Account

Posts of "ቃለ እግዚአብሔር "

newest first

#3129Text
Views627+3%vs avg
Forwards—
Reactions6
Comments—
#3128Text

ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር እንስጠው ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እሳት ውስጥ ጨምሮ እጅግ ንጹህ እስክትኾን ድረስ ይጠብቃታል፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደዚሁ ሰዎች እስኪነጹ፣ እስኪለወጡና ባገኛቸው ነገር ጥቅም እስኪያገኙ ድረስ ፈተና ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅምም እጅግ ከፍ ያለ ጥቅም ነው፡፡ ስለዚህ ፈተና ሲገጥመን ውስጣችን ሊረበሽ ወይም ተስፋ ሊቈርጥ አይገባውም፡፡ ያ ወርቅን የሚያነጥር ሰው በእሳት ውስጥ የጨመራትን የወርቅ ቅንጣት እዚያ ውስጥ ምን ያኽል ጊዜ መቆየት እንዳለባት ያውቃል፤ መቼ ከእሳቱ ሊያወጣት እንደሚገባውም ያውቃል፡፡ እንዲሁ እስከ መጨረሻው በእሳቱ ውስጥ ተጥላ እንድትቀርና በዚያ እንድትቃጠል አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ከወርቅ አንጣሪው በላይ ያውቃል፡፡ መቼ ከርኵሰታችን እንደምንነጻ ያውቃል፡፡ በመኾኑም ራሳችንን በመጣልና ተስፋ በመቁረጥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመርን እንዳንሔድ ሽቶ መቼ ከዚያ ፈተና እንደሚያወጣን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ድንገት ያላሰብነው ነገር ቢገጥመን በፍጹም የምናማርር፣ ወይም ተስፋ የምንቈርጥ ልንኾን አይገባንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ነገሮች ምንነትን የሚያውቅ እግዚአብሔርን መጠበቅ፣ እርሱ እስከ ፈቀደው ጊዜ ድረስም ልቡናችንን በእሳት እንዲፈተን ማድረግ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዲኾን የፈቀደው ለእኛ ጥቅምና በዚያ ውስጥ ኾነን በምናሳየው ጥረት ይበልጥ ሊያከብረን ስለሚወድ ነው፡፡ ይህን በማስመልከትም ጠቢቡ ሰው እንደዚህ ሲል መክሮናል፡- “ልጄ ሆይ! ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሔድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ፤ ልብህን አቅና፤ ኹልጊዜ ታገሥ፤ አታወላውልም፤ በመከራ ብትጨነቅም አትጠራጠር” /ሲራ.2፥1-2/፡፡ “ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ስጠው፡፡” ለምን? እግዚአብሔር ከዚያ መከራ መቼ እኛን ማውጣት እንዳለበት ያውቃልና፡፡ ስለዚህ ኹሉንም ለእርሱ ልንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን ልናመሰግን፣ ኹሉንም ነገር  ጥቅምም ይኹን ቅጣት በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፤ ይህም ቢኾን ለእኛ ረብሕ የሚኾን ነውና፡፡ አንድ ሐኪም፥ ሐኪም የሚባለው ታካሚውን ገላዉን ሲያጥበውና ሲመግበው እንዲሁም ደስ ወደሚያሰኝ ስፍራ ሲወስደው ብቻ አይደለም፤ በእርሱ (በታማሚው) ሰውነት ላይ የቀዶ ጥገና ምላጭና ቢላ ሲያሳርፍም ጭምር ሐኪም ነው፡፡ አባትም አባት የሚባለው ልጁን ሲንከባከብ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ልጁን ከቤት ሲያስወጣው፣ ሲገሥጸው፣ ሲገርፈውም ያው አባት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔር ከሐኪሞችም በላይ ሰውን ወዳጅ እንደ ኾነ በማወቅ፥ ምን ዓይነት የሕክምና ዓይነት እንደሚሰጠን በጥልቀት አንጠይቅ፤ ወይም ደግሞ ለደረሰብን መከራ እርሱን ተጠያቂ አናድርግ፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሱ የወደደውን ነገር  ቅጣትም ይኹን ቅጣት የሌለው ነገር ብቻ ምንም ይኹን ምን በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፡፡ በየትኛውም መንገድም ቢኾን የእርሱ ፈቃድ እኛ እንድንድንና ከእርሱ ጋር አንድ እንድንኾን ነውና፡፡ የትኛው መንገድ ለእኛ እንደሚጠቅምም እርሱ ያውቋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የትኛው መንገድ ወደ እርሱ እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ ኹላችንም እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ልንድን እንደምንችል ያውቃል፡፡ በመኾኑም የሚመራን በዚህ እኛ በምንድንበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደየትኛውም መንገድ ቢወስደንም ልክ እንደ መጻጉዑ እርሱ እንደሚያዘ’ን ተከትለን መሔድ እንጂ ትልቁ ጉዳያችን በለስላሳና በቀላል አልያም ደግሞ በከባድና በሸካራ ጎዳና እንድንሔድ የሚያዘ’ንን ትእዛዝ መኾን የለበትም (ልንሔድበት የሚገባ’ው መንገድ እርሱ ስለሚያውቀው እንዲሁ መታዘዝ እንጂ የመንገዱን ከባድነት ወይም ቀላልነት የእኛ አጀንዳ ሊኾን አይገባውም፡፡) (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ኦሎምፒያስ የተላኩ መልእክታት - በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ) @KaleEgziabeher

Open in Telegram
Views577−6%vs avg
Forwards—
Reactions3
Comments—
#3126Text

ድንግል ሆይ ወደ አንቺ መጥቶ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ያለሽ መልአክ ዛሬም ወደ እኔ ይምጣ፡፡ ኃጢአት ያደቀቃት በኀዘን የተዋጠች ነፍሴን ከጸጋ የተራቆትሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ይበላት፡፡ ጌታ በእኔ ልብ እንዳይፀነስ ‘ያለ ኃጢአት መኖርን ስለማላውቅ እንዴት ይሆንልኛል?’ ብልም ወደ አንቺ የመጣው መንፈስ ቅዱስ ወደ እኔ በምሕረት ይምጣ፡፡ በእስራኤል ልጆች ሠፈር መና እንደወረደ የልጅሽ ምሕረት በእኔ ላይ ይውረድ፡፡ አንቺን ድንግልናን ከማጣት እንደ ጋረደሽ እኔን ከኃጢአት ይጋርደኝ፡፡ አንቺን አምላክን ለመውለድ ያጸናሽ አብ እኔን ልጅሽን በማመን ያጽናኝ፡፡ አንቺ በማሕፀንሽ ዘጠኝ ወር የፀነስሽውን ጌታ እኔ ለደቂቃዎች እንኳን በልቤ እንድፀንሰው ፍቀጂልኝ፡፡ የፀነስሁትን የኃጢአት ሃሳብ ከልቤ አውጥተሽ በሕሊናዬ ልጅሽ እንዲያድር ለምኚልኝ፡፡ ጌታን በእጆችሽ መሃል የያዝሽው ሆይ አንቺ ጌታን ለዓመታት ታቀፈሽው ነበር፡፡ እኔ ግን ለአንድ ቀን እንኳን ሰውነቴ ከኃጢአት አርፎ እሱን ብቻ ታቅፌ እንድውል ፍቀጂልኝ፡፡ እርግጥ ነው ወደ እኔ ልጅሽን ይዘሽ ስትመጪ እንደ ቤተልሔም የእንግዶች ማደሪያ የእኔም ልብ የብዙ እንግዳ ኃጢአቶች ማደሪያ ነውና ልጅሽን ለማስተኛት ቦታ የለኝም ብዬ የልቤን በር ልዘጋብሽ እችላለሁ፡፡ በሩን ብዘጋውም ግን ልጅሽ እንደሆነ ‘በደጅ ቆሞ ማንኳኳት’ እንደማይሰለቸው አውቃለሁ፡፡ ራእ.፫፥፳  እኔ ፈቅጄ ባልከፍትለትም እንኳን የድንግልናሽን ማኅተም ሳይከፍት እንደተወለደ የእኔን የተዘጋም ልብ ሳይከፍተው መግባት አይሳነውም፡፡ ስለዚህ ዐመፄና እምቢታዬን ቸል ብለሽ ለልጅሽ ማደሪያ አድርጊኝ፡፡ አንቺ እርሱን ከወለድሽ ወዲያ በታተመ ድንግልና ጸንተሽ እንደኖርሽ ለልጅሽ ማደሪያ ሆኜ ለሌላ የኃጢአት ፅንስ ዳግም ማደሪያ እንዳልሆን ነፍሴን አትሚልኝ፡፡ የወለድሽው መድኃኒት እኔን ዙፋኑ አድርጎ ቢቀመጥ ሰዎች በእኔ እቅፍ ስላለ ብቻ በእኔ ምክንያት እንደ ሰብአ ሰገል እንደሚሰግዱለት በአንቺ ሲሆን አይቻለሁና ሰዎች በእኔ ምግባር ምክንያት ፈጣሪን መስደብ ትተው እጅ መንሻ ያቅርቡለት፡፡ ለልጅሽ በቀረቡ ሥጦታዎች ተከብቤ ከአንቺም ጋር ፦ ‘ጌታ ሆይ ለአንተ የሚሰግዱልህ ሰዎች ዙሪያዬን ከበቡኝ ፤ ለአንተ በቀረቡ ሥጦታዎችም ዙሪያዬን ታጠርኩ’ ብዬ ላመስግነው፡፡ ድንግል ሆይ አንቺን ያሳደደሽ ሔሮድስ እኔን የማያሳድደኝ ጌታ በእቅፌ ስለሌለ ነው፡፡ እኔ በልቤ ያነገሥሁት ‘የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ’ ስላልሆነ ሔሮድስ ከእኔ ጋር ጠብ የለውም፡፡ የሔሮድስን ሥልጣን አደጋ ላይ የሚጥል ንጉሠ ሰላም በእኔ እቅፍ የለም፡፡ አሁን ግን ፍቀጂልኝና ሔሮድስን ማስደሰት ትቼ ልጅሽን በልቤ ልቀበለው፡፡ የልቤን ክርስቶስ ሔሮድስ እንዳይገድልብኝ እኔም እንደ አንቺ ልሰደድ፡፡ እሱን አቅፌ መከራ ቢደርስብኝ እንኳን ጽናት እንደማገኝ በአንቺ አይቻለሁና የልጅሽን ፍቅር በልቤ አኑሪልኝ፡፡ ለሦስት ቀናት ከፊትሽ ዞር ቢል ፍለጋ የወጣሽዋ ድንግል ሆይ ከእኔ ሕይወት ልጅሽ ከተሠወረ ቆይቶአልና ያለ እርሱ መሰንበት የማልችል የፍቅሩ ምርኮኛ አድርጊኝ” ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ #የብርሃን_እናት - ገፅ 305-308 @KaleEgziabeher

Open in Telegram
Views1,760+188%vs avg
Forwards—
Reactions6
Comments—
#3125Text

✅❝እልኸኛ አትሁን ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።❞በማለት እልኸኝነት በ እግዚአብሔር ኅሊና ከተፈቀደልን የዕድሜ ገደብ በታች ዘመናችንን በአጭሩ እንደሚያስቀር ተናግሯል:: መክ ፯፥፲፰ ። ✅ይህም በንጉሡ በሕዝቅያስ ሕይወት ይታወቃል፡፡ንጉሥ ሕዝቅያስ በትዕቢቱ ዕድሜው ሊያጥር ነበር፣ ሆኖም ግን ብልህ ንጉሥ በመሆኑ ወዲያው ንስሐ ገብቶ ያጠረውን ዕድሜውን ለማራዘም ችሏል:: ዕድሚያችን ለሰው ሁሉ ከተስጠው የዕድሜ ገደብ በታች እንዳይሆን ወይም በአጭሩ እንዳይቀጭ የዕድሜ ማራዘሚያ ቀመሩ ምን እንደሆነ ✅ጥበበኛው ሰሎሞን እንዲህ ሲል ይጠቁመናል:-❝ፈሪሃ እግዚአብሔር ያነውን መዋዕለ ወዓመተ ረሲዓንስ ይውኅድ — እግዚአብሔር መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፥ የኀጥአን ዕድሜ ግን ታጥራለች ታንሳለች።❞ ምሳ ፲፥፳፯ በማለት እግዚአብሔር የሚወዳቸውን እንዲያመሰግኑት በዘመናቸው እንዲመለክበት ረጅም ዕድሜ እንደሚሰጣቸው፤ የኀጥአን ዕድሜ ግን ለብዙዎች የመኖር ጠንቅ ስለሆነ ጤነኞች የክፋታቸው ሰለባ እንዳይሆኑ ዘመናቸውን እንደሚያሳጥረው ተናግሯል:: ✅በመሠረቱ የጥንት ሰዎች በምድር ላይ እስከ ዘጠኝ መቶ ዓመት የመኖር እድል ተሰጥቷቸው ነበር፤ የሰው ልጅ ግን ኀጢአቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎሽ እያገረሽ ምድርን እያበላሽ በመሄዱ እግዚአብሔር የሰው ዕድሜ መርዘሙ ትርጉም ስላጣበት ከዘጠኝ መቶ ወደ መቶ ኻያ፤ ከመቶ ኻያ ወደ ሰማንያ ለመቀነስ ተገዷል፡፡ ዘፍጥ ፮፥፭ ፣  መዝ ፹፱፦፱ ✅ነገር ግን ይህ ሕግና መመሪያ በዘመናቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ፤ በሕይወታቸው እግዚአብሔርን ያከበሩ ቅዱሳን ከተፈቀደው የዕድሜ ገደብ በላይ እንዳይኖሩ አላገዳቸውም። ለምሳሌ እነአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን የመሰሉ ጻድቃን ሁለት መቶ፣ ዐራት መቶ፣ ዐምስት መቶ ዓመታት በዚህች ምድር ላይ እንደኖሩ በታሪክ እንገነዘባለን፡፡ ✅ሄኖክንና ኤልያስን የመሰሉ ጨርሶ ከዓይነ ሞት የተሠወሩ ቅዱሳንም አሉ፤ ጻድቃን ለብዙ ዘመናት በዚህች ምድር የመኖራቸውን ምሥጢር ጥበበኛው ሲራክ ሲነግረን:- ❝የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፣ ሥርዐቷም በሕይወት የሚኖሩበትን ዘመን ያበዛል::❞በማለት ፈሪሃ እግዚአብሔር ኑሯችንን የሚያጣፍጥ ዘመናችንን የሚያስረዝም ትልቅ መንፈሳዊና አምላካዊ ቀመር መሆኑን ተናግሯል:: ሲራ ፩፥፳። ✅#ጠቢቡ_ሰሎሞን_ሲናገር ❝በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ከፉን ለመሥራት ጠነከረ ኀጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉ ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢኾን እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲኾን አውቃለሁ ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም፡፡❞በማለት እግዚአብሔር የማይፈሩ ሰዎች ፈጥኖ እንደሚቀሰፉ ተናግሯል፡፡ መክ ፰፦፲፩ ✅#ግፍን_መጥላት_ዘመንን_ያረዝማል፦ግፍ ማለት የአንድን ነገር ነባር ማንነቱን ረግጦ ልክና መጠን በሌለው በደል መበደል ማለት ነው፤ በአጠቃላይ ግፍ ጭካኔ የተሞላ ሰብአዊነት የጎደለው ሰይጣናዊ ተግባር ነው፤ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ግፍ የአእምሮ ጉድለት ኢሰብአዊነት ነው ሲል ይገልጠዋል፣ግፈኞች ዘመናቸው አጭር ነው ፤ያውም ተቀስፈው ነው የሚሞቱት፤ ✅ጠቢቡ ሰሎሞን ከግፍ ተግባር ራሳቸውን የጠበቁ በዚህ ዓለም እንዲኖሩ ረጅም ዘመን እንደሚሰጣቸው ሲናገር :-❝አእምሮ የጎደለው መኮንን ትልቅ ግፈኛ ነው፡ ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል።❞ ምሳ ፳፰፥፲፮ በማለት ብዙ ዘመን ከሚያሰጡ ተግባራት አንዱ ግፍ መጸየፍ እንደኾነ ነግሮናል፡፡ ✅#የእግዚአብሔርን_ሕግ_መጠበቅ ዘመንን ያረዝማል ረጅም ዘመናትን ከሚያጎናጽፉ ምግባራት አንዱ ሕገ እግዚአብሔርን መጠበቅ ነው ነው ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጠብቁ ረጅም ዘመን ይኖራሉ እንዲያውም እንደነ ሄኖክና እንደነኤልያስ የመሰሉ ቅዱሳን ጨርሶ ከዐይነ ሞትም የተሠወሩ አሉ፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን :- ❝ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለላደረገ ሞት አላገኘውም፡፡❞ ዘፍጥ ፭፥፳፬። ✅አባታችን ኢዮብ ሲናገር:- ❝በሽምግልና ጊዜ ጥበብ በዘመን ርዝመት ማስተዋል ይገኛል፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኀይል አለ።❞— ኢዮ ፲፪፥፲፪ ብሎ እንደተናገረው ዕድሜያችን በጨመረ ቁጥርእያስተዋልንና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የምንሄድ ከኾነ እግዚአብሔር ረጅም ዕድሜ ይሰጠናል፡፡ ✅ነቢዩ ዳዊት :-❝የድሮውን ዘመን አስብኩ የዘለዓለም ዓመታት አሰብኩ! አጠነጠንኩ በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትኩ ነፍሴንም አነቃቃኋት፡፡❞መዝ ፸፮፥፭ ሲል ከዚህ በፊት የተደረገልንን የእግዚአብሔርን ውለታ በማሰብ ነፍሳችንን ለምስጋና ለበጎ ሥራ ማነቃቃት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ሌላው ደግሞ በጎ ዘመን ለማየት የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል ✅ነቢዩ አርምያስ:-❝እነሆ ስለእስራኤል ቤትና ስለይሁዳ ቤት የተናገርኩትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቁጥቋጦ አብቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል❞ኤር ፴፫፥፲፬ ሲል ለሚታገሡት መልካም ዘመን እንደሚያመጣ ተናግሯል፡፡ ✅ስለዚህ ዘመናችን እንዲረዝም ለደሀ ቸርነት ማድረግ ሌላው መንገድ ነው ነቢዩ ዳንኤል ናቡከደነጾርን ሲመክር:- ❝ንጉሥ ሆይ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነት ዘመን ይረዝም እንደኾነ ምክሬ ደስ ያሰኝ ኀጢአትህንም በጽድቅ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር፡፡❞— ዳን ፬፥፳፯ ሲል ለደሀ ቸርነት በማድረግ የኀጢአት ሥርየት እንደሚያገኝና ከታዘዘበት መቅሠፍት እንደሚተርፍ ተናግሯል፡፡ ✅ነቢዩ ዳዊት ደግሞ በጎ ዘመንን ማየት የሚወድ ይህን ያድርግ ይላል:- ❝ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድ አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ ክክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ስላምን ሻ ተከተላትም❞መዝ ፴፫፥፳፩ ሲል የበጎ ዘመን ባለቤት ለመኾን ከክፉ መሸሸ መልካምን ማድረግና ሰላምን መከተል አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደኾነ ነግሮናል፡፡ ✅ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ:-❝እንግዲህ ከጌታ መጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞ ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ ኀጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም❞ — ሐዋ ፫፥፲፱ ይለናል። ✅ንስሐ የምንገባበት፣ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን እያስደሰትን የምንኖርበት የተባረከ ዘመን ይሁንልን ምእመናን። መልካም አዲስ ዓመት!       መልአከ ፀሐይ ሠናይ ባያብል።                2019  ዓመተ ምህረት!!

Open in Telegram
Views2,610+327%vs avg
Forwards—
Reactions12
Comments—
#3124Text

መገናኛ እግዚ አብ አለቃ: ለተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት በሙሉ በያላችሁበት እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ!!! 💥➻📶#ዓመትን_በቸርነትህ_ታቀዳጃለህ📶➻💥 ✅❝ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፥ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም — በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።❞— መዝሙረ ዳዊት ፷፭፥፲፩  ዘመን የሚለወጥበት የመስከረም ወር ዘር ዘርተው ተክል ተክለው የሚኖሩ ሐረስተ ምድር በክረምት የዘሩትን ዘር አሽቶ አፍርቶ ምድርም በልምላሜ ተጊጣ እንስሳትም ለምለሙን ሣርግጠው የጠራ ውኃ ተጎንጭተው ጠግበው አምረው የሚታዩበት የልምላሜና የፍሬ ወር ነው። ✅ነቢዩ ዳዊት፦❝ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፣ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልላታለህ ቡቃያዋንም ትባርካለህ፡ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል:: የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፡፡ ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፣ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም”ብሎ እንደዘመረው። ✅እግዚአብሔር ዓመታትን በቸርነቱ እየለወጠ፤ የበረከት እጁን ሳያጥፍ እየመገበ፤ የሰዎችን ማንነት ሳይለይ ለክፉም ለደጉም፤ ለኀጥኡም ለጻድቁም፣ ለድሀውም ለሀብታሙም፣ ለአሕዛብም ለሕዝቡም የምሕረት ዝናቡን እያወረደ ፍጥረትን በሙሉ የሚያረካ አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያስገነዝበናል:: እንዲሁም ሥነ ፍጥረትን ብንመረምር የበጋና የክረምት መፈራረቅ፤ ተራሮች በዝናብ መርካታቸው፤ከድርቀት (ከፀሐይ) ወራት በኋላ የሚመጡት የበረከት ጊዜያት እንዴት ባለ በሚያስደንቅ ሁኔታ የምድሪቱን ገጽታ እንደሚቀይር እንገነዘባለን፡፡ ✅በመሆኑም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዓመታትን በቸርነቱ ለሚያቀዳጅ ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ የአዲሱን ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዐውደ ዓመት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› በሚል ስያሜ ስታከብረው ኖራለች ትኖራለችም:: ✅ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱና የቤተ ክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርእስ ዐውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ በመደንገጋቸው ነው:: (ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ):: መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ/መስከረምን/ሲያትት-❝ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው❞ በማለት ያስረዳል። ✅ከዚህም በተጨማሪ ብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት) የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ይህ ቀን «የዘመን መለወጫ» ተብሎ ይጠራል:: ✅ከላይ እንዳየነው የዘመን መለወጫ ፍሬ ሐሳብ እንደዚህ ከሆነ እኛስ በአዲስ ዘመን ምን ልናደርግ ይገባናል? ❝አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል❞ ማቴ ፮፥፴፭ ብሎ ጌታችን እንዳስተማረው እኛም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አዲሱ ዓመት ደርሰናል፤ ይህም በእኛ መልካምነት ሳይሆን ሁሉንም ሳይለይ (በአንድነት) በቸርነቱ ከመልካምነቱ እንዲሁ ያለዋጋ በሚያድል በእግዚአብሔር የተከናወነ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ባለፈው ዘመን የነበሩ ዘንድሮ ግን በሕይወተ ሥጋ የሌሉ ብዙዎች ናቸው፤ እኛም የምንጠራበት ሰዓት መቼ እንደ ሆነ አናውቅምና አበው ዘመን ለፍሥሐ እድሜን ለንስሐ እንዲሉ። ​ ✅ይህን የሰጠንን ዓመት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መንገዳችንን በቃሉ በመምራት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም አበው :-❝ትውልድ የኀልፍ ትውልድ ይተርፍ — ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል❞ (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ ትርጓሜ) ከእኛ በፊት የነበረው ትውልድ እንዳለፈ ሁሉ ይኸኛውም ትውልድ በበኩሉ ኅላፊ ነው፡፡ ✅እኛ ክርስቲያኖች አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ሲተካ በምን ዓይነት መንፈስ ነው የምንቀበለው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልእክቱ :- ❝የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፣ በመዳራት እና በሥጋ ምኞት፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለልክም በመጠጣት፤ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና❞ በማለት ያስተምረናል፡፡ ፩ ጴጥ ፬፥፫ ✅በአጠቃላይ እግዚአብሔር በቸርነቱ ዘመንን ያቀዳጀን በመንፈሳዊ ሕይወት ታድሰን ተለውጠን አዲስ የተሻለ መንፈሳዊ ሰው እንድንሆን ነው:: አዲስ ሰው መሆን ማለት ያለፈ ዘመንን ክፉ ግብር መተው፣ ደግሞም ኀጢአት ላለመሥራት መታቀብና ራስን መግዛት ነው:: ✅በተጨማሪም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ለመጨረሻዋ የፍርድ ቀን መልካም ቃል የሚያሰማንን ተግባር ለማከናወን ለመልካም ሥራ መነሣሣት፣ የመንፈስ ፍሬያትን ማፍራት ያስፈልጋል::❝የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።❞ገላ ፭፥፳፪ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው እንዲል:: ፪ኛ ቆሮ ፮፥፪ አዲሱ ዓመት ከኀጢአታችን በንስሐ ውኃ የምንታጠብበት። ✅ጌታችንና መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ በቀራንዮ የቆረሰልንን ቅዱስ ሥጋውን የምንበላበት፣ ያፈሰሰልንን ክቡር ደሙን የምንጠጣበት በጎ ዘመን እንዲሆንልን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳን ተራዳኢነት ያስፈልጋል፡፡ ✅#የበጎ_ዘመን_መገለጫዎች፦በጎ ዘመን ሲባል ዘመኑ በራሱ ደግ ሥራ ሠርቶ ደግ ዘመን፤ ክፉ ሥራ ሠርቶ ክፉ ዘመን የሚባል አይደለም ዘመኑን ደግ አልያም ክፉ የሚያሰኘው በዘመኑ ያለው ትውልድ በሚሠራው ክፉ ሥራ ወይም ደግ ሥራ ነው፡፡ የሰው ልጅ የኑሮ ውድነቱን፣ የሰላም እጦቱን፣ የበረከት መራቆቱንና የመሳሰሉትን ችግሮችን እያየ ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ይሻላል እያለ ያለበት ዘመን ሲረግም ያለፈውን ዘመን ሲመርቅ ይስተዋላል፣ ነገር ግን ያለፈው ዘመን ከዚህ ዘመን የተሻለበት ምክንያት በጥበብ ስለማይመረምር። ✅መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን :-❝ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለህ ብለህ አትናገር❞ መክ ፯ ሲል ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ያለፈውን ዘመን እየመረቅን የሚተካውን እየረገምን መኖር እንደማይገባን ተናግሯል፡፡ ✅#እግዚአብሔርን_መፍራት_ዘመንን_ያረዝማል፦ዕድሜ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ መሆኑን ማንኛው አዳማዊ ፍጡር የሚዘነጋው አይደለም፤ አባታችን ኢዮብ:- ❝የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፤ የወሩም ቁጥር በአንተ ዘንድ ነው፣ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረክለት::❞ በማለት የዕድሜያችን ቁጥር የዘመናችን ቀመር በእርሱ ዘንድ የታወቀና የተወሰነ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ኢዮ ፲፬፦፭ ✅እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ ዕድሜያችንን እንደ ሽማኔ ያደራዋል  ሸማኔ የሽመና ሥራውን ሲሠራ የነጠላውን ለነጠላ፣ የጋቢውን ለጋቢ አድርጎ እንዳቀደው እንደፈቀደው ድሩን ያደራዋል። ✅እግዚአብሔርም የዕድሜያችንን ድር በወደደው መንገድ ያደራዋል፤ ይህን የዕድሜ ድር ከራሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊያሳጥረውና ሊያራዝመው አይችልም:: ነገር ግን ዕድሚያችን ከምንሠራው ሥራ የተነሣ ሊያጥር ወይም ሊረዝም እንደሚችል በሰሎሞን አንደበት ተነግሮናል፤

Open in Telegram
Views1,650+170%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#3123Text

፩ አዲሱ ዓመት (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው) ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የደስታ የሰላምና የጤና እንዲኾንላችሁ ትሻላችሁን? እንኪያስ ገና ከጅመሩ በስካር፣ በዘፈን፣ በገቢረ ኀጢአት ለማሳለፍ አታቅዱ፡፡ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያውን ዕለት ብቻ ሳይኾን እያንዳንዱን ቀን በገቢረ ኀጢአት አትጀምሩት፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ፣ ምግባር ትሩፋት በመሥራት አሐዱ በሉ እንጂ፡፡ ዕለታት ክፉዎች ወይም ጥሩዎች የሚኾኑት በተፈጥሮአቸው እንደዚያ ኾነው አይደለም፡፡ ዕለቱን ክፉ ወይም ደግ እንዲኾን የምናደርገው እኛው ነን፡፡ የአምናው ማክሰኞ ከዘንድሮ ማክሰኞ የተለየ አይደለም፡፡ የተለየ የሚያደርገው የእኛ ብርታት ወይም ስንፍና ብቻ ነው፡፡ የጽድቅን ሥራ የምንሠራበት ከኾነ አዲሱ ቀን ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመት ለእኛ መልካም ነው፡፡ ኀጢአት የምንሠራበት ከኾነ ግን ቀኑ ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመትም ክፉና መከራ የመላበት ይኾንብናል፡፡ አዲሱን ዓመት በበጐ ሥራ የምንጀምረው ከኾነ በዓመቱ በምናደርገው ማንኛውም ክንውን ላይ በጐ ተጽዕኖ ያሳድርብናል፡፡ በትግሃ ሌሊት፣ በቀዊም፣ በጾም በጸሎት እንድንበረታ ስንቅ ይኾነናል፡፡ በስካር፣ በዘፈን፣ በኀዘን የምንጀምረው ከኾነ ግን ዓመቱ ሙሉ እንዲህ የተጐሳቈለ ዓመትን እናሳልፋለን፡፡ ሕይወታችንን በከንቱ እንገፋለን፡፡ ዲያብሎስም ይህን ጥንቅቅ አድረጐ ስለሚያውቅ ዓመቱን በገቢረ ኀጢአት እንድንጀምረው እየቀሰቀሰ ነው፡፡ ፈቃዳችንን አጥፍቶ፣ ዓይነ ልቡናችንን አሳውሮ በዘፈን፣ በስካር፣ በዋይታ እንድንጀምረው በተለያየ መንገድ እየለፈፈ ነው፡፡ ሰነፍ ሰው “ቀኑ ክፉ ወይም መልካም የሚኾነው በእኔ ምክንያት አይደለም” ብሎ ያምናል፡፡ እንዲህ በማመኑም ክፉ ነው ብሎ በሚያስበው ቀን ገቢረ ጽድቅ መሥራት እንደሚቻል አያስብም። ቢያደርግም ትርጕም እንደሌለው አድርጐ ይቈጥሯል፡፡ የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በተመቻቸለት ቀንም ልል ዘሊል ከመኾኑ የተነሣ ምግባር ትሩፋት ለመሥራት አይሽቀዳደምም፡፡ ስንፍናው ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያመጣበት አይረዳም፡፡ ድኅነቱን ሳይፈጽም ዕድሜውን ኹሉ በከንቱ ይገፋል፡፡ እንዲህ ያለ የሥጋም የነፍስም ጕዳት እንደሚያገኘው ዲያብሎስ ዓይነ ልቡናውን ስለሚያሳውርበት ከአጋንንት ወጥመድ ለመሸሽ ዓቅምን ያጣል፡፡ ዲያብሎስም ዕለት ዕለት ይህን እንዳንገነዘብ በተለያየ ማጥመጃ መንገዶች እኛን ለመጣል ይሯሯጣል፡፡ አንዱ መንገድም ስለ ክርስትና ሕይወታችን ግድ እንዳይኖረን ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችንን ያሳጣናል፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ በገቢር እንድንሰድብ ያደርገናል፡፡ ነፍሳችንን በቆሸሸ ስፍራ ተወሽቃ እንድትቀር ያደርጋታል፡፡ የምወዳችሁ ልጆቼ! እኛ ግን ይህን ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ ከኀጢአት በቀር ክፉ ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ ከምግባር ከትሩፋት በቀርም መልካም ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዚህም ዘወትር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን ልንኖር እንዲገባን ማወቅ መረዳት ይገባናል፡፡ መጠጥ ደስታን አያመጣም፤ ደስታን የሚያመጣው ጸሎት ነው፡፡ ደስታን የምናገነኘው ቃለ እግዚአብሔርን ከመስማት እንጂ ከስካር አይደለም፡፡ ስካር የነፍስ መታወክን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ተመስጦን ያመጣል፡፡ ስካር ሁካታን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ሁካታን ያርቃል፡፡ ስካር ዓይነ ልቡና እንዲጨልም ያደርጋል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን የጨለመው ዓይነ ልቡናችን ብሩህ እንዲኾን ያደርጋል፡፡ ስካር የኀጢአት ጓዝ ይዞ ይመጣል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን አዲስ የሚመጡትን ብቻ ሳይኾን የነበሩትንም ያስወግዳል፡፡ ልጆቼ! የዚህን ዓለም ደስታ ንቆ ሰማያዊ ደስታን እንደ መሻት ያለ ጥበብ ምንም የለም ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡ ይህን ገንዘብ የምናደርግ ከኾነ፣ ለሰማያዊ ሕይታችን ቅድሚያን የምንሰጥ ከኾነ የዚህ ዓለም ዝባዝንኬ ቢቀርም አይከፋንም፡፡ አንድ ሰው ባለጸጋ ስለኾነ ቅናት አይይዘንም፡፡ ምንም ምድራዊ ሀብት ባይኖረንም ድኾች እንደኾንን አናስብም፡፡ ባለ ጸጋውን ክርስቶስ የያዘ ሰውስ እንዴት ድኻ ይባላል? በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ በዓል ማድረግ ማለትም ይኸው ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚወዳችሁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! አንድ ክርስቲያን በዓልን ሲያከብር ሳምንትን ወይም ወርን ወይም ዓመትን ጠብቆ መኾን የለበትም፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር እንደሚስማማ አድርጐ ዕለት ዕለት በዓል ሊያደርግ ይገቧል እንጂ፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር የሚስማማ በዓል ማለትስ ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምን እንደሚለን አብረን እናድምጠው፡- “በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም” (1ኛ ቆሮ.5፡8)፡፡ ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ዕለት ዕለት በዓልን ያከብራል፡፡ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተጠበቀለት ነው፡፡ ከሰማያዊው ማዕድና መጠጥ ተካፍሎ ሐሴት ያደርጋል፡፡ በዚህ ምድር ላይ የሚደረጉ ጊዜያዊ ክንውኖች ስለቀረበት የኾነ ነገር እንደቀረበት አያስብም፤ እርሱ ያገኘው ከዚህ በእጅጉ የሚልቅ ነውና፡፡ ነፍሱን ከሚያቆሽሹ ገቢረ ኀጢአቶች ራሱን ይጠብቃል፡፡ በገቢረ ኀጢአት ተሰማርተን ሳለ ሺሕ ጊዜ በዓላትን ብናከብር ግን እንዳከበርን ልንቈጥረው አይገባንም፡፡ ያከበርነው የበዓል ቀን (በዓል ማለት ደስታ ማለት ነው) ሳይኾን የኀዘን ቀን ነውና፡፡ ነፍሴ በኀጢአት ቀንበር ተይዛ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሳለች የደስታን ቀን ባከብር ለእኔ ምን ጥቅም ያመጣልኛል?.....ይቀጥላል (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ- ሰማዕትነት አያምለጣችሁ እና ሌሎች ገጽ 13-36)

Open in Telegram
Views1,890+209%vs avg
Forwards—
Reactions2
Comments—
#3121Text

«ልጅሽን ወስደሽ ቤቱ ቢሞት ይሻላል!» ዶክተሩ ለተጨነቀችው እናት ያለው ቃል ይህ ነበር… ምክንያቱም ህፃኑ ይተርፋል ብሎ ስላላመነ ። ነገር ግን እናት ተስፋ አልቆረጠችም ማንም ያልጠበቀው ድንቅ ነገር እስኪሆን ድረስ አባ ቄርሎስን ተማጸነች! 😭 -➤በዓለም ላይ ከትንሽ ልጇ በቀር ምንም የሌላት በጣም ደሃ ሴት ነበረች፤ የልጇም ዕድሜ 9 ዓመት ነበር።በድንገት ህፃኑ በጽኑ የሰውነት ማቃጠል (ትኩሳት) ተመታ፤ የሰውነቱ ሙቀትም እስከ 40 ዲግሪ አድጎ እየጨመረ ሄደ። -➤እናቱም ፈጥና በአባሲያ ወደ ሚገኘው የትኩሳት ህክምና ሆስፒታል ወሰደችው፤ ነገር ግን ሁኔታው በጣም አደገኛ ስለነበር ዶክተሩ ትክ ብሎ እያያት በግልጽ እንዲህ አላት፦ «እመቤቴ…ልጅሽን ወስደሽ ቤቱ ቢሞት ይሻላል…እንዲያውም ልጅሽ ሞቷል፣ እዚሁ ሆስፒታል ውስጥ አልቅሰሽ ሁከት እንድትፈጥሪ አንፈልግም።» -➣ከዚያም የክፍሉ ኃላፊ መጥቶ ከህክምና አንጻር ህፃኑ እንደ ሞተ ተቆጥሮ የሬሳ የቀብር ሂደቶችን የሚያቃልል ደብዳቤ ሰጣት። ነገር ግን እናት እምነቷን አላጣችም! -➣ዶክተሩን በተስፋ እየለመነች፦«ስለ እግዚአብሔር ብለህ መውጣቴን እስከ ቅዳሜ አዘገይልኝ» አለችው። ➨እርሱም፦«ነገ አርብ ነው፣ እዚህ ምንም ዶክተሮች አታገኚም» አላት። -➤እርሷም በጽናት፦ «ስለ እግዚአብሔር ብለህ… እንዳልኩህ አድርግልኝ» ስትል መለሰችለት። ➨ዶክተሩም፦ «እሺ እመቤቴ… ያመንሽበትን አድርጊ» አላት። በዚህ ጊዜ እናት የመጨረሻዋን የተስፋ ጭላንጭል ጨበጠች -➤ወደ ቤቷ ሄዳ ከቅዱስ ማርቆስ ገዳም (ዴር ማርሚና) ያመጣችውን ትልቅ የአባ ኪርሎስ ምስል አመጣች፤ በወቅቱ ለምስሉ ማዕቀፍ (ፍሬም) እንኳን የምታወጣው ገንዘብ አልነበራትም። -➤በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተመልሳ ምስሉን በልጇ አካል ላይ አኖረችው፤ ከአጠገቡ ተቀብጣ እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር ትማጸን፣ የአባ ቄርሎስንም አማላጅነት ትለምን ጀመር። ➨ከድካምና ከኀዘን ብዛት የተነሳ ድንገት እንቅልፍ ወሰዳት… ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት (3:00 AM) ሲሆን! በድንገት… የልጇን ድምፅ ሰማች፦ «እማዬ… ውኃ ልጠጣ.» 😳 ዓይኖቿን ገልጣ የምታየውን ማመን አልቻለችም! ሁሉም ይሞታል ብለው ይጠብቁት የነበረው ልጇ… ከአልጋው ወርዶ ያናግራታል! ፈጥና አቀፈችው፤ አካሉንም ስትዳስስ ትኩሳቱ ሙሉ በሙሉ ለቆት አገኘችው! -➣ነገር ግን ትልቁ አስደናቂ ነገር ምስሉን ስታይ ነበር የልጁ ሆድ በዘይት (ቅዱስ ቅባት) ተሸፍኖ አገኘችው! ➦እናቱም ጠየቀችው፦ «የኔ ፍቅር፣ ይህ ዘይት ከወዴት መጣ?» ህፃኑም ወደ አባ ቄርሎስ ምስል ጠቅሶ እንዲህ አለ፦«ዘይቱን ያደረገው እርሱ ነው።» ➥እናት ከደስታዋ ብዛት ጮኸች፤ ዜናውም በሆስፒታሉ ባሉ ሰራተኞችና ታካሚዎች መካከል ተሰራጨ። ሁሉም እንዲህ እያሉ ይጠይቁ ነበር፦ «ይህን ተአምር ያደረገው የአባ ኪርሎስ ምስል ወዴት አለ?!» ታሪኩ እንደሚለው የቅዱሱ አማላጅነት እንዲደርሳቸው በሚል ታካሚዎቹ የሕመም ቦታቸው ላይ ለማስቀመጥ ምስሉን ቆራርጠው እያንዳንዳቸው ጥቂት ጥቂት ተካፈሏት። 🙏🏻 ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን የአቡነ ቄርሎስ ምልጀው አይለየን

Open in Telegram
Views2,010+229%vs avg
Forwards—
Reactions12
Comments—
#3118Text

❖✔ ልጇ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ዐድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን ድል ነሥቶ እንደተነሣ አማናዊት ታቦቱ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም በልጇ ሥልጣን ርሷ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ከልጇ ከንጉሡ ቀኝ በክብር ቆማለች (መዝ ፵፬፥፱)፡፡ ✔❖ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በነሐሴ ፲፮ የቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል ብሔራዊ በዓል ተደርጎ በተለያዩ ሀገራት ሲከበር ዕርገቷ ይታሰብባቸው ከነበሩ ሀገራት ውስጥም ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ አንዶራ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ክሮሺያ፣ ኢኳዶር፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ሊባኖስ፣ ጣሊያን፣ ማልታ፣ ስሎቬኒያ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩማኒያ፣ ቺሊ፣ ሳይፕረስ፣ ሀይቲ፣ ሴኔጋል፣ ስሎቬኒያ፣ ስፔን፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ ኮትዲቭዋር፣ ማዳጋስካር እና ሌሎች በርካቶች የዓለም ሀገራት። ❖✔ ልጇ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ዐድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን ድል ነሥቶ እንደተነሣ አማናዊት ታቦቱ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም በልጇ ሥልጣን ርሷ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ከልጇ ከንጉሡ ቀኝ በክብር ቆማለች (መዝ ፵፬፥፱)፡፡ እንኳን አደረሳችሁ እህት ወንድሞቼ

Open in Telegram
Views2,280+273%vs avg
Forwards—
Reactions5
Comments—
#3117Text

❖✔ ያን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በዕለተ ዐርብ ከአምላኩ በስጦታ የተሰጠችውን የአምላክ እናትን ሥጋዋን በድፍረት ሊነኩ መምጣታቸውን አይቶ “ይቤ ዮሐንስ ወኢይገድፍ ምዕቅብናየ ወዘንተ ብሂሎ ወድቀ በላዕሌሃ” ይላል (ዐደራዬን አላፈርስም፤ ከርሷ ጋር እሞታለኊ በማለት ይኽነን ተናግሮ በላይዋ ላይ ወደቀ፡፡ ከዚያም “ወወረዱ ሚካኤል ወገብርኤል እምሰማይ በዐቢይ ግርማ” ይላል ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በታላቅ ግርማ ወርደው የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋዋንና ቅዱስ ዮሐንስን በደመና ነጥቀው በገነት በሕይወት ዛፍ ሥር አኖሯት፡ ፡ ❖✔ ወዲያውኑ “ወአምጽኡ ሎቱ ማዕጠንተ ወርቅ” ይላል የወርቅ ማዕጠንት ለዮሐንስ አምጥተውለት፤ “ወዕጥን ሥጋሃ ለማርያም መዓልተ ወሌሊተ” ይላል የቅድስት ድንግል የከበረ ሥጋዋን በመዓልትና በሌሊት ዕጠን አሉት፤ ዮሐንስም ይኽነን ክብር በመቀበሉ ደስ ብሎት ሥጋዋን እያጠነ “ወፍና ሠርክ ያመጽዕ ሎቱ ራጉኤል መልአክ ኅብስተ ሰማይ” ይላል ሰርክ ሲኾን ራጉኤል መልአክ ሰማያዊ ኅብስት ሰማያዊ መጠጥ እያመጣለት ያን እየተመገበ በገነት ቆይቷል፡፡ ❖✔ ኋላም በጌታ ፈቃድ ከተቀሩት ሐዋርያት ጋር ተገናኘ፤ ሐዋርያትም የእመቤታችንን ነገር እንደምን እንደኾነ ሲጠይቁት ርሱም በገነት ያየውን ነገር ነገራቸው፤ እነሱም ይኽነን ታላቅ ምስጢር ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ሱባኤ ነሐሴ 1 ዠመሩ ነሐሴ 14 ቀን በኹለተኛው ሱባኤ ጌታ የእናቱን ሥጋ አምጥቶ ሰጥቷቸው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ ❖✔ በተወደደች ዕለት ነሐሴ 16 “ወአዘዞሙ እግዚእነ ለሰብአቱ ሊቃነ መላእክት ከመ ይጸውዕዋ ለምድር” (ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ምድርን ይጠሯት ዘንድ አዘዛቸው) እነርሱም ምድርን “ይኤዝዘኪ እግዚእነ ከመ ታውጽኢ ሥጋሃ ለእሙ ቅድስት” (ጌታችን የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ ያዝሻል) አሏት፤ ያን ጊዜ ልጇ “ንዒ ኀቤየ ወላዲትየ ከመ አዕርጊ ውስተ መንግሥተ ሰማያት” (ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ እናቴ ወደኔ ነዪ) አላት፤ ያን ጊዜ በልጇ ሥልጣን የቅድስት ድንግል ማርያም ነፍሷና ሥጋዋ ተዋሐዱ፤ ነሐሴ 16 ዕለትም ከሞት ተነሣች፡፡ ❖✔ ያን ጊዜ “ወረዱ መላእክት ወሊቃነ መላእክት” ይላል ቅዱሳን መላእክት ከሰማይ በታላቅ ግርማ ወረዱ፤ ነቢዩ ዳዊትም “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ” (ንግሥቲቱ ወርቀ ዘቦ ግምጃ ደርባ ደራርባ በቀኝኽ ትቆማለች) እያለ ይዘምርላት ነበር፤ አየሩ ኹሉ በቅዱሳን መላእክት ተመላ፤ እጅግ የሚያስደንቅ መዐዛ አካባቢን ዐወደው፡፡ ❖✔ ስለ አካላዊ ዕርገቷ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው በቊ ፹፪ ላይ፡- “አመ ነሥኡኪ እምኤዶም አዕላፈ ማሕሌት ጾታ እንዘ ይጼልሉኪ ድንግል በአክናፈ መባርቅት ከመ ወልታ ሰራዊተ ሰማይ ይቤሉ ለክብረ ፍልሰትኪ ግርማ ትርሲታ መኑ ይእቲ ዛቲ ዘገዳመ ጽጌ ዕጥነታ ወከመ ሠርጸ ጢስ ዘስኂን ይምዕዝ ዕጥነታ” (ድንግል ወገኖች አመስጋኞች መላእክት በየነገድ በየነገድ ኾነው በመባርቅት ክንፎች እንደ ጋሻ ጋርደው ከኤዶም ገነት በተቀበሉሽ ጊዜ የሚያስደንቅ ክብር ለተገለጸባት ለዕርገትሽ የሰማይ ሰራዊት አበባ ካለበት በረሓ የምትወጣ መዐዛዋም ከነጭ ዕጣን ይልቅ የሚሸትት አወጣጧም እንደ ጢስ አወጣጥ የኾነችይኽቺ ማናት? ይኽቺ ማን ናት ይላሉ (መሓ ፫፥፲፮)) በማለት በአስደናቂ መልኩ ዕርገቷን ገልጸዋል፡፡ ❖✔ ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው ላይ “ፈለሰት ማርያም በስብሐት ውስተ ሰማያት መላእክት ወሊቃነ መላእክት ወረዱ ለተቀብሎታ” (እመቤታችን በምስጋና ወደዚያኛው ዓለም በተለየች ጊዜ ለአቀባበሏ መላእክትና ሊቃነ መላእክት ወረዱ) ይለዋል፡፡ ❖✔ ያን ጊዜ በታላቅ ክብር በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ሰማዩ ኹሉ በቅዱሳን መላእክት ተመልቶ የአምላክ እናት በክብር ስታርግ ተመለከተ፤ ያን ጊዜ ነገሩ ረቆበት ምን ይኾን እያለ ሲል ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችን ዕርገት እንደኾነና እጅ እንዲነሣ ነገሩት፡፡ ❖✔ ርሱም “ከቶ ምን አርጌ ይኾን፤ ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ ሳላይ ቀረኊ ዛሬ ደግሞ የርሷን ትንሣኤ ሳላይ ልቅር” ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል ተበጻብጾ ሊወድቅ ወደደ፤ እመቤታችንም “አይዞኽ አትዘን እነሱ ሞቴን አይተዋል እንጂ ዕርገቴን አላዩም አኹንም እመቤታችን ተነሣች ዐረገች ብለኽ ንገራቸው” ብላ ለበረከት ሰበኗን ሰጠችው፡፡ ❖✔ ርሱም በደስታ ተመልቶ ሐዋርያት ያሉበት በመኼድ የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ ብሎ ጠየቃቸው፤ እመቤታችን ሞተች ቀበርናት አሉት፤ “መቼ ሞተች?” አላቸው በጥር አሉት፤ “መቼ ቀበራችኋት?” አላቸው በነሐሴ አሉ፤ ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይኽ ነገር እንዴት ይኾናል አላቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስም ቶማስን ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ አላምን ብለኽ የጌታን ጐን የዳሰሰ እጅኽ ተቃጥሎ ነበር፤ አኹን ደግሞ እኛ ብንነግርኽ አላምን ትላለኽ ብሎ፤ “ወነሥአ መክርየ” ይላል መቆፈሪያ ይዞ ኼዶ ይቆፍር ጀመር። ❖✔ ርሱም የያዘውን ይዟልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፤ ቈፍረው ሲያጧት ደነገጡ፤ ቶማስም አይዟችኊ አትደንግጡ እመቤታችን እኮ በመላእክት ምስጋና ወደ ሰማይ አረገች ብሎ ሰበኑን አሳያቸው፤ እነርሱም ለበረከት ሰበኑን ተካፍለውታል፡፡ ዛሬም ሐዋርያዊት የኾነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይኽነን በማሰብ በመስቀል ሥር የሰበኗ ምሳሌ የሚኾን ሰፊ ጨርቅ ታደርጋለች፡፡ ❖✔ ባመቱ ቶማስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በድጋሚ ሐዋርያት ሱባኤ ሲገቡ ክብር ይግባውና ጌታችን በደመና ነጥቆ ወስዶ ሥርዓተ ቊርባንን ፈጽሞላቸው፤ ስለ እናቱ ዕርገት በዓለሙ ኹሉ ዙረው እንዲያስተምሩ አዝዟቸዋል፡፡ እነርሱም ዓለምን ዞረው ወንጌልን ሲያስተምሩ የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት ሰብከዋል አስተምረዋል፡፡ ❖✔አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ወደ ምጡቅ ሰማይ ስለተደረገው ዕርገቷ ፡- “እንዘ ይፀውረኪ በሐቂፍ ወይስዕመኪ በአፍ አመ አፍለሰኪ ወልድ ውስተ የማኑ ለዐሪፍ ጽጌ ዕፀ ገነት ማርያም ዘትጼንዊ ለአንፍ እንዘ ይትጓድዑ አክናፈ በክንፍ ለቀበላኪ ወረዱ አእላፍ” (ለአፍንጫ መዐዛን የምትሰጪ የገነት ዛፍ ማርያም ሆይ፤ ልጅሽ በክንዱ ዐቅፎ በአፉ እየሳመ በቀኙ ሊያሳርፍሽ ባሳረገሽ ጊዜ፤ አንቺን ለመቀበል ክንፍ ለክንፍ እየተጋጩ እልፍ አእላፋት መላእክት ወረዱ) በማለት አስተምረዋል፡፡ ❖✔ በተመሳሳይ መልኩ ዳግመኛ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው በቊ፹፬ ላይ፡- “ትእምርተ ፍልሰትኪ እምድረ ጽጌ ድንግል በክልኤ በደመና ሰማይ አርአየ ዘሐዋርያት ጉባኤ ወእለ ሞቱ አንቅሐ እምከርሠ መቃብር ቀርነ ጽዋዔ ለነሰ እንዘ ይብሉ ሶበ ሰማዕነ ውዋዔ መሰለነ ዘበጽሐ ትንሣኤ” (በኹለት ወገን ድንግል የኾንሽ ማርያም ሆይ አበባ ካለበት ምድር ወደ ሰማይ የማረግሽ ተአምር በሰማይ ደመና የሐዋርያት ጉባኤን አሳየ፤ የሞቱትንም ከመቃብር ውስጥ በተአምር ነጋሪት ድምፅ አስነሣ፤ ለእኛስ የምስጋና ከፍተኛ ድምፅን በሰማን ጊዜ የሙታን መነሣት የደረሰ መሰለን እስኪሉ ድረስ) በማለት ሐዋርያትን ተሰብስበው ሳሉ ዕርገቷን እንዲያዩ እንዳደረጋቸው ጽፈዋል፡፡

Open in Telegram
Views1,850+203%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#3116Text

መንፈሳዊ ጉባኤ: መንፈሳዊ ጉባኤ: መንፈሳዊ ጉባኤ: "ቃለ እግዚአብሔር ": ፍልሰታን የፆመ ይህቺን ፁሁፍ ለማንበብ ጊዜ አያጣም። ሳታነቡ እንዳታልፉ። ❖የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕርገት ነሐሴ 16 ✍ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ነሐሴ 16 ቀን አስደናቂውን የእመቤታችንን የዕርገቷን በዓል ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፤ የቅድስት ድንግል ማርያም መላ ዕድሜዋ 64 ሲኾን ይኸውም በእናት ባባቷ ቤት 3 ዓመት፤ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፤ ጌታን ፀንሳ በቤተ ዮሴፍ 9ወር ከ5 ቀን፤ ከልጇ ጋር 33 ዓመት ከ3 ወር ከቆየች በኋላ፤ ዓለምን ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜም የሚወድዳት እናቱን ለሚወድደው ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ “እነኋት እናትኽ” በማለት አደራ በመስጠት በዮሐንስ በኩል ለሚወድደን ለእኛ የአደራ ልጆቿ እንድንኾንና የአደራ እናታችን እንድትኾን ታላቅ ስጦታን በቀራንዮ በእግረ መስቀል ሥር ሰጠን (ዮሐ ፲፱፥፳፮‐፳፯)፡፡ ❖✔ በዚኽም መሠረት ሐዋርያትም ከአምላካቸው የተሰጠቻቸው የአምላካቸውን እናት ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ 72ት ቋንቋ ገልጾላቸው ታላቅ መንፈሳዊ ኀይልን ሰጣቸው (የሐዋ 1፥14)፤ ዮሐንስም በእናትነት የተቀበላት ቅድስት ድንግል ማርያምን በቤቱ 15 ዓመት አኑሯታል፡፡ ❖✔ በነገረ ማርያም በብራናው ላይ እንደተጻፈ 64 ዓመት ሲመላት ልጇ ክርስቶስ ለእናቱ ተገልጾ ከኀላፊው ዓለም ወደ ማያልፈው ሰማያዊዉ ዓለም ሊወስዳት እንደኾነ ነገራት፤ ርሷም ይኽነን ለሐዋርያት ነገረቻቸው፤ እነርሱም “አይቴ ተሐውሪ እግዝእትነ” (እመቤታችን ወዴት ትኼጃለሽ) ብለው ሲጠይቋት “ኀበ ጸውአኒ ወልድየ” (ልጄ ወደ ጠራኝ) በማለት ወደዚያኛው ዓለም የመኼጃዋ ጊዜ እንደደረሰ ነገረቻቸው፤ ይኽነን ሰምተው “ወበከዩ ኲሎሙ ሐዋርያት” ይላል ሐዋርያት በእጅጉ ዐዘኑ አለቀሱ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ተገልጸው ሐዋርያትን ማዕጠንታቸውን ይዘው ደስ አሰኝተው እንዲሸኝዋት እንጂ እንዳያዝኑ እንዳያለቅሱ በመንገር አረጋጓቸው፡፡ ❖✔ ጌታም እናቱን “እኔ ኹሉን መጋቢ የኾንኹትን ያጠቡ ጡቶሽን የተባረኩ ናቸው፡፡ እንዲኹም በከፍታ ቦታዎች ወደሚገኙ ሰማያዊ ስፍራዎች ወስጄሽ በአባቴ በመልካም ነገሮች እመግብሻለኊ፡፡ እስከዚያው በጉልበትሽ ላይ ያስቀመጥሺኝ ድንግል እናቴ ማርያም ሆይ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ በማኖር ከእኔና ከቸሩ አባቴ ጋር ወደ ሰማያት እወስድሻለኊ፡፡ ❖✔ በመጠቅለያ ጨርቆች እንደጠቀለልሽኝ ኹሉ የእኔ ድንግል እናት ማርያም ሆይ በወለድሽኝ ዕለት በከብቶች በረት ከላም እና አህያ ጋር በአንድ ላይ ከብበውኝ እንዳኖርሽኝ ኹሉ (ኢሳ ፩፥፫፤ ሉቃ ፪፥፯)፤ እኔ ደግሞ ዛሬ ከእኔ ጋር ከሰማያት ባመጣዋቸው በሰማይ መጐናጸፊያ ሰውነትሽን እጠቀልለዋለኊ፤ ከዚያም ከሕይወት ዛፍ ሥር አስቀምጠዋለኊ፣ ኪሩቤልም በሰይፈ ነበልባላቸው እንዲጠብቁት አደርጋለኊ (ዘፍ ፫፥፳፬)፡፡ ❖✔ የተባረከችውን ነፍስሽን የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም መንበር በተሸፈነችበት መሸፈኛዎች እንድትሸፈን አደርጋለኊ፡፡ እኔን በሚያሳድድበት ጊዜ ሥርዓት አልባውን ሄሮድስ በመፍራት ወደ ግብጽ ምድር እንደተሰደድሽው ኹሉ (ማቴ ፪፥፲፫-፲፰)፤ መላእክቶቼ ኹልጊዜም በክንፎቻቸው እያጠሉብሽ እና መልካም ዝማሬያቸውን እንዲዘምሩልሽ አደርጋለኊ” አላት፡፡ ❖✔ ይኽነንም ልጇ እያላት ጥር 21 እሑድ ዕለት በልጇ ፈቃድ በመዐዛ ገነት፣ በመዝሙረ ዳዊት፣ በይባቤ መላእክት የእመቤታችን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች፤ ጌታም እንደ በረዶ ጸዐዳ የኾነውን የድንግል ማርያምን ነፍስ በዕቅፉ ውስጥ እንደያዘ ለነፍሷ የከበረ ሰላምታውን ሰጥቶ ባማረው ሸማ ጠቅልሏት ለሊቀ መልአኩ ለቅዱስ ሚካኤል በብርሃናማ ክንፎቹ እንዲሸከማት ሰጠው፡፡ ❖✔ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይኽነን ይዞ በድጓው ላይ “ፃኢ እምሊባኖስ ሥነ ሕይወት ርቱዕ አፍቅሮትኪ ቡርክት አንቲ እምአንስት ማኅደረ መለኮት ሰላም ለኪ፤ ማርያም እመ አምላክ ወልድኪ ይጼውዐኪ ውስተ ሕይወት ወመንግሥተ ክብር” (የሕይወት ደም ግባት የአምላክ እናት ከሊባኖስ ውጪ፤ ፍቅርሽ የቀና ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ፤ የመለኮት ማደሪያ ሰላምታ ላንቺ ይገባል፤ የአምላክ እናት ማርያም ሆይ ልጅሽ ወደ ዘላለማዊ ሕይወትና ወደ ክብር መንግሥት ይጠራሻል) በማለት አመስጥሮታል፡፡ ❖✔ ቅዱሳን ሐዋርያትም ሥጋዋን በክብር ገነዘዋል፤ ከኢትዮጵያ ሊቃውንት መኻከል ስለዚኽ በቅዱሳን ሐዋርያት ስለተደረገው የከበረ የሥጋዋ ግንዘት ቅዱስ ያሬድ አምልቶ አስፍቶ የጻፈ ሲኾን፤ በነሐሴ ፲፭ በአጫብሩ ድጓ ውስጥ በአስደናቂ መልኩ እንዲኽ ተጽፈዋል፡- ╬ “ሐዋርያት አመድበሉ ሥጋ ድንግል ጠብለሉ በሰንዱነ ብርሃን ዘላዕሉ ልብሳ ተካፈሉ” (ሐዋርያት ተሰበሰቡ፤ ከላይ በመጣ በፍታ (መጐናጸፊያ) የድንግል ሥጋን ጠቀለሉ፤ ልብሷንም ተካፈሉ) ╬ “በደመና ተጋቢኦሙ ሐዋርያት ለድንግል ንጽሕት ገነዝዋ በክብር ወበስብሐት ለቀበላሃ ወረዱ ኀይላት ወቀበርዋ ውስተ ገነት” (ሐዋርያት በደመና ተሰብስበው ንጽሕት ድንግልን በክብር በምስጋና ገነዟት፤ ለአቀባበሏ ኀይላት ወረዱ፤ በገነት ውስጥም ቀበሯት) ╬ “ተጋቢኦሙ ሐዋርያት እምኲለሄ በደመናት ዘምሉእ ሡራኄ ገነዙ በክብር ወበስባሔ ሥጋ ድንግል ዘይምዕዝ እምርሔ” (ብርሃንን የተመላ በኾነ በደመናት ሐዋርያት ከአራቱ ማእዝን ተሰብስበው ልብን ከሚመስጥ ሽቱ ይልቅ የሚሸትት የድንግልን ሥጋ በክብርና በምስጋና ገነዙ) ╬ “ተጋቢኦሙ በደመና ሰማይ ሐዋርያት ሥርግዋን በዕበይ ገነዝዋ ለድንግል በብዙኅ ግናይ ዳዊት ዘመራ በመሓልይ” (በገናንነት የተጌጡ ሐዋርያት በሰማይ ደመና ተሰብስበው ድንግልን በብዙ ምስጋና ገነዟት፤ ዳዊትም በምስጋና አመሰገናት፡፡) ╬“ተጋቢኦሙ አርድዕተ ወልዳ በደመና ብርሃን ጸዐዳ ገነዝዋ በስብሐት ለጽርሕ ሳይዳ” (ጸዐዳ በኾነ በብርሃን ደመና የልጇ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበው፤ ውቢቱ አዳራሽን በምስጋና ገነዟት) ╬ “ተጋብኡ በቅጽበት ለግንዘተ እሙ ቅድስት ብፁዓን ሐዋርያት ቦኡ ኀቤሃ በሰላም አምኁ ኪያሃ በስብሐት ገነዙ ሥጋሃ” (ንኡዳን ክቡራን ሐዋርያት ቅድስት የምትኾን የጌታ እናቱን ለመገነዝ በቅጽበት ተሰበሰቡ፤ ወደ ርሷ ገብተው በሰላምታ ርሷን እጅ ነሧት፤ ሥጋዋንም በምስጋና ገነዙ) በማለት ሊቁ ማሕሌታይ በሐዋርያት እጅ የተደረገ የሥጋዋን ግንዘት አምልቶ አስፍቶ ጽፏል፡፡ ❖✔ ሐዋርያት በታላቅ ግርማ በአምላክ እናት ሥጋ ፊት ምስጋናን እያሰሙ ዝማሬን እየዘመሩ ሥጋዋን እጅ እየነሡ ጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ሲኼዱ አይሁድ አይተው ለምቀኝነት አያርፉምና ቀድሞ ልጇ ሞተ፣ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ እያስተማሩ ኖሩ ከመቃብሩም ተአምራት ይደረጋል፤ አሁን ደግሞ ርሷ ሞተች፣ ተነሣች፣ ዐረገች ብለው ሊያስተምሩ አይደል፤ “ንዑ ናውዒ ሥጋሃ ለማርያም ምስለ ዓራታ” በማለት እናቃጥላለን ብለው በምቀኝነት ተነሡባቸው፤ ታውፋንያ የሚባል ከአይሁድ ወገን በድፍረት የአልጋዋን አጎበር ሊነካ ሲሞክር ቅዱስ ገብርኤል በሰይፈ እሳት ቀጣው፡፡

Open in Telegram
Views1,540+152%vs avg
Forwards—
Reactions3
Comments—
#3114Text

↳ ✍️   ቅዱሱ ተራራ ✍️↲(፪ኛ ጴጥ፩÷፲፯-1፲፰ ) ደብረታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከ፱ኙ ዐበይት በዓላት መካከል የደብረታቦር በዓል አንዱ ነው፡፡      በእስክንድርያ ግን ዐበይት በዓላቶቻቸው ፯ ናቸው፡: በዚህም ምክንያት ከዐበይት በዓላት ውስጥ አስገብተው ደብረታቦር አይቆጥሩትም ፡ይሁን እንጂ በበዓልነቱ አይከበርም ማለት ግን አይደለም።       ደብረታቦር ወይም የታቦር ተራራ ጌታ በምድረ እስራኤል እየተዘዋወረ በማሰተማር ላይ በነበረበት ዘመን ነሐሴ ፲፫ ቀን ብርሃ መለኮቱንና ክብረ መንግስቱን የገለጠበት ታሪካዊ በዓል ነው፡፡ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙውን ጊዜ የሚስተምረውና ተአምራት የሚያደርገው በተራራ ላይ ነበር፡(ማቴ ፲፯÷፬) ይህን በዓል ከቅዱስ ዮሐንስ በቀር ፫ቱም ወንጌላውያን በየወንጌሎቻቸው መዝግበውታል(ማር፬÷፪ ፲፫ ፤ ሉቃ ፱÷28-36)      ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም “ ከገናናው ክብር ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ከምስጋናን ተቀብሎአልና እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህ ድምጽ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን” በማለት የተገለጸውን ምስጢር ታላቅነት መስክሮአል(፪ኛ ጴጥ፪÷፲፯-፲፰፣በዓላት በዲ.ን ብርሃኑ አድማስ)      ቅዱሳን ሐዋርያት ብርሃነ መለኮቱን ካዩ በኋላ የቃላቸው ትምህርት የእጃቸውም ተአምራት ብቻ ሳይሆን የልብሳቸውም ቁራጭ ጥላቸው ጋኔን ያወጣ ድወይ ይፈውስ ነበር( ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ)       ይህ ተራራ ከገሊላ ባሕር በምስራቅ ደቡባዊ በኩል ፲ ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን 572 ኪ.ሜ ከፍታ አለው፡፡የታቦር ተራራ በሐዲስ ኪዳን በግልጽ ባይጠቀስም በብሉይ ኪዳን ግን ተጠቅሶ እናገኘዋለን(መሳ ፬÷፮-፲፬) ቅዱስ ዳዊትም “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ወይሰብሑ ለስምከ መዝራዕትከ ምስለ ኃይል፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡ ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፡፡ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች(መዝ 88÷12-13) ይላል፡፡ በደብረታቦር ዲቦራም ዘምራበታለች፡፡       ጌታችን በቂሣርያ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰው ልጅን ማን ብለው ይጠሩታል “ በማለት በጠቃቸው ቀን የቀሩት ደቀ መዛሙርት በተራራው ሥር ትቶ ሦስቱን ( ጴጥሮስን ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በተራራው ላይ ሳሉ የጌታችን መልክ ተለውጦ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፡ልብሱም እንደ በረዶ የነጻ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ብርሃነ መለኮቱንና ክብረ መንግስቱን ገለጠ(ሉቃ9÷29) በደብረታቦር ተራራ ፭  ነገር ተከናውኗል፤ ሙሴና ኤልያስ ሲነጋገሩ ተሰምቷል፡፡       -መልኩ ተለወጠ (ወተወለጠ አርአያሁ በቅድሜሆሙ) (ማቴ ፲፯÷፪) በዚህ ሰዓት በሐዋርያት ላይ ያደረ ሥጋዊ መንፈስ ራቀ፡ በውስጣቸው ያለው የጨለማ ፍርሃት አሰወገደላቸው( ጥርጥርን አለማመን እነዚህን ነገሮች ሀሉ ከልቡናቸው አስወገደላቸው፤ ፡የእግዚአብሔርን ክብር እንዲያስታውሉ አእምሮቸው ብሩህ ሆነ፡፡በደመና ውስጥ ሁኖ የምወልደው የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን የሚል ቃል ተሰማ ( ዝንቱ ወእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ሰምዕዎ) ደመና የእግዚአብሔር የክብሩ ምሳሌ ነው፡፡       ልብሱ እንደ በረዶ ነጻ ( ወአልባሲሁኒ ኮነ ከመ ፀዓዳ) ጌታችን በደብረ ታቦር ተራራ የብሉይና የሐዲስ ኪዳ ሰዎችን ( ነቢያትና ሐዋርያትን ) አንድ አደረጋቸው፡፡ እሱ አምላካችን መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ነውና ፡፡ሌላው ምስጢር ሙሴና ኤልያስ የተጠሩበት ሙሴ ነህ ይላሉ ኤልያስ ነህ ይላሉ ሲሉት እርሱ አምላከ ሙሴ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ሊያሳይ ነው፡፡        ከነቢያቱ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ “ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም ( ዘዳ 33÷28) በተባለው መሠረት “እባክህ ክብርህን ( ፊትህን) አሳየኝ ይህ ካልሆነማ ባለሟል መባሌ ምኑ ላይ ነው (ዘጸ33÷18-23) የሚለውን የባለሟልነት ጥያቄውን ሙሴን ከሙታን አስነስቶ ስለክብሩ የቀናውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ክብሩን አሳይቷቸዋል የሙሴን ጸሎት ሳይረሳ ልመናውን ፈጸመለት፡፡ በጀርባ የተመሰለው ከ5500 በኋላ የተፈጸመው ምስጢረ ሥጋዌ ነው፡፡           ሙሴና ኤልያስ መሆናቸው በምን ይታወቃል?    ሙሴ ብልቱትነቱ ኤልየስም በፀጉርነቱ አንድም በአነጋገራቸው ታውቋል፡፡ ሙሴም የእኔን የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ይልሃል እግዚአ ሙሴ ይበሉህ እንጂ ኤልየስም የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ይልሃል እግዚአ  ኤልያስ ይበሉህ እንጂ ሲሉ ተሰምተዋል፡፡        አንደድም ምውት ለሕያው ሕያው ለምውት ሲጸልዩ ተስምተዋል፡፡ አንድም ሙሴ እኔ ባሕር ብከፍል ጠላት ብገድል ደመና ብጋርድ መና ባወርድ እስራኤላውያንን ከክፋታቸው መመለስ አልተቻለኝም ላንተ ግን መልሶ ማደን ይቻልሃልና፡፡     ኤልያስም እኔ ሰማይ ብለጉም እሳት ባዘንብ እስራኤላውያንን ከክፋታቸው መመለስ አልተቻለኝም ላንተ ግን መልሶ ማደን ይቻልሃልና ሲሉ ተስምተዋል ( አንድምታ ወንጌል ማቴ ምዕ.፲፯)         ፍጻሜው ግን ደብረታቦር የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ናት፡፡ሕጋውያንም ደናግልም እንዲወርሷት ለማጠየቅ ከሕጋውያን ሙሴን ከደናግል ኤልያስን አመጣ፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በምእመናን ዘንድ የተለየ ስም አለው( ቡሄ ይባላል)፡፡    ቡሄ ማለት መላጣ ( ገላጣ) ማለት ነው፡፡ በሀገራችን ክረምቱ አፈናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየው በደብረታቦር በዓል አካባበር ስለሆነ “ቡሄ “ ያሉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሊቃውንት "ቤሄ ከዋለ የለም ክረምት ደሮ ከጮኸ የለም ሌሊት”እንዲሉ(የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ- 127-128) - ሕፃናት የሚያጮሁት ጅራፍ ጩኸት ድምፅ የድምፀ መለኮት ጅራፍ ሲጮህ ማስደንገጡን የሦስቱ ሐዋርያት ምሳሌ ሲሆን  መደንገጣቸው በድምፀ መለኮቱ መደንገጣቸውን መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡    - በአንዳንድ ቦታዎች የቡሄ ዕለት ማታ ችቦ ያበራሉ በደብረታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ - ምእመናን በድበረታቦር ክብሩን አየን ዛሬም ያ ክበሩ ለገለጥን ያስፈልጋል፡፡ እገዚአብሔር ክብሩን የገለጠበት ያ ተራራ ዛሬ የእኛ አካል ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ክብሩና ጥበቡ የሚገለጥበት ማዳኑ የሚታይበት የተባረከ ሕይወት ሊኖረን ይገባል - የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ ስለእኛ ጸልዩ     እንኳን አደረሰን

Open in Telegram
Views1,770+190%vs avg
Forwards—
Reactions4
Comments—
#3112Text

#እንኳን_አደረሳቹ_አደረሰን_የተዋህዶ_ልጆች_በሙሉ😘🙏 ✝️🌿👉 #ቡሄ_ጅራፍ_ማስጮህ ✝️🌿👉 #ችቦ_ማብራት ✝️🌿👉 #ሙልሙል_ዳቦ - ሐይማኖታዊ ምስጢራቸው ምንድነው⁉️ #ደብረ_ታቦር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዕቆብን ፣ ዮሐንስንና ጴጥሮስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ከወሰዳቸው በኋላ በዚያ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትና ሙሴና ኤልያስን ጠርቶ የህያዋንና የሙታን አምላክነቱን ያሳየበት ከዘጠኙ የጌታ ዓበይት በዓለት ውስጥ አንዱ ነው። ✝️🌿💚💛❤ ቤተክርስቲያናችንም የተለያዩ ስርዓቶችን በመፈፀም አክብራው ታልፋለች፡፡ #በደብረ ታቦር በዓል የሚፈጸሙ ( #ቡሄ ፣ #ጅራፍ ማስጮህ ፣ #ችቦ ማብራትና #ሙልሙል_ዳቦ ) ትውፊታዊ የሃይማኖት ስርዓቶች ምሳሌዎች ምን እንደሆነ እናያለን፡፡ ✝️🌿💚💛❤ #ቡሄ ቡሄ ማለት ብራ ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ከስሙ ትርጉም እንደምንረዳው ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል ስለሆነ ብራ፣  ብርሃን ደማቅ የሚል ፍቺ ያለው ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ አንድም ቡሄ ማለት ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት ስለሚመጣ ሰማይም ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቀት ስለሆነ ብራ ተብሏል፡፡ ✝️🌿💚💛❤ " ቡሄ ከዋለ የለም ክረም ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት እንዲሉ " አንድም ቡሄ…..ቡኮ "/ሊጥ" ማለት ነው፡፡ በዚህ በዓል ቡኮ ተቦክቶ ዳቦ/ ሙልሙል / ተጋርሮ የሚታደልበት በዓል ስለሆነ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ✝️🌿💚💛❤ ✝️🌿👉 #ሙልሙል_ዳቦ ሙልሙል ዳቦ አመጣጡ ጌታችን ብርሃናዊ መለኮቱን በገለጠበት በዚህ ዕለት በደብረታቦር አካባቢ የነበሩ ህፃናት እረኞች ቀኑ የመሸ ስላልመሰላቸው / ጌታችን በብርሃን አካባቢውን ሞልቶት ስለነበረ / በዛው ሆነው ከብትና በጎቻቸውን እየጠበቁ ሲቆዩባቸው የሰዓቱን መግፋት የተመለከቱ ወላጆች በችቦ ብርሃን ተጠቅመው ለልጆቻቸው የሚቀመስ ሙልሙል ዳቦ ይዘው ወዳሉበት መምጣታቸውን ያሳያልና ታሪኩን እየዘከርን በዓሉን እናከብራለን፡፡ ✝️🌿💚💛❤ #አንድም እንደ #ሐዋርያት_የምስራችሲነግሩን ወንጌል ሊሰብኩልን በየደጃፋችን መጥተው " ቢሄ በሉ " የሚሉትን ታዳጊዎችን ይበሉት ዘንድ ይሰጣቸዋል ይህም መጽሐፋዊ ነው ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን በደረሳችቡት ሁሉ ተመገቡ /ማቴ 10፥12/ ብሏልና ህፃናቱም የጌታን በዓል ሊያበስሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ ሳይሆን ህፃናቱም የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ ✝️🌿💚💛❤ #መዝሙራቸው ደግሞ የምስራች ወንጌል ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋሪያት በገቡበት ሀገር ሁሉ አስተምረው አጥምቀው የፀጋ ልጅነትን አሰጥተው እንደሚቆዩ ሁሉ ልጆችም ዘምረው አመስግነው መርቀው ውለዱ ክበዱ የመንግስተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ብለው አመስገነው ይሄዳሉና በሐዋሪያት ህፃናቱ ይመሰላሉ፡፡ ✝️🌿💚💛❤ ✝️🌿👉 #ችቦ_ማብራት ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥን የሚያመለክት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር መለኮቱን ሲገልጥ ብርሃን አካባቢውን ሞልቶት ነበርና ያንን በዘመናችን ለመግለጥ የበዓሉ ዋዜማ ማታ ችቦ አብርተን አምላካችንን እናመሰግናለን፡፡ አንድም ደግሞ የችቦ ታሪክ ከላይ እንደገለፅነው የእረኞቹ ወላጆች ይዘውት የመጡት ብርሃን ነው፡፡ ✝️🌿👉 #ጅራፍ የጅራፍ ምሳሌነት በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ሚስጥር በእየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ሞቱ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ በዓል ጅራፍ መገመዱ እና ማጮሁ ሁለት አይነት ምሳሌ አለው፡፡ ✝️🌿💚💛❤ ✝️🌿 #የመጀመሪያው_ምሳሌ - ጌታችን በዕለተ አርብ የደረሰበትን ግርፋትና ህማም እናስብበታለን፣ ✝️🌿 #ሁለተኛው_ምሳሌ -  ደግሞ ድምፁን ስንሰማ የባህሪ አባቱን የአብን የምስክርነት ቃልና በግርማው ሲገለጥ የተሰማውን ነጎድጓድ ያስታውሰናል፡፡ ✝️🌿💚💛❤ የጅራፍን ትውፊታዊ ውርስ መጽሐፋዊ ትምህርቱንና ምስጢሩን ከትውልድ ጠብቆ ማስተላለፉ ተገቢ ነው፡፡ ✝️🌿💚💛❤ በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከነዚህ ሚስጢር ካላቸው ትምህርቶችና ትርጓሜያቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብል እንደመጣልን እኛም ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ሳይለቅ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል፡፡ የዚህ ነገር ባለ ድርሻ አካላት ደግሞ ወጣቶችና ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቡሄ ጨዋታ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ ፊዝና ሳቅ ይታይባቸዋል ተጫዋቾቹም ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን አይነት መልዕክት ያስተላልፋሉ። የሚብሰው አሳባቢ ነገሩ ደግሞ ኃይማኖታዊ ስርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛ መቀየሩ ነው፡፡ ✝️🌿💚💛❤ ስለሆነም ይህን ነገር በተለይ የነገ የሀገር ተረካቢና የቤተክርስቲያን ተተኪ የሆንን ወጣቶች ማስተካከል ይኖርብል፡፡ ወላጆችም ሕፃናት በየደጃፋችን ላይ በዓሉን ሊያበስሩ ሲመጡ አስደንግጦ ከማባረር በሚገባው መልኩ አስተምረን መርቀን ማስተናገድ ይጠበቅብናል ባህሉም እንዳይተው የበኩላችንን አደረግን ማለት ነው። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን

Open in Telegram
Views1,410+131%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—
#3110Text

‹‹ፍልሰታ›› የሚለው ቃል «ፈለሰ» ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ መለየት፣ ማረግ እና ወደላይ መውጣት ማለት ነው። የእመቤታችን ዕረፍት፦ እመቤታችን ድንግል ማርያም ያረፈችው በጥር 21 ቀን ነው። ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሄዱ አይሁድ በምቀኝነት ስለተቃወሟቸው መላእክት አስከሬኗን ነጥቀው በገነት አኖሩት። የሐዋርያት ሱባዔና ቀብር፦ ሐዋርያት ከነሐሴ 1-14 ሱባዔ ገብተው በጸሎት ከጌታችን ተቀብለው በክብር ቀበሯት። የቅዱስ ቶማስ ምስክርነት፦ ሐዋርያው ቶማስ በወቅቱ ባለመኖሩ በሦስተኛው ቀን እመቤታችን ስታርግ በደመና ላይ አያት። እርሷም ማጽናኛ እና ምስክር እንዲሆን ሰበኗን ሰጠችው። የሐዋርያት በረከት፦ ቶማስ ሰበኗን ለአካፈላቸው በኋላ፣ ሐዋርያትም የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገት ለማየት በዓመቱ ከነሐሴ 1 ጀምረው ሱባዔ ገቡ። በነሐሴ 16 ቀን ጌታችን ከመላእክት ጋር መጥቶ እመቤታችንን አስነሥቶ አሳይቷቸዋል። ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሐዋርያትን ምሳሌ ተከተላ ከሰባቱ አጸዋማት አንዱ በማድረግ ይህንን ጾም እንድንጾም አዝዛናለች። የጾሙና የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን! 🙏

Open in Telegram
Views2,100+244%vs avg
Forwards—
Reactions17
Comments—