ይህ ምስጋና ከእግዚአብሔር ተነስቶ ወደ ሰው ይወርዳል። መጀመሪያ እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ ፍጹምና ገዢ መሆኑን ይነግራል፤ ከዚያ ሰማይና ምድርን ፈጥሮ ባሕርን በወሰን እንደገታ፣ ሰንበትንም ለፍጥረት ዕረፍት እንደቀደሰ ያሳያል። በመቀጠል ሰዎችን «ቅረቡ» ብሎ ይጠራል፤ ለሚወዱት የክብር አክሊል ተዘጋጅቷልና። በጸጋና በሃይማኖት የጸኑ ሰማዕታት ያንን አክሊል ወርሰዋል። በመጨረሻም እግዚአብሔር የቅዱሳን መምህር፣ የሰማዕታት አክሊልና የካህናት ሾሚ እንደሆነ በምስጋና ይደመድማል። በማይለወጠው አምላክ እንታመን፤ ማዕበላችንን እንደሚገታ እናስብ፤ በሰንበት ዕረፍት እምነታችንን እንግለጽ፤ በንጹሕ ልብ እንቅረብ፤ በየቀኑ በጽናት እንመስክር፤ ያለንበትም ቦታ ጥሪና ጸጋ እንደሆነ አውቀን በትሕትና እናገልግል። ቅዱስ ያሬድን የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን! ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ትምህርት ክፍል ትምህርታዊ ሥነጽሁፍ ንዑስ ክፍል
Open in TelegramPosts of ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ
፫ኛ መዝሙር ዘዘመነ አስተምህሮ አምላክ፡ ፍጹም፡ በህላዌሁ፡ «አስተምህሮ» የሚለው ቃል «መሀረ» ከሚለው የግእዝ ሥርወ ግሥ የተገኘ ሲሆን፣ ዋና ትርጉሙም አስተማረ ማለት ነው። ማስተማርን፣ መምከርንና በእግዚአብሔር ቃል ማሳሰብን ወይም ማስታወስን ያመለክታል። ይህ ወቅት የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ርኅራኄ፣ ትዕግሥትና የማዳን ሥራ በቤተክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበትና የሚነገርበት በመሆኑ «ዘመነ አስተምህሮ» ተብሎ ይሰየማል። አምላክ፡ ፍጹም፡ በህላዌሁ፡ ዘሃሎ፡ እምቅድመ፡ ይትፈጠር፡ ዓለም፡ ዘበመንግሥቱ፡ ይኴንን ዓለመ፡ «በህልውናው ፍጹም የሆነ አምላክ፤ ዓለም ሳይፈጠር በፊት የነበረ፤ በመንግሥቱም ዓለምን የሚገዛ ነው።» «ህላዌ» የመኖርን ባሕርይ ያመለክታል። የሰው ፍጽምና ከተሰጠ ነገር የሚገኝ ሲሆን፣ የእግዚአብሔር ፍጽምና ግን ከራሱ ባሕርይ የመነጨ፣ ምንም የማይጎድለውና የማይጨመርለት ነው።ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ መኖሩ እግዚአብሔር የታሪክ ውጤት ሳይሆን የፍጥረት ሁሉ መነሻ መሆኑን ያሳያል (መዝሙር 90:2 [ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርና ዓለም ሳይሠሩ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም አንተ አምላክ ነህ])። ይህ ሃሳብ ቤተ ክርስቲያን በየቀኑ በምታነበው ጸሎተ ሃይማኖት ውስጥም ይገኛል፤ በዚያ ወልድ «ከዓለም ሁሉ አስቀድሞ ከአብ የተወለደ» ተብሎ ይመሰከራል፤ ስለዚህ ሥላሴ ከፍጥረት በፊት ፍጹም ነበሩ (ጸሎተ ሃይማኖት [ከዓለም በፊት ከአብ የተወለደ ብለን እናምናለን])። «ይኴንን » ( ኰነነ = ገዛ) እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ እንዳልተወው ያስተምራል። ፍጥረት በራሱ ኃይል ሳይሆን በእርሱ መንግሥት ሥልጣን ይመራል፣ ይጠበቃል (መዝሙር 103:19 [እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማያት አጸና፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች])። ሰማየ፡ ገብረ፡ ለስብሐቲሁ፡ ዓለመ፡ ፈጠረ፡ ወምድረ፡ ሳረረ፡ ወገሠፀ፡ ባሕረ፡ ወገሠፆሙ፡ ለኲሉ፡ ፍጥረት፡ ሰማይን ለክብሩ ሠራ፤ ዓለምን ፈጠረ፤ ምድርንም አጸና፤ ባሕርንም ገሠጸ፤ ፍጥረትንም ሁሉ በሥርዓት አዘዘ። ፍጥረት ያለ ዓላማ የተገኘ አይደለም፤ ዝም ብሎ ሲታይም እንኳ ፈጣሪውን ይመሰክራል (መዝሙር 19:1 [ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጁን ሥራ ያወራል])። ባሕርን መገሠጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ዓለም ውስጥ ልዩ ትርጉም አለው። ባሕር የሁከትና የማይገሠጽ ኃይል ምልክት ነበረ፤ እግዚአብሔር ግን ድንበር አበጅቶለት ይቆጣጠረዋል።እያንዳንዳችን የራሳችን «ባሕር» አለን፤ ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ የማይቆሙ የሚመስሉ ችግሮች። ስለዚህ «ገሠፀ ባሕረ» የእግዚአብሔር ኃይል ከሁከት ሁሉ እንደሚበልጥ ይመሰክራል። «ገሠፆሙ ለኲሉ ፍጥረት» ደግሞ እያንዳንዱ ፍጥረት በእግዚአብሔር ትእዛዝ በየራሱ ሥርዓት የሚኖር መሆኑን ይናገራል። እለ ውስተ፡ ደይን፡ ያእርፉ፡ ባቲ አብ፡ ቀደሳ፡ ለሰንበት፡ በፍርድ (በሥርዓት) ሥር ያሉ ፍጥረት በእርሷ ያርፉ ዘንድ፤ አብ ሰንበትን ቀደሳት። እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ማረፉ ደክሞ አይደለም፤ ሥራው ፍጹም መሆኑን ለማሳየት ነው። ከዚያም ቀኑን ባረከው፣ ቀደሰውም («አብ ቀደሳ ለሰንበት»)። ሰንበት የእግዚአብሔር ዕረፍት ለፍጥረት የተጋራበት ቀን ነው።«ያእርፉ ባቲ» (በእርሷ ያርፉ ዘንድ) የሚለው ሰንበት የዕረፍት ቀን ብቻ ሳትሆን፣ ወደ ዘላለማዊ ዕረፍት የምታመለክት ምልክት መሆኗን ያሳያል)። «ደይን» ከሰንበት ጋር መያያዙ፣ ዕረፍቱ በእግዚአብሔር ሥርዓት ሥር እንደሆነ ያሳያል። ብዙዎቻችን ያለማቋረጥ በመሮጥ ዋጋችን በሥራቸን መጠን እንደሚለካ እናስባለን። ሰንበት ግን «እኔ ሳልሠራ ዓለም አይቆምም፣ ጌታ ይጠብቃል» የሚል የእምነት ልምምድ ነው። ከሥራ እና ከሩጫ አርፎ ለጸሎት፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለተቸገሩት ጊዜ በመስጠት እምነትን በተግባር መግለጽ ነው። ቅረቡ፡ ኀቤሁ፡ለአምላከ፡ ጽድቅ፡ ማህደር፡ ለንጹሃን፡ከመ፡ ትንሥኡ፡ እክሊለ፡ ስብሐት፡ ዘአስተዳለወ፡ ለእለ፡ ያፈቅርዎ፡ የጽድቅ አምላክ፣ የንጹሐን ማደሪያ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ቅረቡ፤ ለሚወዱት ያዘጋጀውን የክብር አክሊል ትቀበሉ ዘንድ። እስካሁን ጽሑፉ ስለ እግዚአብሔር ይናገር ነበር፤ እዚህ ላይ ወደ አድማጩ ዞሮ «ቅረቡ» ብሎ ይጠራል።መቅረብ ርቀትን በመሻገር ሳይሆን ልብን በማጥራት ነው (ያዕቆብ 4:8 [ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፣ ወደ እናንተም ይቀርባል፤ እጃችሁን አንጹ፣ ልባችሁንም አጥሩ])። ጥሪው ተስፋ አለው፤ «ዘአስተዳለወ» (አዘጋጀ) የሚለው አክሊሉ ቀድሞ የተዘጋጀ ስጦታ እንጂ በኋላ የሚፈጠር ሽልማት አለመሆኑን ያሳያል። ደግሞም ለሚወዱት ነው፤ ስለዚህ መነሻው ፍርሃት ሳይሆን ፍቅር ነው (1 ቆሮንቶስ 2:9 [ዓይን ያላየችው፣ ጆሮም ያልሰማው፣ በሰውም ልብ ያልገባው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው])። ብዙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርበው በችግር ጊዜ ብቻ ነው፤ ጥሪው ግን ዘወትር ነው። ንጽሕና ማለት ፍጹም መሆን ሳይሆን ልብን ከቂም ማጽዳት ነው። ደግሞም የምናገለግለው ዋጋ ለማግኘት ብቻ ከሆነ ገና የፍቅር ጉዞ አልጀመርንም፤ ለሚወዱት የተዘጋጀው አክሊል ፍቅርን ያከብራልና። ጸንዑ፡በጸጋ፡ በስን፡ ወበሃይማኖት፡ ወረሱ፡ እክሊለ፡ ስምዕ፡ በእምነቶሙ፡ እለ፡ እም አለም፡አስመርዎ፡ ለእግዚኦሙ፡ በጸጋ፣ በጽናትና በሃይማኖት ጸኑ፤ በእምነታቸውም የምስክርነትን አክሊል ወረሱ እነርሱም ከጥንት ጀምሮ አምላካቸውን ደስ ያሰኙት ናቸው። ጽናት ከሦስት ምንጭ ይመነጫል፤ ከጸጋ (የእግዚአብሔር ስጦታ)፣ ከጽናት (በመልካም ኑሮ የሚታይ እምነት) እና ከሃይማኖት (የእምነት መሠረት)። ጽናት በሰው ጉልበት ብቻ አይገኝም፤ በጸጋ ይደገፋል (ዕብራውያን 13:9 [ልብ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው])። «እክሊለ ስምዕ» የምስክርነት አክሊል ነው፤ «ስምዕ» ምስክርነት ነው፣ ሰማዕት የሚለው ቃልም ከዚሁ ይወጣል። ሰማዕት ማለት እምነቱን በሕይወቱ የመሰከረ ነው (ራእይ 2:10 [እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ])። «እምዓለም አስመርዎ» ሰማዕትነት ከአንድ ዘመን ሰዎች የተገደበ እንዳልሆነ፣ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ጻድቃን ሁሉ እንደሚካተቱ ያሳያል።ሰማዕትነት በደም ብቻ አይደለም። ዛሬ በሥራ ቦታ እውነትን መናገር በፈተና ጊዜ ከእምነት አለመለየት..... የምስክርነት ዓይነቶች ናቸው። ትንሽ ትንሽ በየቀኑ መጽናት ትልቁን ጽናት ያዘጋጃል፤ ሰማዕታትም በአንድ ቀን የተፈጠሩ አይደሉም። መምህረ፡ ቅዱሳን፡ እክሊለ፡ ሰማዕት፡ሠያሜ፡ ካህናት፡ የቅዱሳን መምህር፤ የሰማዕታት አክሊል፤ የካህናት ሾሚ። መደምደሚያው ሦስት ስሞች ነው፤ እያንዳንዱ ለአንድ የሰዎች ክፍል የእግዚአብሔርን ግንኙነት ያሳያል።መምህረ ቅዱሳን፦ ቅዱሳን በራሳቸው ጥበብ ቅዱሳን አይሆኑም፤ እግዚአብሔር ራሱ አስተማሪያቸው ነው። እክሊለ ሰማዕት፦ ሰማዕታት ዋጋቸው ከእግዚአብሔር የተለየ ነገር አይደለም፤ እርሱ ራሱ አክሊላቸው ነው። ሠያሜ ካህናት፦ ክህነት ሰው ለራሱ የሚወስደው ማዕረግ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ጥሪ ነው (ዕብራውያን 5:4 [ማንም ይህን ክብር ለራሱ አይወስድም፤ እንደ አሮን በእግዚአብሔር የተጠራ ነው እንጂ])።እያንዳንዳችን ማንም ብንሆን (ህጻን፣ አዋቂ ፣ አገልጋይ፣ ሠራተኛ) ያለንበት ቦታ በራሳችን ብቃት ብቻ የተገኘ አይደለም፤ ጥሪና ጸጋ ነው። ይህ ትዕቢትን ያስወግዳል፤ በተጠራንበት ቦታ በትሕትና እንድናገለግል ያደርገናል። ክብሩም ለሾመን ለእግዚአብሔር ነው።
Open in Telegramክቡራን፣ በጉጉት የምንጠብቃት ቀን ደረሰች። ⚠️ አንድ አንድ ማሳሰቢያዎች ⚠️ - 5 ኪሎ በር ላይ እስከ 1:30 ድረሱ 2 ሰዓት መነሻችን ነው (Strictly) ከዚያ ወዲህ ሰው አይጠበቅም❗️ - ክርስትያናዊ አለባበሳችን እንደተጠበቀ ይሁን - የጸሎት መጽሐፋችሁን መያዝ እንዳትዘነጉ (ገዳምም አደል ምንሄድ😊🥰) - የጸበል መያዣ እና የእምነት መያዣ ለመያዝም እንደ ማስታወሻ ይሁናችሁ - የጉዞ ትኬታችሁን መያዝ እንዳትረሱ - ከመንገድ ካልያዛችሁን ብላችሁ ላስቸገራቹ ሰዎች 😁 የምንሄደው በጋርመንትና በጀሞና በፉሪ ስለሆነ በእነዚህ ቦታዎች ብቻ ልንይዛችሁ እንችላለን - በእለቱ ትኬት ለምትቆርጡ ሰዎች ትኬት ይዘው የሚጠብቋችሁ አስተባባሪዎች ስላሉ ሃሳብ እንዳይገባችሁ - እግዚአብሔር አምላክ ጉዞአችንን ሰላም እንዲአደርግልን ሁላችንም አንድ ሰላምለኪ እንድንደግም ይሁን። ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in Telegramውድ የ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ልጆች እንዴት ዋላችሁ ሁላችንም ብዙ መንፈሳዊ ዋጋዎችን የምንሸምትበት። ወንድማማቻዊ እና እህትማማቻዊ ፍቅርን የምናገኝበት እና በረከትን ሸምተን የምንውልበት የጉዞ መርሀግብራችን በነገው እለት እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እናደርጋለን። ይሁን እንጅ ይህን ጉዞ ለመሄድ ምናልባት በብር ምክንያት ለመሄድ የተቸገራችሁ እህት ወንድሞቻችን በብር ምክንያት መቅረት ስለሌለባችሁ እናንተ ወይም ደግሞ በአቅም ምክንያት የማይሄዱ የምታውቋቸው ልጆች ካሉ ከታች ባለው ስልክ ደውሉ ። ኤፍራታ @Eph0327 0934344546 እጹብ @Etsuba_19 0944363702 ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in TelegramForwarded from ዕቅበተ እምነት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። በዚህ ሳምንትም የዕቅበተ እምነት መርኃ ግብራችን ይቀጥላል። ትንሳኤ ሙታን እንዴት ይሆናል? መንግስተ ሰማያት እና ገሀንም ምን ይመስላሉ? እና የመሳሰሉት ርእሶች ተነስተው እንወያያለን። ቸር ያቆየን
Open in Telegramሰላም የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እሁድ ለሚኖረን ጉዞ ነገ ቅዳሜ ጠዋት 2 ሰአት ጀምሮ ለጉዞ የሚአስፈልጉንን ነገሮች ስለምናዘጋጅ እንደ ምግብ ማብሰል የመሳሰሉ የአገልግሎት ተግባራት ስላሉ ሁላችንም በቻልነው ልክ መጠን ተባብረን የሚአስፈልገንን አብረን እንድናዘጋጅ ግቢ ጉባኤያችን ታሳስባለች። ቦታ፦ግንፍሌ የሚገኘው የማህበረ ቅዱሳን ህንፃ ሰአት፦ከ 2 ሰአት ጀምሮ ቦታ ከጠፋባችሁ በነዚህ ስልኮች ደዉሉ Medan +251985442997 Dagim [Mobile] +251905057410 5 ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in Telegramበሽማግሌዎች ጉባኤ ቁም፤ ጥበበኛ ማን እንደ ሆነ እወቅ፤ እርሱንም ተከተለው፤ መልካም ንግግርን ሁሉ ለመስማት ትጋ፤ የጥበብም ምሳሌ አይለፍህ።» — መጽሐፈ ሲራክ ፮፥፴፬–፴፭ ከቅዱስ ያሬድ አብነትን የምንቀስምበት፣ከጥሩ ምንጭ ንፁህ ውኃን የምንጠጣበት ፣መንፈሳችንን የምናንጽበት ልዩ ጉባኤ ስለሆነ ሁላችንም ከወንድም እህቶቻችንን ጋር አብረን ቃለ እግዚአብሔርን እንቅሰም። 📆ነገ ህዳር 17 📍ማህበረ ቅዱሳን 4ኛ ፎቅ ⏰11:30 ፭ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in Telegramየንባብ ሳምንት "ንባብ የነፍስ ምግብና ብርሃን ነው" ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ 📖ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ማህበረ ቅዱሳን 6ኛ ፎቅ ቤተ መጽሀፍት ከ3 :00 እስከ 11፡ዐዐ በመሄድ ረጅም ሰዓት በሳምንት ውስጥ በማንበብ ይሸለሙ። መጽሐፍ ለመዋስ: 👉 ሐሙስ ከአንድነት መርሐግብር በኋላ የግቢ ጉባኤያችንን ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት በመቀላቀል የpdf መጻሕፍትን እና መፅሀፍ ዳሰሳ ማግኘት ትችላላችሁ። https://t.me/amstkilo_library ልቡናችን በምን ይለዝባል? ያልከኝ እንደሆነ መጽሐፍ በመመልከት፥ በመማር ይለዝባል ብዬ እመልስልሃለሁ።" {ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ} ያለንን ጊዜ አብቃቅተን መንፈሳዊ መጻሕፍትን በማንበብ በሕይወታችን ለመኖር እንትጋ። ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in Telegram† ጾመ ነቢያት (የገና ጾም) † ከኅዳር 15 ቀን ተጀምሮ እስከ ልደት ለ44 ቀናት የሚጾም ጾም ነው( በዘመነ ዮሐንስ ግን 43 ቀናት ይጾማል፤)፡፡ ከ7ቱ አጽዋማት ማለትም (ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ፍልሠታ፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ድኅነት፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ገሃድ) መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መሆን ሲጠባበቁ የኖሩት ነብያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመሆኑ ጾመ ነብያት (የነቢያት ጾም) እየተባለ ይጠራል። ለአዳም የተነገረውን የድኅነት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም «ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)» ይባላል። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን በስፋት ትምህርት ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመሆኑም «ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)»፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደቱ በመሆኑ ደግሞ «ጾመ ልደት (የልደት ጾም)» በመባል ይታወቃል። ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡ እነርሱም፦ ፩. ጾመ አዳም ፦ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገት ከተባረረ በኋላ; በፈጸመው በደል አዝኖ ፥ ተክዞ፤ አለቀሰ (እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ) ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በደጅህ ድኼ፣ በዕፀ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡›› የሚል ነው፡፡ /ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ/ ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት ‹‹ጾመ አዳም›› ይባላል፡፡ ፪. ጾመ ነቢያት ፦ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች: ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም: ቅዱስ ሙሴ: ቅዱስ ኤልያስ፣ ቅዱስ ዳንኤል ና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: (ዘዳ 9:19, ነገ. 19:8, ዳን. 9:3፣ መዝ. 68:10, 108:24) ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል:: ፫. ጾመ ሐዋርያት ፦ ሐዋርያት ‹‹ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?›› ብለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡ ፬. ጾመ ማርያም ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ‹‹ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?›› ብላ ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና ‹‹ጾመ ማርያም›› ይባላል፡፡ ፭. ጾመ ፊልጶስ ፦ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ እያስተማረ ሳለ በሰማዕትነት ሲሞት፤ አስክሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ፤ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን ሥጋ እንዲገለጽላቸው ከኅዳር ፲፮ ጀምረው ጾመው በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው ስጋ ተመልሶላቸዋል፤ ነገር ግን የመምህራቸው ሥጋ ቢመለስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡ ፮. ጾመ ስብከት ፦ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡ ፯. ጾመ ልደት ፦ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት ስለሆነ ‹‹ጾመ ልደት›› ይባላል፡፡ ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን አሜን!!! ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ትምህርት ክፍል ትምህርታዊ ሥነጽሁፍ ንዑስ ክፍል
Open in Telegramውድ የ፭ኪሎ ግቢ ጉባኤ ልጆች እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም አደረሳችሁ ጾሙን እስከ 9 ሰአት የምትጾሙ ልጆች 9 ሰአት ላይ ካፌ ስለሚከፈት በሰአቱ ተገኝታችሁ መገልገል ትችላላችሁ። ፭ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in Telegram📌 የሳምንቱ መርሐ ግብራት ሰኞ ⌚️[ 11:30 ] የ2ኛ ዓመት ኮርስ 📍 (ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ) የመጻሕፍት ዳሰሳና ጨዋታዎች [ ማታ 1፡30 ] 📍 (ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ) ማክሰኞ ⌚️[ 11:30 ] የ3ኛ ዓመት ኮርስ 📍(ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ) የ4ኛ ዓመት ኮርስ 📍(ማኅበረ ቅዱሳን አዲሱ ሕንጻ 4ኛ ፎቅ) ረቡዕ ⌚️[ 11:30 ] የ5ኛ ዓመት ኮርስ 📍(ማኅበረ ቅዱሳን አዲሱ ሕንጻ 4ኛ ፎቅ) ሐሙስ ⌚️[ 11:20 ] የ 5 ኪሎ ግቢ ጉባኤ የአንድነት መርሃግብር 📍(ማኅበረ ቅዱሳን አዲሱ ሕንጻ 4ኛ ፎቅ) የ1ኛ ዓመት ኮርስ 📍(ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ) ከሰኞ እስከ እሁድ ⌚️(3፡00 - 12:00) የንባብ ሳምንት 📍ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ቤተ መጻሕፍት - 6ኛ ፎቅ) ከሰኞ እስከ አርብ ጠዋት ⌚️(12:00) የአብነት ትምህርት 📍ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ - ቁጥር፣ ንባብ፣ ዜማ፣ እና ቅኔ 📍ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 4ኛ ፎቅ - ቅዳሴ እና ሰዓታት ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን🙏
Open in Telegramየንባብ ሳምንት "ንባብ የነፍስ ምግብና ብርሃን ነው" ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ 📖ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ማህበረ ቅዱሳን 6ኛ ፎቅ ቤተ መጽሀፍት ከ3 :00 እስከ 11፡ዐዐ በመሄድ ረጅም ሰዓት በሳምንት ውስጥ በማንበብ ይሸለሙ። የሰኞ መርሐግብር:- ቦታ: ማኅበረ ቅዱሳን 3ተኛ ፎቅ ሰዓት: 1:30 - 3:00 የሚዳሰሰው መጽሐፍ: ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን መጽሐፍ ለመዋስ: 👉 ሐሙስ ከአንድነት መርሐግብር በኋላ 👉 ሰኞ መፅሀፍ ዳሰሳ መርሀ ግብር ላይ የግቢ ጉባኤያችንን ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት በመቀላቀል የpdf መጻሕፍትን እና መፅሀፍ ዳሰሳ ማግኘት ትችላላችሁ። https://t.me/amstkilo_library ያለንን ጊዜ አብቃቅተን መንፈሳዊ መጻሕፍትን በማንበብ በሕይወታችን ለመኖር እንትጋ። ሙያ እና በጎ-አድራጎት ክፍል ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን! ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ
Open in Telegramእንዴት አመሻችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እግዚአብሔር ቢፈቅድ ነገ እሑድ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ 5 ኪሎ የዶርም ግቢ በር ላይ ተገናኝተን አብረን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን። Google formun የሞላችሁ ልጆች እንደውላለን፤ በመቀጠል ቅዳሴ ተጠናቆ እትው በሰላም ሲባል ማኅበረ ቅዱሳን ማዕከል ህንጻ Program ስለተዘጋጀ አብረን ወደ ማዕከል እንሄዳለን። ሁላችንም በጊዜ እንተኛ። ሰናይ ሌሊት ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!!!
Open in Telegramበስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! እንደምን ሰነበታቹ ቤተሰብ። በዚህ ሳምንትም የዕቅበተ እምነት መርኃ ግብራችን ይቀጥላል። ሁላቹም እንድትገኙ በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን። 📌 ቀን፡ እሑድ 📌 ሰዓት፡ 10፡50 📌 ቦታ፡ ማኅበረ ቅዱሳን 3ኛ ፎቅ 📌 ርዕስ፡ እምነት ብቻ ⚠️ በጊዜ እንድንጨርስ ሰዓቱን ቀደም አድርገዋል!
Open in Telegramቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሾሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል:: ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል ክብርና ርኅሩኅ የለም:: በምልጃውም በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ" ለእግዚአብሔር ይለዋል "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው ለምሕረት የሚፋጠን ደግ መልአክ ነውና:: በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እስራኤልን አርባ ዘመን በበርሃ መርቷል፤ መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: (ዘፍ. ፵፰፥፲፮ ፤ ኢያ. ፭፥፲፫ ፤ መሳ. ፲፫፥፲፯ ፤ ዳን. ፲፥፳፩ ፤ ፲፪፥፩ ፤ መዝ. ፴፫፥፯ ፤ ራዕይ. ፲፪፥፯) ደስ የሚለው ደግሞ ርኅሩኁ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ::" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን፣ በረከትን ያወርዳሉ:: ኢያሱን እንደረዳው በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን እንደ ረዳው ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምራለች:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ ፭ ላይ እንደ ተጻፈው ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ ተገልጦለታል:: እስራኤልን በምድረ በዳ የመራ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ሲያርፍ ታላቅ ሐዘንና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር:: እግዚአብሔር ግን ኢያሱን አስነስቶ አረጋግቷቸዋል:: ቅዱስ ሚካኤል አርባውን ዘመን እስራኤልን ደመና ጋርዶ፣ መና አውርዶ፣ ክንፉን ዘርግቶ፣ ጠላትን መክቶ ከሙሴ ጋር እንደ መራቸው ከኢያሱ ጋርም ይሆን ዘንድ ከሰማይ ወረደ:: በኢያሪኮ አካባቢም የተመዘዘ ሰይፉን ይዞ በግርማ ለኢያሱ ታየው:: ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ "አንተ ከእኛ ወገን ነህን? ወይስ ከጠላቶቻችን?" ሲል ጠየቀው:: ቅዱስ ሚካኤልም መልሶ "እረዳህ ዘንድ እነሆ የሠራዊት አለቃ ሆኜ ተሹሜ መጥቻለሁ::" አለው:: ያን ጊዜ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ በግንባሩ ተደፍቶ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰገደለት:: ቅዱሱ መልአክም አክሎ "ፍታሕ ቶታነ አሣዕኒከ እም እገሪከ እስመ ምድር እንተ ትከይዳ ቅድስት ይዕቲ - የረገጥካት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ::" አለው:: ኢያሱም የተባለውን አደረገ:: ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን "ለመላእክት የጸጋ (የአክብሮ) ስግደት ይገባል፤ በቅዱሳኑ ፊትም ጫማ ተለብሶ አይቆምም::" የምትለው:: ያ መሬት ሊቀ መላእክት ቢቆምበት ተቀድሷል:: ዛሬም ቤቱ በታነጸበት ታቦቱ በተቀረጸበት ቦታ ሁሉ ቅዱሱ መልአክ አለና ጫማን አውልቆ ባጭሩ ታጥቆ መግባት ይገባል:: ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከኢያሱ ጋር ሆኖ አማሌቅን ጨምሮ የእስራኤልን ጠላት አጥፍቷል:: ጥቅመ ኢያሪኮን (ቅጥሩን) አፍርሷል:: ምድረ ርስትን አውርሷል:: በገባኦን ፀሐይን፣ በቆላተ ኤሎምም ጨረቃን ሲያቆም ከእርሱ ጋር ሆኖ ረድቶታል:: ዱራታኦስና ቴዎብስታ ቅዱሳኑ ዱራታኦስ (ዶርታኦስ) እና ቴዎብስታ (ቴዎብስትያ) የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ:: በድርሳነ ሚካኤልና በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎ እንደምናገኘው ሁለቱ ቅዱሳን በተቀደሰ ትዳር ተወስነው፣ ሕጉን ትዕዛዙን ፈጽመው፣ ለነዳያን ራርተው፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የሚኖሩ ነበሩ:: ይልቁኑ ግን የጌታችንን፣ የእመቤታችንን እና የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ያለማስታጐል ያደርጉ ነበር:: ከጊዜ በኋላ ግን ሃብት ንብረታቸው አልቆ ተቸገሩ:: ግን የሚጨንቃቸው መቸገራቸው ሳይሆን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ሊያቆሙ መሆናቸው ነው:: አማራጭ ሲያጡ ተቀምጠው ተመካከሩ:: የቅዱሱ መልአክ ዝክር ከሚቀር ልብሳቸውን (ያውም የክብር ልብሳቸውን) ሊሸጡ ተስማሙ:: በዚህ መሠረት ቅዱስ ዱራታኦስ ወደ ገበያ ሲሔድ ወዳጁ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወረደለት::መንገድ ላይም የጦር መኮንን፣ ሃገር ገዢ መስሎ ተገናኝቶ አጫወተው:: ችግሩን ጠይቆም መፍትሔውን ነገረው:: "እኔ እዋስሃለሁና ለበዓል የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁሉ ገዝተህ አሰናዳ::" አለው:: "እኔ ወደ ቤትህ መጥቼ ስለምስተናገድ አንድ ዓሣ አምጥተህ እቆየኝ:: እኔ ሳልመጣ ግን አትረደው::" አለው:: ቅዱስ ዱራታኦስ የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ ወደ ቤቱ ሲሔድ ድንቅ ነገርን ተመለከተ:: ሚስቱ ቅድስት ቴዎብስታ በቤቱ መካከል ሁና ቤቱ በበረከት ሞልቷል:: ማሩ፣ ቅቤው፣ እሕሉ ሁሉ በየሥፍራው ሞልቷል:: ባልና ሚስቱ ደስ ብሏቸው፣ ነዳያንን ሲያበሉ እንግዳ ሲቀበሉ ዋሉ:: በኋላ ያ መኮንን (ቅዱስ ሚካኤል) በቤታቸው መጥቶ ተስተናገደ:: በእርሱ ትዕዛዝ የዓሣው ራስ (ሆድ) ሲከፈት በውስጡ ሦስት መቶ ዲናር ወርቅ (እንቁ) ተገኘ:: ቅዱሳኑ ይህን ተመልክተው ሲደነግጡ ቅዱስ ሚካኤል ክንፉን ዘርግቶ ራሱን ገለጸላቸው:: ደንግጠው በግንባራቸው ተደፉ:: እርሱ ግን "በተገኘው ሃብት እዳችሁን ክፈሉ:: ከዚህ በኋላ ግን በምድር አትቸገሩም:: በሰማይም ክፍላችሁ ከእኔ ጋር ነው::" ብሎ ባርኳቸው ወደ ሰማይ ዐረገ:: እነርሱም በሐሴትና በበጎ ምግባር ኖረው ዐርፈዋል:: ለርስቱም በቅተዋል:: ከቅዱስ ሚካኤል ረድኤት በረከት ይክፈለን! ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ትምህርት ክፍል ትምህርታዊ ሥነጽሁፍ ንዑስ ክፍል
Open in Telegram