ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የፈጅር ሶላት ስገዱ የሚል ዘመቻ አስጀምሯል። የጧት ሶላት ፀሐይ ሳይወጣ የሚሰገደውን በእስልምና እምነት ተከታዮች የቀኑ የመጀመሪያ ሶላት ማለት ነው። እና ምን ትዝ አለኝ.... ወሎየ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን በጧት ለመሳለም "አላሁ አክበር" ሲል ቀስቅሰኝ የሚለው ነገር። የመስጊድ አዛን ይቀሰቅስሃል ወደመድሃኒአለም ትሄዳለህ ሙስሊሙም ወደመስጊድ። ስትመለስ ቡና ትጠራራለህ። የሆነ ሆኖ እንደአገር ሁላችንም በጧት ተነስተን ብንፀልይ ሳይሻል አይቀርም። በሉ አላሁ አክበር ሲል ቀስቅሱንና ሁላችንም በየፊናችን🙏 ይች አገር የምታስተኛ አልሆነችም😀
Open in TelegramPosts of Alex Abreham አሌክስ አብረሃም
«አቦ ስልጤ» የወራቤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ማይክሮባዮሎጂስት ነው። ነጃቶ ኡስማን ይባላል። አቦ ስለጤ የሚል የግጥም መድብሉን በስልጥኛ ቋንቋ ፅፎ በቅርብ ሊያቀርብ ነው። ጧት ሁሉም በየቋንቋው ብየ ከሰዓት ይሄን ማየቴ ደስ ብሎኛል። ይህን መድብል ያልገዛ ስልጤ የስልጤን ባህልና ወግ ለማሳደግ ምናምን ሲል እንዳልሰማው። ግዙት አበረታቱት.... እንደውም በድምፅ ሁሉ ከነአነባበቡ መስማት እንፈልጋለን! ጋዜጠኞች ጋብዙት! እ...ለቋንቋው እድገት ላበረከተው ድርሻም የስልጤ ህዝብና አስተዳደሩ 200 ካሬ ሜትር ዓይን ቦታ ጣል ቢያደርግበት ምን ይጎዳል? 😀 ስነፅሁፉን ቋንቋውን ያበረታታል እንደውም። ነጃቶ ኡስማን እንኳን ደስ ያለህ ቀላል ነገር አይደለም። አልነበብም ቋንቋየ ተገፋ ተደፋ እያለ ቁጭ ብሎ ለሚያለቃቅሰው ጀመዓ ሁሉ ምሳሌ ነህ! ለምን በኤአይ ተርጉመን አይሆንም እናነበዋለን! የራስህን ቋንቋ ፃፍበት ፣ ተጠበብበት ዛሬ የጀመርከውን ነገ ትውልድ ይቀጥለዋል። ቋንቋን ለነገርና ልዮነት ብቻ አይደለም ለጥበብ ለስነፅሁፍ👊
Open in Telegramአንዳንዴ! "የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማው) የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛው የስልጣን አካል መሆኑን የፓርላማ አባላት ራሳቸው ያውቁ ይሆን?" ብየ አስባለሁ። " ነው እንዴ?" እንዳትሉኝ ግን😀 በበኩሌ ከእንግጭላ ወረዳ የተመረጡ አንድ የተከበሩ ሚስኪን የፓርላማ አባልን ቁጭ አድርጋችሁ "እርሰዎኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመምረጥ፣ ህጎችን የማውጣት፣ በጀት የማጽደቅ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የአስፈጻሚ አካላትን የመጠየቅና የመቆጣጠር ስልጣን አለዎት። እንዲሁም የእርሶና መሰሎችዎ ስብስብ የሆነው ይሄ ፓርላማ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ እምነት ካጣ ከስልጣን የማንሳት መብት አለው" ብትሏቸው በድንጋጤ ራሳቸውን የሚስቱ ነው የሚመስለኝ። ብዙሀኑ የፓርላማ አባል ጠ/ሚንስትሩን ሪፖርት እንዲያቀርብና ጥያቄ እንዲመልስ በፓርላማው ታዞ የቀረበ ሳይሆን ጠ/ሚንስትሩ ፓርላማ የሚባለው ህንፃ ውስጥ በዐበል ለስብሰባ የጠራቸው ነው የሚመስሉት! ሲጨበጨብ ዞር ዞር ብለው የሚያጨበጮቡት ነገር ፣ የሚሽቆጠቆጡበት መንገድ...ጥያቄ ሲያነቡ ድምፃቸው እንደተሰጣ ልብስ የሚወዛወዝበት ጭንቀት 😀 ደግሞ ይሄን አንብባችሁ "እርሶ ስልጣን የሚለቁት መቸ ነው?" ትሉና አሌክስ አብርሃም ካልታወቁ አካላት ጋር ተባብሮ ሶስት ወር አሰረኝ እንዳትሉ😀
Open in Telegramወይኔ እኒህ ፍጥረቶች! (አሌክስ አብርሃም) በተደጋጋሚ ስለሴትና ወንድ ጉዳይ የምፅፈው ከእናንተ በላይ በነገሩ "ተሳትፎ ስላለኝ" "ባለድርሻ አካላት" ስለሆንኩ የሚመስላችሁ የዋሆች አላችሁ። ተሳስታችኋል። ሶስቱም ኤክሶቸ ጋር የተለያየነው ከጋብቻ በፊት "ሌላ ነገር" ከምትሉኝ ግደሉኝ በማለቴ ነው።በእርግጥ ሶስተኛዋ ጋር ሐሳቤን ቀይሬ ጫፍ ደርሸ ነበር። ለአዲስ ዓመት መግቢያ አብረን ልናድር ራት በልተን ስንዝናና የርችት ፍንዳታ ከተማውን ሞላው። "የኔ ማር ...ከተማው ሰላም አይመስለኝም " ብየ ተሰናብቻት ወደቤቴ ሄድኩ። ብዙ ስድብ በቴክስት ላከችልኝ "የወንድ አልጫ፣ ከነገ ጀምሮ ሱሪ እንዳትለብስ ምናምን..." እወዳት ስለነበር ከቀጣዮ ቀን ጀምሮ ቁምጣ ለበስኩ። የሆነ ሆኖ እንደቀደሙት ሁለቱ ትታኝ ሄደች። እኔን የካደ ሰው መቸም መጨረሻው አያምር፤ ሶስቱም እየሄዱ አገቡ😀 እና ስለሴትና ወንድ ለምን አብዝቸ እፅፋለሁ? የምፅፈው የእነዚህ ሁለት ፆታወች ኬሚስተሪ ፈፅሞ ስለማይገባኝ ነው። ባለፈው ከሰርቢያ አገር ቤልግሬድ ከምትባል ከተማ የመጣ ፋርማሲስት ሰውየ ጋር ተገናኝተን እያወጋን ነው። እንዲህ አለኝ 1999 በኮሶቮ ጦርነት ኔቶ ከተማችንን ለአራት ወር በጀት በሚሳኤል ደብድቧታል። ያልተጣለብን የቦንብ አይነት ያልተሞከረብን መሳሪያ አልነበረም። አንድ ቀን ጀቶች ሲመጡ የከተማው የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ እንድንደበቅ ሲጮህ የምሰራበት ፋርማሲ ውስጥ እኔና የፊት ክሬም ልትገዛ የመጣች ከዛም በፊት ደንበኛየ የነበረች ቆንጆ ብቻ ነበርን የነበርነው። በሩን ሮጨ ዘግቸ ከፋርማሲው ስር ወደነበረ የዕቃ ማከማቻ ምድር ቤት ወሰድኳትና ተደበቅን። ድብደባው ለድፍን 4 ሰዓታት የቆየ። የሚሰቀጥጥ ነበር። ቦንቡ ሲፈነዳ በንዝረቱ የተደረደሩ ካርቶኖች እንደግንብ ላያችን ላይ ይናዳሉ። በየት እንደሚገባ እንጃ ጭስ ይሸተናል ፣ ፋርማሲው ተቃጥሎ ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ሚሳኤል እያፏጨ ሲያልፍ እኛ ላይ ወደቀ እያልን ጭንቀቱን ልነግርህ አልችልም ....ብቻ አጠቃላይ ውርጅብኙ አልፎ ፀጥ ሲል ልብሳችንን ለባብሰን ያችን ቆንጆ ልጅ ሸኘኋት..." ብሎ ፈገግ አለ። እ? ....ልብሳችን...? "ልነግርህ አይደል....ከሁለት ወር በኋላ ይመስለኛል ወደፋርማሲው መጣችና እንደፀነሰችልኝ ነገረችኝ" አለ እእእእእእ በዚያ ጭንቅ..... ግራ ተጋብቸ ጠየኩ ....መልሱ አጭር ነበር ፍቅር ሚሳኤልና ፈንጅ ይፈራል ብለህ ነው?! ወይኔ በላቸው!
Open in Telegramሰማኒያ ቋንቋ፣ መቶ ቋንቋ ..ጩኸታችን ሌላ ነገር ነው። ደህና ነገር የተፃፈበት 5 ቋንቋ እንኳን የለንም። ከየገጠሩ አዲስ አበባ እንደገባ ጅንስ ይቀይራል ስካርቩን ጠምጥሞ "እኔ ምልሽ ወዴ" ሲል ይከርምና ለምን በቋንቋህ ባህልህን አታስነብበንም ስንል ተጨቁኘ ተገፍቸ ይልሃል። በቃ ይሄው ነፃ ነህ በፈለከው ቋንቋ ፃፍ ከተባለ ሰላሳ ዓመቱ!! ወፍ የለም! የሚሞክሩትን እንኳ አያበረታታም። እስቲ ከአማርኛ ውጭ የተፃፈ 3 ነፍስ ያለው መፅሐፍ ጠቁሙ...መፅሐፉ ይቅር ነፍስ ያለው አርቲክል? ጭፈራ ብቻ!!
Open in Telegramፌስቡክ በዚህ ሁለት ሳምንት ሶስት ፅሁፎቸንና አንድ ቪዲዮ አንስቶብኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ🙌 አንብቡ ተዝናኑ ባልኩ? ይመስለኛል በጣም እየሳቃችሁ ወይም እየተነጫነጫችሁ ኮሜንቱን በስህተት ሪፖርት ላይ እየፃፋችሁ ነው😀
Open in Telegramየአሜሪካ ፍቅር ግን... ኡኡኡኡኡ! (አሌክስ አብርሃም) አሜሪካ መኖር ቀላል መስሎ ነው አይደል የሚሰማችሁ? ይሄው አንድ ወዳጄ ተው ገንዘብ ከጤናህ አይበልጥም፣ በስርዓት ተኛ ፣ በስርዓት እረፍት አድርግ ፣ ብየ መከርኩ። እምቢ ብሎ 16 ሰዓት መስራት ጀመረ። ጭራሽ ሁለት ሰዓት ኦን ላይን ቢዝነስ ምናምን ብሎ ቁጭ ይላል! የዛሬ ወር ታዲያ ህፃን ልጁ መቀመጫው ተላልጦ እንዲቀባ በተሰጠው ክሬም ይሄ ወዳጀ በእንቅልፍ ልቡ ጥርሱን ቦረሸበት። ሚስቴ በስህተት አንድ ላይ አስቀምጣው ነው አለኝ። ሚስቱም 12 ሰዓት ስለምትሰራ ብዢ ብሎባት ይሆናል። በሳምንቱ ለጆሮ የተሰጠውን ጠብታ አይኑ ውስጥ ሞጅሮ ኡኡ ሲል ዋለ። ደግሞኮ ሚስቱ ናት ጠብታውን የጨመረችለት ። ኧረ እናንተ ሰወች ተው አረፍ በሉ አልኩ አልሰሙኝም። ጭራሽ ባለፈው "እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት አደረሰህ" የሚል ቴክት ኮፒ አድርጎ ላከልኝ። ግራ ገብቶኝ ቸክ ሳደርግ "የሃለዊን ደይ" ነበር። ምናልባት ሚስቱ ዶሮ እየሰራች ይሆናልኮ ተያይዘው አመለጡ በቃ ብየ አሰብኩ። ብዙሃኑ እንዲህ ኩላሊቱ እንደጫማ እስኪዟዟር ሰርቶ ቤተሰብ ይረዳል፤ ልጅ ያሳድጋል .... ቲክ ቶክ ላይ ለምትስለመለም ቦዘኔ አንበሳ የሚሰጥም አለ! ታዲያ ትላንት አሜሪካ አሜሪካ አሜሪካ ለሚል ወዳጀ ይሄን ስነግረው ምናለ? "ትቀልዳለህ እንዴ አብርሽ? አሜሪካ ገብቸ እንኳን በህፃን ልጀ የቂ* ክሬም በህፃኑ ካ* ጥርሴን በቦረሽኩ...የራሴ ልጅ አይደል ምናለበት?!" ደሞ ምሳ እየበላሁ እሱ ጋር ማውራቴ፤ የሚዘጋ ይዝጋህ😀
Open in Telegramበቃ ያ ሰውየ ከእንቅልፉ ሲነቃ የሆነች ቆንጆ መለመላዋን አጠገቡ ቁማ ትስለመለማለች። ስልክ ስጭኝ የለ፣ መጠናናት የለ፣ሽማግሌ የለ፣ ቀለበት የለ፣ ክፍለከተማ መፈራረም የለ በቃ! ሳያጠናት ፣ ካለሽማግሌ ካለፊርማ ሂዶ ወደቀ ይዛው ሞተች! ጦሱ ለኛም ተረፈ። ተፈራረሙ፣ ሁሉን ነገር እማኝ ባለበት አድርጉ አልን ማን ሰምቶን?! ራሳችሁ በየጫካው ተደብቃችሁ ትተቃቀፋላችሁ በኋላ ህዝብ ፍዳውን ይበላል ። ምን እዚህ! ምንም ጋር አይያያዝም ደግሞ😀
Open in Telegramአንዳንዴ ግን ሴቶች ከባድ ፍጥረቶች ናቸው! (አሌክስ አብርሃም) ለስራ ተቀጣጥረን ቡና እየጠጣን ነበር። ሚስቱም አብራን አለች። እና በስሜት እያወራኝ ነው። "ይገርምሃል ላለፉት 14 ዓመታት አምልጥ ፣ አምልጥ ፣ ከዚህ እስራት በተቻለህ ፍጥነት ሰንሰለትህን በጣጥሰህ ውጣና አምልጥ እያለ ውስጤ ይነግረኛል...እኔ ግን ነገ ዛሬ እያልኩ ..." ከማለቱ ሚስቱ ኳ አድርጋ የቡና ስኒዋን አስቀመጠችና ፊቷ ተቀያይሮ "ከየቱ እስራት ? ከየቱ ሰንሰለት?" ብላ አፈጠጠችበት። ጭራሽ ቦርሳዋን አንስታ በቁጣ ገልበጥ ገልበጥ እያለች ወደበሩ አመራች። በጭንቀት ተከትሏት ሮጠ። በእርግጥ ከተጋቡ 14 ዓመታቸው ነው፤ ግን እሱ እያወራ የነበረው ስለስራ ይመስለኛል! የሆነ ሆኖ ለሚስቴ ደወልኩና እየሳኩ ስለሁኔታው ነገርኳት፤ እኔማ በቃ ተጫዋች፣ ዘና ያለ ባል ለመሆን ነበር። ግን "ገልበጥ ገልበጥ እያለች ሄደች" ከማለቴ! የሚስቴ ድምፅ ሲቀየር ተሰማኝ! "ገልበጥ ገልበጥ ? ምን አይነት ቃል ነው?...ከኋላዋ ምን አሳየህ?" ስልኩ ጆሮየ ላይ ተዘጋ። ሰው ከፊቱ ገልበጥ ገልበጥ ሊል አይችልም?😀 ማነሽ የኔ እህት እስቲ ቡና ጨምሪኝ ብየ አዘዝኩና አስተናጋጇ ስትሄድ ከኋላ ላለማየት አቀረቀርኩ።
Open in Telegramለምንድነው ግን አንድ ታዋቂ ሰው ሲሞት ወይም እንደአገር የሆነ ሐዘን ሲፈጠር ...ባለዳቦ ቤቱ ዳቦ ቤቱን ፣ ባለልኳንዳው ልኳንዳውን፣ ባለ ቡና ቤቱን ቡና ቤቱን አይዘጋም፤ ግን አርቲስቶችና የመድረክ ሰወች ስራቸውን እንዳይሰሩ በየአፉ ይጮሀል። ካዘነ ለምን ሁሉም የየራሱን ስራ ዘግቶ አይቀመጥም?
Open in Telegramብዙ ደሃና ኑሮውን ለማሸነፍ የሚጥረው ሰው በሐይማኖትና ፖለቲካ ጉዳይ የሚጨቃጨቀው በመንጋው ወይም በድርጅት ከሚከፈላቸው፤ ወይም በደግ ቀን ሐብት ከሰበሰቡ ኑሮ ከማያስጨንቃቸው ሀብታም ሰወች ጋር ነው። ምክንያቱ የአገሩ የእምነቱ የታሪኩና ማንነቱ ጉዳይ ስለሚያሳስበው ነው። የሚያበሳጩት ሰወችስ? በቃ ምንም አይሰሩም፤ የሚሰሩት ለክብር ለዝና ለተፅዕኖ ነው። እስቲ በጣም የሚያበሳጭህን አንዱን አገር አማሽ "ፖለቲከኛ" ፣ "ሐይማኖተኛ" ወይም ወዘተ ሰው አስብ ...አንዱን.... እንደአንተ ለታክሲ ተሰልፎ ይንቃቃል? መኪና እየቀያየረ ሁሉ የሚኖር ነው! እንደአንተ ደመወዝ ይጠብቃል? አንድ ሚሊየን ህያው የኤቲኤም ማሽን ከቦት ብር ሲረጭበት ነው የሚኖረው። እንደአንተ ክፍለሀገር እንኳ ሄዶ ቤተሰቡን ማየት ይናፍቀዋል? ዓለምን ሲዞር ነው የምታገኘው። እንደአንተ ተሰዶ ይጠገረራል? እእ ለቫኬሽን ወይም ስደተኛውን መንጋ ለማለብ ነው የሚሄደው! እንደአንተ ሰው ከጎኑ አጥቶ የሰው ያለህ ይላል? ሚሊየን መንጋ ሲያሸረግድለት ነው ውሎና አዳሩ። አሁን መሠረቲዊ ጥያቄ ጠይቅ...ይሄን ሰው በዚህ ክፋቱ ፣በዚህ ድድብናውና ሳይኮ ባህሪው ለምን ከአንተ የተሻለ ዓለም ተመቸው? ለምንድነው ይሄን ሁሉ የሰጠችውን አገር የሚረብሻት ለእኔ ካልተመቸች ትውደም የሚለው? ለምን ግልፅ የሆነ ድድብናው እየታየ በዙሪያው ያሉ ሰወች ታወሩ? የተማሩ የተከበሩ ሰወች ለምን ደነቆሩ? ምናልባት ደግፈኸውም ይሁን ተቃውመኸው አንተም መንጋው ሆነህ ቢሆንስ?!! መቃወም ሁሉ መቃወም እንዳይመስልህ? የዚህ ሰው ብቃት (((ስጋት))) መፍጠር ነው። ቁጫጭ የሚያክል ችግርን ተራራ አሳክሎ ያሳያሀል፣ ትንሿን በሰወች መካከል የተፈጠረች የግለሰቦች ስድድብ በብዙ ልፈፋ የአገር ችግር፣ የዓለም መጥፊያ ፣ አምላክህን ከሰማይ አውርዳ የምታፈርጥ ተዓምር አስመስሎ ያሳይሃል። ስሩ ተሸጉጠህ እርሱ እየተዋጋልህ እንደሆነ ታስባለህ። ስንቅና ትጥቅ ታቀርባለህ። መንጋ የምትሆነው የደህንነት ስጋት ሲሰማህ ነው። ለምን አትልም። ያለውን ትቀበላለህ። ለምን ካልክም በሚመልስልህ መልስ ስለተመለሰልህ ብቻ ለመደመም ተዘጋጅተህ ነው። እየነገርኩህ ነው በኋላ አልሰማሁም እንዳትል!
Open in Telegramጭራሽ ሽልማት? (አሌክስ አብርሃም) መምህርነት ክቡር ሙያ ነው፤ በሕይወት ዘመኔ የሚገራርሙ ጥሩ መምህራን አጋጥመውኛል። ግን አንዳንድ ወንድ መምህራን የሆነ ነገራቸው ልክ አልነበረም። እስከአሁንም ባስታወስኳቸው ቁጥር ጤነኝነታቸውን እጠራጠራለሁ። በአጋጣሚ መንገድ ላይ እንኳን ሳያቸው ሰላም ላለማለት መንገድ አቋርጨ ነው የምሄደው። ደግሞ ሰው አይረሱም። "ቲቸር እንትኒት" የሚባል አስተማሪ ነበረን። "እንትኒት" የተባለው በሚጋረፍባት የእንጨት ብትር ስም ነው። እንደደህና ነገር ገና የመጀመሪያ ቀን ዱላውን በስም ለተማሪወች ያስተዋውቃል። ወጥ ማማሰያ የመሰለ ጫፏ ቀይ የተቀባ ብትር። መዳኒት ናት ምናምን እያለ ይሟዘዝና በአየር ላይ እንደሰይፍ እየሰነዘረ ያስቦካናል። የመጀመሪያ ቀን በቃ ይነጅሰናል። ከእኛ በፊት ያስተማራቸው "ዝናውን" ስለሚነግሩን ባያስፈራራንም ፈርተን ነው የምንጀምረው። ሌላውን ተውት ይሄ ሰውየ ገና መስከረም ላይ ሲገባ እንደሆስፒታል የሰርጀሪ አልጋ ከፊት ወንበር አንድ ጠረጴዛ ያመቻቻል። እዛ ጠረጴዛ ላይ የስንት ህፃን ቂ* በደረቅ እንጨት ሰንበር በሰንበር አድርጓል። ሴቶቹን መግረፍ ነፍሱ ነበር። በተለይ ደግሞ እታፈራሁን ካልገረፈ እንደሆነ ሱስ ያዛጋዋል። እታፈራሁ ሚስኪን የደሀ ልጅ ናት፣ ምን ሆንሽ ባይ የሌላት። ሁልጊዜ ፀጉሯ የሚንጨባረር (ቅጫም) ነው የሚላት ቅጫማም አይደለም... ቅጫም! አንድ ቀን ወላጅ አምጭ ተብላ እናቷን ይዛ መጣች...ገና አስተማሪው የቤት ስራ አትሰራም ከማለቱ እናቲቱ የእታፈርን ፀጉር ጨምድዳ "ስታርሽ ነው ስትጎለጉይ" እያለች ትቀጠቅጣት ጀመር ፣ ያ ክፉ አስተማሪ እንኳን "አቁሚ ህፃን አይደለች እንዴ" እስኪል። በነገራችን ላይ በቀጥታ ገርፎኝ አያውቅም ግን ዱላውና ትሮውማው በተዘዋዋሪ ደርሶኛል። አንድ ቀን ይችኑ እታፈራሁን ምን እንዳደረገች ትዝ አይለኝም (መልስ አልመለሽም ብሎ ይመስለኛል) እዛ ጠረጴዛ ላይ በሆዷ አስተኛት። ቀሚስሽን ግለቢ አለ (ሲሪየስ አሁን ይሄ ምንድነው) ልጅቱ ነፍሷ ተጨነቀ። ገና ሳትገረፍ ሽንቷን ለቀቀችው...እንደተደፋ የብርጭቆ ውሃ ሽንቷ ከጠረንጴዛው እየተንኳለለ ስሚንቶው ወለል ላይ ሲያርፍ ድምፁ እስከአሁን ይታወሰኛል። ፊት ወንበር ነበር እኔ የምቀመጠው። "ና አንተ " አለኝ። እየተንቀጠቀጥኩ ሄድኩ። "እዚህ ወገቧ ላይ ግጥም አርገህ ያዝ" አለና በብትሩ ጠቆመኝ። አጥንታም የህፃን ወገቧን ከተገለበ ቀሚሷ ጋር ያዝኩ ። ብቻ የመጀመሪያው ብትር እያፏጨ ሰውነቷ ላይ ሲያርፍና ደም የመሰለ መስመር ሲያጋድምባት ያች ትንሽ ፍጥረት የሷ በማይመስል ሃይልና ጩኸት ገፈታተረችኝ " ሁለተኛው ብትር ሲምዘገዘግና ያመለጠኝን የቀሚሷን ጫፍ ለመያዝ እጀን ስዘረጋ የብትሩ ጫፋ ትንሿ የቀኝ እጀ ጣት አንጓ ላይ አረፈ። ቋ ነው ያለው እንደረቅ እንጨት። ለአመታት ህመሙ ይሰማኝ ነበር ። በተለይ መዳፌን ስጨብጥ። እታፈራሁን ሁልጊዜ አስባት ነበር። የት ሄዳ ይሆን እያልኩ። ምንዱባንን ሳነብ እነ ኤፖኒን ፣አዜልማ፣ ኮዜትን ሁሉ በእርሷ እየተካሁ ትዝ ትለኝ ነበር። ሰውየው ያልገረፈው ህፃንና ያልተለማመደብን አገራረፍ የለም። አለኮ አባታዊ ቅጣት፣ የሆነ ፍቅር ያለው... ልጆች በባህሪም በትምህርትም እንዳይበላሹ መስመር ለማስያዝ ያህል ዘመኑ ይፈቅደው የነበረ ቅጣት። ይሄ ወንዶቹ ላይ ሃይላንድ ያላንጠለጠለብንም በዘመኑ ቅጣቱ ባለመለመዱ ይመስለኛል። በጣት መሃል እስክርቢቶ አስገብቶ ማጣበቅ፣ በማስመሪያ ጠርዝ የጣት ጫፍ መምታት፣ አስጎንብሶ ጆሮ ማስያዝ፣ ተማሪ ፊት ማዋረድ ፣ ጆሮን አፍንጫ ላይ የሚያመጣ ኩርኩም ማጋጨት፣ አይን የሚያንሸዋርር ድንገተኛ ጥፊ፣ በእንብርክክ ስሚንቶ ላይ ማስኬድ፤ በካልቾ መጠለዝማ በረከት ነበር.... ግርርርርም ያለኝ ባለፈው የድሮ ተማሪወቹ ተሰብስበው "ቲቸርን ልንሸልም ነው ተቀላቀለን" አሉኝ። ጭራሽ ሽልማት? ደግሞ በጣም የገረመኝ ሸላሚወቹን ሰብሳቢ ማን ብትሆን ጥሩ ነው? እታፈራሁ! "የቀለም አባታችን" ምናምን እያለች። ምኗ ቅጫም ናት አልኩ በንዴት😀
Open in Telegramስንብት.... ጃንሆይ 44 ዓመት ኢትዮጵያን አስተዳድረው ሲወርዱ ህዝቡን አልተሰናበቱም፣ ጓድ መንግስቱ 17 ዓመት ገዝተው ሲሄዱ አልተሰናበቱም፣ አቶ መለስም አልተሰናበቱንም ለህክምና እንደወጡ ነው የቀሩት። ታዲያ በቀደም በጎተራ በኩል ሳልፍ የትም የማናውቃቸውና የማያውቁን ሙሽሮች መሀል ከተማ ላይ በመኪናው ጣራ ሁለቱም ከወገባቸው በላይ ብቅ ብለው ህዝቡን ቻው ቻው እያሉ ይሰናበታሉ። ሕዝቡ ሰልችቶታል መሰል ዙሮ እንኳን አያይም። ሴቷ ሙሽራ ወደኔ ዙራ እጇን ስታወዛውዝ እኔም ፈገግ ብየ ቻው ቻው አልኳት፤ ይሄ ሜካፕ የማይሰራው ነገር የለ ምናልባት ኤክሴ ልትሆንም ትችላለችኮ፤ በሰላም መሰነባበቱ አይሻልም?😀
Open in Telegramሐይማሔሮች (አሌክስ አብርሃም) ሰሞኑን እዚህና እዚያ የሚዛዛቱና የሚደነፉ የ"ሐይማሔር" ሰወች (የሐይማኖትና ብሔር ድቅል ሰወች) ነገር እንዴት እንደቀፈፈኝ አትጠይቁኝ። በቅርቡ ኢትዮጵያ ደርሶ እንደተመለሰ ሰው የሚያሳዝነኝ ነገር...ሕዝቡ ኦርቶዶክስ በሉት ሙስሊም፣ ፕሮቴስታንት በሉት ካቶሊክ፣ ዋቄፈታ በሉት ኤቲስት ኑሮው ከመክበድ አልፎ እንደዶዘር መኪና እየዳመጠው የሁሉም ነፍስ እንደሊጥ ተደፍጥጧል። ህዝቡ ነፍሱን ለማኖር ያህል እያንዳንዷን ሳንቲም እንደበረሃ ውሃ በስስት እያንጠባጠበ በጥፍሩ ቁሞ ነው የሚኖረው። እናቶች አባቶች በመጦሪያ እድሚያቸው ልመና ወጥተዋል። ህፃን የሚያግተለትሉ እናቶች በየጎዳናው ታያላችሁ። ቢያንስ በከተሞች ለምነው ይኖራሉ። ዘር ሐይማኖት ሳይል ያዘነ ይመፀውታቸዋል። ሁሉም ጭንቅ ውስጥ ነው። ሐብታም ይሁን ደሃ አከራይ ይሁን ተከራይ ሁሉም የሚተማመንበት ዋስትና የለውም። ስለነገ በእርግጠኝነት የሚነግርህ የለም። ስራ ያለውና የሌለው እኩል ይጨነቃል። በዚያ ላይ ሙስናው፣ ጦርነትና በየገጠሩ በየምክንያቱ የሚገደለው ሰው ያሳዝናል፣ ስደቱ የጉድ ነው። ይሔ ሕዝብ የመጨረሻ መደበቂያ ያለው አምላኩን ነው። በየእምነቱ ትንሽ ሰላም የሚያገኝበት ቦታ ቤተክርስቲያንና መስጊዱ ነው። ለዚህ ሕዝብ አንድ ነገር የማይፈይዱ እንደእስስት የመጣ የሄደው ጋር ቆዳቸውን እየቀየሩ የሚለጠፉ የሐይማኖትና ብሔር ድቅሎች ይሄ ሚስኪን ህዝብ ተረዳድቶ እንኳን ኑሮውን እንዳይገፋ በበሰበሰ ቲወሪና ጥላቻ ጦር አውርድ ይሉታል። ይችኑ መጠጊያ መሸሽያውን የነገር ቤት አድርገውበታል። የኔ ነው የበላይ የኔ በሚል ሲያቀረሹ ይውላሉ። እስቲ ሰብሰብ በሉና እንደመቄዶንያ ከዘር ከሐይማኖት ነፃ የሆነ አንድ አገር አቀፍ የእርዳታ ድርጅት ክፈቱ። ደፈር በሉና በጋራ ጦርነት እና እልቂት ተቃወሙ። ሕዝቡን ተውት፤ ፈጠርኩህ የሚለው አምላክ ራሱ ይፈልገዋል። እናተን አጋሰሶቹን ያከበረ አምላክ በባዶ ሆዱ የሚቆራመድ ህዝብ ከገፋ ምኑን አምላክ ሆነ። አሁን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሐይማኖት አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም። እናንተ በሐይማኖት ስም የምትፈጥሩት መከራና ጥላቻ ነው ያንገበገበው። የትም ዓለም ብትሔዱ የወደቀ የሐይማኖት ወገንተኝነትና መጓተት ለዚህ ሕዝብ መከራ እንጅ አንዳች ጥቅም አያመጣም። ሰው ሌላው ቢቀር ኦርጅናል ጠብ አይጣላም? ሳልቫጅ ነገር?? ሳልቫጅ ስብከት፣ ሳልቫጅ ጥላቻ? ኤጭ!!
Open in Telegramበዚህ ሰዓት የሐይማኖት ሰወች ከአምላካቸው በላይ መንጋቸውን ያመልካሉ። ይህን ለማረጋገጥ ከፈለክ ብዙ መንጋ ያለውንና የሌለውን አነፃፅር። ባለብዙው የበዛ ኮንፊደንስ ሲኖረው ትንሽ መንጋ ያለው አንገቱን ደፍቶ ይቅለሰለሳል። መንጋው ሲበዛለት ተነስቶ ይደነፋል። መንጋ ያድናል፣ መንጋ ሀይል ነው፣ የሚመካ በመንጋው ይመካ ነው መንፈሱ። በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የመንጋ እንጅ የሐይማኖት ፀብ አለ ብሎ ለማመን ይቸግራል። ሐይማኖት ከብሔርና ፖለቲካ ተዳቅሎ ዲቃላ ሐይማኖተኞችን ወልዷል።ዲቃላ በባህሪው መንገደኛው ሁሉ አባቱ ይመስለዋል። እናቱን ያገባ ሁሉ አባቱ ይመስለዋል። መንጋ የሐይል፣ መንጋ የገቢ ምንጭ ነው። አማኝ ሳይሆን መንጋ ማብዛት የሐይማኖቶች ዋና ስራ ሁኗል!! ((መንጋ)) በአምላኩ ስም ወደየትም የሚነዳ ግዑዝ የሰው ስብስብ ሲሆን ፣((አማኝ)) ግን በእምነት ወደአምላኩ ብቻ የሚራመድ ሰው ነው!
Open in Telegramግብፅ የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ትንሽ ሳይዘገይባት አልቀረም፤ ሚዲያወቿ ምን ደረሰ እያሉ ነው። ነገሩ ያንን ጅብ አስታውሰኝ። አንድ ጅብ ማታ በሆነ ቤት በኩል ሲያልፍ እናትና አባት አልተኛም ያለ ልጃቸውን ሲቆጡ ይሰማል። "እንቢ ካልክ አስወጥተን ለጅብ ነው የምንሰጥህ" እያሉ። አያ ጅቦ ቆም አለ። በኋላ ልጁ ተኛ። እናትና አባት በነፃነት ሌላ ዓለም ውስጥ ገብተው ፣ ሲጨዋወቱ አያ ጅቦ በራቸውን አንኳኳና "የልጁን ነገር ምን አደረሳችሁት?"😀
Open in Telegramድልነሳው 'ዲስኦርደር' (አሌክስ አብርሃም) የሆነ ጊዜ የሰፈራችን ልጅ ድልነሳው የአእምሮ ሕመም ገጠመው ተባለ። አንዳንዶች በሴት ነው አሉ፤ አንዳንዶቹ በሱስ ነው፤ ሌሎች አይ የሆነ የፍልስፍና መጽሐፍ አንብቦ ነው አሉ። ጓደኞቹ "ኧረ እሱ ሁልጊዜ ፋኖስና ብርጭቆን ነው የሚያነበው" ቢሉ "ሆድ ለባሰው እንኳን ፋኖስ ሻማ ይበቃዋል" ተባለ። ብቻ አንድ ቀን ወደ አስር ሰዓት አካባቢ ድንገት ተነስቶ ሲሄድ እናቱ "ተከተሉልኝ ሊጠፋብኝ ነው" ብለው ስለለመኑን ተከተልነው። በፍጥነት እየተራመደ ወደ አውቶብስ ተራ ሄደና ሰው ለመቀበል የቆሙ ሰዎች ጋር ተቀላቅሎ ቆመ። አውቶብስ ሲመጣ እየተጋፋ ተንጠራርቶና ወደ ውስጥ ይመለከታል። የሆነ የሚመጣ ሰው እየጠበቀ ይመስላል። ጠጋ ብለን "ድሌ ማንን እየጠበቅህ ነው?" አልነው። መልሱ አጭር ነበር፤ "ራሴን! ....እናንተስ?" ግራ ገብቶን "እኛም አንተን እየጠበቅን ነው" በደስታ እየተፍለቀለቀ "በቃ አብረን እንጠብቀው!" አለና አብረን መንጠራራት ጀመርን። ሳስበው እንደ ሀገር እንደሕዝብ የሆነ "ድልነሳው ዲስኦርደር" የያዘን ይመስለኛል። እኛ እዚህ ዘመን ላይ ነን፤ ግን እኛ ራሳችን ገና አልመጣልንም። ይሄ የእኛ እኛነት አይደለም። አንዳንዴ ይሄማ እኔ አይደለሁም የሚያስብል ነገር ሰርታችሁ ራሳችሁን አታገኙትም? ራሳችሁን ትላንት ያሰባችሁት ቦታና ባሕሪ፣ ሕይወትና ምኞት ላይ አገኛችሁት? ለምሳሌ በ30፣ በ40፣ በ50 ዓመቴ እዚህ እደርሳለሁ ብላችሁ ዕድሜው ደርሶ እናንተ ቀርታችኋል?...እና አላመናችሁም፤ የት ሄደ ያ እኔ? እያላችሁ ወደኋላ እያያችሁ ነው? ፒያሳ ናችሁ ግን ኮየ ፈጨም ናችሁ። የሆነ መልዓክ የመሰለ ሰው አግብተሻል ግን ደግሞ ከጎንሽ የተኛው ጭራና ቀንድ የቀረው ሰይጣን ነው...በቃ ድልነሳው ዲስኦርደር ይሄ ነው። አውቶብስ ተራ አንሂድ እንጅ የሆነ የጠፋ እራሳችንን ጥበቃ ብዙወቻችን እየተጋፋን ነው። የሆነውና የተመኘነው ተወጫብረዋል ድሮ ኮሌታችንን ከኋላ አንቆታል ፣ ዛሬ ኮሌታችንን ከፊት ... Expectation vs. Reality Discrepancy ይለዋል ፈረንጅ ሲፈስረው። አቻ ትርጉም "የድሮ ስርዓት ናፋቂ"😀
Open in Telegramችግሩን ለመፍታት ችግር አለ (አሌክስ አብርሃም) አዲስ ተጋቢወቹ በመጀመሪያው ምሽት ምኝታ ቤት እንደገቡ ሚስት ባሏን የጡት ማስያዣዋን ከኋላ እንዲፈታላት ጠየቀችው። ያው ሮማንቲክ ለመሆን እንጅ እድሜ ልኳን ራሷ ስትፈታ ነው የኖረችው። እና አቶ ባል ሰከንድ አልወሰደበትም በግራ እጁ ተረክ አድርጎ ፈታው። ተበሳጨች፤ "ብዙ ልምድማ አለህ፣ አንድም ወንድ በዚህ ፍጥነት ፈትቶልኝ አያውቅም" አለች። ባል የባሰ ቱግ ብሎ "ለስንት ወንድ አስፈትተሽ ነው አንድም የምትይው?" አሁን ደግሞ ስንዘገይ "ፈትቸ አላውቅም ለማለት ነው?" ሊሉን ነው። እንደውም የየራሳችንን ችግር ብንፈታስ?!
Open in Telegram