የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማገገም ጀምሯል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከነበረበት ስብራት ማገገም እንደጀመረና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ደረጃውን እንደሚያሻሽል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል። በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት፣ በሜጋ ፕሮጀክቶችና በፋይናንስ ዘርፎች የሚታየው እንቅስቃሴ የኢኮኖሚውን ማገገም የሚያሳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። አክለውም በዚህ ለውጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ፣ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል። ችግሮች በአንድ ጀምበር እንደማይፈቱ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ደረጃውን የበለጠ ለማሻሻል የሁሉም ወገን ትጋትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል። በሳምራዊት ስዩም #ዳጉ_ጆርናል
Open in TelegramPosts of ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
"የኮይሻ ግድብ በዚህ አመት ይጠናቀቃል" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እየተካሄደ ባለው የኢፌዴሪ 7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ወጪን ለመቀነስ በተለያዩ ደረጃዎች ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ የኢንዱስትሪ ዋና ግብዓት ከሆነው ኢነርጂ አንጻር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ኮይሻ በአፍሪካ ሶስተኛው ግድብ መሆኑን እና በጥልቀቱ ከ2 ሺ ሜጋ ዋት በላይ እንደሚያመነጭ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግድቡ በዚህ አመት ከሞላ ጎደል እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል። የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ወደ ሚቀጥለው አመት ሊሻጋገር እንደሚችል ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ይህም የሆነው አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ በህዳሴ ግድብ ላይ በመዋሉ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። አሁን ላይ ፋይናንስ ማድረግ በመቻሉ ምናልባት ከአንድ አመት ተኩል እስከ ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኮይሻ ተመርቆ ለስራ ሊውል እንደሚችል ገልጸዋል። በጥቂት አመታት ውስጥ ህዳሴን እና ኮይሻን የሚያካክሩ ትላልቅ ግድቦች ተሰርተው ጥቅም ላይ መዋላቸው ትልቅ እመርታ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው፣ ጉዳዩ በተለያየ አቅጣጫ መስፋት እንዳለበት አመላክተዋል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramየ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ ያነሱት ዋና ዋና ሀሳቦች * የመንግስት ኩባንያዎችና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የመንግስት ኩባንያዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቅሰው፣ ወደፊት በወርቅ ሪፋይነሪ፣ በማዳበሪያ፣ በፓይፕላይን እና በመሳሰሉ አዳዲስ ሴክተሮች ከግል ሴክተር ጋር በመቀናጀት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። * የመንግስት ሀብትና ሪፎርም የመንግስት ሀብት ከመበዝበዝ ወጥቶ ትርፋማ እንዲሆንና በቂ ገቢ እንዲያስገባ መደረጉን እንዲሁም የተደረገው ሪፎርም የኢትዮጵያን የሀብት ብክነት ሰብስቦ ወደ ልማት መቀየሩን አመልክተዋል። * የፋይናንስና የባንክ ሀብት እድገት በባንኮች ያለው ተቀማጭ ሀብት ወደ 5.3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል። * ዲጂታል ፋይናንስና ባንኪንግ በሞባይል ባንኪንግ (በኢትዮ ቴሌኮም/ቴሌብር፣ በሳፋሪኮም/ኤም-ፔሳ እና በሞባይል ባንኪንግ) 70 ሚሊዮን ዜጎች መገልገል ችለዋል። * በሞባይል ዋሌት በእያንዳንዱ ባንክ ያለው የዲጂታል ሲስተም 164 ሚሊዮን አካውንቶችን ማፍራቱን ጠቅሰዋል። * በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ በዲጂታል ሲስተም የሚንቀሳቀሰው ሀብት ወደ 11 ትሪሊዮን ብር መድረሱንና ይህም ካለፉት 70–80 ዓመታት የባንክ እንቅስቃሴ ጋር የሚወዳደር አለመሆኑን ገልጸዋል። * የብድር አቅርቦትና ለግል ሴክተር የተሰጠ ትኩረት በተመለከተ ባለፉት ሶስት ወራት የተለቀቀው ብድር 426 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከአምናው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ62 ቢሊዮን ብር ወይም በ62 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። * ቀደም ሲል ባንኮች ቦንድ እንዲገዙ ይገደዱ የነበረበት አሰራር ተቀይሮ፣ አሁን ከሚሰጠው ብድር 98 ፐርሰንቱ ለግል ሴክተር የሚሰጥ ሲሆን መንግስት ከ2 ፐርሰንት በታች ብቻ እንደሚወስድ አብራርተዋል። ይህም የግል ሴክተሩ ገንዘብ አግኝቶ ሀሳቡን ወደ ተግባር እንዲቀይር እድል ይሰጣል። * በመጀመሪያው ሩብ ዓመት (ባለፉት ሶስት ወራት) 3.1 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት መደረጉንና ይህም ካምናው ጋር ሲነጻጸር ከ25 ፐርሰንት በላይ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል። ከሪፎርሙ በፊት ከ3–4 ዓመት በፊት የነበረው የዓመት ኤክስፖርት 3.1 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በአንድ ሩብ ዓመት ያንን የሚያክል ውጤት መምጣቱን እንደ ሪፎርሙ ስኬት ጠቅሰዋል። ትግስት ላቀው #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramየ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክርቤት አባላት የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች 1. የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የወጪ ንግድ እና የታክስ አሰባሰብ ዙሪያ 2. የሕዝብና ቤት ቆጠራ፦ ከ1997 ዓ.ም በኋላ መካሄድ የነበረበት 3ኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ አለመደረጉ በዕቅድ፣ በሀብት ክፍፍል እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር መፍጠሩ ተጠቁሟል። በዚህም ምክንያት ቆጠራው አለመካሄዱ ምን ችግር እንዳስከተለ እና መቼ ሊከናወን እንደሚችል ጥያቄ ቀርቧል። 3. የፖለቲካ እና የፕሬስ ነጻነት ምህዳር ይበልጥ እንዲሰፋ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም መንግሥት ምን እየሠራ ነው 4. በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ የንጹሐን ሰዎች ሞት እና የንብረት ዝርፊያ እንደቀጠለ መሆኑ ተነስቷል። መንግሥት ይህንን ሁኔታ ለማስቆም እና በዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምን ዕቅድ እንዳለው ጥያቄ ቀርቧል። 5.*በሀገራዊ ምክክር የተገኙ የጋራ ምክረ ሐሳቦችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር እንዲሁም በሕግ፣ በፖሊሲ እና በተቋማዊ ማሻሻያዎች ለመተግበር መንግሥት ምን ዝግጅት እና የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅቷል? በትግበራው ሂደትስ ከመላው ኢትዮጵያውያን እና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ምን ይጠበቃል? የሚሉ ጥያቄዋች እና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዋል። በምክር ቤቱ አባላት ላነሱት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በ2019 ዓ.ም. ዕቅድ ዙሪያ ለፓርላማ አባላት ምላሽ እና ማብራሪያ ይሰጣሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመንግሥት ዕቅድ ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያውን የሚሰጡት ምክር ቤቱ ዛሬ ጠዋት ከ2፡30 ጀምሮ በሚያካሂደው የ7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው። ምክር ቤቱ በዚህ ጉባኤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተወያየና የመንግሥትን አቋም ካዳመጠ በኋላ የድጋፍ ሞሽን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ለዛሬው ውይይት ዋና መነሻ የሆነውን የመንግሥት ዕቅድ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ማቅረባቸው ይታወሳል። በዛሬው የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች በክብር እንግድነት ይታደማሉ። ከእነዚህም ባለፈ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉባኤው ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in TelegramViews growthHide views growth
Views growth
Hours after publication
Show as table
| Hours after publication | Views |
|---|---|
| 0 h | 0 |
| 2 h | 1,680 |
| 4 h | 2,840 |
- After 1 hour1,680
- After 6 hours2,840
- Total to date2,840
“አደይ አበባ” በሚል ስያሜ የተቀላቀለ የጥበብ ዝግጅት በኩሪፍቱ አፍሪካን ቪሌጅ ሊካሄድ ነው። ዝግጅቱ በኩሪፍቱ ሪዞርት ኤንድ ስፓ ከአርቲስት ጠረፍ ካሳሁን (ኪያ) እና ከአርቲስት ሳሙኤል ተስፋዬ ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የተለያዩ የጥበብ ዘርፎችን በአንድ መድረክ ላይ ለማቅረብ ያለመ መሆኑን አዘጋጆቹ ተናግረዋል። ህዳር 26 ቀን 2019ዓ.ም.ሊካሄድ የታቀደው የስዕልና የቅርጻቅርጽ ኤግዚቢሽን፣ የሙዚቃ ትርኢት፣ ግጥም፣ ፋሽን እና ቲያትር እንደሚቀርቡ አዘጋጆቹ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል። “አደይ አበባ” የሚለው ስያሜ ተስፋን፣ አዲስ ጅማሬን፣ ውበትንና ለውጥን የሚወክል መሆኑን የገለጹት አዘጋጆቹ፣ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ባህልና ጥበብ ከዘመናዊ የፈጠራ ሥራዎች ጋር በማገናኘት ለሕዝብ ለማቅረብ እንደታሰበ ተጠቁመዋል። ዝግጅቱ የጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውንና ችሎታቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት፣ የተለያዩ የጥበብ ዘርፎች የሚገናኙበት እንዲሁም ለአዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች መነሻ የሚሆን መድረክ እንደሚፈጥር ተገልጿል። የጥበብ ዝግጅቱ ከቀኑ 8:00 እስከ 11:00 በኩሪፍቱ አፍሪካን ቪሌጅ በሚገኘው የጥበብ ጋለሪ እንደሚካሄድ ተመላክቷል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in TelegramViews growthHide views growth
Views growth
Hours after publication
Show as table
| Hours after publication | Views |
|---|---|
| 0 h | 0 |
| 3 h | 2,680 |
| 6 h | 3,390 |
- After 6 hours3,390
- Total to date3,390
አሐዱ ባንክ የ2 ሚሊዮን ዩሮ የውሃ፣ የንፅሕና እና የአረንጓዴ ፋይናንስ የብድር ፕሮግራም በይፋ አስጀመረ። አሐዱ ባንክ ከዓለም አቀፉ ተቋም Aqua for All ጋር በመተባበር ለውሃ አቅርቦት፣ ለንፅሕና አጠባበቅ እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል የ 2 ሚሊዮን ዩሮ (Ahadu WASH Impact Loan እና አካታች አረንጓዴ ፋይናንስ) የብድር ፕሮግራም በይፋ አስጀምሯል። በስምምነቱ መሠረት ከጠቅላላው በጀት 1.5 ሚሊዮን ዩሮ በአሐዱ ባንክ የሚሸፈን ሲሆን፣ ቀሪው 500,000 ዩሮ ደግሞ በ Aqua for All የቀረበ ነው። ፕሮግራሙ በቀጥታ ለተጠቃሚዎች ከሚሰጠው ብድር ባሻገር፣ ለአምስት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ለአንድ የኅብረት ሥራ ማኅበር የጅምላ ብድር በማቅረብ አገልግሎቱ በመሠረታዊ ማኅበረሰብ ደረጃ ለሚገኙ ቤተሰቦችና አነስተኛ ንግዶች እንዲዳረስ እንደሚደረግ የአሐዱ ባንክ የጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ እና ገጠር ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ በለጠ ፍንታዬ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል። በፕሮግራሙ አራት ዋና ዋና የብድር አገልግሎቶች ያብራሩት አቶ በለጠ ንግድ ብድር በውሃና ንፅሕና ዘርፍ ለተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች የአገልግሎት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚሰጥ ሲሆን የWASH አጋር ተቋማት ብድር ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ለቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚቀርብ የጅምላ ብድር እና የውሃ አገልግሎት ተቋማት የእድገት ብድር የውሃ አቅርቦት መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና ለማዘመን የሚውል በተመሳሳይ የWASH እና አካታች አረንጓዴ ፋይናንስ ብድር እንደ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የውሃ መሳቢያ ሥርዓቶችን የመሳሰሉ ለአካባቢ ጥበቃና ታዳሽ ኃይል የሚውሉ ኢንቨስትመንቶችን የሚደግፍ ነው ተብሏል። ባንኩ "ከብዙዎች ለብዙዎች" በሚለው መሪ ቃሉ መሠረት፣ ይህ የፋይናንስ አቅርቦት የማኅበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻልና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተገልጿል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramበእንስሳት ላይ የሚደረግ ዘፈቀዳዊ የመድኃኒት አጠቃቀም በወተት፣ በእንቁላልና በሥጋ አማካኝነት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን እያባባሰ መምጣቱ ተገለጸ በኢትዮጵያ የእንስሳት ህክምና ተቋማት በበቂ ሁኔታ ባለመስፋፋታቸው ምክንያት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ በዘፈቀደ የሚጠቀሟቸው ህገወጥ መድኃኒቶች በሰው ጤና ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ ። በግብርና ሚኒስቴር የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ተጠሪ አቶ ጋሻው አዳነ ለብስራት ሬዲዮ እንደገለፁት አግባብነት የሌለው የመድኃኒት አጠቃቀም ከሰው ልጆች ባለፈ በእንስሳት ላይም በስፋት እየታየ ይገኛል ። አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ያለ ሐኪም ምርመራ ህገወጥ መድኃኒቶችን ገዝተው መጠቀማቸው በእንስሳት ጤናና የምርት ጥራት ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው ብለዋል ። በዚህም የተነሳ እንደ ወተት ፣እንቁላል እና ሥጋ ባሉ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች አማካኝነት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች እየተባባሱ መሆናቸዉ እና አሳሳቢ የህብረተሰብ ጤና ችግር እየሆኑ መምጣታቸዉ ተገልጿል ። የችግሩን ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢነት የሚያሳየው የዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2024 ያወጣው ጥናት እንዳመላከተዉ በዓለም ደረጃ ከተሸጠው አጠቃላይ መድኃኒት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ጥቅም ላይ የዋለው ለሰው ምግብነት ምርት በሚሰጡ እንስሳት ላይ ነው ። በመባ ወርቅነህ #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramየእስራኤሉ ጋዲ አይዘንኮት መንግስት ለመመስረት በሚያደርጉት ጥረት የመጀመሪያውን አጋር አገኙ የቀድሞው የእስራኤል ጦር አዛዥ ጋዲ አይዘንኮት የሚመሩት ያሻር ፓርቲ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ቀጣዩን መንግስት ለመመስረት በሚያደርገው ጥረት ከቀኝ ዘመሙ ተቃዋሚ ፓርቲ Israel Our Home ጋር የጥምረት ስምምነት ለመፈራረም መስማማቱን አስታውቋል። ፓርቲው ከአቪግዶር ሊበርማን ጋር ከተወያየ በኋላ የደረሰበት ይህ ስምምነት፣ ከምርጫው በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው የጥምረት ቃል ኪዳን ነው። ጥቅምት 27 በተካሄደው ምርጫ የትኛውም ፓርቲ 61 መቀመጫዎችን ማግኘት ባለመቻሉ የእስራኤል ፓርላማ ህዳር 10 ቀን ቃለ መሃላ የፈጸመው አዲስ መንግስት ሳይመሰረት ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ መንግስት እንዲመሰርቱ ለአይዘንኮት ኃላፊነት ሰጥተዋል። ቤንጃሚን ኔታንያሁ በምርጫው የፓርላማ አብላጫ ድምጻቸውን ቢያጡም በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እየቀጠሉ ይገኛሉ። አይዘንኮት በተሰጣቸው የ28 ቀናት የጊዜ ገደብ መሰረት መንግስት ለመመስረት እስከ ታህሳስ 6 ቀን ድረስ ጊዜ ያላቸው ሲሆን፣ አስፈላጊ ከሆነም የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ ይችላሉ። አይዘንኮት መንግስት መመስረት ካልቻሉ ኔታንያሁ ዕድሉ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ሁለቱም መንግስት መመስረት ካልቻሉ ግን በመጪው ዓመት ሌላ ምርጫ ይካሄዳል። በሚኪያስ ጸሐዬ #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramየባቢሌን የተፈጥሮ ድንጋይ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ስራዎች ሊጀመሩ ነው በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በባቢሌ ከተማ የሚገኘውንና የከተማዋ ልዩ መለያ የሆነውን የባቢሌ የተፈጥሮ ድንጋይ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የቅድመ ጥናትና የልማት ሥራዎች ሊጀመሩ መሆኑ ተገለጸ። በዓመት እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን የሚስበው ይህ የተፈጥሮ መስህብ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ እንዲለማ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን የባቢሌ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መፍቱሃ ሲራጅ ለብስራት ሬዲዮ ገልጸዋል። ኃላፊዋ እንዳሉት ስፍራውን ለማልማትና ያለውን የቱሪዝም አቅም በሙሉ ለመጠቀም ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ጥያቄ ቀርቧል። የልማትና የምርምር ሥራዎቹ ዋነኛ ዓላማ የተፈጥሮ መስህቡን ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ ማድረግ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግና ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መሆኑም ተጠቁሟል። በቀጣይም የዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ምዝገባን ለማሳካት አስፈላጊውን ጥናት ለማካሄድ መታቀዱን ኃላፊዋ አስረድተዋል። በመባ ወርቅነህ #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramበባንግላዴሽ የጨርቃጨርቅ ሰራተኞች ለሳምንታት የዘለቀ ተቃውሞ ካደረጉ በኋላ የ36 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ አገኙ በባንግላዴሽ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ሰራተኞች ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ ካካሄዱ በኋላ የ36 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገላቸው ተገልጿል። የሀገሪቱ የደመወዝ ቦርድ ሰብሳቢ ረቡዕ ዕለት እንደገለጹት፣ የዘርፉ ዝቅተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ከ12,500 ታካ ወይም 100 ዶላር ወደ 17,500 ታካ ወይም 136 ዶላር እንዲያድግ ተወስኗል። በታህሳስ ወር ተግባራዊ የሚሆነው ይህ ጭማሪ ሰልፈኞቹ ከጠየቁት 30,000 ታካ በታች በመሆኑ ሰራተኞቹ ውሳኔውን ስለመቀበላቸው በግልጽ አልታወቀም። ይሁን እንጂ በቦርዱ የሰራተኞች ተወካይ የሆኑት ባቡል አክተር ሰራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። በዓመት ወደ 38 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኘው የባንግላዴሽ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ለአራት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የወጪ ንግድ አራት አምስተኛውን ይሸፍናል። በሚኪያስ ጸሐዬ #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramየፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመቃወም በፖሊስ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ ዛላ ጋልማ ወረዳ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማስፈፀም በተሰማራ የፖሊስ አባል ላይ የአካል ጉዳት ለማድረስ የሞከረ ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን ፖሊስ አስታወቀ። የዛላ ጋልማ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አማኑኤል ከበደ እንደገለጹት፤ ተከሳሽ ሞላ ማምር የተባለው ግለሰብ በወረዳው ፍርድ ቤት በተከሰሰባቸው ሦስት ክሶች ምክንያት የተላለፈውን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልቀበልም በማለት እምቢተኝነት አሳይቷል። በተጨማሪም ትዕዛዙን ለማስፈፀም በተሰማራው የፖሊስ አባል ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲሞክር በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል። ፖሊስም የተፈጸመውን ድርጊት በማስረጃ በማረጋገጥ የምርመራ መዝገቡን ወዲያውኑ ዛላ ጋልማ ወረዳ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት መላኩን እና ጽሕፈት ቤቱም በሕግ አስከባሪ አካል ላይ ጉዳት ለማድረስ በመሞከር ወንጀል ክስ መመሥረቱን አመላክተዋል። ዛላ ጋልማ ወረዳ ፍርድ ቤት በፍትሕ ጽሕፈት ቤቱ የተመሠረተውን ክስ መርምሮ፣ ሕዳር 11 ቀን 2019 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ሞላ ማምር የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባለመቀበል እና በጸጥታ አካል ላይ ጉዳት ለማድረስ በመሞከሩ የፍትሕ ሂደቱ ላይ ችግር መፍጠሩን አረጋግጧል። በዚህም መሠረት በ4 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ምክትል ኢንስፔክተር አማኑኤል ከበደ ገልጸዋል። ማንኛውም ሰው በወንጀል ሊጠረጠር እና ሊከሰስ ይችላል። ንጽሕናውን የሚያረጋግጠው በፍትሕ ሂደት ብቻ መሆኑ እየታወቀ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልቀበልም ብሎ በጸጥታ አካል ላይ ጉዳት ለማድረስ መሞከር የሚያስከትለው ተጠያቂነት ከባድ መሆኑንም ምክትል ኢንስፔክተር አማኑኤል ከበደ ጨምረው ገልጸው ሕብረተሰቡ ሕግን አክብሮ ለሕግ እንዲታዘዝ አሳስበዋል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramቡርኪናፋሶ 61.5ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ግዙፍ የቴክኖሎጂ አካዳሚ መርቃ ከፈተች ቡርኪናፋሶ የወደፊት መሐንዲሶችን ለማፍራት፣ ሳይንሳዊ ነፃነትን ለማጎልበት እና የኢንዱስትሪ እድገትን ለማፋጠን ያለመ 61.5 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ የቴክኖሎጂ አካዳሚ እ.ኤ.አ. ኅዳር 23 ቀን 2026 መርቃ ከፈተች። ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ፣ በሀገሪቱ ብሔራዊ በጀት በተመደበ 37.37 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እና በ11 ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀውን አካዳሚ ቴክኖሎጂክ ዱ ፋሶ የተሰኘውን ተቋም በይፋ መርቀው ከፍተዋል። 60 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ካምፓስ፣ በመጀመሪያ ዙር 250 ተማሪዎችን ተቀብሎ የኒውክሌር ምህንድስና፣ አቪዬሽን (ኤሮኖቲክስ)፣ ማዕድን ማውጣት፣ ብረታ ብረት፣ ኢነርጂ እና የሳይበር ደህንነትን ጨምሮ በ11 ስትራቴጂካዊ የትምህርት መስኮች ስልጠና ይሰጣል። የሀገሪቱ አመራሮች ተቋሙን የገነቡት በሀገር ውስጥ የበቀለ የቴክኒክ ባለሙያዎችን ለማፍራትና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ይበልጥ ለማጠናከር በማለም ነው። ሰላማዊ ነጋሲ #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramከ10 ዓመታት በላይ የቆየ የኤሌክትሪክ ጥያቄ ምላሽ ማገኘቱን እና 402 አባወራዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸው ተነገረ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ አስተዳደር ፈረስ ወጋ አካባቢ የሚኖሩ ከ400 በላይ አባወራዎች ከአስር ዓመታት በላይ ሲጠብቁት የቆዩትን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል ነዋሪዎቹ በወቅቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ለማስዘርጋት የተጠየቀውን የግምት ወጪ መሸፈን ባለመቻላቸው ከ10 ዓመታት በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳያገኙ ቆይተዋል።የነዋሪዎቹን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስና የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተግባር ላይ ባዋለው የአሠራር አማራጭ አማካኝነት የመሠረተ ልማት ግንባታውን አከናውኗል። ለፕሮጀክቱ አገልግሎቱ 12 ሚሊዮን 289 ሺህ 264 ብር ሲመድብ፣ ማኅበረሰቡም 1 ሚሊዮን 188 ሺህ 825 ብር በማዋጣት በጋራ የመሠረተ ልማቱ እንዲዘረጋ አስችሏል።በፕሮጀክቱ 4 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅና 3 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ተዘርግቷል። በተጨማሪም እያንዳንዳቸው 200 ኪሎ ቮልት አምፒየር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች ተገጥመው ለአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረቡ ይገኛሉ።የተዘረጋው መሠረተ ልማት ለ402ቱ አባወራዎች ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ወደፊት በአካባቢው ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ፈላጊዎችንም ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ያለው ነው የተባለ ሲሆን ይህም አሁን የተገኘውን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ በአካባቢው ለሚኖረው ቀጣይ የልማት እድገት መሠረት ይጥላል። የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ከብርሃን አቅርቦት ባለፈ የቤተሰብ ኑሮን ለማሻሻል፣ የትምህርትና የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማነቃቃትና ማኅበራዊ ለውጥን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና አለው።ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የዜጎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ አገልግሎቱን ወደ ተጨማሪ አካባቢዎች ለማዳረስና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። በተገነባው መሠረተ ልማት ላይ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥና ተጨማሪ ዜጎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማኅበረሰቡ መሠረተ ልማቱን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ አገልግሎቱ ጥሪ ያቀርባል። #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegramተገቢ ያልሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የልጅነት እርግዝናን እያባባሰ እንደሚገኝ ተጠቆመ በባሌ ዞን የልጅነት እርግዝናን ለመቀነስ በተሠሩ ሥራዎች ጥሩ ውጤቶች ቢታዮም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል። በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል የጤና ዞን ምክትል የሰው ሀይል አስተዳደርና የጤና ተቋም ምክትል ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ቱጁባ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በዞኑ የልጅነት እርግዝና ምጣኔ በ2018 በጀት አመት ከነበረበት 17.7 በመቶ አሁን ላይ ወደ 14.9 በመቶ ቀንሷል። ይህም በተከታታይ ዓመታት የልጅነት እርግዝና መጠን መቀነስን ያሳያል ያሉ ሲሆን ለጉዳዮ መፍትሄ ለማምጣት ግን ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።ከ10 እስከ 15 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴት ታዳጊዎች ለልጅነት እርግዝና ተጋላጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ምክትል ሀላፊው ጠቁመዋል። በዞኑ የሚታየውን የልጅነት እርግዝና ችግር ከሚያባብሱ ምክንያቶች መካከል የማህበራዊ ሚዲያና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንደኛው ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።ማህበራዊ ሚዲያ በታዳጊ ወጣቶች አስተሳሰብ፣ ባህሪ እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ በሚፈጥረው ጫና የተነሳ ለልጅነት እርግዝና መባባስ አጋላጭ መንስኤ ሆኗል ነው የተባለው። እንደ ቲክቶክ፣ቴሌግራም እና ፌስቡክ ባሉ መተግበሪያዎች ላይ የሚለቀቁ ወሲባዊ ይዘቶች ታዳጊዎች ያለዕድሜያቸው የወሲብ ፍላጎት እንዲያድርባቸውና ለሙከራ እንዲነሳሱ ያደርጋሉ ተብሏል ።ችግሩን ለመከላከል እና የባህሪ ለውጥን ለማምጣት በትምህርት ቤቶች አካባቢ በወጣቶች ጤና ቡድን በኩል ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል። እንዲሁም ታዳጊ ሴቶችና ወጣቶች ያልታቀደ እርግዝናን እንዲከላከሉ፣ ጤናቸውን እንዲጠብቁ እና የወደፊት ሕይወታቸውን በዕቅድ እንዲመሩ በጤና ጣቢያዎችና በጤና ኬላዎች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በቅድስት ደጀኔ #ዳጉ_ጆርናል
Open in Telegram