳደር በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የመንግሥት ሠራተኞች ሪፖርት አድርገው ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን አንስተዋል። በዚሁ መሠረት በ2018 ዓ.ም በሥራ ላይ የነበሩ ሠራተኞች መጥተው ሪፖርት ያደረጉ ከ1,600 በላይ ሠራተኞች ደመወዝ እንደተከፈላቸው ጠቁመዋል። ባለ አደራ አስተዳደሩ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የመንግስት ሰራተኞች የሚሰሩበት ተቋም በመሄድ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። ለመንግሥት ሠራተኞቹ የ2019 ዓ.ም የጥቅምት ወር ደመወዝ መከፈሉን የገለጹት ሞላ የተከፈለው የአንድ ወር ማለትም የጥቅምት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት ባሉ ጊዜያት ያልተከፈለ ደመወዝን በተመለከተ “የሁሉም ጥያቄ” መሆኑን ጠቅሰው የፌደራል መንግሥትና የክልል መንግሥት እንዲሁም የአስተዳደሩ አካላት ተነጋግረው በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሠረት የሚፈጸም ይሆናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በፌደራሉ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ የሚሰራው ባለአደራ አስተዳደር ከጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ደመወዝ እንደሚከፈል አስታውቆ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶችና አካባቢዎች ይከፈልበታል ከተባለበት ቀን አንጻር የደመወዝ ክፍያው መዘግየቱ ይታወሳል። ሞላ አሁን ላይ ሠራተኞች ሪፖርት አድርገው የጥቅምት ወር ደመወዝ በመከፈሉ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራን እንዲሁም ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ መግባትና ሥራ መሥራት መጀመራቸውን ገለጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ተቀጥረው በአካባቢው ሲሰሩ የነበሩ ሠራተኞችን በተመለከተ ደግሞ፤ በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ወይም በራያ አላማጣ ተቀጥረው ቆይተው ሪፖርት ላደረጉና ወደ ሥራ ለተመለሱ እየተከፈለ መሆኑን በመግለጽ፣ በአማራ ክልል ተቀጥሮ በአማራ ክልል ያለ ሠራተኛን የሚመለከተው ግን የአማራ ክልል መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ በእነዚህ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ስር ይተዳደሩ በነበረበት ወቅት ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያቸው ሳይቆራረጥ በአማራ ክልል እየተከፈላቸው እንደነበረ አዲስ ማለዳ ምንጮቿን ጠቅሳ መዘገቧ አይዘነጋም፡፡ አስተባባሪው ይህንን ጨምሮ ያልተከፈለ ደመወዝ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ክልል መንግስትን ተጨማሪ ውይይቶች እና አቅጣጫን የሚጠይቅ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ የፌደራል መንግስቱ በወቅቱ የደመወዝ ክፍያ ቢያስገባም አስተዳደሩ ለመክፈል ዘግይቷል ማለታቸው ይታወሳል። ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦ YouTube ➲ t.ly/vSgS Telegram ➲ t.ly/SOXU Facebook ➲ t.ly/flx8 Twitter ➲t.ly/mxA
Open in Telegram