Account

Posts of Tirita 97.6 FM Radio

newest first

#6943Photo

የቡና ባንክ የማይንቀሳቀሱ ብድሮች መጠን ወደ 4.28% ዝቅ ማለቱ ተገለጸ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) ቡና ባንክ በ2025/26 የበጀት ዓመት የማይንቀሳቀሱ ብድሮች መጠን ወደ 4.28 በመቶ ዝቅ ማለቱን ይፋ አድርጓል። ባንኩ ባቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደተመለከተው፣ ይህ ውጤት የብድር ጥራትን ለማሻሻልና የፋይናንስ ጤናማነቱን ለማጠናከር የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ነው። የብድር አስተዳደሩ መሻሻል የፈጠረው መደላድል፣ ባንኩ ከታክስ በፊት 3.292 ቢሊዮን ብር ትርፍ እንዲያስመዘግብ አስችሎታል ተብሏል። ከትርፉ ባሻገር የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ በ20.2 በመቶ ዕድገት 53.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ጠቅላላ ሀብቱም በ25.9 በመቶ በማደግ 82.557 ቢሊዮን ብር መድረሱን በሪፖርቱ ተገልጿል። የሀብትና የተቀማጭ ገንዘብ መጠን መጨመርን ተከትሎ፣ ባንኩ በዚሁ በጀት ዓመት ካፒታሉን ወደ 11.283 ቢሊዮን ብር ማሳደስ የቻለ ሲሆን፤ ይህንን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ለማሳካት ባንኩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2026 ድረስ 3,823 ሠራተኞችን በሥራ ላይ ማሰማራቱ በሰነዱ ተጠቅሷል። ይህ የአፈጻጸም ሪፖርት በአዲስ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል በተካሄደ ጠቅላላ ስብሰባ ለባለአክሲዮኖችና ለታዳሚዎች ቀርቧል። በቀጣይም ባንኩ በ2026/27 የበጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ፣ የብድር፣ የትርፍና የካፒታል ዕድገት ግቦችን በማስቀመጥ እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል። (ህዳር 20፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ ትርታ ሪፖርተር 🔹 Facebook: facebook.com/Tirita97.6FM 🔹 YouTube: youtube.com/@tiritaradio 🔹 Telegram: t.me/tiritaradio ​📞 ለበለጠ መረጃ እና ቅሬታ፦ 📩 SMS: 9760 ☎️ ስልክ፦ 0116 68 46 22 | 0116 66 35 82

Open in Telegram
Views21−53%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—
#6941Photo

የኢትዮጵያን እና ሩሲያም የባህል ትስስር የሚያጠናክር የዳንስ ትርኢት በአዲስ አበባ ተካሔደ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) የሩሲያ ብሔራዊ የዳንስ ቡድን “ኮስትሮማ” እና የአዲስ አበባ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር የዳንስ ቡድን በጋራ ያዘጋጁት የዳንስ ትርኢት በአዲስ አበባ ሕፃናትና ወጣቶች ቲያትር ህዳር 19 ምሽት ተካሂዷል። ዝግጅቱ የሩሲያን ባህላዊ ዳንስ እና ጥበብ ለኢትዮጵያ ተመልካቾች ለማስተዋወቅና የሁለቱን ሀገራት የባህል ልውውጥ ለማጠናከር ያለመ ነው። በመድረኩ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፣ መርሐ ግብሩ የታሪክ፣ የማንነትና የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት መገለጫ ነው። የጋራ ትርኢቱ፦ የሀገር ውስጥ ተወዛዋዦች ከዓለም አቀፍ ልምድ እንዲቀስሙና የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበብ ለዓለም አቀፍ ታዳሚያን ለማስተዋወቅ ዕድል መፍጠሩን ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል። አዲስ አበባን የአፍሪካ ግንባር ቀደም የኪነ-ጥበብና የባህል ማዕከል ለማድረግ ግልጽ ግብ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል። ለዚህም የባህል ተቋማትን በማጠናከር በመሠረተ-ልማቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን የማስፋፋት ሥራ መጠናከሩን አመልክተዋል። በብሪክስ አጋርነት ማዕቀፍ የተካሄደው ይህ ዝግጅት በሩሲያና በአፍሪካ መካከል ለሚኖረው የባህል ትስስር አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚከፍት ተጠቁሟል። በቀጣይም በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በፊልም፣ በሥነ-ሥዕልና በሥነ-ጽሑፍ ዘርፎች የሁለቱ ሀገራት ትብብር እንደሚቀጥል ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር ተስፋቸውን ገልጸዋል። --- ✍በ ብርቱካን ዋልተንጉሥ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) 🔹 Facebook: facebook.com/Tirita97.6FM 🔹 YouTube: youtube.com/@tiritaradio

Open in Telegram
Views36−20%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#6940Text

ከዓመታዊ የደም ፍላጎት መሸፈን የተቻለው 43.1% ብቻ መሆኑ ተገለጸ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ከሚፈልገው ዓመታዊ የደም መጠን መሸፈን የተቻለው 43.1 በመቶውን ብቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት አስታውቋል። አገልግሎቱ ኅዳር 19 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ያስጀመረው «ዘ ሂውማን ቼይን» ዘመቻ ይህንኑ እጥረት ለማቃለል ያለመ ነው። ባንኩ ከ"አቦት" ጋር በመተባበር ያቀረበው ዘመቻ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ደም እንዲለግሱና ቋሚ ለጋሽ እንዲሆኑ የማነሳሳት ስራ ይሰራል ተብሏል። የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት፣ ሀገራት መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቢያንስ ከሕዝቡ 1% ወይም ከ1,000 ሰዎች አሥሩ ደም መለገስ እንዳለባቸው ያሳያል። በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ በዓመት 1.1 ሚሊዮን ዩኒት ደም ትፈልጋለች ተብሏል። ሆኖም አሁን በዓመት የሚሰበሰበው ወደ 476 ሺህ ዩኒት የሚጠጋ ደም ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል። የባንኩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደገለጹት፣ የሚሰበሰበው ደም ከዝቅተኛው መስፈርት ግማሽ ያህሉ ብቻ ነው። ዶክተር አሸናፊ አክለውም፣ መስፈርቱን የሚያሟላ እያንዳንዱ ወጣት በዓመት 3 ጊዜ ቢለግስ ክፍተቱ በእጅጉ እንደሚሞላ አመልክተዋል። ደም ልገሳ በወሊድ ጊዜ ችግር የሚገጥማቸውን እናቶች፣ ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸውንና የደም ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ለማዳን ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው ተብራርቷል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መረጃ ለማግኘትና ደም ለመለገስ በነፃ የስልክ መስመር 8040 መደወል ወይም በአቅራቢያ ባሉ የደም ባንክ ጣቢያዎች መለገስ ይችላሉ ተብሏል። (ህዳር 20፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ ንጉሡ በሪሁን 🔹 Facebook: facook.com/Tirita97.6FM 🔹 YouTube: youtube.com/@tiritaradio 🔹 Telegram: t.me/tiritaradio ​📞 ለበለጠ መረጃ እና ቅሬታ፦ 📩 SMS: 9760 ☎️ ስልክ፦ 0116 68 46 22 | 0116 66 35 82

Open in Telegram
Views40−11%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#6935Text

ኑዛዜ በሕግ ተቀባይነት እንዲኖረው መስፈርት እና ቅርጹን ማሟላት እንደሚገባ ባለሙያዎች ገለጹ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) ማንኛውም ዜጋ የሚያደርገው ኑዛዜ በሕግ ፊት ሙሉ ተቀባይነት እንዲኖረው ሕጋዊ መስፈርቶችንና የቅርጽ ሥርዓቶችን ማሟላት እንደሚገባው የሕግ ባለሙያዎች አሳስበዋል። ኑዛዜን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ፊት መፈጸም ከጊዜ በኋላ ከሚነሱ የመጭበርበር ስጋቶችና አላስፈላጊ የፍርድ ቤት ክርክሮች እንደሚያድን ተመላክቷል። በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ዘላለም ሙሉነህ እና ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሜሮን ሱራፌል ለትርታ ኤፍ ኤም በሰጡት ማብራሪያ፣ ኑዛዜ በሕግ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረው ሊሟሉ የሚገባቸውን መሠረታዊ መስፈርቶችና የአፈጻጸም ጥንቃቄዎች አስረድተዋል። በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 881 መሠረት በ4 ምስክሮች ፊት የሚደረግ ኑዛዜ በሂደት ምስክሮች ቢክዱ ወይም ሰነዱ አጠራጣሪ ቢሆን፣ ለፎረንሲክ፣ የፊርማ እና የፊደል አጣጣል ምርመራ እና ለረጅም ክርክር ሊዳርግ እንደሚችል አቶ ዘላለም ገልጸዋል። በአንጻሩ በአንቀጽ 882 መሠረት ውል ለማዋዋል ሥልጣን ባለው አካል በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ፊት የሚደረግ ኑዛዜ፣ እምነት በተጣለበት የመንግሥት ተቋም የሚረጋገጥ በመሆኑ አከራካሪ እንዳልሆነና ከመጭበርበር እንደሚታደግ ጠበቃው አብራርተዋል። በሌላ በኩል ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሜሮን ሱራፌል፣ "ኑዛዜ ሕጋዊ ውጤት እንዲኖረው ተናዛዡ ቢያንስ ዕድሜው ከ16 ዓመት በላይ የሆነ፣ ኑዛዜው በነጻ ፈቃዱ የተደረገረገ እና በሕጉ የተፈቀደውን የቅርጽ ሥርዓት የጠበቀ መሆን አለበት" ብለዋል። ሦስቱ የኑዛዜ ዓይነቶች ማለትም ግልጽ፣ በእጅ ጽሑፍ የሚዘጋጅ እና የቃል ኑዛዜ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ሕጋዊ መስፈርቶች እንዳሏቸው ጠበቃ ሜሮን አስረድተዋል። ቀደም ብለው ኑዛዜ ያደረጉ ሰዎች ኑዛዜያቸውን በሕግ ባለሙያ ማስመርመር እንዳለባቸው የመከሩት ጠበቃ ሜሮን፣ በምርመራውም ኑዛዜው በሕጉ ከተፈቀዱት ዓይነቶች በአንዱ መሠረት መደረጉን ማረጋገጥ እንደሚገባ አክለዋል። በሰነዱ ላይ በውል አዋዋይ ፊት መነበቡን የሚገልጽ ሐረግ መኖሩን፣ እንዲሁም የተናዛዡና የምስክሮች ፊርማና ቀኑ በትክክል መስፈሩን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። በኑዛዜው ላይ ጉድለት ከተገኘ ችግር እስኪከሰት መጠበቅ ሳያስፈልግ፣ ተናዛዡ በሕይወት እያለ ከሕግ ባለሙያ ጋር በመሆን ኑዛዜውን ማስተካከል ወይም አዲስ ማዘጋጀት እንደሚገባው ተመላክቷል። (ህዳር 20፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ ብርቱካን ዋልተንጉሥ

Open in Telegram
Views42−6%vs avg
Forwards—
Reactions3
Comments—
#6933Text

7 የአካል ጉዳተኞች ለማኅበረሰብ ባደረጉት አስተዋጽኦ በ«አካታች አዋርድ» ተሸለሙ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞችን ቀን ምክንያት በማድረግ ኅዳር 19 ቀን 2019 ዓ.ም. በተካሄደው «አካታች አዋርድ» ለማኅበረሰብ አስተዋጽኦ ያበረከቱ 7 የአካል ጉዳተኞች እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ተሸላሚዎቹ ጉዳታቸው ሳያግዳቸው በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች እየሠሩ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል። የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ለአካል ጉዳተኞችም ሆነ ጉዳት ለሌለባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የጎላ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ያካተተ ነው። የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ከ'ቱ ራይዝ መልቲ ሚዲያ' ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ዝግጅቱ በዓለም ለ35ኛ፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀን ተከትሎ ነው የተከናወነ ነው ተብሏል። መርሐ ግብሩን አስመልክቶ የተናገሩት የቱ ራይዝ መልቲ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ መና ፍስሃ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ያሉ የአካል ጉዳተኞች ከጉዳታቸው በተጨማሪ ከቤተሰብና ከማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። መና ፍስሃ አክለውም፣ ተሸላሚዎቹ ይህን ሁሉ ተቋቁመው ለሀገር የሚተርፍ ሥራ በመሥራታቸው ዕውቅና እንደተሰጣቸው አመልክተዋል። ከዚህ አሉታዊ ተጽዕኖ ጋር በተያያዘ፣ አካል ጉዳተኝነት በየትኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል በመሆኑ ዕውቀትንና ችሎታን መጠቀም እንደሚገባ ተጠየቀ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አካል ጉዳ ተኝነት እንደ ዕርግማን መታየቱ ዕውቀታቸውንና ችሎታቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ማነቆ እንደሆነባቸው ተገልጿል። (ህዳር 20፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ ሜሮን ጳውሎስ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) 🔹 Facebook: facebook.com/Tirita97.6FM 🔹 YouTube: youtube.com/@tiritaradio 🔹 Telegram: t.me/tiritaradio ​📅 ህዳር 20 ቀን 2019 ዓ.ም. ​📞 ለበለጠ መረጃ እና ቅሬታ፦ 📩 SMS: 9760 ☎️ ስልክ፦ 0116 68 46 22 | 0116 66 35 82

Open in Telegram
Views47+5%vs avg
Forwards—
Reactions3
Comments—
#6928Text

የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ዕድሎችን ወደ ተግባራዊ ስምምነት ለመቀየር ያለመ መሆኑ ተገለጸ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ያሉትን ዕድሎች ወደ ተግባራዊ የንግድ ስምምነቶች ለመቀየር ያለመ እንደሆነ፤ የኮሜርሺያል ኖሚኒስ ዋና የቢዝነስ ኦፊሰር አቶ ገብረሕይወት ጌታሁን ገልጸዋል። አቶ ገብረ ህይወት እንዳሉት፤ መድረኩ በፋይናንስ እና ባንክ፣ በሪል እስቴት፣ በጤናና ሕክምና፣ በንግድ እና ስርጭት እንዲሁም በኢንዱስትሪ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ወደ ገበያ ያቀርባል። ፎረሙ ኢትዮጵያን እንደ ተመራጭ የንግድና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማስተዋወቅም ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል። ከ600 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችና የንግድ ባለሙያዎች የተገኙበት ይህ መድረክ ትላንት ሕዳር 19 ተጀምሯል። "ንግድና ዕድል" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው ፎረም ዓላማው በንግድ ተዋናዮች መካከል ዘላቂ የንግድ ግንኙነቶችን መፍጠር ነው ተብሏል። በመድረኩም ከ200 በላይ የንግድ መሪዎች፣ ከ75 በላይ ባለሀብቶችና ከ500 በላይ የፋይናንስ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከእነዚህ ተሳታፊዎች ባሻገር የዲፕሎማሲ ተወካዮች፣ የንግድ ተቋማትና የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊዎችም በዝግጅቱ ታድመዋል። ለተሳታፊዎቹ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ አቅም፣ የንግድ ዕድሎችና የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያስተዋውቁ ውይይቶች እየተካሄዱ ሲሆን፤ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት የኤግዚቢሽን አውደ ርዕይና ቀጥተኛ የንግድ ለንግድ ግንኙነት መድረኮችም የዝግጅቱ አካል መሆናቸው ተገልጿል። አቶ ገብረሕይወት ጌታሁን ፎረሙ በ"Connect, Invest, Grow" መፍክር ተጨባጭና ዘላቂ ትብብሮችንና የንግድ ትስስሮችን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። ኮሜርሺያል ኖሚኒስ ከኔክሳ ቢዝነስ ግሩፕ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ዓለም አቀፍ ፎረም ዛሬ ሕዳር 20 ቀን 2019 ዓ.ም. የዲፕሎማሲና የንግድ መሪዎች በሚገኙበት የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ይጠናቀቃል። (ህዳር 20፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ አህመዲን ሸረፋ

Open in Telegram
Views53+18%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#6925Photo

21ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል "ልምዱን የሚመጥን የተቀናጀ ዝግጅት አልነበረውም" የሚል አስተያየት ቀረበበት 👉ብቁ ባለሙያ ለማፍራት ቅድሚያ እንደሚሰጥና ክፍተቶቹን በቀጣይ እንደሚያስተካክል ተገልጿል (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የ21 ዓመታት ረጅም ልምድ ቢኖረውም የልምዱን ያህል "የተቀናጀ ዝግጅት አልነበረውም" ሲሉ በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪዎች ለትርታ ኤፍ ኤም ተናግረዋል። የሽልማት መድረኩና የፕሮግራሙ ይዘት ተወዳዳሪውንና ታዳሚውን በሚመጥን ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ እንደነበርም ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ቲያትር እና ሲኒማ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ ኃላፊ አቶ ማንያዘዋል ጌታቸው ለቅሬታው በሰጡት ምላሽ በፌስቲቫሉ መነቃቃት መታየቱን ገልጸው፤ የተሳትፎ ፍላጎትም ከፍተኛ እንደነበረ አብራርተዋል። ዝግጅቱ ከተከናወነበት ከፍ ባለ ደረጃ ያልተከናወነበትን ምክንያት ሲገልጹም፤ ቅሬታው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣዩ ዓመት ዓመት ክፍተቱን አስተካክሎ የተሻለ ፌስቲቫል እንደሚያካሒድ ቃል ገብተዋል። የአዲስ አበባ ቲያትር እና ሲኒማ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ ኃላፊ አቶ ማንያዘዋል አክለውም "ፌስቲቫሉ ፊልሞችን ከማወዳደር ያለፈ ግብ አለው" ብለዋል። የተመልካቹን የፊልም ፍላጎት ማሟላት እና ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት እንዲሁም የኢትዮጵያ ፊልሞችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ማብቃት ከፌስቲቫሉ ግቦች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። (ህዳር 19፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ አህመዲን ሸረፋ

Open in Telegram
Views77+72%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#6924Text

ሞን ሪልስቴት በአየር ጤና አካባቢ ያስገነባቸውን 90 የንግድ ሱቆች አስረከበ (ትርታ 97.6 ኤፍ ኤም) ሞን ሪልስቴት እና የገበያ ማዕከል ኃ.የተ.የግል ማኅበር አዲስ አበባ ከተማ በአየር ጤና አካባቢ ያስገነባቸውን 90 የንግድ ሱቆች ዛሬ ህዳር 19፥ 2019 ዓ.ም. ሥራ አስጀምሯል። ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ ሦስት ወር ቀድሞ ተጠናቆ ለባለቤቶች መረከቡን ድርጅቱ ገልጿል። የሞን ሪልስቴት የሽያጭ ክፍል ሱፐርቫይዘር አቶ አትናቲዎስ ጥላሁን እንደተናገሩት በእያንዳንዱ ፎቅ 22 ሱቆች ተሠርተዋል። ድርጅቱ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ በዘርፉ ሲሠራ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ አሁንም በአካባቢው 4 ትላልቅ የመኖሪያ አፓርታማ ሕንጻዎችን በአንድ ጊዜ እየገነባ ይገኛል ተብሏል። የድርጅቱን ኃላፊዎች ወክለው የተናገሩት አቶ አብደላ መሃመድ የግንባታ ግብዓት ዋጋ መጨመርንና ጊዜያዊ ተግዳሮቶችን ማለፋቸውን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ከይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሐግብር ቀድሞ ለደንበኞች መቅረቡንም ጠቁመዋል። የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳኛቸው ሹመት ግንባታው የመኖሪያና የሥራ ቦታ ፍላጎትን እንደሚያሟላ ተናግረዋል። የአካባቢውን ልማትና መሠረተ-ልማት ግንባታ ማገዙንም አመልክተዋል። የገበያ ማዕከሉ በአየር ጤና ከመመሥረቱ በተጨማሪ የዘነበወርቅ፣ የካራ፣ የዓለም ባንክ፣ የቤተልና የጦር ኃይሎች ነዋሪዎችን ያገለግላል። ነዋሪዎቹ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችሉበት የገበያ ቦታ እንደሚሆን በመድረኩ ተገልጿል። (ህዳር 19፥ 2019 ዓ.ም.) --- ✍በ በፍቅር ግዛቸው

Open in Telegram
Views57+27%vs avg
Forwards—
Reactions1
Comments—