መረን የለቀቀውና ሸሪአዊ ገደብ ሊበጅለት የሚገባው የለቅሶ ቤት ጉዳይ የጁምአ ኹጥባ ወራቤ አቡበከር መስጅድ 📌አቡ ሱለይማን ኻሊድ ሙሀመድ https://t.me/ibnmuha
Open in TelegramPosts of ፈዋኢድ (فوائد)
Forwarded from ወራቤ[ ደርሶች እና ፈዋኢዶች ]
የወርሃዊ የዳዕዋ ፕሮግራም ጥሪ! ወደ አላህ የሚያቀርብህን ዕውቀት ለመቅሰም፣ ልብህን በኢማን ለማደስና ከመልካም ሰዎች ጋር ለመሰብሰብ ተዘጋጅተሃልን? እነሆ! የወርሃዊ የዳዕዋ ፕሮግራማችን የዚህ ወር ተራ ደርሷል። በቀደሙት ወራት በተለያዩ መስጂዶች የተካሄዱትን የዳዕዋ ፕሮግራሞች በመቀጠል፣ በዚህ ወር የምንገናኘው በ ዓኢሻ መስጂድ ይሆናል። 📖 የአላህን ቃል ለመስማት፣ 🌱 የዲን ዕውቀትን ለመጨመር፣ 🤝 የወንድማማችነትን ትስስር ለማጠናከር፣ ❤️ ልቦችን በኢስላማዊ እሴቶች ለማቀራረብ። 🗓 ቀን፦ መጪው እሁድ 6/3/2019 ዓ.ል. 📍 ቦታ፦ ዓኢሻ መስጂድ 🔺ውድ የወራቤና አካባቢዋ ሙስሊሞች! ይህን ፕሮግራም የሌላው ሰው ጥሪ ብቻ አድርጋችሁ አትመልከቱት፤ ለራሳችሁ የዲን ዕድል አድርጉት። በእውቀት የተገነባ ማኅበረሰብ በአንድ ቀን አይፈጠርም፤ እንዲህ ባሉ የዕውቀትና የኢማን ስብሰባዎች ይገነባል። እንገናኝ! እንማር! እንተሳሰብ! በዲናችንም አብረን እንጠናከር! የአላህ ፈቃድ ከሆነ በዚህ የተባረከ ስብሰባ እንገናኛለን። https://t.me/fewaidworabe
Open in TelegramForwarded from አቡ ሱለይማን ኻሊድ ሙሀመድ ዲናዊ ጥያቄዎች መመለሻ
تركناهم لله … ለአላህ ተውናቸው በክፉ ጥርጣሬ ለተመለከቱን፣ ባልሠራነው ለከሰሱን፣ በእኛ ውስጥ የሌለውን ባሕርይ በእኛ ላይ ለለጠፉት፣ ልባቸውንም በሐሰት ግምት ሞልተው እስከሚያምኑበት ድረስ ለደረሱት… ለአላህ ተውናቸው። ያነወሩንን፣ የበደሉንን፣ ውለታችንን የረሱትን፣ ልባችንን ያቆሰሉትንና የሰበሩትን፣ በሐሰት የከሰሱንንና ያልተናገርነውን የቀጠፉብንን፣ ስማችንን ያጎደፉትን፣ ንግግራችንን ያጣመሙትን፣ በበደል ላይ በደል የጨመሩትን ሁሉ… ለአላህ ተውናቸው። መልስ ማጣት ሳይሆን ከከንቱ ክርክር ራሳችንን ለማራቅ፣ የማይጠቅም ሙግትን ንቀን፣ ከቂምና ከበቀል ስሜት በላይ ሆነን፣ ፍርዳችንን በአላህ ፍትሕና ሚዛን ላይ በመተው… ለአላህ ተውናቸው። እርሱ ስለ እኛ ከራሳችንም በላይ ዐዋቂ ስለሆነ፣ የእኛን እውነታ ከእነርሱ ጥርጣሬ በላይ በሚገባ ስለሚያውቅ፣ የተደበቀውን ሁሉ ስለሚመለከት፣ በስሜትና በግል ጥቅም ከሚነዱ ሰዎች ሁሉ በላይ በፍርዱ ፍትሐዊ ስለሆነ… ለአላህ ተውናቸው። https://t.me/ibnmuha2
Open in TelegramForwarded from ወራቤ[ ደርሶች እና ፈዋኢዶች ]
🔴ሁሉም ተበዳይ ከሆነ፣ በዳዩ ማን ነው? በዘመናችን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በዝተው ከሚታዩ ነገሮች አንዱ የሰዎች የሀዘንና የተበዳይነት ትረካ ነው። አንዱ በሰዎች እንደተከዳ ይጽፋል፤ ሌላው የሰጠው ፍቅር በህመም እንደተመለሰበት ይናገራል፤ ሌላው ደግሞ ማንንም ማመን እንደማይቻል ይመክራል። ብቸኝነት፣ ክህደት፣ ብስጭትና የሰው ልጅን አለመታመን በብዙ ጽሑፎች ውስጥ የሚደጋገሙ ርዕሶች ሆነዋል። ይህን ሁሉ ስናይ ግን አንድ ጥያቄ ማንሳት አይቀርም፦ ሁሉም ተበዳይ ከሆነ፣ በዳዩ ማን ነው? ወይስ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ታሪክ ውስጥ ተበዳይ ሆኖ ሲታይ፣ በሌላው ታሪክ ውስጥ ደግሞ የጉዳቱ ምንጭ ሊሆን ይችላል? የራሳችን ታሪክ ብቻ ሙሉው እውነት አይደለም ሰው የራሱ ስቃይ በጥልቀት ይሰማዋል፤ የሌላውን ግን ለመረዳት ሲቸገር ይስተዋላል። የተደረገበትን ስህተት በቀላሉ ያስታውሳል። እሱ በሌላው ላይ ያደረሰውን ጉዳት ግን በጭራሽ ትዝ አይለውም ። የራሱን ዓላማ በጎ አድርጎ ያያል፤ የሌላውን ምላሽ ግን ሁሌ በመጥፎ መልኩ ይረዳል። ምናልባትም ይህ ነው የሰው ልጅ ከሚያጋጥሙት ትልልቅ ተቃርኖዎች አንዱ፤ ራሳችን ስንጎዳ ቀጥታ እንፈርዳለን፤ ሌላውን ስንጎዳ ግን ሰበብ እናበዛለን። ይህ ማለት የሚያማርር ሰው ሁሉ ተጠያቂ ነው ወይም የሚናገረው እውነት አይደለም ማለት አይደለም። ሰዎች በእውነት ይበደላሉ፤ ይከዳሉ፤ ይጎዳሉ። ነገር ግን የአንድ ሰውን ታሪክ ብቻ በመስማት ሙሉውን እውነት እንደያዝን መቁጠር የለብንም። አንዳንዶች ስሜታቸውን ለማቃለል ይጽፋሉ፤ ሌሎች የሚሰማቸውን ለማካፈል ወይም ድጋፍ ለማግኘት ይፈልጋሉ። አንዳንዶችም ራሳቸውን በተበዳይነት መልክ በማቅረብ የሌሎችን ርኅራኄና ትኩረት ለማግኘት ሊሞክሩ ይችላሉ። ስለ ስቃይ መጻፍ የስቃይ ማስረጃ ብቻ ነው እንጂ የሰውየውን ባህሪ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አይደለም። እንዲሁም ስለ ሌሎች መጥፎነት በተደጋጋሚ መጻፍ የሚጽፈው ሰው እውነትን እንደያዘ በራሱ አያረጋግጥም። ሁሉንም ሰው አትመን የሚለው ምክር ምን ያህል ትክክል ነው? የሆኑ ሰዎች ከዱህና ሰው ሁሉ ከዳተኛ አይሆንም። የሆነ ሰው ከጎዳህ ሰው ሁሉ ጎጂ አይሆንም። በተወሰነ ግንኙነት የደረሰብህ ጉዳት በሌሎች ሁሉ ላይ እንድትፈርድ ምክንያት መሆን የለበትም። አዎን፣ ሰዎችን በጥንቃቄ ማመን ጥበብ ነው። ቃላቸውንና ተግባራቸውን ማነጻጸር፣ ድንበራችንን መጠበቅና እምነታችንን በጊዜ ሂደት መገንባት ያስፈልጋል። ግን ጥንቃቄን ከጥርጣሬ፣ ጥበብንም ከፍርሃት ጋር መደባለቅ የለብንም። የአንድ ሰው ክህደት ለሰው ልጅ ሁሉ የምትፈርድበት ሕግ አይሁን። ያለፈው ልምዳችን ለወደፊቱ ጥበብ ይሁንልን እንጂ ከሰዎች ሁሉ የሚያርቀን ግድግዳ አይሁን። ❓ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ▪️ሌሎች እንዲረዱን እንፈልጋለን፤ እኛስ ሌሎችን ለመረዳት እንሞክራለን? ▪️ስህተታቸውን እንዲቀበሉ እንጠብቃለን፤ እኛስ የራሳችንን ለመቀበል ዝግጁ ነን? ▪️የደረሰብንን በደል እናስታውሳለን፤ እኛ ሳናውቅ በሌላ ሰው ላይ ያደረስነውን ጉዳትስ እንመረምራለን? 🔺አንድ የመጨረሻ ሐሳብ በሕይወት ውስጥ መጎዳት አለ፤ መከዳትም አለ፤ መሳሳትም አለ። ነገር ግን የሰው ልጅ እድገት የሚለካው ስንት ጊዜ እንደተበደለ በመቁጠር ብቻ አይደለም፤ ከደረሰበት ጉዳት ምን እንደተማረ፣ የራሱን ስህተት ለማረም ምን እንዳደረገና ሌሎችን ላለመጉዳት ምን ያህል እንደጣረም ጭምር ነው። ስለዚህ ሁልጊዜ ስለ ቁስላችን ከመናገር ይልቅ እሱን ለመፈወስ እንሥራ። ሁሉም ስለ ተበዳይነቱ በሚናገርበት ዓለም፣ የራሱን ድርሻ በቅንነት የሚመረምር ሰው መሆን እውነተኛ ጥበብ ነው። ✍ أبو سليمان
Open in Telegram🍃 የማይመለከትህን ነገር ተወው! ከሰው ልጅ ውብ ባሕርያት አንዱ፣ የማይመለከተውን ነገር መተው ነው። ሁሉንም ማወቅ አይጠበቅብህም፤ ስለ ሁሉም ነገር መናገርም አይገባህም። የሰማኸውን ሁሉ መከታተል፣ የተመለከትከውን ሁሉ መተንተን፣ በሌሎች የግል ጉዳዮች ውስጥ መግባትና በሕይወታቸው ላይ ፍርድ መስጠት የጥበብ ምልክት አይደለም። አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ እየቻልክ መተው፣ መናገር እየቻልክ ዝም ማለት፣ መግባት እየቻልክ ራስህን መግታት ትልቅ ጥበብ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ነገር አንተን አይመለከትም፤ ሁሉም ነገር የአንተን አስተያየት አይፈልግም። አንዳንድ ሰዎች በሌሎች ሕይወት ውስጥ በመግባት ያላቸውን ጊዜ ሁሉ ያባክናሉ፤ የሰዎችን ምስጢር ለማወቅ፣ ውሳኔዎቻቸውን ለመተቸትና ስህተቶቻቸውን ለመቁጠር ይተጋሉ። በዚህ ሁሉ መካከል ግን የራሳቸውን ጉድለት ለማረምና ሕይወታቸውን ለማሻሻል የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ ያጣሉ። 🌿 የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦ «مِنْ حُسْنِ إِسْلَامِ الْمَرْءِ تَرْكُهُ مَا لَا يَعْنِيهِ» «ከአንድ ሰው እስልምና ማማር ምልክቶች አንዱ፣ የማይመለከተውን ነገር መተዉ ነው።» 📚 ሱነኑ ቲርሚዚ፣ 2317 ወዳጄ ሆይ! ለሁሉም ነገር ምላሽ መስጠት አያስፈልግም፤ በሁሉም ጉዳይ ውስጥ መግባትም ግዴታ አይደለም። አንዳንድ ነገሮችን በዝምታ ማለፍ ለልብህ ሰላም፣ ለአእምሮህ እረፍትና ለጊዜህ በረከት ይሆናል። 🔺ነገር ግን የማይመለከትህን ነገር መተው ማለት በደልን እያየህ ዝም ማለት ወይም እርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው መተው አይደለም። በመልካም ማዘዝ፣ ከክፉ መከላከልና ሰዎችን መርዳት በሚገባበት ቦታ በጥበብና በእውቀት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። እውነተኛ ጥበብ የምታውቀውን ሁሉ መናገር አይደለም፤ መናገር የሚገባውን ማወቅ ነው። እውነተኛ ብስለትም በሁሉም ጉዳይ ውስጥ መግባት ሳይሆን፣ መግባት የሚገባውንና መተው የሚገባውን መለየት ነው። 🌱 የማይመለከትህን ነገር መተው ኪሳራ አይደለም፤ የልብ ሰላምን፣ የጊዜ በረከትንና የባሕርይ ውበትን የሚያስገኝ ጥበብ ነው። أبو سليمان
Open in Telegramነገር ግን የማስተማር አቅም ያላችሁ፣ በዲን እውቀት የተለያችሁ፣ የምታስተምሩት ተማሪ ያላችሁ፣ መጻሕፍትን በማብራራት ሰዎችን ልትጠቅሙ የምትችሉ ወንድሞች ሆይ፦ የምትችሉትን የማስተማር ሥራ በማኅበራዊ ሚዲያ ዝና ፍለጋ እንዳታጡ! በየመድረሳው ተቀምጣችሁ አስተምሩ። መጻሕፍትን አብራሩ። ተማሪዎችን አሳድጉ። ቁርአንንና ሱናን በትክክል አስተምሩ። ሰዎች በዲናቸው የሚያስፈልጋቸውን እውቀት አድርሱ። በዚህ ሥራ የሚያሳልፋችሁ ጊዜ በቀጥታ በተከታይ ቁጥር ላይታይ ይችላል፤ ግን አላህ ዘንድ ያለው ምንዳ ከሰዎች የምስጋና ድምፅ ጋር አይመዘንም። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦ «مَنْ دَلَّ عَلَى خَيْرٍ فَلَهُ مِثْلُ أَجْرِ فَاعِلِهِ» «ወደ መልካም ነገር የመራ ሰው፣ ያንን መልካም ሥራ እንደሠራው ሰው ያለ ምንዳ ይኖረዋል።» 📚 ሰሒሕ ሙስሊም፣ 1893 አንድ ተማሪ ያስተማራችሁትን እውቀት ለሌላ ሰው ሊያደርስ ይችላል፤ ያ ሰውም ለሌላ ሊያደርስ ይችላል። እንዲህ የእውቀት ሰንሰለት በትውልዶች መካከል ይቀጥላል። ይህ የማስተማር ታላቅ ፍሬ ነው። 7. መፍትሔው ማኅበራዊ ሚዲያን መተው አይደለም ማኅበራዊ ሚዲያን መተው አያስፈልግም። ይልቁንም በትክክል መጠቀም ያስፈልጋል። አንድ መምህር በመድረሳ የሚያስተምረውን ትምህርት በድምፅ ወይም በቪዲዮ አዘጋጅቶ ለብዙ ሰዎች ሊያደርስ ይችላል። መጽሐፍ ማብራራት ይችላል። ጠቃሚ የዲን ጥያቄዎችን በማስረጃ መመለስ ይችላል። ለተማሪዎች የሚጠቅሙ የትምህርት ተከታታይ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ይችላል። በዚህ መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያው የማስተማር ተቃራኒ ሳይሆን የማስተማር መሣሪያ ይሆናል። የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ሚዲያን መጥላት ሳይሆን የምንጠቀምበትን ዓላማ ማስተካከል ነው፤ የሚያስፈልገው ዜናን መኮነን ሳይሆን ለእያንዳንዱ ሰው የሚመጥነውን ሥራ መለየት ነው። 8. በመጨረሻ፦ ለምን እንደተነሳን እንመርምር! ወንድሞች ሆይ! ዓላማችን ሰዎች እንዲያውቁን ብቻ ከሆነ፣ የሰዎች ትኩረት ሲቀንስ ጥረታችንም ሊቀንስ ይችላል። ዓላማችን ግን አላህን ማስደሰትና ሰዎችን መጥቀም ከሆነ፣ ብዙ ሰው ባያየንም በትጋት እንቀጥላለን። የማይታወቅ መምህር በየመድረሳው እውቀትን እያስተላለፈ ሊሆን ይችላል፤ ዝናው የማይታወቅ ዳዒ የሰዎችን ሕይወት እየቀየረ ሊሆን ይችላል፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታይ የሌለው አስተማሪ ግን ለትውልድ የሚበቃ እውቀት እያበረከተ ሊሆን ይችላል። እንግዲህ የሚያስፈልገን ተከታይ ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በእውቀት የተገነባ ትውልድ ነው። የሚያስፈልገን የዜና ድምፅ ብቻ ሳይሆን፣ የማስተማር ድምፅም ነው። የሚያስፈልገን የሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሰዎችን ልብና አእምሮ በእውቀት የሚገነቡ መምህራንም ናቸው። አላህ ለዲኑ የሚጠቅሙን ሥራዎች ይምራን፤ እውቀትን እንድንማርና እንድናስተምር ያግዘን፤ ሥራችንንም ለእርሱ ብቻ የተጣራ ያድርግልን። ወንድሞች ሆይ፣ የምታስተምሩበት አቅም ካላችሁ፣ ወደ ማስተማር ተመለሱ! ትውልድ እየጠበቃችሁ ነው። ✍ አቡ ሱለይማን ኻሊድ ሙሀመድ
Open in Telegram✔ ዜናውን ለነ ሙራድ ብንተውላቸውስ? ወንድሞች ሆይ፣ ወደ ማስተማር ተመለሱ! ማን ነው የሚያስተምረው? ማን ነው የሚያሳድገው? ማን ነው የነገውን ትውልድ የሚገነባው? ከዘመናችን አሳሳቢ ክስተቶች አንዱ፣ በእውቀት፣ በማስተማር ችሎታና በዳዕዋ ልምድ የታደሉ አንዳንድ ወንድሞች በማስተማር ላይ ከመትጋት ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ዜናዎችን በማስተላለፍ፣ የሰዎችን ክስተቶች በመተንተንና በተለያዩ የወቅቱ ጉዳዮች ላይ በመናገር ብዙ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ ማየታችን ነው። እዚህ ላይ ጥያቄው ዜና ማስተላለፍ ስህተት ነው ወይ? የሚል አይደለም። ትክክለኛ ዜናን ማስተላለፍ፣ ማኅበረሰቡን ማሳወቅና ለሕዝብ ጥቅም መሥራት የሚያስመሰግን ተግባር ሊሆን ይችላል። ጥያቄው ግን፦ የማስተማር አቅም ያለው ሰው ዋነኛ ጊዜውን፣ ጥረቱንና እውቀቱን በምን ላይ ማዋል አለበት? የሚለው ነው። 1. ተከታይ ማብዛት ነው ዓላማችን፣ ወይስ እውቀትን ማስፋፋት? ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታይ ለማግኘት ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ የወቅቱን ዜና ማስተላለፍ፣ የሰዎችን ንግግር መተንተን፣ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ማንሳትና ስለተለያዩ ክስተቶች ዘወትር መናገር ነው። ይህ አካሄድ በራሱ ስህተት ባይሆንም፣ የዳዕዋ ሰዎች ሁሉ ወደዚህ አቅጣጫ ከተሳቡ ግን ማን ነው የሚያስተምረው? ማን ነው የሚያብራራው? ማን ነው የሚያሳድገው? ማን ነው በየመድረሳው ተቀምጦ የሚያስተምር፣ የተማሪዎችን ጥያቄ የሚመልስና የማያውቁትን በትዕግሥት የሚያስረዳው? ተከታይ ብዛት የእውቀት ጥልቀት መለኪያ አይደለም። ብዙ ሰዎች የሚያዩት መልእክት ሁሉ የሰዎችን እውቀት የሚጨምር አይደለም። በአንድ ዜና ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሰበሰቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን በአንድ ጠቃሚ የዲን ትምህርት ላይ የሚቀመጡት ጥቂቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ግን ያ ትምህርት ከዜናው ያነሰ ዋጋ አለው ማለት አይደለም። የዳዕዋ ስኬት በተከታዮች ቁጥር ብቻ አይመዘንም፤ በሚተላለፈው እውቀት፣ በሚታረሙ ስህተቶችና በሚቀየሩ ሕይወቶችም ይመዘናል። 2. የመድረሳ ሚንበር ሊተካ የሚችለው በማኅበራዊ ሚዲያ ነውን? የመድረሳ ማስተማር ቀላል ሥራ አይደለም። ተማሪዎችን ማስተማር፣ መጽሐፍ ማብራራት፣ የተማሪዎችን ደረጃ መከታተል፣ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ማረምና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ትውልድ ማፍራት ብዙ ጊዜና ትዕግሥት ይጠይቃል። አንድ መምህር ለዓመታት በቋሚነት ያስተማረው ተማሪ፣ በኋላ አስተማሪ፣ ኢማም፣ ዳዒ ወይም ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ሰው ሊሆን ይችላል። ይህ ተጽዕኖ ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያ በተመዘገበ የእይታ ቁጥር ላይ ላይታይ ይችላል፤ ግን በማኅበረሰብ ሕይወት ውስጥ ዘላቂ ፍሬ ያፈራል። አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦ ﴿وَمَا كَانَ الْمُؤْمِنُونَ لِيَنْفِرُوا كَافَّةً فَلَوْلَا نَفَرَ مِنْ كُلِّ فِرْقَةٍ مِنْهُمْ طَائِفَةٌ لِيَتَفَقَّهُوا فِي الدِّينِ وَلِيُنْذِرُوا قَوْمَهُمْ إِذَا رَجَعُوا إِلَيْهِمْ لَعَلَّهُمْ يَحْذَرُونَ﴾ «ምእመናንም ሁሉም በአንድነት መውጣት አልነበረባቸውም። ከእያንዳንዱም ቡድን ከእነርሱ አንዳንዶች በዲን ውስጥ እውቀትን በጥልቀት እንዲያገኙና ወደ እነርሱ በተመለሱ ጊዜ ሕዝባቸውን እንዲያስጠነቅቁ ለምን አይወጡም? ምናልባትም ይጠነቀቁ ይሆናል።» 📖 ሱረቱ አት-ተውባህ፣ 9፡122 ይህ አንቀጽ በዲን ውስጥ ጥልቅ እውቀት የሚያገኙና ያንን እውቀት ለሕዝባቸው የሚያደርሱ ሰዎች አስፈላጊነትን ያሳያል። ስለዚህ እውቀት ያላቸው ሰዎች ማስተማርን እንደ ዝቅተኛ ሥራ ከቆጠሩት፣ ወይም ከማስተማር ይልቅ በየቀኑ በወቅታዊ ጉዳዮች መጠመድን ከመረጡ፣ የእውቀት ተተኪዎችን ማፍራት ላይ ክፍተት ሊፈጠር ይችላል። 3. ዜና ማስተላለፍ እና የዳዕዋ ሥራ አንድ አይደሉም የወቅቱን ዜና ማስተላለፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይገባል። የማኅበረሰቡን ጉዳይ የሚያሳውቁ፣ የሚያስጠነቅቁ፣ የሚያስተባብሩና ለተቸገሩ የሚደርሱ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ሆኖም እያንዳንዱ የዲን እውቀት ያለው ሰው የዜና አስተላላፊ መሆን አያስፈልገውም። የሕዝብ ጉዳዮችን የሚከታተሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በቁርአን፣ በሐዲስ፣ በዐቂዳ፣ በፊቅህና በሌሎች የዲን ዕውቀቶች ላይ በጥልቀት የሚያስተምሩ ሰዎችም ያስፈልጋሉ። ሁሉም ሰው ዜና ላይ ቢሰበሰብ ማን ያስተምራል? ሁሉም ሰው ስለ ሌሎች ንግግር ቢጠመድ ማን የዲን መጻሕፍትን ያብራራል? ሁሉም ሰው የወቅቱን ጉዳይ ቢከታተል ማን ነው በየመድረሳው ተቀምጦ የሚማርና የሚያስተምር ትውልድ የሚያፈራው? ማኅበረሰቡ የሚፈልገው ዜና አስተላላፊዎችን ብቻ አይደለም፤ የሚያስተምሩ፣ የሚያሳድጉና የሚመሩ ሰዎችንም ይፈልጋል። 4. የሌሎችን ስኬት መኮረጅ ሁልጊዜ ትክክል አይደለም አንድ ወንድም በዜና አስተላላፊነት ብዙ ተከታዮችን አገኘ ማለት፣ እኔም ያንኑ ሥራ ብጀምር የበለጠ እጠቅማለሁ ማለት አይደለም። የሌሎችን ስኬት ከመኮረጃችን በፊት የራሳችንን አቅም፣ የተሰጠንን እውቀትና ማኅበረሰቡ ከእኛ የሚጠብቀውን ጥቅም መመርመር ይገባል። አንዱ ሰው በዜና ማስተላለፍ ይበልጣል፤ ሌላው በማስተማር፤ ሌላው በመጻፍ፤ ሌላው በማስታረቅ፤ ሌላው በማኅበረሰብ አገልግሎት። ሁሉም በአንድ ሥራ ውስጥ መግባት አያስፈልግም። የሚገርመው ግን፣ በዲን ማስተማር የተለየ ችሎታ ያለው ሰው ያንን ችሎታ ትቶ በሌሎች ሥራ ውስጥ ለመታየት ከተጣደፈ፣ ማኅበረሰቡ በተፈጥሮው የሚያገኘውን ጥቅም ሊያጣ ይችላል። አላህ እንዲህ ይላል፦ ﴿وَلَا تَتَمَنَّوْا مَا فَضَّلَ اللَّهُ بِهِ بَعْضَكُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ﴾ «አላህ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን ከሌሎቻችሁ ያበለጠበትን ነገር አትመኙ።» 📖 ሱረቱ አን-ኒሳእ፣ 4፡32 አንዱ በተሰጠው ጸጋ ሌላውን ከመኮረጅ ይልቅ፣ በተሰጠው አቅም ማኅበረሰቡን ማገልገል ይገባዋል። 5. የሰዎችን ጉዳይ ማውራት ከዲን እውቀት ማስተማር ይልቅ የበለጠ ትኩረት እያገኘ ነውን? አንዳንድ ጊዜ በዲን እውቀት የሚያስተምር ትምህርት ከጥቂት ሰዎች በላይ ተከታይ ላያገኝ ይችላል፤ ስለ አንድ ሰው የተነሳ ክርክር ግን በአጭር ጊዜ ብዙ ሰዎችን ሊስብ ይችላል። ይህ ሁኔታ የሰዎችን ትኩረት በማግኘት ላይ የተመሠረተ ውድድር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ከዚያም አንዳንዶች በእውቀት ማስተላለፍ ላይ ከመትጋት ይልቅ የበለጠ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ፍለጋ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እዚህ ላይ እያንዳንዱ የዜና አስተላላፊ ይህንን ዓላማ አለው ብለን መፍረድ አይገባንም። ነገር ግን እኛ ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፦ የምናቀርበው መልእክት ሰዎችን ወደ እውቀት እየጠራ ነው፣ ወይስ ለጊዜው ብቻ እያዝናናቸው ነው? ሰዎች ከእኛ የዲን ጥቅም እያገኙ ነው፣ ወይስ የሌሎችን ጉዳይ ብቻ እየተከታተሉ ነው? እውቀትን ለማስተላለፍ ነው የምንጥረው፣ ወይስ በሰዎች ዘንድ ለመታወቅ? በማኅበራዊ ሚዲያ ያለን ጊዜ ከመድረሳ ትምህርት፣ ከመጽሐፍ ማብራራትና ከተማሪዎች ማሳደግ ጊዜያችንን እየወሰደ ነውን? እነዚህ ጥያቄዎች ሌሎችን ለመክሰስ ሳይሆን ራሳችንን ለመመርመር ነው። 6. የዳዕዋ ሰዎች ሆይ፣ ማስተማርን አትተዉ! በኢትዮጵያ ውስጥ ለዲን የሚጠቅሙ መልእክቶችን በማስተላለፍ፣ ማኅበረሰቡን በማሳወቅና በማስተባበር የሚሠሩ ወንድሞች አሉ። እነዚህን ወንድሞች ማቃለል ወይም ሥራቸውን መንቀፍ የዚህ መልእክት ዓላማ አይደለም። አላህ የሚያበረታታቸውን ሥራ ያበርታቸው።
Open in Telegramየዱንያ ሁኔታ አያታልልህ! ﴿لَا يَغُرَّنَّكَ تَقَلُّبُ الَّذِينَ كَفَرُوا فِي الْبِلَادِ مَتَاعٌ قَلِيلٌ ثُمَّ مَأْوَاهُمْ جَهَنَّمُ وَبِئْسَ الْمِهَادُ﴾ «የእነዚያ የካዱት በየሀገሮች መንፈላሰስ አያታልልህ። ጥቂት ጊዜያዊ ጥቅም ነው፤ ከዚያም መጠጊያቸው ገሀነም ነው፤ ምንኛም መጥፎ መኝታ ነው!» — ሱረቱ አሊ ዒምራን፡ 196–197 የዱንያ ብልጽግና የአላህ ውዴታ መለኪያ፣ ድህነትም የቁጣው ማስረጃ አይደለም። አንዱ በሀብት ይንበሸበሻል፤ ሌላው በችግር ይፈተናል። አንዱ የዱንያን በሮች ሁሉ ክፍት አግኝቶ ይኖራል፤ ሌላው በጠባብ ሁኔታ ውስጥ ትዕግሥቱን ይፈትናል። ይሁንና:- የዛሬው ሰፊ ኑሮ የነገውን ዕጣ አያረጋግጥም፤ የዛሬው መከራም የነገውን ደስታ አያግድም። 🔹 ኢማም ኢብኑ ከሲር (ረሂመሁላህ) በዚህ አንቀጽ ተፍሲር ፦ "አላህ ለነሱ የሰጣቸውን ጊዜያዊ ምቾትና ስኬት አትመልከት። ይህ የነሱ 'መታዕ' (ጊዜያዊ መጠቀሚያ) ሲሆን፣ የአማኞች ስኬት ግን ዘላቂና የማይቋረጥ ነው"። ስለዚህ፣ የሌሎችን የተድላ ኑሮ፣ መንፈላሰስ እና ብልጽግና አይተን እምነታችንን አናናጋ፤ በራሳችን መከራም ተስፋ አንቁረጥ። የዱንያ ብርሃን ቢያበራም ይጠፋል፤ ጨለማዋም ቢረዝም ይነጋል። ዛሬ በእጃችን ያለው ሀብት ነገ ከእኛ ሊለይ ይችላል፤ ዛሬ በትዕግሥት የምንሸከመው መከራ ግን በአላህ ፈቃድ የነገ ደስታችን ሊሆን ይችላል። አስታውስ! ዋናው ጥያቄ በዱንያ ምን ያህል እንዳከማቸን ሳይሆን፣ ወደ አኺራ ምን ይዘን እንደምንሄድ ነው። የዱንያን ጥቅም ከአኺራ ዘላለማዊነት ጋር አታስተካክል፤ ጊዜያዊውን በዘላለማዊው አትለውጥ። اللهم لا تجعل الدنيا أكبر همّنا، ولا مبلغ علمنا، واجعل الآخرة خيرًا لنا من الدنيا وما فيها. አላህ ሆይ! ዱንያን ከጭንቀቶቻችን ሁሉ ትልቁ፣ የዕውቀታችንም መጨረሻ አታድርግብን፤ አኺራንም ከዱንያና ከውስጧ ካለው ሁሉ የተሻለች አድርግልን። ✍أبو سليمان
Open in Telegram﴿وَيُحِبُّونَ أَنْ يُحْمَدُوا بِمَا لَمْ يَفْعَلُوا﴾ «ያልፈጸሙት ሥራ እንደፈጸሙ ተቆጥሮላቸው ሊመሰገኑ ይወዳሉ።» — አሊ ዒምራን፡ 188 ከልብ የሚያሳዝኑ የነፍስ በሽታዎች አንዱ፣ ሳይሠሩ የሠሩ ለመባል፣ ሳይጥሩ የደከሙ ለመመስል፣ ሳይገባቸው የምስጋና አክሊል ለመድፋት መጓጓት ነው። ሰዎች የሚያዩትን ገጽታ ማሳመር ይቻላል፤ ነገር ግን አላህ የሚያውቀውን ውስጥ መደበቅ አይቻልም። ምስጋና በሰዎች አንደበት ቢያብብም፣ በእውነት ሥራ ላይ ካልተመሠረተ በአላህ ዘንድ ክብር አይሆንም። ስለዚህ፣ የሰዎችን ምስጋና ከመፈለግ በፊት ሥራችንን እናስተካክል፤ በውጫዊ ገጽታችን ከመኩራት በፊት ውስጣችንን እንመርምር። የሰዎች ምስጋና ይጠፋል፤ አላህ ዘንድ ያለው እውነት ግን አይደበቅም። ✍ أبو سليمان https://t.me/ibnmuha
Open in Telegram🍃 የተበላሹ መንገዶች ሁሉ መውጫ አላቸው! ﴿وَمَن يَتَّقِ اللَّهَ يَجْعَل لَّهُ مَخْرَجًا وَيَرْزُقْهُ مِنْ حَيْثُ لَا يَحْتَسِبُ﴾ «አላህን የሚፈራ ሰው፣ መውጫ መንገድ ያደርግለታል፤ ከማይጠብቀውም አቅጣጫ ሲሳይ ይሰጠዋል።» 📖 አጥ-ጠላቅ፡ 2–3 ኢብኑል ቀይም رحمه الله እንዲህ ይላሉ፦ «ومن صدق مع الله في جميع أموره صنع الله له فوق ما يصنع لغيره» «በጉዳዮቹ ሁሉ ከአላህ ጋር እውነተኛ የሆነ ሰው፣ አላህ ለእርሱ ከሌሎች የተለየ ውለታ ያደርግለታል።» ወዳጄ ሆይ! አንዳንድ ጊዜ መንገዶች ሁሉ የተዘጉ ይመስላሉ፤ መፍትሔዎች ይጠፋሉ፤ ልብም በጭንቀት ይጠባል። ነገር ግን አላህ የመውጫ መንገድ ለመፍጠር የሰዎችን እቅድ አይጠብቅም። መውጫው በምታየው መንገድ ብቻ አይመጣም፤ አንተ ባላሰብከው አቅጣጫም ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ በጭንቀትህ ውስጥ አላህን አትርሳ፤ በምትሰራው ሥራ ሁሉ ተቅዋን አጥብቅ፤ ከኃጢአት ራቅ፤ ሐላልን ጠብቅ፤ ዱዓህን አታቋርጥ። የአላህ ተስፋ እውነት ነው፤ ጥበቡ ግን ከእውቀታችን በላይ ነው። መንገዱ ቢጠብም የአላህ ምሕረት አትጠብም፤ ምክንያቶች ቢዘጉም የእርሱ ችሮታ አይዘጋም። ✍أبو سليمان https://t.me/ibnmuha
Open in Telegram🍃 أَلَيْسَ اللَّهُ بِكَافٍ عَبْدَهُ؟ «አላህ ለባሪያው በቂ አይደለምን?!» 📖 ሱረቱ አዝ-ዙመር፡ 36 ወዳጄ ሆይ! ልብህ በሐዘን ሲደክም፣ ዓይኖችህ በእንባ ሲሞሉ፣ የታመንክባቸው ሰዎች ሲርቁህና የመውጫ መንገድ ሲጠፋህ፤ ለነፍስህ ይህን የቁርአን ጥያቄ አስታውሳት፦ «አላህ ለባሪያው በቂ አይደለምን?!» ሰዎች የውስጥህን ስቃይ ላይረዱ ይችላሉ፤ አላህ ግን ያልተነገረውን ያውቃል። በሌሊት ብቻህን ያፈሰስከው እንባ፣ በልብህ ውስጥ የተደበቀው ሐዘንና በዝምታ የዋጥከው ስቃይ ከእርሱ አይሰወሩም። የሰዎች በሮች ሲዘጉ የአላህን ምሕረት አትርሳ። መንገዶች ሲጠፉ ዱዓህን አታቋርጥ። ልብህ ሲሰበር ከጌታህ አትራቅ። አስታውስ! አላህ በቂ መሆኑ የምትፈልገውን ሁሉ ወዲያውኑ ይሰጥሃል ማለት አይደለም፤ ነገር ግን በጥበቡ ላይ ተመካ፣ በምሕረቱ ላይ ተስፋ አድርግ፣ በምትችለውም መንገድ ጥረትህን ቀጥል። ሰዎች ሊተዉህ ይችላሉ፤ ምኞቶችህ ሊዘገዩ ይችላሉ፤ መንገዶችህም ሊጠቡ ይችላሉ። አንተ ግን በአላህ ላይ ያለህን ተስፋ አትቁረጥ! أبو سليمان
Open in Telegramአትፍሩ! እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ… እሰማለሁ፤ አያለሁም! አንዳንድ ጊዜ ሕይወት በሁሉም አቅጣጫ ይጠብብሃል። የምትሸሸው የለም፤ የምትመለከተው መውጫ አይታይህም። ልብህ በፍርሃት ይንቀጠቀጣል፤ ነገሮች ሁሉ ከአቅምህ በላይ ይሆናሉ። የሰው እርዳታ ይርቃል፤ የምትታመንበትም መንገድ ይጠፋል። በዚያ ጊዜ ግን ልብህን ወደ የአላህ ቃል መልስ፦ ﴿لَا تَخَافَا إِنَّنِي مَعَكُمَا أَسْمَعُ وَأَرَىٰ﴾ «አትፍሩ! እኔ ከሁለታችሁ ጋር ነኝ፤ እሰማለሁ፤ አያለሁም።» 📖 [ጣሃ፡ 46] እነዚህ ቃላት አላህ ሙሳንና ሃሩንን (ዐለይሂማ ሰላም) ፈርዖንን ለመጋፈጥ በላካቸው ጊዜ ያጽናናባቸው ቃላት ናቸው። ፈርዖን በሥልጣኑ ይመካል፤ በግፉ ይገዛል፤ በምድር ላይ የሚችለው የሌለ ይመስለዋል። ነገር ግን ከሙሳና ሃሩን ጋር የነበረው አላህ ነበር! ወንድሜ ሆይ! ሰዎች ሁሉ ቢተዉህ፣ አላህ የሚያውቀውን ማንም አይረሳውም። በሌሊት ስታለቅስ ማንም ባይሰማህ፣ አላህ ይሰማሃል። በደልህን ለማንም መናገር ባትችል፣ አላህ ያውቃል። ልብህ በሐዘን ተሰብሮ፣ ከንፈርህ በዝምታ ተዘግቶ፣ ዓይንህ በእንባ ተሞልቶ ብትቀመጥም፣ ከአላህ የተሰወረ ምንም የለም። አንተ የወደፊትህን አታውቅም፤ እርሱ ግን ያውቃል። መውጫውን አታይም፤ እርሱ ግን ለነገሮች ሁሉ ቻይ ነው። ሰዎች በርህን ሊዘጉብህ ይችላሉ፤ የአላህ ጥበብና ምሕረት ግን ከዚያ ሁሉ በላይ ናቸው። ስለዚህ አትሸበር፤ ወደ አላህ የሚያቀርብህን ተስፋ አትቁረጥ። ፍርሃትህን ወደ ዱዓ ቀይር፤ እንባህን ወደ ሱጁድ ውሰድ፤ ድካምህን በአላህ ላይ ባለህ እምነት አጽና። አላህ ከሙሳና ሃሩን ጋር እንደሆነ ሲናገር፣ አንተም በእርሱ ላይ እምነት አድርገህ በቀጥታ ስትጓዝ፣ በችግርህ ውስጥ አላህን አስታውስ። እዚህ ላይ የተጠቀሰው የአላህ አብሮነት ለሙሳና ሃሩን የሰጠው ልዩ ድጋፍ ነው፤ አላህ በእውቀቱና በእይታው ከሁሉም ጋር ነው። የሚያስፈራህ ችግር ምንም ያህል ቢበዛ፣ ከአላህ ያለህ ተስፋ ከችግርህ ይበልጥ ታላቅ ይሁን! ﴿وَمَن يَتَوَكَّلْ عَلَى اللَّهِ فَهُوَ حَسْبُهُ﴾ «በአላህ ላይ የሚመካ ሰው፣ አላህ ይበቃዋል።» 📖 [አጥ-ጠላቅ፡ 3] ✍ابو سليمان
Open in Telegram