ከኋላ መጥታ አርሴማ፥ አልፋ ኢየሱስን ረምርማ፥ እስድስት ላይ ጕብ አለች፤ የኢየሱስን ቀን ነጠቀች። ዛሬ ቢጠየቁ፣ ኦርቶዶክሶች ኹሉ፥ በስድስት አርሴማ፣ ይላሉ በሙሉ። በቅርብ ለገባችው፣ ከግብጽ በዘመድ፥ ለእማሆይ ኤራኒ፣ በዐዲሱ ትውልድ፥ ተመድቧል አሉ፤ ጥቅምት ኻያ አንድ። የማርያም ዕለት፣ መኾኑ በዓሏ፥ ጠብ እንዳያመጣ፣ የኋላ የኋላ። ልክ እንደ አርሴማ፣ ርሷም በለስ ቀንቷት፥ ማርያምን ከቀኗ፣ ካፈናቀለቻት፥ "ዐይናችን ነሽ ማርያም፣ አንቺን አይንኩብን" ብለው ያዜሙትን፣ እናያቸዋለን። ይብላኝ ለኢየሱስ፣ ቀኑን ለተቀማው በአርሴማ ተጋርዶ፣ ከሰው ልብ ለወጣው። ጣልቃ ሳናስገባ፣ በሠላሳው ቀን፥ የምንዘምርለት፣ በአንድ ልብ ኾነን፥ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ አዳኝ ጌታችን። ደግሞ እንዳንመስላችኹ፣ "ኦንሊ ጂሰስ" (ከሰባልዮስ)፥ እኛ የምናመልከው፣ በሥጋም በነፍስ፥ አሐዱ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ።
Открыть в TelegramПосты канала Agizachew Tefera
ተኣምረ ማርያም፥ ማርያም የምትሰበክበት "የማርያም ወንጌል" ነው ስንል፥ ትክክል ነን። የተኣምረ ማርያም ተረኮች ተጨምቀው በግጥም የቀረቡበት "ማሕሌተ ጽጌ" የተባለው፣ ከመስከረም 26 - ኅዳር 6 ማሕሌት የሚቅቆምበትና ማርያም የምትወደስበት ባለ ፭ እና/ወይም ባለ፮ ቤት ስንኝ የሚመሰክረውም ይህንኑ ነው። በእነዚህ ስንኞች ወንጌልና ተኣምረ ማርያም ተነጻጽረዋል። ስለ እግዚአብሔር ሕግ የተነገረውና "እውነት እላችኋለኹ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ኹሉ እስኪፈጸም ድረስ።" (ማቴ. 5፥18) የሚለው፥ ለማርያምና ለተኣምረ ማርያም ተሰጥቶ፥ "ከቃልሽ አንድ ነገር ከሚወድቅ፥ የሰማይና የምድር ማለፍ ይቀልላል።" ተብሏል። ስለዚህ በአክብሮት ስም ከሚደረግ አምልኮተ ማርያም ልንወጣ ይገባል። ተኣምርኪ መጽሐፈ ጽጌ በኀቤየ ክቡር፤ ከመ ወንጌሉ ቅዱስ ለሕፃንኪ ፍቁር። ጽላተ ኦሪት ማርያም ፀዋሪተ ትእዛዝ ዐሥ፤ እም ይደቅ እም ቃልኪ አሐዱ ነገር፥ ይቀልል ኅልፈቶሙ ለሰማይ ወምድር። እንደ ተወዳጁ ሕፃንሽ ቅዱስ ወንጌል፥ የአበባ መጽሐፍ ተኣምርሽ በእኔ ዘንድ ክቡር ነው፤ ዐሥሩን ትእዛዝ የምትሸከሚ የኦሪት ጽላት ማርያም፥ ከቃልሽ አንድ ነገር ከሚወድቅ፥ የሰማይና የምድር ማለፍ ይቀልላል።
Открыть в Telegramበቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከታዩት ችግሮች መካከል አንዱ በምእመናን መካከል የነበረው መከፋፈል ነው። መከፋፈሉ የመጣውም፥ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፤ እኔስ የክርስቶስ ነኝ” በሚል ክርክር እንደ ኾነ መጽሐፉ ይነግረናል (1ቆሮ. 1፥11-12)። በዚህ ጕዳይ ክርክር ገጥሞ መለያየት ሥጋዊነት መኾኑን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያስረዳል፦ “…ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችኹ ሥጋውያን መኾናችኹ አይደላችኹምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? አንዱ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ኹለተኛውም፦ እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መኾናችኹ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችኹ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልኹ፤ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢኾን ወይም የሚያጠጣ ቢኾን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። የእግዚአብሔር ዕርሻ ናችኹ፤ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችኹ፤ ከርሱ ጋራ ዐብረን የምንሠራ ነንና።” (1ቆሮ. 3፥4-9)። ዛሬም ከዚህ ባለመማር ክርስቲያን ነን በሚሉ መካከል፥ በሕይወተ ሥጋ ባሉ መሪዎቻቸው፣ አስተማሪዎቻቸው፣ መጋቢዎቻቸው፣ ዘማሪዎቻቸው፣ ወዘተ. ጀርባ ተሰልፈው እኔ የእገሌ ነኝ፤ እኔ የእገሊት ነኝ የሚሉ አይጠፉም፤ አሉ። እነርሱ እንደ ሰው ልማድ የሚመላለሱ ሥጋውያን ናቸው። ካንቀላፉ ቅዱሳን ጀርባም ተሰልፈው፥ “እኔ የእገሌ ነኝ፤ እኔ የእገሊት ነኝ” ከማለት ዐልፈው፥ “እገሊት የእኛ ናት፤ እገሌም የእኛ ነው” የሚሉም ሞልተዋል። በዚህ ረገድ፥ የጌታችንን እናት ቅድስት ማርያምን “የእኛ ናት” ብለው ርሷን የእነርሱ ብቻ አድርገው የሚመለከቱና የሌላው አማኝ ወገን እንዳልኾነች የሚቈጥሩ እጅግ ብዙ ናቸው። እንዲህ የሚያስቡ ሐዋርያው እንዳለው፥ እነርሱ እንደ ሰው ልማድ የሚመላለሱ ሥጋውያን ናቸው። የጌታችንን እናት ጨምሮ በክርስቶስ ያመኑ ኹሉ በክርስቶስ አንድ አካል ናቸው። "እናንተም የክርስቶስ አካል ናችኹ እያንዳንዳችኹም ብልቶች ናችኹ።" (1ቆሮ. 12፥27)። ቅድስት ማርያም፥ “ዕንኾኝ የጌታ ባሪያ” (ሉቃ. 1፥38) በማለት፥ የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት በመኾን ያገለገለች ብፅዕት እናት ናት። የኹላችንን አዳኝ በሥጋ በመውለዷ፥ በርሱ የምናምን የኹላችንም ናት። የኹላችንም ስለ ኾነች ግን፥ እግዚአብሔር በርሷ ያደረገውን ታላቅ ሥራ፥ ወልድ እኛን ለማዳን ከርሷ ሰው ኾኖ መወለዱን እንናገራለን። ከዚህ ዐልፈን ግን ለርሷ ወይም በስሟ የምናደርገው አንዳች ነገር ግን የለም፤ ምክንያቱም ማርያም የጌታችን እናት በመኾኗ የእኛ ብትኾንም፥ እኛ ግን የርሷ ሳንኾን የክርስቶስ ነን። ቃሉም ይህን ያረጋግጣል፦ “ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢኾን፥ አጵሎስም ቢኾን፥ ኬፋም ቢኾን፥ ዓለምም ቢኾን፥ ሕይወትም ቢኾን፥ ሞትም ቢኾን፥ ያለውም ቢኾን፥ የሚመጣውም ቢኾን፥ ኹሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችኹ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።” (ቍ. 21-23)። ይህ ቃል በሥጋዊነት የሚያስቡትን አያፈናፍንም፤ እግዚአብሔር ኹሉን የሰጠን፥ የኹሉ እንድንኾን ሳይኾን፥ የክርስቶስ ስለ ኾነን ነው። ስለዚህ በዋጋ ተገዝታችኋልና የሌላው መኾን ቀርቶ የራሳችኹም አይደላችኹም (1ቆሮ. 6፥20)፤ እንዲሁም፥ " በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትኹኑ።" (1ቆሮ. 7፥23) ይላቸዋል። ቃሉ ሕያው ነው፤ ዛሬም ለእኛ ይሠራል። በሥጋዊነት ተይዘን ራሳችንን፥ ላልገዛን አካል ባሮች አድርገን ካቀረብን በክቡር ደሙ የዋጀንን ጌታ እናሳዝናለን። "የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።" (1ቆሮ. 3፥8) እንደ ተባለ፥ የጌታችንን እናት ቅድስት ማርያምን ጨምሮ፥ እግዚአብሔርን ያገለገሉ ኹሉ በጎ ብድራታቸውን ይቀበላሉ። ስለዚህ የራሳችንም ኾነ የሌሎች፥ የማርያምም ጭምር አይደለንም፤ እኛ በውድ ልጁ የዋጀን የእግዚአብሔር ብቻ ነን። ክብር ለርሱ ብቻ ይኹን።
Открыть в Telegramቅዱሳት መጻሕፍት በሚመሰክሩት ምስክርነት፣ በመንፈስ ቅዱስም አብርሆት የተሰቀለውን ያወቀ ሰው የተሰቀለበትን አይሻም። ለተሰቀለበት ይህን ያኽል ቦታ የሚሰጥ ደግሞ የተሰቀለውን እንዳላወቀና ለተሰቀለው ምንም ቦታ እንደሌለው ግልጽ ነው። የተሰቀለበት ወይም ትእምርቱ (ምልክቱ) የተሰቀለውን ካላመለከትና ራሱን ብቻ ካሳየ፥ ምልክትነቱ ቀርቷልና ጣ*ዖ*ት ከመባል አያመልጥም። ንሕነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ አኮ ዘተሰቅለ ቦቱ።
Открыть в Telegramኤችአይቪ ኤድስ 🎗️ የኅብረተ ሰባችን ውስብስብ ችግርና ትልቅ አጀንዳ በነበረባቸው ዓመታት፥ ቫይረሱን ለመከላከልና ከቫይረሱ ጋራ የሚኖሩትን ለመከባከብ፥ ብሎም በሽታውን ለመቈጣጠር፥ የሚመጣ የርዳታ ገንዘብ ነበር። በዚህም ላይ ተመሥርተው፥ የሚንቀሳቀሱ ነበሩ። የሚመጣው የርዳታ ገንዘብ በአብዛኛው የሚውለው በዐውደ ጥናቶችና በስብሰባዎች፥ በየድርጅቱም ለተቀጠሩ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ስለ ነበረና ከቫይረሱ ጋራ የሚኖሩ ሰዎች በስማቸው ከሚመጣው የርዳታ ገንዘብ ብዙም ተጠቃሚዎች ስላልነበሩ፥ ከተጠቃሚነት አንጻር፥ "ከቫይረሱ ጋራ የሚኖሩ" እና "በቫይረሱ የሚኖሩ" የሚል ሐሳብ ይሸራሸር ነበር። እንደ እነዚህ እንደ ኹለቱም ያሉ ሰዎች በኹሉም መስክ አሉ። ለተሰማሩበት ሙያ፣ ሥራ፣ አገልግሎት ራሳቸውን ሰጥተው ከልባቸው የሚኖሩ፥ ከዚህ በተቃራኒው ሙያቸውን፣ ሥራቸውን፣ አገልግሎታቸውን መኖሪያቸው ብቻ የሚያደርጉ ምንደኞች። በወንጌል አገልግሎትም እንኳ፥ የራሳችንን ረብ ፈልገንና ወንጌልን ማትረፊያ አድርገን የምናገለግል ወይም በወንጌል የምንኖር እንዳለን ኹሉ፥ በተቻለና በገባን መጠን ራሳችንን ሰጥተን ለወንጌል የምንኖርም አለን። "ኹሉ #የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ነገር ግን (ጢሞቴዎስ) ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋራ ሆኖ #ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችኹ።" እንዳለ ሐዋርያው (ፊል. 2፥21-22)። ከተሐድሶ አገልግሎት ጋራ በተያያዘም፥ "በተሐድሶ የሚኖሩ" እና "ለተሐድሶ የሚኖሩ" ተብለን ከኹለት ተከፍለን መታየት ያለብን ሰዎችና ተቋማት አለን። በተሐድሶ ከሚኖሩ መካከል አንዱ "ማኅበረ ቅዱሳን" እና ተከታዮቹ ናቸው። ማኅበሩ ከአነሣሡ ጀምሮ እስካኹን ባለው ጕዞ እዚህ የደረሰው፥ በአንድ በኩልና በዋናነት ስለ ተሐድሶ እያወራና እየጻፈ፥ "ተሐድሶ" ያላቸውንም ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን እያባረረና እያስባረረ ነው። እንዲህ ማድረግ ትልቅ "አገልግሎቱ" ነው። በዚሁ አገልግሎት የተጠመዱ ሰዎቹ፥ ዛሬም እንኳ ስለ ተሐድሶ መናገራቸውን አላቋረጡም። https://www.facebook.com/share/p/1CAWMPz968/ በተሐድሶ አገልግሎት ውስጥ ካለን ሰዎች መካከልም "በተሐድሶ የምንኖር" እና "ለተሐድሶ የምንኖር" እንዳለን ግልጽ ነው። በተሐድሶ የምንኖር፥ ልክ በቫይረሱ መኖር በሚገኘው ርዳታ ይኖሩ እንደ ነበሩ ሰዎች፥ ስለ ተሐድሶ እየለፈፍንና ከእኛ በቀር ተሐድሶ የለም እያልን፥ አገልግሎቱን የገንዘብ ማግኛ ምንጭ አድርገን እንደ ቀጠልን፣ በሥራው ላይ ግን ብዙም እንደሌለን፥ ይህም ሳያንስ አገልግሎቱን ወዳልተነሣበት አግጣጫ ለመሳብ እየታተርን እንዳለ የአንዳንዶች አካኼድ ይናገራል። በዚህ መንገድ ከቆምነው ከእኛ የተነሣም፥ የተሐድሶ አገልግሎት እየተነቀፈ ይገኛል። ለተሐድሶ የምንኖርና ለኢኦተቤ መታደስ ብዙ ዋጋ ከፍለን እያገለገልን የምንገኝ ወገኖችም፥ አገልግሎታችንን ሰዎች ላያዩት፣ ላያውቁት ይችላሉ። እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሸክም ግን ብዙ እየተባልንና ብዙ ዋጋ እየከፈልን በማገልገል ላይ እንገኛለን። በተሐድሶ የምንኖር ደግሞ የተሐድሶ አገልጋይ መስለን በተሐድሶ እንነግዳለን። ለተሐድሶ ስኬት ሳይኾን፥ ለራሳችን የግል ጥቅምና ዝና ስንል፥ ጥቅም እስከ ተገኘበት ድረስ፥ ከማይመስሉን ጋራ በመወዳጀት ጭምር የእነርሱ አጀንዳ አስፈጻሚ እስከ መኾን መድረሳችን እየታየ ነው። በአገልግሎቱ ውስጥ ሳንኖር፥ ያለን አስመስለን ብዙዎችን እያደናገርን እንገኛለን። በዚህም እግዚአብሔር ያዝናል። ለተሐድሶ ሸክም ያላቸው ወገኖችም፥ ለተሐድሶ የምንሠራ መስለን፥ ኪሳቸውን በአገልግሎት ስም በማራቈታችን ተስፋ ይቈርጣሉ። በእኛ ሰበብ ለአገልግሎቱ ያላቸው ልብ ይወድቃል። እነርሱም ነገሩን ሲረዱት የተሐድሶን አገልግሎት በእኛ ልክ እየመዘኑ አገልግሎቱን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባሉ። ስለዚህ ራሳችንን እንመርምርና በተሐድሶ ከመኖር ለተሐድሶ ወደ መኖር እንምጣ። እኛ እግዚአብሔር እንደ ጠራን ለተሐድሶ ስናገለግል፥ እግዚአብሔር ደግሞ የእኛን ሕይወት፣ የእኛን ሥራ፣ የእኛን ኑሮ ይባርካል። አቢግያ ዳዊትን፦ "የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና" እንዳለችው (1ሳሙ. 25፥28)። እግዚአብሔርን መምሰልን ማትረፊያ ከምናደርግም፥ ኑሮዬ ይበቃኛል በሚለው መንፈሳዊ ስሌት ሕይወታችንን ብንመራ አንዳች አይጎድልብንም። "ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤" ይላልና (1ጢሞ. 6፥2) ለተሐድሶ እንጂ በተሐድሶ መኖር ያብቃ!
Открыть в Telegram"የተቀበረ መክሊት፦ ለመድሎተ ጽድቅ ከተሰጠ ምላሽ ጋራ"፥ "ዝተቐበረ መክሊት፦ ምስ ንመድሎተ ፅድቂ ዝተውሃበ ግብረ መልሲ" በሚል ርእስ፥ ወደ ትግርኛ ተመልሷል (እግዚአብሔር ሲፈቅድ ይታተማል)። መላሹ ወንድም ኀይሉ ጫቕሉ ሲኾን፥ "ሓጢኣተኛ ዘፅድቕ ፀጋ እግዚኣብሄር፦ ቅኑዕ ትምህርቲ ድሕነት" የተሠኘውንና "ኀጢአተኛውን የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ" በሚል ርእስ ወደ ዐማርኛ የመለሰውን መጽሐፍ፥ ጳጕሜን 1/2018 ዓ.ም. ለንባብ ያበቃል። ኹላችኹም በዕለቱ ተገኝታችኹ መጽሐፉን እንድትመርቁ ተጋብዛችኋል። አድራሻ፦ ሣር ቤት፣ አዳምስ ፓቪሊዮን (Adams Pavilion) — ዐዲስ ሕይወት አደራሽ ሰዓት፦ የኅብረቱ ፕሮግራም ሙሉ ቀን ሲኾን፥ የምረቃው መርሐ ግብር ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ይኾናል፤ መጽሐፉን በቀኑ ከጧቱ ጀምረው ማግኘት ይችላሉ። "በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ" ይሏል ይህ ነው።
Открыть в Telegramዛሬ ከጧቱ 4:06 ሰዓት ላይ አንዱ በስልክ ቍጥር +251722233639 ደውሎ "ጥቅል ፓኬጅ ስሞላ በስሕተት ወደ አንተ ተላከ፤ ስለዚህ መልስልኝ" ብሎ አለኝ። ዕሺ አልኹና ለማረጋገጥ ስገባ የገባ ፓኬጅ የለም። ከዚያ ከደወለበት ስልክ የጽሑፍ መልእክት ደረሰኝ። በቍጥሬ የገባ የጽሑፍ መልእክት እንጂ የገባ ጥቅል መልእክት የለም። ወጣቱ 4:13 ላይ መልሶ ደወለና "አልመለስኽልኝም እኮ" አለኝ። እኔም ስምኽ ማነው? አልኹት። ተሳደበና ስልኩን ዘጋው። ወዲያው ትሩኮለር ላይ ገብቼ የተመዘገበበትን ስም ስመለከት አጭበርባሪ ይላል። መልሼ ብደውል ስልኩ ተዘግቷል። ወይ አጭበርባሪ!😉
Открыть в Telegramhttps://www.facebook.com/reel/1024927656808740/ መጽሐፍ ቅዱስ፥ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።” ይላል (ምሳሌ 12፥10)። አራዊት ግን እንዲህ ዐይነት ዕውቀት ማስተዋል ስለ ሌላቸው፥ አንዱ አውሬ ሌላውን የዱር እንስሳ እየበላ መኖሩ ሕገ ተፈጥሮ ነው። ሰው ደግሞ በሰው ላይ ልዩ ልዩ የጭካኔ ተግባራትን ሲፈጽም ከጥንት እስከ ዘመናችን አይተናል። ልጆች እያለቀሱ ወላጆችን በልጆቻቸው ፊት የቀጠፉ ወይም ለልጆቻቸው ሳያስቡና ሳይራሩ ወላጆችን በልጆቻቸው ፊት ያጠፉ ሰዎች የጭካኔ ድርጊት፥ ለሚሰማውና ለሚያየው ሰው ሰቅጣጭ ነው። ከዚህ አንጻር ከታየ፥ ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲመላለስ አግኝቼ፥ ከታች የለጠፍኹት የቪዲዮ ትዕይንት፥ አውሬ ከሰው ተሽሎ የተገኘበት ነው ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር በዐውሎ ነፋስ ኾኖ ኢዮብን፥ “እንግዲህ እንደ ሰው ወገብኽን ታጠቅ እጠይቅኻለኹ፥ አንተም ተናገረኝ።” (ኢዮ. 38፥3) ብሎ ከዘረዘራቸው የፍጥረት ጕዳዮች አንዱ፥ አንስት አንበሳን ያጣቅሳል፤ “በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ ዐደን ታድናለኽን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለኽን?” (ኢዮ. 38፥39-40) የሚለው ይገኝበታል። አንበሳይቱ የያዘቻትን የዱር እንስሳ እናትና በርሷው ቍጥጥር ሥር ያለችውን ግልገሏን እንደ ለመደችው ተራ በተራ መዘነጣጠልና መብላት ትችላለች። ነገር ግን የከለከላት ምን ይኾን? ሮጣ ለማምለጥ ዐቅም የሌላት ግልገሊቱ፥ እናቷን ከአንበሳይቱ አፍ ለማስጣል ያደረገችው የመውጋት ሙከራ፣ የአንበሳይቱን ፊት አንዳች ያልጐዳው ቢኾንም፥ በድርጊቷ ግን ልቧ በጣም እንደ ተነካና ርኅራኄ እንደ ተሰማት እንመለከታለን። ምናልባት አንበሳይቱ እንስት ስለ ኾነችም አንዳች የእናትነት ስሜት ተሰምቷት ይኾናል። ስለዚህ ባልተጠበቀና የሚመለከታትን ሰው አጀብ በሚያሠኝ አኳኋን፣ ከአፏ የገባውን የእናቲቱን ዐንገት ለቅቃ ኹለቱንም ትታቸው ኼደች። እንዲህ ያለ የርኅራኄ ልብ ያጣ ሰው፥ ከዚህ የአውሬ ርኅራኄ አንዳች ትምህርት ያገኛል ብዬ ለጠፍኹት።
Открыть в Telegramhttps://www.facebook.com/share/p/1JR7jm7PQS/ ለኅትመት የተዘጋጀውን "ጥላ እና አካል" የተሠኘውን ፪ኛውን መጽሐፌን መሠረት በማድረግ፥ ከ"ድንቅ ፍጻሜ" የቴሌቪዥንና ዩቲዩብ ቻናል ጋራ የተደረገው ውይይት ፪ኛ ክፍል ዕንኾ። "ጥላ እና አካል" የተሠኘውንና ለማኅበረ በኵር የወንጌል አገልግሎት የሚውለውን ይህን ዕትም ለማሳተም ዐብራችኹን እንድትቆሙ በሥራው ባለቤት በልዑል እግዚአብሔር ስም እንጋብዛለን። Mahbere Bekur CBE 1000002276848
Открыть в Telegramhttps://youtu.be/h-v1CziFJ_U?si=pWSH_37leMKtLvbg ለኅትመት የተዘጋጀውን "ጥላ እና አካል" የተሠኘውን ፪ኛውን መጽሐፌን መሠረት በማድረግ፥ ከ"ድንቅ ፍጻሜ" የቴሌቪዥንና ዩቲዩብ ቻናል ጋራ የተደረገውን ውይይት የመጀመሪያ ክፍል ታደምጡ ዘንድ ዕንኾ።
Открыть в Telegram"በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ" (ሐ.ሥ. 3፥6) ላለማለት "በናዝሬቱ በእግዚአብሔር ስም ተነሣና ተመላለስ" ይላል ያለው "ሰባኪ" ማን ነበር?
Открыть в Telegram