• የፍቅር ዓይነቶች • "Types of Love" ━━━🧡━━━ Colors of Love በተሰኘውና እ.ኤ.አ. በ1973 በታተመው መጽሐፉ J. A. Lee ስለ ስድስቱ የፍቅር ዓይነቶች ለንባብ አብቅቷል። 1. Eros Love፡ ኤሮስ ብዙውን ጊዜ የጾታ ፍቅር ወይም በአካል እርስ በርስ የሚፈላለጉ ሰዎች መካከል ሊቀሰቀስ የሚችለውን ስሜት ለመግለጽ የምንጠቀመበት ቃል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ የግሪክ ፍቅር አምላክ ስም ሆኖ ያገለግልም ነበር። ኤሮቲክ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ስርወ-መሰረቱ ይህ እንደሆነ ልብ ይሏል። ይህ የፍቅር ዓይነት ሮማንቲክና ስሜታዊ የሆነ ፍቅር ሲሆን ለሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነ የፍቅር ዓይነት ነው። ይኽኛው የፍቅር ዓይነት የሚይዛቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሰውነትን ቅርጽና ቁንጅና ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ናቸው። 2. Ludus Love፡ ይኽ ቁርጠኝነት የማይታይበት በእንግሊዘኛው Game-playing or Uncommitted Love የሚሉት ሲሆን፤ የዚህ ዓይነቱ ፍቅር የያዛቸው ሰዎች ዓላማቸው አንድ ብቻ ነው፣ ይኸውም የግል ፍላጎታቸውን ማስከበር ብቻ ነው። 3. Storge Love፡ ይኽ ቀስ በቀስ እየጠነከረ የሚመጣ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ውጤት ነው። በዚህ ዓይነት ፍቅር የተጠመዱ ሰዎች ብዙ ጊዜያቸውን በጋራ ማሳለፍ ይወዳሉ። 4. Pragma Love፡ የዚህ ዓይነት ፍቅር ጣራና መሰረቱ “የጋራ ጥቅምና መመሳሰል” የሚሉት ቃላት ናቸው። እንደዚህ ዓይነቱ ፍቅር ስሜታዊ አይደለም። ምክኒያቱም እነዚህ ፍቅረኛሞች የሚመሩት በሎጂክ ነውና። ብዙ ሰዎች በሥራ ቦታ አብረዋቸው ከሚውሉ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት የሚጀሚሩትም ለዚሁ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ እሷ የተማረች ከሆነ የምትመርጠው የተማረ ወንድን ነው። ወንዱም እንደዚሁ። 5. Mania Love፡ ይኽ ዓይነቱ ደግሞ በጣም አስቸጋሪና “እሱን/እሷን ካላገኘሁ እሞታለሁ” የሚያሰኝ ሲሆን በእንግሊዘኛው Obsessive or Possessive Love የሚባለው ነው። ለምሳሌ፦ ዝነኛ ሰውን የራስ ለማድረግ የሚደረገው የፍቅር ግብግብ ይኽ ዓይነቱ ፍቅር ነው። 6. Agape Love፡ ይኽ ዓይነቱ ፍቅር መተሳሰብ የተሞላበት፣ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ላይ የሚያደላ፣ ወንድማዊ የሆነና ከራስ ወዳድነት የፀዳ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን ፍቅር ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ለምሳሌ፦ ማዘር ቴሬዛ ለተቸገሩ ሰዎች ያሳዩት የነበረው ፍቅር ይኽን ዓይነቱን ፍቅር ነበር። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ወንዶች በአመዛኙ Ludus የተሰኘውን የፍቅር ዓይነት የሚያሳዩ ሲሆን ሴቶች ደግሞ Storge እና Pragma በተሰኙት የፍቅር ዓይነቶች ይያዛሉ። ━━━━━━━━━━━━ ምንጭ ➢ ድረ-ገጽ 📖 📖 📖 📖 📖 https://t.me/Ethiobooks
Открыть в TelegramПосты канала ከስነ-ፅሁፍ ዓለም
💬 ❝የፍቅር ቦታው ልብ ነው፤ ልብ ደግሞ ንፁህ ወርቅ ነው።❞ ሼህ ሙዛፊር 💬 ❝ፍቅር ማለት ሰዎች ነገሮች ሲሳኩላቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የገቡ እንዲመስላቸው የሚያደርግ ጊዜያዊ እብደት ነው።❞ አምብሮይስ ቢርስ 💬 ❝የሰው ልጅ የፍቅር ውሃ እየጠጣ ባይለመልም ኖሮ በአዳም ዘመን ደርቆ በረገፈ ነበር።❞ ዊልያም ጀምስ 💬 ❝ፍቅር፣ በተለይም ከቆንጆ ሴት ጋር የሚያከንፍ ፍቅር፣ "ወርቅ አልፈልግም፣ አልማዝ ካልሆነ በስተቀር" የሚባልበት የሰው ልጆች ራስ ማታለያና ከንቱ ድካም ነው።❞ ኦስካር ዋይልድ 💬 ❝ለማንኛውም የሰው ልጅ የምግባር በሽታ ጠንካራው መድኃኒት ፍቅር ብቻ ነው።❞ ራማያና 💬 ❝አንድ ወንድ አንዲት ሴት ሲያፈቅርና ያቺም ሴት ያን ወንድ ስታፈቅር፣ መላእክት ከሰማየ ሰማያት ወርደው በጎጇቸው እየኖሩ የደስታ መዝሙራቸውን ያንቆረቁራሉ።❞ ብራህማ 💬 ❝ፍቅር ማለት ሁለት አካል በአንድ ነፍስ ውስጥ ሲታቀፍ ነው።❞ ፕሌቶ 💬 ❝ፍቅረኞች ዓለምን ረስተው ዓለማቸውን የሚቀጩ ይመስላቸዋል እንጂ፤ ዓለም ምን ያህል እንደምትረሳቸው አይታወቃቸውም።❞ ማቲው አርኖልድ 💬 💬 ጥቅሶች @ethiobooks
Открыть в Telegramፍቅርና ፍቅረኞች ━━•✦•━━ ✍ መስፍን ሀብተማርያም ' በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንድ አስደናቂ ነገር ፖላንድ ውስጥ እንደተፈፀመ "ሪደርስ ዳይጀስት" በተባለው መጽሔት ላይ ሰፍሮ ተመልክቻለሁ። የናዚ ጀርመን አምባገነንነት በሰፈነባት አውሮፓ ብዙ ሰዎች በየጊዜው ከአሰቃቂ እስር ቤቶች እየተወሰዱ ይረሸኑ ነበር። እና በአንድ ወቅት ከሁለት መቶ የማያንሱ እስረኞች እንዲወጡ ይታዘዙና ሽማግሌዎቹንና አሮጊቶቹን ትተው ሌሎቹን ሊገድሉ ተዘጋጁ። የሚጠበቀው የኮሎኔሉ ትዕዛዝ ብቻ ነበር። ኮሎኔሉ ትዕዛዝ ሊሰጥ ሲል አንድ ኮሳሳ ሽማግሌ «እባክህ ኮሎኔል! ፍቀድልኝና ለአንዲት ደቂቃ ልናገር!» ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጠየቁ። «በል ፈጠን በል ተፈቅዶልሃል!» አላቸው ኮሎኔሉ። «ያንን ወጣት ተመልከተው» አሉ አዛውንቱ «በአንድ እስር ቤት ለሁለት ዓመት ኖረናል። ሚስቱን እንደሚያፈቅር ሌት ከቀን ይነግረኝ ነበር። ሙሽርነቱን ገና ጠግቦ ሳይጨርስ ነበር የታሰረው። ስለዚህ ዘወትር ሚስቱን እያነሳ ያለቅሳል፤ ይብሰለሰላል። ምግቡን እንኳን አጣጥሞ በልቶ አያውቅም። ፈገግታ ከረሳ ቆይቷል። ስለዚህ አሁን እንድትፈቅድልኝ የምጠይቅህ ... እኔ ሞቴን የምጠብቅ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴንና ልጆቼን ቀብሬያለሁ። እባክህ በሱ ምትክ እኔ ልገደል። እሱን ግን አንድ ቀን ሚስቱን ለማግኘት በቅቶ ፍቅሩን እንዲጨርስ እድል ስጠው።» በዚህ አነጋገር ኮሎኔሉ ልቡ ተነክቶ እንባ ተናነቀውና ሊረሸኑ የተወሰነባቸውን ሁሉንም ምሕረት አደረገላቸው። ፍቅር የሚሉት ነገር ይሄን ያስደርጋል? ወደ ሌላ አጋጣሚ ደግሞ እንለፍ። አንድ ሰውዬ ነበረ። ይሄ ሰው ሳይቤሪያ አምስት ዓመታት ታስሮ በሕይወት መቆየቱ ያስገረማቸው የሶቪየት ባለስልጣኖች «ሌሎች የእስር ቤት ጓደኞችህ በበረዶ እየተሰቃዩ ሲሞቱ አንተ እንዴት ተቋቋምከው?» ሲሉ ጠየቁት። «ሚስቴን ሁልጊዜ ስለማስብ ብርዱ እምብዛም አይሰማኝም!» በማለት ነበር እርሱም ምስጢሩን የገለፀላቸው። ... ❝ፍቅር ፍቅር አሉት ስሙን አሳንሰው፣ ከድንጋይ ይከብዳል ለተሸከመው ሰው።❞ ከተባለለት ወዲያ ኃይለኝነቱ መች ይጠየቃል። >>> ━━━━━━━━━━━ 📔 እፍታ - ቅፅ 1 (44 ትረካዎች) 📄 197 - 198 🗓 1991 ዓ.ም. 📖 📖 📖 📖 📖 https://t.me/Ethiobooks
Открыть в Telegramልደትና ተዝካር ══✦══ ✍ ሲሳይ ታደሰ /ዘ-ለገሃሬ/ ' ዘመድ አዝማድ ሁሉ - ጎረቤት ወዳጆች፣ ጓደኛ አብሮ አደግ - ሥጋ አበ-ልጀች... ብቻ 'ምትገኙ - በቅርብም በርቀት፣ ይድረሳችሁ ይኼ - የጥሪ ወረቀት። የበኩሯ ልጄ - ቀን ቆጥሮ ውልደቷ፣ የፊታችን እሁድ - ነውና ዓመቷ፣ 'ባካችሁ አትቅሩ - ኑላት ለልደቷ። ታዲያ እንዳትረሱ፣ ጥሪውን በማክበር - ከቤቴ ስትደርሱ፣ በልጄ ልደት ኬክ - ብቻ አትመለሱ፣ እዛው ተዝካር አለ - ጠበልም ቅመሱ። ለ'ኔ ውዷ ሚስቴ - ለልጄም እናቷ፣ ፍሬ ስትሰጠኝ - ያለፈው ሕይወቷ፣ እኩል በዚህ ቀን ነው - እሷም ሙት ዓመቷ። እኔም ሁለት ሆኜ፣ ከፊል ተሰብሬ - ከፊል ተጠግኜ... ባ'ንድ እጄ አቅፌ - ባ'ንድ እጄ ቀብሬ፣ ያ'ንዷ ልጄን ልደት - ዓመቷን አክብሬ፣ ደ'ሞ 'ዘክራለሁ - ሚስቴንም አብሬ። ልደትና ጸዲቅ - ኃዘንና ደስታ፣ ሁለቱም በቤቴ - ይኸው አንድ ቦታ። አደራ ተገኙ - ተጠሪዎች ሁሉ፣ "መልካም ልደት"ና - "ነፍስ ይማር"ም በሉ። ═══════ 📔 ለፍቅራችሁ 🗓 2006 ዓ.ም. 📖 📖 📖 📖 📖 https://t.me/Ethiobooks
Открыть в Telegram«ኦ... ያ_ _» ━•✦•━ ✍ ሕይወት እምሻው ' አፍላ ፍቅራቸውን እንደሚያጣጥሙ ወጣት ፍቅረኛሞች እጅ ለእጅ ተያይዘን ከምንወደው ካፌ እየወጣን ነበር፤ ላብ ያጠመቃቸው ጣቶቻችን ተሳስረው። ወደ ዋናው መንገድ ለመድረስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩን ግን በድንገት እጇን ከእጄ መንጭቃ አላቀቀችና፣ «እኔ እኮ አላምንም... ያ ያፌት አይደል እንዴ?!» አለች። ያፌት። የቀድሞ ፍቅረኛዋ። ከእኔ በፊት የነበረው ፍቅረኛዋ። በሄድንበት የሚከተለን፣ ከመሃከላችን የማይጠፋው ረዥም ጥላ። ከእኔ ጋር ዘጠኝ ወር በፍቅር ስንቆይ ከአፏ ልትነጥለው ግን አልቻለችም። ስሙን በሰበብ በአስባቡ ታነሳለች። 'ያፌት እንዲህ ብሎ።' 'ያፌት እንዲህ አድርጎ።' 'ያፌት ቢሆን እንዲህ ይል ነበር።' 'ያፌት ቢጠየቅ እንዲህ ያደርግ ነበር።' እኔ እና እሷ ባለንበት ቦታ ሁሉ፣ አብረን በምናሳልፋቸው ቅጽበቶች መሃከል ስሙ ዝቅ ተደርጎ እንደተከፈተ ለስላሳ ሙዚቃ ያጅበናል። ሳይጋበዝ አብሮን ይቀመጣል። አንድ ሆኖ እንደ ብዙ ሰው ይከበናል። ነገር ግን እኔ ቀናተኛና በራሱ የማይተማመን ወንድ ስላልሆንኩ አይቼ እንዳላየ፣ ገብቶኝ እንዳልገባኝ አልፋታለሁ። ☆ ☆ ☆ አንድ ጊዜ፣ በስሜት እየተወዘወዝኩ ረዥምና የሚያምር አንገቷን ከላይ እስከ ታች እየሳምኳት፣ «ኦ... ያ_ _» ስትለኝ ልቤ ለአፍታ ምት አቆመ። ደርቄ ቀረሁ። የሁኔታዬን መቀያየር ስትረዳ የሚርበተበቱ ከንፈሮቿን ወደ ከንፈሮቼ አስጠጋችና ትኩስ ትንፋሽዋን በመቀዝቀዝ ላይ ካለ ትንፋሼ ጋር እየደባለቀች ሳቅ ብላ፣ «... ያ...ያበደ ነው...እንዳታቆም...» አለችኝ። ልትል የነበረውን እያወቅኩ እንዳላወቅኩ መስዬ ይሄንንም አለፍኳት። ☆ ☆ ☆ አሁን፣ በማላየው ገመድ ይጎትታት ይመስል ወደፊት፣ ወደ እርሱ ተንደረደረች። «አቦ ባላየኝ!» አለች ልትደርስበት እየተጣደፈች። «ያየኝ ይመስልሃል? ካየኝ በጣም ይደብራል አይደል…? ማለቴ ከሌላ ወንድ ጋር ሲያገኘኝ?» ቃላቶቿ እርስ በርስ እስኪደራረቡ ፈጥና እየተናገረች ፈጥና ስትራመድ እኔም በዚያው ፍጥነት ከኋላዋ ተከተልኳት። ልትደረስበት ግን አልቻለችም። ያን ጊዜ ነው በድንገት፣ «ያፌት! አንተ ያፌት!» ብላ ጮኻ የጠራችው። እኔ ቆምኩ። በድንጋጤ። እሷ ሮጠች። ወደ እርሱ። ጥሪዋን ሰምቶ ዞር ሲል እንዳያት ፈገግ አለና፣ «እኔ እኮ አላምንም... ኮኪ?» ብሎ ፊቱን አዙሮ ወደ እሷ መምጣት ጀመረ። ተቃቀፉ። በኃይል። ተሳሳቁ። በጣም። የሁለቱም ፊት በድንገት የበራ መሰለ። በተለይ የእሷ። እኔ ግን ከናካቴው፣ ከነመፈጠሬም ተረሳሁ። እኔን በማያካትት የናፍቆትና የትዝታ ቅጽበት በሰከንዶች ከሚኖሩት አምባ ተደመሰስኩ። አይቼባት በማላውቀው መንገድ ተሽኮረመመች። እንደ ሆነ ነገር አደረጋት። ድምጿ እየሰለለና እየቀጠነ፣ አነጋገሯ ከዚህ በፊት በማላውቀው አኳኋን እየተሞላቀቀ ታዋራው ጀመር። ብዙ ደቂቃዎች እንዲህ ካለፉ በኋላ መኖሬን በድንገት እንዳስታወሰች ሁሉ ቁጣዬን እየታገልኩ ፈንጠር ብዬ በቆምኩበት መልከት አድርጋኝ፣ «በቃ ደውልልኝና እንገናኝ... አንጠፋፋ... ስልኬ ከጠፋብህ ያዘው... ያንተ ነገር ይሄኔ ደልተኸዋል» አለችው። ያፌት ስልክ ቁጥሯን ለመቀበል ጉጉት ያደረበት አይመስልም። ዓይኖቹ ከትከሻዋ ባሻገር እኔን ይመለከታሉ። እሷ ግን አላስተዋለችም። ዓይኗን በጨው አጥባ መቃበጡ ጊዜ አልሰጣትም። ☆ ☆ ☆ ይህ በሆነ በሳምንቱ አንድ የጋራ ጓደኛችን ከያፌት ጋር "ገላኒ ኮፊ" እንዳያቸው ግራ በመጋባት ነገረኝ። ይህንን ግን ማለፍ አልቻልኩም። ያንኑ ዕለት ማታ ስንገናኝ አነሳሁባት። «ካንተ ጋር ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ ልነግረው እኮ ነው ያገኘሁት» አለችኝ ፈርጠም ብላ። ሳቅ ታገለኝ። «በአሁን የፍቅር ሕይወታቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች ለቀድሞ ፍቅረኛቸው ደስተኛ ነኝ ማለት አይጠበቅባቸውም... ያውም በቀጠሮ» አልኳት። «ባክህ አንተ ደሞ... የሌለብህን ቅናት ዛሬ አትጀምር!» አለችኝ ባለማፈር። ረጅም ትንፋሽ ወሰድኩና ትኩር ብዬ ካየኋት በኋላ ለራሴም ባልገባኝ መንገድ ተረጋግቼ፣ «ኮኪ... አንድ ውለታ ዋይልኝ?» እልኳት። «የምን ውለታ?» «ለወደፊቱ ከአዲሱ ፍቅረኛሽ ጋር ሆነሽ መንገድ ላይ ብታዩኝ በሩቁ እጅሽን አውለብልበሽ ሰላም በይኝ እንጂ ሮጠሽ እንዳታቅፊኝ... እንደውም ጭራሽ ሰላም አትበዪኝ... ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ኑሮሽን ቀጥይ... እሺ?» አልኳት። ግራ እንደገባት ሁሉ ፊቷን አኮሳትራ፣ «ማለት... ምንድነው ምታወራው?...» ብላ ጠየቀችኝ። «የማወራውማ ከዚህች ደቂቃ ጀምሮ የቀድሞ ፍቅረኛሽ ስለመሆኔ ነው!» ብዬ መለስኩላትና ለበላነውና ለጠጣነው የሚበቃ ገንዘብ ጠረጴዛው ላይ ትቼና ከወንበሬ ተነስቼ ወደ ሬስቶራንቱ በር አመራሁ። 'ያፌት' 'ያፌት' ማለት የሚወደው አንደበቷም ሆነ መቼም የእኔ ሆኖ የማያውቀው ውብ ገላዋ ስላልተከተሉኝ ደስ አለኝ። ━━━━━━━━ 📖 📖 📖 📖 📖 https://t.me/Ethiobooks
Открыть в Telegramእረፍ አንተ ባንዳ፤ እንዳትሆን የኔ እዳ ━━━━━━✦━━━━━━ የኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያዎች ጦሩን ለማንቃት፣ ወታደሩን በርታ ለማለት አስመራ ኦዲዮ የሚባለው ቲያትር ቤት «ባልቻ አባ ነፍሶ» ቲያትርን ለማሳየት ቀጠሮ ይዘዋል። በቀጠሮው መሠረት ወታደሮቹ ምድብ ቦታቸውን ያዙ። የ2ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩት መርዕድ ንጉሤም በምድብ ቦታቸው ተቀመጡ። ወደ ቲያትር ቤቱ የገቡት ወታደሮች በሙሉ ተፈትሸው መሣሪያቸውን አስቀምጠው ሲገቡ፣ ጄኔራል መርዕድ ግን ሽጉጣቸውን ከጎናቸው ሻጥ እንዳደረጉ ወደ አዳራሹ ዘለቁ። ሁሉም ሰው መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ቲያትሩ ተጀመረ። በልዩ ወኔ ይ'ሠራ የነበረው "ባልቻ አባ ነፍሶ" ቲያትርን ሊመለከቱ የገቡት በሙሉ በአድናቆት ዓይናቸውን አፍጥጠው «ይኼ ነው ኢትዮጵያዊነት፤ የጀግንነት መሠረት» እያሉ በስሜት ይመለከቱ ጀመር። ጣሊያኑን ተላብሶ የሚጫወተው ገፀ-ባህርይ ባልቻ አባ ነፍሶን ቢያያቸው ያንን ጀግንነታቸውን ረስቶ፣ ያንን አርበኝነታቸውን ዘንግቶ እየሳቀ «ባልቻ አባ ነፍሶ ይቺ ነች? የሆነች ደካማ ሽማግሌ» ብሎ ሲናገር ጄኔራል መርዕድ ሽጉጣቸውን ከወገባችው ሳብ አደረጉት። አጠገባቸው የነበሩት የሥራ ባልደረባቸው ቲያትር መሆኑን ቢነግሯቸውም አልሰሟቸውም። የጣሊያናዊውን ገፀ-ባህርይ ተላብሶ የሚጫወተው ተዋናይ «ባልቻን ሮም ወስጄ ለሞሶሎኒ አስረክባለሁ» እያለ ሲፎክር ጄኔራል መርዕድ ትዕግስታቸውን አጡ። ሽጉጣቸውን አቀባበሉት። «ይኼ ነጫጭባ ባልቻ ላይ አይሳለቅም!» ብለው ቃታውን ሊስቡ ሲሉ አጠገባቸው የነበሩት የሥራ አጋራቸው ለምነው አስቆሟቸው። በቲያትሩ ላይ ባልቻ አባ ነፍሶ «እምዬ ምኒልክ ፊት ምን ብዬ ልናገር ነው? እጄን ሰጥቼ መጣሁ ብዬ ልቀርብ ነው?» እያሉ ሲያለቅሱ ጄኔራል መርዕድ «ይኼንን ጣልያን ደፍቼው ሰው ይሳቅብኝ፣ ቲያትር ብሎ ነገር የለም» ብለው የጣሊያኑን ገፀ-ባህርይ የተላበሰውን ሊገድሉት ወስነው ባሉበት ወቅት ባልቻ አባ ነፍሶ በቲያትሩ ላይ ጣሊያኑን ተኩሰው ገደሉት። ይኼኔ ጄኔራል መርዕድ «እኔም ልጨምርለት» ብለው ድጋሜ ሽጉጣቸውን አቀባበሉት። የሥራ ባልደረባቸው ግን «ጄኔራል መርዕድ፣ የቲያትሩን ልማድ አይሻሩት በግድ» ብለው መክረው ድርጊቱን አስተዋቸው። ከጄኔራል መርዕድ ሽጉጥ ሳይገደል የተረፈው ተዋናይ የመድረኩ ፈርጥ አብራር አብዶ ነበር። አብራር አብዶ ከጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ጥይት ተርፎ እስከ አሁን ድረስ በርካታ ቲያትሮችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን (ፊልሞችን) እየሠራ ይገኛል። ━━━━━━━━━━━━ 📔 አዲስ 1879 / ፲፰፻፸፱ ✍ ዳግማይ ነቅዓጥበብ (ዘ-ብሔረ ኢትዮጵያ) 📄 21 📖 📖 📖 📖 📖 https://t.me/Ethiobooks
Открыть в Telegram