Кабинет

Посты канала ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ Henok Haile

сначала новые

#894Текст

ነቢያት ጌታ “ይወርዳል ይወለዳል” ብለው የተናገሩት ትንቢት እንዲፈጸም ተመኝተው ጾሙ ጸለዩ:: እኛ ስለምን እንጾማለን? ክርስቶስ ተወልዶ ፣ ተጠምቆ ፣ አስተምሮ ፣ ተሰቅሎ ፣ ሞቶ ፣ ተነሥቶ ፣ ዐርጎ ፣ በአባቱ ቀኝ አይደለምን? አሁን ለምን እንጾማለን? ብለን እናስባለን:: ጌታ በእኔና አንተ ልብ ውስጥ እውነት ተወልዶአልን? እውነት የእኛ ልብ እንደ ቤተልሔም ግርግም ለክርስቶስ ማደሪያ ሆኖአል? ማደሪያ አሳጥተን ከእናቱ ጋር አልመለስነውም? የጥምቀቱ ትሕትና በእኛ ልብ መቼ ደረሰ? የስቅለቱ ሕማም መች በእኛ ሕሊና ተጻፈ? የትንሣኤው ተስፋ የዕርገቱ ልዕልና በእኛ ልቡና መቼ ዐረፈ? ስለዚህ ነቢያት “ውረድ ተወለድ” ብለው የጾሙትን ጾም እንጾማለን:: ጌታ ሆይ በእኔ ሕይወትም ውስጥ ውረድ ተወለድ የእኔን ሰውነት ማደሪያህ አድርገው:: ሕዋሳቶቼ ከኃጢአት አርፈው እንደ ቤተልሔም ግርግም ማደሪያህ ይሁኑ:: የቤተልሔም እንስሳት ትንፋሽ ገበሩልህ ፣ የቢታንያ ድንጋዮች ዘማሪ ቢጠፋ ሊዘምሩ ዝግጁ ነበሩ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለክብርህ ተቀደደ ፣ ጨረቃ ላንተ ደም ለበሰች ፣ ፀሐይ ስላንተ ጨለመች ፣ ከዋክብት ለስምህ ረገፉ ፣ ዓለቶች ለፍቅርህ ተሰነጠቁ:: ከቤተልሔም እንስሳት ፣ ከቢታንያ ድንጋዮች ፣ ከቤተ መቅደስ መጋረጃ እኔ እንዴት አንሼ ልገኝ? የቢታንያ ድንጋይ ያወቀህን ያህል ሳላውቅህ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ የተረዳህን ያህል ሳልረዳህ እንዴት ልኑር? ዓለት ላንተ ሲሰነጠቅ የኔ ልብ ለምን ከዓለት ደነደነ? ጨረቃ ደም ስታለቅስ እኔ መከራህ ለምን አልተሰማኝም? ሙታን በሞትህ ሲነሡ እኔ ምነው ከኃጢአት ሞት መነሣት ተሳነኝ? ለዚህ ነው በእኔ ሕይወት ገና አልተወለድክም የምለው:: ስለዚህ ጌታ ሆይ የነቢያትህን ጾም ጸሎት ሰምተህ የወረድህ የተወለድህ ጌታ ሆይ በእኔም ሕይወት ውረድ ተወለድና እኔም ከመላእክት ጋር አብሬ ልዘምር ፣ ከሰብአ ሰገል ጋር ሥጦታህን ልቁጠር ፣ ከእረኞች ጋራ ልደነቅ:: ልደትህ ሳይገባኝ ምጽዓትህ እንዳይደርስብኝ እርዳኝ:: ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ጾመ ነቢያት 2015 ዓ.ም. @diyakonhenokhaile

Открыть в Telegram
Просмотры1 7800%к среднему
Пересылки—
Реакции128
Комментарии—
#893Фото

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሰጠ የኀዘን መግለጫ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአርሲ ዞን ጥቅምት 10 እና 14 ቀን 2019 ዓ/ም በመርቲ ወረዳ አንጋዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጎራ ሲሊንጎ 14 ምእመናን፣ በሸርካ ወረዳ ጠሬታ ጮሌ ቢርቦ 46 ምእመናን ግፍን በተሞላ ጭካኔ ተገድለው ሕይወታቸው ማለፉን፣ የ20 ምእመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን፣ ከ20 በላይ የሆኑ ወገኖቻችን ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል እንደሚገኙ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የቀረበውን ሪፖርት የሰማነው በከፍተኛ ኀዘን ነው፡፡ በአርሲ ሀገረ ስብከትና በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ንፁሐን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ተከታታይነት ባለው ሁኔታ፣ ያለማቋረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱና ከአሁን በፊትም በዞኑ ሥር በሚገኙ ወረዳዎች በርካታ ምእመናን መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን እጅግ አሳዛኝ ግፍና መከራ ጥልቅ በሆነ የኃዘን ስሜት ተመልክቶ እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በየትኛውም እምነት አስተምህሮም ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ የሃይማኖት ነፃነትና በሕይወት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የጣሰ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕገ ሰብእና የወጣ፣ ተከባብሮ የመኖር ሀገራዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጽኑ አውግዞታል፡፡ የንፁሐኑ ግድያ እንዲቆም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በይፋ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና በነጻነት የማምለክ መብትን እንዲያስከብሩልን፣ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙትን ወንጀለኞችም ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ በኋላ እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ በደረሰው የልጆቻችን ሕልፈተ ሕይወት የተሰማንን ከፍተኛ ኃዘን በድጋሚ እየገለጽን፣ ምእመናን ልጆቻችን በያሉበት ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ፣ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ እንደመንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉና አደጋዎችን ማስቀረት የሚያስችል ሥራ እንዲሠሩ እያሳሰብን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን በመመኘት በግፍ ሕይወታቸውን ላጡት ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላክ ዕረፍተ ነፍስንና ክብረ ሰማዕታትን እንዲያድልልን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጸልያለች፡፡ በመጨረሻም በዛሬው ዕለት ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አባላት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎተ ፍትሐት እንዲፈጸም፣ ነገ ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም. ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ በመላው ዓለም በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አድባራት በሙሉ ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚመለከተው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ቀጠሮ ተይዞለት ውይይት እንዲያደርግና በቀጣይም ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታት ተገቢው ጥረት እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ ምንጭ :- EOTC TV

Открыть в Telegram
Просмотры8 490+377%к среднему
Пересылки—
Реакции223
Комментарии—
#892Превью ссылки

+ ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? + ዮሴፍ በግፍ የሸጡት ወንድሞቹን ለሁለተኛ ጊዜ ሲያገኛቸው እንዲህ ሲል ጠየቃቸው ‘የነገራችሁኝ ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? ገና በሕይወት አለን?’ እነርሱ መለሱ ፦ አባታችን ደህና ነው ገና በሕይወት አለ አሉት፡፡ (ዘፍ 43:27) ዮሴፍ የጠየቀው የአረጋዊውን አባቱን የያዕቆብን ደህንነት ነበር፡፡ እርሱ ወንድማቸው መሆኑን ገና ስላላወቁ ‘አባቴ ደህና ነው?’ በማለት ፈንታ ‘ሽማግሌው አባታችሁ’ አለው፡፡ እርግጥም ያዕቆብ መቶ ሠላሳ ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሴፍ እንደፈራው አልሞተም፡፡ ገና በሕይወት ነበረ፡፡ ይህንን ዮሴፍ ለወንድሞቹ የጠየቀውን ጥያቄ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ጻድቁን አቡነ አረጋዊን ለመጠየቅ በሔደ ጊዜ ዳግም ተናግሮታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ወደ ደብረ ሃሌሉያ ዳሞ ተራራ በደረሰ ጊዜ ከተራራው ግርጌ ዮሴፍና ማትያስ የተባሉ ሁለት የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፡፡ ‘ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ’ [ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነውን] ብሎም ጠየቃቸው፡፡ ይህ ንግግሩ መልስ አግኝቶ ሳያበቃ ምስጋና ሆኖ በአቡነ አረጋዊ ማሕሌት ይዜማል፡፡ ሽማግሌው አባታችሁ [አረጋዊ አቡክሙ] የተባለለት ጻድቁ አቡነ ዘሚካኤል አረጋዊ ተብሎ ለመጠራት እንደ ያዕቆብ 130 ዓመታት መቆየት አላስፈለገውም፡፡ ገና በዐሥራ አራት ዓመቱ መንኖ ለብዙዎች መመነን ምክንያት የሆነ በዕድሜው ሳይሆን በቅድስናው አረጋዊ ለመባል የደረሰ ጻድቅ ነበር፡፡ ዛሬም ላይ ሆነን የዮሴፍንና የቅዱስ ያሬድን ጥያቄ ደግመን እንመልስ፡፡ ‘’ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? ገና በሕይወት አለን?’’ ለሚለን ሁሉ መልሳችን ‘አረጋዊው አባታችን [አቡነ አረጋዊ] ደህና ነው፡፡ አሁንም ድረስ በሕይወት አለ ፤ እግዚአብሔር ሰወረው እንጂ አልሞተም፡፡ የሚል ነው፡፡ ጻድቁ አባታችን አረጋዊ ሆይ ዮሴፍ ስለ አባቱ ደህንነት እንደጠየቀ እኛ ስለ አንተ ደህንነት አንጠይቅም፡፡ እግዚአብሔር ያከበረህ ሆይ ባይሆን እኛ ልጆችህ ግን ደህና አይደለንም፡፡ ነፍሳችን ዛሬ በፊትህ የከበረች ትሁንና ልጆችህን በምልጃህ አስበን፡፡ ዮሴፍ ሽማግሌ አባቱን በፈርኦን ፊት እንዳቀረበ እኛም አረጋዊ አባታችንን በእግዚአብሔር ፊት ትማለድልን ዘንድ በጸሎታችን እናቀርብሃለን፡፡ ከዳሞ ተራራ ላይ ሆነህ ከችግር መውጫ ቸግሮአት ሰማይ ሰማዩን ለምታይ ሀገራችን የምልጃህን ገመድ ወርውርላት፡፡ ሊተናኮሏት የተጠመጠሙባትን ዘንዶዎችም ወደ መልካም ዘመን መወጣጫ መሰላሎችዋ አድርግላት፡፡ ካለችበት ውድቀት ወደ ከፍታ መወጣጫ ወደ መልካም መሸጋገሪያ ገመድ ትፈልጋለችና የጸሎት ገመድህን ላክላት:: ያን ጊዜ እንዲህ ትላለች ፦ ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ ርስቴም ተዋበችልኝ’ መዝ 16፡6 ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ጥቅምት 14 2013 ዓ.ም. @diyakonhenokhaile

Открыть в Telegram
Просмотры9 750+448%к среднему
Пересылки—
Реакции252
Комментарии—
#891Текст

የትምህርት ዕድል ያመለጠህ መስሎህ ነው? ገና ሺህ የትምህርት ዕድሎች አሉህ:: ዕድሜህ ያመለጠህ መስሎህ ነው? ነገ የሚጠብቁህ ብሩሕ ዘመናት እኮ ቁጭ ብለው አሉ? የሚረዳኝ ሰው የሚያስብልኝ ሰው አጥቼያለሁ? ብለህ ከሆነም ካልሰሙህ ጥቂቶች በላይ ልንሰማህ የምንሻ “ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ” መከራ ጸናብኝ ኑሮ ጨለመብኝ የሀገሪቱ ሁኔታ ተስፋ አሳጣኝ ብለህ ይሆን? እኛስ አብረንህ አይደልንም? አብረን ከገባንበት ችግር አብረን ብንወጣ አይሻልም? ከአንተ በባሰ ሁኔታ የታሰርንና የተገረፍን ጳውሎሶችና ሲላሶች “ሁላችን በዚህ አለንና በራስህ ክፉ አታድርግ” ስንልህ ስማን:: ይልቅ አንተም እንደ ወኅኒው ጠባቂ “እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብለህ?”ነፍስህን የምታድንበትን መንገድ ወደ መቅደሱ ቀርበህ ጠይቅ:: ወዳጄ ይህንን ጽሑፍ ያነበብኸውም በሕይወት ስላለህ ነው:: የአንተን ዓይን የሚጠብቁ ብዙ ጽሑፎች ፣ የአንተን ጆሮ የሚፈልጉ ብዙ ድምፆች ፣ የአንተን መሐረብ የሚፈልጉ ብዙ ዕንባዎች ፣ የአንተን ሳቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀልዶች ... ገና ብዙ ብዙ አሉ:: ስለዚህ ሰይጣንን አሳፍረው:: እንዲህ በለው :- “ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ” ሚክ. 7:8 ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ጥቅምት 2016 ዓ.ም. ሜልበርን አውስትራሊያ #share @diyakonhenokhaile

Открыть в Telegram
Просмотры27 200×15к среднему
Пересылки—
Реакции668
Комментарии—
#890Текст

+ በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ + ይድረስ ለተከፋኸው ወንድሜ መኖር ለደከመህ ፣ ሕይወት ለታከተህ ፣ የሚሰማህ ላጣኸው ፣ የሚረዳህ ሰው ላላገኘኸው መከረኛው ወዳጄ! ከሞት ውጪ ሌላ መፍትሔ አልታይ ካለህ የአንተ ቢጤ መከረኞቹ ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት ውስጥ ሆነው እንዲህ ይሉሃል:: “በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ” ሐዋ. 16:28 አውቃለሁ ዙሪያው ገደል ሆኖብሃል:: ምነው ባልተፈጠርሁ እስክትል ድረስ ተጨንቀሃል:: ግን ይህ ስሜት በአንተ አልተጀመረም:: ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ኑሮ ያልመረረው ማን አለ? መሞት ያልተመኘስ ማን አለ? ሞት ያማረህ አንተን ብቻ መሰለህ? “ ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ” ያለውን ጻድቅ ኢዮብ አልሰማህም? (ኢዮ. 10:18) “ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ” ብሎ እንዲሞት የለመነውን ኤልያስን አላየኸውም? 1ነገሥ. 19:4 ዮናስንስ “አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ፡ አለው” ሲል አልሰማኸውም? (ዮናስ 4:3) ወንድሜ እመነኝ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መኖር ያላስጠላው ሰው በታሪክ ፈልገህ አታገኝም:: ሞት ሞት የሸተተው ልቡ የተሰበረ ብዙ ነው:: አንተ ላይ ብቻ የደረሰ ልዩ ፈተና የለም:: “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” ይላል መጽሐፍ:: 1ኛ ቆሮ. 10:13 ምናልባት የልብህን መሰበር የኀዘንህን ጥልቀት አይቶ ምቹ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ራስህን እንድትጎዳ ሰይጣን ሊገፋፋህ ይችላል:: እንዴት እንዲህ ዓይነት ሃሳብ በልቤ ሊመጣ ቻለ ብለህ አትረበሽ:: ሰይጣን ይህንን ክፉ ሃሳብ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስም አቅርቦለታል:: “የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር” ብሎ ክርስቶስን እንኳን [ማንነቱን ሳያውቅ] ራሱን እንዲወረውር ሊገፋፋው የሞከረ ደፋር ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ግን ራሱን አይጎዳም:: “ጌታ አምላክህን አትፈታተነው” “ሒድ አንተ ሰይጣን” ብለህ ሰይጣንን ገሠፀው:: ሰይጣን ክርስቶስን “ከሕንፃ ጫፍ በመወርወር የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አሳይ” ሲለው ክርስቶስ ሰይጣንን ሒድልኝ ብሎ በመገሠጹ በክብር ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ:: ወንድሜ ሆይ አንተም ሰይጣንን አትስማው ሃሳቡ ራስህን ጎድተህ ከፈጣሪህ እንድትጣላ ሊያደርግህ ነው:: ሰይጣንን ከገሠጽከው በእግዚአብሔር ቀኝ ከበጎቹ ጋር ትቆማለህ:: አሁን ያለህበት ችግር ያልፋል:: የሚሰማህ ክፉ ስሜት መቼም የማይለወጥ አይምሰልህ:: ኀዘኑም ፣ ብቸኝነቱም ፣ ተስፋ ቢስነቱም ያልፋል:: ጨለማው ይነጋል:: የተዘጋው በር ይከፈታል:: ችግሩ ሲፈታ አንተ ከሌለህ ግን ትርጉም የለውም:: ስለዚህ ለሚፈታ ችግር የማይቀለበስ ውሳኔ አትወስን:: ራስን ማጥፋት ከጊዜያዊ ችግር ለመሸሽ ሲሉ ዘላቂ ችግር ውስጥ መግባት ነው:: ጊዜያዊ ሕመምን ለማስታገስ የዘላለም ሕመምን ለምን ትመርጣለህ? “የሞተ ተገላገለ” ሲሉ ሰምተህ እንዳትታለል ሞት ዕረፍት የሚሆነው ራሱ እግዚአብሔር ሲጠራህ ብቻ ነው:: “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ያለው ጌታ ሳይጠራህ ራስን ማጥፋት የዘላለም ስቃይ ያመጣል:: ወዳጄ “በራስህ አንዳች ክፉ አታድርግ” የሕይወትህን ዋጋ ታውቅ ይሆን? አንተ እኮ የእግዚአብሔር ልጅ ለአንተ ሲል የሞተልህ ነህ:: ሊፈውስህ የቆሰለ ፣ ሊያከብርህ የተዋረደ ፣ ሊያረካህ የተጠማ ፣ ሊያለብስህ የተራቆተ ለአንተ እኮ ነው:: ክርስቶስ ስለ አንተ ሞቶአል:: አንተን ግን የጠየቀህ እንድትሞትለት ሳይሆን እንድትኖርለት ነው:: ለሞተልህ አምላክ እንዴት መኖር ያቅትሃል? ወዳጄ ሆይ ሰውነትህ በአምላክ ደም የተገዛ ክቡር ሰውነት ነው:: አካልህ “አንተ” እንጂ “ያንተ” አይደለም:: “በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” ይላል ስለዚህ በከበረ የእግዚአብሔር ልጅ ደም የተገዛ ሰውነትህን ለሰይጣን በርካሽ አትሽጠው:: አትግደል የሚለው ሕግ ራስህንም ይጨምራል:: ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነትህን ለማፍረስ አታስብ:: “ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ” 1ኛ ቆሮ. 3:17 ሰዎች አስቀይመውህ ይሆን? “አሳያቸዋለሁ ፤ ስሞት የእኔን ነገር ይገባቸዋል” ብለህ በሰዎች ተቀይመህ ራስህን አትጉዳ:: እመነኝ ብትሞት ሰዎች ከሳምንት በላይ አያስታውሱህም:: ለሕይወትህ ዋጋ ያልሠጡ ሰዎች ለሞትህ ዋጋ አይሠጡም:: ፈጥነውም ይረሱሃል:: ለሚረሱህ ሰዎች ብለህ የማይረሳህን አምላክ አታሳዝን:: ሰው ስለ አንተ ግድ የለውም እግዚአብሔር ግን የራስህን ጸጉር ሳይቀር በቁጥር ያውቀዋል :: እንኳንስ ራስህን ልትጎዳ አንዲት ጸጉር እንኳን ከአንተ እንድትወድቅ አይፈልግም:: እግዚአብሔርን በኃጢአት ብታሳዝነው እንኳን ኖረህ ንስሓ እንድትገባ እንጂ እንድትሞት አይፈልግም:: አባትህ ነውና ከእርሱ ጋር ባትሆንም እንድትኖር ይፈልጋል:: በምሳሌ ልንገርህ :- ሁለት ሴቶች አንድን ሕፃን “የኔ ልጄ ነው” ብለው እየተከራከሩ ጠቢቡ ሰሎሞን ፊት ቀረቡ:: ጠቢቡ ሰሎሞን ሰይፍ አመጣና “ልጁን ቆርጬ ለሁለት ላካፍላችሁ” አላቸው:: አንደኛዋ ሴት “እሺ እንካፈል” ስትል እውነተኛዋ እናት ግን “ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው” አለች:: እናት መሆንዋም በዚህ ታወቀ:: ወዳጄ ያንተም ኑሮህ ከእግዚአብሔር ጋር ላይሆን ይችላል:: ዓለም የራስዋ አድርጋህም ይሆናል:: በሱስ ውስጥ ትዘፍቀህ ፣ እንደ ሶምሶን በደሊላ እቅፍ ፣ እንደ ዴማስ በተሰሎንቄ ውበት ተማርከህ ይሆናል:: እግዚአብሔር ግን አባትህ ነውና ሞትህን አይፈልግም:: “ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው” እንዳለችው እናት ፈጣሪህ ከነኃጢአትህም ቢሆን እንድትሞት አይፈልግም:: ከእርሱ ጋር ባትኖርም መኖርህን ይፈልጋል:: “የሟቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ” ሕዝ. 18:32 የይሁዳ ኃጢአቱ ጌታውን መሸጡ አልነበረም:: ራሱን መግደሉ ነው:: እግዚአብሔር የሚያዝነው ከበደልህ በላይ በእርሱ ተስፋ ቆርጠህ ራስህን ስትጎዳ ነው:: ወዳጄ የአንተን መኖር የሚፈልጉ ብዙ ናቸው:: ፈጣሪ ወደዚህች ዓለም ያለ ምክንያት አላመጣህም:: በአንተ አለመኖርም የሚጎድል ነገር አለ:: አንተን የሚመስል ሌላ ሰው አልፈጠረምና ለዚህ ዓለም አንተን የሚተካ የለም:: በክብር ወደዚህ ዓለም ያመጣህ አምላክ በክብር ወደራሱ እስኪወስድህ ድረስ “በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ” “የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፡ ብሎ ጮኸ” ሐዋ. 16:27-28 ይህ ሰው እስረኛ ያመለጠ መስሎት ራሱን ሊያጠፋ ሲል ጳውሎስ “ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ” አለው:: ወዳጄ አንተስ ተስፋ የቆረጥኸው ምን ያመለጠ መስሎህ ነው? #share

Открыть в Telegram
Просмотры23 800×13к среднему
Пересылки—
Реакции294
Комментарии—
#889Фото
Просмотры25 200×14к среднему
Пересылки—
Реакции403
Комментарии—
#885Фото
Просмотры35 400×20к среднему
Пересылки—
Реакции341
Комментарии—