Посты канала Zelalem Mengistu
የዚህን ሰው አንዱን የአምልኮ ወይም የቴሌቪዥን ስርጭቱን (አሁን የከሰረ ነጋዴ ከሆነ በኋላ ብሶበታል፤ ግን የቀድሞውንም ቢሆን) ብታዩት፥ የሚስቡ ልብሶች ለብሶ ስብከት ሲቀነስ ክርስቶስ፥ ዲስኩር ሲቀነስ መስቀል ደስኳሪና ሰባኪ ነው። ይህ አንድ ምሳሌ ነው። ወደ አገራችን ሐሰተኛ ነቢያት እና ሐሰተኛ ሐዋርያት ስንመጣም፥ ሁሉም ክርስቶስንና መስቀሉን ወይም ደሙን አይሰብኩትም። የማይሰብኩት ስለሚኮንናቸው ነው። እርሱን ሰብከው መቅጠፍና መዋሸት አይችሉም፤ ገንዘብ መዝረፍና መበዝበዝ አይችሉም። ክርስቶስን ሰብከው ራሳቸውን ማሳየት አይችሉም። ከሁሉም በላይ ክርስቶስን የማይሰብኩት ክርስቶስን ስለማያውቁት ነው። ድነትን አያውቋትም፤ የደሙን የማዳን ሥራ አያውቁትም፤ የማያውቁትን እንዲሰብኩ መጠበቅም የለብንም። ሐሰተኛ ነቢይ ኢዩ ጩፋ ሃቻምና በዲላ ያደረገው ዘረፋ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነበር። በጆንያዎችና ከረጢቶች የታጨቁት ብሮች ባንክ እንዲገቡ የባንክ ሠራተኞች ትርፍ ሰዓት እና ባንክም ከሥራ ሰዓት ውጪ ለሊሎች ሳይሆን ለእርሱ ሰዎች ብቻ ክፍት ሆኖ ቆይቶ ነበር። አምና ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ሲል አሠራሩ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ታገደ። ጩፋ ዘንድሮ ማባበያዎችንና ማስፈራሪያዎችን በመጠቀም፥ በዞንም በክልልም ውስጥ የሚገኙ፥ (ለምሳሌ፥ እንደ የመካነ የሱሱን ቄስ ወልዴ አየለ እና የቃለ ሕይወቱ አቶ በጸጋ ጂላ የመሰሉ) የቆንስላ መሪዎችን መጠቀሚያ በማድረግ እንደገና የቡና ምርት ገንዘብ ዝርፊያ ለማድረግ እየታገለ ነው። የመካነ ኢየሱስ እና የቃለ ሕይወት አብያተ ክርስቲያናት በሐሰተኛ ነቢያት ላይ ቆራጥ አቋም ቢኖራቸውም እነዚህ የቆንስላ መሪዎች ለቤተ ክርስቲያናቸው አስተምህሮና አቋም ሳይሆን ለቆንስላው አባል ሐሰተኛ ነቢይ ወግነው መቆማቸው ያስደነግጣል። በዚህ መልኩ አስተምህሮ ገበያ ላይ ለልዋጭ ትቀርባለች ማለት ነው። ሌሎችም አሉ፤ ሁለቱን ብቻ በስም የጠቀስኩት የመካነ የሱስ እና የቃለ ሕይወት ሰዎች ስለሆኑ እና ሁለቱም በሐሰተኞች ላይ በቅርቡ አቋማቸውን ስለገለጡ ነው። የዲላ ከተማ ቃለ ሕይወት አጥቢያዎች ኅብረት በአቋም የኢዩ ጩፋን እንቅስቃሴ በግልጽ ተቃውሞ ሲጽፍ፥ ቆንስላው ውስጥ ያሉ የቃለ ሕይወት ሰዎች ደግሞ ሲደግፉ፥ ይህ ቆንስላ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናው ላይ ምን እየሠራ እንዳለ ደማቅ ማሳያ ነው። ቆንስላው በአገር አቀፍ ደረጃ መበከል ብቻ ሳይሆን እላይ የሚሠራው የነጌትነት ለማ መንፈስ አሠራር በተዋረድ እስከ ታች ድረስ ወንጌላዊ ክርስትና ላይ የሚሠራው እኩይ ሥራይ ቀላል አይደለም። ሙስናና ጉቦ እላይም እታችም አለ። ማስፈራራትና ባለ ሥልጣናትን መጠቀም እላይም እታችም አለ። ለዲላ ቅዱሳን የምለው ይህ ነው። 1. ሐሰተኛ ነቢይ ኢዩ ጩፋ ሐሰተኛ ነቢይ ነው። ክርስቶስ ስላልተቀበለ ክርስቶስን መስበክ አይችልም። ክርስቶስን የት ተቀብሎ በማን እግር ስር ደቀ መዝሙሮ ሆኖ ተኮትኩቶ እንዳደገ፥ የት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ቅዱስ እንደተማረ ጠይቁት። ልክ እንደ ቲ ቢ ጆሽዋ ማለት ነው። ቲ ቢ የት ጌታን ተቀበልክ? ማን በጌታ ትምህርት አሳደገህ? ወዘተ ሲባል እናቱ ማኅፀን ሆኖ ጌታን እንደተቀበለ እንደተናገረው ማለት ነው። ጌታን የማያውቅ ሰው ጌታን አይሰብክምና ራሱን አይስበካችሁ። 2. ሐሰተኛ ነቢይ ኢዩ ጩፋ ዲላ ቢመጣና እስቴዲየም ቢሰብክ መስቀሉ (የመስቀሉ ቃል) ያለው ከእስቴዲየሙ ውጪ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖቻችሁ እንደሆነ እወቁ። 3. ሐሰተኛ ነቢይ ኢዩ ጩፋ እና መሰሎቹ የቡና ጊዜ እየጠበቁ ወደ ቡና አምራች ዞኖች የሚመጡት ለምንም ሳይሆን ለገንዘብ ጠረጋ ብቻ እንደሆነ እወቁ። ጌታ ማስተዋልን ይስጣችሁ። ዘላለም ነኝ።
Открыть в Telegramመስቀሉ ያለው ከእስቴዲየሙ ውጪ ነው። ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። 2ቆሮ. 4፥5 በዚህ ጥቅስ ጳውሎስ ሁለት ዋና ነገሮችን ተናገረ፤ አንዱ ራሱን ሳይሆን ክርስቶስን መስበክ ነው። ሌላው ራሱን ላገለገላቸው ሰዎች ባሪያ ማድረግ ነው። ሁለቱንም አስቧቸው። ጳውሎስ ክርስቶስን ሰባኪ ነበረ፤ የተጠራበትን ምስክርነቶች ሲመሰክር እንኳ፥ (ለምሳሌ፥ ሐዋ. 22 እና 26) ስለ ራሱ እና በእጁ ስለተደረጉትን ድንቆች ሳይሆን ክርስቶስን ነበር የመሰከረው። መታወቂያውን ማሳየትና አርማውን ማውለብለብ ሳይሆን ያዳነውን ጌታ ነበር ያሳየው። በመካከላቸው መከፋፈልና አምልኮተ ሰብእ በነበራቸው፥ ‘እኔ የእገሌ ነኝ!’ ለሚሉት የቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ፥ ‘ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? . . . ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም። . . . አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ።’ ነበር ያላቸው። 1ቆሮ 1፥13-16 እና 3፥5። ራሱን ቢሰብክ ጳውሎስ ራሱን የሚሰብክባቸው ርእሶች ነበሩት፥ ልደቱ፥ እድገቱ፥ ትምህርቱ፥ የውሸት ያልሆኑ ዶክትሬቶቹ፥ አይሁዳዊነቱ፥ ሃይማኖታዊ ቅንዓቱ፥ ያለ ነቀፋ የሆነ ሃይማኖታዊ ጽድቁ፥ የሚያውለበልባቸው ብዙ ባርኔጣዎች አሉት። አድርጎ አያውቅም። የዘመናችን ሐሰተኞች ክርስቶስን ሲጠሩ ለንግድ ማስታወቂያነት ብቻ መሆኑን ማወቅ ከተሳነንን ቆይተናል። ለምሳሌ፥ ቤኒ ሂንን በቅርብ ደጋግሜ ጽፌበታለሁ፤ የዚህን ሰው አንዱን የአምልኮ . . .
Открыть в Telegramመስቀል ዙፋን አይደለም። የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም። 1ቆሮ. 1፥17 የክርስቶስ መስቀል ከንቱ መሆን ይችላል። ዓላማው የእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን የራስ ጥቅም ከሆነ ከንቱ መሆን ይችላል። ግቡ ወንጌልና የቤተ ክርስቲያን ጥቅም ካልሆነ ከንቱ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ይህን ጥቅስ የጻፈው ግቡ ወንጌልን መስበክ እንጂ ሌላው ቀርቶ ማጥመቅ እንኳ እንዳልሆነ ሲናገር ነው። ከክርስቶስ የማዳን ወንጌል፥ ከመስቀሉ ቃል፥ ቀጥሎ ያለ ማናቸውም ነገር መስቀሉን ከንቱ ያደርገዋል። ጥምቀትም እንኳ ቢሆን። ጥምቀት አያድነንማ! ሌላውስ? ሌላውማ ምን ቦታ እንዳለው መገመት አይከብድም። ጉደኛው ቆንስላ አቶ ጌትነትን ማጣራት ከጀመረ በኋላ አሁን ሥራው መጠናቀቂያ ጊዜው ነው። ማጣራት ከማለት ማጣሪያ ወይም የማጣሪያ ግጥሚያ ቢባል የተሻለ ይመስለኛል። ማጣሪያው የሚሆነው እርሱ በቢሮውና በቆንስላው ላይ ተንፈራጥጦ ተቀምጦ ነው። ይህ ምርመራ መደረግ የነበረበት በቤተ ክርስቲያን መሆኑ በራሱ ስላቅ ነው። ይህ እኮ የመንግሥት ሥራ ነው መሆን የነበረበት። ቤተ ክርስቲያን ወንጀል አጣሪ የሆነችበት ዘመን ላይ መሆናችን ራሱ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን ሚና እየተጫወተች መሆኗን እና መንግሥትም ለዜጎች እንግልት ደንታ የሌለው መሆኑን አመልካች ይመስለኛል። ስለ አቶ ጌትነት ለማ ወንጀሎች ዛሬ አንድ ብቻ ምሳሌ ልስጥ። ርኆቦት አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሚባለው ኅብረት የአቶ ጌትነትንን የስልክ ድምጽ ቅጂ ባወጣንበት ማግሥት ተሽቀዳድመው የai ድምጽ ነው ብለው ካወጡት ማኅበሮች አንዱ ነው። ያንን ደብዳቤ የፈረመው በስፍራው ሄዳችሁ ልትመለከቱት እንደምትችሉት ፓስተር ካሳሁን እምሩ የተባለው ፕሬዚደንት ነው። ደብዳቤው የተጻፈው ነሐሴ 19፥ 2018 ነው። ሌተርሄዱ አዲስ ማኅተሙም አዲስ ነው። ለምን? ያ ሰው ከማኅበሩ ፕሬዚደንትነት ከ5 ቀናት በፊት በማኅበሩ መተዳደሪያ አንቀጽ 17 መሠረት ታግዶአል። የታገደባቸው ወንጀሎችም በጥቅሉ በግልጽ በማገጃው ላይ ተጽፈዋል። በዝርዝር በሌላ ሰነድ ይገኛሉ፤ ደብዳቤውን በአስተያየት መስጫ አስቀምጣለሁ። ይህ የታገደው ሰው ለአቶ ጌትነት ወንጀሎች ቁልፍ ተባባሪ ነው፤ የአንድ አካባቢ ሰዎችም ናቸው። ይህ ሰው ወንጀሉ እንዲታጠብለት ተብሎ ከቆንስላው አሻንጉሊት ኮሚሽኖች አንዱ የሰላምና እርቅ ኮሚሽን የሚባል አካል ክሱ ለስልሶ እንዲታገድለት ሚናውን ይጫወታል። እርሱ በዚያ ሥልጣን መቆየት እንዲኖርበት በአስቸኳይ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሌላ ተመሳሳይ ስም የያዘ ማኅበር ይቋቋማል። ልብ በሉ፤ ማኅበር ለማቋቋም የሚወስደው ቆንስላዊ ውጣ ውረድ በሙሉ በአንድ ዝላይ ተዘሎ ማለት ነው። ይህ ሰው ነው የአቶ ጌትነትን ድምጽ የai ነው ብሎ ወዲያው የጻፈው። እነዚያ ደብዳቤዎች የተጻፉትም በአቶ ጌትነት ትእዛዝ እንደሆነ መገመት አይከብድም። ያ ብቻ አይደለም፤ የርኆቦት ኅብረት ፕሬዚደንቱን አስወግዶ ሌላ (ፓስተር አዲስ አዳነ) ሲመርጥ፥ አመራረጣችሁ የቆንስላውን መዋቅር ያልተከተለ ነው ብለው ረብሻ ተፈጠረ። ኅብረቱ በደንቡ መሠረት ፕሬዚደንቱን መሻር ይችላል። ቆንስላው ደግሞ ያንን ነው ሊራመድበት የሞከረው። የማጣሪያው ሥራ ሲጀመር አቶ ጌትነት ራሱ የፈለጋቸው ሰዎች በአጣሪው ውስጥ እንዲገቡ አንዳንዶችን በማዘዝ የሚፈልጋቸው ሰዎች እንዲወከሉ፥ ሌሎቹን ደግሞ በመለመንና በማማለድ የሚደግፉት ሰዎች እንዲገቡ ጥረት አድርጓል። በዚህ ተሳክቶለታል። ከወከለችውና ካገደችው ከቃለ ሕይወት እንኳ ለአቶ ጌትነት ወንጀሎች የሚራሩ ሰዎች መኖራቸውን መስማት ያሳፍራል። በውክልናው ጊዜ ከርኆቦት (አሁን ሁለት ሆነዋል) ሁለት አጣሪ መወከል ስለማይችሉ የሚወከለው አንድ ሰው በአቶ ጌትነት የተፈለገው ፓስተር ደሳለኝ ተፈራ የተባለው ከፓስተር ካሳሁን እምሩ ጋር በአጋሮ የአንዲት አጥቢያ ሰው የሆነ ተወከለ። የተወከለው በአዲሱ ፕሬዘደንት ሲሆን ለዚህኛው ውክልና የአዲሱን ፕሬዚደንት ወካይነት ተቀብሎአል። ይህ ሰው ፓስተር ደሳለኝ ከዚህ በፊት በማኅበራዊ ሚድያ እዚያ አጣሪ ኮሚቴ ውስጥ መገኘት እንደሌለበት በግልጽ የተጻፈበት ሰው ነው። እንግዲህ አቶ ጌትነት እቢሮው ተቀምጦ እየተመረመረ የሚሠራቸው ነገሮች፥ የሚያጠፋቸውና ገድሎ የሚቀብራቸው ሰነዶች፥ እዚያው ሆኖ እርሱን እንዲመረምሩ የሚያስመርጣቸው እና የሚያባብላቸው ሰዎች፥ ቀጥሎም እዚያው የሚቆይ ከሆነ ደግሞ (መቼም ቅሌታችን አያልቅምና ሊቀጥል ይችል ይሆናል) ገና ለገና የሚሆንባቸውን ፈርተው የሚሸማቀቁ ሰዎች እየተወኑ ባሉበት በዚህ ሂደት ፍትህ ድል ነሥታ ትወጣለች ማለት የመነመነ ተስፋ ነው። አቶ ጌትነትም ዓይኑን በጨው ታጥቦ እዚያ ቢሮ ይቀመጥ ይሆናል። እኛም ወንጀሎቹን ከመናገር፥ ጉዳዩ በእርግጥም ወንጀል ነውና መንግሥት ጣልቃ እስኪገባ ድረስ፥ ዝም ማለት አንችልም። መስቀል ዙፋን አይደለም። ዘላለም ነኝ።
Открыть в Telegramየቁርኣኑ ዒሳ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም ወደ ትግርኛ ተመልሶአል። ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ላይ ነው። በ2027 መጀመሪያ በእንግሊዝኛ ይታተማል።
Открыть в Telegramእግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች። መዝ. 10፥17 እግዚአብሔር እንዲሰማን የተመረጡ ቃላት አያስፈልጉንም። በምርጥ ቃላት አንሸነግለውም። በልሳን መጸለይም፥ መወራጨትና መርበድበድም አያስፈልገንም። የተሸመደዱ ቃላት አይጠቅሙንም። ጌታ፥ 'አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።' ብሎአልና የመናገር ብዛትና ከንቱ ድግምትም አይረባንም። የመናገር ብዛት ብቻ ሳይሆን የመናገር ማነስም ትልቅ ጉዳይ አይደለም። በእውነቱ፥ ፈጽሞ መናገር አለመቻልም እርሱ እኛን እንዳይሰማ እንቅፋት አይሆንበትም። አንዳንድ እውነተኛ ጸሎቶቻችን በቃላትም ልንናገራቸው የማንችላቸውና የማንናገራቸው፥ ቃላትም የማናገኝላቸው ናቸው። ጳውሎስ፥ 'ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤' እንዳለው ቃላት የሌለባቸው መቃተቶችም አሉ። ብዙ መቃተቶች። እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች። #ምኞት ቃል አይደለም፤ አይሰማም። ግን ለእርሱ እንደ ቃል የሚሰምማ ድምጽ ነው። #አሳብ ቃል አይደለም፤ አይደመጥም። እንዲያውም በተጻፈበት ቋንቋ ማዘንበል እንደማለት ነው። ግን ለእርሱ እንደ ቃል የሚሰምማ ድምጽ ነው። መናገር ሳይኖር፥ ቃልም ሳይኖር መሰማትና መደመጥ አለ። እግዚአብሔር በፊቱ ስንቀርብ ቃላችንን ያለ ግብዝነት የሆነ ቃል፥ ምኞታችንን እንደ እርሱ ፈቃድ የሆነ ምኞት፥ የልባችንን አሳብ ሲያደምጠው ፈገግ የሚያሰኘው አሳብ ያድርግልን። ዘ. መ.
Открыть в Telegramሙላትና ሙሌት። ሙላትና ሙሌት።እውነተኛ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እና ሰው ሠራሽ የመንፈስ ሙሌት ልዩነታቸው ምንድር ነው? View on YouTube
Открыть в Telegramቄሱና ጌቱ፤ የቆንስላው (ካውንስሉ) መዘውር ዘዋሪዎች። ቄሱና ጌቱ፤ የቆንስላው (ካውንስሉ) መዘውር ዘዋሪዎች።አቶ ጌቱ ለማ በቆንስላው ጠቅላይ ጸሐፊነት ሥልጣን ሽፋን ብዙ የሙስና ሥራዎች ሲሠራ በመቆየቱ በቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንም በራሱ በቆንስላውም አጣሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየተፈተሸ ይገኛል። ይህ የማጣራት ሥራ እንዲደናቀፍ ደግሞ ቄስ ደረጀ የራሱን ሚና በትጋት በመጫወት ላይ ይገኛል፤ ለምን? View on YouTube
Открыть в Telegramየወንጀል አናቶሚ ከዚህ በፊት አንድ ሦስት ያህል አናቶሚዎች መጻፌን አስታውሳለሁ። የመጀመሪያው በኮቪድ ጊዜ የጻፍኩት የፍርሃት አናቶሚ (2020) ሲሆን ሌሎቹ የመግገንጠል አናቶሚ (2022) እና የዝሙት አናቶሚ (2024) ናቸው። ይህ አራተኛው ነው። በየሁለት ዓመት መራራቃቸው አጋጣሚ ብቻ ነው። አናቶሚ ምንጩ የግሪክ ቋንቋ የሆነ ብዙውን ጊዜ በሕክምና መስክ የሚገለገሉበት ቃል ነው። ‘አና’ እንደገና ማለት ሆኖ ‘ቶሜ’ (ቶሜኦ) መቁረጥ መሰንጠቅ ማለት ነው። በሕክምና እና በስነ ሕይወት አናቶሚ መስክ ውስጥን ለማየት መቅደድ፥ መቁረጥ፥ መሰንጠቅ፥ መፈንከት፥ መክፈት ነው። የወንጀል አናቶሚ ስል ወንጀል አካል ቢሆን ቀድዶ ውስጡን ማየት ነው። ከሁለት ዓመት በፊት እስቲቭ ሎውሰን በጣም ሰፊ ከሆነው አገልግሎቱ ታገደ። የታገደው ከዚያ በፊት በነበሩት 5 ዓመታት ከሚስቱ ውጪ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ስለነበረው ነው። የአንዲት ቀን መውደቅ ሳይሆን ለዓመታት የተፈጸመ በስሌትና በእውቀት የተደረገ ነገር ነው። በሪፎርምድ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ሰባኪና አስተማሪ የሆነ መጋቢ በዚህ ኃጢአት ከተገኘ እስከ ፍጻሜው ነው ከአገልግሎት የሚታገደው። በቅርብ የታተመው እስቲቭ የጻፈው መጽሐፍ ራሱ መነበብ አለበት? ወይስ የለበትም? የሚለው ጥያቄ እየናኘ ይገኛል። ንስሐውን ከሆነ የጻፈው ለምን ይሸጠዋል? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው። አገልጋይ የመድረክ ሰው ሲሆን የሕዝብ ንብረት ነው። መሪ ሲሆን የሚሊዮኖች ንብረት ነው። የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ሲሆንና፥ ‘ፓስተር፥ ነቢይ፥ ሐዋርያ፥ ቢሾፕ፥ ሬቨረንድ፥ ወዘተ፥’ ተብሎ እየተጠራ፥ አንዴ በኃጢአት መውደቅ አይደለም፤ ወይም አንድ ወንጀል መፈጸም አይደለም፤ በባህሩ ውስጥ ሲዋኝ ቢገኝስ? ኃጢአት ሁሉ ወንጀል አይደለም፤ ወንጀል ሁሉ ግን ኃጢአት ነው። ይህች አጭር ጽሑፍ ወንጌላውያን አማኞች የተንሸራተትንበትን መንሸራተት ርቀት እንድናጤን ጥሪ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ነገሮች እየሰማን ኖረን አሁን መደንገጥ አቁመናል። ጆሮቻችንን ያደነቆሩት ጩኸቶች እጅግ ኃይለኛ ድምጾች ነበሩና ምናልባት የጆሮ ታምቡራችን ተሸንቁሮአል። ምናልባት የመስሚያችን ነርቮች ሥራ አቁመው ደንዝዘናል፤ ስለዚህ ምንም ድምጽ አያስደንቀንም፤ አያስደነግጠንም። ልብ ወለድ መጽሐፎች ማንበብ ስለምወድ፥ እየቆየሁ በጣም መራጭ ብሆንም፥ በጣም ብዙ አንብቤአለሁ። በውስጣቸው የተካተቱ ወንጀሎች ዓይነታቸው ቢለያይም ውቅራቸው አንድ ዓይነት ነው። የወንጀል አናቶሚ ስል ቀድደን ብናየው ምን ይመስላል? የሚለው አሳብ ነው። ወንጀል ብቻ ሳይሆን ይህ ኃጢአትንም ይመለከታል። የዝሙት አናቶሚ ያልኩትን ተመልከቱ። ሦስት ነጥቦች በአጭሩ፤ ወንጀል ተቀድዶ ቢታይ እነዚህ ይታያሉ፤ 1፥ ማሰብ። ማናቸውም ወንጀል በማሰብ ይጀመራል። ይታሰባል፥ ይወጠናል፥ ይታለማል፥ ይሰመራል፥ ይታቀዳል። ቢታወቅ ምን እንደሚደረግ፥ እንዴት እንደሚሸፈን ይውጠነጠናል። እነማን ምን ማድረግ እንዳለባቸው፥ መቼ ምን እንደሚደረግ፥ እንዴት መደረግ እንዳለበት፥ ይጠናል። ምን እንደሚያስወጣ፥ ምን እንደሚያስገባ ጥልቅ ስሌት ይደረጋል። 2፥ ማድረግ። ያ የታሰበው፥ የታለመው፥ የተወጠነው፥ የተውጠነጠነው፥ የተጠናው፥ የተሰላው ይተገበራል። ምስጢር በመጠበቅ፥ ረቂቅ ስልቶችን በመከተል፥ ዱካና አሻራ እንዳይታይ በመጠንቀቅ፥ ጊዜና ቦታ፥ ሁኔታና የሰው ኃይል ተጠንቶ አሳቡና ውጥኑ እመሬት ይወርዳል፤ ሥጋ ይለብሳል። መጀመሪያው እፍታው ይቀመሳል። ደም የላሰ፥ የቀመሰ አውሬ መሆን ይጀምራል። ቅምሻው ማቆሚያ የለውም፤ ቢኖርም አይታይም። ወንጀል ወንጀልን ይወልዳል፤ ከመጀመሪያው ወንጀል በኋላ፥ ‘የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም’ ጨዋታ ይሆናል። በእርግጥም ወንጀል ጨዋታ መምሰል ሳይሆን ጨዋታ ይሆናል። 3፥ መደበቅ። ወንጀልን የሚፈጽሙ ሰዎች ሰዎች ከሆኑ ወንጀሉ ወንጀል መሆኑን ያውቁታል። ሰዎች ከሆኑ። ወንጀል ደግሞ ቅጣት እንዳለውም ያውቃሉ። ከወንጀሉ በኋላ ከቅጣት እንዴት እንደሚያመልጡ የሚያደርጓቸው ብዙ መከላከያዎች አሏቸው። ጥርጣሬን ማስወገድ፥ ጨዋ መስሎ በአደባባይ መታየት፥ በጎ አድራጊ መሆን፥ ራስን በታማኞች ማጠር፥ በጠባቂዎች ብቻ ሳይሆን በሰፊው ሕዝብ እይታ ስር መውጣትና መግባት፥ ወንጀሉ ሲታወቅ ከጥርጥር በላይ የሆኑ ለመሆናቸው በቂ እማኝ መጥራት፥ ጠያቂ ጠበቃ ሳይጠይቁ ጯኺዎችን መነስነስ፥ ሕዝባዊና ማኅበራዊ ሚድያውን መሙላት፥ ሣይሆን ወንጀሉን ዓይኔን ግንባር ያርገው፤ አላየሁም፥ አልሰማሁም፥ አልነበርኩም፥ አላውቅም፥ ብሎ ፈጽሞ መካድ፤ አሻራንና ፍለጋን ማጥፋት፥ ከሳሾችን ከማሸማቀቅ፥ እስከ ማስፈራራት፥ ከመዛት እስከ ማስመታትና ማስደብደብና ማስገደል መሄድ፥ ጥቂቶቹ ናቸው። የዝሙት አናቶሚን ስንመለከት ንጉሥ ዳዊት እነዚህን ሦስት ነገሮች እንዴት እንዳከናወነ ተመልክተናል። አሁን በአገራችን እየሆነ ያለው የሚያሳየን የዝቅታችንን ጥልቀት ብቻ አይደለም። ፈውስ የሌለን የመሆናችንን እውነትም ይመስለኛል። ስሕተት ብሆን ብዬ ሺህ ጊዜ እመኛለሁ፤ ነፍስያዬ የምትነግረኝ ግን ሌላ ነው። ዘላለም ነኝ።
Открыть в Telegramበአንድ አገር ሕግ ወንጌል መመስከር ወንጀል ቢሆን ይህ ድርጊት ኃጢአት መባል ይችላል? (R. M.) ይህ ጥያቄ፥ ‘የወንጀል አናቶሚ’ በሚል ርእስ ባካፈልኩት አጭር ጽሑፍ ስር በቀረቡት አስተያየቶች ውስጥ የተጻፈ ጥያቄ ነው። ጥያቄውን ያጫረው፥ ‘ኃጢአት ሁሉ ወንጀል አይደለም፤ ወንጀል ሁሉ ግን ኃጢአት ነው።’ ብዬ የጻፍኩት ነው። አጭሩ መልሴ፥ ‘ይህንን ሕግ የደነገጉት አገሮች ወንጀል ነው የፈጸሙት፤ የሕሊና ነጻነትን ስላገዱ። ሆኖም፥ እነሱ ወንጀል ቢሉትም ወንጀል ስላልሆነ ኃጢአት ሊሆን አይችልም።’ የሚል ነው። ጥያቄው መጠነኛ ማብራሪያ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች የሚፈልግ ጥሩ ጥያቄ በመሆኑ ይህንን መጨመር ፈለግሁ። ወንጌል ወንጀል የሆነባቸው አገሮች አሉ። በተለይ ሃይማኖት እና መንግሥት ሕጋዊ ጋብቻ በፈጸሙባቸው አሐዳውያን አገሮች ይህ የሚደረግ ነገር ነው። ለምሳሌ፥ በሸሪዓ በሚተዳደሩ እስላማዊ አገሮች ክርስቲያኖች ዲሚዎች ወይም ግብር ከፋይ አናሳ ዜጋዎች እንዲሆኑ ቁርኣን ስለሚያዝዝ፥ ወንጌልን በግልጽ መመስከር፥ ድምጽ አሰምቶ መዘመር፥ ቤተ ክርስቲያን መሥራት፥ ቢፈርስ ማደስ፥ ወዘተ፥ የተከለከለ ነው። ወንጌልን በግልጽ መመስከር ከነዚህ ክልክል ድንጋጌዎች አንዱ ነው። ከሙስሊሞች ወደ ክርስቶስ የሚመጣና በክርስቶስ ጌትነት የሚያምን ከተገኘም ድንጋጌው መገደል ነው። ይህ ካስፈለገ የሚብራራ እውነት። ወደ ጥያቄው ስመለስ፥ እነዚህ አገሮች ወንጌል እንዳይነገር ወይም ሰዎች የሕሊና ነጻነት እንዳይኖራቸው ማድረጋቸው ተፈጥሮአዊና ሰብዓዊ ነጻነትን መግፈፋቸው በመሆኑ፥ ወንጀሉ ወንጌልን የመሰከሩት ሰዎች ሳይሆን ነጻነትን የገፈፈው የነዚያ ሰዎች ሕግና ድንጋጌ ነው። ከዚህ ጀርባ ወንጌል እንዳይነገርና ሰዎች እንዲድኑ የማይወድድ ጠላት (ስሙ ሰይጣን ይባላል) እንደሚሠራ እናውቃለን። መንግሥታት አምልኮን በሞኖፖል ይዘው ሰዎች አምላካቸውን ሳይሆን አማልክቶቻቸውን እንዲያመልኩ የሚያስገድዱባቸው አጋጣሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኖረው ያውቃሉ። ወንጌልን እንዳይነግሩ፥ የክርስቶስን ጌትነትና ትንሣኤም እንዳይናገሩ ከልክለው ያውቃሉ። ከብሉይም ከአዲስ ኪዳንም ምሳሌ ላሳይ። በዳን. 3 ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል እንዲሰግዱ ታዝዘው ሰዎች ሁሉ ወድቀው ሲሰግዱ ያልወደቁና ያልሰገዱ የጀርባ አጥንት የነበራቸው ሦስት ወጣቶች ነበሩ። ዕድሜያቸው ከ20 ከበለጠ ብዙም የሚበልጥ አይመስለኝም። ይህ የንጉስ ትእዛዝ ነው፤ ሕግ ነው፤ ድንጋጌ ነው፤ የታወጀ አዋጅ ነው። መተላለፍ እንደሚያስቀጣም አዋጁ በመጨረሻው አንቀጽ ግልጽ አድርጎታል። እነዚህ ባለ ጀርባ አጥንት ወጣቶች ግን ሰው ሁሉ ሲወድቅ አልወደቁም፤ ሲሰግድ አልሰገዱም። በመቆማቸው ማንነታቸውን እና የአምላካቸውን ማንነት ያለ ድምጽ መናገራቸው ነው። ይህ መመስከር ነው። ተጠቆሙ፥ ተከሰሱ፤ በቁጣና በብስጭት ወደጦፈው ወደ ንጉሡ ቀርበው መልስ ሰጡ። ከመልሳቸው ውስጥ ይህ ይገኛል፤ የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት። ዳን. 3፥17-18። ወደ እቶኑ ተጣሉ፤ ታሪኩ በዳን. 3 ይገኛል። አዋጅ ተላልፈዋል? አዎን። ወንጀል ነው? በአገሩና በንጉሡ ድንጋጌ መሠረት አዎን። ኃጢአት ነው? አይደለም። ወንጀሉና ኃጢአቱ የማን ነው? በሰዎች ሕሊናና ሃይማኖት ላይ የተጫነው የናቡከደነጾር። ዓይኖቹ ማዳኑን ሲያዩ በፍጻሜው ሌላ አዋጅ ጻፈ፤ በአዋጁ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። አለ፤ ቁጥር 28። አስደናቂው ቃል፥ የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን የሚለው ነው። የራሱን አዋጅ መተላለፋቸውን ነው አድንቆ የጻፈው። ያ የመጀመሪያው አዋጅ ስሕተት ነበር። ሌላው በዚያው በዳንኤል መጽሐፍ (ዳን. 6) የሚገኘው ዳንኤል ነው። ወንጀል ሆኖ የተከሰሰበት ክስ ወደ አምላኩ መጸለዩ ነው። በሰሎሞን ጸሎት መሠረት በምርኮ አገር ሆኖም ቢሆን ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አድርጎ መስኮቱን ከፍቶ በቀን ሦስቴ ይጸልይ ነበር። አዋጅ ወጣ፤ ተንኮል አለበት፤ ሴራ አለበት፤ የመነጨው ከንጉሡ አይደለም፤ ግን አጽዳቂው እርሱ ነው። አዋጁ ተጻፈ፤ የቅጣት አንቀጽም አለበት። ዳንኤልም አነበበው። በአዋጁ መሠረት ዳንኤል ጸሎትን ተከልክሎአል። እርሱ ግን ገብቶ ቀድሞ ያደርግ እንደነበረው ምንም ሳይለውጥ ጸሎቱን ቀጠለ። የንጉሡን ሕግ ተላልፏል? አዎን። አዋጁን ጥሶአል? አዎን። ችግሩ ምንድር ነው? አዋጁ ራሱ ነው ችግሩ። ከንጉሥ በላይ የሆነ አምላክ መኖሩን ያለማወቅ ነው ችግሩ። ያ በራሱ ኃጢአት ነው።የዚህም ጠቅላላ ታሪኩ በዳን. 6 ተጽፎልን ይገኛል። ሌላው ታሪክ በሐዋ. 4 ይገኛል። በዚያ በኢየሩሳሌም በሐዋርያት እጅ ተአምር ሆኖ፥ ወንጌል ተነግሮ፥ ብዙ ሰዎች አምነው፥ ጉዳዩ ወደ አይሁድ ሽማግሎችና ካህናት ሸንጎ ቀረበ። ሐዋ. 4፥18 ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ይላል። እነዚህ ሰዎች በእርግጥ መንግሥት አይደሉም። ሃይማኖትን በተመለከተ ግን የመንግሥት ያህል ሥልጣን ያላቸው ናቸው። እነዚህን መቃወም በተዘዋዋሪ መንግሥትን መቃወምም ነው። የነጴጥሮስ መልስ ምን ነበር? ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው። ሐዋ. 4፥19-20። የሸንጎውን ትእዛዝ ተላልፈዋል? አዎን ተላልፈዋል። ግን ከሸንጎው በላይ የሆነ አምላክን ትእዛዝ እየፈጸሙ ነበሩ። ሳጠቃልል፥ ኃጢአት ሁሉ ወንጀል አይደለም፤ ወንጀል ሁሉ ግን ኃጢአት ነው። ግን ያ ወንጀል የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስ ነው የተፈጸመው? ወይስ የእግዚአብሔርን ሕግ በመጻረር የእርሱን ተከታዮች ለመጉዳት ተብሎ የተደነገገ ድንጋጌ ነው? በአንድ አገር ሕግ ወንጌል መመስከር ወንጀል ቢሆን ይህ ድርጊት ኃጢአት መባል ይችላል? አይቻልም። ለምድራዊ መንግሥት መገዛት እንዳለብንስ ሮሜ 13 አይደነግግም? ይደነግጋል፤ መገዛት ያለብን ያ መንግሥት ከእርሱ በላይ ያለውን መንግሥት ሕግ እንድንጥስ እስካላደረገን ድረስ ነው። አምላካችንን እንድንክድ አዋጅ ቢያወጣ ለምድራዊ መንግሥት እንድንታዘዝ ስለታዘዝን አምላካችንን እንክዳለን? አንክድም። ወንጌል እንዳንሰብክ ቢከለክለንስ ዝም እንላለን? አንልም፤ አስቀድሞ ትልቁ ጌታ ይህንን የምሥራች እንድናበስር አዝዞናልና። ትልቁን ጌታ መታዘዝ በምንም መልኩ ወንጀል አይደለም። ዘ. መ.
Открыть в Telegram