Account

Posts of Arba Minch University

newest first

#35265Link preview

21ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የእግር ኳስ ውድድር መርሐ ግብር ተካሄደ ስፖርታዊ ኩነቶች ከሚሰጡት የመዝናኛ አገልግሎት ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ለመፍጠር እንዲሁም መከባበርንና አንድነትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚዎች ናቸው። በዚህ ረገድ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ «በብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች ሥልጡን ኢትዮጵያ» በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዘንድሮውን 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የወንዶችና የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር መርሐ ግብር በአባያ ካምፓስ ስታዲየም አካሂዷል። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ምክትል ዲን አቶ ዮርዳኖስ መኩሪያ መርሐ ግብሩ 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው የእውቀት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ልዩነቶች የሚከበሩበት ማዕከል መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዲኑ፤ ተማሪዎች አንድነትን፣ መቻቻልንና አብሮ የመኖር ባህልን አጠናክረው ከማስቀጠል አኳያ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል የስፖርትና መዝናኛ ቡድን መሪ አቶ በዛብህ አማረ በበኩላቸው በ2018 ዓ.ም. በሁሉም ካምፓሶች በተካሄዱ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድሮች የአሸናፊዎች አሸናፊ የሆኑ የትምህርት ክፍሎች በመርሐ ግብሩ መሳተፋቸውን ገልጸዋል። አክለውም ስፖርታዊ ውድድሮች ጤንነትን ከማስጠበቅ ባሻገር ከተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች የመጡ ተማሪዎችን በማስተሳሰር ለልማት የሚያነሳሱ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የፎረንሲክና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል የ4ኛ ዓመት ተማሪ የአብሥራ ደመቀ ባለፉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው በሚያዘጋጃቸው ስፖርታዊ ውድድሮች በመታደሟ የብዝኃ ባህልና ቋንቋ ባለቤት ከሆኑ ሌሎች ተማሪዎች ጋር መልካም ቅርርብ እንድትፈጥር እንዳስቻላትና በትምህርት ቆይታዋም ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች። የ2019 ዓ.ም. አዲስ ገቢ ተማሪ አብዱልጀምበር መሐመድ በበኩሉ «ይህ መርሐ ግብር ከነባር ተማሪዎች ጋር ትውውቅ እንድፈጥር መልካም አጋጣሚ ሆኖኛል» ብሏል። በተጨማሪም የውኃ ምኅንድስና ትምህርት ለማጥናት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በቀዳሚነት ምርጫው አድርጎ መምጣቱንና የትምህርት ክፍሉን በቀዳሚነት ለማግኘት የሚያስችለውን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጊዜውን በጥናት እያሳለፈ መሆኑን አክሏል። ዋናው ግቢ፣ አባያና ኩልፎ ካምፓሶች እንዲሁም ጫሞና ነጭ ሣር ካምፓሶች በሁለት ምድቦች የተሳተፉበት ይህ የወንዶች እግር ኳስ ውድድር አሸናፊዎች የፍጻሜ ጨዋታቸውን ኅዳር 26/2019 ዓ.ም. የሚያካሂዱ መሆኑም ተመላክቷል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጥበብ ምንጭ ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-   ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/ ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/ ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA    የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

Open in Telegram
Views1,110+2%vs avg
Forwards—
Reactions—
Comments—